“የኢትዮጵያ ህዝብ ይፍረድ!” ትላለች አባባሏ፤ በእርግጥ አባባሏ ሰው ፊት የምታቆምና ደማም እንዲሁም መልከ-መልካም ነች፡፡ የኢትዮጵያን ህዝብ “ፈራጅ” ለማድረግ ወይም አባባሏን ለመተግበር ግን ፈታኝ ይሆናል፡፡ አንዳንዴም አባባሏ በአንደበት የምትላወስ ነገር ግን በእጅ የማትዳሰስ እና መላ ሰውነቷ በእሾህ የተከበበ ፅጌሬዳ ትመስለኛለች፡፡
በተለያዩ ህብረ-ቀለማት ያሸበረቀችው ፅጌሬዳ አበባ ሲያዩዋት እጅግ ማራኪና መንፈስ አርኪ ብትሆንም፤ እልፍ የገደለ ሰው እንኳን በእጁ ጨብጦ ሊይዛት አይችልም፡፡ ከላይ ባማረ አፃፃፍ ተፅፋ መቀመጫዋን ኢትዮጵያ ያደረገችው አባባልም የፅጌሬዳ አበባ እህት ኩባንያ ሳትሆን አልቀረችም መሰለኝ ለያዥ ለገናዡ አልጨበጥ ካለች ረዥም ዘመናት ተቆጠሩ፡፡ ይህ ማለት አባባሏን የሚተገብር ወይም የኢትዮጵያ ህዝብ ፈራጅ እንዲሆን የሚተጋ ኃይል ጠፍቷል፡፡ አልያም ነጥፏል ማለት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ደግሞ በዚህ በሰለጠነ ዘመን በሀገሩ ጉዳይ ፈራጅ መሆን አለበት፤ ወይም መንግስት የህዝብን ፍርድ ለመቀበል የሚያስችል ትከሻ ሊኖረው ይገባል፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብ ኃይማኖተኛ ነው፡፡ ሁሉም አማኞች በየእምነታቸው የሚመሩበት ወይም የሚገዙበት መፅሐፍ አላቸው፡፡ እርግጠኛ ነኝ የየትኛውም ኃይማኖት መፅሐፍ ውሸት አያበረታታም፡፡ እስኪ ኃይማኖተኛ ነኝ የሚል ሰው ሁሉ ውሸት የማያበረታታውን መፅሐፉን መሰረት አድርጎ የሚከተለውን ጥያቄ የመልስ ባለቤት ያድርገው፡፡
እውነት የኢትዮጵያ ህዝብ ፈራጅ ነውን? ማነው ለኢትዮጵያ ህዝብ የመፍረድ ስልጣን የሰጠው? እናንተ ኢትዮጵያውያን ፈርዳችሁ ታውቃላችሁ? ከፈረዳችሁስ ምን ዓይነት ፍርድ?…..የኢትዮጵያ ህዝብ የወያኔን አምባገነናዊ አገዛዝ አውግዞ፣ እየጨቆኑት የኖሩትን አምባገነን ባለስልጣናት የተፋረደው መቼ መቼ ይሆን?……ፍርዱን ለኢትዮጵያ ህዝብ ትቼዋለሁ፡፡
አባባሏ የኢትዮጵያን ህዝብ ሆድ ለመብላት የምትነገር ካልሆነ በስተቀር የመፍረድ ቀርቶ ለጠየቀው ጥያቄ በቂ መልስ የማግኘት መብት ለሌለው ህዝብ “የኢትዮጵያ ህዝብ ይፍረድ” ማለት ምን ማለት ነው? የኢትዮጵያ ህዝብ መፍረድ ቢችልማ ደርግ 17 አመት ስልጣኑን ተቆናጥጦ ባልተንፈላሰሰ ነበር፡፡ ህዝቡ በተቃወመው ማግስት ወርዶ በወታደራዊው መንግስት ፈንታ ህዝቡ የሚፈልገው ዓይነት መንግስት በተቋቋመ ነበር፡፡
