Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

ስምንት ጠቃሚ ነጥቦች ከእስራኤላውያን -ክፍል 5 (ዮፍታሔ)

$
0
0

ከዚህ ቀደም በነበሩት 4 ክፍሎች የእስራኤልን ታሪክ በአጭር በመቃኘት ስለአንድ ማዕከላዊ ድርጅትና ስለተቋማት አስፈላጊነት፣ ትግሉን ዓለምአቀፋዊ ስለማድረግ፣ ስለዳያስፖራው ወሳኝ ሚናና የጋራ ቋንቋ ለአንድ አገር ያለውን ጥቅም በሚመለከት ተገልጿል። ክፍል 5 በአገር ጉዳይ የሀይማኖት መሪዎችና አገልጋዮች ሊኖራቸው ስለሚገባው የመሪነትና የማስተባበር ሚና ከእስራኤል ታሪክ በማጣቀስ ያብራራል።

 

  1. የሀይማኖት መሪዎችና አገልጋዮች ሚና

 

Jewish+Ethiopians+Reunited+Families+Israel+o1h5oGhsf2Vlበኢየሩሳሌም የነበረው ቤተመቅደስ በሮማውያን ፈርሶ እስራኤል በየአገሩ ከተበተኑ በኋላ ብዙ የአይሁድ ካህናት አልነበሩም። ምክንያቱም ቤተመቅደስ በሌለበት ካህን ሊኖር ስለማይችል ነው። ሆኖም ይህ ባይቻልም ብዙዎች መምህራን (ረበናት) ሆኑ። በአይሁድ ታሪክ ውስጥ እነዚህ የአይሁድ መምህራን የነበራቸው አስተዋጽኦ ሁሌም ገንቢ ባይሆንም እጅግ ከፍተኛ ነበር። በየሄዱበት ፈጽሞ እምነቱ እንዳይጠፋና አይሁድም የሚሰባሰቡበትና እየተገናኙ በዓላትን የሚያከብሩበት የአምልኮ ስፍራዎች (Synagogues) ከማቋቋም ጀምሮ በማንኛውም አገርን የሚመለከት ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳይ ሁልጊዜም ከፊት የሚገኙት እነዚህ መምህራን ነበሩ።

 

ያቋቋሟቸው ቤተመቅደሶች እምነቱ ባህሉና የእብራይስጥ ቋንቋ (በንግግርም ባይሆን በጽሑፍ) ፈጽሞ እንዳይጠፋ ዋና ምክንያት ነበሩ። አይሁዳውያን በተጠቁ ጊዜ መጠለያ፣ በትግሉ ጊዜ መሰባሰቢያ ወዘተ ሆነው አገልግለዋል።

 

እነዚህ የሀይማኖት መምህራን በዚህ ብቻ አልተወሰኑም። ጠንካራ ማኅበራትን በማቋቋም በትግሉ ውስጥ የመሪነትና የአስተባባሪነት ሚና ተጫውተዋል። በአንደኛው የዓለም ጦርነት (እ. ኤ. አ በ 1914) በኦቶማን ቱርኮች ጭቆና ሥር የሚማቅቁትን አይሁድ ለመታደግ ሲባል በአስቸኳይ በተፈለገ 50,000 ዶላር መነሻ ከአሜሪካ ግዛቶች ብቻ የተሰባሰቡት አይሁድ በተወሰነ ጊዜ ውስጥ ከ 78 ሚሊዮን ዶላር በላይ ለማዋጣት የቻሉት በእንደዚህ ዓይነት ማኅበራት (ኦርቶዶክስ አይሁድ በአብዛኛው የሚገኙበት American Jewish Distribution Committee ዋናው ነው) የተሰባሰቡ ነበሩ። ይህ ማኅበር ለተፈናቀሉ ርዳታና የመልሶ ማቋቋም አገልግሎት ከማበርከቱም በላይ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከመቀስቀሱ በፊት በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ አይሁድ ጀርመንን ለቀው እንዲወጡ በማድረግ ሕይወታቸውን ታድጓል። በ 1943 (እ. ኤ. አ) ከአራት መቶ በላይ ከተለያዩ የአሜሪካ ግዛቶች የተሰባሰቡ የአይሁድ መምህራን በአውሮፓ በአይሁዳውያን ላይ የሚደርሰውን ግፍ በመቃወምና የተባበሩት መንግሥታቱ ኃይል ግፉን ለማስቆም የወሰደውን ርምጃ በመደገፍ በአሜሪካን አገር ያደረጉት ሰልፍ በጊዜው የዓለምን የመገናኛ ብዙሐን ቀልብ በመሳብ  የአይሁድ ሕይወት በስደት ምን እንደሚመስል ለዓለም ሕዝብ ያስገነዘበና በእስራኤል የትግል ታሪክ ሁልጊዜም ሲጠቀስ የሚኖር ነው።

