Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

ብርሀነ መስቀል ረዳን በጨረፍታ

$
0
0

ጸሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ
—-
በዩኒቨርሲቲ ቆይታዬ (ከ1989-እስከ 1992 በነበረው ጊዜ) “ሐቄ” የምትባል ልጅ አውቃለሁ፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት የሴቶች ጉዳይ ሃላፊ የነበረችው (በኋላ በኮትዲቯር የኢትዮጵያ አምባሳደር የሆነችው) ወ/ሮ ታደለች ሀይለሚካኤል የዚያች ልጅ እናት እንደነበረች ይወሳ ነበር፡፡ በዚህም የተነሳ የባለስልጣን ልጅ መሆኗን በመፍራት ብቻ ብዙዎች አይጠጓትም ነበር፡፡ ከልጅቷ ጋር የሚቀራረበው ተወልደ መዝገቡ የሚባል የአዲግራት ልጅ ብቻ እንደነበረ አስታውሳለሁ፡፡

BerhaneMeskael Reda የዩኒቨርሲቲው ትምህርት ከተጠናቀቀ ከጥቂት ወራት በኋላ መጽሔቶችን ሳገላብጥ ያቺ ልጅ ለምልክት ከሞት የተረፈች የፈጣሪ ተአምር እንደሆነች ተረዳሁ፡፡ አባቷ ነፍሲያውን ሊጠነቅ በተቃረበበት ወቅት ታሪኩን ትመሰክር ዘንድ የዘራት ብቸኛ ፍሬው ነበረች፡፡ ብዙዎች በእናቷ ሆድ የነበረችበትን ጊዜ በብዕራቸው ነካክተውታል፡፡ ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማሪያም በበኩላቸው ያቺ ነፍስ በእናቷ ሆድ ውስጥ በመገኘቷ እናቷን ከሞት ያተረፈች መሆኗን መስክረውላታል፡፡ ለዚህም ይመስላል እናቷ “ሐቄ” የሚለውን ስም የሰጠቻት፡፡

ህይወት ተፈራ Tower in the sky የተባለውን መጽሐፍ ስትጽፍ ለዚያች ልጅ መጠነኛ ሽፋን ሰጥታለች፡፡ ከእናቷ ጋር የተነሳችውንም ፎቶግራፍ በመጽሐፉ ውስጥ አካተዋለች፡፡
*****
በፎቶግራፉ ላይ የምትመለከቱት የዚያች ልጅ አባት የነበረውን ሰው ነው፡፡ ይህ ሰው ከታሪካዊው የኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ መሪዎች መካከል አንዱ የነበረውና የመጀመሪያው የኢህአፓ ዋና ጸሓፊ ሆኖ የተመረጠው ብርሀነ መስቀል ረዳ ነው፡፡ ለብዙሃን ህይወት መለወጥ በብርቱ የታገለ፣ ሁለቱን ጠንካራ ስርዓቶች ፊት ለፊት የተጋፈጠ፣ ላመነበት ዓላማ ትምህርቱን ሰውቶ መታገልን የመረጠ፣ ከሀገር ወጥቶ በሰው ሀገርና በበረሃ የተንከራተተ፣ በመጨረሻ ላይ ግን ከገዛ ጓዶቹ ጋር ተጣልቶ የራሱን መንገድ የመረጠ፣ በዚህም ከፍተኛ የውዝግብ ርዕስ ለመሆን የበቃ የዚያ ዘመን ፋኖ!…

