ከሙሼ ሰሙ
በመጀመርያዎቹ ሃያኛው መቶ ክፍለ ዘመን ማብቂያ ላይ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶችን አስመልክቶ ባረቀቀው ደንብ አንቀጽ 18 ላይ ስደተኞችን ወይም መጤዎችን ስለማፈናቀል ድንጋጌ አውጥቶ ነበር፡፡ ድንጋጌው እንደሚያትተው ከሆነ መጠነ ሰፊ በሆነ ደረጃ፣ ያለማመዛዘን፣ ልዩነት ሳያደርግ ሃይል በታከለበት ሁኔታ መጤዎችንና ስደተኞችን ማፈናቀል በሰብአዊ ፍጡር ላይ እንደተሰራ ከባድ ወንጀል ተቆጥሮ አባል ሃገራት በድርጊቱ ፈጻሚ መንግስታት ላይ የጋራ አቋም እንዲወስዱ ስምምነታቸውን የሚጠይቅ ነበር፡፡
ይህ የተባበሩት መንግስታት ደንብ የሁሉንም ሃገራት ይሁንታ በተለያየ ምክንያት ማግኝት ባይችልም፤ በዓለማችን ላይ ስደተኛ የሌለው ሃገር ከቶም ሊገኝ ስለማይችል በመርህ ደረጃ ሁሉም መንግስታት የሚስማሙበት ጉዳይ እንደሆነ ጥርጥር የለውም፡፡ የዓለማችን የመጎጎዣ ስርዓት እጅግ በመቀልጠፉና በመዘመኑ፣ የጉዞ ውጣ ውረዳችን ከቀናት ወደ ሰዓታት በመቀነሱ፣ መረጃዎች በስፋትና በጥልቀት በመናኘታቸው ምክንያት ዓለማችን ከመቼውም ጊዜ በላይ ጠባለች፡፡ በዚህም ምክንያት የተሻለ ኢኮኖሚያዊም ሆነ ፖለቲካዊ ሕይወት ፍለጋ ቁጥራቸው ይብዛም ይነስ ዜጎቹ ለስደት የማይዳረጉበት ሃገር የለም፡፡ እንግሊዞች ሁለተኛ ሃገራችን ወደሚሏት አሜሪካ ተሰደው፣ ይሰራሉ፡፡ እስራኤሎች፣ የሳኡዲ አረቢያና የአውሮፓ ዜጎች ሳይቀሩ በየሃገሩ በመኖር ሕይወታቸውን ለማቃናት ብሎም ለሃገራቸው ለመትረፍና ከግፍና መከራ ለመሸሽ ይሰደዳሉ፡፡ ዛሬ ላይ ሲወሳ እውነት ሊመስል ባይችልም፤ አብዛኛዎቹ የመካከለኛው ምስራቅ ሃገራት ነዋሪዎች ሕይወታቸውን የሚገፉት በስደተኛነት እንደነበረ እጅግ ቢርቅ ከአንድ ትውልድ የማይዘል ሃቅ መሆኑን መረዳት ያሻል፡፡
መጠነ ሰፊ ማፈናቀል (Mass Deportation) በዓለምችን ላይ አዲስ ክስትት አይደለም፡፡ የሳሳንያው ስረወ መንግስትና የፐርዢያው ንጉስ ኮስራው/ሽራው/ 292,000 ባርያዎችንና ምርኮኞችን በጦርነት ካሸነፋት ሃገር አፈናቅሏል፡፡ አሜሪካኖች በየዓመቱ በአስር ሺህ የሚቆጠሩ የላቲን ዜግነት ያላቸውን ስደተኞች አስገዳጅነት በተቀላቀለበት መንገድ ወደ ትውልድ ሃገራቸው ታባርራለች፡፡ እስራኤሎች ቁጥር ስፍር የሌላቸው ፈለስጢናውያንን ከቤታቸውና ከቀያቸው ሲያፈናቅሉና ሲያሰድዱ ዘመናት ተቆጥሯል፡፡ እስከዛሬም ድረስ ፈለስጢናውያን ሃገር አልባ እንደሆኑ ይታወቃል፡፡
በዓለም ታሪክ ከፈለስጢኖች ቀጥሎ በመጠነ ሰፊነቱና በአሰቃቂነቱ በተለይ ተጠቃሽ የሆነው ማሰደደና ማፈናቀል ቱርኮች በአርመኖች ላይ እ.ኤ.አ ከ1915 ጀምሮ በሶስት ተከታታይ ሂደት የፈጸሙት ማፈናቀል ነበር፡፡ በአንደኛው ዓለም ጦርነት ከጀርመንና ከኦስትሮ ሃንጌሪያውያን ጋር ያበረችው ኦቶማን ቱርክ እ.ኤ.አ በ1922 የደረሰባት አሳፋሪ ሽንፈትና ውድቀት ከአንድ ሚሊያን ለሚበልጡ አርመኖች ከቀያቸውና ከመንደራቸው ለመነቀልና ሃገር አላባ ሆነው የስደተኛ ሕይወት እንዲገፉ ምክንያት ሆኗል፡፡ በሃንጌሪ፣ በሎክስመበርግና በቤልጅየም የተፈጸሙ በርካታ ማሰደዶችና ማፈናቀሎች ሌሎች ተጠቃሽ ምሳሌዎች ናቸው፡፡
