በዘሀበሻ ገጽ ላይ የተነበበ አንድ ጽሁፍ ለወያኔ አገዛዝ መራዘም የሕዝብ ድክመት እንደሆነ በመግለጽ ተራበ ተጠማ ተጨቆነ ወዘተ ተብሎ ሊጮኸለት እንደማይገባ ገልጾ ለሕዝብ ሲሉ መስዋዕትነት የከፈሉም ሆነ እየከፈሉ ያሉ ለማን ብለው ነው በማለት ይጠይቅና መስዋዕት ሊሆኑለት የማይገባ ሕዝብ ነው ወደሚል ድምዳሜ ያመራል፡፡
የጽሁፉ መነሻ ምክንያትም ሆነ መድረሻ ድምዳሜ ትክክል ሆኖ ስላልተሰማኝና ራስን ከሕዝብ አካልነት ለይቶ ሕዝቡ እያሉ መውቀስና ተጠያቂ ማድረግ በተለያየ ግዜ ከተለያየ ሰዎች የሚሰማ በመሆኑ ሀሳብ የምናቀርበው ከምር ለውጥ ከመሻት ከሆነ ጉዳዩን እንነጋርበት ዘንድ የበኩሌን ለማለት ፈለግሁ፡፡ በርግጥ ሕዝቡ ተወቃሽ ተከሳሽ ነው? የዚህ አይነት ሀሳብ ባለቤቶችስ እነርሱ የሚወቅሱት ሕዝብ አካል አይደሉም? በተለመደው ተራ የመዘላለፍ ስሜት ሳይሆን ለመማርና ቁም ነገር ለማትረፍ እንነጋገር፡፡
በየትኛውም ዘመን በማናቸውም ሀገር በሰላማዊም መንገድም ይሁን በጦር ሕዝብ በአንድ ግዜ ተነስቶ ሥርዐት የቀየረበትና ከአገዛዝ የተላቀቀበት ታሪክ የለም፡፡ መነሻ ምክንያታቸው ምንም ይሁን ምን (ሥልጣን መፈለግ፡በጭቆና መማረር፤ለሕዝብ አለኝታ መሆን፤ለውጥ መሻት ወዘተ) ጥቂት ግንባር ቀደሞች ዓላማ አልመው፤ እቅድ አውጥተው፤ ስትራቲጂ ቀይሰው ትግል ይጀምራሉ ሕዝቡን ያስተባብራሉ፡፡ ይህም ሆኖ መላው ሕዝብ ተከታያቸውም ሆነ ደጋፊያቸው አይሆንም ሊሆንም አይችልም፡፡
የተሻለ ድጋፍ ለማግኘትና ትግልቸውን ለውጤት ለማብቃት ታጋዮቹ እቅድ ዝግጅታቸውም ሆነ የተግባር እንቅስቃሴያቸው የሀገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ የህብረተሰቡን ባህል፤ ታሪክና ስነ-ልቦና እንዲሁም የሚታገሉትን ኃይል ማንነትና ምንነት ብሎም ሥልጣኑን ለማስጠበቅ ሲል እስከምን ድረስ ሊሄድ እንደሚችል ወዘተ ያጤነ መሆን አለበት፡፡
በዚህ መልኩ የተደራጁና የሚያምናቸውና ተስፋ የሚጥልባቸው ፓርቲዎችም ሆነ ግንባር ቀደም ግለሰቦች በማጣቱ ተስፋ ያደረገባቸውም ብቅ ብለው የሚጠፉ፤ ሳያብቡ የሚቀጠፉ እየሆኑበት ተቸግሮ ያደርገው አጥቶ በሚኖርበት ወቅት የኢትዮጵያ ሕዝብ ሊወቀስ ሊከሰስ አይገባም፡፡ ሌላው ሌላው ቢቀር በ1997 ምርጫ የታየው የሕዝብ ትግል ምንግዜ ተረስቶ ነው ሕዝቡ መስዋዕትነት ሊከፍሉለት የማይገባ እስከመባል የሚደረሰው፡፡
ከራስ በላይ ማሰብ የተሳናቸው ለሥልጣን ጥማቸው እንጂ ለሕዝብ ስቃይ ቅድሚያ መስጠት አልሆንልህ ያላቸው ፖለቲከኞች የሚያብጡትን ፖለቲካ መልክ በማስያዝ፤ ወያኔ የሚያላግጥበትን ምርጫ የምር ምርጫ ለማድረግ የቆረጡ ጥቂት ምሁራን የጎሪጥ የሚተያዩ ፖለቲከኞችን አቀራርበው ሀራምባና ቆቦ የቆሙ ፓርቲዎችን አገናኝተው ቅንጅትን በመመስረት ባሳዩት እንቅስቃሴ ሕዝቡ አምነት አሳድሮ፤ የለውጥ ተስፋ ሰንቆ፤ ሴት ወንድ ወጣት አዛውንት ሳይል ያሳየው እንቅስቃሴ የሚዘነጋ አይመስለኝም፡፡
