Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

“ትግራይ በመወለዴ ልዩ ነገር ይገባኛል የሚል አመለካከት የለኝም” –ዶ/ር ኃይሉ አረአያ (ቃለ-ምልልስ)

$
0
0

“ትግራይ በመወለዴ ልዩ ነገር ይገባኛል የሚል አመለካከት የለኝም”
“እነ አቶ ልደቱ የፖለቲካ መጠቀሚያ ነው ያደረጉን”

 

ዶ/ር ኃይሉ አርአያ

ዶ/ር ኃይሉ አርአያ በኢዴፓ በኋላም በቅንጅት አመራርነት አገልግለዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የአንድነት ፓርቲ ምክር ቤት አባል ናቸው፡፡ የ”ሎሚ” አዘጋጅ ቶማስ አያሌው ከዶ/ር ኃይሉ አርአያ ጋር ሰፊ ቃለመጠይቅ አድርጓል፡፡ በሃገር ቤት የሚታተመውን ሎሚ መጽሄት በውጭ ሃገር ለማታገኙት ወገኖች ቃለምልልሱን ዘ-ሐበሻ ትካፈሉት ዘንድ አስተናግዳዋለች።

dr hailu areayaሎሚ፡- እርስዎ ያዘጋጁዋት የነበረችው “ፕሬስ ዳይጀስት” ለዲፕሎማቲኩ ማህበረሰብ ኢትዮጵያን በተመለከት መረጃ የሚሰጥ “ታብሎይድ” ነበር፡፡ የትንሿን ጋዜጣ ዝግጅት ለምን አቋረጡት?