 

በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የቤተክርስቲያንና የመስጊድ አገልጋዮች ከአይሁድ ጋር የሚመሳሰሉት በየሄዱበት ከሕዝቡ ጋር በመተባበር አብያተክርስቲያንንና መስጊዶችን በማቋቋም ያበረከቱትና አሁንም እያበረከቱት ያለው አስተዋጽኦ ነው። እነዚህ የሀይማኖት ተቋማት ለሕዝቡ መንፈሳዊ አገልግሎት ከማበርከት በተጨማሪ እንደመሰባሰቢያ በመሆንም ያገለግላሉ።

 

ኢትዮጵያውያን የሀይማኖት መሪዎች በሕዝቡ ዘንድ ከማንም ይልቅ ተቀባይነትና ተሰሚነት ቢኖራቸውም ይህን ተቀባይነትና ተሰሚነት እስካሁን ለአገር ጉዳይ በአብዛኛው ሲጠቀሙበት አልታየም ቢባል እውነት ነው። ይህ ደግሞ የአገርን ጉዳይ ብቻ የሚመለከት ሳይሆን መንፈሳዊ (የተጎዱትን የማጽናናት፣ የተጨነቁትንና የተሸበሩትን የማረጋጋት፣ ርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ፈጥነው ርዳታ እንዲያገኙ የማስተባበር ወዘተ) እና ማኅበራዊ አገልግሎቶችን በሚመለከት ነው። ቋንቋን፣ ባህልንና ታሪክን ጠብቆ ለሚቀጥለው ትውልድ የማስተላለፍ ሥራ የነዚህ የሀይማኖት ተቋማት፣ አገልጋዮችና መምህራን ሥራ ሆኖ ለዘመናት የዘለቀ ቢሆንም በአሁኑ ጊዜ መድረክ ላይ ቆሞ ከማስተማር ባለፈ በተጠናና በተዘጋጀ መንገድ ለቀጣዩ ትውልድ (ለልጆች) በበዓላት መዝሙር ሲዘምሩ ከማሳየት ባለፈ ይህን መሰል እውነተኛ አገልግሎት ሲሰጥ አይታይም። በቋንቋና በሀይማኖት ትምህርት በኩል አንዳንድ ሙከራዎች ቢኖሩም ከወላጆችና ከሰንበት ትምህርት ቤቱ የሚያልፍ አይደለም። ይህም በሚገባ በተደራጀና ተከታታይነት ባለው ሁኔታ የሚፈጸም ባለመሆኑ ውጤት አይታይበትም።

 

በውጭ የሚገኙት አባቶች፣ ካህናት፣ የሀይማኖት መሪዎችና አገልጋዮች በውጭ ያላቸውን ነፃነት ተጠቅመው በመንፈሳዊውም ሆነ ከመንፈሳዊው እጅግ የተሳሰረ በሆነው የሕዝቡ ማኅበራዊና የአገር ደኅንነት ጉዳይ በመሪነትና በማስተባበር ብዙ ሊያደርጉ ሲገባ መክሊታቸውን አልተጠቀሙበትም። በየአረብ አገራት (በቅርቡ በሳውዲ አረቢያ የተፈጸመውን ጨምሮ) በኢትዮጵያውያን ላይ ለሚደርሰው የማያቋርጥ ችግር ተባብረው የውግዘትና የተቃውሞ ድምጻቸውን ለሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ከማሰማትና ለጥቃቱ ሰለባዎች የመንፈሳዊ ማረጋጋትና ማጽናናት አገልግሎት ከመስጠት ጀምሮ ምእመናንንና ዳያስፖራውን በመሪነት በማስተባበር “ሠርገኛ መጣ በርበሬ ቀንጥሱ” ዓይነት ሳይሆን የደረጁ ቋሚ ማኅበራትን በመፍጠር ችግሩ ለደረሰባቸው ወገኖች አስቸኳይ ርዳታ እንዲደርስ ማድረግና ችግሩን ከምንጩ ጀምሮ በማየት የረጅም ጊዜ ዘላቂ መፍትሔ መስጠት ከማንም በፊት የሀይማኖት አባቶችና አገልጋዮች ሥራ ነው። ይህን አላደረጉም። ልጆች በማደጎ ሰበብ ካገር እየወጡ ብዙ ችግር ሲደርስባቸውና አሁንም የልጆች ሽያጭ ሲቀጥል ይህን ለማስቆምና ሌላ አማራጭ መፍትሔ ለማግኘት አንዳችም ነገር አላደረጉም። ከሕዝቡ ፊት መገኘት ሲኖርባቸው የነርሱ ኃላፊነትና ሥራ በሆነው ሁሉ ሕዝቡና የፖለቲካ ድርጅቶች እየቀደሟቸው እነርሱ ከኋላ ሲጎተቱ ታይተዋል።  አንዳንዴም ሀይማኖታዊ ግዴታቸውን ረስተው በጥቅምና በዘር እየተደለሉ ከሚያልፈው ጋር እየተሰለፉ ሊያገለግሉት የሚገባውን እግዚአብሔርንና የእግዚአብሔርን ሕዝብ ከአምባገነኖች ጋር ተባብረው ሲጎዱት ታይተዋል። በዚህም ሕዝቡ ተስፋ ከእነርሱ መጠበቁን ትቶ ከሌሎች መጠበቅ ከጀመረ ቆይቷል። ሕዝቡንና አገርን የመታደግ፣ የመጠበቅና የሕዝቡን ኑሮ በመንፈሳዊም በቁሳዊም የማበልጸግ ኃላፊነት ብቻ ሳይሆን ግዴታም አለባቸው። ምክንያቱም ቁሳዊው መንፋሳዊውንም ስለሚጎዳው ነው።

