Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

[በዚህ ሳምንት የተማርናቸው ሦስት ነገሮች] 1ኛ) ቼዘኛውን አልሲሲ በጥንቃቄ እንያቸው * 2ኛ) ለመናገር ነጻነት ታጋዩ ዳኛቸው ጽዋችንን እናንሳ * 3ኛ) ውስጣዊ ሉዓላዊነታችም አርበኝነት ይሻል

$
0
0

ከአንድ ዓመት በፊት አብድል ፈታ አልሲሲ የግብጽ ፕሬዝዳንት እንደሚኾኑ ሲታወቅ አገሪቱን በቅርብ የሚከታተሉ ምሁራን እና የፖለቲካ ተንታኞች የሰውየውን የፖለቲካ አቋም ለማወቅ ጥናታቸውን አጧጧፉ። የአልሲሲ የቀድሞ ጽሑፎች፣ ንግግሮች እና ቃለ ምልልሶች ተበረበሩ። በተለይ እ.ኤ.አ. በ2006 ፔንሴልቬንያ በሚገኝ የአሜሪካ ጦር አካዳሚ በነበሩበት ወቅት የጻፉት የመመረቂያ ጽሑፍ እና እ.ኤ.አ በ2008 በካይሮ በሚገኘው አሜሪካን ዩኒቨርሲቲ ለዓለም አቀፍ ግንኙነት ተማሪዎች የሰጡት ሌክቸር መስመር በመስመር በጥንቃቄ ተነበቡ፣ ተመረመሩ። በእነዚህ ጥናቶች የአልሲሲ የፖለቲካ እምነት ግልጽ ብሎ ይወጣል። ፕሬዝዳንቱ ፖለቲካን (በውስጥም በውጭም) የራስን ጥቅም ለማስጠበቅ በሚታገሉ ግለሰቦች፣ ቡድኖች እና አገሮች መካከል የሚደረግ የሥልጣን እና የሐይል ሽሚያ አድርገው ይመለከቱታል። እንደ ፍትህ፣ እኩልነት፣ ነጻነት እና ዴሞክራሲን የመሳሰሉ የፖለቲካ እና የሞራል እሴቶች የሚኖራቸውን ቦታ ባይክዱም የፖለቲካ አይዳያሊስቶች እንደሚሉት የተቀበረ ዋጋ (intrinsic value) ያላቸው እሴቶች ሳይኾኑ የሥልጣን ሽሚያን እና ሽኩቻን ለመፍታት አልፎ አልፎ የምንጠቀምባቸው መሣርያዎች እንደኾኑ ያምናሉ። ይህ አቋማቸው የፖለቲካ ሪያሊስት ያስብላቸዋል።

ethiopia2

አልሲሲ በሕዝብ ፊት ንግግር ሲያደርጉ ስሜታዊ ኾነው ቢታዩም ፖለቲካን ሲያሰሉ ግን ዐይናቸው እምባ የማያቆረዝዝ እና ልባቸው የማይደማ ቀዝቃዛ ሪያሊስት ናቸው። ይህ አቋማቸው በወታደራዊ ደህንነት ውስጥ በመሪነት በቆዩባቸው ጊዜያት ካካበቱት የስትራቴጂ ጫዎታ ልምድ ጋራ ተዳምሮ በውስጥም በውጪም ላሉ ወዳጆቻቸው እና ጠላቶቻቸው ፈታኝ ግለሰብ እንዲኾኑ አድርጓቸዋል። ግብጽን የሚያጠኑት ታወቂው ፖለቲካል ሳይንቲስት ስቲቨን ኩክ እንደሚሉት “ሲሲ የአንዋር ሳዳት እና የቭላድሚር ፑቲን ቅይጥ” ናቸው።