ብርሀነ መስቀል ማን ነው?… በኢትዮጵያ ህዝቦች የፖለቲካ ትግል ውስጥ ምን ሚና ነበረው?… የርሱ ህይወትና የትግል መንገድ እንዴት ይገመገማል?… እነኝህ በኔ አቅም የሚመለሱ ጥያቄዎች አይደሉም፡፡ ታሪኩ እስከ አሁን ድረስ እያወዛገበ ስለሆነ ሐቁን ከግርድፉ ማጣራቱ ከባድ ጥረት ይጠይቃል፡፡ ብርሀነ መስቀል በወዳጆቹም ሆነ በጠላቶቹ የሚከበርና የሚፈራ መሆኑን ግን ማንም አያስተባብልም፡፡ ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማሪያም በእስር ቤት አናዝዘውት ከገደሉት በኋላ “የመርሐቤቴ ገበሬዎች ገደሉት” እያሉ ለመዋሸት ቢሞክሩም በኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ ውስጥ የነበረውን ሚና በአዎንታዊ መልኩ ነው የገለጹት፡፡ በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው የቅርብ ጓደኛው የነበሩት አንጋፋው ገጣሚና ባለቅኔ ኃይሉ ገብረ-ዮሐንስ (ገሞራው) “ችኩል እና ቁጡ ከመሆኑ በስተቀር ለሀገር መሪነት የሚበቃ ስብዕና ነበረው” በማለት መስክረውለታል፡፡

ከሁሉም በላይ የብርሀነ መስቀልን ቆራጥነትና ልዩ ተሰጥኦ ሰፋ ባለ ሁኔታ የገለጹት የኢህአፓው ክፍሉ ታደሰ ነበሩ፡፡ አቶ ክፍሉ “ያ ትውልድ” በተሰኘውና በከፍተኛ ደረጃ ተነባቢ ለመሆን በበቃው መጽሐፋቸው “ብርሀነ መስቀል በኢህአፓ ውስጥ የራሱን አንጃ ፈጥሯል” የሚል ክስ እያቀረቡበት እንኳ ለትግሉ ያበረከተውን አስተዋጽኦ በተዋቡ ቃላት ገልጸዋል፡፡ ለምሳሌ ያህል የሚከተለውን መጥቀስ ይቻላል፡፡
“በተማሪው እንቅስቃሴ ውስጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከተውና አንደበተ ርቱእ የሆነው ብርሃነ መስቀል፣ በእንቅስቃሴው ውስጥ ሲታሰርና ሲፈታ የኖረ ነው” (ክፍሉ ታደሰ፣ ያ ትውልድ፣ ገጽ- 144)
*****
ብርሀነ መስቀል ለደርግ መርማሪዎች የሰጠው ቃል ሰሞኑን በኢንተርኔት ተበትኖ የብዙዎች መነጋገሪያ ሆኗል፡፡ እኔም ይህ 98 ገጾች ያሉት የምርመራ ቃል ከአንድ የፌስቡክ ጓደኛዬ ደርሶኝ እያነበብኩት ነው (ሙሉውን ዶክመንት www.zehabesha.com ከተሰኘ ዌብሳይት ማግኘት ትችላላችሁ)፡፡ እስከ አሁን ድረስ 1/3ኛ ያህሉን አገባድጄዋለሁ፡፡ ይሁንና ፊት ከማውቀው የብርሀነ መስቀል ታሪክ የተለየ ነገር አላገኘሁበትም፡፡ በሚቀጥሉት ቀናት አትኩሮት የሚስቡ መረጃዎችን ካገኘሁበት ልመለስ እችላለሁ፡፡ እስከዚያው ግን ስለብርሀነ መስቀል በትንሹ ላውጋችሁ፡፡

ብርሃነ መስቀል ረዳ ወልደ-ሩፋኤል በ1930ዎቹ አጋማሽ በትግራይ ገጠር ነው የተወለደው፡፡ ያደገው ግን በደሴ ከተማ የከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ በነበሩት አጎቱ ቤት ነው፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደሴ በሚገኘው የወይዘሮ ስሒን ት/ቤት ካጠናቀቀ በኋላ በ1955 ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገብቷል፡፡ በዩኒቨርሲቲ ቆይታው ትምህርቱን ከመከታተል ይልቅ ተማሪዎችን ለተቃውሞ በማንቀሳቀሱ ላይ ነበር ያተኮረው፡፡ በዚህም መሰረት ወደ ዩኒቨርሲቲው እንደገባ ከርሱ ቀደም ብለው “አዞዎቹ” በሚል ቡድን ዙሪያ የተሰባሰቡትን የስር-ነቀል ለውጥ ደጋፊ ተማሪዎችን ለመቀላቀል በቅቷል፡፡ ከዓመት በኋላ በ1956 በዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ተማሪዎች ህብረት ውስጥ የመረጃ ኦፊሰር ሆኖ ተመርጧል፡፡ በአመቱ ደግሞ የብሔራዊ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ህብረት ዋና ጸሓፊ ሆኖ ነበር፡፡

