Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

የመለስ ጎጂ ሃሳቦችና ድርጊቶች (የኢትዮጵያ ሲቪክ ንቅናቄ)

$
0
0

and ethiooia

Email: ethiocivic@gmail.com  

የመለስ ጎጂ ሃሳቦችና ድርጊቶች

ሕዳር 2006

የኢትዮጵያ አንድነትንና የመንግስት ስርዓቱን የሚመለከቱት የመለስ ሃሳቦችና ድርጊቶች ለኢትዮጵያ ህዝብ ከባድና አሳሳቢ ትርጉም አላቸው፡፡ የአንድነቱ ጥያቄ የኢትዮጵያ እንደ አገር የመኖርና ያለመኖር ጉዳይ ሲሆን፣ ስርአቱ ደግሞ በኢትዮጵያ ህዝብ መብቶች ላይ ማን መወሰን እንደሚችል ያመለክታል፡፡ የአገር ህልውና እና የህዝብ መብትን ያህል ትልቅ ጉዳይ ሊኖር ስለማይችል ክብደቱና አሳሳቢነቱ አያጠያይቅም፡፡

መለስ አንድነትን በሚመለከተው ሃሳቡ ትግራይን ከመገንጠል ኣላማ ጀምሮ ሳይተገብረው ቢቀርም፤ ኢትዮጵያን ወደብ አልባ አድርጓል፤ ህዝብን በቋንቋ ክልሎች ከፋፍሎ በጉራ ፈርዳና ቤኒሻንጉል-ጉሙዝ ለተከሰቱት አማሮችን የማፈናቀል ግፍ መሰረት ጥሏል፤ የመገንጠል “ህገ መንግስታዊ” አንቀፅ አዘጋጅቷል፤ ለሱዳን መሬት አድሏል፤ ዜጎችን አፈናቅሎ ለም መሬት ለውጭ ድርጅቶች በርካሽ ለረዥም ጊዜ አከራይቷል፡፡

የመንግስት ስርዓቱ በቃላት መድብለ ፓርቲ በተግባር ያንድ ፓርቲ አፋኝ ስርዓት ነው፡ስለዚህም ስርዓቱ በኢትዮጵያና በኢትዮጵያውያን ላይ ወሳኙ መለስ እንደነበረ ለ21 ዓመታት ደጋግሞ አረጋግጧል፡፡ ሰውየው በኢትዮጵያ በነበሩ መንግስታት በተለመደ መሳሪያ ማለትም የፈላጭ ቆራጭነት ስልጣንን በመጠቀም፣ በኢትዮጵያ ግን ያልተለመደና በውጭ ሃይሎችም ያልተሳካ፣ ኢትዮጵያን የማፍረስ ዓላማ ለመተግበር ሞክሯል፤ በከፊልም ተሳክቶለታል፡፡

አሁን ጥያቄው ከመለስ ህልፈተ-ህይወት በሁዋላ የኢትዮጵያ ህዝብን አፍኖ አንድነቱን የሚሸረሽረው ስርዓት ምን ይሁን? ነው፡፡ መልሱም የመለስ ስርዓት መፍረስ፣ አስተሳሰቡም መወገዝ አለበት እንደሆነ ለኢትዮጵያውን አሻሚ መሆን የለበትም፡፡

በዚህ መሰረት ካልታረሙ ለወደፊቱም ሊቀጥሉ የሚችሉ፣ ህወሓት የትጥቅ ትግል ከጀመረበት ጀምሮ እሰካሁን ያሉ በዋናነት ከመለስ የፈለቁ ጎጂ አስተሳሰቦችና አሰራሮች ባጭሩ መቃኘት ያስፈልጋል፡፡

ያልተፃፈ የጥንት ታሪክ አሁን ሲፃፍ ያልተረጋገጡ ወሬዎችና ግምቶች እንደ እውነተኛ ታሪክ የመፃፈቸው አደጋ ከፍተኛ ቢሆን የሚጠበቅ ነው፡፡ ታሪኩ ሲፈፀም የነበሩ ሰዎች በህይወት እያሉና የፅሁፍ ማስረጃዎች ሳይታጡ ያልተፈፀመ ታሪክ ብቻ ሳይሆን የእውነቱ ተፃራሪ የሆነ ታሪክ ሲፃፍና ሲነገር ግን በጣም ያሰገርማል፡፡ ጠንቁም ብዙ ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነት ውሸት የሚያሰራጩ ሰዎችን እንዴት ማመን ይቻላል? ለምንስ በዚህ መልክ ይቀጥላሉ? |ብለን መልስ-አዘል ጥያቄን በማቅረብ ጉዳዩን ላንባቢዎች ፍርድ መተው እንችል ነበር፡፡ ይሁን እንጂ በመለስ ትእዛዝ ውሸቱን የሚያሰራጩት ሰዎች ደግሞ በበኩላቸው በውሸቱ የሚያምኑ ሰዎችን መፍጠር ችለዋል፤ ምክንያቱም በጉልበት መገናኛ ብዙሃንን ለሁለት አሰርት ዓመታት በብችኝነት በመቆጣጠር የተወሰነ ህዝብ ጀሮን አይንና አእምሮን ተቆጣጥረው ህዝቡ መስማት፣ ማየትና መግለፅ ያለበትን ሲወስኑ ቆይተዋል፡፡ ስለዚህ ውሸቱ እውነት መስሎ ህዝብን ማወናበዱ እንዳይቀጥል የሚያመዛዝን አእምሮ ያላቸው ዜጎች እውነቱን ለማወቅና ለማሳወቅ ጥረት ማድረግ አለባቸው፡፡ ባንድ በኩል በውሸት ላይ በተመሰረተ ቅስቀሳ የተስፋፋውን ድንቁርና ማጋለጥና ማስወገድ፤ በሌላ በኩል ለዘለቄታዊ የህዝብ ደህንነት ጥፋት የሚያስከትሉትን ሃሳቦችና አሰራሮች እንደ አደገኛ ቆሻሻ ላንዴና ለሁሌ መቅበር ያስፈልጋል፡፡

