Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

የአንድነት ተልእኮና የፋሲል የኔአለም ጫፍ የቆመ እይታ

$
0
0

ዳንኤል ተፈራ

Daniel-Tefera አንድነት ፓርቲ በተሳካ ሁኔታ ጠቅላላ ጉባኤውን ፈጽሞ በበርካታ ወጣቶች የተገነባውን ካቢኔ ይፋ ካደረገ በኋላ ጥቂት ሳምንታት አለፉ፡፡ በነዚህ ጥቂት ሳምንታትም ትግሉን በማያዳግም ሁኔታ የህዝብ አድርጎ የሚፈለገውን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን ለማድረግ ቀን ከሌሊት መስራት ይገባል የሚል እቅድ አንግቦ ደፋ ቀና በማለት ላይ ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያለን ግን የግል አስተያየት በማለት የኢሳቱ ጋዜጠኛ ፋሲል የኔአለም “የአንድነት ፓርቲ የመጭው ጊዜ ፈተና›› በሚል የፃፈውን ያልታሰበበት ጽሁፍ አነበብኩ፡፡

በቅድሚያ ጽሁፉን አንብቤ ሳበቃ ለምን መልስ መስጠት አስፈላጊ ሆኖ እንዳገኘሁት መግለጽ ይገባኛል፡፡ ፋሲል ማስተላለፍ የፈለገው ‹‹አንድ ጫፍ ብቻ›› የረገጠ መልእክት የተዛነፉ ሃሳቦች የተላለፈበት፣ ከግለሰብ ጥላቻ በመነሳት ፓርቲውን ፈተና ውስጥ ያለ በማስመሰልና ዋጋ እየከፈሉ ያሉትን ውድ አባሎቻችንን በግብአትነት በመጠቀም ክፍፍል ለመፍጠር የፈለገ በመሆኑ ነው፡፡ ወይም ፀሀፊው ‹‹ሁለት የከረሩ ጫፎች ብቻ ያስፈልጋሉ›› ከሚል አይነት አመለካከት ላይ ቆሞ ከመፃፍ የመነጨ ነው፡፡ ሁለተኛው ምክንያቴ በአምባገነኑ ስርዓት ተጠፍንገው ከተያዙ የብሮድካስት ሚዲያዎች ውጭ አማራጭ አልባ ለሆነው ህዝብ በአማራጭነት ለቀረበው ኢሳት ካለኝ አክብሮት ነው፡፡ ምክንያቱም ጋዜጠኛ ፋሲል የኔዓለም የኢሳት ባልደረባ እና ኃላፊነት ያለበት ሰው በመሆኑ፡፡

