ታሪክ ድርሳኑ ሲፈተሽ፣ ጦቢያ መንገደኛ ነው፡፡
ባዘመመ ጎጆው፣ በተውተፈተፈ ግርግዳ፤
የተንጠለጠለ ቅል የተሰቀለ አቁማዳ፤
ካለው፤
ጦቢያ መንገድ ይወዳል፣ ጦቢያ መንገድ ያመልካል፣ የተጫነ ጌኛ ነው፡፡
ህቅ.. እንቅ ቢል ከመንገድ፣ ቅሉ ጠብታ አቁማዳው ጥሪት ባይኖረው፤
ምንቸገረው!
ቼ! ባይ ጋላቢ ካገኝ፣ አበሽ መንገደኛ ነው፡፡
የጉዞው ነገረ ጥንት…ድርሰነ ወጉ እንደሚለው፤
የተጓዥነቱ ምስጢር አልፋ ኦሜጋው እንዲህ ነው፡፡
በለምለም የትሩፋት ምድር፣ እምኩሉ ባልተጓደለ፤
አምላክ ጦቢያን ፈጠረ፣ ፈጥሮም አበሽን አኖረ፤፡፡
ከአመታት ኋላ ተመልሶ፣ ፈጣሪ ጦቢያን ቢያየው፤
ከጎጆው አቁማዳ ሰቅሏል፤
ቅል አቁማዳ አንጠልጥሏል፡፡
ምን ለምለም ምድር ቢቸረው፣ ለጉዞ. . . ለመንገድ ቋምጦ፤
ገብስ በሶውን ቋጥሮ፣ ዳቦቆሎውን ቆርጦ፤
ድንገት ክፉ ቀን ቢመጣ፣
ዘልዝሎ ሰቅሏል ቋንጣ፡፡
የጦቢያን ጓዳ ጎድጓዳ፣ አስተዋለና ፈጣሪ፣
በአበሽ የጉዞ ናፍቆት፣
በጦቢያ የመንገድ መሻት፣ልቡ ስለተነካ፤
መስፈሪያ ከሌለው ጸጋው በቸርነቱ እየለካ፤
አገልግሉን ተሸክሞ፣ የሚንከራተትበት፤
ቅል አቁማዳውን፣ አንጠልጥሎ፤
ቋንጣና ዳቦ ቆሎ፣
ለማኘክ አቅሙ ዝሎ፣
ተዝለፍልፎ ሚወድቅበት፤
ላይደርስ የሚጓዝበት፤
ቁርጥ መድረሻ የሌለው፣
ለጦቢያ መንገድ ፈጠረለት፣ የልቡን መሻት ሰጠው፡፡
ይኸው ከዚያን ጀምሮ፣
ጊዜ ፈረስ የጫነለት፣ ነፍጥ እርካብ ያስረገጠው፤
ጭካኔ ሉጋም ያስጨበጠው፤
ይሰግር ይጋልበዋል፤
‹‹በርታ! እንደርሳለን!›› ይለዋል፡፡
ጦቢያም..በመከራ እየተጠቃ፣ ምኞት ከተስፋ አርግዞ፤
ቀልና አቁማዳ ይዞ፤
መድረሻ በሌለው መንገድ፣ ምስ በሌለው ጉዞ፤
ውስጠ ሞራውን ያነበበ፣ ጉልበተኛ ይጋልበዋል፤
ዶሮ ማታ ..ካድማስ መና… በርታ ደርሰናል ይለዋል፡፡
እና እኔንም…ጉድ እኮ ነው! እኔንም
በዚያ አይጨርሱት መንገድ ከወደቀው ዘርማንዘሬ፣ የመከራ ድርሳን ሊጥፈኝ፤
አንድ ብኩን ገጽ ሊያደርገኝ፤
ቢመኘኝ
ጊዜ ፈረስ የጫነለት፣ ነፍጥ እርካብ ያስረገጠው፤
ጭካኔ ሉጋም ያስጨበጠው፤
‹‹በርታ እንደርሳለን!›› አለኝ!
ለመንገዱ የቅል ውሀ፣ የአቁማዳው ጥሬ ሊያደርገኝ፡፡
በጀርባዬ ሊሸጋገር፣ በጀርባው ላያሻግረኝ፤
‹‹በርታ እንደርሳለን!›› አለኝ!
እኔ ግን. . . . .እኔ ግን
‹‹ምን ሲባል የብስል መሀል ጥሬ፤
የጅል ተስፈኛ፣ ህልም ቋጥሬ፤
ያነደደ የጣደ ይቀቅለኛል፤
መዳፉ የሰፋ ባለጌ፣ እንዳሻው ዘግኖ ይቅመኛል!
. . . ምን ሲባል!›› አልኩት፡፡
‹‹ምን ሲባል!
ቅዠት ቀስተደመና፣ ወንዙን ላልሻገረው፤
እነእማማና እነአባባ፣ በባዶ ቅል ባዶ አቁማዳ፣ የወደቁበትን መንገድ፣ ጉዞ ብዬ ልጀምረው!?
ምን ሲባል!
ዶሮ ማታ ንፉግ ድርጎ፤
ስንቅን እብብት ሸሽጎ!?
እምቢ! አቁማዳው ይከፈት፣ ወይድ ቅሉን አሳየኝ!
ያሻግረኝ እንደሁ ዠረቱን፤
ያወጣኝ እንደሁ ዳገቱን፤
ያነጋልኝ እንደሁ ሌቱን፤
ይከልለኝ እንደሁ መአቱን፤
አይኔ ብረቱ ካላየው፤
አንተን አምኜ ንክች እግሬን፣ ጉበኔን አልሻገርም፣ ጉዞ አልጀምርም እምብየው!››
አልኩት፡፡
እንሂድ ይለኛል ደግሞ!
የእነአባባን ጸሀይ አጨልሞ፤
የነእቴቴን ጨረቃ አስለምልሞ፡፡
ከዙሪያ ገባው አናክሶኝ፣ የገድ ባላዬን ሰብሮ፤
ከእንቁጣጣሽ አደዬ ላይ፣ የመስቀል ወፌን አባሮ፤
ጎጥ በማያሻግር ጎዳና፣ ዙሪያ ገባዬን አጥሮ፤
በርታ እንደርሳለን ይለኛል፣ በህልሙ ሾተላይ ሰክሮ፡፡
እንሂድ ይለኛል ደግሞ!
መከራ ድርሳን እንጂ፣ ስርየት መድረሻ የሌለው፤
ክታብ ድርሳኑ ሲፈተሸ፣ጦቢያ መንገደኛ ነው፡፡
እም ከመ እግዚኦ ቃሉ፣ ጦቢያ መንገደኛ ነው፡፡
እንሂድ ይለኛል ደግሞ!
ጎጥ አያሻግር እንቅፋት፣ እሾህ ጋሬጣ ቸምችሞ፤
እማጠሊት እንደቀመሰ ህጻን፣ የእናት ጡት እንደቀፈፈው፤
ምነው መንገድህ ሸከከኝ፤
መድረሻህ አልታይ አለኝ?
ቬርሙዳ አለው እንዴ ጎዳና?
አይሻገሩት ፈተና፤
አይሸከሙት ጫና?
መቼም ልደትና ሞታችንን፣ ከባድማ መንገድ ካሰረው፤
የእነአባባስ መንገድ ይሁን፣ አይታደል ገድ አይኑረው፤
ምነው. . .
የማለደ ያጎበደደ፣
የሰነቀ የታጠቀ፤
የፎከረ የነቀነቀ፤
የቀደሰ የመነኮሰ፤
አንዱም አይሻገረው?
ያ አያቴ ውጅግራ የወዘወዘ፤
አድዋ ታቦት ያነገሰ፤
ማይጨው የመነኮሰ፤
በጦር ሜዳ፣ ከንጉስ ባለሟል ቀድሞ፣ በጀግነትም በጅልነትም፣ እያቅራራ እየፎከረ፤
ህይወቱን እየገበረ፤
በሰላም ቀን፣ አመት ሙሉ አርሶ አበራይቶ፤
አርብቶና አስብቶ፤
ለምስለኔ እየገበረ፤
ከመስዋእትነቱ ባድማ ቀረ እንጂ፣ መች ለደሙ ፍሬ አደለው፣ መች ድልድዩን ተሸገረ!?
እማማና አባባስ ቢሆኑ!
በቀኝ አውለኝ ሀጢያት ሆኖ፣ አጣብቷቸው ግራ ከተጋባ ግራ ጥንውት፤
አስራ ሰባት አመት እንግልት፤
ምን መዝሙር ቢያቀነቅኑ፤ ምን ክንድ ቢወነጭፉ፤
ምን ደም መስለው፣ ደም ለብሰው፣ ደም ሆነው ቢተሙ፤
የቤተ ጸሎታቸውን ጉልላት፣ መስቀልና ጨረቃ፤ በማጭድና መዶሻ ተክተው፤
ባእድ ጣኦት አንግሰው፤
በአንድ ጎረምሳ እድሜ፣ አገር ሙሉ ወጣት ሰውተው፤
መች ለትሩፋቱ በቁ፣ መች ቆሌው ታረቃቸው፤
ስጋቸውን ለአቁማዳው ጥሬ፣ ደማቸውን ለቅሉ ውሀ አድርጎ አይደል ያስቀራቸው!
መች ተሻገሩት ዥረቱን!
መች ረከሰ ቁጣው! መች አሳለፉት መአቱን?
እንሂድ ይለኛል ደግሞ!
የአድማሴን ጸሀይ ሰርቆ፣ አለሜን በጨረቃው አጠይሞ›
ከዙሪያ ገባው አናክሶኝ፣የገድ ባላዬን ሰብሮ›
ከእንቁጣጣሽ አደዬ ላይ፣ የመስቀል ወፌን አባሮ፤
ወንዝ በማያሻግር ጎዳና፣ ዙሪያ ገባዬን አጥሮ፤
በርታ እንደርሳለን ይለኛል፣ በህልሙ ሾተላይ ሰክሮ፡፡
እንሂድ ይለኛል ደግሞ!
መከራ ድርሳን እንጂ፣ ስርየት መድረሻ የሌለው፤
ክታብ ድርሳኑ ሲፈተሸ፣ ጦቢያ መንገደኛ ነው፡፡
ጊዜ ፈረስ የጫነለት፣ ነፍጥ እርካብ ያስረገጠው፤
ጭካኔ ሉጋም ያስጨበጠው፤
ይሰግር ይጋልበዋል
‹‹በርታ እንደርሳለን!›› ይለዋል
እና እኔንም
ወፌ ቆች፣ ዶሮ ማታ. . . ‹‹በርታ እንደርሳለን›› አለኝ፤
ለመንገዱ የቅል ውሀ፣ የአቁማዳው ጥሬ ሊያደርገኝ፡፡
በጀርባዬ ሊሸጋገር፣ በጀርባው ላያሻግረኝ፡፡
‹‹ይምር ይምር አትኪት›› ብዬ፣ ገድ ያሰርኩባትን ጸሀይ፤
ምኑ እንዳደረጋት እያየሁ፣ ምኔ መሆኗን ሳያይ፤
የአርባ ቀን እጣውን ንግር፤
ኩፍ ያለ ሊጤን ደፍቶ፣ የእሱን አፍለኛ ሊጋግር፤
በየወንዙና ጎጡ፣ እልፍ ጨረቃ አኑሮ፤
ለገዴ ምልክት ያልኳትን፣ ጸሀዬን ከአድማስ ሰውሮ፤
ጉዞው እሩቅቅቅ ነው ይለኛል፣ በህልሙ ሾተላይ ሰክሮ፡፡
እኔ ግን . . .እኔ ግን . .
‹‹ጀግንነትም ጅልነትም በቃኝ፣ መንገድ ጦስ ጥንቡሳሴን፤
ከጎጤ ካሰርከው ከይሲ፣ ያኖርክልኝን ምሴን፤
ጸሀዬን ካድማስ መልሰህ፤
ካላሳየኸኝ ገልጠህ፤
ምን ሲባል! ምን ደዌ ቢጸናብኝ፣ ድፍን ቅል ተስፋ አዝዬ፤
በነደፈ
በለከፈ
የተቀመመልኝን ምስ፣ እጠጣለሁ ይሁን ብዬ?
ምን ሲባል!
ነዶው አውድማ ተጥሎ፣ ተወቅቶ ካልተበራየ፤
ሽቅብ ለንፋስ ተሰጥቶ፣ ምርትና ግርዱ ካልየ፤
ምን ሲባል. . ለጫነ ለቀረቀበ፤
ቼ! ላለ ለኮረኮረ፤
ሆ! ብዬ እተማለሁ፤
ለባለ ነፍጥ እጋለባለሁ¬¬¬?›› አልኩት
ምን ሲባል!
ቅዠት ቀስተደመና፣ ወንዙን ላልሻገረው፤
እነእማማና እነአባባ፣ በባዶ ቅል ባዶ አቁማዳ፣ የወደቁበትን መንገድ ጉዞ ብዬ ልጀምረው!?
ዶሮ ማታ ንፉግ ድርጎ፣ ‹‹በርታ እንደርሳለን›› አትበለኝ፤
ልስማህ ደፍረህ ንገረኝ፤
ስንደርስ ከዚያ ምናለህ፣ ለኔስ ከዚያ ምን አለኝ¬?
ይርቃል ቤተመንግስቱ፤
ከድሀው ከእኔ አይነቱ?
በንጉስ ነው፣ በፓርላማ፣ በነፍጥ ነው በወታደር፤
አገር የሚተዳደር?
ግቤ ካልከው ከመድረሻችን፣ ዴሞክራሲ ይታወቃል?
እንዴት ነው ነጻነታችን. . . . . ?
ካላወቅኩት፣ ካልነገርከኝ፤
ምን ብዬ ምን በወጣኝ፡፡
መቼም አንተ እጣህ ነውና፣ ለነፍጥ ለመንገድ የፈጠረህ፤
ቢያሻህ ጽላትክን ተሸክመህ፤
ጽዋህን በጀርባ አዝለህ፤
ያማተበ፣ የተሳለመ. . . ጸበልህን የቀመሰ ካገኘህ፤
ጨርቅ ያድርግልህ! ሂድ ወንድም አለም፤
እኔ ይቅርብኝ ግዴለም›› አልኩት፡፡
ከማያውቁት መልአክ፣ የሚያውቁት ሴጣን እንዲሉ፤
ሞራ ለሞራ ካልተናበብን፣ ልብህን ካላሳየኸኝ፤
የለመድኩት ያስለመድከኝ፤
የእጄ የደጄ፣ ምን አለኝ!?
ሲየሻው የሚቀቅለኝ፤
ሲያሻው የሚጋግረኝ፤
ሲያሻው የሚያደራጀኝ፤
ሲያሻው የሚበትነኝ፤
ሲያሻው የሚያሰልፈኝ፤
ሲያሻው የሚቆልፈኝ፤
የለመድኩት ያስለመድከኝ፤
የእጄ መከራ ምን አለኝ!?¬
እንሂድ ይለኛል ደግሞ!
The post እንሂድ ይለኛል ደግሞ!! – (ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ) appeared first on Zehabesha Amharic.