ብርሃነ መስቀል በ1957 የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች “መሬት ላራሹ” የሚል መፈክር አንግበው ድምጻቸውን ለፓርላማ ያሰሙበትን ታሪካዊ ሰልፍ ካደራጁት መካከልም ነበር፡፡ በዚያ ሰልፍ ሳቢያ ከትምህርታቸው ከተባረሩት ዘጠኝ ተማሪዎች መካከልም አንዱ ነው (በወቅቱ ከርሱ ጋር የተባረሩት ገብሩ ገብረወልድ፣ ሀይሉ ገብረዮሐንስ፣ ዮሐንስ ስብሐቱ፣ ታዬ ጉርሙ፣ ዘርዑ ክህሸን፣ ስዩም ወልደ ዮሐንስ፣ ሀብቴ ወልደ ጊዮርጊስና ሚካኤል አበበ ናቸው)፡፡ እነዚያ ተማሪዎች ከአንድ ዓመት በኋላ ወደ ዩኒቨርሲቲው ቢመለሱም በተረጋጋ ሁኔታ ትምህርታቸውን መከታተል አልቻሉም፡፡ በየጊዜው በሚካሄዱት ሰልፎችና የተቃውሞ ስብሰባዎች ግንባር ቀደም ተጠያቂ እየሆኑ ይታሰሩ ነበር፡፡ በስተመጨረሻ ግን የ“አዞዎቹ” ቡድን አባላት ከነአካቴው ከዩኒቨርሲቲው ተባረሩ፡፡ በመሆኑም በተደራጀ ሁኔታ ለመታገል ወሰኑ፡፡

በዚህም መሰረት ብርሃነ መስቀልና አምስት ጓደኞቹ ከባህር ዳር ወደ አዲስ አበባ የሚበር አንድ አውሮፕላን በመጥለፍ ወደ ካርቱም ኮበለሉ፡፡ ከጥቂት ወራት በኋላም ወደ አልጄሪያ ተሻገሩ፡፡ በአልጀርስ ቆይታቸው እጅግ ቀስቃሸ የሆኑ ጽሑፎችን እያዘጋጁ ወደ ሀገር ቤት ይልኩ ጀመር (በዚያ ዘመን “ጥላሁን ታከለ” በሚል የብዕር ስም በመጠቀም አስደናቂ ጽሑፎችን ይጽፍ የነበረው ብርሃነ መስቀል ረዳ እንደሆነ ነው የሚታመነው)፡፡ በአልጄሪያ የነበሩት ስደተኛ አብዮተኞች በውጪው ዓለም ትምህርታቸውን ከሚከታተሉ ኢትዮጵያዊያን ጋር በሚያደርጓቸው ግንኙነቶች በተደራጀ መንገድ የሚታገሉበትን መንገድ ቀየሱ፡፡ እነዚያ ውይይቶች እያደጉ ሄደው በ1964 ኢህአድ (የኢትዮጵያ ህዝብ አርነት ድርጅት) የተሰኘ ህቡዕ ፓርቲ ተወለደ፡፡ ብርሀነ መስቀል ረዳም የድርጅቱ ዋና ጸሐፊ ሆኖ ተመረጠ (የድርጅቱ ስም በ1967 “የኢትዮጵያ ህዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ” በሚል ተለውጧል፤ ይህም በአህጽሮት “ኢህአፓ” የሚባለው ነው)፡፡