ሕጋዊ በሆነ መንገድም ሆነ ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ወደ አንድ ሃገር የሚገቡ መጤዎችንና ስደተኞችን ወደ መጡበት ሃገር ማሳደድ ወይም ማፈናቀል (Mass Deportation) የሉዓላዊ ሃገራት ወይም መንግስታት የማይገሰስ መብት ነው፡፡ ከሞራል ሙግት ውጭ ምክንያት ሊጠየቅበት የሚችል አይደለም፡፡ ይህንን ስንል ግን ዜጎቹ የተሰደዱበት ሃገር መንግስት በዜጎቹ መሳደድና መፈናቀል ምክንያት የተከሰተውንና የሚከሰተውን ኢኮኖሚያና ማህበራዊ ቀውስ አስመልክቶ ሊነሳ የሚገባው ጥያቄ የለም ማለት አይደለም፡፡ አጠቃላይ የካሳ ጥያቄ አንዱ ነው፡፡ በተለይ ትኩረት ከሚሰጣቸው ጉዳዮች ውስጥ ቅድሚ የሚሰጠው ስደተኞቹ ከውርደትና ከመብት ረገጣ ከለላ የሚያገኙበትን ሁኔታ ማምቻቸት አንዱ ሲሆን ሌላው ተሰዳጆቹ ሃብት ንብረታቸውን ሳይነጠቅ እንዲሰናበቱ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ነው፡፡ ምክንያታዊ የሆነ መንግስት የዜጎቹ ውርደት የሃገር ውርደት መሆኑ ሊነገረው የሚገባ ጉዳይ አይደለም፡፡ ሃገር ያለ ዜጎቹ የሚዋረድበት ሌላ መገለጫ የለውም፡፡ ከዜጎች ውጭ ሃገር ማለት ድንጋይ፣ ተራራ ወይም መሬትና ወንዝ… ነው፡፡
በኢትዮጵያዊያን ስደተኖች ቁጥር ዙርያ ተጨባጭ መረጃ ማቅረብ ባይቻልም በዓለም ላይ በኢኮኖሚያዊም ሆነ ፖለቲካዊ ምክንያቶች በየሃገሩ የተበተኑ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ቁጥራቸው በሚሊዮኖች እንደሚቆጠር ይነገራል፡፡ ምናልባትም
ኢትዮጵያዊ ስደተኛ የሌለበት ሃገር ማግኝት አዳጋች እንደሆነም በርካታ ለስራም በግል የሚጓዙ ኢትዮጵያዊያን ይናገራሉ፡፡ በተቃራኒው ግን ስደት እንደዚህ ርካሽ የሆነባት ኢትዮጵያ ደግሞ ለስደት የተዳረጉ ዜጎቿን እውቅና በመንሳት፣ ጥበቃናና ከለላ በመነፈገ አቻ የማይገኛላት ሃገር ነች፡፡ ዜጎቻችን ለስደት የዳረገው ኢኮኖሚያዊም ሆነ ፖለቲካዊ ወይም የሰብአዊ መብት ጥሰት መንስኤ የሆኑ መሪዎቻችን በስደተኛ ዜጎቻችን ላይ የሚደርሱ ግፎችን አይቶተው እንዳለዩ ሰምተው እንዳልሰሙ መሆን መገለጫቸው ነው፡፡ ጫጫታው ገፋ ሲል ደግሞ የእብድ ገላጋይ ይመስል በስደተኞቹ ላይ ስም እየለጠፉ ለጥቃት ማጋለጥ ከአንዴም ሁለቴ የታዘብነው ፈተና ነው፡፡