ፋሲል በጠቅላላ ጉባኤው በከፍተኛ ድምጽ የአንድነት ፓርቲ ፕሬዚደንት ሆነው የተመረጡት ኢ/ር ግዛቸው ሽፈራው ከሪፖርተር ጋዜጣ ጋር ቃለ-ምልልስ ካደረጉት ውስጥ ‹‹ከኢህአዴግ ጋር ገንቢ ግንኙነት (Contractive engagement) እንዲኖረን እንፈልጋለን. . .›› የሚለው ለሱ ሃሳብ የሚመቸውን ቆንጥሮ በማውጣት ከልደቱ አያሌው ‹‹ሦስተኛ መንገድ›› ካለው ወይም ‹‹ መሀል ላይ መቆም›› ብሎ ከተረጎመው ሃሳብ ጋር ለማያያዝ ሞክሯል፡፡ ስህተቱ እዚህ ላይ ይጀምራል፡፡ አንድነት ሊበራል አስተሳሰብ የሚያራምድ በመሆኑ የግለሰቦች መብት በቅድሚያ መረጋገጥ አለበት ብሎ ያምናል፤ በስትራቴጂው እንዳስቀመጠውም የኢህአዴግ አይነት ብሔር (የቡድን) መብትን ማክረር ወይም የዚህ ተቃራኒ የሆነው የኢትዮጵያ ብሔርተኝነት ላይ ብቻ ቆሞ ሌሎችን አለማዳመጥ ዴሞክራሲያዊ አይደለም ይላል፡፡ ሁሉም ባልተሸራረፈ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ውስጥ ያለምንም ጣልቃ ገብነት የመደራጀት መብታቸው መከበር አለት፡፡ ስለዚህ ጥያቄው ጫፍ የመቆም ሳይሆን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የመፍጠር ነው፡፡
UDJ
ስለዚህ አንድነት እንደ ሊበራል ፓርቲ ከገዢው ፓርቲ ጋር መደራደር ይገባል፡፡ መደራደር፣ ሰጥቶ መቀበል እንደነውር መታየት የለበትም ብሎ አስቀምጧል፡፡ ኢ/ር ግዛቸውም በቃለ ምልልሱ ያስቀመጡት ይህንን ነው፡፡ መደራደር የፖለቲካ ፓርቲዎች አንዱ ሥራ ነው፡፡ መደራደር ዘመናዊ አስተሳሰብም ነው፡፡ አሁንም እየታገልን ያለው ችግራችንን በጠረጴዛ ዙሪያ እንፍታ፣ ሆደ ሰፊ እንሁን፣ ጠርዝ ከያዘና ከፍረጃ ፖለቲካ እንላቀቅ በማለት ነው፡፡ አቶ ፋሲል ‹‹መሀል ላይ መቆም›› ያለው እንደዚህ አይነቱን ሃሳብ ነው፡፡ እንጅ ራሱ ፀሀፊው አንድነትም ሆነ አመራሩ ተንበርክኮ እንዳልሆነ፣ እንደ አንድነት ዋጋ የከፈለና እየከፈለ ያለ ፓርቲ እንደሌለ የሚያውቅ ይመስለኛል፡፡

ጠርዝ ላይ የቆመ ሃሳብ አለማራመድ ወላዋይ አያሰኝም፡፡ አንድነት መሀል መንገድ የሚለው የብሔረሰብ አክራሪነትም ሆነ የህብረ ብሔር አክራሪነት አይጠይቅምም ከሚል ነው፡፡ ሁለቱን የሚያቀራርብ የመሀል መንገድ መኖር አለበት እንደማለት፡፡ እንደዚህ ማሰብም ጤናማ ነው፡፡ መብትም ነው፡፡ ሁላችንም ሃሳብ የምናቀርበው ለሀገር ይጠቅማል የምንለውን ነው፡፡ አሸናፊው ሃሳብም በህዝብ ዘንድ ቅቡል ይሆናል፡፡

