የኢሕአደግና የግንቦት ስባት ድርድር ? ግርማ ካሳ
Muziky68@yahoo.com
ዲሴምበር 3 ቀን 2013 ዓ.ም
«የኢሕአዴግ መራሹ መንግስት ለግንቦት ሰባት የእንደራደር ጥያቄ አቀረበ» ሲል ኢሳት ሰበር ዜና አሰማን። ዶር ብርሃኑ ነጋንም በማቅረብ በጉዳዩ ላይ ሰፋ ያለ ማብራሪያ እንዲሰጡም አድርጓል። ምንም እንኳን የቀረበዉን ዘገባ ከሌላ ምንጭ ማጣራት ባይቻልም፣ ዜናዉ እዉነት ሊሆን የሚችልበት ሁኔታ እንዳለ ግን ይሰማኛል። አገዛዙ ከኦብነግ፣ ኦነግ ከመሳሰሉ ጋር ድርድር እየጀመረ፣ የማቋረጥ ልማድ እንዳለው ታሳቢ በማድረግ። የግንቦት ሰባት «እንደራደር» ጥያቄም ከዚያ የተለየ አይሆንም። በሳዊዲ
የድርድር ጥያቄዉን ይዘው የመጡ መልእክተኖች እነማን እንደሆኑ የተገለጸ ነገር የለም። ዶር ብርሃኑም «ጥያቄዉ የመጣዉ ከብዙ አቅጣጫዎች ነው» ከማለት ዉጭ ትንፍሽ ያሉት ነገር የለም። ከአንዳንድ የግንቦት ስባት አመራር አባላት ጋር የቅርብ የስራ ትውውቅ ባላቸውና፣ በቅርቡ ኢትዮጵያን በጉበኙት ፣ በተከበሩ አና ጎምዜ ይሆን መልእክቱ የመጣዉ ? ወይንስ ብዙ ጊዜ በሽምግልና ተግባር በመሰማራት በሚታወቁት በተከበሩ ፕሮፌሰር ኤፍሬም ይሳእቅ ? ወይስ በሃይማኖት አባቶች ? ወደፊት የምናውቀዉ ይሆናል።
ድርድር መቼም ቢሆን የሚደገፍ እንጂ የሚጠላ አይደለም። እርቅና ሰላም እንዲሰፍን፣ ኢትዮጵያዊያን ልዩነቶቻችንን በዉይይት እንድንፈታ የሚገልጹ በርካታ ጽሁፎችን አስነብቢያልሁ። ነገር ግን በኢትዮጵያ መልካም አስተዳደር ለማስፈንና የዲሞክራሲ ተቋማትን ለመገንባት ያስችል ዘንድ፣ ያለ አንዳች ቅደም ሁኔታ ለመነጋገር ፍቃደኛ ከሆኑ፣ አገር ዉጥ ካሉ ሰላማዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር፣ ኢሕአዴግ «በፍጹም አልደራደርም» እያለ፣ በሌላ በኩል «ጠመንጃ አንስተን እንታገላለን» ለሚሉ የድርድር ጥያቄ ማቅረቡ ግን ምን ይባላል ? በአንድ በኩል ብእር አንስተዉ በመጻፋቸው፣ «ከግንቦት ሰባት ጋር ተነጋግራቹሃል። ከሽብርተኞች ጋር አብራቹሃል» እየተባሉ፣ በዉሸት ክስ ዜጎች ለእድሜ ልክ እስራት እየተደረጉ፣ በሌላ በኩል ከ«ሽብርተኞቹ» ግንቦት ሰባቶች ጋር መነጋገር፣ ግብዝነትን አያሳይምን? አገዛዙ ሌላ አላማ ኖርት እንጂ በርግጥ ሰላም ፈልጎ ነዉ ማለት እንችላለን ?