በገዢዎቻችን ታሪክ ስደተኞች በመካድ፣ ከለላና ድጋፍ በመንፈግ በተለይ ኢህአዴግን የሚደርስበት የለም፡፡ ኢህአዴግ ከሽግግሩ ጊዜ ጀምሮ በኤርትራ መሬት በጦርነቱ ተሸንፈው ወደ የመን፣ ሱዳን ሊቢያና የመሳሰሉት ሃገራት የተሰደዱ ኢትዮጵያዊን ወታደሮችን እውቅና በመንሳት በርካታ ግፍና መከራን እንዲቀበሉ አድርጓል፡፡ ከጦር ቀጠናቸው ውጭ ኤርትራን የማያውቁ በርካታ ወታደሮቻችን በኤርትራ በረሃዎች ላይ ሰብሳቢና ተመልካች ማጣታቸው ሳይንስ ከሰው ፍጠሩ ያልተወለዱ ይመስል የቂም በቀል መወጣጫ ሲሆኑ ኢህአዴግ “ሃይ፣ ጉዳዩ በዓለም አቀፍ ሕግን ስርዓት ይዳኝ” ማለት ስላልፈለገ ዜጎቻችን የትም ባክው ቀርተዋል፡፡ ይበልጥ የሚያስደንቀው ደግሞ ዜጎቻችን “ለወረራ የዘመቱ የደርግ ወታደሮች” ናቸው በማለት የእብድ ገላጋይ ዱላውን በማቀበሉ ወታደሮቹ አይከፍሉ ዋጋ እንዲከፍሉ መንስኤም ሆኖ ነበር፡፡ ዛሬ የተረሳ ቢመስለም በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ታሪክ በአስከፊነታቸው ከሚብጠለጠሉት አሳዛኝ ግፎች ባልተናነሰ ደረጃ ጠባሳውን ጥሎ ያለፈ ሂደት ነበር፡፡
ደርግ በሽብር እየታገዘ እንደ እርድ ከብት ከእርሻ መሬታቸውና ከየትምህርት ቤቱ ያነዳቸው የድሃ አርሶ አደርና የከተሜ ልጆች በኤርትራ መሬት ላይ ለሽንፈት መዳረጋቸው ሳያንሰቸው ተጨማሪ ግፍና መከራ ይቀበሉ ዘንድ ኢህአዴጎች ከሻቢያ ጋር ሊመሳጠርባቸውም ባልተገባ እንደነበር ዛሬ ላይ ድርጅቱ የሚስተው አይመስለኝም፡፡ ጥርሳቸው እየተነቀለ፣ ንብረታቸውን እያተዘረፉ እርቃናቸውን ወደ መጡበት እንዲመለሱ በመደረጋቸው ቁትር ስፍር የሌላቸው ዜጎች በየበርሃውና ጥሻው ውስጥ ወድቀው ቀርተዋል፡፡ በኮንቴይነር ውስጥ እየታሸጉ በባርነት ጉልበታቸውን የተበዘበዙ ወታደሮች ቁጥር ማንም ሊገምተው ከሚችለው በላይ እንደሆነ የሚዘነጋ አይደለም፡፡
ጊዜ ማለፉ እንደማቀር የሚውቁ አብው ሲተርቱ “ለሕሊናህ መፈረድ ቢያቅት ለጊዜ ፈረድ ይላሉ፡፡ ዛሬ ላይ ያ ሁሉ አልፎ ለደረሰው ውጥንቅጥ ሁሉ መንስኤ የነበሩት አዝማች የደርግ ባለስልጣናት “ይቅርታን አግኝተው” መጽሐፍ ለመድረስና በኢህአዴግ መድረኮች እያተጋበዙ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ለመወያየትና ኢህአዴግን ለማማከር በቅተዋል፡፡ በተቃራኒው ደግሞ እነዚህ ወጣቶች ባልቀሰቀሱትና ባልፈቀዱት ጦርነቱ ውስጥ ተማግደዋል፡፡ ብዙዎቹም ከሞት መንጋጋ ማምለጥ ቢችሉም “የደርግ ሰራዊት” ነበሩ በሚል ሰበብ ብቻ በዓለም አቀፍ ሕግ የተደነገገውንና ለጦር ምርኮኛ የሚገባውን ጥበቃና ከለላ ሳያገኙ በመቅረታቸው የቂም በቀል መወጣጫ ለመሆን ሆነዋል፡፡ ኢህአዴግ በወቅቱ ለሕሊናም ሆነ ለጊዜ ባለመፍረዱ ቢያንስ አዝማቾቻቸው በይቅርታ ሰበብ የተቋዳሱትን የእፎይታ ሕይወት እንኳን ለመቋደስ አልታደሉም፡፡ ከጥፋታቸውም ሆነ ከሕሊና ጸጸት ይድኑ ዘንድ እድል አላገኙም፡፡