መለስና ግብረ-አበሮቹ በ1968 ባወጡት የህወሓት (የዚያን ጊዜ ተሓህት) መግለጫ (ማኒፌስቶ) ትግራይን ከኢትዮጵያ የመገንጠል ዓላማ እንደነበራቸው በይፋ ስለገለፁ፣ መለስ ኢትዮጵያን የሚያፈርስ እንጂ ኢትዮጵያን የሚጠቅም ራእይ ይዞ ለትግል አልተሰለፈም፡፡ ሰውየው የፈለገው ራእይ ቢኖረው ኢትዮጵያን የሚመለከት በጎ ነገር ሊሆን አይችልም፡፡ ሃቁ ይህ ነው፤ በቃ፡፡

የመለስ ፍጡራን ማኒፌስቶው መታረሙን በመጥቀስ ቁም ነገር የተናገሩ ሊመስላቸው ይችላል፡፡ ቁምነገሩን ጭራሽ የሳቱት ቢሆኑም፣ ማኒፌስቶው እንደታረመ የሚገልፁት ሰዎች ቢያንስ የእርማቱን አስፈላጊነት ስለሚገነዘቡ ይህንን ግንዛቤ ከሌላቸው ሰዎች ይሻላሉ፡፡ ሆኖም፡

1ኛ ትግራይን ከኢትዮጵያ የመገንጠል ዓላማ ማንሳቱ ራሱ በኢትዮጵያዊነቱ በሚያምን ሰው ሊነሳ እንደማይችል ሊያስተባብሉ አይችሉም፡፡

2ኛ እርማቱ (በ1971 የህወሓት ጉባኤ) በመገንጠል ፈንታ የትግራይ ህዝብ የራሱን እድል በራሱ እንዲወስን መታገል እንደ ድርጅታዊ ዓላማ ማስቀመጥ ስለነበረ ከማጭበርበር የተለየ ትርጉም የለውም፡፡ ምክንያቱም በአንድነትና በመገንጠል አማራጮች አንድ ህዝብ ድምፁን በመስጠት መወሰን የሚያስፈልገው የአንድነትና የመገንጠል ሃይሎች ሲኖሩ ነው፡፡ ደርግ ፀረ ዴሞክራሲ ቢሆንም አቋሙ ላንድነት ነበር፤ የትግራይ ህዝብም የመገንጠል ጥያቄ አላነሳም፡፡ ስለዚህ የመገንጠል ፍላጎቱ የመለስና ግብረ-አበሮቹ አቋም ነበር፡፡ መለስና ግብረ-አበሮቹ በመገንጠል ፍላጎታቸው ያልቀጠሉበት አንዱ ምክንያት በተለይ ህዝብን አፍነው ከመቆጣጠራቸው በፊት ለዓላማቸው የህዝብ ሰፊ ድጋፍና ያንዳንድ ታጋዮች ትብብር እንደማያገኙ ስለተገነዘቡ ነው፡፡ በዛም ምክንያት በድርጅታቸው ውስጥ በ68 የፃፉትን ማኒፌስቶ ለድርጅቱ አባሎች ሳያሰራጩ ቀርተዋል፡ ሁለተኛው ምክንያት የህወሓት ሰራዊት በኢትዮጵያ ደረጃ ስልጣን ለመያዝ የሚያስችል ጥንካሬ ስላካበተና እነ መለስ ራሳቸው በጠፈጠፏቸው አሻንጉሊት ድርጅቶች መሳሪያነት ኢትዮጵያውያንን እየከፋፈሉና እጨፈጨፉ መግዛትና መዝረፍ ስለቻሉ ነው፡፡ ትግራይን የመገንጠል ቅሰቃሳ ከቆመ በሁዋላም የመለስ ነገድ-ተኮር ፖለቲካ በመገንጠል መብት ስም ህጋዊ ልባስ እንዲያገኝ በህገ መንግስት ተካትቷል፡፡

እውነቱ ከላይ እንደተገለፀው የማሻማ እያለ መለስ የተቆጣጠረው ህወሓት ከመጀመሪያ ጀምሮ ለኢትዮጵያ አንድነት እንደታገለ፣ ያ ቡድን ዓላማው ኢትዮጵያን ለመታደግ እንደነበረ አሁን የሚወራው የፈጠራ ታሪክ ከየት መጣ? በኢህአዴግ የረቀቀው ህገ መንግስት ኢትዮጵያን ከመገነጣጠል እንዳዳነ የሚሰራጨው ቅስቀሳ በታሪክ ውሸት፣ በአመክንዮ የተዛባ ነው፡፡ ሻዕብያ በራሱ አቅምና በመለስ ጥረት ኤርትራን መገንጠል ችሏል፤ በኢትዮጵያ የመገንጠል ጥያቄ ካነሱት በቂ ወታደራዊ አቅም ያልገነቡ ድርጅቶች ከማስገንጠል የተገቱት በኢህአዴግ ጉልበት እንጂ በህገ መንግስቱ አይደለም፡፡ ስለሆነም የመለስ ነገድ-ተኮር ፖለቲካ አንድነትን የሚያጠናክር ሳይሆን በአገራችን በመታየት ላይ እንዳለው ህዝብን የሚያጋጭና የሚያፈነቅል መርዝ በመሆኑ መወገድ አለበት፡፡

መለስ በህወሓት ውስጥ በ1968 ተጠባባቂ የማእከላዊ ኮሚቴ አባል ከሆነ ጀምሮ እሰከ 2004 ህልፈተ ህይወቱ ድረስ ለ36 ዓመታት በሰው ህይወት ላይ ለመወሰን የሚያስችለው ስልጣን ይዞ የዜጎች ህይወት እየቀጨ ቆይቷል፡፡ የመለስን አገዛዝ መገለጫዎች በሚከተሉት አርእስት ስር ማየትና የያንዳነዱ ባህርይ፣ አቋምና ድርጊት እውነታ በማስረጃ እያረጋገጥን እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ሰብአዊ ክብሩ እንዲጠበቅ የመለስ እኩይ ስርኣት ተወግዞ ካገራችን እንዲወገድ ከፍተኛ ጥረት እንደሚያስፈልግ እናሳስባለን፡፡