ባለፈው ሳምንት በሊቢያ ለአይሲስ ጥቃት ተጋልጠው የነበሩ ኢትዮጵያውያንን ግብጽ “ነጻ እንዳወጣች” ገለጸች። አልሲሲ አውሮፕላን ጣቢያ ድረስ በመሄድ ኢትዮጵያውያንን ተቀበሉ። የግብጽ ሚዲያዎች ለሁለት ቀናት ወሬውን አደሩት። አንዳንድ ኢትዮጵያውያን አስተያየት ሰጪዎች “የቁርጥ ቀን ደራሽ እና እውነተኛ ጓደኛ” ሲሉ አንቆለጳጰሷቸው። በሶሻል ሚዲያም በርካቶች ለግብጽ እና ለፕሬዝዳንቱ ምስጋናቸውን ቸሩ። ፕሬዝዳንቱ ለኢትዮጵያውያን እንዲህ ዐይነት ተቆርቋሪነት ሲያሳዩ የመጀመርያቸው አልነበረም። ከአሰቃቂው የሊቢያ ግድያ በኋላ ቁጣቸውን እና ሐዘናቸውን ለመግለጽ የመጀመርያ መሪ ነበሩ፤ በጊዜው ዘብረቅረቅ ብሎባቸው የነበሩትን ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝን ሁሉ ቀድመው። ከጭብጨባው እና ከምስጋና ችሮታው አልፈን ይህን ድርጊት ፕሬዝዳንት አልሲሲ ከሚያምኑበት የፖለቲካ ሪያሊዝም አንጻር እንግምግመው። እንዲህ ዐይነት በጎ ድርጊቶች ሲፈጸሙ የሪያሊስት የመጀመርያ ጥያቄ “አድራጊው ምን ፈልጎ ይኾን?” የሚል ነው። አልሲሲ እና ግብጽ ምን ፈልገው ይኾን? አልሲሲ ካርታቸውን ወደ ደረታቸው አስጠግተው የሚቆምሩ ፖለቲከኛ በመኾናቸው ርምጃቸውን ለማወቅ ያስቸግራል፤ ነገር ግን የግብጽ ፖለቲካ ተንታኞች የፕሬዝዳንቱ ሁለት ግቦች ቀስ እያሉ እየጠሩ መታየት መጀመራቸውን ያወሳሉ። እነዚህን ሁለት ግቦች እንደ መነጽር እንጠቀምባቸው።

