ከገለታው ዘለቀ
geletawzeleke@gmail.com
መቼም ሰው ሥጋ ነኝና ታከተኝ
እረፍት ለጎኔ ናፈቀኝ
ሩጫዬን ግን ጨርሻለሁ
እምነቴንም ጠብቂያለሁ
እነሆ ከፊቴ ……….
ከሰማዩ ከላይ ኣባቴ
የድል ኣክሊል ተዘጋጅቶልኛል
የሰላም የፍትህና የ’ኩልነት
ደግሞ የህግ በላይነት
ዋንጫዎች ይጠብቁኛል
እስትንፋሴ ሳይለይ ግን ኣንድ ነገር ልበል……..
ኣንቺ ኣፍሪካ………
እትብቴ ስወለድ የተቀበረብሽ
ዘመኔን ሁሉ የሰጠሁሽ
እናት ዓለም ኣዳምጪኝማ
ኑዛዜ ቃሌን ጻፊልኝማ
ኣዳምጪኝማ ልንገርሽ
ምክር ተግሳጼን ልስጥሽ
ብዙህ ተፈጥሮሽን
ቀስተ ደመናነትሽን
ውበትሽ ኣርጊው ድሪሽ
ክብርና ልዕልናሽ
ኣትለይው ካንገትሽ ላይ
ዘመን ሲመጣ በዘመን ላይ
ኣንቺ ደቡባዊት ኣፍሪቃዬ
አትብቴ የተቀበረብሽ እመዬ
እንደገና ኣንድ ነገር ላስተንክርሽ
ኣዳምጪኝ እማ ሆይ እባክሽ
ያኔ በለቅሶ ዘርን ስትዘሪ
የነጻነትን፣ የፍትህን ኣባት ስትጣሪ
ጩኸትሽ ከጸባኦት ገብቶ
ቅንፈረጁን ኣምላክ ኣትግቶ
የኢያሪኮን ግንብ ኣፈረሰው
የግዞት ቤቱን ደረመሰው
የብረት በሩን ኣባተው
እግረ ሙቁንም ኣቀለጠው
ት ዝ ይለኛል……
ስወጣ እስራቴ ተፈቶልኝ
ምናቤ ተከፍቶ እንዲህ ኣሳየኝ
አነሆ ጸሃይ ህጉዋን ሰብራ
የተፈጥሮ ልማዱዋን ሽራ
በደቡብ በኩል ስትወጣ
የዘንባባ ዝንጣፊ ኣምጥታ
ኣየኋትና ደስ ኣለኝ
ተሰፋና ሃሴት ወሰደኝ
ኣይኔ በሮቶልኝ ኣሻግሬ ሳይ
ከጸሃይ መውጪያ ወዲያ ማዶ ላይ
ከኒያ ካሳለፍናቸው ክፉ ዘመናት በላይ
ክምር የመልካም ነዶ ዘመን ተቆልሎ ባይ
የኣሁኑ ዘመን ስቃይ
ሊመጣ ካለው ክብር ጋር ሲተያይ
እንደ ኢምንት ሆኖ ኣየሁትና
የዘንባባ ዝንጣፊ ኣነሳሁኝ
ሰላምና ፍትህን ኣወጅኩኝ
በቀልና ዘረኝነትን ኮነንኩኝ
የኩልነትን እጀታ ኣጥብቄ ኣጥብቄ ያዝኩኝ
ያ ነበር በውነት ያስደሰተኝ
በርጅና ዘመኔ ሁሉ እንደ ንስር የሚያድሰኝ
ኣንቺ ደቡባዊት ኣፍሪካዬ
አትብቴ የተቀበረብሽ እናትዬ
ከምድርሽ ፍሬ በልቼ
ከሖድሽ ጠበል ጠጥቼ
ኣድጊያለሁኝና
ምስጋናዬ ይሄውና
ያ የክረምቱ ጊዜ ኣልፎ
ዶፍ ዝናሙ ደመናው ሁሉ ተገፎ
እሰይ እሰይ ኣጨዳሽን ጀምረሻል
የመኸር ጊዜ መጥቶልሻል
ኣጨዳሽን እጨጂ
በርቺ ሂጂ ተራመጂ
ግን ደሞ ….
ኣንድ ነገር ኣትርሺ
ያን ያፓርታይድ ዘረኝነት እንዲያ አንደጠላሽው
ኣንገፍግፎሽ ኣንዘፍዝፎሽ ወዲያ እንዳልሺው
እንደዚያው እንደጠላሽው ኑሪ
በፍቅር ባቡር ብረሪ
አንዳትመለሽበት ኣደረሽን
ከነፍስሽ ጥይው እባክሽን
በራስሽ ላይ አንደጠላሸው
በሌላውም ላይ አታድርጊው
እነሆ አግዚኣብሄር በሰጠኝ ኣገልግሎት
የፍቅርና የሰላም ክህነት
ውጉዝ ውጉዝ ከመ ኣርዮስ
ውጉዝ ከኣፍሪካ ብያለሁ ዘረኝነትን
ኣምባገነንነትና ኢፍታዊነትን
ኣትብቀሉ በምድሪቱ
ኣትለምልሙ ኣታኩርቱ
ባለም ሁሉ በምድሪቱ
ያለም ህዝቦች ሁላችሁ
የሰው ዘር ሁሉ የሆናችሁ
ከሰላምና ከእኩልነት ገበታ ብሉና ጠጥታችሁ ርኩ
ሰላም በሰላም ላይ ፍቅር በፍቅር ላይ ተኩ
የናቴ ያባቴ ልጅ ኣፍሪካ…………
ኣሁን ስጋዬ ረፍት ብጤ ናፈቀው
መቼም ሰው ነውና ስጋ ነውና ታከተው
ሄዶ ሄዶ ከዚህ ኣይቀርምና
የተፈጥሮ ህግ ኣይሻርምና
እኔ እንግዲህ ሄጃለሁ
ፍቅር ሰላም አኩልነት ላለም ሁሉ አመኛለሁ
ኣበቃሁ ቃሌ ይሄው ነው ኑዛዜየን ኣድርሻለሁ
ሃብቴ ቅርሴ ያለኝ ይሄው
ኑዛዜየ ስጦታዬ እምነቴ ነው