ምክንያታቸው ሊዋጥልኝ ባይችልም ኢህአዴግን ለመከላከል ሲባል ብቻ ጉዳዮችን በቀላሉ ከማያጣፉት የኢህአዴግ ካድሬዎች የሚያነሱ ኢህአዴግ መንግስት አልነበረም የሚሉ መከራከርያዎች እንዳሉ እገምታለሁ፡፡ ችግሩ የሚነሳው ኢህአዴግ መንግስት ለመሆን መደላድሉን ያላመቻቸና እርካቡን ያልተቆናጠጠ በመሆኑ ነው አልነበረም፡፡ ችግሩ የርዕዮተ ዓለምና የአመለካከት ነው፡፡ ዛሬም የሳኡዲውን ሌሎችንም ስደተኞችን በሚመለከት ያለው ግንዛቤ ይህው ነው፡፡ ኢህአዴግ ፍላጎቱ ቢኖረው ኖሮ መንግስት መሆን ሆነ አለመሆኑ ሊገድበው ባልተገባ ነበር፡፡ ተደማጭነቱ ቢቀር እንኳ፤ ቢያንስ አቤቱታ በማሰማት ጉዳዩ እንዲታሰብብትና አጀንዳ እንዲሆን ግፊት ለማድረግ ከግለሰብ የላቀ አቅም ነበረው፡፡ ደርግ በትጥቅ ትግል ዘመን በሕዝቦች ላይ በሚያካሂደው ማሳደድ ምክንያት ቀላል የማይባል ህዝብን እየተቀበለና እያገዘ እጅግ አስከፊ ስደቶችንና ውጣ ውረዶችን ከሕዝብ ጋር ያሳለፈ ድርጅት ውሎ ሳይድር በዚህ ዓይነት ድርጊት ውስጥ እጁ ሲገኝ መመልከት ለትንታኔ የሚከብድ መሆኑ አጠራጣሪ አይደለም፡፡
በዚህ ጉዳይ የኢህአዴግ ሁነኛ ባሕሪ ለመደገም ተጨማሪ አስርት ዓመታትን መጠበቅ አላስፈለገም ነበር፡፡ “ያዳቆነ ሰይጣን ሳያቀስ አይለቅም” እንዲሉ በ1990 ዓ.ም ያልተጠበቀው የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ሲፈነዳ ነገሮች ይበልጥ ፍንትው ብለው ወጡ፡፡ የደርግ ወታደሮች በሚል ስም ገና ከጅምሩ ስደተኞችን ከለላ በመንፈግና እውቅና በመንሳት አዲስ ታሪክ ያሟሸው
ኢህአዴግ፣ በመቀጠል ሚናውን ከተመልካችነት ወደ ስደተኛ አባራሪነት (Mass Deportion) አሳድጎ ብቅ አለ፡፡ ለዝንተ ዓለም ኢትዮጵያ ውስጥ በመኖር ኢትዮጵያዊነታቸውን በሕግ የተቀዳጁ፤ ነገር ግን በደም ኤርትራዊ የነበሩ አባወራ፣ ሴት፣ ሕጻናት ወይም ሽማግሌ ሳይመርጥ በጅምላ በማፈስ እስር ቤት እያጎረ ሃብት ንብረታቸውን ለመሰብሰብ እንኳን በቂ ጊዜ ሳያገኙ ከኢትዮጵያ አባሯል፡፡ ኢህአዴግ በኤርትራዊያን ላይ ኢ-ሰብአዊ ድርጊት ሲፈጸም ሂደቱን ለመቀልበስም ያልቻለው ወይም ያልፈለገው በሌላ ምክንያት ሳይሆን እንደዚህ ዓይነት የማሳደድ ድርጊቶች በሌሎች ላይ ሲፈጸም ዝምታን የመረጠ ድርጅት በመሆኑ ነበር፡፡
ዛሬ ላይ ኢህአዴግ በስደተኞች ላይ የሚያሳየው ፍጹም የሆነ ቸልተኝነት መንስኤው ገጽታ ያበላሻሉ ከሚል ጥቅል ድምዳሜ እንደሚነሳ እገምታለሁ፡፡ በተለይ ደግሞ ወደ አረብ ሃገርት በድህነት ምክንያት ስራ ፍለጋ ለሚሰደዱ ዜጎች እውቅና መስጠት የልማት አጀንዳዬንና ያስመዘገብኩትን ኢኮኖሚያዊ እድገት ያጨልማል፣ በስራ ፈጠራና በልማት ተጠምጄ እያለሁ እነሱ በስደት በመጠመድ የችግሩን ስፋትና ጥልቀት ገሃድ ያወጣሉ የሚል ድብቅ ( የማይነገር) ሰበብ ስላለው እንደሆነ መገመት አያዳግትም፡፡ ኢህአዴግ ከነባራዊ ሁኔታው ተነስቶ ስደተኞቹ ከችግሩ ጥልቀትና ስፋት የተነሳ ከመሰደድ እንደማይቦዝኑ ያውቃል፡፡ በዚህም ምክንያት ድህነትን ከስሩ አድርቄዋለሁ ማለትና በድህንት ሰበብ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ተሰደዋል ማለት ለፕሮፓጋንዳ አያመችም፡፡ ያለው አማራጭ ስደተኞቹ በሚሊየን ቢቆጠሩም በሰላሳ ሺዎች እየገደቡ እንደ ሳኡዲዎቹ ጉዳዩ ገንፍሎ ገሃድ እስኪወጣ ድረስ እውቅና መንሳት ብቻ ነው፡፡