ብርሀነ መስቀል የኢህአድ ዋና ጸሓፊ በነበረበት የመጀመሪያ ዓመት በአብዛኛው ፓርቲውን የማስተዋወቅና ድጋፍ የመፈለግ ስራዎችን ነበር የሰራው፡፡ በዚህም ከአውሮፓ እስከ መካከለኛው ምስራቅ ድረስ ተጉዟል፡፡ ከባለቤቱ ታደለች ሀይለሚካኤል ጋር የተዋወቀው በዚያን ጊዜ ነው፡፡ በ1966 ብርሃነ መስቀልና ጥቂት ሰዎች የድርጅቱን የትጥቅ ትግል እንዲጀምሩ ወደ ኤርትራ ተላኩ፡፡ ወታደራዊ ስልጠና ለመውሰድ ለአንድ ዓመት በኤርትራ ከቆዩ በኋላ በ1967 መጀመሪያ ላይ ትግራይ ውስጥ ወደሚገኘው አሲምባ ተራራ ተሻገሩ፡፡ ሆኖም የትጥቅ ትግሉን ሳይጀምሩ በአሲምባ ቤዛቸው ለስድስት ወራት ቆዩ፡፡ በዚህ መሀል ስምንት ያህል የቡድኑ አባላት ከብርሀነ መስቀል ጋር የነበራቸውን ቀየሜታ በማሳበብ ድርጅቱን ጥለው ለደርግ መንግሥት እጃቸውን ሰጡ፡፡ ብርሀነ መስቀል በፋኖዎቹ አድራጎት በመቆጣቱ በሌሉበት የሞት ፍርድ ፈረደባቸው፡፡ ሆኖም ይህ ውሳኔው ከሌሎች የኢህአፓ አባላት ተቃውሞ ገጠመው፡፡ የኢህአፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጉዳዩን ካጣራ በኋላ በሰዎቹ ላይ የተላለፈው የሞት ፍርድ እንዲነሳ ወሰነ፡፡ ብርሀነ መስቀልም ከሰራዊቱ ተነጥሎ ወደ አዲስ አበባ እንዲሄድ ተወሰነ፡፡ ይህም በብርሀነ መስቀልና በሌሎቹ የኢህአፓ መሪዎች መካከል ንትርክ ፈጠረ፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ በነሐሴ ወር 1967 አህአፓ ራሱን በአዲስ መልክና በአዲስ ስም ሲያደራጅ “ዋና ጸሐፊ” የሚባል የስልጣን እርከን ተሰረዘ፡፡ ድርጅቱ ሊቀመንበርም ሆነ ዋና ጸሐፊ የለውም ተብሎ ታወጀ፡፡ ብርሀነ መስቀል ይህንን እርምጃ እርሱን ከቦታው ለማንሳት የተሸረበ ሴራ አድርጎ ስለወሰደው ከፍተኛ ቅሬታ አደረበት፡፡ ከማዕከላዊ ኮሚቴው ጋር የሚያደርገውንም ግንኙነት ማቀዝቀዝ ጀመረ፡፡ የደርግ መንግሥት በሚያዚያ ወር 1968 በህቡዕ ለተደራጁ ድርጅቶች ሁሉ የግንባር ጥሪ ሲያደርግ ብዙሃኑ የኢህአፓ አመራር ጥሪውን በመሰረቱ እንደሚቀበል ከገለጸ በኋላ መሟላት ያለባቸውን ቅድመ ሁኔታዎች አስቀመጠ፡፡ እነዚያ ሁኔታዎች ካልተሟሉ በስተቀር ከደርግ መንግሥት ጋር እንደማይሰራ ገለጸ፡፡ ብርሀነ መስቀል ግን “ቅድመ- ሁኔታ ማስቀመጡ ልክ አይደለም” በማለት ተከራከረ፡፡ በነሐሴ ወር 1968 የኢህአፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ “ራሳችንን ለመከላከል የከተማ ትጥቅ ትግል ማድረግ አለብን” በማለት ሲወስን ብርሀነ መስቀል “ውሳኔው አደገኛ ነው፤ ኢህአፓን ያስመታል፤ ደግሞም ደርግ ማርክሳዊ ነኝ ብሎ ያወጀ መንግሥት ስለሆነ ማርክሳዊ መንግሥትን በትጥቅ አመጽ መቃወም የአብዮታዊያን ጸባይ አይደለም” በማለት በብርቱ ተቃወመው፡፡ ይህም ታቃውሞ ከኢህአፓ አመራር ጋር እስከ ወዲያኛው አቆራረጠው፡፡