ዶ/ር ኃይሉ፡- ጋዜጣዋ አሁንም እየተዘጋጀች ነው፡፡ እኔ ግን ያቋረጥኩት ጋዜጣዋ የምትፈልገውን ጊዜ እና ጥረት ማበርከት ባለመቻሌ ነው፡፡ በአጭሩ ብዙ ጊዜ ይጠይቃል፡፡ ዝግጅቱ ብዙ ጊዜ የመጠየቁን ያህል ደግሞ ብዙ ጥቅምም አያስገኝም፡፡ ከዚያም ባሻገር ስራው የሦስት ሰዎች ስራ ነበር፡፡ ግን የሦስት ሰዎችን ጥረት የሚጠይቅ ስራ አልነበረም፡፡ በዚያን ጊዜ ሌላ የምሰራው ስራ ስላልነበረ ሁላችንም ትንሽ ትንሽ እየሰራን ነበር የምናሣልፈው፡፡ የአንድ ሰው ስራ ነው፡፡ የአንድ ሰውም የሙሉ ጊዜ ስራ አልነበረም፡፡ ስለዚህ ጊዜ ከማባከን ያንን ለአንድ ሰው ትቶ ሌሎቻችን ሌላ ስራ ብንሰራ ይሻላል በሚል ነው የተውነው፡፡
ሎሚ፡- በደርግ ዘመን “የብሔረሰብ ጥናት ኢንስቲቲዩት” ኃላፊ እርስዎ እንደነበሩ ይታወሳል፤ ኢንስቲቲዩቱ ምን አስተዋጽኦ አበረከተ? አሁን የብሔረሰብ መብት ተከብሯል ከሚባለው ጋር ሲያነጻጽሩት “የብሔረሰብ ጥናት ኢንስቲቲዩት” ሰርቶታል የሚሉትን አብይ ጉዳይ ሊገልፁልን ይችላሉ?
ዶ/ር ኃይሉ፡- በመጀመሪያ የኢንስቲቲዩቱ ኃላፊ አልነበርኩም፡፡ ኢንስቲቲዩቱ ራሱ ኃላፊ ነበረው፡፡ እንደውም ኃላፊው የሚኒስትር ማዕረግ ነበረው፡፡ በኢሠፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ ውስጥ የብሔረሰቦች ጉዳይ መምሪያ በሚባለው ቦታ በምክትል ኃላፊነት ነበር የምሰራው፡፡ ያ መምሪያ ነው ተቋሙን ያቋቋመው፡፡ ብዙ የሚሰሩ ስራዎች ነበሩ፤ ጥናቶች ነበሩ፤ ሕገ መንግስቱን ለማዘጋጀት ብዙ ጥናቶች መደረግ ነበረባቸው፡፡ የኢሠፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ ውስጥ የነበረው የኛ መምሪያ ብዙ ስራ ሊሰራ ስለማይችል የግዴታ ራሱን ችሎ ለመንቀሣቀስ “ኢንስቲቲዩቱን” መመስረት አስፈላጊ ነበር፡፡ ስለዚህ “የብሔረሰቦች ጥናት” ኢንስቲቲዩት ተቋቋመ፡፡ ነገር ግን በመምሪያችን ስር ነበር፡፡
የእኛ መምሪያና ኢንስቲቲዩቱ አብረው ነበር የሚሰሩት፡፡ ጥናቶች ሲካሄዱ አብረን ሁላችንም እንሳተፋለን፤ አመራር የሚሰጠው ግን ከመምሪያው ነበር፡፡ በሁሉም ዘርፍ ለአምስት ዓመት ያህል ነው ኢንስቲቲዩቱ ጥናት ያካሄደው፡፡ በዛን ጊዜ የተሰሩ ስራዎች ኢህአዴግም ከመጣ በኋላ ብዙ ጠቅሞታል ብዬ ነው የምገምተው፡፡ ያኔ የህግ መምሪያ ኃላፊ የነበሩት ሰው አሁን በሚኒስትሮች ምክር ቤት ያሉ ይመስለኛል፤ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የህግ አማካሪ ናቸው፡፡ ሌሎችም በሀገሪቱ አሉ የተባሉ ምሁራን ተሰባስበው ከፍተኛ ጥናት አካሂደዋል፡፡ በጣም ጠቃሚ የሆኑ ጥናቶች ናቸው የተካሄዱት፡፡ ጥናቶቹ አልባከኑም ብዬ አምናለሁ፡፡ በርግጥ የተፈለገው ሕገ መንግስት በተደረጉት ጥናቶች መሠረት ተቀርጿል፡፡ መቅረፅ ብቻም አይደለም፤ ስራ ላይም ውሏል፡፡ በተለይ በብሔረሰቦች ላይ የተደረገው ጥናት በዝርዝር ነው የተካሄደው፡፡ በአሁኑ ጊዜ የብሔረሰቦች መብት ምን ያህል ተከብሯል የሚለው የትኩረት መጠን ካልሆነ በስተቀር ያኔ የተደረገው የብሔረሰቦች ጥናት እና የተሰጠው የብሔረሰቦች ትኩረት በጣም ከፍተኛ ነበር፡፡ የኢህአዴግ መንግስት ስለ ብሔረሰቦች መብት መከበር እንደ አዲስ የጀመረ በማስመሰል ሲናገር ስሰማ በጣም አዝናለሁ፡፡ በዛን ጊዜ የነበረውን ነገር አልተከታተለውም፤ ውጊያ ላይ ስለነበር ሊከታተልም አይችልም፡፡ ውጊያ ላይ እያለ ባይከታተልም ስልጣኑን እና ኢንስቲቲዩሹኑን ከተረከበ በኋላ በዛን ጊዜ የነበሩ ሰነዶችን መመርመር ይችል ነበር፡፡ ሰነዶቹ አሁንም ይኖራሉ ብዬ እገምታለሁ፡፡ ኢህአዴግም ተጠቅሞባቸዋል ብዬ ነው የምገምተው፡፡