የህወሓት/ኢህአዴግ ማለትም የመለስ የስልጣን መሰረት ጉልበት ነው፡፡ ውሸትና ሙስና የተንሰራፉትም ከጀርባቸው ጉልበት ስላለ እንጂ በቀላሉ ተጋልጠው ሊወገዱ ይችሉ ነበር፡፡ ስለዚህ ህወሓት/ኢህአዴግ የመለስ ፈር መከተሉን ከቀጠለ በሰላማዊ ህዝብ ላይ ጉልበት ስለሚጠቀም ብዙ ዓይነት ወንጀሎች መፈፀም ይችላል፡፡ ሌሎች ፀረ ህዝብ ድርጊቶቹም ህዝብን በማሸማቀቅ ስለሚፈፅማቸው ጉልበት ሰውን እንደመጉጃና እንደማስፈራሪያ ለፖሊሲዎቹ ተፈፃሚነት የሚፈጥረው አመቺ ሁኔታ መገንዘብ ይቻላል፡፡

1.   ፈላጭ ቆራጭነት

በኢትዮጵያ ያንድ ግለ-ሰብ ፈላጭ-ቆራጭ አምባገነንነት አዲስ ክስተት አይደለም፡፡ ቢሆንም ከተካሄደው ረዥም ትግልና፣ ከተከፈለው እጅግ ከባድ መሰዋእት አንፃር ሲታይ ትውልዱን በበላ ትግል ፈላጭ-ቆራጭ ግለ-ሰብ መንገሱ ባንድ በኩል የሰውየው ኢሰብአዊነት አረገግጧል፡፡ የመለስ ፈላጭ ቆራጭነት በህወሓት ውስጥ ከማሌሊት ምስረታ ጋር የሚፈልጋቸውን ካድሬዎች መልምሎ፣ የማይፈልጋቸውን አባላት ካጠቃ በሁዋላ የጀመረ ነው፡፡ በሌላ በኩልም ታጥቆ ከታገለው ሃይል ጥቂቱ ባለው ሙስና ጎልቶ እንደሚታየው ለዝርፊያ የቆመ እንደሆነ፣ አብዛኛው የድርጅቱ አባል ደግሞ ታግሎ ዴሞክራሲያዊ ስርአት የመገንባት ብቃት እንደሌለውና የአምባገነን መሳሪያ ሆኖ የግለ-ሰብ አምባገነንነት በመመስረቱ፣ ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በመረገጣቸው፣ ፍትሕና የህግ የበላይነት ባለመኖራቸው ተረጋግጧል፡፡ ስለዚህ የመለስ ፈላጭ ቆራጭነትና የህወሓት/ኢህአዴግ አባላት አድርባይነትና መሰሪያነት ህዝብን የሚያሸማቅቅ ገዳይና አፋኝ ስርኣት ፈጥሯል፡፡

2.   ተከታታይ የጅምላና የተናጠል ግድያዎች

ቀደም ብሎ የደርግ ግፎች የታዛቢዎችን ቀልብ በሳቡበት የትጥቅ ትግል ጊዜ ግልፅነትና ተጠያቂነት ባልነበረበት ሁኔታ የህወሓት አመራር በድርጅቱ አባላት እና በሰላማዊ ህዝቡ ላይ በምስጢር ብዙ ግድያዎች ይፈፀሙ ነበር፡፡ ብዙ የትግራይ ህዝብና የህወሓት ተራ አባሎች በዝምድና፣ በጐረቤትነትና በጓደኝነት የሚያውቃቸው የህወሓት ሰለባዎች መኖራቸውን ቢያውቁም ባገዛዙ ስለታፈኑ፣ ከስርዓቱ ጋር በጥቅም ስለተሳሰሩ፣ ወይም የህወሓት ወታደራዊ ድል እንደ ጀብድ ስለሚያዩና ጀብዱን በመጋራት ዝና የሚያገኙ ስለሚመስላቸው በህወሓት ስለተፈፀሙት ወንጀሎች በይፋ አይናገሩም፡፡

በትጥቅ ትግሉ ጊዜ በተለይ በሲቪሎች በድብቅ የተፈፀሙት ግድያዎች ተደብቀው አይቀሩም፤ በግድያው ጊዜ ህፃናት የነበሩና ባገር ቤትና በስደት ያደጉም በቤተሰብ መረጃው ስለተላለፈላቸው ያውቁታል፡፡ ስለዚህ የድብቅ ግድያዎቹ፣ በአዲስ አበባ በተደጋጋሚ (1985፣ 1993፣ 1997፣ 1998) እና በሌሎች ከተሞች በይፋ እንደተፈፀሙት ጭፍጨፋዎች በታሪክ ይመዘገባሉ፡፡ ስለዚህም ግፍ ከፈፀመው ሃይል ጋር የወገኑት ዜጎች ቆም ብለው ማሰብ አለባቸው፡፡

3.   የፖለቲካ ሙስና እና ጎጠኝነት

ብዙ ጊዜ ስለ ሙስና ሲወራ ከጉቦና ስልጣንን ካለአግባብ ከመጠቀምና ሃብት ከማካበት ጋር ይያያዛል፡፡ ባለስልጣኖች የሚፈፅሟቸውን የሙስና ድርጊቶች ለመፈፀም የሚያስችላቸው መሰረት ግን ስልጣኑን ለመያዝ የሚፈፅሙት በጉልበት የታጀበ ቅጥፈት ነው፡፡ ህወሓት/ኢህአዴግ በውሸት ምርጫ ስልጣኑን በህዝብ ፍላጎት እንዳገኘ የሚገልፀው በጉልበት የሚፈልገውን ማድረግ ስለሚችል እንጂ ማጭበርበሩ፣ ህዝብን ማስገደዱና ድምፅን መዝረፉ ህዝብ ስለማይነቃበት አይደለም፡፡ በውሸት ምርጫ ከፍተኛውን የስልጣን እርከን የመያዝ አሰራር የስርዓቱ መገለጫ እስከሆነ ድረስ ለሙስና ድርጊቶች አመቺ ሆኖ ይቀጥላል፡፡ ከላይ ከፈተኛውን መንግስታዊ ስልጣን በጉልበትና ቅጥፈት የሚቆጣጠሩና ስልጣኑን ለዝርፊያና ለግል ምቾት የሚጠቀሙ ሰዎች አስካሉና ለዚህ ድርጊት በውስጣቸው መተማመን እንዲኖራቸው በነገድ፣ በጎጥና በዝምድና የተሳሰሩ ሰዎች እስከገዙ ድረስ፣ ከታች የገዢዎቹን አርአያ እየተከተለ ሙሰኛ የሚሆን መብዛቱ የሚገርም አይደለም፡፡

መለስ ሙስናን በቅንነት የሚቃወም ቢሆን ኖሮ በነበረው ፍፁም ስልጣን ሊገታው እየቻለ ከሱ በፊት ከነበሩት አገዛዞች ባጠረ ጊዜ ውስጥ ለከት የሌለው ሙስና አይስፋፋም ነበር፡፡ በተፃራሪው ግን መለስ ገና ከትጥቅ ትግሉ ጀምሮ ለተራበ ህዝብ የመጣውን እርዳታ ለምሳሌ ተጋይ የነበረውን ገብረመድህን አርአያን እህል የሚሸጥ ነጋዴ መስሎ ገንዘብ ከእርዳታ ሰጪዎች እንዲቀበል ያደርግ ነበር (Tigray, Ethiopia’s untold story, by Max Peberdy)፡፡ ትእምትን (ኢፈርት) ለመመስረት የተጠቀመበት ገንዘብ ከእርዳታ ተጭበርብሮ የተወሰደ ነው፡፡ የመለስ ሚስት የትእምት ከፍተኛ ስልጣን የያዘችው በቤተሰባዊ የሙስና አሰራር ነው፡፡ መለስ ያገዛዙ አካል ሆነው የተፈጠሩት ሙሰኞች ለስርዓቱ የቆሙ የሱ ደጋፊዎች እንደሆኑና እንደሚያስፈልጉት አያውቅም ማለት የዋህነት ነው፡፡

ሰውየው ግን ደርጊቶቹን በቃላቱ፣ ቃላቱን በድርጊቶቹ የማፍረስ አመል ነበረው፡፡ ዴሞክራሲን የማይፈልገው ወንጀሎቹ እንዳይጋለጡ ስለሚሰጋ መሆኑ እየታወቀ፣ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን እንዳይገነባ ሙስና እንዳደናቅፈው ለውጭ ዜጎች እንደሚከተለው ይገልፅ ነበር፡፡ ለምሳሌ አሌከስ ዴ ዋል (Alex de Waal) መለስ በተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶችና ሲቪክ ማህበራት ላይ በሚወስዳቸው እርምጃዎች ምክንያት ለሚያወግዙት ሰዎች መልሱ ምን እንደሆነ ጠይቆት መለስ ሲመልስ „የአባታዊነትና የሙስና የበላይነት ባለበት የፖለቲካ ኢኮኖሚ (በሚወስዳቸው እርምጃዎች ምክንያት እሱን) የሚያወግዙት ሰዎች ዴሞክራሲን እንዴት እንደሚገልፁትና ወደ ዴሞክራሲ የሚወስደው አዋጪ መንገድ እንዴት እንደሚፈልጉ ያውቃሉ ወይ?“ ብሎ በመጠየቅ ዴሞክራሲ እንደሌለ ከማመን አልፎ ጥያቄውን ማንሳቱን ስህተት ሊያስመስለው ይሞክራል፡፡ (Alex de Waal ፣ Dec. 06, 2012፣ ጉግል) የዜጎች መብቶችን ያፈነው ራሱ፣ ሙስና ያንሰራፋውም ራሱ መሆኑ ቢታወቅም መለስ ለኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንደገነባ ከመግለፅ ቦዝኖ አያቅም፡፡

4.   ህዝቡን በአንድ ሰው ሃሳብ እንዲመራ ማስገደድ

የተለያዩ ሃሳቦች ሲገለፁ እየተፋተጉ ስህተቶች ይታረማሉ፤ ከተለያዩ ሃሳቦች የተሻሉ ሃሳቦች ሊፈልቁ እና በተግባር እየተፈተኑ ሲጎለብቱ እውቀት በሂደት ያድጋል፡፡ መለስ የራሱ ሃሳብ ቢይዝና በፍላጎት ለሚቀበሉት ሃሳቡን ለማስፋፋት ቢሞክር ችግር አይሆንም ነበር፡፡ ችግሩ የፖሊቲካ ስልጣኑን፣ መገናኛ ብዙሃንን፣ የሚቆጣጠረው አስተዳደርንና ከተነገራቸው ውጪ የራሳቸውን ሃሳብ መግለፅ የማይፈቀድላቸው አሻንጉሊት ካድሬዎችን እየተጠቀመ የዜጎች ሃሳብ የሚቆጣጠርበት ስርዓት መመስረቱ ነበር፡፡

የመለስ ሃሳብ በጉልበት ከሚሰራጭ የሃይማኖት ስብከት የማይለይ፤ አማራጭ ስለሚከለክል ሚዛናዊ አስተሳሰብ ከነፃነት ጋር የሚያፍን፤ በማስረፅ (indoctrination) መልክ የሚሰራጭ፣ ካለ ደራሲው ፍላጎት አዲስ ግብአት ስለማይቀበል የማያድግና፤ የተለየ ሃሳብ የሚያቀርቡ ዜጎችን በጠላትነት በመፈረጅ በዜጎች መካከል የጠላትነት መንፈስ የሚፈጠር ቀኖና ነበር፡፡ ሰውየው ዜጎች በሱ ትእዛዝ እንዲተዳደሩ ብቻ ሳይሆን እሱ ራሱ ቢያምነበትም ባያምነበትም ላጭር ጊዜም ቢሆን ዜጎች በሱ ሃሳብ እንዲመሩ ያደርግ ነበር፡፡ በዚህ አሰራሩም ማመዛዘን የማይችሉ አምላኪዎችና አምላኪዎች በመምሰል የግል ጥቅማቸውን የሚያሳድዱ አድርባዮች ፈጥሯል፡፡ መለስ በትጥቅ ትግሉ ጊዜ የማሌሊትን እምነት ያልተቀበሉ እንደ ጠላት ያሳድዳቸውና የጋንግሪን ስም አውጥተላቸው በጋንግሪን እንደተለከፈ አካል እዲቆረጡ ይቀሰቅስና በተግባር የተለየ ሃሳብን ለማጥፋት የተለየ ሃሳብ ባላቸው አባላት ላይ ግፍ ይፈፅም ነበር፡፡