በውጭ ፕሬዝዳንት አልሲሲ ግብጽ በሙባረክ የአስተዳደር ዘመን አጥታ የነበረውን የዓለምአቀፍ መድረክ እና የነበራትን ተሰሚነት መመለስ ይፈልጋሉ። ይህን ለማስፈጸም የመንትያ መዘውሮች ስትራቴጂን (double pivot strategy) ይከተላሉ። ይህ ስትራቴጂ ሁለት አንጓዎች አሉት። አንደኛው፦ የግብጽን የውጪ ግንኙነት ማሰባጠርን የሚመለከት ነው። ኩክ እንደሚሉት አልሲሲ ልክ እንደ ሳዳት ከምዕራብ አገሮች ጋራ ጥብቅ ወዳጅነት መመሥረት ይፈልጋሉ። ይኹንና ከሳዳት በተቃራኒው እንቁላላቸውን በሙሉ በአንድ ቅርጫት ውስጥ ማስቀመጥ አይፈልጉም። ከምዕራብ ወዳጆቻቸው ጋራ ያላቸውን ግንኙነት በማያሻክር ኹኔታ ከቻይና፣ ከሩስያ እና ከብራዚል ጋራ አዎንታዊ ግንኙነትን ለማዳበር እየተንቀሳቀሱ ነው። ሁለተኛ፦ አልሲሲ ግብጽ በዐረቡ ዓለም የነበራትን ጉልበት እና ተሰሚነት መልሳ እንድታገኝ ቢሹም በዚያ እንድትወሰን አይፈልጉም። ለዐረቡ ዓለም ለዘብ ያለ ጨለምተኛ አመለካከት አላቸው። ፕሬዝዳንቱ የዐረቡ ዓለም በውስጥ ግጭት፣ በርስ በርስ ሽኩቻ እና ክፍፍል፣ በአክራሪ ሃይማኖተኝነት መበራከት፣ በዐረብ ብሔርተኝት መዳቀቅ፣ በኢኮኖሚ እና ማኅበራዊ ቀውስ ምክንያት የተዳከመ እና መዳቀቁም የሚቀጥል እንደኾነ ያምናሉ። ይልቁንስ ግብጽ ከናስር አብደላ በኋላ ዘንግታው የቆየችው የአፍሪካ አህጉር በኢኮኖሚም ኾነ በፖለቲካ የመጪው ጊዜ ኹነኛ መድረክ እንደሚኾን ይገምታሉ። ስለዚህም በአፍሪካ በሕዝብ ብዛቷና በኢኮኖሚዋ ከፍ ያለችው ግብጽ በአህጉሩ ፖለቲካ ከቁመቷ የሚተካከል ቦታ እንድታገኝ ይፈልጋሉ። ይህ ወደ አፍሪካ የመቀየስ ፖሊሲ የአልሲሲ አስተዳደር ልዩ መገለጫ መኾኑን የግብጽን የውጭ ግንነኙነት ሚያጠኑ ምሁራን ይጠቁማሉ። አልሲሲ በግልጽ ወደተለያዩ የአፍሪካ አገራት ፊታቸውን እያዞሩ ተንሳፋፊ ስሞሽ (air kiss) እየላኩ ነው።
በቅርብ በየዓመቱ በሚካሄደው የግብጽ የኢኮኖሚ እድገት ኮንፈረንስ ላይ ለመጀመርያ ጊዜ ሰባት ከሰሃራ በታች የሚገኙ የአፍሪካ አገራት ከፍተኛ ልዑካን ቡድኖች ተገኝተዋል። ከሁለት ሳምንታት በፊት የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ጄኮብ ዙማ ወደ ካይሮ እንዲመጡ ተጋብዘው ሁለት ቀን ቆይተው ወደ አገራቸው ተመልሰዋል። አልሲሲ ተመራጩ የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ግብጽን እንዲጎበኙ የጠየቁት የመመረጣቸው ዜና ትኩስ እያለ ነበር። ከኢትዮጵያም ጋር በአባይ ዙርያ የስምምነት ሰነድ ተፈራርመዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ የኢኮኖሚ ኮንፈረንሱ ተጋባዥ ነበሩ። ኢትዮጵያውያኑን “የማዳኑን” ርምጃ በዚህ የግብጽ አዲስ የአፍሪካ ፖሊሲ አውድ ውስጥ ልንመለከተው እንችላለን። በተጨማሪም የአባይ ስምምነት ሰነድ ማስፈጸሚያ ስምምነቶች ድርድር እንደቀጠለ ነው። ግብጽ ከዚህ ድርድር ከፍ ያለ ድርሻ ማግኘት ትፈልጋለች። ድርድሩ ከባድ፣ ፈታኝ እና ላይ-ታች የሚበዛበት እንደሚኾን ይጠበቃል። አልሲሲ በተለይ ለኢትዮጵያ ሕዝብ የግብጽን ወዳጅነት በማሳየት በድርድሩ ወቅት ሊከሰት የሚችል ጠበኝነትን መከላከል እና ጥቅምን ማስጠበቅ ይፈልጋሉ። ለአጭር ጊዜም ቢኾን የአልሲሲ ድርጊት ይህን የሕዝብ ግንኙነት እና የዲፕሎማሲ ግብ ያሳካ ይመስላል። በተለይ በዚህ ጉዳይ ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት ያሳየው ማመንታት፣ ንቁ አለመኾን፣ ማንቀላፋት እና መደነባበር አልሲሲ በዲፕሎማሲ ቡጢ ነጥብ እንዲያስቆጥሩ ዕድል ሰጥቷቸዋል።

