Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

ምርጫ እና የስርዓት ለውጥ

$
0
0

ሙሉጌታ አሻግሬ
mulugetaashagre@yahoo.com

አገራት ዘመናዊ የተባለውን የመንግስት አስተዳደር መተግበር ከጀመሩበት ግዜ አንስቶ እስከዚህኛው ዘመን ድረስ የተለያዩ የመንግስት አወቃቀርና ርዕዮተ ዓለም ተስተናግደዋል። ሰዎች መለኮታዊ እምነታቸውን ወደጎን አድርገው ከማኦ እስከ ማርክስ ከሌኒን እስከ ካስትሮ ‘ማርክሲዝም ያነበቡና የተገበሩ ብፁዓን ናቸው’ ብለው የችግርን ጥግ እስኪገነዘቡ ድረስ ነጉደዋል። ዓለማችን በሶሻሊዝም ስትናጥ፤ ኮምኒዝምም የዓለማችንን ህዝቦች ሁሉ እኩል አደርጋለሁ ብሎ በተነሳ ሰባ ምናምን ዕድሜው ተንኮታኩቷል። ምዕራባውያን ምስራቆችን በኢኮኖሚ ብልጫ ማርከዋቸዋል። የምስራቅ አውሮፓ አገራት ከምዕራብያውያኑ በኢኮኖሚ አቅማቸው እጅግ ዘቅጠው ተገኝተዋል።
election
ይሁን እንጂ አሁንም የዚህ ርዕዮተዓለም አራማጆች በአንድ ወይም በሌላ መልኩ እዚህም እዚያም ይታያሉ። የቻይናው ዘመናዊ ‘ልማታዊ መንግስት’ አወቃቀር ለዚህ አባባል አንዱ ማሳያ ነው። አሁን በአገራችን ያለው መንግስት ትላልቆቹ ‘ተሰሚ’ ባለስልጣናት የማሌሊት ደቀመዛሙርት ነበሩ። አሁንም በውስጣቸ እንደዛው ሊሆኑ ይችላሉ…ማን ያውቃል። ለዚህም ይሆናል ኢትዮጵያ የቻይናን ጠረን እየያዘች የመጣችው። የቻይና አካሄድ የአፍሪካ አምባገነን ባለስልጣናትን በወንበራቸው ለማቆየት ፍቱን መንገድ ነው። “ከዳቦ በኋላ ዲሞክራሲ”። አጭር እና ግልጽ አምባገነናዊ አካሄድ። ስለዚህ የመጨረሻው ሰው ዳቦ እስኪያገኝ ድረስ ዴሞክራሲ አላስፈላጊ ትሆናለች። ይህች አካሄድ በአገራችን መንግስት ይፋ ዕውቅና የተሰጣት ግዜ… አዲዮስ መድብለ ፓርቲ ስርዓት በኢትዮጵያ።

በሌላ በኩል ‘ ዲሞክራሲ ዘመናዊነት ነው’ ብለው የተነሱት ምዕራባውያን፤ ሃሳብን የመግለፅና የመንግስትን በህዝቦች በጎ ፍቃድ የመመረጥ ሁኔታን ጠቅልለው ለህዝባቸው በመስጠት ህዝቡ የዚህ ዕድል (መብት) ተጠቃሚ እንዲሆን አድርገውታል። ይሁን እንጂ እንደ ኮሚኒስቶቹ የጎላ የኢኮኖሚ ችግር ባይታይም በዲሞክራቶች በኩልም የኢኮኖሚው ሁኔታ ኮለል ብሎ እየፈሰሰ ነበር ለማለት ያስቸግራል። ዓለማችን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የተዘፈቀችበት የኢኮኖሚ መውሸልሸል ምክንያትም ሃብት በተወሰኑ ቡድኖች እጅ እየተጠቀለለች መግባቷና የመንግስታት (የመስተዳድሩ) ኢኮኖሚውን የመቆጣጠር አቅም መልፈስፈስ ውጤት ነው የሚሉ ወገኖች አሉ። ይህ አስተያየት ትክክል ሊሆን ይችላል። ምክንያቱም ስርዓቱ ሃብትን ማዕከል በማድረግ ስለተገነባ ኢኮኖሚው ጡንቻ አውጥቶ የመንግስታትን የመወሰን አቅም ሲፈታተነው ታይቷል።