ግን የኢትዮጵያ ህዝብ ሲፈረድበት ማየት እንጂ፣ መፍረድ ስለማይችል ብዙ ህዝብ ከደርግ ጋር እየተላተመ ሞቷል፡፡ በህዝብ ፈቃድም ሆነ ያለ ህዝብ ፈቃድ ራሳቸውን “መንግስት” አድርገው የሾሙ እንደ ወያኔ ያሉ የኢትዮጵያ መንግስታት ሁሉ ስልጣን ላይ ሊወጡ በተቃረቡበት ዋዜማ የኢትዮጵያ ህዝብ ፈራጅ እንደሆነ በየቦታው ይናገሩ ነበር፡፡ ስልጣን ከያዙ ማግስት ጀምሮ ደግሞ ፈራጁ ሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብ መሆኑ ይቀርና አንድ ድንኳን መትከል የማይችሉ ጥቂት ሰዎች (ባለስልጣናት) ብቻ ፈራጅ ይሆናሉ፡፡ ወያኔን ጨምሮ ሌሎች የእሱ ቢጤ አምባገነኖች ከፈራጅነት አልፎም ፈላጭ ቆራጭ ሆነው በስልጣን ዋዜማ በጠራራ ጸሐይ የገቡትን ቃል ያለ አንዳች ይሉይንታ ያጥፉታል፡፡ ለዚህ ደግሞ ዋነኛ ምሳሌ የሚሆነው አምባገነኑ ወያኔ መሆኑ አያጠራጥርም፡፡ በ97 ምርጫ የኢትዮጵያ ህዝብ ድምፁን ለቅንጅት ሰጥቶ ወያኔን በምርጫ ካርድ ቢፋረደውም፤ ለህዝብ ፍርድ ደንታ የሌለው ወያኔ ግን ቅንጅቶችን እስር ቤት ወርውሮ አምባገነንነቱን በተግባር አሳይቶ ነበር፡፡ እነሆ ዛሬም እንደ አንድነት ያሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን አፈራርሶ፣ ፓርቲውን ራሱ ጠፍጥፎ ለሰራቸው ሰዎች አሳልፎ ሰጥቶታል፡፡ ዛሬ ጠንካራው እና በህዝብ ዘንድ ተቀባይነት የነበረው የቀድሞው አንድነት ፓርቲ የለም፡፡ ለኢህአዴግ ራስ ምታት የነበረው የቀድሞው አንድነት ፓርቲ፣ ሲጠሯቸው አቤት ሲልኳቸው ወዴት በሚሉ የወያኔ አጎብዳጆች ተሞልቷል፡፡ በግንቦት ወር አጋማሽ በሚካሔደው ሀገር አቀፍ ምርጫ ላይ ለወያኔ ራስ ምታት ይሆኑ የነበሩ የተቃዋሚ መሪ አመራሮች እስር ቤት ተወርውረዋል፡፡ በወጣቶች የተገነባው ሰማያዊ ፓርቲ፣ ወያኔ የሚያደርስበትን ጫና ተቋቁሞ ወደ ምርጫው እየተጠጋ ነው፡፡ ሰማያዊም ቢሆን ሰበብ አየተፈለገ አባላቶቹ እስር ቤት ተወርውረውበታል፡፡ የፓርቲው ሊቀ-መንበር ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት በወያኔ ሸፍጥ ከምርጫው ውጪ መደረጋቸው የስርዓቱን አስከፊነት ቁልጭ አድርጎ ያሳያል፡፡ በመጪው ምርጫ ህዝቡ ድምጹን ለተቃዋሚዎች በመስጠት እንደሚፋረደው አስቀድሞ የተረዳው አምባገነኑ ወያኔ፣ የውድድሩን ሜዳ ለብቻው ሊጋልብበት አሰፍስፏል፡፡ ይሁን እንጂ ህዝቡ ያለችውን ቀዳዳም ቢሆን ተጠቅሞ ወያኔን ለመፋረድ ተዘጋጅቷል፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ የህዝብ ዓይን ማረፊያ መሆን ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡ ለምርጫው ያለው ተስፋም እሱ ነው ለማለት ያስደፍራል፡፡ እንደዚሁም ደግሞ በዶክተር መረራ ጉዲና የሚመራው ተቃዋሚ ፓርቲ በቅርቡ በኦሮሚያ ክልል ባካሔደው ሰላማዊ ሰልፍ በርካታ ህዝብ በነቂስ ወጥቶ ነበር፡፡ ወያኔን ባስደነገጠው ሰላማዊ ሰልፍ ላይ ተገኝተው የነበሩት ዶክተር መረራ ጉዲና በመጪው ምርጫ ቀንደኛ የወያኔ ተፎካካሪ መሆናቸውን አስመስክረዋል፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብም እንደ ሰማያዊ ፓርቲ እና የዶክተር መረራ ፓርቲ (መድረክ) ላሉ ተቃዋሚዎች ድምጹን በመስጠት ወያኔን እንደሚከዳ እና እንደሚፋረድ ታውቋል፡፡ ምክንያቱም ህዝቡ ለወያኔ ፍቅር እንደሌለው በተለያዩ ወቅቶች አሳይቷል፡፡ ወያኔም በበኩሉ፣ የኢትዮጵያ ሙስሊሞችን ተወካዮች (መሪዎች) በማሰር እንዲሁም አይሲስ በሊብያ በኢትዮጵያውያን ላይ የፈጸመውን አሰቃቂ ግድያ ለማውገዝ ሰልፍ የወጡ ዜጎችን በፌዴራል ፖሊስ በማስደብደብ ለኢትዮጵያ ህዝብ ምንም ዓይነት ፍቅር እንደሌለው በአደባባይ አስመስክሯል፡፡ በሰልፉ ላይ ተገኝተው በወያኔ ፖሊሶች ከተደበደቡ ንጹኃን ዜጎቻችን መካከል አንዱ በደረሰባቸው ክፉኛ ድብደባ የተነሳ ህይወታቸው ማለፉ በቅርቡ ተገልጽዋል፡፡ ከዚህ መሰሉ የስርዓቱ አስከፊ ባህሪ ተነስተን፣ መጪው ምርጫ ወያኔ የሽንፈት ጽዋዉን የሚጋትበት እንደሚሆን መናገር ይቻላል፡፡
በዓለም ላይ ያልተካሰ ህዝብ ቢኖር የዚህችው ጉዷ የማያልቀው የኢትዮጵያ ህዝብ ነው፡፡ ቃል ገቢዎቿ ብዙ ፈፃሚዎቿ ግን ጥቂት አንዳንዴም ባዶ እየሆነ የተቸገረችው ይህቺው የኛው ጉድ ኢትዮጵያ ነች፡፡
አንድ ተማሪ ከ1ኛ ክፍል እስከ ዩኒቨርስቲ ድረስ ለመጓዝ ቢያንስ ሁሉንም ክፍል ሳይወድቅ ካለፈ 12 አመት ይፈጅበታል፡፡ አስቡት! 12 አመት ማለት አንድ ልጅ ተወልዶ የአንድን መንግስት ክፋትና በጎነት የሚለይበት ጊዜ ነው፡፡ እነዚህ አመታት ከግምት ውስጥ ስለማይገቡ ብዙ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች በወያኔ ተገድለዋል፡፡ መብታቸውን በመጠየቃቸው ብቻ በየእስር ቤቱ የተወረወሩ ዜጎቻችን ቁጥር ስፍር የላቸውም፡፡