በሁሉም የሀገሪቱ ክፍል ከጠመንጃ እየተጋፋ ቅንጅትን ደግፎ ሰልፍ ወጣ፤የቅንጅትን የምርጫ ምልክት የእለት ተእለት የሰላምታ መለዋወጫው እስከ ማድረግ ደረሰ፤ድምጹን ሰጠ፤ድምጼ ይከበር ብሎ አደባባይ ወጥቶ በአረመኔ ጦረኞች ተፈጀ፤የቅንጅት አመራሮች ሲታሰሩ፤የመረጥናቸው ለፓርላማ እንጂ ለቃሊቲ አይደለም በማለት እስኪፈቱ ድረስ በቻለው መንገድና ዘዴ ከጠመንጃ ጋር እየታገለ ጮኸ፡፡ ትግሉ በሀገር ውስጥ ሳይወሰን በመላው አለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያንም ልዩነታቸውንና መቃቃራቸውን ወደ ጎን ብለው ጸኃይና ብርድ ሳይበግራቸው ሰልፍ እየወጡ አንድ ሆነው በአንድ ላይ ጮኹ ይፈቱ ብለው ጠየቁ፡፡
የተጮኸላቸው፤ መሪዎቻችን ተብለው የተሞገሱ የተደነቁት ሰዎች ግን እድሜ ለኢ/ር ኃይሉ ሻውል በተፈቱ ማግስት የእንቧይ ካብ ሆኑ፡፡ ሕዝቡ ግን በዚህም ተስፋ ሳይቆርጥ ተለያይተው በየመንገዳቸው የቀጠሉትን ዛሬም ለአለመበታተናችሁ ምን ዋስትና አለ እያለ እየጠየቀ ድጋፉን ቢቀንስም አይናችሁን አልይ ግን አላላም፡፡
እናም የኢትዮጵያ ሕዝብ ጽናት፤ተአማኒነት፤ብቃት ወዘተ ያለው እራሱን ቤተ መንግሥት ማየትን ሳይሆን የህዝብን የሥልጣን ባለቤትነትን ማረጋገጥን ቀዳሚ ዓላማው ያደረገ፤ ተባብሮና ተከባብሮ ወደ ድል የሚመራው አጣ እንጂ የለውጥ ፍላጎቱን፤ለሚፈልገው ለውጥም እስከ ሕይወት መስዋእትነት መክፈሉን በተግባር አሳይቷል፡፡
ሎሬት ጸጋየ ገብረ መድህን ከምርጫ 97 በፊት የካቲት 1/97 ለንባብ ከበቃችው ጦቢያ መጽሔት ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ ከተናገረው የሚከተለው ከላይ ለማሳየት የሞከርኩትን ሀሳቤን ይበልጥ የሚገልጽልኝ ይመስለኛል፡፡
{ የሕዝብን እውነት በልብ ሳይቋጥሩ ሕዝብ ግንባር ፊት መቆም እንደ ወያኔ ድፍረት ሕዝብን ማርከስ ነው፡፡ መተባበር ያቃተው ‹ኀብረትና ቅንጅት›ደግሞ ሕዝብን ሊያስተባብር አይችልም፡፡ አለንልህ የሚሉት ፖለቲከኞች ርስ በርሳቸው ሲጠላለፉ እያየ ሕዝቡ በመራራ ትዝብት ያስተውላቸዋል፡፡ አይቆስሉ ቁስለት ማለት የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁስለት ነው፡፡አይችሉ መቻል ማለትም የኢትዮጵያ ሕዝብ መቻል ነው፡፡ ‹በላይ እሳት በታች እሳት› እንደ ድፎ ዳቦ እየነደደ በፅናቱ ብቻ ሳይሆን ሕዝቡ በትእዝብቱም ቀድሞናል}
እንዲህ የተመሰከረለትን ሕዝብ ነው ዛሬ መስዋእት ሊከፍሉለት የማይገባ የተባለው፡፡ ነፍሱን ይማረውና ከርሱ ሞት በኋላ የተፈጸመውን የፖለቲካ መመሰቃቀል፤የፖለቲከኞች መጠላለፍና መከዳዳት የወያኔን መቶ በመቶ አሸናፊነት ቢያይ ጸጋዬ ምን ይል ነበር!
The post መሪ ያጣ ሕዝብ ምን ያድርግ – ይገረም አለሙ appeared first on Zehabesha Amharic.