ከዚህ በተቃራኒ ጠንካራ ኢኮኖሚ በራሱ አገራትን እንደ አገር ሊያቆም እንደሚችል በተለያዩ አገራት በተከሰቱ ሁኔታዎች ታዝበናል። ከጥቂት ዓመታት በፊት ቤልጄየም ያለመንግስት ከአንድ ዓመት በላይ ቆይታለች። በዚህ ግዜ ውስጥ ሁሉ ይህ ነው የሚባል ችግር ሳይከሰት ዜጎች በነባር ህጎች ሲተዳደሩና ባለሃብቱም የታክስ ግዴታውን ሲወጣ ተስተውሏል። አንዳንድ ግለሰቦች የዚህ ውጤት ምክንያት የህግ የበላይነት በአገሩ በመስፈኑ ነው ብለው ቢከራከሩም የኢኮኖሚው ጥንካሬ በራሱ ትልቁ የወሳኝነት ድርሻ ነበረው። በእርግጥ የተዘረጋው አስተዳደራዊ ስርዓት(System) ጉልህ ድርሻ ነበረው። በኔዘርላንድም የተከሰተው ተመሳሳይ ሁኔታ ነበር። የመንግስት ካቢኔ አባላት ተኮራርፈው ምክር ቤታቸውን ከአንዴም ሁለቴ ዘግተው ፓርላማውን የልጆች እቃ እቃ ጨዋታ ባስመሰሉበት ግዜ ሁሉ የአገሩ ዜጎች ይህ ትርምስ እና ጫጫታ ትዝ ሳይላቸው የዕለት ተዕለት ድርጊታቸውን ሲያከናውኑ ታይተዋል። ዲሞክራሲና ኢኮኖሚ ከተባበሩ አይቀር እንዲህ ነው።

ስለዚህ በአግባቡ የተገራ ኢኮኖሚ የዜጎችን ሰላምና አኗኗር ለማቃናት ብቻ ሳይሆን ለአገር ህልውናም የራሱ አስተዋፅኦ አለው ማለት ነው።

ወደ አገራችን ይህን ሁኔታ ስንወስደው ያለመታደል ሁኖ ኢትዮጵያ ባዶ እጇን እያጨበጨበች ትገኛለች። ኢኮኖሚው የለ፣ ዲሞክራሲው የለ።

ኢትዮጵያችን ከተገነባችበት የነፃነትና የተጋድሎ ታሪክ ባሻገር ነፃነታችን ዳቦ እንዲሆንና አገራችን ዘመናዊ የመንግስት አወቃቀር እንዲኖራት ሁሉም ቅን አሳቢ ዜጋ ይመኛል። ዘመናዊነት ዘመናዊ ቁሶችን መጠቀምና ዘመን አመጣሽ ሁኔታዎችን መከተል ብቻ አይደለም። ዘመናዊነት ማለት መግባባት፤ ዘመናዊነት ማለት መቻቻል፤ ዘመናዊነት ማለት እርስ በእርስ መቀባበል፤ ዘመናዊነት ማለት ሃሳብን የመግለጽ ሁኔታ መመቻቸት፤ ዘመናዊነት ማለት የሕግ የበላይነት፤ ዘመናዊነት ማለት ህዝቦች በመረጡትና በፈቀዱት አካል መወከልና አገር እንድተዳደር ማድረግ ነው። በዚህ ዓለምአቀፋዊ የኢኮኖሚና ማህበረሰባዊ ትስስር (Globalization) ስርዓት ውስጥ ለመኖር የሌሎችን በጎ ልምድ መውሰዱ ብልህነት ነው። ካልሆነ ግን ያለንበትን ደረጃ አሻሽለን ቁልቁል እናድጋለን። ስለዚህ በአንጻራዊ ሁኔታም ቢሆን የተሻሉ የሚባሉትን አገራት የኢኮኖሚና መንግስት አስተዳደር ስርዓት ከኢትዮጵያ ባህልና አኗኗር ጋር አስታርቆ መተግበሩ እጅግ አስፈላጊ ነው።

