ሰኔ 2007ዓ.ም.
በዚህ ጽሑፍ የ1 ለ5 አደረጃጀት ማለት ምን ማለት ነው?፣ የ1 ለ5 አደረጃጀት ዓላማ ምንድን ነው? ይህ አደረጃጀት አገዛዙ እንደሚለው ምንም ዓይነት ፖለቲካዊ ዓላማ የለውም ወይስ አለው?፣ አደረጃጀቱ ሕጋዊ አሠራር ነው ወይስ አይደለም?፣ ይህ አደረጃጀት ከሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ (በይነ ሕዝባዊ) መብቶች አንጻር የጋረጠው አደጋ አለ ወይስ የለም? የሚባሉ ነጥቦችን በዝርዝር ዕናያለን፡፡
ይህ አደረጃጀት መጀመሪያ ላይ ሥራ ላይ የዋለው ትግራይ ላይ ነበር፡፡ በእርግጥ ይሄንን ዓይነት አደረጃጀት ወይም ጥርነፋ ወያኔ በረሀ እያለ ጀምሮ ሲጠቀምበት የነበረ አሠራሩ ነው፡፡ ወያኔ የህልውናየ መሠረት የሚለው የትግራይ ሕዝብ በሌሎች ተቃዋሚ የፖለቲካ ኃይሎች እንዳይወሰድበት ለመከላከል ለመጠበቅ ሲል ነበር እዚያ ሥራ ላይ አውሎት የነበረው፡፡ ይህን አደረጃጀት በተቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ላይም መተግበር ያስፈለገበት ምክንያት ወያኔ ሕዝቡን በየ ብሔረሰቡ ስም ባደራጃቸው የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች እንደ ብአዴን ኦሕዴድና የመሳሰሉት የሕወሀት አሻንጉሊት ድርጅቶች በተለያየ መንገድ እያስገደደ አባል እንዲሆን ያደረገው ጥረት እንብዛም የፈለገውን ያህል ውጤት ስላላመጣለት ሌላ ዘዴ በመጠቀም ጥቅሙን ለማስጠበቅ ትግራይ ላይ ውጤታማ አድርጎኛል ብሎ የሚያስበውን የ1 ለ5 አደረጃጀት “ምንም ዓይነት ፖለቲካዊ ዓላማና ተልዕኮ የለውም” እያለ በተቀረው የኢትዮጵያ ክፍል ላይም ተግባራዊ ለማድረግ አስቦ ነው ይሄንን ያደረገው፡፡ ዛሬ ላይ ከ3ኛ ክፍል ሕፃናት ጀምሮ እስከ መንደር ሽማግሌና አሮጊቶች ድረስ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከገጠር እስከ ከተማ ከመንግሥት ሠራተኛ እስከ የግል ድርጅት ሠራተኛ አልፎም የሃይማኖት ተቋምንም በማጠቃለል አባቶችና አገልጋዮች ድረስ በ1 ለ5 አደረጃጀት ያልተጠረነፈ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ብትፈልጉ አታገኙም ወይም ቢፈለግ እንዳይገኝ በብርታት እየሠሩ እየጣሩ ይገኛሉ፡፡
1 ለ5 አደረጃጀት ማለት ምን ማለት ነው?
ብዙ ሰዎች 1 ለ5 አደረጃጀት ሲባል አምስቱ የሕዝቡ ወገን ሆነው አንዱ ጠርናፊው ደግሞ የወያኔ አባል ይመስላቸዋል፡፡ በእርግጥ በአጋጣሚ አልፎ አልፎ እንዲህ ዓይነት ሁሌታ ሊያጋጥም ቢችልም አደረጃጀቱ ግን እንደዚህ አይደለም፡፡ የሚበዛው የ1 ለ5 አደረጃጀት 6ቱም የሕዝብ አባላት የሆኑበት ነው፡፡ ሕዝቡን በሥራ ቦታ ወይም በመንደር እንዳለው ቅርበት በስድስት በስድስት ያቧድኑና ከመሀላቸው አንዱን ትምህርት ያለውን ወይም ነቃ ያለውን መሪ በእነሱ አማርኛ ጠርናፊ ያደርጉታል፡፡ በዚህ አደረጃጀት የመታቀፍ ያለመታቀፍ ጉዳይ በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ አይደለም፡፡ እንቢ አልደራጅም ማለት አይቻልም ክልክል ነው ቀለል ሲል ከወያኔ ተጻራሪ ከበድ ሲል ከአሸባሪነት ያስቆጥርና ከሥራ ከትምህርት ከመሳሰሉት ያስባርራል፣ የተለያዩ የዜግነት ጥቅሞችንና መብቶችን ያሳጣል፡፡ ይሄ ግን በድርጊት ሲሆን ታዩታላቹህ እንጅ በይፋ በአዋጅ አይነገርም፡፡ አሠራሩ ሕገ ወጥ በመሆኑ አገዛዙ በይፋ እንዲህ ማለት ስለማይችል እንቢ ያለውን ዜጋ ሌላ ሰበብ እየፈለገ የሚያጠቃበትና የሚያሳምንበት አኪያሔድ አለው የአሠራር ስልት መሆኑ ነው፡፡ ቀደም ሲል እነኝህን ቅጣቶች የሚያስቀጣው የተቃዋሚ ፓርቲዎች አባል ሆኖ በመገኘት መንቀሳቀስና አገዛዙ የኔ አባል ሁን ወይም ሁኝ ሲል አልሆንም አልፈልግም ሲባል ነበር፡፡ በየ ፓርቲው ሔዳቹህ ብትጎበኟቸው የዚያ ፓርቲ አባል ሆነው በመንቀሳቀሳቸው ከሥራ ገበታቸው የተባረሩ ከከፍተኛ ትምህርታቸው የተባረሩ የከፍተኛ ትምህርት ዕድል የተነፈጋቸው የተለያየ የሕገ ወጥ ጥቃት ሰለባ የሆኑ ዜጎችን በብዛት ታገኛላቹህ፡፡
