Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

ሙስሊሙ እና ምርጫ

$
0
0

Muslim in ethiopia
ረቡእ ግንቦት 12/2007

ድምጻችን ይሰማ!
አላሁ አክበር!

ምርጫ የአንድ አገር ህልውና በህዝብ ውሳኔ እልባት የሚያገኝበት ሂደት ነው፡፡ በዚህም ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ የውጭ ግንኙነት ወዘተ አማራጮች ለህዝብ ቀርበው ሁሉም እንደየፍላጎቱ ድምፁን በመስጠትም ይሁን ድምፁን በመንፈግ ይሁንታውን ገልፆ የፈለገውን የሚመርጥበት፣ ያልፈለገውን የሚያስወግድበት ስርዓት ነው፡፡ አሁን በአገራችን በቅርቡ የሚደረገው የምርጫ ስርዓትም ቢሆን በዚሁ ፅንሰ ሀሳብ መሰረት የሚደረግ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ‹‹ህጉና ስርዓቱ በአግባቡ ስራ ላይ ይውላል›› የሚለው እንደተጠበቀው የመሆኑ ጉዳይ እንዳለ ሆኖ ማለት ነው፡፡

እኛ ሙስሊሞች ላለፉት 3 ዓመታት የመብት ጥያቄ አንስተን፣ ወኪሎቻችንን መርጠን በአግባቡ እና ስርዓቱን በተከተለ ህጋዊ መልኩ ስናቀርብ አሁን ስልጣን ያለው መንግስት ‹‹ለጥያቄያችን አግባብ የሆነ መልስ ይሰጠናል›› ከሚል እሳቤና ተስፋ በመነሳት መሆኑ እሙን ነው፡፡ ነገር ግን ያነሳናቸው መሰረታዊ ጥያቄዎች በአግባቡ መልስ ሳያገኙ፣ ከመረጥናቸው ወኪሎቻችን ከፊሎቹ እና ሌሎች በርካታ ወንድምና እህቶቻችን፣ እንዲሁም ኢማሞቻችን እና ዳዒዎቻችን ለእስር፣ ለእንግልት እና ለስደት ተዳርገውብናል፡፡ ምግባረ ሰናይ ድርጅቶች (NGO) ተዘግተዋል፡፡ ሚዲያዎች ከህትመት ውጪ ሆነውብናል፡፡ አሁንም ቢሆን በህዝበ ሙስሊሙ ላይ ጫና እየተደረገ ያለ መሆኑም እንደረፋድ ጸሐይ ግልጽ ነው፡፡ የፍትህ ስርዓቱም የተንዛዛና ተስፋ አስቆራጭ፣ እንዲሁም ተዓማኒነት የጎደለው መሆኑ በግልጽ ታይቷል፡፡ ይህ ምርጫ ተደረገም አልተደረገም ጥያቄዎቻችንን እና ብሶታችንን ሁሉ ምላሽ እስኪያገኙልን እና ወኪሎቻችን፣ እንዲሁም ሌሎች እስረኞቻችን እስኪፈቱልን ድረስ በፅናት ትግላችንን መቀጠል እንዳለብን ሁላችንም መገንዘብ ይኖርብናል፡፡

ምርጫውን አስመልክቶ የሚወሰነው ውሳኔ ፖለቲካዊ ውሳኔ እንደመሆኑ መጠን በአንዳንድ ወገኖች ‹‹የህዝበ ሙስሊሙ ጥያቄ ወደ ፖለቲካ ጥያቄነት ተቀይሯል›› የሚል የተሳሳተ አመለካከት እንዳለ ተረድተናል፡፡ አሁንም ሆነ ወደፊት ሊታወቅ የሚገባው ህዝበ ሙስሊሙ ያነሳቸው ጥያቄዎች ሃይማኖታዊ እና ሃይማኖታዊ መሆናቸው ብቻ ነው፡፡ ወደፊትም ይህን ይዘቱን ሳንለቅ ለመብታችን መከበር እንታገላለን! ከላይ ለመግለፅ እንደሞከርነው ፖለቲካ የአንድን አገር የኢኮኖሚ፣ ማህበራዊ፣ የውጭ ግንኙነት ወዘተ ፖሊሲዎች የሚነደፉበት እና የአገሪቱ መፃዒ ዕድል የሚወሰንበት ሰፊ ስርዓት ከመሆኑ አኳያ ህዝበ ሙስሊሙ ካነሳቸው ሃይማኖታዊ ጥያቄዎች ጋር ግንኙነት የለውም፡፡

ማንኛውም ሙስሊም ከላይ ያሉት የአንድ አገር ህልውና የሚረጋገጥባቸው ፅንሰ ሀሳቦች ለተካተቱበት የፖለቲካ ምርጫ ‹‹ይበጀኛል›› የሚለውን፣ ለአገራችን ህዝቦች፣ ብሄር ብሄረሰቦች፣ ለውጭ ግንኙነቶች፣ በአጠቃላይ ለህልውናው እና ለሙሉ መብቱ ይጠቅማል የሚለውን አማራጭ በማገናዘብ እና በመፈተሽ ድምፁን ላሻው ፓርቲ የመስጠት ሙሉ መብቱን መጠቀም እንዳለበት እናምናለን፡፡ ይህን መናገር መብቱን ማስታወስ እንጂ ‹‹ፖለቲካዊ አቋም መያዝ››፣ አልያም ‹‹የትግሉን ዓላማ ፖለቲካዊ ማድረግ›› ማለት እንዳልሆነ ግን ግንዛቤ ሊወሰድ ይገባል፡፡

በተነጻጻሪ መልኩ ከዚህ ምርጫ በፊትም ሆነ በኋላ ባለፉት 3 ዓመታት ኢትዮጵያዊው ሙስሊም ባካሄደው ትግል የታየው አስደማሚ ሰላማዊ የመብት ጥያቄ እንቅስቃሴያችን አሁንም መቀጠል ይኖርበታል፡፡ እምነታችን ረብሻን፣ ስርዓት አልበኝነትን እና የሌሎችን መብት መንካትን አይፈቅድልንምና በዚሁ መሰረት መብቶቻችን ሁሉ ተከብረው፣ የጀመርነው ሰላማዊ የመብት ጥያቄ ዳር እስኪደርስ እና በድል እስከምናጠናቅቅ ድረስ ትግላችንን በፅናት እንቀጥላለን!

ትግላችን እስከድል ደጃፎች በአላህ ፈቃድ ይቀጥላል!

The post ሙስሊሙ እና ምርጫ appeared first on Zehabesha Amharic.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>