መለስ ማሌሊትን በህወሓት ውስጥ ፍፁም ስልጣን ለመጠቅለል ከተጠቀመባት በሁዋላ ስለ ነጭ ካፒታሊዝም ማውራት ጀመረ፡፡ ስለዚህ ሰውየው የተወሰነ ሃሳብ ሲያሰራጭ በመርህ ደረጃ አምኖበት ሳይሆን ሃሳቡን ለስልጣን መሳሪያ ለመጠቀም ነበር፡፡ እሱ ራሱ ሃሳቡን መቀየር ስለሚችል፣ ይዞት ቆይቶ የሚጥለው ሃሳብ ትክክል እንዳልነበረ ማመኑን ያመለክታል፡፡ መሳሳቱን የሚገነዘብ ሰው ደግሞ ሌሎች ሰዎችም ትክክል ሊሆኑም ሊሳሳቱም እንደሚችሉ መገንዘብ መቻል አለበት፡፡ መለስ ሁሉንም የሱ ተከታዮች ያልሆኑትን በራሳቸው ፖለቲካዊ ሃሳብ የሚመሩትን ዜጎች በራሱ ብቻ ሳይሆን በህዝብ ጠላትነት እየፈረጀ አልፏል፡፡ ስለዚህ ማመዛዘን የሚችሉና ቅንነት ያላቸው የኢህአዴግ አባሎች ካሉ የመለስን መንገድ መከተል የለባቸውም፡፡

5.   የሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መርገጥ

የኢህአዴግ ህገ መንግስት ብዙ ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ቢያካትትም የኢህአዴግ ባለስልጣኖች ህገ መንግስቱን ባያከብሩ አያስገርምም፡፡ ህገ መንግስቱ የተዘጋጀው በወንጀለኞች ማለትም በመለስና ግብረ-አበሮቹ ይሁንታ ስለሆነ በትጥቅ ትግሉ ጊዜ ወንጀል ሲፈፅሙ የቆዩ ሰዎች መንግስታዊ ስልጣን ከያዙም በሁዋላ በተራ ቁጥር 1 እንደጠቀስነው ወንጀል መፈፀማቸውን ቀጥለዋል፡፡ ግፈኛ ገዳዮች “እያንዳንዱ ዜጋ በህይወት የመኖር መብት” እንዳለው ቢገልፁ ምን ትርጉም አለው?

የኢህአዴግ አባሎችና ደጋፊዎች ህገ መንግስቱን በታጋዮች ደም እንደተፃፈ ተኩራርተው ሲገልፁ ታጋዮቹ ራሳቸው የራሳቸውን መብት አስከብረው እንደማያውቁ የተገንዘቡ አይመስሉም፤ ወይም እውነቱ እንዲገለፅ አይፈልጉም፡፡ በትግሉ ጊዜ ድርጅቱን መለስና ጥቂት ግብረ-አበሮቹ ታጋዮችን ሲያስገድሉ፣ አስረው ሲያሰቃዩና ሲያባርሩ እንኳንና ተቃውሞ ማቅረብ መጠየቅም በአመራሩ የተወሰዱ እርምጃዎችን ትክክለኛነት እንደ መጠራጠር፣ በአመራሩ እምነት ማጣትና ሌሎችም እምነት እንዲያጡ በማድረግ ድርጅቱን ለማፈረስ እንደመሞከር እየተተረጐመ ያስወነጅል ነበር፡፡ ሁሉም እንደ በቀቀን የተባለውን እንዲደግም ስለሚፈለግም ዝምታም ያስጠረጥር ነበር፡፡ የድርጅቱን ማለትም የኢህአዴግን በተለይም የህወሓትን ታሪክ የማያውቁ አንባቢዎች ታሪኩን ማጥናት ሳያስፈልገቸው ከኢህአዴግ መንግስት ባህሪ የዜጎች ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንደሚረግጡ ያውቃሉ፤ የተለየ ሃሳብ ያላቸውና መብታቸው እንዲከበር የሚጠይቁ ሰዎች እንዴት በቅጥፈት እየተወንጀሉ እንደሚጠቁ ማንም በቅን ህሊና የሚያስተውል ኢትዮጵያዊ ሊያረጋግጥ ይችላል፡፡

6.   በግድ ማደራጀትና ነፃ ድርጅቶች እንዳይኖሩ/እንዲዳከሙ ማድረግ 

የተማሩና በከተሞች የሚኖሩ ዜጎች ራሳቸውን ማደራጀት ይችላሉ፤ በገጠር የሚኖረው ህዝብ ግን የመደራጀት ልምድ ስለሚያንሰው፣ እንደፈለገው በዘመናዊ መጓጓዣ መጠቀም ይሁን በስልክ መገናኘት ስለማይችል፣ ከማሃይምነት ስላልተላቀቀና፣ የኑሮረው ሁኔታ ፋታ ስለማይሰጠው ራሱን የማደራጀት አቅሙ የተወሰነ ነው፡፡

