(ተመስገን ደሳለኝ)
…አውሮፕላኑ ቅዳሜ ጠዋት ሶስት ሰዓት ላይ ድሬዳዋ አየር ማረፊያ ደርሶ ከተርሚናሉ ስወጣ፣ ተጠራጥሬ ሰዓቴን ተመለከትኩ፤ የድሬ የጠዋት ፀሐይ ከተለመደው ንዳዷ ጋር የአዲስ አበባን የቀትር መራራ ፀሀይን ታስከነዳለች፤ እናም አጥበርባሪ ጨረሯን ያለምህረት ስትለቅብኝ፣ ጓደኛዬ መኪና ይዞ እቦታው እስኪደርስ መጠበቁ በገዛ ፍቃድ መለብለብ ስለመሰለኝ፣ በቀጥታ ከተደረደሩት ታክሲዎች አንዱን ይዤ ወደ ከዚራ አመራሁ፤ ድሬ የሄድኩት በዋናነት ከማህበራዊ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ምክንያት በመሆኑ ሊቀበለኝ የተዘጋጀውን
ጓደኛዬን ደውዬ ከማውቃቸው የአንዱን ሆቴል ስም ጠቅሼ እዚያ እንድንገናኝ ነገርኩት፡፡
የሆቴሉ ፍተሻ ከወትሮው ጠንከር፣ ጠጠር ያለ በመሆኑ ትዕግስትን ይፈትናል፡፡ እንዲህም ሆኖ ወደ ውስጥ ስንዘልቅ ማረፊያ ክፍሎች በሙሉ መያዛቸው ተነግሮን ቀኝ ኋላ ለመዞር ተገደድን፤ ይሄኔም ነው የጓደኛዬ ፊት ልውጥውጥ ሲል ያስተዋልኩት፤ ጭንቅላቴን በማነቃነቅ በምልክት ምን እንደተፈጠረ ጠየኩት፤ ለአፍታ አመንትቶ ከፊት ለፊታችን በግምት አስር ሜትር ርቀት ላይ ወደቆሙ ሁለት ሰዎች ጠቆመኝ፤ ልብ ብዬ አየኋቸው፤ ሁለቱንም ከዚህ ቀደም አይቻቸው አላውቅም፤ ደግሞም በዙሪያችን ከሚርመሰመሱ ሰዎች የተለየ ምንም አይነት ሁኔታ ላስተውልባቸው አልቻልኩም፤ እናም ወደ ጓደኛዬ ዞሬ በግርታ ግንባሬን ቋጥሬ ጥያቄ በተሞላ ዓይን አተኮርኩበት፤ ጓደኛዬም ከሁኔታዬ እንዳልገባኝ ተረድቶ ከሹክሹክታም ዝቅ ባለ ድምፅ ‹‹ደህንነቶች ናቸው፣ እየተከታተሉህ ነው›› አለኝ፤ ቢሆኑስ ታዲያ!? በግዴለሽነት ትከሻዬን እየሰበቅሁ ‹‹ለራሳቸው ጉዳይ መጥተው ሊሆን ይችላል›› ብዬው ወደ ሌላ ሆቴል አቀናን፤ እዛም የተለቀቀ ክፍል አለመኖሩ ተነግሮን ፊታችንን ከእንግዳ መቀበያው ‹‹ዴስክ›› ዘወር ስናደርግ እነዛ ‹ደህንንቶች› ቆመው ተመለከትኳቸው፡፡ አሁን ከልምዴ በመነሳት ክትትል ሊሆን እንደሚችል ለማመን በተቃረበ ጥርጣሬ ተውጬ ሌላ ሆቴል ደርሰን ክፍል ጠየቅን፤ በለስ ቀናንና የሆቴሉን መስፈርት አሟልቼ ሳበቃ ጓደኛዬን ቡና ቤቱ ውስጥ እንዲጠብቀኝ አድርጌ፣ ክፍሉን ከተረከብኩ በኋላ ሻንጣዬን አስቀምጬ፣ ገላዬን ተለቃልቄ፣ ልብስ ቀይሬ ደረጃውን መውረድ እንደጀመርኩ ከሰዎቹ ጋር ፊት ለፊት ተገጣጠምኩ፡፡ የጭንቅላት ሰላምታ ሰጥቼ አለፍኳቸው፤ ምላሽ የለም፤ ፈገግ አልኩ፡፡ ከወዲሁ የሰሞኑ ምስራቅ ኢትዮጵያ አክራሞቴ ምን ሊመስል እንደሚችል አሰብኩና፣ በልጅነቴ ከሰፈር ማቲዎች ጋር የምንጫወተውን የአኩኩሉ ድብብቆሽ አስታውሼ፣ በድጋሚ ለራሴ ፈገግኩ፡፡
ገና ከአዲስ አበባ ስነሳ ማህበራዊ ጉዳዬን ስጨርስ የድሬዳዋ፣ ሐረር እና ሶማሌ ክልልን ወቅታዊ የፖለቲካ ትኩሳት ለማዳመጥ ለተጨማሪ ስድስት ቀናት የሚያቆይ ፕሮግራም አስቀድሜ ይዤ ነበር፤ ከአራት ቀን ቆይታ በኋላም ቀጥታ ወደዚሁ ስራዬ ነበር የገባሁት፡፡ ለጉዳዩ ትኩረት እንድሰጥ ያደረገኝ በቅርቡ ሐረር ከተማ ውስጥ በተከበረው ‹‹የዓለም የመቻቻል ቀን›› ላይ በክልሉ የተንሰራፋው መድልዎና የሐብሊ ተፅዕኖ ተደብቆ፣ ፍትሐዊ አስተዳደር የሰፈነ ለማስመሰል መሞከሩ፤ እንዲሁም ህዳር 29 ቀን በሶማሌ ክልል ዋና ከተማ ጅጅጋ (ጅግጅጋ) የሚከበረውን ‹ስምንተኛው የብሔር ብሔረሰብ ቀን›ን አስመልክቶ አካባቢውን ከዋጠው ስጋት በተቃራኒው መንግስት እየነዛ ያለው የሀሰት ፕሮፓጋንዳን ከተጨባጩ እውነታ ጋር ለመፈተሽ ፍላጎት አድሮብኝ ነው፡፡
ፊታችሁን ወደ ምስራቅ…
ምስራቅ ኢትዮጵያ ከሀገሪቱ የ3ሺ ዓመት ታሪክ ዕኩሌታውን ሰላምና መረጋጋት የተሳነው ከመሆኑም በላይ፣ ለማዕከላዊ መንግስት የስጋት ምንጭ ሆኖ ነው ዛሬ ድረስ የቀጠለው፡፡ ከአቶማን ተርኪሽ ወታደሮች እስከ አል-ሸባብ ሰርጎ ገቦች ድረስ መተላለፊያ ‹‹ኮሪደር›› ሆኖ አገልግሏል፡፡ በተለይም የኢትዮጵያ ሶማሊያውያን የዘር ግንድ ከጐረቤት ሀገራት ሶማሊያና ጅቡቲ ጋር የሚተሳሰር መሆኑና የሃይማኖትና የኢኮኖሚ ምንጭም ተመሳሳይነት አካባቢውን በበቂ ደረጃ ለመቆጣጠር አስቸጋሪ እንዳደረገው የፖለቲካ ተንታኞች ያምናሉ፤ ነዋሪዎቹ በቀላሉ ከአንዱ ሀገር ወደ ሌላው እየተዘዋወሩ የሚኖሩ መሆናቸውም ሌላው ችግር እንደሆነ ይጠቀሳል፡፡ ቅኝ ገዥዎቹ የአውሮፓ ሀገራት በበኩላቸው አካባቢውን ‹ፍሬንች ሶማሌ ላንድ›፣ ‹ብሪታኒያ ሶማሌ ላንድ› እና ‹ኢታሊያ ሶማሌ ላንድ› በሚል ከፋፍለው ማስተዳደራቸው፣ ከሶማሊያ ነፃነትም በኋላ የሞቃዲሾን ቤተ-መንግስት የተቆጣጠሩ ገዢዎች ‹ታላቋን ሶማሊያ እንመሰርታለን› በሚል ቀቢፀ ተስፋ ከአንድም ሶስቴ የኢትዮጵያን ወሰን ተሻግረው የኃይል ወረራ መፈፀማቸው የአካባቢውን ውጥረት ይበልጥ አባብሶት ነበር፤ ከዚያም ባሻገር የዚያድባሬ ሶማሊያ መፈራረስም የቀጠናውን ሠላምና ፀጥታ ከድጡ ወደ ማጡ አድርጎታል፡፡
በዚህ ሁሉ ከባቢያዊ ውጥረት እየታመሰ እስከ 1983 ዓ.ም. ድረስ በአንድነት በሐረርጌ ክፍለ ሀገር ስር ሲተዳደር የቆየው የምስራቁ የሀገራችን ክፍል፣ ኢህአዴግ ወደ ስልጣን ሲመጣ ባነበረው ‹‹ፌደራሊዝም›› በሶስት ሊከፈል ችሏል፤ ‹‹የሶማሌ እና ሐረር ክልል›› እንዲሁም ‹‹የድሬዳዋ አስተዳደር›› በሚል፡፡ ይህ ሁኔታም ከዚህ ቀደም በውጭ ተፅዕኖ ይተራመስ የነበረውን ‹ጂኦ-ፖለቲክስ› ብሔር ተኮር ለሆነ ተጨማሪ አዲስ ቁርቁስ አጋለጠው፡፡ በአናቱም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይ ኦጋዴን፣ ጎዴ፣ ደጋሀቡር፣ ቀለፎን የመሳሰሉ ከተሞች ክልሉን ‹እንገነጥላለን› የሚሉት የኦጋዴን ብሔራዊ ግንባር ታጣቂዎች መርመስመሻ መሆናቸው አካባቢውን የስጋት ቀጠና አድርጎታል፤ ይህንን ጉዳይ በተመለከተ ድሬዳዋ ላይ ያነጋገርኳቸውና በሽግግር መንግስቱ ወቅት የአስተዳደሩ አባል የነበሩ አቶ ኡስማን (ለዚህ ፅሁፍ ስማቸው የተቀየረ) ‹‹የዚህ ሁሉ ተጠያቂ ለጣልቃ ገብነቱ ያልተመቹትን የአካባቢው ልሂቃን ‹ለወረራ የመጡ የዚያድባሬ መኮንኖች› እያለ አሸማቅቆ ከፖለቲካው ገፍቶ በማስወጣት ክልሉን ዛሬ ላለው ደካማ አስተዳደር የዳረገው ኢህአዴግ ነው›› ይላሉ፡፡ በግልባጩ የፌዴሬሽን ም/ቤት አፈ-ጉባዔ ካሳ ተክለብርሃን የተገፉት ሰዎች ኢትዮጵያዊ አለመሆናቸውን ለ‹‹ዘመን›› መፅሄት የገለፀው እንዲህ በማለት ነበር፡-
‹‹ሶማሊያ የፈራረሰበት ወቅት ስለነበር በጣም ትላልቅ የሶማሊያ ተፈናቃዮች የሰፈሩባቸው ካምፖች ነበሩ፡፡ እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ አንዱ የስደተኞች ካምፕ የነበረባት አገር ነበረች፡፡ በተለይ አርትሼክ አካባቢና ሌሎች አካባቢዎችም ትልልቅ ካምፖች ነበሩ፡፡ በዚህ ጊዜ የመጡ የዚያኛው ሶማሊያ መኮንኖች፣ ሲቪል ሰራተኞች ኢንጂነሮችና ፓይለቶች ነበሩ፤ በአካል ያገኘናቸው የምናውቃቸው እነዚህ ከኢትዮጵያ ሶማሌ ጋር የሚለያቸው ነገር ስላልነበረ በአብዛኛው በስደተኛነት ከመጡ በኋላ የአካባቢውን የፖለቲካ ስልጣኑንም ያደራጁት እነሱ ነበሩ፡፡ አንዱ ትዝ የሚለኝ ይሄ ነው፡፡ ይሄንን የኢህአዴግ ሰራዊትና ከላይ የሄደው የኢትዮጵያ ሰራዊት ሊለየው አይችልም ብቻ ሳይሆን ያ የመጣውን እንዳለ የሚያቅፍ ሁኔታ ነው የነበረው በአካባቢው፡፡ ስለዚህ ለረጅም ጊዜ ያ ኃይል ነው እንግዲህ አዲስ በተፈጠረው አጋጣሚ የታላቋ ሶማሊያን አስተሳሰብ የኢትዮጵያ ሶማሊያ ላይ ለመዝራት ትልቅ ጥረት ያደረገው››
ይህ ክርክር በራሱ ኢህአዴግ ‹‹ፊታችሁን ወደተረጋጋችው ምስራቅ ኢትዮጵያ (ሶማሊ ክልል) መልሱ›› ያለበት አውድ የተለመደው የቅጥፈት ፕሮፓጋንዳ እንጂ አካባቢው የጦርነት ወረዳን ያህል የሚያሰጋ መሆኑን ያመላክታል ፡፡ እናም ከአርቲስቶች እና ጋዜጠኞች እስከ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ፊት-አውራሪነት የተካሄደው የጉብኝት ፕሮግራም፣ መንግስት ምንም እንኳ የህዝቦችን አንድነት ‹የማጥበቅ ዕቅድ› የሚል የዳቦ ስም ቢሰጠውም፣ ‹ሶማሌ ክልል ፍፁም ሰላም ነው› የሚል የሀሰት ፕሮፓጋንዳን ለመንዛት መሆኑን ለመረዳት በአካባቢው ያለውን የፀጥታ አጠባበቅ ብቻ መመልከቱ በቂ ይመስለኛል፡፡
የቦምባስ ዕገታ
ዘንድሮ ለስምንተኛ ጊዜ ‹‹ሕገ-መንግስታችን ለህዳሴያችን›› በሚል መሪ ቃል የሚከበረው ‹‹የብሔር ብሔረሰቦች ቀን›› በሶማሌ ክልል ዋና ከተማ ጅጅጋ በመሆኑ በአካባቢው ያለውን የፖለቲካ ትኩሳት ለመለካት ረቡዕ ህዳር 11 ቀን 2006 ዓ.ም. ወፍ ጭጭ ሳይል ነበር ድሬዳዋን ለቅቄ ወደ ሐረር ጉዞዬን የተያያዝኩት፡፡ ይህንን ሰዓት የመረጥኩት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አዲስ አበባ ላይ እንኳ ጋብ እየለ የመጣውን የደህንነት ሰራተኞች ክትትል ድሬዳዋ ላይ በየደረስኩበት ሲያንዣብብብኝ፣ በማስተዋሌ፣ ምናልባት ከዕይታ ውጪ መንቀሳቀስ ብችል በሚል እሳቤ ነበር፡፡ መኪናው ከአንድ ቀን በፊት የተከራየሁትና ድሬ ውስጥ ያልተጠቀምኩበት በመሆኑ፣ በስጋት የሚንጠውን የደንገጎ አቀበትም ሆነ ጥንታዊቷን ሐረር ከተማ አቋርጠን እስክናልፍ አንዳች ችግር አላጋጠመንም፡፡ ይሁንና ከሐረር በግምት 80 ኪሎ ሜትር ያህል ርቀት ላይ በሶማሊያ ክልል የምትገኘው ቦምባስ ከተማ ደርሰን ጥቂት እንደተጓዝን፣ መኪናውን ዳር አስይዞ እንዲያቆም አንድ የትራፊክ ፖሊስ ለሹፌሩ የእጅ ምልክት አሳየው፤ ይሄኔም ነው ድሬ ላይ እንደ ተሰወርኩባቸው እርግጠኛ ሆኜ በልቤ ከሳቅኩባቸው ሁለቱ ሰላዮቼ ጋር ፊት ለፊት የተፋጠጥነው፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ስሜን ጠርተው አነጋገሩኝ፤ እኔም ከምንም ነገር በፊት መታወቂያቸውን እንዲያሳዩኝ ጠየቅኩ፤ ሳያቅማሙ አሳዩኝ፤ ወዲያውኑም የአፍ መፍቻ ቋንቋው አማርኛ እንዳልሆነ የአነጋገር ዘዬው በግልፅ የሚያስታውቀው አንደኛው የደህንነት አባል፣ ከዚህ በላይ ጉዞውን መቀጠል እንደማልችልና በቀጥታ ወደ ድሬዳዋ መመለሱ እንደሚጠቅመኝ ሊነግረኝ ሞከረ፡፡ ከመገረሜ ብዛት ንግግሩን ለመረዳት ጥቂት ሰከንዶች ፈጅተውብኝ ነበር፡፡ መቼም ይህ ሰው ቀልደኛ መሆን አለበት! አለዛ በገዛ ሀገሬ የት ድረስ መሄድ ወይንም የት ቦታ ጉዞዬን መግታት እንዳለብኝ ሊወስንልኝ ባልደፈረ ነበር፤ ሆኖም ንዴቴን ዋጥ አድርጌ ምን ማለት እንደፈለገ እንዲያስረዳኝ በትህትና ጠየኩት… ይኼኔ ጓደኛው ጣልቃ ገባና ወደ ጅግጅጋ ለመሄድ ማሰቤን እንደደረሱበትና ወደ ከተማው እንድገባ እንደማይፈቅዱልኝ ቆጣና ኮስተር ብሎ አሳወቀኝ፡፡ እኔም ፈርጠም ብዬ እዚህ ድረስ መጥቼ ጅጅጋ ሳልደርስ እንደማልመለስ ቁርጡን ነገርኳቸው፡፡ ቃለ-ምልልሱ እየከረረ ሲሄድ ማስፈራራቱን ወደ ሹፌሩ አዞሩትና በብርቱ ያዋክቡት ያዙ፤ ይህ ድርጊታቸው ያልጠበቅኩት በመሆኑና የሹፌሩንም ምላሽ አለማወቄ መጠነኛ ድንጋጤ አጫረብኝ፡፡ እንደገመትኩትም ሁኔታውን በፍርሃት ተውጦ ይከታተል የነበረው ሹፌር ትንሽ እንኳ ሳያንገራግር መኪናውን ቆስቁሶ ወደ ሐረር አዞረው፡፡
‹‹ምን ሆነሃል?›› አልኩት በንዴት ጮኽ ብዬ፡፡
‹‹ወንድሜ እኔ ቤተሰብ የማስተዳድር ሰው ነኝ፡፡››