“የብሔረሰቦች መብት” ኢህአዴግ እንደ አዲስ የጀመረው ጉዳይ አይደለም፡፡ በባህላቸው፣ በቋንቋቸው…በሌላውም አቅጣጫ ኢህአዴግ እንደ አዲስ እንደጀመረ አድርጐ ነው የሚያወራው፡፡ ይህንን ትዝብት መቼም ለታሪክ እንተወዋለን፡፡ የደርግ ስርዓት ሌሎች ድክመቶች ሊኖሩበት ይችላል፡፡ የብሔረሰቦችን ጉዳይ በተመለከት ግን መሠረቱን ያስቀመጠው የደርግ ስርዓት ነው፡፡ ኢህአዴግ ምናልባት አጠናክሮታል፣ አስፋፍቶታል ማለት ይቻላል፡፡ አንደ አዲስ ጀመርኩት የሚለው ነገር ግን ከእውነት የራቀ ነው፡፡ ይህ ሊስተካከል ይገባል፤ ምክንያቱም ታሪክ ራሱ ቁጭ ብሎ የሚመሰክርበት ጉዳይ ስለሆነ በዝምታ ማለፍ ነው የሚሻለው፡፡ የብሔረሰቦችን ጉዳይ በተመለከተ እንዲሁ ለይስሙላ ከሚደረግ በስተቀር ነፃ የሆነ ለውጥ ተደርጓል ብዬ አልገምትም፡፡ ምናልባት በጥቅም፣ በሀብት አከፋፈል በጀትን በተመለከተ ለብሔረሰቦች የሚመደበው ገንዘብ አሁን በከፍተኛ መጠን ጨምሯል፡፡ ሌላው የቅርፅ ጉዳይ ነው፡፡ ብሔረሰቦች የሕገ-መንግስት ባለቤት ሆነዋል፡፡ ህገመንግስትን መስርተዋል፤ ሕገ መንግስት አላቸው፤ ሰንደቅ አላማም ያውለበልባሉ…እነዚህ ከቅርፅ አኳያ ለውጦች ናቸው፡፡ እነዚህ የቅርፅ ለውጦች በተግባር ቢደገፉ ጥሩ ይሆኑ ነበር፡፡ ነገር ግን አልተደገፈም፡፡ ምክንያቱም ብሔረሰቦች አሁንም መሠረታዊ የሆኑ ችግሮች አሉባቸው፡፡ መሠረታዊ የምላቸው በኔ በኩል የህግ መከበር ነው፡፡
ህጐች ይጣሳሉ፤ መብቶች ይደፈራሉ፤ ምን ያህል ነፃነት እንዳላቸውም እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ምንም እንኳን ስርዓቱ ፌዴራል ቢሆንም ቅርፁ ፌደራላዊ ቢሆንም በተግባር ግን “አሃዳዊ” ነው፤ ምክንያቱም በደርግ ጊዜ መንግስት “አሃዳዊ” ነበር፡፡ ክልሎች የአስተዳደር መብት ነበራቸው፡፡ ያም ቢሆን በሚገባ ተግባራዊ አልሆነም፡፡ ከይዘት አኳያ በደርግ አሃዳዊ መንግስትና በኢህአዴግ ፌደራላዊ መንግስት መካከል ልዩነት አለ፡፡ “ደርግ” የነበረው የውስጥ አስተዳደር ነው፤ የኢህአዴግ ግን ፌዴራል ነው፡፡ በዚህ ጊዜ ብሔረሰቦች ሕገ መንግስት አላቸው፣ የራሣቸው መንግስትና ባንዲራ….አላቸው፡፡ በዛን ጊዜ የነበረው ኢሠፓ መዋቅሩን ታች ድረስ አውርዶ ሀገሪቱን የሚያስተዳድረው ኃይል እርሱ ነበር፡፡ ኢህአዴግ ምንም እንኳን በቅርፅ “ፌደራላዊ” ቢባልም ሀገሪቱን ጠርንፎ በአሃዳዊ መልክ ነው የሚያስተዳድረው፡፡ በሁለቱ መካከል የይዘት ልዩነት የለም፡፡ ለውጡ ምንድነው? ብትለኝ ጥቂት ነው፡፡ እምቢልታና መለከት የሚያስነፉ አይደሉም፡፡ አሁንም ብሔረሰቦች ይጨቆናሉ፡፡
የሚጨቁኗቸው ደግሞ የራሣቸውን ቋንቋ የሚናገሩ የራሣቸው ወገኖች ናቸው፡፡ ስለዚህ አሁንም ከጭቆና እና ከችግር አልወጡም፡፡ ፌደራላዊ ስርዓት ጥሩ ሆኖ ከአሃዳዊ ሲለይ አልታየም፡፡ ሕዝቡ ቢጨቁነኝም ይጨቁነኝ፣ ቢረግጠኝም ይርገጠኝ፣ የኔን ቋንቋ እስከተናገረ ድረስ የሚል ከሆነ ሌላ ነገር ውስጥ ነው የሚገባው፡፡ ለኔ ቋንቋ አይደለም ትልቁ ነገር:: ከዛ ባለፈ ሕግ መከበር አለበት፤ ፍትህ መከበር አለበት፤ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት መከበር አለበት፡፡ እውነተኛ ነፃነት መኖር አለበት፡፡ አሁን የብሔረሰቦች ቀን ተብሎ “በዓል” ይከበራል፡፡ ሰባት ዓመት ሙሉ ተከብሯል መሰለኝ፡፡ ስምንተኛው በዓል በኢትዮጵያ ሱማሌ ክልል ነው የሚከበረው፡፡ በአንድ በኩል ይህ ጥሩ ነው፡፡ ምክንያቱም በብሔረሰቦች መካከል ያለውን ስሜት በማጠናከር እና በራስ መተማመንን ለማምጣት የሚረዳ ነገር ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ እንዲሁ ዘፈንና ጫጫታ ሆኖ መሠረታዊ ጉዳዮች ሣይደረጉ ሲቀሩና እዛው በቦታው ሲመለስና እንደ ድሮው የሚጨቆን ከሆነ ምንድነው ትርጉሙ? የሰው ልጅ ፍላጐት ከዛ ያለፈ ነው፡፡ ይሄ ግን እየተመለሰ አይደለምና ከዳንሱና ከጭፈራው ጐን ለጐን የብሔረሰብ ነፃነት ሊከበር ይገባል፡፡ ሊሰሩ የሚችሉበት ነፃነት ይኑራቸው፡፡ ትምህርትን፣ የጤና አገልግሎትን ያየን እንደሆነ ተስፋፍቷል፡፡ “በቁጥር” ተስፋፍቷል፤ “በጥራት” ግን ገና ነው፡፡ መስፋፋቱ ጥሩ ነው፤ ግን ቁጥር ብቻ በቂ አይደለም፡፡ ይሄ መንግስት አሁን እየጠቀሰልን ያለው ቁጥር ነው፡፡ ይህን ገንብቻለሁ እያለ በሁሉም ዘርፍ ይገልፃል፡፡ ያ ብቻ በቂ አይደለም፡፡ በጥራት መሻሻል አለበት፡፡ ቁሣዊና ሰብአዊ ልማት አለ፡፡