የተማሩና በከተሞች የሚኖሩ ዜጎች የገጠሩን ህዝብ እንዲደራጅ ሊያግዙት ይችላሉ፡፡ ይሁን እንጂ ኢህአዴግ የመንግስት ስልጣን፣ ጉልበት፣ አስተዳደርና የመንግስት ንብረት እየተጠቀመ ስጋት በማስፈን ህዝቡን እንደመሳሪያ ለማሽከርከርና ትእዛዙን ለማስፈፀም በመለሳዊ ነገድ-ተኮር ስልትና እስከ ቤተሰብ ድረስ ለመቆጣጠር በሚያመች መልክ በራሱ ሹመኞች ስር ያደራጃል፡፡ ይህ ኣይነት ስልት አፋኝና አማራጭን የሚነፍግ የሁሉም ጠርናፊ (totalitarian) ስርዓቶች አደረጃጀት ነው፡፡ ከኢህአዴግ ነፃ ሆነው በሙያ፣ እንደ ሲቪክ ማህበራትና እንደ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለመደራጀት የሚሞክሩ ዜጎች በአገዛዙ ይዋከባሉ፤ እንቅስቃሴያቸው ይገታል፤ ፍርሃት በማስፈን አባላትና ደጋፊዎች እንዳይጠጓቸው፣ ለህይወታቸውና ነፃነታቸው ዋስትና እንዲያጡ ይደረጋሉ፤ ህይወታቸው የተቀጨም አሉ፡፡ በዚህ አሰራር አገዛዙ በቃላት ስለ መድብለ ፓርቲ እያወራ በተግባር የአንድ ፓርቲ ስርዓት አስፍኗል፡፡

7.   ህዝብን በቋንቋ መከፋፈል

የአገራችን ክፍለ ሀገሮች በቋንቋ ላይ የተመሰረቱ እንዲሆኑና የነገድ ድርጅቶች በብዛት እንዲመሰረቱ መደረጋቸው በተወሰኑ ምሁራን መካከል የነበረውን ነገዳዊ ቅራኔ ተቋማዊ በሆነ መልክ፣ ማለትም በቋንቋ ክልሎች፣ በነገድ ድርጅቶችና ባስተዳደራዊ መዋቅር ለሁሉም ህዝብ እንዲዳረስ ተድርጓል፡፡

የብሄር ብሄረሰቦች መብት መከበር የሚደገፍ መሠረታዊ የዴሞክራሲ ጥያቄ ቢሆንም፣ የመለስ ነገድ-ተኮር ፖለቲካ ግን በዋናነት የኢትዮጵያ ህዝብን ከፋፍሎ ለመግዛት የተጠቀመበት ስልት ነው፡፡ ስለሆነም የኢትዮጵያ ህዝብ አንድነት እየተሸረሸረ ይገኛል፡፡ የሱማሌ ክልል ፕረዚደንት ትግሬዎች አማሮች ወደ ስልጣን እንዲመለሱ እንደማይፈልጉ መናገሩ፣ አማሮች በአገራቸው ውስጥ ከጉራ ፈርዳና ከቤኒ ሻንወጉል-ገሙዝ በግፍ እንዲባረሩ መደረጉ፣ ባገሪቱ እስር ቤቶች የኦሮሞዎች ቁጥር መብዛቱ እና ባንዳንድ ወገኖች መለስና ተከታዮቹ ለፈፀሟቸው ወንጀሎች የትግራይ ህዝብ ተጠያቂና እንዲሁም በልማት ተጠቃሚ ተደርጎ መታየቱ መለስ በመሃንዲስነት የመሰረተው መርዘኛ ስርአት ውጤት ነው፡፡

8.   የተቋሞች ወገንተኝነት

መለስ ስልጣን ከመያዙ በፊት የነበሩ የተማሩና ልምድ ያካበቱ ኢትዮጵያውያን የሲቪልና የሰራዊት አባሎችን እንደ ባእድ አባርሮ ከነበቴሰባቸው ለስራ አጥነትና ለችግር እንዲጋለጡ አድርጓል፡፡ ቀጥሎ ሁሉም ታጣቂ ሃይሎች፣ ህግ አውጪው፣ ያስተዳደርና የፍርድ ቤት ተቋሞች፣ የሙያና የሃይማኖት ድርጅቶች ሳይቀሩ ያንድ ፖሊቲካ ድርጅት(መለስ በህይወት እስከነበረበት ጊዜም ያንድ ግለ-ሰብ) መሳሪያ እንዲሆኑ አድርጓል፡፡ እነዚህ ተቋሞች ለራሳቸው ተነፃፃሪ ነፃነት እንዲኖራቸውና ህዝብን በእኩልነት እንዲያገለግሉ ያንድ ፓርቲ ስርዓቱ ፈርሶ፤ በቃላት ብቻ ሳይሆን በተግባር የመድብለ ፓርቲ ስርዓት መገንባት አለበት፡፡

9.   መርዘኛ የጥላቻ ቅስቀሳ

በኢትዮጵያዊነቱ የሚያምን ማንም ዜጋ ኢትዮጵያውያንን እንደ ወገኑ ማየትና ለራሱ የሚፈልገው የዜግንት ክብር ለማንም ኢትዮጵያዊም እንደሚገባ መቀበል አለበት፡፡ ፖለቲካው ነገድ-ተኮር ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በዋናነት በቅንጅት ላይ ተመስርቶ የነበረው የዘር ማጥፋት ክስ የጥፋት ዒላማ ተደርጎ የተገለፀው የህዝብ ወገን (የትግራይ ህዝብ) አጥፊ ተደርጎ በተወነጀለው ወገን ላይ (በዋናነት በአማራው) የጥላቻ ስሜት ለመቀስቀስ ነው፡፡