በመካከለኛው ምስራቅ በተለይ በሳኡዲ አረቢያ፣ በኩዌትና በሊባኖስ በሌሎቹም ሃገራት የዜጎቻችን የአካል ክፍሎች (Organs) ባልሰለጠኑ የመንደር ሃኪሞች ስለት እየተሞሸለቀ ለቱጃር አረቦች ሲቸበቸቡ ኢህአዴግን ጨምሮ ሁላችንም ለመታዘብ ችለናል፡፡ ዜጎቻችን ከህንጻ ላይ እየተወረሩ ተነኳኩተው በቃሬዛ አሊያም ከተሸከርካሪ ወንበር ጋር ተቆራኝተው ያለ ካሳ አንደ አሮጌ እቃ ሲወረወሩ ተመልክተናል፡፡ በየመን፣ በሱማሌና በሊቢያ በረሃዎች ዜጎቻችን አይዋረዱ ውርደት ሲዋረዱና መሸሺያና መከለያ አጥተው ጦርነት ላይ እንደተማረኩ የዝሙት ባርያዎች (Sex Selave) በሰንሰለት እየታሰሩ የዝሙት ፍላጎት ማርኪያ ሆነዋል፡፡ ወንዶቹ በባርነት ሲያገለግሉ የተቀረጹ ዶክመንትሪ ፊልሞችን በዓለም ዓቀፍ መገናኛ ብዙሃን አማካኝነት በጋራ ተመልክተናል፡፡ በደርግ ስርዓት ጦርነትና የመልካም አስተዳደር እጦት ፤ የተቃና የኢኮኖሚ ፖሊሲ አለመኖርን የመብት ረገጣ ባደረሱቡን ፈተና ምክንያት ሰቆቃችን፣ እርዛታችንና ልመናችን ዓለምን እንዳላሰለቸ ሁሉ ዛሬ ደግሞ ስደታችንና የስደተኝነት ታሪካችን መንግስታዊ ከለላና ድጋፍ በመነፈጉ የዓለም መገናኛ ብዙሃን መጠቋቆሚያና መዘባበቻ እንድንሆን አድርጎናል፡፡
በዚህ መልኩ በኢትዮጵያውያን ስደተኞች ላይ የሚደርሰው የተናጠል ኢ-ሰብአዊ ድርጊት ተባብሶና ገዝፎ ጭካኔ ወደ ተሞላበት መጠነ ሰፊ ማፈናቀልና ማሰደደ ሲሸጋገር ኢህአዴግ የጉዳዩ ባለቤት መሆኑን መቀበል ባለመፈለጉ እራሱን በታዛቢነት አስቀምጦ መክረሙ ቀጣዩ አሳዛኝ ትዕይንት ነበር፡፡ ኢህአዴግ በተለይ በስደተኛች ጉዳይ ዘንድሮም እንዳልተሻሻለ የሚያረጋግጠው፤ በኤርትራ መሬት ላይ በስደት ሲባክኑ የነበሩ ወታደሮችን “ወራሪ የደርግ ወታደር” ማለቱ ለጥቃት በር የከፈተ መሆኑን ዘንግቶ፤ ዛሬ ላይ ደግሞ ከሳኡዲ በግፍ ለተፈናቀሉ ዜጎቻችንን ሌላ ተቀጻላ ስም ለመስጠት አለመቦዘኑ ነበር፡፡ ኢህአዴግ ግፉ እንደተጀመረ ሰሞን እራሱን ከደሙ ንጹሕ ለማድረግ ያቀደ በመሆኑ “ሕገ ወጥ ስደተኞች” የሚል ተቀጽላ በመስጠት ለመከራቸውና ውጣ ወረዳቸው ጀርባውን መስጠቱ ይታወሳል፡፡
የእስልምና ሃይማኖት ተከታይ ስደተኞችን በመቀበሏ ትልቅ ስፍራ የሚሰጣትን የኢትዮጵያ ሃገራችን ስደተኞች የእስልምና መሰረት በሆነችው በሳኡዲ አረቢያ አምባገንን ፖሊሶች፣ ደህንነትና ሰራዊት አማካኝነት በጠራራ ጸሃይና በዓለም አቀፍ መገናኝ ብዙሃን ካሜራ ፊት አስነዋሪ ድርጊት ፈጽመውብናል፡፡ ሰብአዊ ክባራችንን አዋርደዋል፡፡ ዜጎቻችንን ገድለዋል፡፡ ሴቶቻችንን ደፍረዋል፡፡ ሃገራዊ ክብራችንን ተፈታትነዋል፡፡ ይህ ሁሉ ድርጊት በሳኡዲ አረቢያ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኢምባሲ ደጃፍ ስር መፈጸሙ ሌላ አሳፋሪ ጉዳይ ነው፡፡ ኢምባሲው በሩን ከፍቶ የዜጎቻችንን መከራ ለመቋደስ መድፈር ቢያቅተው አንኳን ብሶታቸወን ለመዳመጥ በሩን ገርበብ አድርጎ መታዘብ አልቻለም፡፡