ጋዜጠኛ ፋሲል ግን ለኢ/ር ግዛቸው ካለው የግል ጥላቻ ይመስለኛል ጥቂት ነገር ቆንጥሮ ‹‹ፍርሃት ነው›› ለማለት ይሞክራል፡፡ በውጭ ሀገር እየኖሩ መታገል፣ ትግሉን መደገፍ እንደሚችል አምናለሁ፡፡ ለፋሲል ግን አንድ ጥያቄ መጠየቅ እፈልጋለሁ፡፡ የሚፈራ ሰው መቀመጫው የት ነው? እንደሚመስለኝ ወይ የኢኮኖሚ ጥያቄ ካልሆነ በስተቀር ፀሀፊው ከሀገር የወጣው ሀገሩን ስለሚጠላ ሳይሆን ሥርዓቱን ስለፈራ ነው፡፡ ሥርዓቱን ፈርቶ በተሰደደ ሰውና ከሥርዓቱ ጋር ፊት ለፊት ግብግብ እየፈጠረ ያለ ሰው መካከል ትልቅ የሞራል ልዩነት አለ፡፡ ስለዚህ ጋዜጠኛ ፋሲል የኔዓለም ፍርሃትን የተረጎመበት መንገድ ድንጋዩ ተመልሶ ወደ እርሱ እንዲያርፍ የሚያደርግ ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ ከሀገር ወጥቶ ትግሉን መደገፍ ትክክል ቢሆንም ፖለቲካውን ለመምራት መሞከርም ሌላ ትልቅ ስህተት ይሆናል፡፡ እንዲህ ሲባል እዚሁ ኢትዮጵያ ውስጥ ለውጥ ለማምጣት የአቅማችንን እያደረግን ያለን ሰዎች መተቸት የለብንም ብዬ አላምንም፡፡ በመሳደበና በመተቸት መካከል ግን ትልቅ ልዩነት እንዳለ ሊሰመርበት ይገባል፡፡
ሌላው ማንሳት የምፈልገው ጋዜጠኛ ፋሲል የአንዱዓለምንና ናትናኤልን ስም በመጥቀስ ጫፍ ላይ የቆመ ሃሳብ የሚያራምዱ አድርጎ መግለፁም ስህተት ነው፡፡ አንዱዓለምም ሆነ ናትናኤል ፋሲል የጠቀሰውን አይነት ሃሳብ የሚያራምዱ አይደሉም፡፡ ሆነውም አያውቁም፡፡ በተለይም የአንዱዓለምን ሃሳብ ለመረዳት መጽሀፉን ማንበብ ተገቢ ነው፡፡ ወጣቱ ፖለቲከኛ በሆደ ሠፊነት ‹‹ ኧረ የመቻቻል ያለህ፣ ኧረ የድርድር ያለህ፣ ኧረ የመደማመጥ ያለህ . . .›› በማለት አንድ ጫፍ ላይ ቆሞ ማክረር እንደማይጠቅም ገልጿል፡፡ ለአዲሱ አመራርም እውቅናና ድጋፍ ሰጥቷል፣ ደስተኛም ነው፡፡ ይሄን የምለው አንዱዓለም ለገና በዓል በአካል አግኝቼ ሃሳቡን ለረዥም የማዳመጥ እድል ስለገጠመኝ ነው፡፡

በመጨረሻ ግን ስለ ኢሳት ማንሳት እፈልጋለሁ፡፡ ኢሳት ለኢትዮጵያውያን በአማራጭነት ብቅ ያለ ትልቅ ሚዲያ ነው፡፡ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን ያለውን አበርክትቷል ማድነቅ እፈልጋለሁ፡፡ እኔም በተለያየ ጊዜ በዚሁ ሚዲያ ላይ የተለያዩ ሃሳቦችን ሰጥቼ አውቃለሁ፤ ወደ ፊትም እድሉን ባገኘሁ ቁጥር እሰጣለሁ፡፡ የተለያዩ አማራጭ ሃሳቦችን በተደራጀ ነፃ ሚዲያ ማግኘት የተራበው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዳያዝን የኢሳት ጋዜጠኞችን የኢዲቶሪያል ቦርድ አባላት በእጅጉ ሊየስቡበት ይገባል፡፡ ማንኛውም ሚዲያ ከአድሎ አሠራር ነፃ መሆን አለበት፡፡ በዚህ ሚዲያ ላይ የሚሰሩ ጋዜጠኞቹ ግን የግል አመለካከታቸውንና እምነታቸውን በማስቀደም አንድን ድርጅት ለማጥቃት የሚሄዱበትን መንገድ መፈተሽ ጠቃሚ ነው፡፡ ጋዜጠኛ ፋሲል በአንድነትና አመራሩ ላይ የሰነዘረው የተዛባ አስተሳሰብ “በግል አስተያየት ስም” የቀረበ ቢሆንም ግለሰብ አንድ ትልቅ ፓርቲ ላይ ሲጽፍ መውሰድ የሚገባውን ጥንቃቄ አላደረገም፡፡ ስለዚህ ብዙ ተሳሳተ፡፡ ለማንኛውም ሁሌም ከጥላቻ የሚነሳ ሃሳብ ለህዝብም አይጠቅምም በማለት ላጠቃልል፡፡


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>