በውስጥ አልሲሲ የፖለቲካ ሳይንቲስቶች የሦስት እዮሽ ጥምረት (tripartite alliance) ብለው የሚጠሩትን በወታደሩ፣ በሲቪል አዛዥ (establishment) እና በደንህነቱ መካከል የነበረውን ቅንጅት መመለስ ይፈልጋሉ። ይህ ቅንጅት ከአንዋር ሳዳት አስተዳደር ጅምሮ አገሪቱን ለ40 ዓመታት ሲመራ ቆይቶ በግብጽ ዐመጽ ተፈረካክሷል። ይኹንና አልሲሲ ሥልጣናቸው ከዚህ የሦስት እዮሽ ጥምረት አልፎ የግብጽ ብሔርተኞችን፣ የመካከላኛው መደብ አባላትን፣ ለዘብተኛ ሙስሊሞችን እና የኦርቶዶክስ ክርስቲያኖችን ያካተተ የሕዝብ ኅብረት እንዲኖርም ይፈልጋሉ። ራሳቸውን የእነዚህ ኅብረተሰብ ክፍሎች ጀግና አድርጎ ለማቅረብ የተለያዩ ጥረተቶችን አድርገዋል፤ በተለይ የሙስሊም ብራዘርሁድ አጭር የሥልጣን ዘመን የተደጋጋሚ ጥቃት ሰለባ የነበሩትን የግብጽ ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች ለመሳብ ብዙ ታትረዋል፤ ተሳክቶላቸውም ጠንካራ ድጋፍ አግኝተዋል። ፕሬዝዳንቱ ከቤተ ክርስቲያኗ ጳጳሳት እና ከሃይማኖቱ ተከታዮች የቢዝነስ እና የማኅበራዊ ጉዳዮች መሪዎች ጋራ ጠበቅ ያለ ግንኙነት ፈጥረዋል። በሊቢያ በአይሲስ በግብጽ ክርስቲያኖች ላይ የሰጡት ፈጣን ምላሽ፣ ለኦርቶዶክስ ሃይማኖት እየሰጡ ያሉት ጥበቃ እና በቤተ ክርስቲያኗ ላይ ጥቃት ባደረሱ ግለሰቦች ላይ የወሰዷቸው ርምጃዎች ለዚህ ጠንካራ ድጋፍ ኹነኛ ምክንያቶች ናቸው። የግብጽ ሚዲያ ኢትዮጵያውያውያኑን “የማዳን” ዘመቻ፣ የሁለቱ አገሮች ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያናት ካላቸው ታሪካዊ ግንኙነት ጋራ በማያያዝ ተንትኖታል። አልሲሲ በዚህ ዲስኩር የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታዮች ጠበቃ እና ተከላካይ ኾነው ቀርበዋል። ከዚህም ሌላ ፕሬዝዳንቱ በዚህ ድርጊታቸው በአካባቢው የእስልምና አክራሪነት ላይ የሚደረገው ትግል መሪ መኾናቸውን ለማሳየት ሞክረዋል። ይህ በእስልምና አክራሪነት ላይ ልባቸው ለደነደነው ለግብጽ ሲኩላሪስቶች እና ብሔርተኞች መልካም ዜና ነበር። ርምጃቸው በአጠቃላይ በውስጥ እና በውጪ አዎንታዊ ድጋፍ እና አቀባበል አግኝቷል። በፖለቲካ ቀዳሚ ስፍራ ያለው ፍላጎት እንጂ እሴት አለመኾኑን የሚያምኑት ሪያሊስቱ አልሲሲ ቼዝ እየተጫወቱ ነው፤ በጥንቃቄ እንያቸው።