 

ኢትዮጵያዊና ትውልደ ኢትዮጵያዊ የሆኑ ልጆች ማንነታቸውን፣ ባሕላቸውን፣ እምነታቸውን፣ ታሪካቸውንና ቋንቋቸውን እንዲያውቁ ማድረግ የትግሉ አንድ አካል ነው። ግእዝ አዋቂ የሆነው የኢትዮጵያዊው መሪጌታ፣ ካህንና ዲያቆን ልጅ አማርኛ የማያውቅ ከሆነ ችግር አለ ማለት ነው። በአገራችን ላይ እየተፈጸመ ያለው ጥቃት ታሪክን፣ ባሕልን፣ እምነትንና የጋራ ቋንቋ እንዳይኖር በማድረግ አገሪቷን የመበተን ዘርፈ ብዙ ስለሆነ ትግሉም እንደዚሁ ሥርዓቱን ከመቀየር ጎን ለጎን ብዙ ዘርፍ እንዲኖረው ያስፈልጋል። ዘረኛው ሥርዓት ኢትዮጵያን አጠፋለሁ ስላለ አትጠፋም። ኢትዮጵያን ኢትዮጵያ የሚያደርጓት በዋናነት እነዚህ እሴቶቿ ናቸው። እነዚህ ካልጠፉ አትጠፋም። ነገር ግን እኛም ተባባሪ ሆነን እነዚህን እሴቶች በማቃለል ይልቁንም ለሚቀጥለው ትውልድ ማስተላለፍ ካልቻልን ያን ጊዜ በርግጥ የኢትዮጵያ ሕልውና አደጋ ላይ ይወድቃል። ይህ እንዳይሆን የወላጆች ድርሻ ትልቅ ቢሆንም የሀይማኖት መሪዎች እነርሱ አርአያ በመሆን ወላጆችን በማነሳሳትና በመርዳት ባሕሉ፣ ታሪኩ፣ እምነቱና ቋንቋው ተጠብቆ ወደልጆች እንዲተላለፍ ከፍ ያለ አስተዋጽኦ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

 

እነዚህ አቢያተክርስቲያናት ያላቸውን ተቋማዊ አቅምና የያዟቸውን በተግባር በጉልበታቸው፣ በጊዜአቸውና በገንዘባቸው ላመኑበት ነገር (ሀይማኖት) ወደኋላ የማይሉ ምእመናን ችላ እያለ በዳያስፖራው ትብብር ጠንካራ ተቋማትንና ድርጅቶችን እመሠርታለሁ ብሎ የሚያስብ ማንኛውም አካል የተሳሳተ ነው። ሕወኀት አብያተክርስቲያንን እያበጣበጠ በሥሩ አድርጎ ለመቆጣጠር ሙሉ ኃይሉን የሚጠቀመው ለምንድን እንደሆነ በሚገባ ልንረዳ ይገባል። በጠቅላላ አብያተክርስቲያንን ከዚህ ተጽእኖና ቁጥጥር ነፃ ማድረግና በምትኩ ለአገራቸው አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ መንገዱን ሁሉ ማመቻቸት የትግሉ አንድ ዘርፍ እንደሆነ መረዳት ያስፈልጋል።

 

(ይቀጥላል)

 

ኢትዮጵያ በቆራጥ ልጆቿ ሥራ ታፍራና ተከብራ ለዘለዓለም ትኖራለች!

 


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles