Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

‹‹የጥላሁን ገሠሠ ሚስትነት ከሕግ የበላይ አያደርግም.. ወ/ሮ ሮማንን በሕግ እፋረዳታለሁ!›

$
0
0

በቅርቡ በዘከርያ መሀመድ ተጽፎ ለንባብ የበቃውን ‹ጥላሁን ገሠሠ የህይወቱ ታሪክና ሚስጥር› የሚለውን መጽሐፍ ተከትሎ የጥላሁን ገሠሠ ባለቤት ወ/ሮ ሮማን በዙ ‹ከመጽሐፉ መታተም ጀርባ ሌላ ታሪክ አለ› በሚል በቁምነገር መጽሔት ቅጽ 14 ቁጥር 203 አስተያየቷን ሰጥታ ነበር፡፡ በቃለምልልሱ ላይ ስማቸው ከተጠቀሱ ሰዎች መካከል የአቶ ፈይሳ ልጅ የሆነው ሳምሶን ፈይሳ ‹ወ/ሮ ሮማን ስሜን ስላጠፋች በህግ እፋረዳታለሁ› ይላል፡፡ ሳምሶን የሰጠው ምላሽ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡
Tilahun Legend
ቁምነገር፡- በቅርቡ ለህትመት በበቃው አዲሱ የጥላሁን ገሠሠ የሕይወት ታሪክ መጽሐፍ ውስጥ የአንተ ሚና ምንድን ነው?

ሳምሶን፡ በአባታችን በአቶ ፈይሣ ኃይሌ ሐሰና ከ1934 ጀምሮ የተጻፈ የቤተሰብ ታሪክ ማስታወሻ አለ፡ ፡ ያን ማስታወሻ መነሻ በማድረግ የጥላሁን የሕይወት ታሪክ እንዲጻፍ ቤተሰቤን ወክዬ ባለሙያ ፍለጋ የተንቀሳቀስኩት እኔ ነኝ፡፡ ለዚህ ጉዳይ ጋዜጠኛ ሲሳይ ገብረጻድቅን አነጋገርኩት፡፡ በእርሱ አማካይነት ከዘከሪያ ጋር ተዋወቅሁና የቤተሰብ ታሪክ ማስታወሻዎቹን፣ ተዛማጅ ሰነዶችን እና የጥላሁን የሕጻንነት ፎቶዎችን ጨምሮ የቤተሰብ ፎቶግራፎችን አሳየኋቸው፡፡ ዘከሪያ ማስታወሻዎቹን ጊዜ ወስዶ ማየት እንደሚያስፈልግ በመግለጽ ልሰጠው እችል እንደሆን ጠየቀኝ፡፡ ሰጠሁት፡ ፡ በዚሁ የመጽሐፉ ሥራ ሂደት ተጀመረ፡፡

ቁምነገር፡- የመጽሐፉ ዝግጅት ሥራ ከተጀመረ በኋላ የአንተ ሚና ምን ነበር?
ሳምሶን፡ ዘከሪያ ሥራውን ከጀመረው በኋላ የእኔ ሚና ከጥላሁን ጋር በተያያዘ ያሉኝን የግል ትውስታዎች ማካፈል፣ ለሚያቀርብልኝ ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት እና መረጃ ሊሰጡት የሚችሉ ሰዎችን መጠቆም የመሳሰለ ነበር፡፡

ቁምነገር፡- ከወ/ሮ ሮማን ጋር ከመቼ ጀምራችሁ ነው የምትተዋወቁት? ቅርርባችሁስ ምን ያህል ነበር?

ሳምሶን፡ ከወ/ሮ ሮማን ጋር የተዋወቅነው ከአሜሪካ መጥታ ጥላሁን ቤት ከገባች በኋላ ነው፡ ፡ ቅርርባችሁስ ላልከው፣ የተለየ ቅርርብ የለንም፡ ፡ በእንግድነት ቤታቸው ስሄድ፣ በመልካም ሁኔታ ታስተናግደኛለች፡፡ በወቅቱ ጥላሁን ቤት የምሄደው ለጉዳይ ፈልጎ ሲጠራኝ ብቻ ነበር፡፡ ከወ/ሮ ሮማን ጋር የምንገናኘውም በእንደዚህ ያሉት አጋጣሚዎች ነው፡፡
ከዚያ ውጪ እኔ እና ወ/ሮ ሮማንን የሚያገናኝ ወይ የሚያቀራርበን ነገር አልነበረም፡፡

ቁምነገር፡- ወ/ሮ ሮማን ግን አንተ እነርሱ ቤት ትኖር እንደነበር ተናግራለች፡፡

ሳምሶን፡ እውነት አይደለም፡፡ ወ/ሮ ሮማን ከአሜሪካ መጥታ ጥላሁን ቤት ከመግባቷ በፊትም ሆነ ከዚያ በኋላ፣ ጥላሁን ለራሱ ጉዳይ ሲፈልገኝ፣ ወይም ቤት መጥቼ አብሬው እንድውል ሲጠራኝ ወይም ልጠይቀው ሄጄ ለአንድ፣ ለሁለት ወይም ግፋ ቢል ለሦስት ቀናት ያህል አድሬ ይሆናል፡፡ እንጂ፣ እኔ በየትኛውም ዘመን በቋሚነት ጥላሁን ቤት ኖሬ አላውቅም፡፡
ቁምነገር፡- ከዛሬ ሃያ ዓመት በፊት በአንተ እና በወ/ሮ ሮማን መካከል የተፈጠረ ግጭት ነበረ? ከነበረ የግጭታችሁ መንስዔ ምንድን ነው?
ሳምሶን፡ ከወ/ሮ ሮማን ጋር ምንም ዓይነት ግጭት የለንም፡፡

ቁምነገር፡- ወ/ሮ ሮማን ጥላሁን ቤት ጥሎ የወጣውና ከእኔ ጋር የተለያየው በሳምሶን ምክንያት ነው ትላለች፡፡ ለዚህ አንተ የምትሰጠው ምላሽ ምንድን ነው?
ሳምሶን፡ ጥላሁን በጋብቻም ሆነ ከጋብቻ ውጪ በአብሮ መኖር ጎጆ ከተጋራቸው ሴቶች ወ/ሮ ሮማን ሰባተኛ ወይም ስምንተኛዋ ነች፡፡ ከእርሷ በፊት ከአምስት ወይ ስድስት ቤቶች ሻንጣውን ይዞ መውጣቱ ይታወቃል፡ ፡ ወ/ሮ ሮማን ከአሜሪካ መጥታ አብራው መኖር ከጀመረች በኋላ ቤቱን ትቶ የወጣውም በራሱ ውሳኔ እንጂ፣ የ30 ዓመት ታናሹ በሆንኩት በእኔ ምክንያት አይደለም፤ ሊሆንም አይችልም፡፡ ወ/ሮ ሮማን ከምን ተነስታ ይህን ልትል እንደቻለች ለእኔ ግልጽ አይደለም፡፡

ቁምነገር፡- ወ/ሮ ሮማን ከጥላሁን ጋር በተለያዩበት ወቅት አካባቢ ልብሶችና ወርቆች ጠፍተውባት እንደነበረ፣ ከዚያ ጋር በተያያዘም አንተ ፖሊስ ጣቢያ ታስረህ እንደነበርና፣ ፖሊሶች ደብረ ብርሃን ይዛ ሄዳ ‹‹ሰባት ሻንጣ ልብስና ወርቆቼ ሳይቀር ተገኙ›› ብላለች፡፡ ለዚህ ያንተ ምላሽ ምንድን ነው?

ሳምሶን፡ እቃ ጠፍቶኛል ብላ እኔን እና የጥላሁንን ልጅ ዳንኤልን በተጠርጣሪነት ፖሊስ ጣቢያ አሳስራን ነበር፡፡ በተጠርጣሪነት ተይዞ መመርመርም ሆነ ፖሊስ ጣቢያ ታስሮ መቆየት ጥፋተኝነትን አያሳይም፡፡ በፍርድ ቤት ክስ አልተመሰረተብንም፤ አልተመሰከረብንም፤ በጥፋተኛነትም አልተፈረደብንም፡፡ ሐቁ ይህ ሆኖ ሳለ፣ ወ/ሮ ሮማን በቁም ነገር መጽሔት (14ኛ ዓመት፣ ቅፅ 14፣ ቁጥር 203) የሥርቆት ወንጀል እንደፈፀምኩ አድርጋ ተናግራለች፡፡ ይህ ብቻም ሳይሆን፣ ሳምሶን ‹‹ጥላሁንን ገና በሕይወት እያለ ሊሸጠው ሊለውጠው የፈለገ ሰው ነው››፣ ሳምሶን ማለት ‹‹ጥላሁንን ትብትብ አድርጎ የተጫወተበት ሰው ነው››፣ ‹‹ፖሊሶች ከሳምሶን ኪስ ውስጥ ‹ጥላሁንን እንዲህ አድርግልኝ … ምናምን› የሚል የጥንቆላ ነገሮችን አግኝተዋል›› በማለት በአደባባይ ስሜን አጥፍታለች፡፡ የጥላሁን ገሠሠ ሚስትነት ከሕግ የበላይ አያደርግም፡፡ ስለዚህም፣ በአደባባይ ስሜን በማጥፋቷ ወ/ሮ ሮማን በዙን በሕግ እፋረዳታለሁ፡፡

ቁምነገር፡- በዚሁ ምክንያት ከዚያ ጊዜ በኋላ ከጥላሁን ጋር ተነጋግራችሁ እንደማታውቁ፣ ሌላ ቀርቶ በለቅሶው ላይ እንኳ እንዳልተገኘህ ወ/ሮ ሮማን ተናግራለች፡፡ እውነት ከጥላሁን ጋር ተጣልታችሁ ነበር? በለቅሶውስ ላይ አልተገኘህም?

ሳምሶን፡ ወ/ሮ ሮማን፣ ጥላሁን ገሠሠ ታላቅ ወንድሜ መሆኑን የዘነጋችው ይመስለኛል፡፡ እርግጥ ነው እኔም፣ በወንድሜ ለቅሶ ላይ መገኘቴን ታውቅልኝ ዘንድ ወ/ሮ ሮማንን እጅ ነስቼ መውጣት እንደነበረብኝ ዘንግቼ ይሆናል፡፡

ቁምነገር፡- ወ/ሮ ሮማን ጥላሁን ገሠሠ፡ የሕይወቱ ታሪክ እና ምሥጢር የተሰኘው አዲስ መጽሐፍ ለጥቅም እና የእኔን ስም ለማጥፋት ተብሎ ነው የተጻፈው፤ ሳምሶን ከደራሲው ጋር በጥቅም ተደራድሮ ነው ያስጻፈው፣ ከመጽሐፉም ጀርባ ሳምሶን አለ የሚል ስሞታ አቅርባለች፡፡ በዚህ ላይ የአንተ ምላሽ ምንድን ነው?
tilahun Gesese
ሳምሶን፡ መጽሐፉ ለጥቅም እና የሰው ስም በማጥፋት መናኛ ዓላማ እንዳልተጻፈ ያነበበ እና የሚያነብ ሁሉ በቀላሉ የሚረዳውና አፍ አውጥቶ የሚመሰክረው ነው፡፡ እኔም ሆንኩ ሌላ የቤተሰቤ አባል ከደራሲው ጋር ምንም ዓይነት የጥቅም ድርድር አላደረግንም፡፡ ያደረግነው ነገር ቢኖር፣ አባታችን ከ1934 ዓ.ም. ጀምሮ ጽፈው ያኖሩትን የቤተሰብ ታሪክ ማስታወሻ መነሻ በማድረግ የጥላሁንን የሕይወት ታሪክ በራሱ ጥረት አዳብሮ እንዲጽፍ ሙሉ ፈቃደኝነታችንን የሚገልጽ ሰነድ ፈርመን ሰጥተነዋል፡፡ ያም ሰነድ ዘከሪያ ጋ ይገኛል፡፡ እኔም ሆንኩኝ ወንድም እና እህቶቼ ጥላሁንን በተመለከተ በዉሱን ደረጃ የየግል ትውስታዎቻችንን ከማካፈልና በሥራው ላይ ሳለ ደራሲውን ከማበረታታት ባለፈ፣ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ‹‹ይህን ጻፍ፣ ይህን አትጻፍ›› ያልንበት አንድም አጋጣሚ የለም፡፡ ደራሲው በዚህ መጽሐፍ ላይ ስድስት ዓመት ገደማ ለፍቶበታል፡ ፡ የልፋቱ ውጤትም እጅግ ያማረ መሆኑን ብዙዎች በአደባባይ እየመሰከሩ ነው፡፡ በመጽሐፉ ውስጥ ደራሲው ወ/ሮ ሮማንን በተመለከተ ከእኔ የወሰደው አንድም መረጃ የለም፡፡ ከ2003 በኋላ ከደራሲው ጋር በስልክ ካልሆነ በቀር በአካል የተገናኘንባቸው ጊዜያት በጣም ውሱን ናቸው፡፡ በእነዚህም ጊዜያት “መጽሐፉ እንዴት እየሄደልህ ነው? አይዞህ በርታ” ከማለት በቀር አንድም ጊዜ በመጽሐፉ ይዘት ዙርያ አላወራንም፡፡ ስለዚህ፣ የወ/ሮ ሮማን ስሞታ በጭፍን የተሰነዘረና መሠረተ ቢስ እንደሆነ አረጋግጥልሃለሁ፡፡ ይህን ደግሞ ማንም መጽሐፉን ያነበበና ወደፊትም የሚያነብ ሰው እንደሚመሰክር ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

ቁምነገር፡- ወላጅ አባትህ አቶ ፈይሣ ኃይሌ የጻፉትን የቤተሰብ ታሪክ ማስታወሻ ለደራሲያን ማኅበር ለምን አልሰጠህም?

ሳምሶን፡ ይህን ያላደረግሁት የጥላሁን የሕይወት ታሪክ ከማንኛውም ዓይነት ተፅዕኖ ነፃ፣ ሚዛናዊና ገለልተኛ በሆነ ባለሙያ በጥንቃቄ መሠራት እንዳለበት ስላመንኩኝ ነው፡፡ እንዲህ ስል የደራሲያን ማኅበርን ገለልተኛነት ጥያቄ ውስጥ ለመክተት አይደለም፡፡ ነገር ግን፣ በደራሲያን ማኅበር የሚጻፈው የጥላሁን የሕይወት ታሪክ የአንድ አካል ተፅዕኖ ሊያርፍበት ይችላል የሚል ሥጋት ነበረኝ፡፡ ጥላሁን ገሠሠ ከተለያዩ ትዳሮችና የአብሮ መኖር ግንኙነቶች ሰፊ ቤተሰብ ያፈራ ሰው እንደመሆኑ፣ የሕይወት ታሪኩ ከአንዱ ወይም ከሌላኛው ቤተሰብም ሆነ ከማንኛውም ተፅዕኖ ነጻ በሆነ ፕሮፌሽናል መንገድ ቢሠራ የጥላሁን አፍቃሪ ለሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥሩ ሥራ ይቀርብለታል ከሚል እምነትም ነው፡፡ በአጋጣሚ ከዘከሪያ ጋር ተዋወቅን እና ሥራውን እርሱ ጀመረው፡፡ ላለፉት ስድስት ዓመታት በከፍተኛ የኃላፊነት ስሜት፣ ሥራውን በፍቅር ሲያከናውን ከርሞ ‹‹ለሌሎች ፀሐፍያን አዲስ ጎዳና የቀደደ›› ተብሎ በምሁራን የተሞገሰ አስገራሚ እና መሳጭ መጽሐፍ ጽፎ ለኢትዮጵያ ሕዝብ አቀረበ፡፡ ማስታወሻዎቹን ለደራሲያን ማኅበር ሰጥቼ ቢሆን ኖሮ፣ የጥላሁን ታሪክ እንዲህ ተተንትኖ ይቀርብ ነበር ብዬ አላምንም፡፡ ስለዚህም፣ ባለመስጠቴ አልቆጭም፡፡ የሚገርመው፣ ዘከሪያ አራት ምዕራፍ ጽፎ እንደጨረሰ፣ ‹‹እውነተኛውን የጥላሁን ገሠሠ የትውልድ፣ የልጅነትና የቤተሰብ ታሪክ ከፎቶግራፍ ማስረጃዎች ጋር ልስጣችሁ›› ብሏቸው ነበረ፡፡ ‹‹አራቱ ምዕራፎች፣ የአቶ ፈይሣ ኃይሌን ማሥታወሻዎች መነሻ በማድረግ በእኔ የተጻፉ መሆኑን ጠቅሳችሁ ተጠቀሙበት›› ሲላቸው እምቢ አሉ፡፡

ቁምነገር፡- ወ/ሮ ሮማን በዙ ጥላሁን ደብረ ብርሃን ወስዶ ከአቶ ፈይሣ ጋር እንዳስተዋወቃት ተናግራለች፡፡… እውነት ነው?
ወ/ሮ ሮማን እና አቶ ፈይሣ ይተዋወቁ ነበር?

Roman Bezu

Roman Bezu


ሳምሶን፡ በቁም ነገር መጽሔት (14ኛ ዓመት፣ ቅፅ 14፣ ቁጥር 203) ላይ ወ/ሮ ሮማን በዙ ከተናገረቻቸው ንግግሮች ውስጥ እጅግ በጣም የሚያስገርሙ ሦስት ተከታታይ ዓረፍተ ነገሮችን ቃል በቃል እንዳነብባቸው ፍቀድልኝ፡ … ‹‹አቶ ፈይሣን አውቃቸዋለሁ፡፡ ደብረ ብርሃን ወስዶ ጥላሁን አስተዋውቆኛል፡፡ የእሳቸው ልጅ ሳምሶን ደግሞ እኛ ቤት ይኖር ነበር፤›› ብላለች፡፡ እነዚህ ሦስቱም ዓረፍተ ነገሮች ውሸቶች ናቸው፡፡ ወ/ሮ ሮማን አባቴን (አቶ ፈይሣን) አታውቃቸውም፡፡ ጥላሁንም ደብረ ብርሃን ወስዶ ከአባቴ ጋር አላስተዋወቃትም፡፡ እኔ ሳምሶን ደግሞ እነርሱ ቤት አልኖርኩም፡፡ … እነዚሁ የሐሰት ንግግሮች በቀጣዩ ገጽ ላይም ይደገማሉ፡፡ ‹‹[አቶ ፈይሣን] አንድ ሁለት ጊዜ ነው ደብረ ብርሃን ሄጄ ያገኘኋቸው፡፡ … በጣም በቅርብ የማውቀው ልጃቸው ሳምሶንን ነው፡፡ እሱ እኛ ቤት ነው ይኖር የነበረው፤›› ብላለች፡፡ ወ/ሮ ሮማን ከጥላሁን ጋር ለመጀመርያ ጊዜ ደብረ ብርሃን የመጣችው፣ ሄሎም የምትባል እህታችን ባረፈችበት ወቅት፣ በሚያዝያ 1989 ነው፡፡ አባቴ አቶ ፈይሣ በዚያን ጊዜ በሕይወት የሉም፡፡ እርሳቸው በሐምሌ 1985 ዓ.ም. ነው ያረፉት፡፡ ወ/ሮ ሮማን፣ ይህን መጽሐፍ ጭቃ ለመቀባት ቸኩላ አደባባይ ከመውጣቷ በፊት መጽሐፉን ከመጀመርያ እስከ መጨረሻው በእርጋታ አንብባው በነበረ፣ እንዲህ ያለ ዓይን ያወጣ የሐሰት ንግግር በአደባባይ ከመናገር ትድን ነበር፡፡ ጨርሳ ስላላነበበችው ነው’ንጂ መጽሐፉ ውስጥ አባቴ ያረፉበት ቀን በግልጽ ተጽፏል፡፡ … ወ/ሮ ሮማን በቃለ ምልልሱ ላይ ‹‹አንድን መጽሐፍ ሽፋኑን ዓይተህ ግምት አትስጥ›› የሚል ጥቅስ ጠቅሳለች፡፡ መልሳ ግን እዚያው ቃለ ምልልስ ላይ፣ “‹በመጽሐፉ ላይ የሳምሶን እጅ እንዳለ ሳውቅ፣ መጽሐፉ በምን ደረጃ እንደሚጻፍ ይገባኛል፡፡ እያንዳንዱን ገጽ እንኳ ማንበብ አይጠበቅብኝም፤›› አለች፡፡ ይህ ‹አንድን መጽሐፍ ሽፋኑን ብቻ ዓይቶ ግምት ከመስጠት› በምን ይለያል? … በመጽሐፉ ውስጥ የሳምሶን እጅ እንዳለ እና እንደሌለ ለማወቅም’ኮ መጽሐፉን ገጽ በገጽ ማንበብ ነበር የሚጠቅማት፡፡ ቃለ ምልልሱን ከመስጠቷ በፊት መጽሐፉን ብታነብ ኖሮ፣ ደራሲው ከአባቴ ማስታወሻዎች በተጨማሪ የጥላሁን የረጅም ዘመን ወዳጆችን፣ የወሊሶ የትምህርት ቤት ጓደኞችን፣ በሶየማ የጥላሁን የትውልድ መንደር የሚገኙ የቤተሰብ አባላትን እና በተለያዩ ዘመናት ከጥላሁን ጋር የጓደኝነት ወይም የሥራ ቅርበት ከነበራቸው ሰዎች በቃለ መጠይቅ መረጃ በመሰብሰብ፣ እንዲሁም ከ1950 ገደማ ጀምሮ በሚዲያ የወጡ ዘገባዎችን እና መጻሕፍትን በማገላበጥ በከፍተኛ ጥረትና ድካም የሠራው መሆኑን መረዳት ትችል ነበር፡፡ ይህን በቅን ልቡና መመልከት ብትችል ኖሮ ደግሞ በመጽሐፉ ከልብ ልትደሰትና ደራሲውንም ልታመሰግነው ነበር የሚገባት፡፡ ከዚያ በተቃራኒ መጽሐፉን ያነበቡትና ወደፊትም የሚያነቡት ሰዎች ይታዘቡኛል እንኳ ሳትል፣ መጽሐፉን ማጣጣል መሞከሯ በጣም የሚያሳዝን ነው፡፡

ቁምነገር፡- ወ/ሮ ሮማን በቤተሰብ ታሪክ ማስታወሻው ተዓማኒነትም ላይ ጥያቄ ታነሳለች፡፡ በዚህ ላይ አንተ ምን ትላለህ?

ሳምሶን፡ በቅን ልቡና የቀረበ ቢሆን ኖሮ፣ ይህ ጥያቄ በራሱ ምንም ችግር የለውም፡፡ ነገር ግን፣ ለእኔ እንደሚገባኝ፣ ወ/ሮ ሮማን የዚህን መጽሐፍ ለህትመት መብቃት ተከትላ ወደ መገናኛ ብዙኃን የወጣችው፣ በቀጥታ በመጽሐፉ ላይ አሉታዊ ዘመቻ ለመክፈት፣ መጽሐፉን ለማጣጣል ነው፡፡ በዚህ የአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ይህን መጽሐፍ ገዝተው ካነበቡ ብዙ ሰዎች ጋር ተገናኝቻለሁ፡፡ ከወጣት እስከ ጎልማሳ ስለ መጽሐፉ የሚያደንቅና የሚያሞግስ እንጂ፣ አንድም መጽሐፉን የሚተች የሚያጣጥል ሰው አልገጠመኝም፡፡ ሐያሲያንም መጽሐፉን በማድነቅ እየጻፉ ነው፡፡ እንዳውም አንድ ጋዜጠኛ በመጽሐፉ ዙርያ የጻፈውን በሳል ትንተና በዚሁ በቁም ነገር መጽሔት ላይ ነው ያነበብኩት፡፡ በአንፃሩ፣ ከማንም አስቀድማ ይህን መጽሐፍ ማድነቅ እና ደራሲውንም ማመስገን የሚጠበቅባት ወ/ሮ ሮማን፣ መጽሐፉን፣ ያውም ሙሉ በሙሉ ሳታነበው፣ [ብታነበው ኖሮ ‹‹አቶ ፈይሣን አውቃቸዋለሁ›› ባላለች] በአደባባይ ስታጣጥለው መስማት በጣም ያስገርማል፡ ፡ ያላነበበውን መጽሐፍ በአደባባይ የሚያጣጥል ሰው፣ ይህን ያደረገው ከቅን ልቡና ነው ለማለት ይከብደኛል፡ ፡ ስለዚህም፣ ወ/ሮ ሮማን አባቴ ከ1934 ጀምሮ ጽፈው ባኖሯቸው የቤተሰብ ታሪክ ማስታወሻዎች ላይ የተዓማኒነት ጥያቄ ለማንሳት የሞራል ብቃት አላት ብዬ አላምንም፡፡ ይህን ካልኩ በኋላ ግን፣ በወላጅ አባታችን የተጻፉትን የቤተሰብ ታሪክ ማስታወሻዎች እና ሌሎችም በርካታ ለሕዝብ የሚጠቅሙ ሰነዶች፣ ለጥናት እና ምርምር ይውሉ ዘንድ ለተገቢው የጥናትና ምርምር ተቋም መስጠት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ጉዳዩ የሚመለከታቸውን አካላት እንደምናነጋግር በዚሁ አጋጣሚ ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡

ቁምነገር፡- በመጨረሻም ማስተላለፍ የምትፈልገው መልዕክት፣ ወይም በአቶ ፈይሣ ማስታወሻዎች ላይ ተመስርቶ ስለተጻፈው የጥላሁን ገሠሠ የሕይወት ታሪክ መጽሐፍ “ሰዎች ሊያውቁት ይገባል” የምትለው ነገር አለ?

ሳምሶን፡ ይህን ዕድል ስለሰጠኸኝ አመሰግናለሁ፡፡ እንደ ጥላሁን ቤተሰብ ሆኜ፣ ሕዝብ እንዲያውቀው የምፈልገው አንድ ነገር ቢኖር፣ ‹ጥላሁን ገሠሠ የሕይወቱ ታሪክና ምሥጢር› በሚል ርዕስ ታትሞ የወጣው መጽሐፍ ከመሠረቱ ጀምሮ በፍፁም ቅንነት፣ በእውነት፣ በፍቅር እና በከፍተኛ ትጋት ነው የተጻፈው፡፡ የመጽሐፉን መሠረት በቃላት የተከሉት ወላጅ አባቴ አቶ ፈይሣ ኃይሌ ሐሰና ሲኾኑ፣ በዚህ መሠረት ላይ ዘከሪያ ለጥላሁን ገሠሠ ድንቅ የሆነ ሐውልት በውብ ቃላት አዋቅሮ አንጾለታል፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ ለመጽሐፉ ግብዓት የሚሆን መረጃ ለደራሲው በመሥጠት የተባበሩትን የጥላሁን ወዳጆች፣ የሥራ ባልደረቦች እና የቤተሰብ አባላት በመላው የአቶ ፈይሣ ልጆች ስም ከልቤ ለማመስገን እወዳለሁ፡፡ እግዚአብሔር ይስጥልኝ፡፡

ቁምነገር፡- አመሰግናለሁ፡

ምንጭ – ቁምነገር መጽሔት

The post ‹‹የጥላሁን ገሠሠ ሚስትነት ከሕግ የበላይ አያደርግም.. ወ/ሮ ሮማንን በሕግ እፋረዳታለሁ!› appeared first on Zehabesha Amharic.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>