ይልቁንም የኢምባሲው አባላት በዘመናዊ ፎቴ ላይ ተቀምጠው የዜጎቻችንን ግፉ በዲሽ እንደ ፊልም እየተመለከቱ መመሪያ ከመጠበቅ ያለፈ ሚና አልነበራቸውም፡፡ ኢምባሲው የስደተኞቹን ፓስፖርት ለማደስ የአባይ ቦንድ መዋጮ ካልከፈላችሁ በማለት ቁም ስቅል ሲያሳያቸው ከርሞ ከሰባት ወር ውጣ ውረድ በኃላ ፓስፓርታቸውን ሳያድስና ሕጋዊነታቸውን ሳያረጋግጥ በመቅረቱ ያ ሁሉ መዓት በዜጎቻችን ላይ ሊወርድ ችሏል፡፡ ይህ የተለመደው የኢህአዴግ ችግር መገለጫ በመሆኑ
ለዚህ የዜጎቻችን ፈተና የተጠየቀም ሆነ ኃላፊነት የወሰደ የለም፡፡ ሕዝባዊ ነኝ ለሚል ድርጅት በግብር ከፋይ ሕዝብ ወጭ ለሚያለግሉና ለሕዝብ ለማይቆሙ ጥቂት የኢምባሲ ሰራተኞችን ከላላ መሆኑና ከሕዝብ ቁጣ መሸሸጉ እንቆቅልሽ ከመሆን ሊዘል አይችልም፡፡
እርግጥ ነው የሳዑዲ መንግስት የስራ ፈቃድ የሌላቸውን ቀርቶ ፈቃድ ያላቸውን ስደተኞችም ቢሆኑ ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ ተገቢውን ካሳ ከፍሎና ንብረታቸውን እንዲሰበስቡ አደርጎ ባዘጋጀላቸው ትርንስፓርት ግፍና መንገላታት ሳይደርስባቸው ማሰናበት ይችላል፡፡ የሳኡዲ መንግስት ይህንን አድርጎ ቢሆን ኖሮ ጥያቂ ሊነሳበት ባልተገባ ነበር፡፡ ነገር ግን፤ ከላይ ለማንሳት እንደሞከርኩት የተፈጸመው ግፉ መስመሩን የሳተ እንደመሆኑ መጠን ኢህአዴግ ለስደተኞቹ ተቀጸላ ስም እየሰጠና ቁጥራቸውን እያወራረደ ለጥቃት ከማጋለጥና ከደሙ ንጹሕ ለመምስል ከመትጋት ይልቅ፤ በቂ ምክንያት ስለነበረው ቢያንስ ማፈናቀሉንና ማሰደዱን ማስቆም ባይችል እንኳ መፍትሔ ሊያገኙ በሚገባቸው በርካታ የዜጎነት ጉዳዮች ዙርያ ጥላ ከለላ በመሆኑ በሕጋዊ መድረኮች ሁሉ መሟገት ነበረበት የሚል ጽኑ እምነት አለኝ፡፡ ለዚህም ቢያንስ ቢያንስ እነዚህን መሰረታዊ ጉዳዮች ማከናወን ነበረበት፡፡
የመጀመርያውና ወሳኙ ጉዳይ ለዜጎቹ እውቅና መስጠትና ለክብር ዘብ መቆም ነበር፡፡ ሳኡዲዎች በዚህ ደረጃ ዜጎቻችንን ሰብአዊ ክብራቸውን እንዳያዋርዱ ለመከላከል ኢህአዴግ ከሳኡዲ መንግሰት ጋር በማንኛውንም ጉዳይ ጋር ለመነጋገር ዝግጁነቱን ቀድሞ በመግለጽ በዜጎቹ ጉዳይ ሃላፊነት የሚሰማውና የዜጎቹን ክብር ለመታደግ ግዴታውንና ኃላፊነቱን የሚወጣ መንግስት መሆኑን ማረጋገጥ ነበረበት፡፡ ስደተኞቹ ለዚህ ሁሉ ጥቃት ለመጋለጥ የቻለሁትም ይህ ባለመሆኑና ባለቤት፣ ተጠሪም ሆነ ወቃሽ የሌላቸው ተደርገው በመወሰዳቸው እንደሆነ መረዳት ይቻላል፡፡ ስደተኞች ኑሮ ስለደላቸውና ስለተረፋቸው እንዳልተሰደዱ ይታወቃል፡፡ በርካታዎቹ መሬታቸው ምርት መስጠት አቅቶት በማረጡ ምክንያት ሌላ የሕይወት መንገድን የመረጡ ናቸው፡፡ ይህንንም የስደት ሕይወት ለማሳካት ሃብት ንብረታቸውን ሽጠው ወይም ተበድረውና ተለቅተው ጉዞ የጀመሩ ናቸው፡፡ ፊታቸውን ወደ ሃገር ቤት አዙረው ለመመለስም መጀመርያ እዳ መክፈል የሚችሉ መሆናቸውን ማረጋገጥ ነበረባቸው፡፡ ቀጥሎም እዳቸውን መክፈል ቢችሉ ዳግም ወደ ችጋርና ሰቆቃ ሕይወት ላለመመለስ ትንሽም ብትሆን ጥሪት መቋጠር ነነበረባቸው፡፡ አብዛኛዎቹ ስደተኞቹ ይህንን ማቃናት ባለመቻላቸው ተይዘው ከመመለስ ይልቅ እራሳቸውን ከሕግ በመሰወር ለመደበቅና ለመሸሽ መሞከራቸው የግድ ነበር፡፡ ይህንን ውስብስብ ችግር ለሳኡዲ መንግሰት፣ የደህንነትና የፖሊስ ተቋማት ቀድሞ በማስረዳት በሕገ ወጥነት ተፈርጀው ግፍ እንዳይፈጸምባቸው መከላከል ይቻል ነበር ፡፡
ሁለተኛው አነሰም በዛ የጉልበታቸውን ዋጋ የማስከበር ጉዳይ ነው፡፡ በመጀመርያውንም ዜጎቻችን የተሰደዱት ሃብት ለማፋራት አቅደው በመሆኑ ሃብታቸውን የማሰባሰብ ጉዳይ ኢህአዴግ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነበር፡፡ እነዚህ ስደተኞች በሳኡዲ ኢኮኖሚ ውስጥ ርካሽ ጉልበታቸውን በመሸጥ ቀላል የማይባል አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸው መገመት ይቻላል፡፡ በተለይ ደግሞ ማሰደዱ ሃይልና ግፍ የተቀላቀለበት በዘመቻ የተደረገ እንደመሆኑ መጠን ብዙዎቹ ያፈሯትን ጥሪት ለመሰብሰብና ደሞዛቸውን ለመቀበል እንኳን ፋታ አላገኙም፡፡ ስደተኞቹ ወደ ሃገር ተመልሰዋል፡፡ ሃብት ንብረታቸው ግን የትም ተዝረክርኮ ይገኛል፡፡ ሃብት ንብረታቸውን የማሰብሰብ ጉዳይ አሁንም ያልተፈታ ጥያቄ በመሆኑ ኢህአዴግ ዛሬም ላይ ሆኖ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ ኢህአዴግ ዓለም አቀፍ ግፊትና ተጽእኖ ፈጣሪ ተቋማትንና መንግስታትን መሰረት በማድረግ የሳኡዲን መንግስት ወደ ድርድር መውሰድ አለበት፡፡ ይህ ካልሆነም ጉዳይን ወደ ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት በመውሰድ ዜጎቻችን ተገቢውን ካሳ አንዲያገኙ ክስ በመመስረት ለዜጎቹ ጉዳይ ተጠሪና መንግስት መሆኑን በተግባር ማሳየት አለበት፡፡ ይህ እንቅስቃሴ ለስደተኞቹ ከሚያስገኘው ጥቅም በላይ ወደፊት ሌሎች መንግስታት በኢትዮጵያዊያን ላይ እንዲዚህ ዓይነት ድፍረት የተሞላበት ኢ-ሰብአዊ ድርጊት እንዳይፈጽሙ ተመክሮ ይሰጣል የሚል እምነት አለኝ፡፡
