Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

የ24 ሰዓት ተቃውሞ በአዲስ አበባ !

$
0
0

ደካማ የመንግስት አስተዳደር ለመለወጥ ምርጫ ያስፈልጋል፡፡ይሁን እንጂ ነጻነት በሌለበት ፍትሃዊ ምርጫ ማካሄድ አይቻልም፣ በምርጫ ሥም ጫፍ ላይ የደረሰው ሠላማዊ የነጻነት ትግል ጥያቄ መዳፈን የለበትም፡፡

ይድነቃቸው ከበደ

ይድነቃቸው ከበደ

ይድነቃቸው ከበደ

“ብልህነት የተሞላበት ታላቅ የትግል መርህ ማድረግና መስፋፋት፣ጥንቃቄ የተሞላበት ዕቅድ፣ጠንካራ ሥራና ሥነ-ሥርዓታዊ አበራታች ትግል ለድል የመብቃቱ ዕድል የሰፋ ነው፡፡” ይህ ፁሑፍ የተወሰደው ከአምባገነን አገዛዝ ወደ ዲሞክራሲ ከሚለው ከ ጄን ሻርፕ መፃሐፍ ነው፡፡ በዙህ አጋጣሚ ይህ መፃፍ እጅግ በጣም ጠቃሚ ነው፣በተለይ በአገር ውስጥ ለሚንቀሳቁ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ለሚያደርጉት አመፅ አልብ ትግል ብዙ አመላካች መረጃዎችን የሚሰጥ ነው፡፡
ዜጎች በሰላማዊ መንገድ የመሰብሰብና የመንግስትን የፖሊሲ ውሳኔዎች እና አሰራሮች የመቃወም መብታቸው የተጠበቀ ነው፣በሰላማዊ ሰልፍ፣በተቃውሞ የፊርማ ሰነድ ፣ለመንግስት ጥሪ ባለመተባበር፣በሥራ ማቆም አድማና በመሳሰሉት ዘዴዎች ተቃውሞ መግለፅ አለም አቀፍ ተቀባይነት ያለው የዲሞክራሲ መብት ነው፡፡
addis-ababa-realethiopia-141
በዓለም አቀፍ የተባበሩት መግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ጉባሄ ባፀደቀው መግለጫ ኢትዮጵያም በፈረመችው ስለ መሰብሰብ እና መደራጀት መብቶች የሚከተሉትን ብሏል ‹‹ የዜጎች የመሰብሰብ እና የመደራጀት መብቶች ተግባራዊ ሂደት ገደብ በማይጣልበት ሁኔታ መከበር ሲኖርበት ነገር ግን ገደብ ቢደረግ እንኳን ገደቡ የዓለም ዓቀፍ ህግና ሰብአዊ መብቶችን መሰረት ያደረገ እና የእነዚህን መብቶች ሁለንተናዊ ጥበቃ እዉን የሚያደርግ መሆን አለበት፤በተለይም ዜጎች የፖለቲካ እና የአይማኖት ለማስከበር የሚያደርጓቸው ተቃውሞዎች መደገፍ አለባቸው፡፡ ››የሚል ሲሆን ፡፡የኢፌዴሪ ህገ መንስት አንቀፅ 30 ንዑስ አንቀፅ 1 ማንኛውም ሰው ከሌሎች ጋር በመሆን መሣሪያ ሳይዞ በሰላም የመሰብሰብ ፣ሰላማዊ ሠልፍ የማድረግ ነፃነት እና አቤቱታ የማቅረብ መብት አለው፡፡ በማለት በህገመንግስቱ ተደንግጎ ይገኛል፡፡

ሆኖም ግን ይህ መብት ምን ያህል በአገራችን ተፈፃሚ ነው ብሎ መጠየቅ እና ምላሹን ማወቅ ብዙ እርቀት መሄድን የማይጠይቅ አይደለም፡፡ ከዚህ ቀደም በተለያየ ወቅት እና ቦታ በሰማያዊ እና በአንድነት ፓርቲ የተደረጉ አመፅ አልባ የአደባባይ የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች ምን ያህል ፈተኛ እንደነበሩ ለአብዛኞቻችን ግልፅ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ሂደቶ የገዥው መንግስት ፍላጎት ከማስጠበቅ አንፃር እንጂ በየትኛውም ሕግ ድጋፍ ሣይኖረው አብዛኛው የተቃውሞ እንቅስቃሴ ውጤት አልባ እንዲሆን ተደርጓል፡፡ይህ ማለት ግን የተደረጉ የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች ሁሉ ውጤት አልነበራቸውም ማለት አይደለም፡፡ መንግሰት የሕግ ድጋፍ ሣይኖረው በራሱ ፍላጎትና ፍራቻ ብቻ የህዝቡን ቅሬታዎች ሁሉ ጫና በመፍጠር አፍኖን እንገኛለን፡፡

እንዲህ አይነቱን ሕገ-ወጥ መንግስታዊ ሥራ፣ አልቀበለም ማለት የማንኛውም ኢትዮጵያዊ ግዴታም ነው፡፡ይህን ደግሞ የማሳውቅ እና የማንቃት ኃላፊነት ስለ-አገሬ ጉዳይ ያገባኛል የሚል ሁሉ የሚመለከተው ሲሆን ፣በተለይ ፓርቲዎች የቀን-በቀን ሥራቸው መሆን አለበት፡፡ይሄንን ኃላፊነታቸውን በአግባቡ የተረዱ፣ ጥቅምት 12 ቀን 2007 ዓ.ም ትብብር የመሰረቱት ዘጠኝ ፓርቲዎች “ ነፃነት ለፍትሃዊ ምርጫ” የሕዝባዊ ትግል ፕሮግራም የመጀመሪያ ዙር እንቅስቃሴ ይፋ አድርገዋል፡፡ በኢትዮጵያ የተቃወሞ እንቅስቃሴ በተቃዋሚ ፓርቲዎች ትብብር የተጠራ አመፅ አልባ የ24 ሰዓት የአዳር የአደባባይ የተቃውሞ ትይንት በታሪክ የመጀመሪያ ጊዜ ነው፡፡እንዲህ አይነቱ የሞራል የበላይነት እና ጥልቀት ያለው ሃሳብን የሚጠይቅ የተቃውሞ እንቅስቃሴ ጥሪ ላስተላለፉት ፓርቲዎች በሙሉ አድናቆትን በሙሉ ልብ የሚያሰጥ ነው፡፡ በዚህ አጋጣሚ ሌሎች እውነተኛ የተቃዋሚ የፓርቲዎች በትብብሩ ያልታቀፉ፣ በተለይም በሂደቱ ከጅምሩ እስከ መጨረሻው ተሳትፋው በተለያየ ምክንያት የስምምነቱን ሰነድ ያልፈረሙ፣ የተቃውሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ከጋራ ትግሉ ብትቀላቀሉ ውጤቱ የበለጠ ያማረ ይሆናል፡፡በመሆኑም ከሕግ አግባብ ውጪ በማን-አልብኝ እና ትምክተኝነት የተነጠቅነው “የአደባባይ ተቃውሞ” የምናስመልስበት ታሪካዊ አጋጣሚ ነው፡፡

ይዚህ ጽሑፍ አቅራቢ፣ ከዚህ ቀደም “ኢህአዴግ ለምርጫ አልተዘጋጅም” በሚል ርዕስ፡፡ “ኢሕአዴግ በጭራሽ እራሱን ነፃ ለሆነ የምርጫ ውድድር እያዘጋጀ አይደለም !የፖለቲካ ሊቃውንት እንደሚያስገነዝቡት እና ዓለም አቀፍ ነባሪዊ ሁኔታ የሚያመላክተው ለምርጫ መሰረታዊ ከሆኑት ውስጥ ፤በእኩል ደረጃ ባይወንም እንኳን በአንፃራዊነት የተወዳዳሪ ፓርቲዎች ነፃነት እና እኩል ተሣትፎ ሊኖር ይገባል፣ፓርቲዎችን ሊያወዳደሩ የሚችል ከማንኛውም ተጽእኖ ነፃ የሆነ ምርጫ ቦርድ እና ጉዳዩን ሙያዊ ስነምግባር መሠረት በማድረግ ለህዝብ መረጃ የሚያደርስ ነፃ ሚዲያ ያስፈልጋል፡፡እነዚህ መሰል ዋንኛ መስፈርቶች ባልተሟሉበት በአገራችን ወቅታዊ ሁኔታ፣ በመጪው ግንቦት ወር ነፃ ምርጫ ማካሄድ የሚታሰብ አይደለም፡፡” ሲል ግንዛቤውን አቅርቧል፡፡