እሩቅ ሳልሔድ እኔ እራሴ አንዱ ምሳሌ ነኝ፡፡ እኔ እንዲያውም የማንም የፖለቲካ ድርጅት አባል አይደለሁም፡፡ ነገር ግን የዜግነት ግዴታየን ለመወጣት፣ በማያቸው በምታዘባቸው ጉዳዮች ላይና በሚታየኝ ነገር ሁሉ ላይ በመጽሔቶች ጋዜጦችና ድረ ገጾች ላይ ስለምጽፍ (ምን ስለምጽፍ አሁንማ እነዚያ እጽፍባቸው የነበሩ መጽሔቶች ሁሉም በአገዛዙ አንባገነናዊና አፋኝ ትዕዛዝ ስለተዘጉ እጽፍ ስለነበር ብል ይሻላል መሰል) በዚህ የያገባኛል እንቅስቃሴየ ምክንያት “እየተሰለልን ነው” በሚል ለ12 ዓመታት ስሠራበት የነበርኩበት ድርጅት ከአራት ዓመታት በፊት ከሥራየ አባረረኝ፡፡ በዚሁ እንቅስቃሴየ ምክንያት ሌላ ቦታም የሚቀጥረኝ ማግኘት አልቻልኩም፡፡ አሁን አሁንማ የእግዜር ሰላምታ የሚሰጠኝ ሰውም እያጣሁ ነው በተለይ መጽሔት ላይ በጻፍኩት ጽሑፍ ታስሬ ከተፈታሁ በኋላ፡፡ ኑሮየ በጣም ነው የተመሰቃቀለው፡፡ አንደኛየን ብረት ወዳነሡት ጀግኖች ወገኖቸ ተቀላቅየ እንዳልታገልም እውነቱን ለሕዝብ ለማስገንዘብ ለማሳወቅ፣ የሀገሬን ጥቅም ለማስጠበቅ ስል ሸአቢያና ኢሳይያስ ፍጹም የተሳሳቱና አጥፊ እንደሆኑ ወይም “እንደነበሩ” ጠንካራ ጠንካራ የመከራከሪያ ነጥቦችን በመጥቀስ መታረማቸው የግድ እንደሆነ በጻፍኳቸው ጽሑፎች አስተሳሰቤን ዓላማየንና አቋሜን በማስታወቄና የኢሳይያስን ወይም የሸአቢያን ጥቅምንም ስለጎዳ በዚህም ምክንያት ስላቄሙብኝ የውስጤን በውስጥ አድርጌ ለሀገሬ ያለኝን ዓላማ ከነሱ ደብቄ እዚያ ገብቸ እንድታገል የሚያስችለኝ ዕድል ስለሌለኝ መቀላቀል አልቻልኩም፡፡
ወደ ኬንያ እንዳልሰደድ አሁንም የሀገሬን ጥቅም ለማስጠበቅ ያለውን እውነታ ለሕዝብ ለማሳወቅ ለማስገንዘብ ስል በጻፍኳቸው ጠንከር ደፈር ያሉ ጽሑፎች ኦነግና እስልምናን ተንተርሰው ዓለምን የሚያሸብሩት አሸባሪ ቡድኖች ሊያስተባብሏቸው በማይችሏቸው አመክንዮዎችና የመከራከሪያ ሐሳቦች ድንቁርናቸውና ሰይጣንን አገልጋይነታቸው ቁልጭ ብሎ በመታየቱ በዚህ በመበሳጨት አርደው እንደሚጥሉኝ ክፉኛ ዝተውብኛልና ኬንያ እንደገባሁ አፍነው ስለሚወስዱኝ እዚያም መሔድ አልችልም፡፡ ምን እባካቹህ እኔ በሀገሬ ላይ ሰይጣናዊ ጦሩን የወረወረውን ማንኛውንም አካል ሁሉ እኔም መልሸ ያልወጋሁት ያላቆሰልኩት አለ እንዴ! የጸፍኩባቸው ሁሉ አቂመውብኝ በተለያየ መንገድ ጥርስ እንደነከሱብኝ አሳውቀውኛል፡፡ አይሁዶቹም አልቀሩ ዝተውብኛል፡፡ የምዕራባዊያኑን ባላውቅም እነሱም ለውድቀት ጥፋታችን ዋነኛ ጠንቆች እንደመሆናቸው ከብዕር ሰይፌ አላመለጡምና እስከ አሁን ያሉኝ ነገር ባይኖርም ጥርስ አልነከሱብኝም ማለት ግን አልችልም፡፡ ይሄንን ስል አንዳንድ ሰዎች “ራስህን ማን ታደርጋለህ ባክህ! አንተ ማን ነህና ለእነዚህ ሀገራትና ቡድኖችስ ምን ያህል ሥጋትና አደጋ ሆነህ ነው ይሄንን ያህል ትኩረት የሚሰጥህ?” የሚሉ ሰዎች ይኖሩ ይሆናል፡፡ እኔ ማንም ስለሆንኩ አይደለም፡፡ ይሄንን የሚሉ ሰዎች ብዕር ያለውን ኃይል ካለማወቅ የተነሣ ነው እንዲህ የሚሉት፡፡ አውሮፓውያን “ከእልፍ ጦር አንድ ብዕር” የሚል አባባል አላቸው ናፖሊዮን ቦና ፓርቲም ተመሳሳይ ጥቅስ አለው “The pen is mightier than the sword, ከሰይፍ ይልቅ ብዕር ያይላል” የሚል፡፡ በእኛም ሀገር “ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው” ይባላል፡፡ ብዕር ማለት ክብሪት ማለት ነው፡፡ ክብሪት ትንሽ ናት ተብላ አትናቅም ሀገር ልታቃጥል ትችላለች፡፡ ምዕራባዊያን የብዕርን አቅም ጠንቅቀው ያውቃሉ፡፡ በእነሱ መርሕ ምንም ዓይነት መረጃ አይናቅም ምንም ዓይነት ትችት ቸል አይባልም፡፡ ከዚህ አንጻር ከምትገምቱት በላይ እነኝህ ሀገራት ኤምባሲ (የመንግሥት እንደራሴ ጽ/ቤት) እና ቆንሲላ (የመንግሥት ጉዳይ አማካሪ ጽ/ቤት) ባላቸው ሀገራት ሁሉ የየሀገሮቻቸውን ጥቅም የሚጋፉ ማንኛውም ዓይነት መጣጥፎችን በከፍተኛ ትኩረት ይከታተላሉ ይመለከታሉ፡፡ በተለያየ መንገድ የመልሶ ማጥቃት እርምጃን ይወስዳሉ ወይም በጥቅም ሊይዟቹህ ይሞክራሉ፡፡ በግል የሚደርሱኝ ዛቻና ማስፈራሪያዎች ያረጋገጡልኝ ነገር ቢኖር ይሄንን ነው፡፡ በተለይ የምትጽፉት ነገር በአሳሳቢ ጉዳዮች ላይ ጠንካራና አሳማኝ ከሆነ ፕሮፌሰር ሆናቹህ ታራ ዜጋ የናንተ ደረጃ ለነሱ ጉዳያቸው አይደለም፡፡ የሚያተኩሩት በጽሑፉ ጥንካሬ የተነሣ በጥቅማቸው ላይ ሊያመጣ የሚችለው አሉታዊ ውጤት በምን ያህል ደረጃ ጥቅማችንን ይጎዳል? የሚል መሆኑ ነው የሚያሳስባቸውና በቸልታ መመልከት የማይፈልጉበት ምክንያት፡፡
እናም እንግዲህ ያለኝ አማራጭ ወያኔ እስኪያጠፋኝ ድረስ እየራበኝም እየጠማኝም እዚሁ መታገል ነው፡፡ የግል ሕይዎቴን እንዳይጎዳብኝ፣ እራሴን ለአደጋ እንዳላጋልጥ፣ በራሴ ላይ ጠላት እንዳላበዛ ብየ ስልታዊ አኪያሔድ አልከተልም፤ ማድረግ ካለብኝ ነገር አልታቀብም፡፡ ዓላማየ መቸ እንደምሞት አላውቅምና በሕይዎት እስካለሁ ድረስ ሀገሬ ከኔ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም እንድታገኝ መጣር፣ ሕዝባችን ማወቅ መገንዘብ መረዳት ያለበትን ነገር ሁሉ በሰዓቱ እንዲያውቅ ማድረግ፣ የሀገሬን ጥቅም ለማስጠበቅ የመጨረሻ አቅሜን በመጠቀም መጣር ነው፡፡ ስንት ወገን መቸ በምን ምክንያት እንደሚሞት የሚያውቅ ይመስል ምቹ ጊዜን ሲጠብቅ አንዳችም ነገር ሳያበረክት ሳይጠቅም አፈር የገባ አለ መሰላቹህ፡፡ ሀገርም ከነሱ ማግኘት የነበረባትን ስንት ጥቅም በማጣቷ እንዴት ተጎድታለች መሰላቹህ?