የሳኡዲ ስደተኞቹ ወደ ሃገራቸው ከመመለሳቸው ውጭ እዚህ ግባ የሚባል ተጨባጭ ስራ እየተሰራ እንዳልሆነ ለመገመት አያዳግትም፡፡ የሳኡዲ ስደተኞች ሕይወት ምናልባትም ከነበሩበት በባሰ ሁኔታ አስቸጋሪ ነገር ላይ እንደወደቀ የሚያሳዩ በርካታ ጠቋሚ ምልክቶች እያታዩ ነው፡፡ በቁጥር ቀላል የማያባሉት ወደ ቀያቸው ከመመለስ ይልቅ በየመንደሩ በሚገኙ ዝቅተኛ መኝታ ቤቶች አስርና አስራ አምስት እየሆኑ በደቦ መኖር ጀምረዋል፡፡ ሴቶች እህቶቻችን በሂደት ለምን አይነት ሕይወት እያተዘጋጁ እንደሆነ መገመት ይቻላል፡፡ ወንዶቹ ዳግም በተለመደው መንገድ ወደ መጡበት ስደት ለመመለስ ጉልበትና አቅም እስኪፈጠር በመጠባበቅ ላይ ናቸው፡፡ ለመሰንበት ሲባልም ወደ አስከፊ ሕይወት ማዝገማቸው የሚገመት ጉዳይ ነው፡፡
ችግሩ ሁሉንም ዜጋ ያስቆጣና በአንድ ያስተባበረ ጸጸትን የፈጠረ እንደነበር የሚረሳ አይደለም፡፡እንደተለመደው ጸጸቱ ቁጣ ከመቀስቀስ ውጭ ወደ ተግባራዊ እርምጃ መለወጥ አልቻለም፡፡ አጋጣሚው የቁጭትና የዋይታ ከመሆን አልፎ ለምን እንደዚህ ዓይነት ፈተና ላይ ወደቅን የሚል መሰረታዊ ጥያቄም ሊወልድ አልቻለም፡፡ ቀጥሉም በጥሞና ለመነጋገርም ሆነ መፍትሔ ለማመንጨት መንስኤና መንገድ ሊዘረጋ አልቻለም፡፡ የዲያስፖራ ፖለቲከኞችም የፖለቲካ ትኩሳቱን በማጋል ለሰልፍ ከመገባበዝ ውጭ የስደተኞቹን ሕይወት በቀጣይ ከአደጋ ለመታደግ ምን መደረግ አለበት ለማለት አልቻሉም፡፡ ዲያስፖራዎች “ከደማቁ ሰልፋቸው” በኃላ ጥቂት መዋጮ አድርገው፣ ቁጣቸውን አብርደው፤ አጀንዳቸውን በእንጥልጥል እጀመሩት ጉዳና ላይ ጥለውት መደ ጉዳያቸው ተመልሰዋል፡፡ ታዋቂ ሙዚቀኞች፣ ግለሰቦች፣ ባለሃብቶች አርቲስቶች… የኢቲቪን መድረክ ሲያጨናንቁ እንዳልነበረ ሁላ የስደተኞቹን ጉዳይ በቀጣይ ምን መፍትሔ ሊቸሩት እንዳቀዱ ለማሳየት አልደፈሩም፡፡ በእርግጥ መንግስት የጉዳዩ ቀዳሚው ባለቤት ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ መንግስት ፈተናውን ሊያልፍ አልቻለም፡፡ መንግሰት ፈተናውን ማለፍ ባለመቻሉ ዜጎቻችን አጋር የሌላቸውና ለዘለቄታው ከንቱና ተንከራታች ሆነው መቀረት አይገባቸውም፡፡
በአጠቃላይ ሂደቱ በአሳዛኝ መልኩ ቢጠናቀቅም፤ ከፍተኛ ትምህርት ሰጥቶ እንዳለፈ መረዳት ይቻላል፡፡ መንግስት የዜጎች ጉዳይ በሃገር ወስጥም ሆነ በወጭ ሃገር ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ነው፡፡ የትኩረት አቅጣጫው በመጀመርያ መሆን ያለበት ዜጎች በሃገራቸው ተጠቃሚ የሚሆኑበትንና መብታቸው የሚከበርበትን የመልካም አስተዳደርና የኢኮኖሚ ስርዓት በመዘርጋት ከስደትትና ከውርደት መታደግ ነው፡፡ በዚህ ሁሉ ሁኔታ አጣብቂኝም ውስጥ ሆነው ልባቸው በሕጋዊም ሆነ በሌላ መንገድ ለመሰደደ የተዘጋጁ ዜጎች መኖራቸው ስለማይቀር የስደተኞች ጉዳይ በአለም አቀፍ ግንኙታችን ላይ የምንመዘንበት አንዱ መገለጫችን በመሆኑ ዜጎቻችን ተገቢው ጥበቃና ከለላ እንዲያገኙ ማድረግ ያሻል፡፡ መንግስት፣ኢምባሲዎችና ቆንስላዎች በስደት ላይ የሚገኙ ዜጎቻችንን የገቢ ርዕስ አድርጎ ከማየት መታቀብ አለባቸው፡፡