2ኛ) ለመናገር ነጻነት ታጋዩ ዳኛቸው ጽዋችንን እናንሳ

ከሰባት ዓመታት በፊት የፖለቲካ ፈላስፋው ዳኛቸው አሰፋ በአዲስ ነገር ጋዜጣ አማካኝነት ከሕዝብ ጋራ ከተገናኙ ጀምሮ በአደባባይ ምሁርነታቸው አላሰለሱም፤ በጋዜጦች፣ በመጽሔቶች፣ በፖለቲካ ፓርቲዎች እና ሲቪል ማኅበራት መድረኮች ላይ እየተገኙ ጽሑፎቻቸውን አቅርበዋል፤ ንግግሮች አድርገዋል። የፈላስፋው ዋነኛ ትኩረት የፖለቲካ ነጻነቶች ላይ ያነጣጠረ ነው፤ በተለይ የማሰብ እና የመናገር ነጻነት ላይ። በኢትዮጵያ ከ1966ቱ አብዮት ጀምሮ የተለያዩ ፖለቲካዊ እና ማኅበራዊ ጥያቄዎችን ያነገቡ ንቅናቄዎች ተነስተዋል፤ አንዳንዶቹ ለረዥም ጊዜ ሲቆዩ አንዳንዶቹ በአጭር ተቀጭተዋል። አንዳንዶቹ ጥያቄዎች የሕዝብ መሠረት (constituency) ሲያገኙ ሌሎቹ ያለ ድጋፍ ጭል-ጭል ብለው ተፍጠዋል። ይህን የፖለቲካ ታሪክ በጥንቃቄ ስንመረምረው አንድ ትልቅ ቀዳዳ እናገኛለን፤ የመናገር ነጻነትን ዋነኛ ጥያቄ ያደረገ ንቅናቄ አለመከሰቱ እና ነጻነቱ የሕዝብ መሠረት አለማግኘቱ።

ጋዜጠኞች እና ሌሎች በንግግር (speech) ሥራ ላይ የተሰማሩ ሰዎች አልፎ አልፎ በግለሰብ እና በቡድን በመኾን ለመናገር (በተለይ ደግሞ ለፕሬስ) ነጻነት ተዋግተዋል። ይኹንና እነዚህ ቡድኖች ራሳቸውን ወደ ንቅናቄ አሳድገው ከማኅበረሰቡ ድጋፍ ለማግኘት፣ የመናገር ነጻነት ያለውን የሞራልና የፖለቲካ ፍልስፍና መሠረት ለማስረዳት እና ከአብዮቱ ጀምሮ የመናገር ነጻነትን አንዳንዴ “የቅምጥል ቡርዣዎች ጥያቄ”፣ አንዳንዴ “ትርጉም የሌለው መደበኛ መብት (formal right)” አንዳንዴ ሥልጣኔ ሲስፋፋ እና መብትን በአግባቡ የሚጠቀም ሕዝብ ሲፈጠር መፈቀድ ያለበት፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ “ከኢኮኖሚ ዕድገት እና የመካከለኛው መደብ መስፋት ጋር የሚመጣ” እያሉ ሲነቅፉትና ወደ ጎን ሲያንገዋልሉት የቆዩትን ለመታገል እና ሐሳባቸውን ለማርከስ አልሞከሩም። ዶክተር ዳኛቸው እንዲህ ዐይነት የሕዝብ መሠረት በሌለበት መርገጫ ኔትዎርክ ሳይኖራቸው የመናገር ነጻነት ቀንደኛ ተሟጋች ኾነው ከወጡ ጊዜ አንስቶ ሳይታክቱ የነጻነቱን መሠረት፣ ትርጉም እና ምክንያት ከፍልስፍና እና ሶሻል ሳይንስ ሥራዎች እየጠቀሱ ለማስረዳት እና ድጋፍ ለማስገኘት ትግል አድርገዋል። ነጻነቱ የፖለቲካ ሙግት ኹነኛ አካል እንዲኾን ሞክረዋል። ለነጻነቱ የሕዝብ መሠረት ለመፍጠር ለፍተዋል፤ ደክመዋል። በመናገር ነጻነት ላይ የጻፏቸው ጽሑፎች ተሰብስበው ሊነበቡ እና ሊጠረዙ የሚገባቸው ግሩም ሥራዎች ናቸው።

ዳኛቸው በቦስተን ዩኒቨርሲቲ የዶክትሬት ዲግሪ መመረቂያ ጽሑፋቸውን የሠሩት በፈረንሳዊው ፈላስፋ ዦን ፖል ሳርተ ላይ ነው። በአማርኛ ጽሑፎቻቸው ውስጥ የሳርተን ተጽዕኖ ባንመለከትም ከእርሱ ጋር የሚያመሳስላቸው ነገሮች አሉ። ልክ እንደ ሳርተ ዶክተር ዳኛቸው የምሁርነት ኑራቸውን በአዳባባይ እየኖሩት ነው። ልክ እንደ ሳርተ የነጻነት ሐይለኛ ጠበቃ ናቸው። ልክ እንደ ሳርተ ከጭቆና እና ከአፈና ጋር ከተፋጠጡ በኋላ የኋላ ማርሽ አላስገቡም። ልክ እንደ ሳርተ ብዕራቸው ተናካሽ ነው። ልክ እንደ ሳርተ በጥብቅናቸው ምክንያት ዋጋ ከፍለዋል። ባለፈው ሳምንት ዶክተር ዳናቸው ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከመምህርነት የተባረሩበትን ምክንያት በማስመልከት የዩኒቨርሲቲው ባለሥልጣናት በሚዲያ በሰጡት ማብራሪያ በጽሑፍ ያቀረቡትን ምላሽ ስናነብ ይህን ዋጋ እና የተከፈለበትን ምክንያት እናስታውሳለን። ለመናገር ነጻነት ትንፋሽ በመስጠታቸው፣ ለመናገር ነጻነት በመናገራቸው ተቀጥተዋል። ይህ ትግላቸው ሕያው የሚኾነው የመናገር ነጻነት የሕዝብ መሠረት ሲኖረው ነው። ጽሑፋቸውን እየኮመኮምን ለዶክተር ዳኛቸው ትግል ስኬት ጽዋችንን እናነሳለን።

3ኛ) ውስጣዊ ሉዓላዊነታችም አርበኝነት ይሻል

የሐሳቦች ታሪክ ምሁር፣ ፈላስፋ፣ ጋዜጠኛ እና ምርጥ የንግግር ሰው የኾኑት አንግሎ-ሩስያዊው አይዛ በርሊን ከሚታወቁባቸው ጽሑፎች መካከል በቀደምትነት የሚጠቀሰው “Two Concepts of Liberty” ነው። በዚህ እስከ አሁን ድረስ ይዘቱ በሚያወዛግበው ጽሑፋቸው ሁለት የነጻነት ጽንሰ ሐሳቦችን ይተነትናሉ፤ አሉታዊ ነጻነት (negative freedom) እና አዎንታዊ ነጻነት (positive freedom)። በርሊን ነጻነት የግለሰቦችም የቡድንም ሊኾን እንደሚችል ያስምጣሉ። የአንድ ቡድን ወይም ግለሰብ አሉታዊ ነጻነት የሚለካው በግለሰቡ/ቡድኑ ድርጊት ላይ በተቀመጠው መሰናክል እና እንቅፋት መጠን ልክ ነው። መሰናክል ሲጨምር አሉታዊ ነጻነታችን ይቀንሳል። በሌላ በኩል ደግሞ የአዎንታዊ ነጻነታችን መጠን የሚለካው ራሳችንን በማስተዳደር (self rule) ብቃታችን ነው። የኬምብሪጅ ፖለቲካ ፈላስፋ የኾኑት ሬይመንድ ጊዩስ ይህን የበርሊንን ሐሳብ ቀለል አድርገው በዚህ መልክ ያቀርቡታል።