አገራችን ንጉሣዊ ስርዓትን በሰፊው አስተናግዳለች። ከዚያም ሶሻሊዝምን ብሎም ያለፈው ስርዓት ዕድሜ ጥንፋፊ ላይ ቅይጥ ኢኮኖሚ ጭልጭል ብላ አልፋለች። በዚህኛውም መንግስት ‘ዲሞክራሲያዊ’ (እንዳትታዘቡኝ) ስርዓት እየተከተለች ነው።

በጄ!!! ዲሞክራሲውን ተቀብለን ስርዓቱን ለመገንባት ሰማይ እየቧጠጥን ይኼው ሃያ ሦስት ዓመት እንደምንም አለፈ። በ1997 አገር ጉድ ብሎ ፤ ህዝብ ተጨንቆ፤ ዲሞክራሲ በኢትዮጵያ ልትወለድ የምጥ ሂደት ውስጥ ገባን። ዲሞክራሲ ለጥቂት እውን ሳትሆን ጨነገፈች። ‘ዲሞክራቶቹ’ መግደል ጀመሩ። ዲሞክራሲ ናፋቂዎች ታሰሩ፤ ተገደሉ። ሌሎች የሚዜ አገልግሎት ለመስጠት ፓርላማ ገቡ። ለአምስት ዓመት በዘለቀው የመሣቂያ መሣለቂያ ድራማ እንደ ችሎታቸው ተውነው፤ ህዝቡ ዲሞክራሲ ይዘውልን ይመጣሉ ብሎ ደጅ ደጁን እያየ ሲጠብቅ ከፓርላማ ተሰናበቱ። አራት ነጥብ።
ቀጠለች አብዮታዊ ዴሞክራሲ። ምረጡ አስመርጡ ። ሃሳባችሁን ስጡ ተናገሩ ተባለ። እጅግ የተሳካ ምርጫ ተደርጎ ታሪካዊዋ አብዮታዊ ዲሞክራሲ 99.96% የፓርላማ ወንበር አግኝታ ኑሮ ቀጠለ።

አሁንም በቅርቡ ምርጫ አለ። ህዝቡ ጥያቄ አለው፤ ነፃነትና ፍትህ። ልማትና ዕድገት። እኩልነትና ሰላም። ይኽን ጥያቄ እንመልሳለን ያሉት ሰላማዊ የትግል ስልት የሚከተሉ የፖለቲካ ድርጅቶች ጓዛቸውን እየሸከፉ ነው። በምርጫ ሊወዳደሩ። መንግስትም የ ’ ይቻላል’ አረንጓዴ መብራት አሳይቷቸዋል። ለእነዚህ ድርጅቶች ጥያቄው የሚጀምረው እዚህ ላይ ነው።

የመጀመርያው ጥያቄ፣ የመጪው ምርጫ ዓላማ ምንድን ነው?

ህዝቡ የአጃቢነት ስራ የሚሰሩ ግለሰቦችን በፓርላማ ማየት አይፈልግም። ፓርላማ ገብቶ የአምስት ዓመት የስራ ኮንትራት የሚፈልግ የሰላማዊ ትግል አራማጅ አባል ካለ፤ በህዝቡ ስም ከመነገድ በየትኛውም የመንግስት ይሁን ሌላ ድርጅት መቀጠር ቢሞክር መልካም ነው። ለፓርላማ የሚደረገው ሩጫ ውጤት ለህዝቡ የሚታይና የሚጨበጥ ለውጥ ማምጣት አለበት። ካለፉት የፓርላማ ኳኳታዎች እንደታዘብነው፤ ድምፀ ተዓቅቦ በማድረግ ይሁን ድጋፍ ባለመስጠት አንዲት ነገር ስትለወጥ አሊያም ስትስተካከል አላየንም። ለውጥ ለማምጣት ደግሞ ፓርላማ ገብቶ በቃላት ጉሽሚያ የነፃ ትግል ማድረግ የትም እንደማያደርስ በደማቁ አይተነዋል።