መንግስት እየተገበረ ያለው ቁሣዊ ልማትን ነው፡፡ ሰብዓዊ ልማት የለም፡፡ ሰብዓዊ ልማት ያለ ነፃነት፣ ያለፍትህ፣ ያለ ዴሞክራሲ ይሄን ያህል ጠቃሚ አይደለም፡፡

ሎሚ፡- በሚያዝያ 1983 ዓ.ም. ደርግ ባቋቋመው ሸንጐ የመጨረሻ ስብሰባ ላይ አባል እንደመሆንዎ ተገኝተው ለኮ/ል መንግስቱ ኃ/ማርያም የተናገሩትን ለዚህ ትውልድ መረጃ እንዲሆን ቢያስታውሱን?
ዶ/ር ኃይሉ፡- ጊዜው በጣም አስቸጋሪ ነበር፡፡ ሀገሪቱ የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ነበረች፡፡ ሀገሪቱን እመራለሁ፣ ግንባር ቀደም ነኝ የሚለው የፖለቲካ ድርጅት (ኢሠፓ) በየጊዜው እየተሰባሰበ የሀገሪቱን ሁኔታ እየገመገመ ሕዝቡ ምን እንደሚልና በሚለው መሠረት ምን መደረግ እንዳለባቸው ማወቅ ነበረበት፡፡ ግን ሳያደርግ ቀረ፡፡ ስብሰባዎች እንዲካሄዱ ነበር ብዙ ጊዜ የምንጐተጉተው፡፡ ከዛ ከፓርላማ ስብሰባው በፊት ኢሠፓ ተሰብስቦ የዚህችን ሀገር ሁኔታ እንዲገመግም፣ መፍትሄ እንዲፈልግና ተግባራዊ እንዲያደርግ በየጊዜው በሚደረጉ የመሠረታዊ ድርጅት ስብሰባዎች እንከራከር ነበር፡፡ ነገር ግን ምንም አይነት ውጤት አልተገኘም፡፡ ነገሮች እየተባባሱ ሄዱ፡፡
በመጨረሻ የተደረገው ተስፋ የመቁረጥ ዓይነት ሙከራ ነው፡፡ ሙከራው ቢዘገይም ከሚቀር ይሻላል፡፡ ምንም ካለማድረግ የተወሰነ ነገር ማድረግ ጥሩ ነው፡፡ ይሄ የግል ስሜቴ ነው፤ የግል ስሜቴን ለመግለፅ ነው የሞከርኩት፡፡ ግን አሁን መለስ ብዬ ያለንበትን ሁኔታ ሳይ ደግሞ ያን ያህል ጊዜ መዘግየት አልነበረብንም እላለሁ፡፡ ጊዜ መስጠት አልነበረብንም የሚል እምነት አለኝ፡፡ አሁን ደግሞ ለዚህ ስርዓት አላግባብ ተገቢ ያልሆነ ጊዜ እየሰጠን ነው፡፡ በስልጣን በቆየ ቁጥር እየበሰበሰ ነው የሚሄደው፡፡ በተፈጥሮው ስልጣን ያሞስናል፤ ያበሰብሳል፡፡ አንድ ወገን፣ አንድ ኃይል ስልጣን ላይ ከሚፈለገው በላይ በቆየ ቁጥር እየበሰበሰ ይሄዳል፡፡ ይሄ እኮ የተፈጥሮ ሂደት ነው፡፡ ሌሎች ሀገሮች የፕሬዚዳንትና የጠ/ሚኒስትር (በተለይ “የፕሬዚዳንት”ን) የስልጣን ቆይታ የቱንም ያህል ጥሩ ቢሆን ከስምንት አመት በላይ አያልፍም፡፡ ስለዚህ ሀገሪቱን ትጐዳለህና ቦታ ልቀቅ ነው የምትባለው፡፡ የኛ መንግስት እስካሁን ድረስ ብዙ ቆይቷል፡፡ 22 ዓመት ብዙ ነው፡፡ በኔ እምነት መበስበስ ከጀመረ ቆይቷል፡፡ የመበስበሱ ምክንያቶች በየጊዜው እየታዩ ናቸው፡፡ መቀጠል የለበትም ብለን መናገር አለብን እንጂ ዝም ማለት የለብንም፡፡ ከዚህ በፊት ዘግይተን ከነበረ እናዝናለን፡፡ በስንፍናችን እናዝናለን፤ እንቆጫለን፡፡ ነገር ግን ከዚያ ተምረን ያ መደገም የለበትም እንላለን፡፡ የሀገራችን ጉዳይ መፍትሄ ማግኘት አለበት፡፡ ገደብ የሌለው ስልጣን መፍትሄ ማግኘት አለበት፡፡ እነሱ ሥልጣን ላይ የተቀመጡት ሕዝብ ስለፈለጋቸው አይደለም፡፡ በእንዴት ዓይነት ሁኔታ ስልጣን ላይ እንደወጡ የኢትዮጵያ ሕዝብም እነሱ ራሣቸውም ያውቁታል፡፡ አዲሱ ትውልድ በተለይ ወጣቱ ትውልድ መናገር መቻል አለበት፡፡ ለመብቱ ለነፃነቱ መቆም መቻል አለበት፡፡ አስፈላጊ ከሆነም ደግሞ መስዋዕትነት መክፈል አለበት፡፡
ሎሚ፡- በዚያ ወቅት በትግራይ ተወላጆች ላይ ግድያ ሲፈጸም የድፍረት ንግግር ለመናገር የገፋፋዎት የተለየ ምክንያት ምን ነበር?
ዶ/ር ኃይሉ፡- በወቅቱ ካለፈው ታሪኬ የተነሣ እንደ አደገኛ ሰው የታየሁ አልመሰለኝም፡፡ ፍራቻም አልነበረኝም፡፡ እንዲያውም የትግራይ ተወላጅ መሆኔን
ያስታወስኩት እኮ ዘግይቼ ነው፡፡ ጐሣ፣ ጐጥ… እየተነሣ ሲመጣ ነው ይሄ ነገር
መጉላት የጀመረው፡፡ እንጂ በፊት እኔ የዚህ ተወላጅ ነኝ፣ የዛ ተወላጅ ነኝ የሚል
ነገር አልነበረም፡፡ ስሜቱም አልነበረኝም፤ ትግራይ ነው የተወለድኩትና በተወለድኩበት አካባቢ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ ነው ያደግኩት፡፡ በአጋጣሚ ትግራይ ማይጨው ራያ ተወለድሁ፡፡ የተወለድኩበትን አካባቢ እቀበላለሁ፡፡ ግን እዚያ ትግራይ በመወለዴ ልዩ ነገር ይገባኛል የሚል አመለካከት የለኝም፡፡ እዚያ መወለዴም ስጋት አላሳደረብኝም፡፡

በመጀመሪያ ደረጃ ሰው ነኝ፤ ከዛ በኋላ ደግሞ ኢትዮጵያዊ ነኝ፡፡ በዛ ምክንያት እንዲህ እሆን ወይ ጉዳት ይደርስብኝ ይሆን ወይ ብዬ አላስብም፡፡ እንደውም በዛን ጊዜ ኮ/ል መንግስቱ ፊት እንደዛ ስናገር ሰዎች በጣም ደንግጠው ከአካባቢው ለመራቅ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል፡፡ በኋላ ደግሞ ታስታውስ እንደሆነ ኮ/ል መንግስቱ በፃፉት ጽሁፍ /እኔ እንኳን መፅሐፉን ሣይሆን በቴፕ ነው የሰማሁት/ “ዶ/ር ኃይሉ እንደዛ የተናገረው ምናልባት ዘመዶቹ አምቦ ስለደረሱ ይሆናል፤ /ሣቅ/ ነው፤ ለኔ እንዲህ ዓይነት ስሜት ነው የፈጠረብኝ” ብለው ነበር፡፡ በጣም አሣዘነኝ፤ ምናቸው ነው ለኔ ዘመድ የሚያደርጋቸው?… በጣም አዘንኩ፤ የማንነት ጉዳይ አንዳንዴ ብወድም ባልወድም ብልጭ ማለቱ አይቀርም፡፡ ትኩረት የምሰጠው ነገር ግን አይደለም፡፡ ፍርሃት አልነበረብኝም፡፡ ያኔ የትግራይ ተወላጆች ብቻ አይደለም የሚገደሉት፤ ማንም ያንን መስመር የሚቃወም ሁሉ ነበር የሚገደለው፡፡

 
ሎሚ፡- ኮ/ል መንግስቱ እንደዛ ከተናገሩ በኋላ ቤትዎ ገብተው በሰላም አደሩ?… ሌሊቱን የት አሣለፉ? የኮ/ል መንግስቱ የደህንነት ሰዎች ምላሽስ ምን ነበር?
ዶ/ር ኃይሉ፡- ምንም ችግር አልደረሰብኝም፡፡ ሰዎች ወስደው የት እንዳሳደሩኝ አላስታውስም፡፡ ብቻ የሆነ ቦታ ነው የወሰዱኝ፡፡ የተለየ ነገር አልገጠመኝም፡፡ አስታውሳለሁ፤ ኮ/ል ተስፋዬ ወ/ስላሴ /የደህንነት ኃላፊው/ “ጐሽ ጥሩ ነው ያደረግከው” ብሎ መለስ ቀለስ እያለ እየፈራ እየቸረ ነው ያናገረኝ፡፡… /ረዥም ሳቅ/፡፡… በኋላ ጡረታ እንድወጣ ደብዳቤ ተፃፈ፡፡ በነገራችን ላይ ቀደም ብዬ ነበር ጡረታ እንድወጣ የጠየቅኩት፡፡ ነገር ግን በተለያየ ምክንያት ጥያቄዬ ተግባራዊ ሳይሆን ቆይቶ ነበር፡፡ ወዲያው የተወሰደውን እርምጃ ሰዎች ነግረውኛል፡፡ …ኮ/ል መንግስቱ በጣም ተቆጥተው ነበር፡፡ ነገር ግን ብዙዎቹ ለምነን አባብለን ነው ያስታገስናቸው ብለውኛል፡፡ አንደኛው የማውቀው ወዳጄ “እንዲያውም እግራቸው ላይም እስከመውደቅ ደርሰናል“” ሲል ነበር የነገረኝ፡፡ ይህ ምን ያህል እውነት እንደሆነ አላውቅም፡፡ መናደዳቸው አያከራክርም፤ እግዚአብሔር ይመስገን የከፋ ነገር ግን አልደረሰብኝም፡፡ በእሣቸው የደህንነት ሰዎችም የደረሰብኝ ነገር የለም፡፡
ሎሚ፡- እንግዲህ ውይይታችን ሰፊ ነውና ወደኋላም ወደፊትም እያልን ጥያቄ እናንሳ፤ ወደ ቅርብ ጊዜው እንመለስና ወደ ቅንጅት (ምርጫ 97) ግርግር እንምጣ፡፡ በወቅቱ አቶ ልደቱ የነበረው አቋም በእርግጥም የኢዴፓ ውሣኔ ነበር? በቅርቡ አቶ ልደቱ ከመፅሔታችን ጋር ባደረገው ቃለ መጠይቅ “የስልጣን ጥያቄ ስላልነበረን የበሰሉ ሰዎች ቢመሩት ይሻላል ብለን ነው ዶ/ር ኃይሉ አርአያን እና ዶ/ር አድማሱን ከቤታቸው አምጥተን ስልጣን እንዲይዙ ያደረግነው” ብሏል፡፡ ይሄን እንዴት ይመለከቱታል?

 
ዶ/ር ኃይሉ፡- በዚህ ጉዳይ ዙሪያ ብዙ መናገር አልፈልግም፡፡ ይሄ በእኔና በአንተ ቃለ መጠይቅ ላይ ብቻ ተገልፆ የሚያልቅ አይደለም፡፡ በጣም ሰፊ የሆነ ታሪክ ነው፡፡ ግን መናገር ካለብኝ አንድ ወጣት (ታምራት ታረቀኝ) የሚባል መፅሐፍ ፅፎ ነበር፡፡ ምናልባት እዚያ ላይ ያለውን ብደግመው በቂ ይሆናል፡፡ ተጠቅመውብናል ማለት እችላለሁ፡፡ በዛን ጊዜ የነበሩ የኢዴፓ አመራር /እነ አቶ
ልደቱ/ ተጠቅመውብናል፡፡ ከተጠቀሙብን በኋላ ጊዜው ሲመጣ እኛን ወደ ጐን ለማግለል ሞክረዋል፡፡ አቶ ልደቱ ብዙ ውይይት የሚከፍት ሰው ነው፡፡ መጠቀሚያ አደረገን እንጂ በምሁርነቴ ጠርቶ ይሄ ቦታ ይገባሀል ብሎ አይደለም ቦታ የሰጠኝ፡፡ በኔ ውስጥም የሚሰማኝ ይሄ ነው፡፡
ሎሚ፡- አቶ ልደቱ “ዶ/ር ኃይሉ አርአያ ከቅንጅት ጋር የትም አንደርስም” ብሎ
ይከራከር ነበር ሲልም ገልጿል፤ ይሄስ እውነት ነው?

ዶ/ር ኃይሉ፡- ፈጽሞ ከእውነት የራቀ ነው፡፡ በተቃራኒው ነው እሱ የገለፀው፡፡ ከቅንጅት ጋር አብሮ ስለመስራት ነበር የኔ ክርክር የነበረው፡፡ አቶ ልደቱ በወቅቱ ብዙ ነገር የተወሳሰበና የተተበተበ ነገር ነበር የሚያነሣው፡፡ እንዲያውም “ቅድመ ሁኔታዎች” በሚል ይከራከር ነበር፡፡ በኔ በኩል በቅንጅት ዙሪያ መግባባት አለብን የሚል አቋም ነው የነበረኝ፡፡ በአቶ ልደቱ የተገለፀው የተገላቢጦሽ ነው፡፡
ሎሚ፡- ኢዴፓ ያንን አጋጣሚ አክሽፏል ብለው ያምናሉ?
ዶ/ር ኃይሉ፡- አዎ! አምናለሁ! በሁለት ምክንያት፡፡ አንደኛ ከምርጫ በኋላ የቅንጅት አመራር የአራቱ ፓርቲ አመራር ከልደቱ በስተቀር ለመዋሃድ ውሣኔ ሲያሳልፍ እና መሪዎቹ ፊርማቸውን ሲያሳርፉ በስምምነቱ ላይ አቶ ልደቱ በኢዴፓ ሰነድ ላይ ማህተም ለማድረግ ፈቃደኛ ባለመሆኑ ማህተሙ ሳያርፍ ቀረ፡፡ ይሄ የሆነው ማህተሙን የሙጥኝ ብሎ በመያዙ ነው፡፡ ሁለተኛ ለምርጫ ቦርድ በቅንጅት የተጠየቀው የውህደት ጥያቄ ተግባራዊ እንዳይሆን የሚል ደብዳቤ በማስገባቱ ያለጥርጥር ያንን ዕድል አክሽፎታል ብዬ አምናለሁ፡፡ ይሄን ስል ግን ሌሎችም ችግሮች አልነበሩም ማለቴ አይደለም፡፡ ሌሎችም ችግሮች ነበሩ፡፡ ቀሪዎቹ የፖለቲካ ድርጅቶች ራሣቸው አስፈላጊውን ጉባኤ አካሂደው ማሟላት ያለባቸውን ነገሮች አሟልተው አንድ መሆን ሲገባቸው ሣይችሉ ቀርተዋል፡፡ ያ ብቻም ሣይሆን ያከሸፈው ሌሎች የውስጥ ችግሮችም ነበሩ፡፡
hailuሎሚ፡- በወቅቱ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ሲመረጡ በአቶ ልደቱ ላይ ምን ዓይነት ስሜት ነበር የታየው?
ዶ/ር ኃይሉ፡- ብርቱካን በተመረጠችበት ጊዜ አቶ ልደቱ መበሣጨቱ ምንም የሚያከራክርና አንድና ሁለት የሚባል ነገር አይደለም፡፡ በጣም በጣም ተበሣጭቷል፡፡ በግል የተመለከትነው ነገርም ነው፡፡
ሎሚ፡- ከእርስዎ ጋር በኢዴፓም ሆነ በቅንጅት ውስጥ ሲሰሩ የነበሩት ዶ/ር አድማሱ ገበየሁ ከፖለቲካ የራቁበት ምክንያት ምንድን ነው?
ዶ/ር ኃይሉ፡- ይህንን ጥያቄ መመለስ የሚገባው እሱ ዶ/ር አድማሱ ነው፡፡ እንደው ስገምተው ግን አንደኛ የትምህርትና የስራ ዕድልም ስላገኘ ይመስለኛል፡፡ ለባለቤቱም ጭምር ነው ይህ ዕድል የመጣው፡፡ ምክንያቱም የኛን ሃገር የመሰለ ፖለቲካ በሩቅ የሚከናወን አይደለም፡፡ ምናልባት አንድ ቀን ይመለስና የጀመረውን ትግል ይቀጥልበታል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ሁለተኛ ደግሞ የዚህ ሀገር ተቃዋሚዎች ሁኔታ ደግሞ የሚያበረታታና ተስፋ የሚያጭርም አይደለም፡፡ ብዙ ችግሮች አሉ፡፡ አሁን አንዳንድ መሻሻሎችና መስተካከሎች የሚኖሩ ይመስላሉ፡፡ ምናልባት እነዚህ የ33ቱ ፓርቲዎች የመሰባሰብና አንድ ላይ ለመስራት የመወሰን ጉዳይ የሚያበረታታ ነው፡፡ ነገር ግን የፖለቲካ ፓርቲዎች በሀገራችን በፊትም ቢሆን እንኳን ሩቅ ላለና እዚህ ሀገር ውስጥ ላለም የሚያበረታታ ተስፋ የሚሰጥ አይደለምና አልፈርድበትም፡፡ እንዲህ እግዚአብሔር ሲፈቅድ ወደሀገሩ ጠቅልሎ መጥቶ እገባበታለሁ ካለ መልካም ነው፡፡ ውስጡ ግን ማሰቡና መጨነቁ አይቀርም፡፡
ሎሚ፡- አቶ ልደቱ በሕይወትህ ምን የሚፀፅትህ ነገር አለ ለሚለው ጥያቄጠይቄው ነበር፡፡ ሲመልስም “በሕይወቴ ከሚፀፅተኝ ነገር አንዱ ምሁራንን ማመኔ ነው፡፡ ለምሁራን የነበረኝ ግምትና አስተሳሰብ ነው የሚጸጽተኝ” ብሏል፤ አባባሉን እንዴት አዩት?
ዶ/ር ኃይሉ፡- በመጀመሪያ ደረጃ ማንን አመነና ነው፡፡ ምንስ ተጓደለበት ነው የኔ ጥያቄ፡፡ ሣልፈልግ ወደዚህ የማልወደው ነገር ውስጥ እያስገባኸኝ ነው፡፡ የሚፀፅተኝ ሊል አይገባም፤ ምንም የሚፀፅት የተፈጠረበት ነገር የለም፡፡ የእሱን ተወውና በራሴ ግን በምሁራን ዙሪያ ከተባለ “ምሁራን በሀገራቸው ጉዳይ ላይ ንቁ ተሣታፊ አለመሆናቸው ነው የሚያሣዝነኝ፡፡ የማመንና ያለማመን ጉዳይ አይደለም፡፡ አምነናቸው ጉድ አደረጉን፤ አሳልፈው ሰጡን የሚል መንፈስ ያለው
ይመስላል አባባሉ፡፡ በምን ጉዳይ ምንድን ነበር የጠበቀው? ምንስ ቀረበት?

 

 


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>