የኢህአፓ አመራር ብርሀነ መስቀል ያሳያቸውን የአቋም ልዩነቶች ከገመገመ በኋላ ከማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነቱ ሰረዘው፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላም “ብርሀነ መስቀል በፓርቲው ውስጥ የራሱን አንጃ ለመመስረት ጥረት እያደረገ ነው” የሚል ክስ አቀረበበት፡፡ በድርጅቱ ጋዜጦች ላይ ግለ-ሂስ እንዲያደርግም አዘዘው፡፡ ብርሀነ መስቀልም ሂሱን ካወረደ በኋላ በድርጅቱ ታጣቂዎች እንዲጠበቅ ተደረገ፡፡ በሚያዚያ 1969 ግን ለማንም ግልጽ ባልሆነ መንገድ ከአዲስ አበባ ከተማ ተሰውሮ ወደ መርሐቤቴ አውራጃ ገባ፡፡ እዚያም ከተወሰኑ ሰዎች ጋር የትጥቅ ትግል ለማድረግ ሞከረ፡፡ ይሁን እንጂ በእርምጃው ከጥቂት ወራት በላይ አልዘለቀም፡፡ የደርግ አዳኝ ሀይሎች በ1970 መጀመሪያ ላይ ይዘውት ወደ አዲስ አበባ አመጡት፡፡ ለአንድ ዓመት ከሰድስት ወራት ያህል በታላቁ ቤተ መንግሥት ከታሰረ በኋላ በሚስጢር ተገደለ፡፡
*****
የብርሀነ መስቀል አንጃ የመፍጠር ሙከራ በራሱም አንደበት የተረጋገጠ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ብርሀነ መስቀል “እኔ ያካሄድኩት የእርማት ንቅናቄ እንጂ ፓርቲውን ለማጥፋት ያለመ አንጃ አልፈጠርኩም” ባይ ነው፡፡ በተጨማሪም ባለቤቱ ወይዘሮ ታደለች ሀይለ ሚካኤል በአንድ ወቅት በሰጡት ቃለ ምልልስ ብርሀነ መስቀል የእርማት ንቅናቄ ለማካሄድ መሞከሩን ተናግረዋል፡፡ በዚያ ዘመን በርሱ ስም የተሰራጩትን ልዩ ልዩ ዶክመንቶች በሙሉ የርሱ ናቸው ለማለት ይከብዳል፡፡ አንደኛው ጽሑፍ ግን በርሱ እጅ ጽሑፍ የተጻፈ መሆኑ ስለሚታወቅ የርሱን እምነት ይገልጻል ተብሎ ይታመናል፡፡ ብርሀነ መስቀል በዚያ ጽሑፉ የኢህፓን አመራር ቢኮንንም ደርግንም በሚገባ ይቃወማል፡፡ እንዲሁም በርሱ ስም ድርጅቱን የበጠበጡ በርካታ ቅጥረኞች እንደነበሩም ያወሳል፡፡ ሆኖም የኢህአፓ አመራር እርሱ ያለውን አምኖ የተቀበለው አይመስልም፡፡ ኢህአፓዎች “ለድርጅቱ ብተና ፈር የቀደደ ከሀዲ ነው” ነው የሚሉት፡፡

ማንም የማይክደው አንድ ሐቅ ግን አለ፡፡ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ ሲነሳ ብርሀነ መስቀልን መርሳት በጭራሽ አይሞከርም፡፡ በርካታ የለውጥ ፈላጊው ትውልድ አባላት የርሱን አርአያ በመከተል ወደ ትግሉ ጎራ መቀላቀላቸውንም ማስተባበል አይቻልም፡፡ ስለዚህ ምሁራን በቅጡ ያልተመረመውን የዚህን ፋኖ ታሪክ ጎልጎለው በትግሉ ውስጥ የነበረውን አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ሚና ሳይሸፋፍኑ ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል፡፡
*****
አፈንዲ ሙተቂ
ህዳር 28/2006


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>