በነገራችን ላይ ኢሕአዴግ ድርድር የጠየቀው ግንቦት ሰባትን ፈርቶ እንዳልሆነ መታወቅ አለበት። በዚህ ላይ ብዙ አንሳሳት። ግንቦት ሰባትን ኢሕአዴግ አይፈራም። እስቲ ንገሩኝ ለምንድን ነዉ ኢሕአዴግ ግንቦት ሰባትን የሚፈራዉ? የድርድር ጥሪ መቅረቡ በምንም መስፈርትና መለኪያ የግንቦት ሰባት ጥንካሬንም አያሳይም። ጥንካሬ የሚለካው በፍሬና በዉጤት ነዉ። ጥንካሬ የሚለካው በሜዳ ነዉ። ጥንካሬ ኢሕአዴግ በሚያወራዉ አይለካም። በመሆኑም ግንቦት ሰባቶች «ኢሕአዴግ ድርድር ከኛ ጋር የፈለገዉ ፈርቶ ነዉ፤ ስላሰጋነው ነዉ፤ ጥንካሬያችንን አይቶ ነዉ፤ ወዘተረፈ» እያሉ ብዙ ዳንኪራ ባይመቱ ይሻላል። ሰዉ ይታዘባቸዋል። ይልቅስ እራሳቸዉን ቢመረምሩ ዉጤት በሚያመጡ እንቅስቃሴዎች ላይ ቢሰማሩ ይበጃል ባይ ነኝ። (በዚህ አርእስት ላይ፣ ይረዳቸው ዘንድ ፣ ለግንቦት ስባቶች የተጻፈ ምክር አዘልና አቅጣጫ ጠቋሚ ግልጽ ደብዳቤ በቅርብ ጊዜ አቀርባለሁ)
እንደሚመስለኝ ኢሕአዴጎች ለመደራደር ጥያቄ ያቀረቡት፣ የአለም አቀፍ ማህበረሰብን ግፊት ለመቀነስ ነዉ። አራት ነጥብ። ግንቦት ሰባት ከሻእቢያ ፍቃድ ዉጭ ሊደራደር እንደማይችል፣ ጥያቂያቸዉን ዉድቅ እንደሚያደርገዉ ከወዲሁ ያዉቃሉ። ነገር ግን «ይኸው እናንተ ከተቃዋሚዎች ጋር ተደራደሩ ስትሉን፣ እሺ ብለን፣ በራሳችን አነሳሽነት፣ ለግንቦት ሰባት፣ ኦብነግ ጥያቄ አቀረብን። እነርሱ ግን ፍቃደኛ አልሆኑም። ከኦብነግ ጋር ተደራደርን ፣ ግማሾቹ እሺህ ብለው የተወሰኑት ግን እምቢ አሉ። ታዲያ ምን አድርጉ ነዉ የምትሉን ? » ለማለት ነዉ።
አገር ቤት ያሉ ፓርቲዎችን «እንደራደር» ቢሉ እሺ እንደሚሉ፣ በዚያም ድርድር የፖለቲካ ምህዳሩን በትንሹም ቢሆን መክፈት ኢሕአዴጎች እንደሚኖርባቸው፣ የፖለቲካ ምህዳሩን በትንሹ ከከፈቱና በአንጻራዊነት ዴሞክራቲክ ምርጫ ከተደረገ፣ እንደሚሸነፉ ያውቃሉ። በመሆኑም ባለ አቅምና ጉልበት፣ ጠንካራ ፓርቲዎችን እያዳከሙ፣ ዋጋ ቢስና ምናምንቴ ዘጠና፣ መቶ የሚቆጠሩ ፓርቲዎችን አየለቃቀሙ፣ ዲሞክራሲ እንዳለ ለማስመሰል ይሞክራሉ። አገር ቤት ያሉት ጠንካራ መሪዎችን በአንድ በኩል እያሰሩና እያወኩ፣ ዉጭ ካሉ፣ ሊስማሙ ከማይችሉ ጋር እንደራደር በማለትም፣ የ«ሰላም አርበኞች» መስሎ ለመታየት ይጥራሉ። አሳዛኝ !!!!!
ድርድርና ሰላም የሚጠላ የለም። ኢሕአዴግ በቅንነት ለእርቅ ተዘጋጅቶ፣ እራሱን አሻሽሎ፣ የሕዝብን ጥያቄ ሰምቶ ፣ የዜጎችን መብትና ነጻነት አክብሮ፣ ለአገራችን ልማትና ብልጽግና ከሁላችንም ጋር በጋራ ለመስራት ቢዘጋጅ፣ ደስታዬ ገደብ አይኖረዉም። ያም እንዲሆን የድርሻዬን ከመወጣት ወደ ኋላ አልልም። ጸሎቴም ነዉ።
ነገር ግን ፣ ያ አልሆነም። ኢሕአዴግ ዉስጥ ያሉ ጥሩ ሰዎች እየተዋጡ፣ ከመጋረጃ ጀርባ የተቀመጡ፣ ጥቂት ፈላጭ ቆራጭ የሆኑ፣ አክራሪዎች ድርጅቱን ወደ ገደል እየከተቱት ነዉ። ምንም እንኳን በአቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ የሚመራ የመንግስት መዋቅር ቢኖርም፣ አክራሪዎቹ የሚመሩት ሁለተኛና ሚስጥራዊ የመንግስት መዋቅር ያለ ይመስለኛል። በዚህ መዋቀር ያሉቱ የፈለጉትን ይገድላሉ። የፈለጉትን ለፍርድ ቤት ትእዛዝ ሰጥተዉ ያሳስራሉ። የፈለጉትን መሬት ለዉጭ አገር ዜጎች (ለእንደነ ሳዉዲዎች) በርካሽ ይሸጣሉ። የፈለጉትን እቃ ያለ ቀረጥ ያስገባሉ። የፈለጉትን ከአገር ያስወጣሉ ። ለዘመዶቻቸው ቢዝነስ ስለተፈለገ፣ ዜጎችን በግፍ አፈናቅለው ፣ የዜጎችን ቤት አፍርሰው በቦታዉ የነርሱን ሕንጻ ያሰራሉ። የፈለገ ወንጀል ሲሰሩ አይጠየቁም። እነርሱ በዊስኩ እጃቸዉን እየታጠቡ፣ ሌላዉ ወገናችን ግን ለስደት፣ ለጠኔ የተጋለጠ ሆኗል።
ምንም እንኳን ከኢሕአዴግ ዘንድ ሊታዩ የሚችሉ ጥቂት መልካም አዝማሚያዎች ላይ በር መዝጋት ባያስፈልግም፣ ምንም እንኳን ኢሕአዴግ ዉስጥ ያሉ ጥሩ ኃይላትን ማበረታቱ ጠቃሚ ቢሆንም፣ እንቁላሎቻችንን በኢሕአዴግ ቅርጫት ዉስጥ ብቻ ማድረጉ ግን ጉዳት አለው። የአገዛዙንም ርካሽ ፕሮፖጋንዳም ሆነ የድርድር ወሬ ከቁም ነገር መዉሰድ ያለብንም አይመስለኝም። ኢትዮጵያዉያን አንድ ዜና በመጣ ቁጥር፣ ወደዚህና ወዲዚያ እየነፈስን፣ ከዋናዉ ነገር ላይ ትኩረታችንን ማንሳት ማቆም ይኖርብናል። ዉጤት ከማያመጣና በስሜት ላይ ብቻ ከተመረኮዘ እንቅስቃሴዎች አልፈን መሄድ ይጠበቅብናል። በተለይም ደግሞ፣ አጠንክሬ የማሰምረበት፣ ሻእቢያ ወይንም ሻእቢያ ጋር ያሉ ቡድኖች ነጻ እንዲያወጡን አንጠብቅ። አሜሪካና አዉሮፓውያንም ጥቅማቸውን እንጂ ለኢትዮጵያ አያስቡም። «እናንተ ለመብታችሁ ካልታገላችሁ እኛ ምን አገባን ነዉ ?» ነዉ የሚሉት።
እግዚአብሄር በጸጋዉ የቸረንን፣ ጥቂቶች የሰረቁንን መብታችንን፣ ነጻነታችንና እኩልነታችንን የምናስጠብቀዉ እኛዉ እራሳችን ነን። በአሥር ሚሊዮኖች እንቆጣራለን። እያንዳንዳች ከልባችን «በቃ» ብንል፣ ለመብታችን ብንነሳ፣ ብንቆርጥ፣ ብንጨክን፣ የለበስነዉን ፍርሃት አዉልቀን ብንጥል፣ ለውጥ የማናመጣበት ምንም ምክንያት የለም። እኛን ማስፈራራትና መከፋፈል በመቻሉ እንጂ፣ ኢሕአዴግ እፍ ቢባል በቀላሉ የሚበን፣ የሞተና የበሰበስ ድርጅት ነዉ። እራሳችንን አሳንሰን አንመልከት። በዘር በሃይማኖት አንከፋፈል። ከአዲግራት፣ እስከ ሞያሌ፣ ከወልወል እሰከ አሶሳ፣ በቆላዉና በደጋዉ የአገራችን መሬት የምንኖር፣ በስደት በአለም ዙሪያ የተበተንን ኢትዮጵያዊያን ሁሉ እንነሳ። ሰላማዊ በሆነ መንገድ፣ ጥይት ሳይተኮስ፣ በሰለጠነ የፍቅር ፖለቲካ የኢትዮጵያን ትንሳኤ ማወጅ እንችላለን። ሰላማዊ በሆነ የእምቢተኝነት ዘመቻ የአገዛዙን ቀንበር መስበር እንችላለን። እየገደልን ሳይሆን እየሞትን አናሸንፋለን።