የመንግስትን ኪሳራነትና ድክመት ዲያስፖራው ሳይቀባባና ሳይፈራ እንደ ጉድ ያጎነዋል። “የተከበሩ” “ክቡርነትዎ” ምናምን ሳይል አካፋን አካፋ ይለዋል። ጉድለትን መናገር ለውጥ የሚያመጣ ቢሆን፤ የህዝቡን ጥያቄ እያሽጎደጎደ በየዕለቱ በሚጮኽው ዲያስፖራ ብቻ ኢትዮጵያ ውስጥ ከዛሬ ስንት ዓመት በፊት ዲሞክራሲ በነገሰች። የመንግስት ተቃዋሚ ነን የሚሉት ፓርላማ ቁጭ ብለው የሚያሽሞነሙኑትን ጥያቄ ገዥው መንግስት እጅግ ቀድሞ ከዲያስፖራው እርቃኑን ይነገረዋል። ስለዚህ ይህ ችግር “በክቡርነትዎ ታጅቦ ሲቀርብ የፓርላማው ስራ እንደተለመደው የፕሮቶኮል አገልግሎት ይሆናል ማለት ነው። የፓርላማ መግባት ዋነኛ ግብ በስማ በለው “የተከበሩ” ለማለት ሳይሆን የህዝቡን ጥያቄ ለመመለስ ብቻ ነው። የህዝቡ ጥያቄ ምላሽ ደግሞ በተግባር መሆን አለበት። ዳቦ እና ነፃነት ከቃላትነት ወርደው የሚዳሰሱ መሆን አለባቸው። የመንግስትን አሰራር አቃቂር በማውጣትና በቃላት መጎንተል ዳቦ አልሆነም። የህሊና እስረኞችንም ነፃ አላወጣም። በዚህ ሂደት ውስጥ አንድም ግዜ ቢሆን ገዥው መንግስት ለማከናወን ያቀደው ተግባር ተከልሶ አሊያም ተሰርዞ አያውቅም።

ስለዚህ። ስለዚህ ህዝቡ ለውጥ ይፈልጋል። ይህ ለውጥ የሚመጣው ደግሞ በ50+ የፓርላማ ጨዋታ ብቻ ነው። ይህን በኢትዮጵያ ፓርላማ ስንተረጉመው በፓርላማው ካሉት 547 መቀመጫዎች ቢያንስ 274 መቀመጫዎች (ሁሉም ተመራጮች አምስቱን ዓመት በሰላም ካጠናቀቁ) ያስፈልጋል። በመሆኑም የሰላማዊ ትግል አቀንቃኞች ይህን ያህል መቀመጫ ማግኘት ግድ ይሆንባቸዋል። የወንበሯ ቁጥር ከዚህ ዝቅ ካለች የተለመደው አጃቢነት በመሳቂያ መሣለቂያነት ይቀጥላል። ስለዚህ አጃቢነት መብቃት አለበት።
ሁለተኛው ጥያቄ፣ የሰላማዊ ትግል ሰልፈኞች ድል ለማድረግ ምን ያህል ዝግጁ ናቸው?

የፓርቲዎቻችንና ድርጅቶች ዋና መቀመጫ አዲስ አበባ ናት። ሁሉም ሰላማውያን የሰፈሩት ከከተሜው ጋር ነው። አገሪቱ ደግሞ 85% ህዝብ አለኝ የምትለው ከከተማው ውጭ ነው። ስለዚህ የፓርላማው ወንበር ያለው ከተማ ላይ አይደለም። ወንበር ከድሃው ገበሬ ጋር ነው ያለችው። ከህዝቡ የወንበር አደራ ለመቀበል መታመን ያስፈልጋል። ህዝባችንስ ደግሞ ለማያውቀው ሰው እንዴት ወንበሩን በአደራ ይሰጣል ? ለዚያውም ለአምስት ዓመት። ስለዚህ እንሂድ ፤ እንውረድ። የደፈረሰውን ጠጥተን፤ ጢስ አይናችንን እየወጋን የድሃውን ወገን ክፉ እና ደግ እንካፈል። የሃዘን እንጉርጉሮውን ቅኔ እንፍታ።
የእኛ ነጭ ሸሚዝ በከረቫት መታነቁ በጠኔ ለሚመታው፤ በበሽታ ለሚማቅቀው፤ ለታረዘው ላልተማረው ወገን ምኑም አይደለም። ምናልባት የበላይነታችንን ለማሳየት ካልተጠቀምንበት በስተቀር። ነገርግን አገሪቷን እንደ አገር ለማቆም ደም እና ላቡን ለማፍሰስ የማይሰለቸው ወገን የእኛ ነጭ መልበስና ማማር መሠረት ነው። አገር ስትወረር ደሙን የሚያፈስ ድሃው ገበሬ ነው። ሃገርህ አይደለም ተብሎ የሚፈናቀለው ይሄው ወገን ነው። ረሃብና ድርቅ ሲመታው የሚረግፈው ይሄው ድሃ ዜጋ ነው። እኛ ነጭ ከሻኛ እያማረጥን እንድንበላ አፈር ምሶ አፈር ሆኖ የሚለፋው ይህ ድሃ ገበሬ ነው። ስለዚህ እሱን ሳንይዝ ሰላማዊ ታጋዮች ሆነን ከተማ ውስጥ ተሞሽረን በአምስት ዓመት ውስጥ ሁለት ቀን ሄደን ምረጠን ስንለው ይታዘበናል። መቼም ቋንቋውን ስለምንናገር፤ ብንወዛም መልኩን ስለምንመስል የአንድ አገር ህዝብ እንደሆንን ከመገመት ውጭ ችግሬን ይገነዘባሉ ፤ መፍትሄ ያመጣሉ ብሎ አያምንም። ህዝባችን እንዲያውቀን አብዛኛው ኑሯችን ከእሱው ጋር ይሁን።

