እዉቁ ቦክሰኛ ሙሐመድ አሊ በብዙዎች ዘንድ ተወዳጅ ነዉ።እኔም ወደዋለሁ፣አከብረዋለሁ።እ.ኤ.አ በ1974 ከጆርጅ ፎርመን ጋር ያደረገዉ ዉድድር ታሪካዊ ነበር።የነጭችን የበላይነት ለመቀነስ፣የ አፍሪካን ግርማ ሞገስ ለማጉላት እና በሌሎች ጉዳዮች ሳቢያ ዉድድሩ የተደረገዉ ዛየር ዉስጥ ነበር።ለዉድድሩ ስኬት የዛየሩ መሪ ሞቡቶ ሴሴኮ አስተዋጽኦ ማድረጋቸዉም ተዘግቧል።
ከሙሐመድ አሊ በአስራ አንድ አመት የሚያንሰዉ ጆርጅ ፎርማን ሙሐመድ አሊን ይበትነዋል፣የአሊ አስክሬን ወደ አሜሪካ ይመለሳል በማለት ተንታኞች ቢያስፈራሩም አሊ ግን ፍርሃት አልተሰማዉም።
“አሸንፋለሁ አልጠራጠርም!”ብሎ ቢጮህም “ያዉ የአሊ ጩኸት…ተፎካካሪዎችን ዝም ለማሰኘት የሚጠቀምበት ስልት”ተብሎም ነበር።
አለም ዉድድሩን በጉጉት ጠበቀዉ። ታላላቆቻችን “ዝናቡ ዘነበ…ተንጠባጠበ…አሊ ሙሐመድ ***እንትኑን አጠበ” እያሉ የጎረቤት ልጆች ያበሽቁን ነበረ ሲሉ… ከወላጆቼ ለመረዳት እንደቻልኩት እለቱን… ተጎዝጉዞ ሷሒብ (ወዳጅ)ተሰብስቦ ድዓ (ጸሎት) ተቀምጠዋል።
የቁርጡ ሰዓት ደረሰ! ወጣቱ አንበሳ ጆርጅ ፎርማን ያንን ድንቅ አንበሳ ሙሐመድ አሊ ቀጠቀጠዉ። ሌላ ግዜ በመስፈጠርና በመደነስ የሚታወቀዉ አሊ የቦክስ ገመዱን ተገን አድርጎ እራሱን ይከላከላል ጀመር።
ዳኞች የአሊ መዉደቅን ይጠብቃሉ።አሊ ለሰባት ዙር የፎርማንን ቡጢ እየጠጣ ወደገመዱ እየተለጠጠ አቅሙ የቻለዉን ለመሰንዘር ይሞክራል።ስምተኛዉ ዙር ላይ አሊ አንዴ ዘርግቶ በሐይለኛ ቡጢ ጆርጅ ፎርማን ሲመታዉ…ተዘረረ መነሳት አልቻለም። ሙሐመድ አሊ አሸነፈ።
ምስጢሩ ገመዱን ተገን ማድረጉ ነበር።ለካስ እያንዳንዱ ጆርጅ ፎርማን የሚዘረጋዉ ቡጡ አሊ ሰዉነት ላይ ሲያርፍ ግፊቱ ከአሊ ሰዉነት ላይ ተቀንሶ፣ገመዱ ላይ ደርሶ ጆርጅ ፎርማንን እራሱን ቡጢ ሆኖ እየደበደበዉ ነበር። በዚህም ሳቢያ ጆርጅ ፎርማን ዝሎ በጣሙን ዝሏል።
የአሊ ምላስና የስነ-ልቦና ጫና በጣሙን የላቀ ነበር። አሊ ወደ ፎርማን ጆሮ ጠጋ በማለት” ጆርጅ በቃ ይህቺዉ ናት ያለችህ?”ይለዋል። ፎርማን ዛለ፣ተንገፈገፈ፣ ስሜታዊ ሆነና የቦክሰኛ የመከላከል ቀመርን አፋለሰ። ታዳሚዉ “አሊ ቡመሜ! አሊ ቡመሜ! አሊ ጨርሰዉ! አሊ ጨርሰዉ!” እያለ ያስተጋበል::
አቅልን የሚያስተዉን፣እንደ ኤሌክትሪክ ሐይል የሚነዝረዉን፣የሚያንደፋድፈዉን ሐይለኛ ቡጡ ሙሐመድ አሊ አድብቶ በጆርጅ ፎርማን ላይ አሳረፈ። ወጣቱ አንበሳ በታላቁ አንበሳ ተዘረረ። ዳኛዉ ቆጠሩ። ፎርማን መነሳት አልቻለም።እስከዛሬ ሻምፒኦን ተብሎ ይዘከራል።
ከገመዱን ተገን ( Rope-a-dope)ተምሬ አለሁ። የሐያ አራት አመቱ ቡጢኛ በማለት ህወሃትን መስዬዋለሁ (ጆርጅ ፎርማን ያኔ ሐያ አምስት አመቱ ነበር) ሙሐመድ አሊን በነጻነት ታጋዮች መሰልኩት። ለምሳሌ በታሰሩ ጋዜጠኞች፣ፖለቲከኞች፣የሙስሊም የመፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴዎች፣የዞን ዘጠኝ ጦማሪያንና ወዘተ…። “አሊ ቡመሜ !አሊ ጨርሰው!” የሚለዉንደግሞ በሰፊዉ ህዝብ ጩኸት መሰልኩት። ህወሃት በራሱ ቡጡ እራሱን ሲደበድብ በአይነ-ህሊናዬ አየሁት።
የዛሬዉ የዛሬዉ ቡጢኛ መሳይ ህወሃት ዱላዉን፣ቡጢዉን፣ግርፋቱን፣ቶርቸሩን አራግፎ ሲያበቃ በራሱ ቡጢ እራሱ እየተደበደበ መዉደቁ አይቀሬ ነዉ።
ዳኛ ብርቱኳን ሚደቅሳ እስር ቤት ዉስጥ ጻፍኩት ባለቸዉ ግጥም “አዉሬነትህን ጨርስ!…ከዚህ በላይ ምን ታመጣለህ?” ስትል ጨቋኙን በምናባዊ ሰላም ትሞግታለች። አዉሬነትህን እስክትጨርስ፤በራስህ ቡጢ እራስህን ዘርረህ እስክትጥል በትእግስት እንታገልሃለን እንጂ በዘር በብሔር፣በሐይማኖት የመከፋፍል ድግስን አንደግስልህም:: ሰፊዉ ህዝብ አሽናፊ ሻምፒዮን መሆኑ አይቀሬ ነዉ።ኢንሻ አላህ። ልብ ያለዉ ልብ ይበል!
The post ገመዱን ተገን (Rope-a-dope) – ከሳዲቅ አህመድ appeared first on Zehabesha Amharic.