የፖለቲካ ፓርቲ አባል ተሁኖ ወይም ሳይኮን ወያኔን እታገላለሁ፣ ሀገሬን አገለግላለሁ፣ የዜግነት ኃላፊነቴንና ግዴታየን እወጣለሁ፣ ለሆዴ አድሬ ኅሊናየን በማርከስ እራሴን በማዋረድ ከሰውነት ወደ እንስሳነት አልለውጥም፣ ባሪያ አልሆንም፣ የሀገሬ ጠላት አልሆንም ማለት እንግዲህ ይሄንን ይሄንን ለመሳሰለ ፈተናና መከራ ይዳርጋል፡፡ ይሁን እንጅ እኔ በበኩሌ በእነኝህ ውርደቶች የጎደፈ የረከሰ ሰብእና ስለሌለብኝ ውሳጣዊ ሰላም አለኝና ፈጽሞ አልጸጸትም፡፡ በተለየ ምክንያት ወይ ባላቸው ጉብዝና በንቁነታቸው ወይም ደግሞ ወያኔ በራሱ ምክንያት አባሌ ሁኑ ብሏቸው እንቢ አንሆንም አንፈልግም በማለታቸው ብቻ ከከፍተኛ ትምህርት ገበታቸው የተባረሩ በርካታ ዜጎች አሉ፡፡ ከእነኝህ አንዱን ብቻ ለምሳሌ ያህል ላቅርብ፡፡
መጋቢት 6, 2004ዓ.ም ላይ አንድ በሀገራችን ውስጥ ሥራ ላይ ካሉ ሕጎች ውጭ በሆነ ወይም በማይፈቅዱት ሁኔታ ተቋቁሞ በሕገ ወጥ መንገድ ሲሠራ በቆየና እየሠራም ባለ የራሱን ከተለያየ አቅጣጫ የተቀናጀ የኢኮኖሚ ኢምፓየር (የሀብት ግዛት) እስከ መገንባት የደረሰ ቀደም ሲል የሕወሐት ፓርቲ የነበረ የገዛ ሕጋቸው እንደማይፈቅድ ከየአቅጣጫው አቤቱታ ሲበዛባቸው የአክሲዮን (የማኅበር) ነው ቢሉም ባለንብረትነቱ እነማን እንደሆኑ በማይታወቀው ፋና በሚባል የሬዲዮ (የነጋሪተ-ወግ) ጣቢያ ላይ አንድ ሳምንታዊ ዝግጅት በመተላለፍ ላይ ነበር፡፡ ይህ ምስናድ የቀጥታ ዝግጅቱን በሚያስተላልፍበት በዚህ ዝግጅቱ ስቱዲዮ (መከወኛ ክፍል) እስኪገኙላቸው ድረስ የምስናዱ አዘጋጆች ለሥራቸው መቃናት ሲሉ ሌላ ሌላ ምክንያቶችን በመስጠት ለምን ጉዳይ እንዳመጧቸው አያውቁ የነበሩት መከወኛ ክፍል ውስጥ እንዲገኙ የተደረጉት እንግዳ ከልጃቸው ጋር እንዲታረቁ እዚያ እንደተገኙ ከተነገራቸው በኋላ አዘጋጆቹ ለሚጠይቋቸው ጥያቄዎች መልስ ሲሰጡ ከቆዩ በኋላ በድንገት በብሶት በመገፋት ሁላችንም የምናውቀውን ደፍረን ግን በአደባባይ የማናወራውን ነገር መናገር ጀመሩ፡፡
እንዲህም አሉ “እኔ ልጀን ጠልቸ አይደለም ልጀን እንዴት እጠላለሁ? ለ26 ዓመታት በረሀ ተቃጥዬ ነው ያሳደኳቸው ነገር ግን የት ይደርሱልኛል ያልኳቸው ተስፋ የጣልኩባቸው ልጆች ከንቱ በመሆናቸው ውስጤ በጣም ስለተጎዳ ጤና አሳጥቶኝ፤ ይህች እንደምታይዋት ጎረምሳ አታሏት ካስወለዳት በኋላ “ዞር በይ አላውቅሽም” ብሎ ሸኛት ሕይወቷን አበላሸብኝ ያኛው የሷ ታላቅ ጥሩ ጭንቅላት ነበረው ጎበዝ ተማሪ ነበር አዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የዲግሪ ተማሪ ነበር “አባል ካልሆንክ አትማራትም” እያሉ ይሄው ለሦስተኛ ጊዜ በተከታታይ ዓመታት እያባረሩት ዘንድሮም እዲያቋርጥ አደረጉት እስካሁን ተመርቆልኝ ነበር” እያሉ እንባ በተናነቀው ተስፋ በቆረጠ ድምፅ እየተናገሩ እንዳሉ ጋዜጠኞቹና የነጋሪተ-ወጉ ኃላፊዎች ሰውየው እንዲናገሩ የማይፈልጉትንና የማይፈቅዱትን የአገዛዙን ግፍ ሳያስቡት በመናገር ላይ እንዳሉ በድንገቱ የተደናገጡት አዘጋጆቹ ተጣድፈው አቋረጧቸው፡፡ አሁን እንግዲህ ይሄ ልጅ በገዛ ሀገሩ ላይ ተምሮ መለወጥ ሠርቶ ማደር ባለመቻሉ ያለመሰደድ ሌላ አማራጭ አለውን? ይሄኔ ተሰዶም ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ ተማሪ የደረሰበት ችግር ሁሉም ላይ የሚደርስ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ዜጎች እንዲህ ዓይነት መሥዋዕትነቶችን እየከፈሉ ወያኔ የፈለገው ነገር ሊሆን ስላልቻለ ለሽፋን ያህል “ምንም ዓይነት ፖለቲካዊ ዓላማ የለውም ዓላማው የልማት ሠራዊትን መፍጠር ብቁ ተወዳዳሪና ታታሪ ሠራተኞችን ማፍራት ነው” እያለ የ1 ለ5 አደረጃጀትን አመጣ፡፡
የ1 ለ5 አደረጃጀት ዓላማ ምንድን ነው?
የዚህ አደረጃጀት ዓላማ ሕዝብ ያለውን ሰብአዊና ሕገ መንግሥታዊ መብቶችና ነጻነቶችን በማሳጣት መበንጠቅ በአገዛዙ ፈቃድና ፍላጎትና ቁጥጥር ሥር ቀፍድዶ ለመያዝና ተቃዋሚ ወይም ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ወያኔ የደህንነቴ ሥጋት ናቸው የሚላቸው ሕዝባዊ ማኅበራት ሕዝባዊ መሠረት እንዳያገኙ ማድረግ መከላከል ነው፡፡ አገዛዙ ግን እያለ ያለው “የልማት ሠራዊት ለመፍጠር” ነው፡፡ ይህ ግን ሽፋን ነው፡፡ በእርግጥ ከገጠር እስከ ከተማ ከተማሪ እስከ ሠራተኛ ሕዝቡን ሲያደራጀው አንዳንድ የልማት እንቅስቃሴዎችንና ርእሰ ጉዳዮች (አጀንዳዎች) አድርጎ በማንሣት እንዲንቀሳቀሱበት ያደርጋል፡፡ ለምሳሌ ተማሪዎችን ከ3ኛ ክፍል ጀምሮ ካደራጀሁበት ምክንያቶች አንዱ የሚለው፡- “የተሻለ ዕውቀት ያለው ተማሪ ደከም ያሉትን አምስቱንም በማስረዳትና በማስጠናት እሱ ካለበት ደረጃ ላይ ማድረስ አንዱ ኃላፊነቱና ግዴታው ነው” በማለት ነው፡፡ ይሄ አሠራር ምንም እንኳ በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ ባይንም የሚበረታታ እንጅ የሚነቀፍ የሚኮነን አልነበረም ችግሩ ያለው እዚህ ላይ አይደለም፡፡
ይህ አደረጃጀት አገዛዙ እንደሚለው ምንም ዓይነት ፖለቲካዊ ዓላማ የለውም ወይስ አለው?
አገዛዙ ፖለቲካዊ (እምነተ አሥተዳደራዊ) ዓለማ የለውም የሚለው ሐሰት ነው፡፡ ዋነኛ ዓለማው ፖለቲካዊ ነው፡፡ ፖለቲካዊ ነው ስል የሀገርንና የሕዝብን ሳይሆን የሕወሐት ኢሕአዴግን ጥቅምና ዓላማ ለማስጠበቅ ሲባል የተዘረጋ ሥራ ላይ የዋለ አደረጃጀት አሠራር ነው ማለቴ ነው፡፡ እንዴት ሆኖ ነው ከተባለ አገዛዙ “የአካባቢ ሰላምና መረጋጋት” የሚል አጀንዳን (ርእሰ ጉዳይን) ለየ1ለ5ቱ አደረጃጀት በማንሣት የፖለቲካ ፓርቲዎችንና በክርስትናውም በእስልምናውም ያሉ አገዛዙ በግልጽ “አክራሪ ብሎም አሸባሪ” በሚል የሚጠራቸውን ማኅበራትንና በውስጣቸው ያሉ ግለሰቦችን የአካባቢ የሀገር ሰላምና መረጋጋት ሥጋቶችና ጠንቆች እንደሆኑ አድርጎ ይሰብካል ስም ያጠፋል፡፡ ይሄንን ማለቱ የሚለው ነገር በሕዝቡ ዘንድ ታምኖለት ሕዝቡ እነኝህን አካላት እሱ እንደሚለው ፀረ ሰላምና መረጋጋት አድርጎ ይወስዳቸዋል ከሚል እምነት ሳይሆን ሕዝቡን የእነኝህ አካላት አባል ደጋፊ እንዳይሆን ለማሸማቀቅ ለማራቅ “የእነኝህ አካላት አባል ደጋፊ ብትሆን ወዮልህ!” የሚል መልዕክት ለማስተላለፍ ለማስያዝ የሚያደርገውና በአጭር ጊዜ እንዲከስሙ ለማድረግ የሚጠቀምበት ዘዴ ነው፡፡ ከዚህም የተነሣ ሕዝቡ የወያኔን ሐሰተኛ የስም ማጥፋት አምኖበት ሳይሆን በ1ለ5 በመጠርነፉ ብቻ በፈጠረበት የበእንተእፍረት ስሜት ሊከበርለት የሚገባውን ሰብአዊና ሕገመንግሥታዊ መብቶቹን ለመጠየቅና በሕጋዊ የተቃውሞ እንቅስቃሴዎችም ደፍሮ እንዳይሳተፍ ከእንደዚህ ዓይነቶች እንቅስቃሴዎች ራሱን እንዲያርቅ እንዲያገል አድርጎታል፡፡ ወያኔም እያስገደደ ሕዝቡን በዚህ አደረጃጀት ሲጠረንፍ ቢያንስ ይህችን የሥነ ልቡና መሸበብ ውጤት እንደሚያስገኝለት በመተማመን ነው፡፡
እነኝህ ወያኔ ስማቸውን የሚያጠፋባቸው አካላት ለአገዛዙ “ልብ በሉ” ለአገዛዙ አደጋ ይሆኑ ይሆናል፡፡ ለዚህ አገዛዝ አደጋ ናቸው ማለት ግን ለሀገርና ሕዝቧ አደጋ ናቸው ማለት በፍጹም አይደለም፡፡ ወያኔ ለዚህች ሀገርና ሕዝቧ ቅን አሳቢ አይደለምና ከእሱ በተሻለ አልልም እንጅ ላቅ ያለ የሀገርና የወገን ፍቅር የሚያቃጥላቸው ለሀገርና ለወገን የሚያስቡ የዜግነት ድርሻቸውንም ለማበርከት የሚታትሩ መሆናቸው በሕዝብ ዘንድ በሚገባ ይታወቃል፡፡ የአገዛዙና የእነኝህ አካላት መሠረታዊ ልዩነትና የጥቅም ግጭትም ይሄው ነው፡፡ እሱ ሊያፈርሰው ሊንደው ሌት ተቀን የሚጥርበትን የሚለፋበትን የሀገር ፍቅር ስሜት፣ ዘርና ሃይማኖት ያልተለየበት የአንድነትና ትስስር ጥንካሬንና ሌሎች እሴቶቻችንን እሱ በናደ ባፈረሰ ቁጥር ከስር ከስር የሚገነቡ መሆናቸው ነው፡፡ አሁን ታዲያ ለዚህች ሀገር ሰላምና መረጋጋት አደጋው ማን ነው? መንግሥት ነኝ ከሚል አይደለም ከጠላት እንኳን በማይጠበቅ ደረጃ መርዘኛ ሴራ እየሸረበ ሕዝቡን በዘርና በሃይማኖት ሊያፋጀን እየጣረ ያለው፣ ከሕዝብ ዕውቅናና ይሁንታ ውጪ የሀገርን ሉዓላዊ መሬታችንን እየቆራረሰ ለጎረቤት ሀገራት እያደለ ያለው፣ ከአንድም ሁለት ሦስት ብሔረሰቦችን በጠላትነት ፈርጆ ጨርሶ ለማጥፋት የዘር ማጥፋት ወንጀሎችን እየፈጸመ ያለው፣ ሌላም ሌላም በርካታ የሀገር ክህደቶችንና አደጋዎችን እየፈጸመብን ያለው ወያኔ ወይስ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሲቪክ (ሕዝባዊ) ማኅበራት? ሕዝቡ ይሄንን ጠንቅቆ ያውቃልና አይሳሳትም፡፡ ወያኔም ሕዝቡ ያምነኛል ብሎ አይደለም ይሄንን ሐሰተኛ ወሬ የሚነዛው፡፡ ነገር ግን “እንዲህ ናቸው ብያለሁ እኔ የማውቃቸው በዚህ መልኩ ነው እያንዳንድህ ሔደህ ብትቀላቀል አንተም አሸባሪ ፀረ ሰላምና መረጋጋት ነው ብየ ፍዳህን አሳይሀለሁ!” የሚል መልእክት ለማስተላለፍ ነው፡፡
በመሆኑም ወያኔ ይሄንን አደረጃጀት ያዋቀረው እንዲህ ዓይነት ፖለቲካዊ ጥቅሙን ሊያስጠብቅበት ህልውናው ለአደጋ እንጋይጋለጥ ሊከላከልበት በመሆኑና እየሠሩት ያለውን ሥራ የመሥራት ሕገ መንግሥታዊና ሰብአዊ መብታቸው የሆኑ አካላትን እያጠቃበት ያለ አደረጃጀት በመሆኑ ይህ አደረጃጀት ዋነኛ ዓለማውና ግቡ ፖለቲካዊ እንጅ ልማታዊ አይደለም፡፡ ወያኔ የእነኝህ ፖለቲካዊና ሕዝባዊ ማሕበራትና ድርጅቶች ሥራ መብታቸው እንደሆነ ተረድቶ በዚህ አደረጃጀት ላይ ይሄንን የስም ማጥፋት አጀንዳ እያነሣ እነኝህ አካላትን ሕዝባዊ ተቀባይነት እንዳይኖራቸው የሚሠራበት አደረጃጀት ባይሆንና ንጹሕ የልማት ሥራ ብቻ የሚሠራበት አደረጃጀት ቢሆን ኖሮ ይህ አደረጃጀት ፖለቲካዊ ዓላማ የለውም ልማታዊ ነው ባልን ነበር፡፡ እየሆነ ያለው ግን የዚህ ተቃራኒ በመሆኑ የሚወገዝና የሚኮነንም ነው፡፡
ወያኔ እሱን የማይመስሉትን ሁሉ ለሀገርና ለወገን ተቆርቋሪ እንደሆኑ ልቡ እያወቀ የፈጸመብንንና እየፈጸመብን ያለውን የሀገር ክህደቶችና ወንጀሎቹን ስለሚያጋልጡ ከዚህም የተነሣ ለህልውናየ አደጋና ጠንቅ ናቸው ብሎ ስለሚያስብ ብቻ ለሀገርና ለወገን ተቆርቋሪ የሆኑትን ሁሉ “ፀረ ሰላም ፀረ ሕዝብ በመሆናቸው፣ ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለመናድ በመሞከራቸው” የሚል ክስ እያነሣ በርካታ ንጹሐን ወገኖቻችንን በግፍ ገሏል አስሯል አንገላቷል፡፡ ሕዝብ ግን እውነቱን ያውቃል፡፡ በዚህች ሀገር ሕገ መንግሥቱንና የሕገ መንግሥታዊ ሥርዓትን በኃይል የሚያፈራርስ የሚያመሰቃቅል ጠላት ከወያኔና መሰሎቹ በላይና ሌላ ማንም የለም፡፡ ወያኔ እኮ የገዛ የራሱን ሕገ መንግሥት ለአንድም ቀን እንኳን አክብሮ የማያውቅ ለ24 ዓመታት ሲያፈራርሰው ሲሸራርፈው የኖረ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት እንዳይመሠረት ደንቃራ የሆነ አካል ነው፡፡ ሲጀመር ሕገ ምንግሥታዊ ሥርዓት በዚህች ሀገር የለም፡፡ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት በሌለበት ሁኔታ “ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለመጣል” የሚለው ክስ አስቂኝና አሳፋሪ ነው፡፡
የምለው ነገር ቢኖር የሀገራችንና የሕዝባችንን ጥቅምና ህልውና አለመቀናቀናቹህን አለመቃረናቹህን እርግጠኛ ሁኑ እንጅ በወያኔ ላይ ብታምፁና ለማመፅ ባታስቡ ብረት ብታነሡና በወያኔ ላይ ብትተኩሱ “ፀረ ሕዝብና ፀረ ሰላም” ወይም “ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለመጣል” የሚል ክስ ይነሣብኛል እንዲህ እባላለሁ እፈረጃለሁ ብላቹህ ቅንጣት እንዳትሠጉ እንዳታስቡ ወይም በወያኔና በጌቶቹ “አሸባሪ” የምትባሉ በመሆናቹህ ቅንጣት ታክል ሊደንቃቹህ ሊገርማቹህ ሊያሳስባቹህ በፍጹም በፍጹም የሚገባ እንዳልሆነ መረዳት ይሆርባቹሀል፡፡ እየሠራቹህ ያላቹህት እንደ እናት አባቶቻችን ሀገርንና ሕዝብን የመታደግ የአርበኝነት ተግባር እንጅ እንደ ወያኔ የውንብድና ተግባር አይደለምና፡፡ ወያኔ የሀገርና የሕዝብ ጠላት እስከሆነ ጊዜ ድረስ ወያኔንና መሰሎቹን መዋጋት ጥቅማቸውን መጉዳት ለአንድ ዜጋ መብቱ ብቻ ሳይሆን የዜግነት ግዴታውም ነው፡፡ ሀገር አልባ ሆነናል ሀገራችንን ተቀምተናል ሕዝባችን ባለቤት እንደሌለው ውሻ የትም ተቅበዝባዥ ሆኗል፣ ውርደት መለያችን ሆኗል፣ ሀገሪቱ የአንድ ጎሳ ብቻ ሆናለች ይሄንንም ዘለዓለማዊ ለማድረግ በከፍተኛ ደረጃ እየተሠራበት ይገኛል፣ በሀገራችን መኖር የማንችልበት ሁኔታ በመኖሩ ከሞት ማዶ ያለችን መንማና የሕይዎት ተስፋን የማግኘት አደገኛን የስደት አማራጭ ለመጠቀም ተገደናል፣ በገዛ ሀገራችን በውጭ ዜጎች በሰብአዊ ክብራችን ላይ አስነዋሪና ዘግናኝ ጥቃቶች እንዲፈጸምብን እየተደረገ ቅስማችንንና ብሔራዊ የማንነት ክብራችንን ለመግደል ለመሰባበር፣ በውርደት ስሜት አፍረን ተሸማቀን እንድንቀር ለማድረግ በየዕለቱ ሊባል በሚችል ደረጃ ጥረቶች ተደርገውብናል እየተደረጉብንም ይገኛል፡፡
በእርግጥ ላሚቱ ላይ ተተክሎ ደሟን የሚመጠውን መዥገር እናንሣ እናስወግድ እንንቀልላት ሲባልና ሲነቀል መዥገሩ ላለመነቀል ነክሶ ስለሚይዛት በግድ ስትነቅሉት የላሚቱ ገላ ተቦጭቆ መጎዳቱና መድማቱ አይቀርምና፤ ወይም ደግሞ ከላሚቱ አካል ላይ ያለውን መግልና ደም የያዘ እባጭ አፍርጠን አፍሰን ላሚቱን ከዚህ ሰላሟን ካሳጣት ሕመሟ እንገላግላታለን እፎይ እናሰኛታለን ብላቹህ ይሄንን ስታደርጉ ላሚቱን ለጊዜው ሕመም ሊሰማት መቻሉ አይቀርምና የዚህችን ሀገርና ሕዝብ ጠላት ወያኔን ለማስወገድ ወያኔን እናጠቃለን ስንል የሀገር ጥቅም መነካቱ መጎዳቱ አይቀርም ይሆናል፡፡ ነገር ግን ጉዳቷ መግሉ ተፍረጥርጦ እስኪፈስ መዥገሩ እስኪነቀል ድረስ ጊዜአዊና ለዘለቄታዊ ጥቅም ደህንነትና እፎይታ ሲባል የሚደረግ ነውና እንደ ጉዳት የሚቆጠር ባለመሆኑ ይሄ አያሳስባቹህ፡፡ የሀገር ጥቅም ተነካ ብላቹህም አትዘኑ፡፡ ይህ ሳይሆን ቁስሏን ማከም መዥገሯን ማንሣት አይቻልምና፡፡
ስለሆነም ወያኔ የራሱን ጠላት ነገር ግን ለሀገርና ለወገን የሚታገሉትን የሀገርንና የሕዝብን ልጆች የሆኑ አካላትን የሀገርና የሕዝብ ጠላት እንደሆኑ አድርጎ ሊፈርጅና የኢትዮጵያም ሕዝብ እንደዚያ አድርጎ እንዲቆጥራቸው እንዲያስባቸው ማድረግ የሚያስችለው ምንም ዓይነት ሕጋዊና ሞራላዊ (ቅስማዊ) መብት ጨርሶ የለውም፡፡ ሕዝብ ማን ጠንቅ ማን ጠቃሚ ማን ጠላት ማን ወዳጁ እንደሆነ በሚገባ ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ ወያኔ የኢትዮጵያን ሕዝብ “አንተ አታውቅም እኔ ነኝ የማውቅልህ” ሊል ፈጽሞ ፈጽሞ አይችልም፡፡ ይሄንን ሊል የሚችልበት መብትም የለውም፡፡ ይሄ አንባገነናዊ አስተሳሰብ እንጅ ዲሞክራሲያዊ (በይነ ሕዝባዊ) አስተሳሰብ አይደለም፡፡ ወያኔ እንዲህ ብሎ የሚያስበው አንባገነን ስለሆነ ነው፡፡ የዲሞክራሲያዊ አስተሳሰብ መሠረቱ ሕዝብ አዋቂ ነው ሕዝብ ባለ መብት ነው ሕዝብ ወሳኝ ነው ሕዝብ የሁሉም ነገር መሠረት ነው ብሎ ማሰብ ነው፡፡ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት የሕዝብን ውሳኔ የመጨረሻውና የማይቀለበስ አድርጎ ይቆጥራል ይቀበላል፡፡ የመጨረሻው ባለሥልጣን ሕዝብ እንደሆነ ያምናል፡፡ ወያኔ ግን አንባገነን እንጅ ዲሞክራት (በያኔ ሕዝብ) አይደለምና ከተጀመረ ጀምሮ ሕዝብን “እኔ ነኝ የማውቅልህ አንተ አታውቅም” የሚል ነው፡፡ ወያኔ ለየት የሚልበት ነገር ቢኖር እንደ አንባገነንነቱ በራሱ ውሳኔ ማድረግ የሚችለውን ጉዳይ ሁሉ ሕዝብን ለማጨስ የራሱን የሕዝቡንና የሀገሪቱን ጥቅም በሚጎዱ ነገሮች ላይ “የሚጎዳህ መሆኑን ብታውቅም አንተ ባትልም እኔ ብያለሁና አንተ እንዳልክ ተቆጥሮ ይፈጸማል!” ብሎ እያወናበደ “ሕዝብ ብሏል” እያለ የሚያስፈጽም መሆኑ ነው፡፡ ይሄ የወያኔ የራሱ የብቻው መገለጫ ባሕርይው ነው፡፡
ይህ አደረጃጀት ሕጋዊ አሠራር ነው ወይስ አይደለም?
በፍጹም አይደለም ምክንያቱም የአደረጃጀቱ ዓላማና ግብ የመንግሥትን መዋቅር በመጠቀም የፓርቲን አጀንዳና ጥቅም ማስጠበቅ መከወን ስለሆነ፡፡ አንድ መንግሥት እንደ መንግሥትነቱ ሊከውናቸው የሚገቡ በርካታ ጉዳዮች አሉ፡፡ ልማት አንዱ ነው፡፡ ወያኔ ላይ ስንመጣ ግን ወያኔ የመንግሥት አቅል ፣ ሥነ ሥርዓት (discipline) ሰብእና (personality)፣ ቅርጽ (formation)፣ ሥርዓት (system)፣ ኃላፊነት (responsibility)፣ ቃል አጠባበቅ (commitment) አስተሳሰብ (Mentality) ተአማኒነት (credibility) ተቀባይነት (acceptability) የሕዝብ ውክልና (public representation) ኖሮት ስለማያውቅና ወደፊትም እንደነዚህ ዓይነት ለመንግሥትነት የሚያበቁ ብቃቶች ችሎታዎችና ሰብእና ሊኖረው የሚችልበት ዕድል ከምንም ወይም ከዜሮ በታች ስለሆነ ወያኔን መንግሥት ብሎ መጥራት አይቻልም፡፡ በመሆኑም ወያኔን ስንገልጽ መንግሥት ሳይሆን አገዛዝ የሚለውን ቃል ለመጠቀም እንገደዳለን፡፡ እናም ይሄ አገዛዝ በዚህ የ1 ለ5 አደረጃጀት የመንግሥትን ሥልጣንና መዋቅር በመጠቀም የመንግሥትን ወይንም የሕዝብን ጥቅሞች የሚያስጠብቁ ሳይሆን የሀገርንና የሕዝብን ጥቅሞች የሚጎዱ የሕወሐት ኢሕአዴግን አጀንዳና ዓላማ እያራመደበት እያስፈጸመበት በመሆኑ አደረጃጀቱ የለየለት ሕገ ወጥ አሠራር ነው፡፡
የወያኔ ሕገ መንግሥት ልክ እንደ ምዕራባዊያን ሕገ መንግሥታት ሁሉ መንግሥትና ፓርቲ የተለያዩ መሆናቸውንና አንዱ የሌላውን መዋቅርና ንብረት መጠቀም መገልገል እንደማይችል ይደነግጋል፡፡ ወያኔ በሕገ መንግሥቱ ላይ ይሄንን ብሎ ይደንግግ እንጅ በተግባር ግን እያደረገ ያለው የገዛ ሕገ መንግሥቱ ከሚለው ፍጹም የተቃረነ ነው፡፡ የመንግሥት ንብረትና መዋቅር ሁሉ ስንጥር ሳትቀር የሕወሐት ኢሕአዴግ ንብረትና መጠቀሚያ ነው፡፡ ወያኔ ፈጽሞ ፓርቲና መንግሥት እንዲነጣጠሉ አይፈልግም፡፡ ከአንባገነናዊ ማንነቱ አንጻር ጥቅሙ በከፍተኛ ደረጃ እንደሚጎዳበት ለህልውናውም አደጋ እንደሆነ ጠንቅቆ ያውቃልና፡፡ ይሄንን አደረጃጀት ለሽፋን እያለው እንዳለው ሁሉ የልማት ሠራዊትን ለመፍጠር ሕዝቡን ለልማት ለማነሣሣት ቢሆን ኖሮ አደረጃጀቱ በግዳጅ ከመሆኑ በቀር ምንም ችግር አልነበረውም፡፡ ከዚህ አሳፋሪ አንገት ሰባሪ አዋራጅ ድህነት ለመውጣት የመጨረሻ አቅማችንን አሟጠን እስከመጠቀም ድረስ መትጋት የግድ ይኖርብናልና፡፡ ሕዝቡ የራሱን መንግሥት ቢያገኝ እስኪያስገድዱትም የሚጠብቅ ሕዝብ አልነበረም፡፡ መንግሥትን ቀድሞ ከፊት ከፊት እየሔደ ነፍሱንም እስከመስጠት ለእናት ሀገሩ የማይሆነው ነገር እንደሌለ የማይከፍለው የመሥዋዕትነት ዓይነት እንደማይኖር ከታሪኩ መረዳት ይቻላል፡፡
ሕዝባችን ያጣው የራሴ የሚለው የሚሰማው የሚታዘዘው መንግሥት ነው፡፡ ሕዝባችን ያጣው ክብርና ፍቅር ሰጥቶት ድርሻውን ሥልጣኑን አውቆለት ምን እናድርግ? ምን ይሻላል? ብሎ ፋንታ የሚሰጠውን መንግሥት ነው፡፡ ሌላው ሁሉ በእጁ ነበር የሚቸግረው ነገር ባልነበረ፡፡ ምክንያቱም ሕዝባችን ሞራል (ቅስም) ያለው ሕዝብ ነውና ቅስም የመነቃቃት አቅም ያለውን ሕዝብ ለምንም ጉዳይ ቢሆን ያሳምኑት ብቻ እንጅ ተራራን ይገፋል ኮረብታን ያፈልሳል፡፡ ቅስም ማለት ለአንድ ሀገር ሕዝብ ምንም ነገር የማይተካው የትም ሊያደርሰው የሚችል ኃይል አቅም ጉልበት ነው፡፡ የእኛ ሕዝብ የትኛውም ሕዝብ ሊወዳደረው በማይችለው ደረጃ ይህ ሀብት አለው፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ በሥርዓቶች መበላሸት ምክንያት ይሄንን አቅሙን እንዲጠቀምበት ማድረግ አልቻልንም፡፡ የእኛ ችግራችን የሕዝብና መንግሥትህ ነን የሚሉት አካላት ልብና ቋንቋ አለመገናኘት አለመጣጣም ነው፡፡
እናም ይህ አደረጃጀት የተፈጠረበት ወይም ሥራ ላይ የዋለበት ዓላማ የሀገሪቱንና የሕዝቧን ጥቅም ለማስጠበቅ ለማሳደግ ለማበልጸግ ሳይሆን ከሀገርና ከሕዝብ ጥቅም በተጻራሪ ያለን የፓርቲን ሕልውናና ጥቅም ለማስጠበቅ ነው፡፡ ሲጀመር ከላይ እንደገለጽኩት የወያኔ ሰብእናና ማንነት በአንድ ጎጥ ላይ ጠቦና ተወስኖ ያለ እንጅ በኢትዮጵያና ብሔረሰቦቿ ልክ በእኩልነት ሰፍቶ ያለና ለኢትዮጵያ የሚበቃ ኢትዮጵያን የሚመጥን አይደለም፡፡ ወያኔ በምንም ነገር ላይ ቢሆን ቅድሚያ የሚሰጠው የራሱን (የፓርቲውን) ጥቅምና ጉዳይ እንጅ የሀገርንና የሕዝብን አይደለም፡፡ ለአንድም ጊዜም እንኳ ተሳስቶ ከራሱ ጥቅም ይልቅ የሀገርንና የሕዝብን ጥቅም አስቀድሞ አያውቅም፡፡ ይልቁንም የራሱን ነውረኛ ጥቅም ለማስጠበቅ ሲል ከባባድ የሀገርንና የሕዝብን ጥቅም አሳልፎ በመስጠት የፈጸማቸው የሀገር ክህደቶቹ በርካቶች ናቸው፡፡ የወያኔ ማንነትና ሰብእና ይሄ ሆኖ እያለ የ1 ለ5 አደረጃጀትን የሀገርንና የሕዝብን ጥቅም ለማስጠበቅ ነው ብሎ ማሰብ ፈጽሞ የማይቻል ነው፡፡ እንደ ወያኔና መሰሎቹ ሁሉ ከሀገርና ከሕዝብ ጥቅም ጋር የሚጋጭ ዓላማና ግብ ያለው የሕዝብ ተቀባይነት ያገኘ የፖለቲካ ፓርቲም ሆነ ሕዝባዊ ማኅበር በዚህች ሀገር የለምና ቢያንስ በግልጽ የምናውቀው የለምና የጥቅም ግጭቱ ያለው በወያኔና በማኅበራቱ እንጅ በሀገር ወይም በሕዝብ ጥቅምና በማኅበራቱ መካከል ባለመሆኑና ወያኔም የመንግሥትን መዋቅር በመጠቀም የራሱን (የፓርቲውን) አጀንዳ እያስፈጸመበት በመሆኑ ይህ አሠራር ሕገ ወጥ እንጅ ሕጋዊ አይደለም፡፡ አቶ መለስ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውይይት ላይ ማኅበረ ቅዱሳንን ያህል ለሀገርና ለሕዝቧ እሴቶች ጥቅሞችና ማንነቶች ተቆርቋሪ ማኅበር በስም ጠርቶ በአሸባሪ ድርጅትነት ፈርጆ መወንጀሉ ይታወሳል፡፡
ይህ አደረጃጀት ከሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ (በይነ ሕዝባው) መብቶች አንጻር የጋረጠው አደጋ አለ ወይስ የለም?
በሚገባ እንጅ! ዋናው የፈጠረው ችግር ምን ሆነና? ዜጎች የመሰላቸውን ፖለቲካዊም ሆነ ማኅበራዊ አስተሳሰቦች የመከተል የማንጸባረቅ ሕገ መንግሥታዊና ሰብአዊ የሆነ መብት አላቸው፡፡ ይሄንን መብት በመጠቀም የመሰላቸውን የፖለቲካ ፓርቲ እንዳይደግፉ በአባልነት እንዳይሳተፉ በመሰላቸው ሕዝባዊ ማኅበራት ታቅፈው ለሀገራቸው ሊያበረክቱት የሚፈልጉትን አስተዋጽኦ እንዳያበረክቱ የሚከለክል የሚያሸሽ አገዛዙ እኔ የማስብላቹህን እኔ የምነግራቹህን አስተሳሰብ ብቻ ተቀበሉ የሚልበት አደረጃጀት በመሆኑ ይህ አደረጃጀት ከሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ (በይነ ሕዝባዊ) መብቶች አንጻር የጋረጠው ብቻ ሳይሆን ያደረሰውና እያደረሰ ያለው ጉዳትና አደጋ አለ፡፡ ወደፊት ወያኔ ዕድሜ ከሰጠው ይሄንን አደረጃጀት በመጠቀም ኢትዮጵያዊነትን አጥፍቶ ወያኔያዊነትን በቦታው ሊተካበት ያስባል፡፡ የምላቹህ ገብቷቹሀል? ወያኔ ምን ብሎ ያምናል መሰላቹህ? “ኢትዮጵያዊነትን ደብዛውን አጥፍቸ ወያኔያዊነትን በቦታው ስተካ ብቻ ነው ከተጠያቂነት ከታሪክ ተወቃሽ ተከሳሽነት ላመልጥ የምችለው” ብሎ ያምናል፡፡ ይህ የ1 ለ5 አደረጃጀት ማለት ኢትዮጵያዊነትን የሚያጠፋ በአንድ ጊዜ ሳይሆን ቀስ በቀስ በተለያየ ጊዜ እየፈነዳ ኢትዮጵያዊነትን የሚያፈራርስ በኢትዮጵያዊነት አካል ላይ የተጠመደ የሰዓት ፈንጅ (time bomb) ነው፡፡
ይሄ የገባው በርካታ ዜጋ መኖሩን እጠራጠራለሁ፡፡ የወያኔን ጥቅም የሚጻረሩ እንደ ታሪክ ያሉ የኢትዮጵያዊነት እሴቶች በዚህ አደረጃጀት ፊት እየተለቀሙ ይረሸኑና ከኢትዮጵያ ምድር እንዲጠፉ ይደረጋሉ፡፡ ወያኔ በራሱ ፍላጎትና ዓላማ ልክ የሚፈጥራት ታሪክና ማንነት አልባ አዲስ ሀገር ብቻ እንድትቀር ይደረጋል፡፡ ይሄንን አደረጃጀት ወያኔ እዚህ ድረስ ተስፋ ጥሎበታል፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ይህ አደረጃጀት ለወያኔ ሠራዊቱ በላይ “ለህልውናየ ትልቅ አቅምና ዋስትና ይሆነኛል” ብሎ ያስባል፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ በዚህ አደረጃጀት ያልታቀፈ ዜጋ በዚህች ሀገር መኖር እንዳይችል ኅብረተሰቡ ወዶም ይሁን ተገዶ እንዲያገለው እንዲተፋው የሚያስችል፣ ምንም ዓይነት መንግሥታዊ አገልግሎት እንዳያገኝ እንዳይፈጸምለት የሚያደርግ አጋንንታዊ ተንኮል ሸር አሻጥር የተሞበት አሠራር ቀርጾ አስቀምጧል፡፡ ይህ ነገር የመጽሐፍ ቅዱሱን የአውሬውን ማለትም የ666ን አሠራር አደረጃጀት ዓይነት መዋቅር የያዘ ነው፡፡ ለነገሩ እነሱስ የሱ መንገድ ጠራጊዎችም አይደሉ? ለዚህ ማስረጃ መጥቀስ አያስፈልግም ፀረ ቤተክርስቲያን መሆናቸውን ፍጹም እንግዳ በሆነ መልኩ በሸር ክፋት ሸፍጥ የተካኑ ቅንነት ደግነት ታማኝነት ፈጽሞ ያልፈጠረባቸው ጭካኔ የተሞሉ እኩዮችና እርኩሶች መሆናቸውን ማየቱ ብቻ በቂ ማስረጃ ነው፡፡ ወገኔ አንቀላፍተህ ዝም ብለህ በማየትህ ወያኔ የከፋ አውሬ ሆኖ እራሱን እንዲፈጥር ዕድል እንዲያገኝ አደረከው፡፡ ከዚህ በኋላ እያንዳንዷ ቀን ወያኔን እያበረታች እያፈረጠመች እያገዘፈች ትሔዳለች፡፡ ልናደርገው የምንችለው ነገር ካለ በተቻለ ፍጥነት ቶሎ ማድረግ ካልቻልንና ጊዜ ከሰጠነው አትድከሙ ወያኔ የሚነቀል አይሆንም፡፡
የቅድስት ድንግል ጽዮን ማርያም ልጅ መድኃኔዓለም ክርስቶስ ሆይ! በቃ ላትታደገን ነው? በቃ ላትምረን ነው? በቃ ይቅር ላትለን ነው? እባክህን ካንተ ይቅር? የፍጻሜ ዘመን ሰዎች መሆናችንን አስብ? ለንስሐ በቅተን ምሕረትህን እናገኝ ዘንድ ጸጸትና ትጋት ጨርሶ የማይጎበኘን የጥፋት ዘመን ትውልድ ነን፡፡ ደስ ስላሰኙህ ስለ ደጋግና ቅዱሳን እናት አባቶቻችን ብለህ ይቅር በለን? የአውሬው ኃይል ፍጹም ይበረታብን ይሠብረን ያደቀን ዘንድ አትፍቀድ? አንሣን? ነጻ አውጣን? ማረን? ይቅር በለን? አንተን የሚፈራ ለአንተ የሚገዛ ልብ ስጠን? ደስ የማያሰኘውን ሊመጣ ያለውን ክፉ የጨለማ ዘመን ከእኛ አርቅ? እባክህ ስለ እናትህ ስለ እናትህ ስለ እናትህ ብለህ? እንዲያው እ ባ ክህ? እባክህ? አሁንስ ተስፋ ቆረጥኩ ከሥራችን፣ ወደ አንተ ከመመለሳችን አንጻር ዐይተህ ከሆነ ልትምረን ይቅር ልትለን የምትፈልገው የዘመኑ ፍጻሜ ሰዎች እንደመሆናችን መጠን መቸም ልናደርገው አንደማንችል ስለማስብ እየባሰን እንጅ እየተሻለን አይሔድምና ምሕረትህ መቸም ላይጎበኘን ነው ማለት ነውና ተስፋ የመቁረጡ ስሜት ክፉኛ ተጫነኝ ትንፋሽ አሳጠረኝ፡፡ መቸ እንደሆነ ባላውቅም በምሕረት ወደኛ እንደምትመለስ ከቅዱስ ቃልህ አውቃለሁ፡፡ እባክህን ሩቅ አይሁን? አሁን ማር? አሁን ይቅር በለን? አሁን በቃቹህ በለን? ምህረትህን አሁን አድርገው?
ልዑል እግዚአብሔርን “የሠራዊት ጌታ ሆይ! እነኝህን ሰባ ዓመታት የተቆጣሀቸውን ኢየሩሳሌምንና የይሁዳን ከተሞች የማትምራቸው እስከ መቸ ነው?” ትን. ዘካ. 1፤12-17 ብለህ ጠይቀህ ለምነህ ተማጽነህ እግዚአብሔር በመልካምና በሚያጽናና ቃል ለልመናህ መልስ የሰጠህ፤ ኢይሩሳሌምንና የይሁዳን ከተሞች ልዑል እንደማረ ይቅር እንዳለ ያወጅክና ነቢዩ ዘካርያስ ሕዝቡን እንዲያበስር የላክ የእግዚአብሔር መልአክ ሆይ! ለእኛም እንደ ኢየሩሳሌምና የይሁዳ ከተሞች ሁሉ “ኢትዮጵያን የማትምራት እስከ መቸ ነው?” ብለህ ለምነህ እግዚአብሔር በምሕረት ወደኛ እንደተመለሰ ይቅር እንዳለ የምታውጅልን መቸ ነው? እባክህን ፍጠንልን?
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
The post 2.36, የ1 ለ5 አደረጃጀትና በሀገር ላይ የጋረጠው አደጋ! – ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው appeared first on Zehabesha Amharic.