Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

ሰሞናቱ። ዳ እና ቃ ….

$
0
0

SAmuel awee bu

ከሥርጉተ ሥላሴ 17.06.2015 /ሲዊዘርላንድ – ዙሪክ/

ሰሞኑን በርከት ያሉ ጸሐፊዎች በነፃነት ፍለጋ ሂደት ዙሪያ በርካታ ጹሑፎችን ጽፈው – አስተዬቶችን አነበብኵኝ። ወቀሳዎቹም ቢሆኑ መምህር ሆነው አግኝቻቸዋለሁ። በሌላም በኩል ላቅ ባለ ዝግጅት የተካሄደውን የኢሳት ዓለምአቀፋዊ ጉባኤንም ጊዜ ወስጄ – አዳመጥኩት። እርግጥ በጉባኤው እርዕስና ጭብጥ ላይ ቅሬታ ያለበት አንድ በፒዲኤፍ ጹሑፍ እዚህው ዘሃበሻ ላይ አንብቤያለሁ። ያም ነፃነት ነው። በሌላ በኩል ግን  አይደለም ለአፍሪካ ቀንድ ለመካከለኛው አፍሪካ፣  ለአህጉራችን ለአፍሪካና ለዓለም ሰላምና መረጋጋት በጠቃሚ ሃሳቦች ዙሪያ መወያዬቱ የሚበጅ እንጂ የሚጎዳ ሆኖ አላገኘሁትም – ተገኝቶ ነው። ከዚህም ሌላ በጸሎት መረዳዳቱም ይገባል። አባቶቻችን ስለሀገረ ኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ስለ ዓለምም ነው አብዝተው የሚጸልዩት። የዓለም ሰላም ለእኛም ሁነኛ ነውና። ዛሬ ዓለም እንዲህ በስጋት በተወጠረችበት ወቅት ችግሮችን ቁጭ ብሎ መነጋገሩ መልካም ነው። ዛሬ ያልተነሱ ሰበነክ ጉዳዮች ደግሞ ነገ ቀልብ ያገኛሉ። ዋናው መጀመሩ ነው። ወያኔ ሃርነት ትግራይ እያደባ ነው ትልሙን የሚፈጽመው እንጂ ለመካከለኛውም ምስራቅም ቢሆን ጊዜ የሚጠብቅ ፈንጅ ይኖረው – ይሆናል። ጠጠር ጥጥር እንጂ ጥጥ አይደለምና። ለማንኛውም እንደ እኔ እንደ ሥርጉተ ዕይታ ኢሳት ያሰናዳው ስብሰባ ምራቁን የዋጠ ነበር ማለት እችላለሁ፤  ከጊዜ ማነስ በስተቀር … ሳልጠግባቸው የቀሩ ዕርእሰ ጉዳዮች ነበሩ። ለአፍሪካም ቢሆን ጉልበታም ጉልህ የተመክሮ ማሳ ሆኖ አግኝቸዋለሁ። እንዲሁም ለሚዲያ ታሪካችንም፤ በተለይ የእንግሊዘኛው ውይይት ዓይን የከፈተ ሃላፊነትን የተጋራ ማለፊያ ዬአቅም ጅምር ነው። …

በስብሰባው ላይ አዳዲስ ሃሳቦች ተነስተዋል „እርቅ፤ ዬንጉሣዊ ሥርአት ዘመኑ በሚፈቅደው መልክ እንደ እስካንድብያ ሀገሮች ቢሞከሩ ወዘተ ..“ የሚል ጫሪ ሃሳቦች። እንደነዚህ ዓይነት ሃሳቦች መልካም ናቸው። እርግጥ ግጭት ይፈጥራሉ፤ የሃሳብ ጦርነት ያውጃሉ፤ ፍትጊያን ይልካሉ፤ ተከክተው – ተሰልቀው – ግን እንጀራን ይፈጥራሉ። ስለዚህ በህሊና ውስጥ የሚጉላሉትን ሃሳቦች እንዲህ አደባባይ አውጥቶ ከወዲሁ ወለሉን መደልደል ከተቻለ ነገ የሰመረ ይሆናል። እኔ ተመሳሳይ ሃስብና ውይይት አይማርከኝም፤ ይልቁንም ፍጭትና ግጭት ያላቸው፤ አቧራውን የሚያጨሱ ጠቃሚ ዕይታዎች ይመርኩኛል፤ ለዚህም ነው ግጭት ፍልጋ ብዕሬን የመንፈሴ ልዩ መልእክተኛ ያደረግኳት። ወጣ ያሉና የተለዩት አምክንዮዎች ቀልቤን ይስቡታል – ይማርኩኛልም።  ዬእኔማ – የእኔ ነው፤ የእኔውን ቀለማም ውብ የሚያድርግ ነው የሚፈለገው። ምክንያቱም የራሴ ብቻ ከሆነ – ይሰለቸኛል፤ አዲስ ሃሳብ ከእኔ ለዬት ያለ ሲቀርብ ግን ለመንፈሴ ድሎት ነው – ይመቸዋል። ስለዚህ አዳዲስ ሃሳቦች መፍለቃቸውን – ወድጀዋለሁ፤

ሌላው የሰሞናቱ ንፋስ ደግሞ የ2007 የምርጫን ሸሩባው በሚመለከት ምላጭ ላጥ አድርጎ አዲሱን ሹርባ እንደበላው ዜናዎች በግራ በቀኝ ይደመጣሉ። ያገባኛል የሚሉ ወገኖቼም አስተያዬታቸውን በቅናነትና በታታሪነት እዬሰጡበት ነው። እንዲያውም አዲስ ሥም በተካታታይ ጭብጥ ዙሪያ አይቻለሁ – በተቆርቋሪነት። ማለፊያ ነው።

ሁሉም የምርጫ ስኬት፤ የድል እርቀት፤ የተስፋ ዝግመት፤  ምከንያታዊ ናቸው። ከመነሻው ወያኔ ሃርነት ትግራይ ሥልጣን ላይ ከመውጣቱ በፊት ማንፌስቶውን ሲያዘጋጀው ነበር የገማ እንቁላል የነበረው። መቼም ከገማ እንቁላል የሚያድግ ጫጩት አይጠበቅም። ይህን ወያኔ ሃርነት ትግራይ ጫካ በነበረበት ጊዜ በቅርበት ይከታተሉት ከነበሩት እጅግ በጣም ጥቂት ወገኖች በስተቀር ወያኔ ሃርነት ትግራይን የርትህ አደባባይ አድርጎ የተመለከተው ምልዐት ነበር። „ከደርግ የባሰ“ አይታሰብም ነበር። ስለሆነም ይህ የምልዕት ታዳሚነት መወቀስ አለበት ወይንስ የለበትም? ለሚለው – ሳያዩ የሚያምኑ ጥቂቶች በመሆናቸው መወቀስ የለበትም። ማንም ዜጋ ከወያኔ ሃርነት ትግራይ ጋር ይሆናል መስሎት የሠራው – የተባበረው  – መንገድ የደለደለ፤ ጥሪውን የተቀበለ ሁሉ … ለወቅቱ ህሊናው የፈቀደለትን ተግባር መፈጸሙ ማንም የማይሰጠው ህጋዊው የነፃነቱ ማዕድ ነውና።

ለምን ተርቦ ማዬትና ስለ ራህብ ማድመጥ፤ ሰክሮ ማዬትና ሰካራም ማዬት፤ ሙሽራ ሆኖ ማዬትና ታዳሚ መሆን፤ መስማትና ማድመጥ፤ ማዬትና መስማት፤ ታስሮ ማዬትና እስረኛ መጠዬቅ አንድ አይደሉምና። ስለዚህም በስማበለው ሳይሆን ቀርቦ ማዬቱ ለውሳኔም ለመንገድም መልካም ነው።  „ቁርጥ ያጠግባል“ ይላሉ ጎንደሬዎቹ ሲተርቱ። ካዩት በኋላ ወጣ ገብ ያልሆነ፤ ቀጥ ባለ ውሳኔ የሰጡትን ድጋፍ መንጠቅ ብልህነት ነው። ወጣ ገብ ከሆነ ግን ጊዜ ይበላል ተስፋንም እያማለለ – እንዲህ ይሸረሽራል።

ያው እንደሚታወቀው ምርጫ በመጣ ቁጥር አዲስ ህብረት፤ አዲስ ፓርቲ ይኖራል። ያላዬነው – ያልሄድንበት መንገድ አለና እኛ የያዝነው ሃሳብ አሸናፊ ነው በማለት አዲሶቹ በአዲስ ተስፋ ጉዞውን ይጀምራሉ። ይህ ደግሞ አዲሱ በተፈጠረበት ጊዜ ወቅቱን አይቶ ስለሆነ ፕሮግራሙን የሚተለመው አዲስነቱን ያጎላውና ደጋፊ ይቸረዋል። በነገራችን ላይ – ወያኔ ሃርነት ትግራይ ዕድል ለቀጣይ ምርጫ ከኖረው ቀደም ብሎ አዲስ ፓርቲ ይፈጠራል። በሆነ አዲስ ሥያሜ።  አረንጓዴ ቢጫ ቀይ፤ ግሪን የለው ሬድ ወይንም ሰንደቅዓላም ወይንም ኢትዮጵያ ብቻ በሆነ ሥም ይፈጠራል። የዛሬ አዲሶች ከአምስት ዓምት በኋላ በሥራቸው የታሰረው ታስሮ፤ የተሰደደው – ተሰዶ፤ የበቀል መከርከሚያ የሆነው – ታጭዶ፤ የሞተው  – ሞቶ፤ የተፈታው ቤት ተፈቶ ቀሪው ነባሩ አሮጌ ይሆናል። ስለዚህ አሮጌው እኛ አይተነዋል አያዋጣም ቢል አዲሱ ደግሞ ኖ! እኔ የተሻለ አለኝ ብሎ ያው ፍልሚያውን – ይቀጥላል። ነባሮችን – ይወቅሳል። ወያኔም አጋጠመኝ ይልና አዲስ ገብ በማግኘቱ – ይፈነጫል። በዙርና በፈረቃ የሚደቃ ፈቃድ ማግኘት ሎተሪ ነው። … ስለሆነም ወያኔ ሃርነት ትግራይ ያዝ ለቀቅ እያደረገ አዲሱን እያባበለ መጋረጃ ጠባቂ ያደርገዋል። መጨረሻ ላይ ጉሩቦውን ተረግጦ ሚሊዮኖች ከኑሯቸው ያፈናቅላል ….. ያሻውን ደባ ማወራረጃ ያደርገዋል፤ ይህ በዙር የታየ የአምክንዮ ቁንጮ ነው።
awke
ይህ ለምን ሆነ? የወያኔ ሃርነት ትግራይን ተፈጥሮ  ዕውቀት ላይ „ሀ“ ላይ ስላለን፤ ምንአልባት አቡጊዳ የደረሱ ካሉ ዕድለኞች ናቸው። ቀላል ዬገበጣ ጨዋታ የሚመስላቸውም አሉ። „አብዮት አደባባይ የዛሬ ዓመት እንገናኛልን – የሚሉ።“ መሰረታዊ ችግራችን የወያኔ ሃርነት ትግራይን ተፈጥሮ፤ ሁለገብ የተከደነ አሉታዊ ሚስጢረ – ገብ ሴራ አናውቀውም። ከእኛ ይልቅ ክብርት ወ/ሮ አና ጉምዝ አሳምረው ያውቃሉ። ለዛውም ሃበሻ ሳይሆኑ። ሊቀል የሚገባው ግን ለእኛ በነበር። ምክንያቱም እኛ በደማችን ውስጥ ባሉ ጥበቦች ተመራምረን ልንደርስበት የሚያስችሉን ረቂቅ ህዋሶች – ስለነበሩን። ነገር ግን ሁልጊዜም ዳ  እና ቃ

ቀድሞ ነገር በሽታን ለማዳን ሃኪሞች በመዳህኒት ካልሆነም በገዶ ጥገና – ይገላግላሉ። እኛ በሽታችን እራሱ ገና አላወቅነውም። ሥም የለሹን በሽታ ካለማወቅ በመነጨ ለማናቸውም ጉዳይ „ቅድመ ሁኔታ“ ይጠዬቅበታል። ለታመመ መዳን ብቻ ነው አጀንዳው እንጂ ከመዳኔ በፊት ቅድመና ድህረ ድርድር ይደረግልኝ አይልም – በሽተኛው። እንዲያውም በሽተኛ „በሽታው“ የታወቀ ዕለት መዳኑን – መኖር መቻሉን ያረጋግጣል፤ ስለሆነም ደስ ይለዋል። ለዚህ ነው እንግሊዞች ችግርን ማወቅ 50% መፍትሄው እንደተገኘ የሚቆጥሩት።

ችግርን መሞከር ያስፈልጋዋልን?

ብዙ ጊዜ ስለወያኔ ሃርነት ትግራይ ተገልፆል በእሱ ላይ ጊዜ ማጥፋት አይገባም፤ ተዘውትሮ የሚደመጥ ክስተት ነው። እኔስ እላለሁ  ወያኔን – አናውቀውም። የምናቀለውም በዚህ ምክንያት ነው። ስለዚህ ቁጭ ብሎ መማር ያስፈልጋል። ለዚህም ነው ኢሳት አዘጋጅቶት በነበረው ጉባኤ  „ህግን“ በሚመለከት እነዛ ፍሬዎች – የተስፋ ገለጣቸው በአጭር ሲሆን ክፍት ያለኝ። ለምን? ወሳኙ ጉዳይ መማር አለመቻላችን በመሆኑ። በህግ ጉዳይ ምን መብት ምንስ ግዴታ እንዳለ አለማወቅ ብዙ ነገርን ያሳጣል። ዜጋ ነኝ። በዜግነቴ ላገኝ የምችለው ምንድን ነው? ዜግነቴ ብቻ ለእኔ ሊሰጠኝ ከሚገባው ምን ያህሉን አግኝቻለሁ? በዜግነቴ ብቻ በቀጥታ ላገኘው የሚገባኝን የከለከለኝ – ያገደኝ ምንድነው? አላውቀውም። ስለዚህ ትራሴን ከፍ አድርጌ ተኛሁ። ወይንም መነሻዬን የዜግነቴን አምክንዮ የጠቀጠቀው ማዕከላዊ አመክንዮዊ ጉዳይ ላይ አትኩሮት – ነፈግኩት፤ ወይንም ተስማሚ ብርሃን እንዳያገኝ አደረኩት፤ ወይንም ጠውልጎ እንዲረግፍ – ፈቀድኩኝ እኔው እራሴ ተከሳሽ በሌለበት ሁኔታ። እኔ ዜጋ መሆኔ ሳይኖር ነው ሌላ ጥያቄ የማነሳው። እነኛ ጥያቄዎች ግን ዜጋ መሆኔ ሲረጋገጥ በቀጥታ ከዜግነት መብቴ ጋር ካለ ፍርፋሪ ለማኝነት ማግኘት ያስችለኝ ነበር – ግን ተራራቅን። ስለምን ዜግነት ጽንሰ ሃሳቡን ከህግ አንፃር የመተርጎም ዕውቀት የለኝም። አልተማርኩ – ማ። ዜጋ መሆን ካልቻልኩ ግዴታ የለብኝም ማለት ነው። መብቴን ዬነጠቀኝ ግዴታውን አስኪያሟላ ድረስ ቁጥር አንድ ጥያቄዬ ዜግነቴን ማስከበር ይሆናል። መብቴን ሲያከብር ግዴታዬን እወጣለሁ። ግን ግንዱ ሥሩ ተዘሎ ቅርንጫፍ ጭፍጫፊው ላይ ነው አቅም እንዲህ የሚባክነው – የ“ዳ“ ዕዳ የ“ቃ“ም ግብዕት ተመቻችቶ መሰንጠቅ – መተርተር እንደ ግራምጣ፤ እንደ ሰበዝ – መሰበዝ።

ትልቅ ጉባኤ አይስፈልገውም፤ አጫጭር በራሪ ጹሑፎች፤ ፓስተሮች፤ አሰባሳቢ – አባባሎች፤ ውይይቶች፤ ንግግሮች ሁሉ የራሳቸው አስተዋፆ አላቸው። „አክሱም ለጋንቤላው ምኑ ነው“ ይህ ሠርቷል። የሄሮድስ መለስ የምጻት አገላላጽ የአራት ቃል – ትርፍ። ጋንቤላ እሳት ቢነድ፤ ጋሞ በአውሎ ቢናጥ፤ ድሬ በረዶ ቢወርድባት፤ ባህርዳር ነጎድጓድ ቢሰነጥቃት፤ መተማ የሱዳን ብትሆን ለሌላው ባዕዱ ነው። አያችሁ አንድ የአራት ፊደል ስንኝ ምን ያህል መንፈሳችን እንደ ቦረቦረው – ተሸናፊም እንዳደረገው? እንዴትም እንደዘረፈው – እትብታዊ የግንኙነት ሃዲዳችን። ስለዚህ ከአባባሎች ጀምሮ አዳዲስ መንፈስን የሚገሩ ተግባራት ላይ ማተኮር በእጅጉ ያስፈልገናል። አብሶ ፓርቲዎች፤ ንቅናቄዎች፤ ግንባሮች፤ ተቋማት ዬአባሎቻቸውን ህሊና በመገንባት እረገድ ተከታታይነት ያለው ተግባር ለመከወን ማቀድ ግድ ይላቸው – ይመስለኛል። ምክንያቱም የትናንት ችግር ዛሬም መኖሩ ብቻ ሳይሆን፤ ችግሩን ሊፈቱ በሚችሉት ላይ ሳይሆን አቅም የሚባከነው ችግሩን እንሞክረው በማለት – የሚቀጠፉት ነፍሶች በግፍ መርገፍ የልብ እሳት ነው። ለመሆኑ ችግር ስንት ጊዜ ነው የሚሞከረው? ዓመታት ጥለውን እዬሸራረፉን እዬነጎዱ ነው ያሉት። ወያኔ ሃርነት ትግራይን ያላገላጠ አንድም ዓለምአቀፍ የሰብዕዊ መብት ድርጅት የለም። ስለዚህ – የምናጋልጠው ወያኔን አብጠርጥረን በማወቅ ለወያኔ ሃርነት ትግራይ ማንፌስቶ ሽወዳ በራችን ስንቀረቅር ብቻ ነው። እንጂ ወያኔ ሃርነት የዘር አስተዳደር፤ እና አሸባሪ መሆኑ አሳምሮ አለም ያውቀዋል። ዓለም ባገለጠው ዕውነት ላይ የምልዕት መንፈስን ማደራጀት ነው ያነሰን። የፕሮፖጋንዳ ተግባር በር አያስከፍትም። ከተጨባጩ ከምድጃ የተነሳ የሃቅ አውድ እንጂ …..

ደወላትን (signal ‚ ponter) የማዳመጥ አቅምን ማሳደግ –

ድወሎችን የመተርጎም አቅም ማነስ ሌላው ችግራችን ይመሰልኛል። በ2002 ምርጫ „መድረክ“ የሚል ህብረት ስለነበር ህብረቱ አቅም ጉልበት አለው ስለዚህም አብላጫውን ወንበር የማግኘት ዕድሉ ሰፊ ነው ተባለ – ተሞከረ፤ ዛሬ የዛን ጊዜ የነበሩት አብዛኞቹ የሉም። ግን ካሳና ግብር ማገዶዎቹ አቶ አንዷለም አቶ ናትናኤል ሆኑ። አቶ አንዷአለም አራጌ ሲታሰር ጨዋታው አብቅቷል። በቃ! ወደ ክ/ሀገር ሲወረድ ደግሞ ገላጭ፣ ተገርጓሚ፣ ቃል አይገኝለትም። እስከ ዘንድሮው ምርጫ ድረስ የቋሳው ፖሊሲው – ይፈጫል። አሳዛኙ ነገር ሌላ አዲስ የቋሳ ስብስብ መንፈስ ሳይታከት በማሰናዳት ለወፍጮ ምርት አቅራቢ ከመሆኑ ላይ ነው።

መምጣት አይቀርም 5 ተቆጥሮ — 2007 መጣ። „የ2007 እንደምናሸነፍ እርግጠኛ ነን – እናውቀዋለን። ወያኔ ጓዙን ይጠቅልል“ የሚሉ መሪ ቃሎች ተደመጡ። ዋጥ ተደርገው ቢያዙ መልካም በሆነ ነበር። „ዬሚሊዮኖች ድምጽ ለነፃነትም“ ሰፊ ተግባር ከውኗል። በነገራችን ላይ አውሮፓ በዬአመቱ የሙዚቃ ውድድር ያደርጋል – በወል። ኢሮ ሶንግ ኮንቴስት /euro song contes / ይባላል። ከጉዳዬ ጋር ብቻ የሚያያዘውን ነው የማነሳው። ግን እጅግ በሰብዕዊነት ዙሪያ አብልጎ የሚሰራ፤ መንፈሱ ውብ ጠርን ያለው፤ ፉክክሩም ልብ ሰቃይ ብቻ ሳይሆን የአውሮፓውያኑን ባህልና መሰል ግንዛቤዎችን የሚያስጨበጥ ነው። ስለሆነም እኔ እታደምበታለሁ። ሰው – ሰው ነው። ሰው ጥበብን፣ በጥበብ ለማኖር እራሱ ጥበብ መሆኑን ማረጋገጥ ሲችል ብቻ ነውና።
Samuel Aweke
በዚህ ዓመት 60ኛ ዓመቱን ሲያከበር በ2014 አሸናፊ በነበረው ኦስትሪያ ቬና ላይ 40 የአውሮፓ ሀገሮችን፤ ከአህጉሩ ውጪ አውስትራልያን ለመጀመሪያ ጊዜ አሳትፎል። ቻይናም በቀጥታ ዝግጀቱን ታስተላልፍ ነበር። ማጠሪያውን ያለፉት 27 ሀገሮች ነበሩ። ከ27 ሀገሮች እስከተወሰነ ደረጃ በአንድነት መርቶ ሁለተኛ የወጣው „የሚሊዮኖች ድምጽ A Million Voices“ ዬPolina Gagarina የአርቲስት ፖሊና ጋጋሪን የራሽያዊቷ ነበር። አውስትርልያን ጨምሮ አውሮፓ ሀገሮች በሁለተኛ ደረጃ በፍቅር የመረጡት። እርግጥ አንደኛ የወጣው ዬሲዊዲን ነው። መንፈሱ „ሰው ጀግና ነው በተፈጥሮው“ የሚል ነበር። እርእሱ „ጀግና“ ይል ነበር። አርቱም ቅንብሩም እጅግ ያደገ ሥልጡን ነበር።  ወደ ጉዳዬ ስመለስ እንዴት ያለ ህሊናና መንፈስ „የሚሊዮኖችን ድምጽ ለነፃነት“ መርህ እንደ ነደፈ እጅግ ..  እጅግ በጣም ነበር ዬገረመኝ። በመንፈሴ ውስጥ የአንድነት ዓርማ ቤተኛ ነበር። አውሮፓውያንን መንፈስ በፈቃደ – ፍቅር ሰጥ አድርጎ የገዛም፤ በቂ አድማጭና አትኩሮት የተለገሰው ክብሩ ነበር። ይሄን ሞገድ ነበር –  ወያኔ ከሥሩ የነቀለው። ወያኔን  …. አቅልለን ስለምናዬው እንጂ እራሱን ለማቆዬት የሚያስችለውን በርግጫም በፍጥጫም የሚያዋጣውን መስመር እንደሚተልም – ይታወቃል። የላቀና የበለጠ – ተወዳጅና ተናፋቂ ነገ ማዬት ለወያኔ ሃርነት ትግራይ ማንፌስቶ ምጡ ነው።

ደወል አንድ – ወጣት ተደማጭነት ያላቸው ታሰሩ አብርሽ፤ ሃብታሙ አያሌው፤ የሽዋስ አሰፋ፤ ዳንኤልን ሺበሺ /አቶ/

ደወል ሁለት – የወያኔ ጋዜጠኞች ቢጨፈለቁ የማይተኩትን አንደበታችን ተመስገን ታሰረ /ጋዜጠኛና ጸሐፊ/

ደወል ሦስት – አንድነት ፈረስ / ብሄራዊ ተደማጭነት ያለው መጠነ ሰፊ ትልም ቀብር ተበዬነበት/

ደወል አራት – አርበኛ አንዳርጋቸው ታሠሩ – የኢትዮጵያን ህዝብ ምርጫ አልቦሽ በማድረግ ብቸኛ ሃብቱን ድምጹን ለታላቋ ትግራይ ህልም እንዲያውል – መንፈሱን ተዘረፈ …

ደወል አራት – የአውሮፓ ማህረሰብ ሆነ ሌሎችም ምርጫውን እንደማይታዘቡ አሰገነዘቡ።

ደወል አምስት – በቅድመ ምርጫ መሰናዶ ላይ ተፎካካሪዎች ሰፊ አፈና እስር እንግልት ተፈጸመባቸው ግን ጆሮ አልባ ነበርን?

ከዚህ ላይ ክብርት ወይዘሮ አና ጉምዝ ከአሜሪካ ድምጽ አማርኛው ፕሮግራም ጋር ካደረጉት ቃለምልልስ እንደተረዳነው ያልተገኙበት ምክንያት ዕውቅና ለወያኔ ሃርነት አለመስጠት ብቻ አልነበረም። „ወያኔ ሃርነት ትግራይን ለሚያቆላምጡ ዲታ ሀገሮችም እውቅና በመስጠት ሽፋን አንሆንላቸውም፤ የደራ የዜና ገብያ አንከፍትላቸውም“ ነበር ያሉት ግን አብዛኛውን ወንበር እንሸንፋልን በሚል ሙሉዑ ተስፋ ተሞከረ። ድምጽ ለተፎካካሪዎች የሰጡት ምን ይደርስባቸዋል በሚለው ላይ ብዙም ትኩረት ያልሳበ ዕሴት ነበር። እነኛ የነፃነት ናፊቂዎች አሁን ሦስተኛ ዜጎች ናቸው። ተራው የወያኔ ሃርነት ትግራይ አባል ሳይቀር ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ቁጫኑን – ይወጣባቸዋል። የመንፈስ ድቀቱና የሥነ ልቦናው ጫና ሌላው ያልተከፈለ ዕዳ ነው።

ጆሮ ቢኖር ሂደቱ ብቻውን ዬወያኔን የምርጫ ትልም ልናስተውልበት የምንችለው ቀዳሚ የህሊና ሰብል በነበር። ነገር ግን ችግር ፈተና ይሁን ሞት ተሞከረ – ሆነም። ለምን? አበጥረን አናውቀውማ – ወያኔ ሃርነት ትግራይ የተመሰረተበትን አመክንዮ። ሥሙን እንኳን በድፈረት ለመጥራት አንችልም – እንኳንስ ጥንስሱን – ዝልሉን – የመርዝ ድፍድፉን ለመተርጎም …. እና እኔው እምለው የወያኔ ሃርነት ትግራይ ማንፌስቶ ቁጭ ብሎ ማንበብ፤ ማጥናት፤ ተያያዥ ህጎቹ፤ የአፈጻጸም መመሪያዎቹ ለምን? ስለምን? እንደተረቀቁ እንደ ጸደቁም ልብ ገዝቶ መመርምር ያስፈልጋል። አሁን በዚህ ምርጫ ዘመዱ የሆኑትም ቢሆኑ ለአሁን ብቻ ነው። በሚቀጥሉት ጊዜ አይስፈልጉትም – እረክሳዋል ብሎ ቆሻሻ ውስጥ ይጨመርና አዲስ አመላቸው የማይታወቁትን ዱቅ ያደርጋል። ወያኔ ሃርነት ትግራይ በትጋትና በታታሪነት እዬሠራ ነው – ለታላቋ ትግራይ ህልሙ። ተፎካካሪዎች አብዛኛውን ወንበር እንሸንፋልን ዬሚል ተስፋ ነበራቸው – ባልከፋ፤ ግን ቀድሞ በህግ የታሰረ ስለሆነ ሰማይ ከፍ ምድር ዝቅ ቢል እንዲህ በቀላል የወረቀት ቅልቅል ማስፈታት አይቻልም – ተቆልፏል። „ቁርጥ ያጠግባል“ – ሃቁ ይህ ነው።… በተአምር ወያኔ ሃርነት ትግራይ ስለ ሰብዕዊ መብት፤ ስለመናገር ነፃነት፤ ስለ ህዝብ በደል ብናኝ ጊዜ በክርክር ሸንጎው ላይ ማቃጠል አይሻም። በጎጥ በተጠረገ አስፓልት እራሱን እያዳመጠ ሌላውን መዳጥ ….

የሚገርመው አቤቱታ አቅራቢም እኛው፤ አቤቱታም ሰሚው እኛው፤ እለቅሶ ተደራሾችም እኛው፤ አልቃሾችም እኛው — ከሁሉ የሚከፋው ግን ቀደም ብዬም በተከታታይ ጹሑፎቼ በራዲዮ ፕሮግራሜ እንደገለጽኩት ይሆናል መስሎት ጥግ አልባ የረዳ፣ የተባበረ እዬታደና እስር ቤት መወርወሩ የባሩድ እራት መሆኑ —- .። እንደርስለታለን ….? ለራሳችንም አቅም የለንም እንኳንስ በዬምርጫ ጣቢያው ከጥርስ የገባውን ህዝብ እና ሰፈር ለማዳን …. በብሄራዊ የተፎካካሪ ፓርቲዎች ሊቀመናብርት ላይ ወያኔ ካቴና የሚያስበው ሲያሰጉት ብቻ ነው። ካላሰጉት ታች ያለውን መሠረቱን ለመናድ ሴሉን – ያፈርሳል። ለፕሮፖጋንዳውም „ከእነሱ አልደረስኩም ያጠፋ ግለሰብ ነው ያሰርኩት“ ይላል። የተፎካካሪ ሊቀመናብርት እንደልባቸው – ይናገሩታል፤ አያስራቸውም፤ ለውጪ ዜና መልካም – ቅዳሜ ገብያ //// ለነገሩ ቧልትም ጎጥም ሀገርን በመምራት ደረጃው ቧልት ይመሰልኛል። መሻል – ይጠይቃል።

መማር ያለመቻላችን መሰረታዊው ምክንያት የወያኔ ሃርነት ትግራይ የተፈጠረበትን መሰረታዊ ሥነ ምግባር አለማወቅ ብቻ ነው። አሁን ወያኔ ሃርነት ትግራይ ሥልጣን ላይ ስላለ ብቻ አይደለም፤ ሌላማ ጎሳዊ ድርጅት ወንበሩን ቢይዝ ይሄው ነው። የሚያስበው ለራሱ ብቻ ነው። የሚቆረቆረው ለራሱ ብቻ ነው። የሚያሳድገው የራሱን ልጆች ብቻ ነው። ስለዚህ ከዚህ የራስና የግልዮሽ ጥብቆ ዕዬታ መውጣት የሚቻልበትን መንገድ ስንተልም ብቻ ወያኔን ማሸነፍ እንችላልን። ወያኔ ሃርነት ትግራይን አወቀነዋል ማለት የሚቻለውም ድል የሚደርጉትን እርምጃዎች ስናሰብል ብቻ ይሆናል። በሥነ ልቦና ማሸነፍ በራሱ የወያኔ ሃርነት ትግራይ ሥልጣኑን ከመልቀቁ በፊት መንፈሱን ማሟሸሽ ያስቻላል። ጎሳን አንጋሽዎች ጎሳና ጎጥ ዋጋ ቢስ መሆኑን ስንመሰክር፤ ቁመን ስንሰብክ፤ ሐዋርያ  ሆነን ስንገኝበት ብቻ ሃይላችን ከዛ ይቀዳል። ዬትም ቦታ መከራን አብዝተው የሚቀበሉት ወገኖቻችን „ኢትዮጵያዊ“ በመሆናቸው ብቻ ነው። መፍትሄ አምንጪውም ሆነ መንገድ ጠራጊውም፤ የስሜትና የፍላጎት ገዢውም በዚህ ማዕፍ ውስጥ የተጠቃለልን ዕለት ሚስጥርና እኛ እኛና ሚስጢር ጥምረት አይደለም እእ – ጋብቻም አይደለም እእ በአህቲነት  – እንፈጠራለን። እንደገና መፈጠረ —– ችግርን ለመመንጠር – የጎጥን ሴራ ስንንድ — ግን ነገር ግን – አሁንም ቅድምም “ኢ“ ተትታ – ተንቃም ኦ. ት. ኡ. ሱ. አ እያልን እምንተክዝ ከሆነ ዕንባን ዋጥ አድርጎ መቀመጥ።

የሚከብዱ – ስምምነቶች፤ የሚያቃቱ – ፈተናዎች መበራከት የመግባባት ሂደቶች ጨዋታው ያለው ዬወያኔ ሃርነት ትግራይን ተፈጥሮ ካለማወቅ የሚመነጭ ነው። የወያኔ ሃርነት ትግራይን ሥነ ደንብ ለመተርጎም አቅም ስለሚያነስን ብቻ ነው። የወያኔ ሃርነት ትግራይ ተልዕኮን ከጥላቻ አልፈን የጥላቻው ችግኝ ዕድገት እንዲገባን ለራሳችን ስለማንፈቅድለት ነው፤ እንጂ ማንይሙት እፍኞች 24 ዓመት እንዲህ አንበርክከው መፍለጥ ባልቻሉ ነበር። ለእኔ የግንዛቤ ችግር አለብን – የወያኔ ሃርነት ትግራይን የመሰሪነት – ህጋዊነት፤ የተንኮለኝነት ሴራው ምንጩ መነሻው መድረሻው ሆኖ ሳለ፤ እኛ ላዩን እንጂ ነፍሱን ገና አለገኘነውም። ለዚህም ነው አድጎ መሄድ የቻለውን እንኳን ለማስተናገድ ህሊናችን አሻም በማለት ራሳችን የራሳችን የህሊና ሃብት ስንነቅፍ፤ ስናሳድድ የምንገኘው። ባደገው ወይንም ለግለግ ብሎ በወጣው ላይ ያነሰው ምንድን ነው? አፈር? ማዕድን? ውሃ? የጸሐይ ብርሃን? ያ አይደለም ጭንቀቱ —- እህሳ – ኮፒራይት … ወያኔ ሃርነትን ያህል ጠላት አስቀምጦ – ለመደርምስ መፍቀድ፤ ለመፍለስም።

ስለዚህ አቅም ያላቸው ወገኖች ሌላ ቦታ ሳይሄዱ፤ ወጪም ሳያቃጥሉ እራሳቸውን – ይዳኙ። እራስን መዳኘትም – ሌላው የአቅም አመክንዮ ነው። ምክንያት መሆን የለባቸውም – ለብርሃን ግርዶሽ በመሆን። አንድ ታሪክ ትዝ አለኝ። አንድ ወንድሜ የሚሆን መርጌታ አሞት ሁዳዴን ገደፈ እና ለእኔ ነገረኝ። ታዲያ ምን አለበት ለሌሎችስ ብትነግራቸው ታመህ ነው አልኩት „ለሌሎች መሰናከያ አልሆንም“ አለኝ። ብልህነት ነው። ሌላም አንድ ልከል ጀርመን ውስጥ ቤፋውቤ (BVB) የሚባል የእግር ኮስ ቡድን አለ። በጣም ታዋቂ ነው። ታዋቂነቱ ዘንድሮ እዬቀነሰ፣ አቅሙም እዬመነመነ ሲመጣ – ባልታሰበ ቀን ከ7 ዓመት በላይ ያሰለጠኑት ጀርመንን ለዋንጫ ያበቀውን ጎትሰንና መሰሉን ሳተና ወጣቶችን ያፈረቱ ታላቅ አሰልጣኝ በድንገት „እለቃለሁ“ አሉ። ሥራ ፈላጊም እሆናለሁ አሉ። አስደንጋጭ ነበር። ጋዜጣዊ መግላጫቸው አጭር ነበር „ …. እኔ ከዬትኛውም የእግር ኳስ ቡድን ቡድን ጋር ውል የለኝም። ስለሆነም በቀጥታ ሥራ ፈላጊ ነው የምሆነው። ቁጭ ብዬ ሳስበው እኔ ከቦታው እያለሁ እያደገ መሄድ የሚገባውን የቡድኑን ዕድል ላጨናግፍ አይገባም። እኔ ስለቀው ያድጋል“ በቃ የአንድ እግር ኳስ አስልጣኝ ደሞዝ በወር ምን ያህል እንደሆነ ታውቁታላችሁ። ክብሩም ሞገሰም ወዘተ …. ለዛውም በ2015 በለስ ቀንቶት BVB ለሀገሩ የዋንጫ ውድድር መድረስ ችሎ ነበር ባያሸንፍም ….

ስለዚህ እንቅፋት የሆንባቸው ቦታዎች ካሉም፤ በቅንነት – በሙያችን፣ በተመክሯችን እያገዝን ዞር ማለቱም የሚበጅ ይመስለኛል። ይህን ማለቴ የአመራር ተከታታይነት ይሰረዝ ማለቴ አይደለም። መርህ ብቻ ሳይሆን ካለእርሾ ሊጥ አይቦካምና …. የሆነ ሆኖ ሁልጊዜ አዲስ የምንሆንበት ምክንያት፤ አዲስ ፓርቲዎች በመፍጠር ችግሮችን የምንፈታቸው የሚመስለን ምክንያቶች ዕልባት ሊሰጣቸው ይገባል። ወይንም ህብርት በፈጠርን ቁጥር ድሉን ቅርብ አድርገን ተስፋ የምንደርገው ሁነት ሁሎቹም ሲደመሩ ሲባዙ የወያኔ ሃርነት ትግራይን ተፈጥሮ ካለማወቅ ይቀዳሉ። ስለዚህ መሥራት ካለብን መሠረታዊ ጉዳይ ትልቁ መንፈስን በመስኖ ማልማቱ ላይ ነው። ከዚህም በላይ ባለቤት የሌላቸው ጹሑፎች ይበተናሉ እነሱም የሚያሳድሩት ተጽዕኖ ቀላል አይደለም። ለምን? የሚመከት ተግባር ለመከወን አቅምን ስለሚበሉ …. ከእነዚህ መሰል ጉዳዮችም ነፃነት ፈላጊ ቅን ዜጋ መታቀብ በእጅጉ አለበት። መከራው ከመረረን፤ መርዶው ከጎመዘዘን፤ የዛሬ 20 ዓመት በጎሳ ዛሬም በጎሳ ተደራጅቶ ጎሰኝነትን አምልኮ ጎሰኛውን ዘውደኛ ማሸነፍም አይቻልም – በፍጹም። ኢትዮጵያ ኢትዮጵያውያን ሳታዳላ የመገበች የግብር – ማዕዶት ናት። ዛሬ መከራውን ለመሸምገል ግን እንደ ሥጋ ቀረመት ላይ ተሆኖ ሳይሆን ውስጧን በመሆን ብቻ ነው። የምትፈልገው እናት የልጆቿን አብሮነትና አንድነት ብቻ ነው።

ወቀሳ።

ወቀሳው እራስን፤ ነቀሳው እራስን ….. ዳኝነቱ እራስን፤ ኩነኔውን ወደ እራስ፤ ሃጢያቱን ወደ እራስ እንጂ ሃይልና አቅምን ነፃነት የተፈለገበት ምክንያት ላይ …. መለቀቅ የተገባ አይደለም። አለሎ ድንጋይ እዬፈለጉ አናት ሲፈልጡ እራስን በዙር እንደሚፈልጥ ማስተዋል የሚገባ ይመስለኛል። „ወያኔ ሃርነት ትግራይ ኮረጆውን በሙሉ ዘረፈ፤ ሟጠጠ¡“  ምን አዲስ ነገር አለው? ከጎሳ ድርጅት ፓሊሲ የሚጠበቅ ነው። እኛም በጎሳ መንፈስ ውስጥ ነው ያለነው። … „የዘንድሮው የባሰ የበዛ ነው¡“  ትናንትም በሞት ተሞከረ ዛሬም በሞት 2007 ተዘከረ። ምንአልባት የትናንቱን የእኔ ወይንም የእኛ ብለን ሳናስጠጋው ቀርተን ካልሆነ በስተቀር ሲጀመር ጀምሮ ይሄው ነው። 4 ዓመት ተስድስት ወር የለሁም፣ ከዛ እባንና ከማይክ ጋር እገናኛለሁ። በማይኩ ጀርባ ግን በድምጹ ልክ ለወያኔ ሃርነት ትግራይ የበቀል ፓሊሲ ጥሬ ሃብት አቀርባለሁ – ለዛውም የሰው ልጅ። ከእኔ እስካልደረሰ ሌላው መሞከሪያ ይሁን በቃ — አራት አመት ከስድስ ወሩን ግን ደሙ ሲፈስ፤ ሲታሰር፤ ተደብድቦ ሆስፒታል ሲገባ፤ ለድርጅቱ ሲል በካቴና ሲጠረነፍ ቤተሰቡን ተገኝቶ በማጽናናት፤ ህዝቡን በአብሮነት ላይ በማሰለፍ፤ መንፈሱን ለማልማት ሰሚናሮችን፤ ወርክሾፖችን እስከ ታች ድረስ ወርዶ መልክ ለመልክ ለመተያዬት ሙከራው – እሩቅ ነው። ሌላው ቀርቶ በክንድ እቅፍ ውስጥ አንድን የነፃነት ራህብተኛ መቆዬት እራሱ እኮ ልዩ መንፈስን ይለግሳል።

መቋጫ – አንድ ጹሑፍ ላይ „ማረድ“ የሚል አንብቤ ነበር። ስለቃሉ ከብራናዬ ላይ ለማዋል እዬሰቀጠጠኝ ነው የጻፍኩት። በጉልህ ይህ አስፈሪ ቃል የሚያመልክተው ፋይዳ ህሊናን የማልማት ተግባር ምን ያህሉን እንደከወን የሚያሳይ አሉታዊና አዎንታዊ ናሙናችን ነው። —አዎንታዊ የተገበርነውን ሪፖርት ገላጭነት መሆኑ ሲሆን፤ አሉታዊ ደግሞ በሰውና በአራዊትነት መሃከል ያለውን ልዩነት በጥበት ስለሚወጥረው ነው። ሰው እንዴት ይታረድ? አንደኛ ደብዳቢነቱ – በማህያ ነው ይሸጎጥለታልም – በፋሽስት በምትመራ ሀገር። ሁለተኛ ደብዳቢነቱ በበቀል በወረዛ ፖሊሲ ሥር ነው። አንድ ወንጀለኛ „በማረድ“ ይወገድ። ሥርዓቱ ፓሊሲው ስለሆነ ሌላ ይተካበታል ሌላ ነፍሰ በላ። ስለዚህ መቀዬር መለወጥ ያለበት የሥርዓቱ ፓሊሲ መሠራች የሆነው ማንፌስቶው ነው። ያም የወያኔ ሃርነት ትግራይ የጎሳ ማንፌስቶ፤ እሱን እንታገለዋለን የሚሉትም እራሳቸውን እንዲዳኙ በአክብሮት አሳስባለሁ። ከጎጥ የሚመነጭ ማናቸውም መንፈስ ለብዙሃኑ ኢ- ሰብዕዊ፤ ኢ – ህጋዊ ነው። ጎጠኝነት ለጥቂት ድሎት ለብዙኃን መከራን በህግ ማረጋገጥ ነው። ስለሆነም ከጎጥ መንፈስ ጋር የሙጥኝ ያሉት ሁሉ ቁጭ ብለው እራሳቸውን ለመዳኘት ጊዜ ይኑራቸው። ደም ማዬት ስቃይ ማድመጥ ከአንገፈገፋቸው –

የሆነ ሆኖ ወንጀለኛነትን  „በማረድ“ መፍትሄ አይገኝለትም። ለዛ ሰውኛ ላልሆነ መንፈስ እራሱን ዳኛ በማደረግ እንደገና ከአራዊትነት ወደ ሰውነት በማሸጋገር በሚካሄድ ተከታታይ የመንፈስ ተግባር ነው መለወጥ የሚቻለው፤ „አራጁም“፤ ደብዳቢውም፤ ገዳዩም፤ ኮረጆ ገልባጩብም፤ ጭካኔው እራሱን እንዲደበድበው መልሶ እንዲጎርሰው ህሊናውን በሰብዕነት ተፈጥሮ መግራት፤ እንዲጸጽተው፤ እንዲያርመጠምጠው፤ እንዲወቅሰው በማድረግ ፈቃደ ህዝብ ነፃ ይወጣል። ከቀላል ጠላት ጋር አይደለም ግብግቡ – ሁሉም ካለው ዘመንተኛ ጋር ነው። ለራሳችን መልስ የሚሆነው ብቸኛው ዘዴ ከበዳዩ የጎጥ ድርጅት የተለዬ አቅምን ማሳደግ ሲቻል ብቻ ነው። ምርጫ ለአንድ ሀገር አንድ ዘላላ ጉዳይ ነው። ከዛ የገዘፉ በርካታ መንገዶች ላይ ቢተኮር የዛሬ የወያኔ ሃርነት ትግራይ መሪ ተዋናይ የነገ የአብነት አጋር ሊሆን ይችላል። ፍላጎታችን ስናዘገዬው „ዳ“ ራዕያችን በዝግመት ስናድርቀው „ቃ“ የሁሉ መከራ ተሸካሚ ደግሞ የኢትዮጵያ ህዝብ – ። ቁልምም እንዳለ ድፍት ክፍት እንዳለ እርግፍ ….

ለነበረን መልካም ጊዜ መልካሙን ተመኘሁ። መሸቢያ – ጊዜ።

  • „ማረድ“ እባካችሁን ወገኖቼ እንዲህ ያለ ጥቅርሻማ መንፈስን አታስጠጉት – መንፈሱ የባህሩ ነውና። እኔ እንጃ ሀገሬ ኢትዮጵያ ብሄድ ከእንግዲህ በኋላ ዶሮ ወይንም በግ ከፊቴ ታርዶ ደሙን አይቼ በፍጹም አልበላውም። ተመጣጣኝ እርምጃ፤ የሚመክት እርምጃ ማለትም ይቻላል …. ይህን የገሃነም ቃል ወደ ድርጊት ተለውጦ የማዬት ራዕይ ማለም ነገን አያመጣም ዛሬንም አያሰጥም።

ለእኔስ ሰው መሆኔ ብቻ ይበቃኛል። እግዚአብሄር ይስጥልኝ።

The post ሰሞናቱ። ዳ እና ቃ …. appeared first on Zehabesha Amharic.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>