ፓርቲዎችና ድርጅቶች በአገሪቱ የተለያዩ ቦታዎች ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት እንዳላቸው ይናገራሉ። የእነዚህ ጽህፈት ቤቶች ስራ ምን እንደሆነና ምን እንደሰሩ የሚያሳይ ሪፖርት ለህዝብ የቀረበበት ግዜ የለም። አንዳንዶቹ በራቸው በወር አንዴ ይከፈት ይሆናል። የበዙት ደግሞ የሸረሪት ትዕይንት ማሳያ ሆነው ይከርማሉ። የተወሰኑት ደግሞ የፊት በሩ ተቆልፎ በስተጀርባው የግለሰብ መኖሪያም እንደሆኑ የአደባባይ ምስጢር ነው። ምን እየሰራን ነው የህዝቡን ጥያቄ እንመልሳለን የምንለው? በቃ ከታገልን የእውነት እናድርገው። ከተማ ላይ ተከማችተን በፓርላማ ናፍቆት ከምንቆዝም ፤ ህዝቡን ተጠግተን ኑሮውን እንኑር።

ስለዚህ የፓርላማ ወንበር የምታልሙ ድርጅቶች ተባብራችሁም፤ ተዛዝላችሁም ቢያንስ 274 ወንበር ማምጣት አለባችሁ። ሰሞኑን እንደተሰማው ከሆነ አዳዲስ ድርጅቶች ልምድ ለማግኘት እንዲችሉ ፓርላማ ቢገቡ የተሻለ ነው የሚል አንዲት ቀልድ ተለቃለች። የምን ልምድ እንደሆነ ግልፅ አይደለም። የፓርላማ ወንበር ምን ያህል እንደሚመች? አፈጉባዔው ስንት ግዜ እንደሚያስፈራራና መነጋገሪያውን ስንት ግዜ እንደሚያጠፋብን? ወይስ የፓርላማው በር ላይ ጫማ እና ቀበቶ እያወለቁ የሚደረገው ቅጥ አንባሩ የጠፋውን ፍተሻ መለማመድ?
የኢትዮጵያ ህዝብ ሲጀመር ሰው ነው። ከዚያም የአገሩ ዜጋ። መለማመጃ አይደለም። ስለዚህ ለፓርላማ እንሮጣለን የምትሉ ወገኖች የተለመደውን የሚዜ አገልግሎት ላለመስጠት እርግጠኞች መሆን ያስፈልጋችኋል። ከዚህ በዘለለ ፓርላማ በመግባት በገዥው ስርዓት የሚዘጋጀውን ድራማ በአጃቢ ተወናይነት በመተወን የምታተርፉት መሳቂያና መሳለቂያ መሆን ብቻ ሳይሆን የህዝቡንም ችግር ለአምስት ዓመት ማራዘም ነው። በጥልቀት አስቡበት።
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!!!


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>