ፍትሃዊ ምርጫ የማይታሰብ በመሆኑ፣ የተዘጋውን በር ለማስከፈት ይቻል ዘንድ በ9 ፓርቲዎች ትብበር ትግሉን የ ‹‹ ነጻነት ለፍትሃዊ ምርጫ›› በሚል የፕሮግራም መርህ የመጀመሪያውን ዙር እንቅስቃሴ በአዲስ አበባ ከተማ ለማድረግ የአንድ ወር ዕቅድ አዘጋጅቷል፡፡ በዕቅዳቸው መሠረት ዝግጅቱ የፕሮግራሙ የአፈጻጸም ስልት ፣የጊዜ ሰሌዳ፣ የቦታ ሽፋን፣የፋይናንስ ምንጭ፣ ዓላማዎች፣ትኩረት የሚደረግባቸው ጉዳዮችና መንግስታዊና የህዝብ ክፍሎች፣ዋና ዋና ተግባራት ፣በተጨማሪም በታሳቢነት በአፈጻጸም ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮች/ደንቃራዎችና ሥጋቶች እንዲሁም ለፕሮግራሙን ስኬት አጋዥ ሁኔታዎች እንዲካተቱ አድርገዋል፡፡ይህ ደግሞ ከላይ እንደተገለፀው የፓርቲዎቹ ጥንቃቄ የታከለበት ዕቅድ መንደፋቸው የሚያመላክት ነው ፡፡ዘጠኙ የትብብር ፓርቲዎች በህዳር ወር የሚያተኩሩባቸው የተቃወሞ ተግባራትን እንደሚከተለው ይፋ አድረገዋል፡-

1.በየቤተ እምነቱ ጸሎት ፕሮግራም እንዲደረግ ጥሪ ማድረግና አባላት እንደየእምነታቸው ተሳትፎ ማድረግ፤
2. በምርጫ ዙሪያ የፓናል ውይይቶችን ማድረግ፤
3. የአደባባይ ህዝባዊ ስብሰባዎችን ማድረግ፤
4. ለመንግሥታዊ ተቋማት ደብዳቤ ማስገባት፤
5. የተቃውሞ ድምጽ ማሰማት፤
6. የህዝብ ተሳትፎ ማበረታታትና ድጋፍ ማሰባሰብ፤ ናቸው፡፡

የነዚህ እንቅስቃሴዎች ማጠቃለያ ሕዳር 27 ተጀምሮ ሕዳር 28 የሚያበቃ የ24 ሰዓት የአዳር “የአደባባይ ተቃወሞ” ነው፡፡ በዚህ ፁሑፍ መግቢያ ላይ እንደተገለፀው “ብልህነት የተሞላበት ታላቅ የትግል መርህ ማድረግና መስፋፋት፣ጥንቃቄ የተሞላበት ዕቅድ፣ጠንካራ ሥራና ሥነ-ሥርዓታዊ አበራታች ትግል ለድል የመብቃቱ ዕድል የሰፋ ነው፡፡” እንደተባለው ሁሉ በዘጠኙ የተቃወሚ ፓርቲዎች የተጠራው የሕዳር ወር የተቃውሞ እንቅስቃሴ በስልት የተሞላ ስለሆነ ሂደቱ እና ውጤቱ ታሪካዊ እንደሚሆን ተስፋ የሚጣልበት ነው፡፡

ገዥው ፓርቲ እንዲህ አይነት ገፍቶ የመጣ ሕዝባዊ ጥያቂ ዕድል በመስጠት ፣ለሚጠየቁ ሕጋዊና ሰላማዊ ጥያቄዎች አዎንታዊ ምላሽ መስጠት ይጠበቅበታል፡፡ይህ ደግሞ መንግሰት ደግ ስለሆነ የሚያደርገው ሣይሆን ግዴታውም ጭምር ስለሆነ ነው፡፡ሆኖም ግን ከዚህ በተቃራኒ በጦር መሣሪያ ኃይልና በደህንነት አቅም በመመካት የሕዝብን ጥያቄ ለማፈን በተለመደው መልኩ መሄድ ከባድ ቀውሶች እንዲፈጠሩ መመኘት ነው፡፡ ይሁን እንጂ እንዲህ አይነቱ አሉታዊ ነገር መንግስት እንዲፈጠር ቢፈለግ እንኳን፣ ሕዝብ ከፓርቲዎቹ በሚሰጠው መመሪያ ሥነ-ሥርዓታዊና ደፋር እርምጃ ፣ብልህነት የተሞላበት አካሄድ በመከትል ፤አደባባይ ይዞ የወጣውን ጥያቄ ምላሽ አሰጥቶ፣ ሁሉም ነገር በሠላም እንደሚያበቃ የለውጥ ፈላጊ ኢትዮጵያዊያን በሙሉ ፍላጎት ነው፡፡