በተለያዩ የምርጫ ክርክሮች ወቅት የወያኔ ፓርቲ አመራሮች “የኢትዮጵያ ህዝብ ይፍረድ” የምትለዋን አባባል ደጋግመው ይጠቅሳሉ፡፡ ይህን የሚሉት ህዝቡ በሀገሩ ጉዳይ እውነት ፈራጅ ሆኖ አይደለም፡፡ ወቅቱ የምርጫ ጊዜ በመሆኑ ብቻ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ በአምስት አመት አንዴ ዳኛ ነው፡፡ ይህ አይካድም፤ ግን በአምስት አመት አንዴና እንደ ወር አበባ ጊዜ እየጠበቀ የሚያገረሽ ዳኝነት ተሰምቶም ታይቶም ስለማይታወቅ በዳኝነት ወይም በፈራጅነት ለመቀበል ይከብዳል፡፡ ዳኝነት በየዕለቱ ነው፤ ፈራጅነትም እንደዛው፡፡ የሆነው ሆኖ ግን በመጪው ምርጫ ወያኔ ከህዝብ ፍርዷን እንደምትቀበል የበርካቶች እምነት ነው፡፡
አስቡት! ለምሳሌ አንድ መንግስት በኢትዮጵያ ለ20 አመት ነገሰ እንበል፤ ህዝቡም በአምስት አመት አንዴ ነው የሚፈርደው የሚለውንና እየተተገበረ ያለውን አባባልም እንያዝ፡፡ በዚህም ምክንያት 20 አመት ስልጣን ላይ በቆየው የመንግስት አስተዳደር ጊዜ ህዝቡ አራት ጊዜ ብቻ ነው የፈረደው፡፡ ይህን አካሔድ ለመለወጥ እና የኢትዮጵያ ህዝብ በየዕለቱ በሀገሩ ጉዳይ ላይ የመፍረድ (የመወሰን) ሥልጣን እንዲኖረው ለማድረግ የሚወዳደሩት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ብዙ ባይሆኑም፤ ያሉትም ቢሆኑ ለወያኔ ራስ ምታት ሆነውበታል፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ በእያንዳንዱ ኢኮኖሚያዊም ሆነ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ፈራጅ መሆን አለበት፡፡ የጎደለ ነገር ሲያይ ፖለቲካውን አልያም ኢኮኖሚውን አስቁም ክፍተቱን ለመሙላት እንዲህ ይደረግ የሚል ፍርድ መስጠት አለበት፡፡ ፖለቲካ የመንግስት ብቻ አይደለም፤ የህዝብ ጭምር ነው፡፡
ያለ ህዝብ ተሳትፎ ፖለቲካ የለም፡፡ ህዝብን ጥሎ ፖለቲካውን አንጠልጥሎ መጓዝ መንገድ ላይ ለመቅረት ካልሆነ በስተቀር የትም አያደርስም፡፡ ይህንን እውነታ ያልተረዳው እና ለሃያ አራት ዓመታት አምባገነንነቱን በተገቢው ሁኔታ ያስመሰከረው ወያኔ በግንቦቱ ምርጫ፣ በኢትዮጵያ ህዝብ ክህደት ይፈጸምበታል፡፡ እንደለመደው ኮሮጆ ገልብጦ የምርጫ ደምጽ ካላጭበረበረ በስተቀር፣ ህዝብ ወያኔን የሚመርጥበት ምክንያት የለውም፡፡ ምክንያቱም አምባገነንን የሚመርጥ ህዝብ የለም!!!! ወያኔም ህዝብ እንደማይመርጠው አምኖ ትከሻውን ለሽንፈት መቀበያ ቢያዘጋጀው መልካም ነው እላለሁ!!! ኢትዮጵያ መልካም መንግስት ይገጥማት ዘንድ እየተመኘው መጣጥፌን እቋጫለሁ፡፡
The post እነሆ፡- ሕዝብ ወያኔን የሚከዳበት ጊዜ ደረሰ appeared first on Zehabesha Amharic.