ተከሳሹ ኢንተርሃምዌን መስሎ እንዲታይ ቅስቀሳ ተደርጓል፡፡ ኢንተርሃምዌ በሩዋንዳ በ1994 እ.አ.አ. እስከ 800 000 የሚደርሱ ሰላማዊ ሰዎችን (በዋናነት ቱትሲዎችንና እንዲሁም ለዘብተኛ ሁቱዎችን) የገደለ የመንግስት አካል የሆነ የሁቱ ሚሊሽያ ነበር፡፡ በቅንጅት አባላትና ሌሎች ዜጎች ላይ የተመሰረተው የፈጠራ የዘር ማጥፋት ክስ ውድቅ ቢሆንም የቅስቀሳ መልእክቱ ተላልፏል፤ በህዝብ አለመተማመን አሰራጭቷል፡፡ ኢንተርሃምዌ፣ ትምክህተኛ፣ ነፍጠኛ፣ ጥግተኛ፣ ቅንጅት ወዘተ ተመሳሳይ ትርጉም እንዲኖራቸውና በተወሰነ የህዝብ ክፍል ላይ የኢትዮጵያ አንድነትን በሚፈልጉ ዜጎች ላይ የጥላቻ መቀስቀሻና ማስፈራሪያ ተደርገዋል፡፡

10.  አስፀያፊ ባህል

አገዛዙ ህዝቡን እያሸበረ አሸማቅቆና አፍኖ ስለሚገዛ ተቃዋሚዎች፣ ጋዜጤኞችና የህዝብን መብቶች ለማስከበር የሚሞክሩ ህዝባዊ (ሲቪክ) ድርጅቶች ሊያድጉ አልቻሉም፡፡ በእንቅርት ላይ ጀሮ ደግፍ እንደሚባለው ግን መለስ አገዛዙን አሰፀያፊ የሆነ ዜጎችን የማዋረድና የማሰቃየት አመል አስለምዶታል፡፡

መለስ ሁሉንም ስለተቆጣጠረ ተቃዋሚዎቹም በቁጥጥሩ ስር እንዳሉና ምንም እንደማያሰጉት እያወቀ የሚፈፅማቸው ድርጊቶችና የሚረጫቸው ቃላት የቆሰለ ምርኮኛን ረግጦ እንደሚደበድብ፣ በላዩ ላይ እንደሚተፋና እንደሚቅራራ ሰው ነበር፡፡ ለምሳሌ በ2002ቱ የህወሓት 37ኛ ዓመት ሲያከብር ለውሸት ምርጫም ይቀሰቅስ ስለነበረ፤ በህዝብ ድምፅ ላይ እሱ ራሱ ወሳኝ መሆኑ እያወቀ አስነዋሪ ንግግር ከማድረግ አልተቆጠበም፡፡ የድሮ ጓደኞቹን በይፋ ገለባ፣ እንጉብላይ፣ ለህዝብ ጠላቶች ሽፋን የሆኑ እያለ ሰደባቸው፡፡ ህዝባችን ጨዋነትን እንደ ትልቅ እሴት ያያል፡፡ መለስ ግን ባህላችንን የሚበክልና ለነበረው የራሱ ስልጣንም ክብር የማይሰጥ አመሉ አስፀያፊ ነበር፡፡ መለስ የተለየ ሃሳብ የገለፁ ሰዎችን አመክንዮ ባለው አቀራረብ ስህተት የሚለውን ሃሳባቸው በመግለፅ ፈንታ የሰዎቹ ጭንቅላት እንደበሰበሰ ይሰድብ ነበር፡ ሰው በፅኑ ካልታመመ ጭንቅላቱ አይበሰብስም፤ ጭንቅላቱ እስኪበሰብስ ከታመመም ተቃዋሚ አይሆንም፡፡ ስለዚህ በመለስ የሚሰደቡት ጤኔኛ ሰዎች ናቸው፡፡

አገዛዙ ራሱ ሊያስከበረው የሚገባውን ህግ በመጣስ ሊያጠቃው የሚፈልገውን ሰው (ለምሳሌ ስየን) ካሰረ በሁዋላ ያሰረውን ሰው የሚጎዳ አዲስ ህግ በማውጣት፣ ህግ ወደ ሁዋላ ተመልሶ ተፈፃሚነት እንዲኖረው ማድረጉ አሰፀያፊና ፍርደ ገምደላዊ የበቀል ድርጊት ነው፡፡ በውሸት ተከሰው ታስረው የሚሰቃዩ ዜጎችን በሽምግልና ስም እርቅ ፈላጊ መስሎ በመታየት ህዝብን ለማወናበድ የሚደረግ ቅስቀሳ፣ ነፃነታቸው የተነፈጉ እስረኞች በስነ-ልቡና በማሰቃየት ራሳቸውን እንዲወነጅሉ (ቅንጅት ወዘተ.. ብርቱካን ሚደቅሳ ለሁለተኛ ጊዜ) ማድረግ መለስ ምን ያህል የሰውን ሰብአዊ ክብር የማንቋሸሽ አመል እንደነበረው ያመለክታሉ፡፡ መለስ በአንድ በኩል ለሰብአዊና ዴሞክራሲአዊ መብቶች በሚታገሉ ዜጎች ላይ የጭካኔና አስፀያፊ ድርጊቶች ሲፈፅም በሌላ በኩል ጤንነትን ለሚጎዱና የስነ ምግባር ብልሹነት ለሚያስከትሉ የጫትና አደንዥ እፆች ሱስ መስፋፋት ሊበራል ዴሞክራሲያዊ ሆኖ አልፎአል፡፡

የውሸት ምርጫ ማካሄዱ ራሱ ብዙ አሰፀያፊ ድርጊቶችን ያጠቃልላል፤ ህዝቡንና ተቃዋሚዎችን ያሸማቅቃል፣ የምርጫ ቦርዱን፣ ዳኞቹን፣ የመንግስት ሰራተኞቹንና ካድሬዎቹን ለቅጥፈት፣ ታጣቂዎቹን ለጉልበት ተግባሮች ያሰማራል፤ ማጭበርበር፣ ጉልበት መጠቀምና፣ መዋሸት ስልጣንን ለመያዝ፣ በስልጣን ተጠቅሞም የህዝብና የእርዳታ ሃብት መዝረፍ መጥፎ አርአያ የሆኑ የአገዛኡ መገለጫዎች ሆነዋል፡፡