በዚህም መሠረት የጉዳዩ ባለቤት የሆኑት የተቃዋሚ ፓርቲዎች ‹‹የፖለቲካ ምህዳሩ ጠቧል›› ከሚለው አልፎ ‹‹ ተዘግቷል›› ወደሚል ድምዳሜ መሸጋገራቸውን በተጨባጭ ማስረጃ አረጋግጠዋል፡፡እዚህ ደረጃ ላይ መድረሳችሁንም በጋዜጣዊ መግለጫቸው ለሕዝብ አሳውቀዋል፤ሕዝቡ ደግሞ ወትሮም ቢሆን በአገራችን እየተካሄዱ ባሉ ምርጫዎች ሙሉ በሙሉ እምነት የለውም፡፡ይህ ደግሞ “ሰኔ እና ሰኞ” እንደሚባለው ነው፡፡

አሁን ላይ የእምነት ነጻነት ጠያቂዎች፣ጋዜጠኞች፣ጦማሪያን፣የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችና አባላት፣ ከገዢው ፓርቲ የተለየ ሃሳብ ያላቸው ዜጎች በአፋኝ ህጎች፣ በፈጠራ ወንጀል ተከሰው አንድም በወህኒ ወይም በስደት ይገኛሉ፡፡በአገራችን የተረጋጋ የፖለቲካ ሥርዓት የለም፣የኑሮ ውድነት የአብዛኛ ኢትዮጵያዊ ትከሻ ያጎበጠ ነው፣ዜጎች በአገራችን ኢትዮጵያ ከቦታ ቦታ ተዘዋውሮ የመንቀሳቀስ እና ንብረት የማፍራት እንዲሁም የመኖር መብት እየተነፈገ ነው፣ሥራ-አጥነት፣ስደት ፣በአገር ላይ ተስፋ መቁረጥ እና ሌሎች መሰል ችግሮች በመንግሰት አስተዳደር ድክመቶች አማካኝነት የተከሰቱ ናቸው፡፡ ስለዚህም እንዲ አይነቱ ደካማ የመንግስት አስተዳደር ለመለወጥ ምርጫ ያስፈልጋል፡፡ይሁን እንጂ ነጻነት በሌለበት ፍትሃዊ ምርጫ ማካሄድ አይቻልም፣ በምርጫ ሥም ጫፍ ላይ የደረሰው ሠላማዊ የነጻነት ትግል ጥያቄ መዳፈን የለበትም፡፡

በመጨረሻም ለዚህ ጽሑፍ ማጠቃለይ እንዲሆን ሙሉ በሙሉ ከዘጠኙ የፓርቲዎች ትብብር ከሰጡት ጋዜጣዊ መግላጭ ሃሳብ በመዋስ ነው፣የዚህም ፁሑፍ አቅራቢ ከዚህ የተለይ እምነት የለውምና፡፡

“ ገዢው ፓርቲ በጉዳይ ፈጻሚው የምርጫ ቦርድ በኩል በተለመደው መንገድ በምርጫ ሥም ለመሥራት የተያያዘውን ቧልት ራቁቱን በማስቀረት ለ ነጻ፣ፍትሃዊ፣ ተኣማኒና አሳታፊ ዲሞክራሲያዊ ምርጫ፣ የምርጫ ሜዳውን እንዲያስተካክል በሠላማዊ ትግል አዎንታዊ ተጽዕኖ ለማሳረፍ በእኛ በኩል አስፈላጊውን መስዋዕትነት ሁሉ ለመክፈልና እስከ መጨረሻው በጽናት መቆም ” በማለት ድምዳሜ ላይ ደርሰዋል ፡፡ይበል !!!
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር !


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>