“ 1ኛ) የግለሰብ አሉታዊ ነጻነት፦ እጄ ከእስር ከተፈታ አንድ የድርጊት መሰናክል ስልተቀነሰልኝ አሉታዊ ነጻነቴ ይጨምራል፤ 2ኛ) የግለሰብ አዎንታዊ ነጻነት፦ ከባርነት ነጻ ከወጣሁ ራሴን የማስተዳደር ብቃቴ ስለሚጎለብት አዎንታዊ ነጻነቴ ያድጋል፤ 3ኛ) የቡድን አሉታዊ ነጻነት፦ ተንቀሳቃሽ ጎሳ በድንበር መዘጋት ምክንያት ወደ አንድ አካባቢ እንዳይገባ ከታገደ የቡድኑ አሉታዊ ነጻነቱ ይቀንሳል። 4ኛ) የቡድን አዎንታዊ ነጻነት፦ በቅኝ የተያዘ አገር ሕዝብ ዐምፆ አዲስ የፖለቲካ ማኅበረሰብ ቢመሠርት የተገኘው ራስን የመግዛት ነጻነት አዎንታዊ የቡድን ነጻነት ነው።”
arbegna
ሬይመንድ ጊዩስ እንደሚያብራሩት እነዚህ የግለሰብ እና የቡድን ነጻነቶች የውጪ እና የውስጥ ተብለው ሊከፈሉ ይችላሉ። ለምሳሌ፦ ከቅኝ ገዢ የሚላቀቅ ሕዝብ የሚያገኘው ነጻነት ውጫዊ አዎንታዊ ነጻነት ነው። የዚህ ሕዝብ ውስጣዊ አዎንታዊ ነጻነት የሚለካው ደግሞ ከቅኝ ነጻ ከወጣ በኋላ በሚፈጥረው የማኅበራዊና ፖለቲካዊ ሥርዐት ነው። አምባገነንነትን ከመሠረተ የውስጣዊ አዎንታዊ ነጻነት ተቀዳጅቷል ለማለት አይቻልም። እነዚህ ሁለት የውጪ እና የውስጥ ነጻነቶች የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው። አንዱን ከአንዱ ማስበለጥ ያስቸግራል። በታሪክ እንደምንመለከተውም በበርካታ አገሮች ታጋዮች ውጫዊ አዎንታዊ ነጻነታቸውን በማግኘታቸው በመነሸጥ ውጫዊ ነጻነትን ይጠይቃሉ። ለዚያ ይታገላሉ፤ ይሞታሉ።

ይህ ምሳሌ አንደርድሮ ባለፈው ሳምንት ወደተከበረው የአርበኞች ቀን ይወስደናል። ብዙዎቻችን አያቶቻችን ለአገሪቱ ሉዓላዊነት ያደረጉትን ትግል እና ተጋድሎ በዚህ ቀን አማካኝነት በኩራት እንዘክራለን፤ በትግሉ ግለሰቦች እና ቡድኖች ያላቸውን ሚና በሚመለከት የሚደረጉ ሒሳብ አወራራጅ ጠንካራ ክርክሮች ያላቸውን ፋይዳ ሳናሳንስ። ይህ በኩራት የምናስበው የሉዓላዊነት ትግል እና ተጋድሎ የሚመለከተው የውጭ ሉዓላዊነትን (የውጭ አዎንታዊ ነጻነትን) ነው። የታሪክ ማስታወሻዎች እና ምልክቶች ከታሪክ ጋራ ንግግር እያደረግን ስለ አሁኑ ጊዜ/ እኛ የምንኖርባቸው እና የምንጋራቸው የፖለቲካ እና ማኅበራዊ ሥርዐቶች በጽሞና እንድናስብ ይረዱናል። የአርበኞችን ቀን ስንዘክር አያቶቻችን የጀመሩት የሉዓላዊነት ትግል የት ደርሷል የሚል ጥያቄ በማንሳት ነው። የውጪው ሉዓላዊነት መልስ አግኝቷል። የእርሱ ሌላ ገጽታ የኾነው የውስጥ ሉዓላዊነት ግን እስካሁን በጥያቄ ምልክት ውስጥ ይገኛል። በዚህ ጉዳይ ማምሰልሰል አንዳንዶቻችን ከምንሸሻቸው የእኩልነት፣ የነጻነት፣ እና የዴሞክራሲ የፖለቲካ ጥያቄዎች ጋር ፊት ለፊት ያፋጥጠናል። ለሉዓላዊነት ቀናዒ ነን ካልን፣ የአያቶቻችንን የሉዓላዊነት ትግል ከዘከርን፣ ከፊት ለፊታችን የተጋረጠውን ጥያቄ ማምለጥ የምንችል አንኾንም፤ አለበለዚያ ዝክሩ እና ኩራቱ የምላስ ብቻ ኾኖ ይቀራል።

The post [በዚህ ሳምንት የተማርናቸው ሦስት ነገሮች] 1ኛ) ቼዘኛውን አልሲሲ በጥንቃቄ እንያቸው * 2ኛ) ለመናገር ነጻነት ታጋዩ ዳኛቸው ጽዋችንን እናንሳ * 3ኛ) ውስጣዊ ሉዓላዊነታችም አርበኝነት ይሻል appeared first on Zehabesha Amharic.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>