ከላይ የተጠቀሱት ዘርፈ-ብዙ ጎጂ ድርጊቶችና ጠባዮች ስንገልፅ ባገዛዙ የተጀመሩ ጠቃሚ ድርጊቶች የሉም ለማለት አይደለም፡፡ በተለይ የመሰረተ ልማት ጥሩ ጀማሮዎች አሉ፡፡ ያሉትም በጥራት እንዲያድጉ ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡

ጥሩ ስራዎች እንዳሉ በመጥቀስ ጎጂዎቹን ለመደበቅ መሞከር ግን ጉዳቶቹ እንዲቀጥሉ ከማድረግ አይለይም፤ ስታሊን ከኢንዱስትሪ እድገት፣ ጋዳፊ ከውሃ አቅርቦት ጋር መንግስቱ ሃይለማርያምም ማሃይምነትን በማጥፋት ሙከራ በአዎንታዊ ሚናቸው ይጠቀሳሉ፤ በዚህ ምክንያት ግን አረሜኔያዊ ድርጊቶቻቸው እየተወገዙ እንዳይደገሙ የሚደረገው ጥረት አልተገታም፡፡ ስለዚህ ባገራችንም በዋናነት መለስ ያመጣቸው የአረሜኔው ስርአት መገለጫዎች እንዲወገዱ ጥረታችን መጧጧፍ አለበት፡፡

ከላይ እንደተገለፀው መለስ በአገርና በህዝብ ዘርፈ-ብዙ ወንጀሎች የፈፀመ፣ በወንጀሎቹ ህዝባዊ ፍርድ ሳያገኝ ያለፈ ሰው ነው፡፡ ቢሆንም እሱ ያሳደጋቸው ደጋፊዎቹና ተከታዮቹ የስልጣን እድሜቸውን ለማራዘም ታላቅ አገራዊ ራእይ የነበረው መሪ ነበር እያሉ በሚቆጣጠሩት የመገናኛ ብዙሃን ህዝብን ሲያደነቁሩ ከርመዋል፤ አሁንም ይቀጥላሉ፡፡

በተለይም መለስ „ዴሞክራሲያዊ ልማታዊ መንግስት“ እንደተመሰረተና ኢትዮጵያም በኢኪኖሚ በጣም እንዳደገች ያልተቆጠበ የውሸት ፕሮፓጋንዳ በመንዛት ላይ ይገኛሉ፡፡ ለዚህ የውሸት ፕሮፓጋንዳ መሠረት ደግሞ በመለስ አገዛዝ ተሰሩ የተባሉትን ወይም እሱ ያቀዳቸው ናቸው የተባሉትን የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶችን በመጥቀስ ነው፡፡ ሃቁ ግን ከዚህ ነጭ ውሸት የተለየ ነው፡፡

በመሠረቱ ማንኛውም ስርዓት ወይም መንግስት፣ ዴሞክራሲያዊ የሆነም ያልሆነም፣ የተወሰኑ የመሠረተ ልማት ስራዎች መስራቱ የሚጠበቅ ነው፡፡ እጅና እግሩን አጣጥፎ የሚቀመጥ ስርኣት የለም፡፡ በተለይም ዴሞክራሲያዊ ተቀባይነት (legitimacy) የሌላቸው ስርአቶች በልማት ለውጥ አምጥተናል እያሉ አገዛዛቸውን ለማራዘም እንደሚጠቀሙ በታሪክ የታየ አሁንም በተለያዩ አገሮች የሚታይ ክስተት ነው፡፡ መለስ ባጭበረበራቸው ምርጫዎችና በፈፀማቸው የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ዴሞክራሲያዊ እንዳልነበረ እንኳን የኢትዮጵያ ህዝበ ይቅርና የሚደግፉት የውጭ መንግስታትና እንዲሁም አለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች የሚመሰክሩት ሃቅ ነው፡፡ ስለሆነም መለስ „ልማታዊ መንግስት“ የአገዛዙን እድሜ ለማራዘምና እሱና ተከታዮቹ የህዝብ ሃብትን ለመዝረፍ የተጠቀሙበት ስልት ነው፡፡

በመለስ አገዛዝ የተሰሩ የመሰረተ ልማት አውታሮች በአብዛኛው አገሪቱ ከውጭ ባገኘችው በብዙ ሚልዮን ዶላር የሚቆጠር ብድርና እርዳታ ነው፡፡ ህወሓት/ኢህአዴግ በሚፈፅመው ሙስናና ዘረፋ አይጠየቅምና በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በአብዛኛው የመሰረተ ልማት ግንባታዎች ህወሓት/ኢህአዴግ ተጠቃሚ መሆኑ የሚካድ አይደለም፡፡ ለአብነት የአባይ ወንዝ ግድብ ስሚንቶና ብረታ ብረት የሚያቀርበው የህወሓት ትእምት (EFFORT) መሆኑ የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡

ባጠቃላይ በመለስ አምባገነናዊ አገዛዝ በዘረፋ የበለፀጉት የሱ ተከታዮችና ደጋፊዎች ሲሆኑ፣ አብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ ግን ተጠቃሚ አይደለም፡፡ የኢኮኖሚ እድገት ቢኖር አብዛኛው የከተማ ህዝብ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከፋ በሚሄደው የኑሮ ውድነት አይሰቃይም ነበር፡፡ አርሶ አደሩም የማዳበሪያ ዕዳ መክፈል አቅቶት ሳይቸገር የምርቱ ተጠቃሚ በሆነ ነበር፡፡ በብዙ ሺ የሚቆጠር የአገሪቱ የተማረ ሃይልና ወጣት ለስደት ተጋልጦ በሳወዲ አረብያ የግፍና ውርዴት ሰለባ አይሆንም ነበር፡፡

በመጨረሻምው ኢትዮጵያውያን መለስ የፈፀማቸው ወንጀሎች አደገኛነት በመገንዘብ፣ በተለይም የቀበራቸው የአገር አንድነትን የሚሸረሽሩ ፈንጂዎችን ለማፅዳትና የአገራችን አንድነትን ለማጠናከር ከመቸውም ጊዜ በበለጠ በአንድነት መታገል ታሪካዊ ግዴታችን ነው፡፡

 


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles