Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

የውስጤ ብቁ ዳኛ!

$
0
0

ከሥርጉተ ሥላሴ (ሲዊዘርላንድ – ዙሪክ)

አምቄ ብይዘውም ጠብታወቼ ዘመን አመጣሹን ብራና አራሱት
አይቀርም ደግሞ ደረሰ …. ጥር 21 የሚሉት ….
ለብር አንባር – የካቴና እራት የዶለተ – ጨጎጎት ….
የዓይናማዋ የመከራ ቀን አከባበር የልደት።
reeyot alemu
ወጣትነት ውበት የሚሆነው ቀድሞ ማለም፤ ቀድሞ መሆን ሲቻል ብቻ ነው። ወርቅ በእሳት እንደሚነጥረው እንሆ በዬጊዜያቱ የነፃነት ደቀ መዝሙራት የሆኑት የኢትዮጵያ ወጣቶች ማገዶ ሆነው ይነዳሉ፤ ይፈልቃሉ ወጣትነታቸውን በመሰዋት — በሐዋርያነት። እነሱ አራሳቸውን አሳልፈው የሚሰጡበት ሚስጢር ኢትዮጵያዊነት ነው – ትኩስ ሁልጊዜም ቋያ ነው። የእናቱ ነገር አይሆንለትም። ገላጫቸው ብሄራዊነት ነው፤ ማንነት ላላው ጌጣማ ዜግነት የሚከፈል ታላቅ ዋጋ፤ አብይ ጉዳይ፤ እራስን ፈቅዶ ለበለኃሰብ የሰጠ የፍጽምና ገድል። ወጣቶቹ የሚከፍሉት ምክንያታዊ ግብር የአደራ ዕዳ ነው። ወጣት የሀገሩን ክብር ረዘም አድርጎ የሚያይ ድንቅ የማህበረስ አካል ነው። እግዚአብሄር ይስጥልን የእኛ መብራቶች። ለሰማዕታትም በአርያመ – ገነት ያኑርልን አባታችን ክርስቶስ። አሜን!

ጥር ጣና ዘገሊላ – የእናት ክብር ብቸኛው ጊዜው ሳይደርስ ታዕምር የተገለጸበት ሚስጢራዊ ወርኽ ነው። ወጣትና የእኩልነት መምህር፤ ዓላማውን ያወቀች፤ መንገዷን ጠንቅቃ የተረዳች፤ የምልዕትን አንጡራ የህልውና ፍላጎትን አስመችታ በልቧ ጽላት በቋሚነት ያነጸች የጋዜጠኛ ርዕዮት ዓለሙ ልደት እ.ኤአ. ጥር 21.20014 በነፃነት ፈላጊ ቤተሰቦች በውስጥነት ደምቆ ይከበራል። በቃሊቲ እስር ቤት በአጋዚ የጭካኔ መጋዘን ግን ይከበራል ከምል ይልቅ በቋሳ ይቀጠቀጣል፤ በግፍ ይቀጣል፤ በበቀል ይጨቀጨቃል ብል ይሻላል። አህህህ …

ክብርት እህታችን … በወፈ በላ ታጥራ፤ በጉልበተኞች ታፍና፤ እዬተገላመጠች፤ በክፉ ዓይን እዬተገፈተረች የሚከበር ጥቁር ዕለት። አስኪ ይሁን ትኑርልን። … ትሰንብትልን። እርግጥ ነው ይህ ጥንካሬ የሴቶችን የብቃት ልኬታ ሙሉ አቅም በእጅጉ ያጎላዋል – ነገ ደግሞ ካልዘለልነው።
በ2005 ዓ.ም የዘሃበሻ ማህበራዊ ድህረ ገጽ ድንቅ ሰው ተብላ በህዝብ ድምጽ የደመቀቸው፤ በተመሳሳይ ዓመት ማለት በ2013 እ.ኤአ. ዬዓለምዓቀፍ ሽልማት ያገኘችው ጋዜጠኛ ርዕዮት ዓለሙ የ2006 ዓዲስ ዓመትን በወያኔ ቀደመት አቀንቃኝ በኮ/ሌ ኃይማኖት የሚደርስባትን ዙሪያ ገብ ፈተና አሻም ብላ፤ በራህብ አድማ ነበር የተቀበለችው። ከወላጅ እናቷ በስተቀር ከዕምነት አባቷ ጀምሮ የቤተሰብ ጥዬቃ ማዕቀብም ተጥሎባት እንደ ነበር ይታወሳል።
የእኩልነት ህሊናችን! ለወያኔ ቀለጦና ተውሳክ ፍላጎት እስር ቤት ሆና የምትጋተራዋ ቀንበጥ፤ በራስ የመተማመን ስሜቷ ከብረት ቁርጥራጭ የተሰራ ነው፤ ድፍረቷም ሙሴ ነው፤ ስለሆነም ወጣቷ ጋዜጠኛ ነገሮችን ከተለያዬ አቅጣጫ ተመልክታ የምትሰጠው አፋጣኝ ውሰኔና የምተወስደው ቁርጠኛ እርምጃ ለተለዬ ተልዕኮ ፈጣሪ አምላካችን መምረጡን ያመላክታል። ከልብ ካስተዋልነው። የምትመክታቸውን የፈተና ትብትቦች ሁሉ በዘርፍ በዘርፍ ለይተን ስንመረምራቸው አባታችን መዳህኒተአለም ለዚህ ታላቅ ኃላፊነት እንደመረጣትም ይተረጉምልናል። የህሊናዋን መስኮት ቧ አድርጎ ከፍቶ የብርሃኑ ተጠቃሚ እንድንሆንም ፈቅዶልናል። አዬን ሰማን … በታናሻችን …. ድንቅ ነገር። ከድንቅ ፍሬ ሲገኝ ዘሩን ማብቀል ደግሞ የእኛ ተግባር ይመስለኛል።
አህትዓለም! እንኳንም አደረሰሽ የእኔ የነፃነት አረበኛ! አንበሲት! ግንባር ቀደምት ቅንነት – የውስጤ ብቁ ቀጥተኛ ዳኛ! እንኳንም በመከራ ተከበሽ ይህን ቀን ለማዬት አበቃሽ – አንቺ ቀለሜ! እመቤቴ ….. ዘመኑን በመከራ፣ እኩልነትሽን በአሳር በከዘነው፤ የአፍላ ዕድሜሽን የወጣትነትሽ ውበት ፈተና በስፋት በሚናኝበት፤ አፍ ባላው መቃብር ሆነሽ፤ በሰንሰለት ታስረሽ እኩልነትሽን በነጠረ አስተምህሮ በኪዳን አከበርሽው። እግዚአብሄር ይስጥልን አንቺ የጽናት ልዩ አድማጭ።

እንቺ …. ትርጉም
የማንነት ንቁ ዓለም!
መሆንን በመቻል ይሁንተኛነት፤
ቀደምሽለት ….
አንችኑ እራስሺን ማግደሽ …. በሐሤት – በቀሉን – አዋዋጥሽበት፤
አዳራን – ልታበሪ
ዘመንን – ልትገሪ
ነገን ልታስተምሪ! ውብ ድሪ …. የእናት ጠበቃ – የነፃነት ቃና ዘማሪ!

አንቺ ፋና! … ፈተናው በጸጋ ተቀብልሽ፤ መንፈስሽን በቋሚ ብርታት ገርተሽ፤ ወጣትነትሽን ለእኛ ሸልመሽ። አንቺ በጨለማ አሳርሽን – ፍዳ – መከራሽን – ታያለሽ። በጽኑ በሽታ እዬተሰቃዬሽም እንሆ ለእኛ አንችን – ውስጥሽን በልግሥና ታድያለሽ። አንቺ የዕልፍ ትውልዳዊ ድርሻ ቀዳሚ …. ችግርን በፈቃድሽ ተቀብለሽ የምትቀልጪ የአንስት አብነት፤ የወጣትነት ልዩ ጉልላት፤ ማን እንደ አንቺ? …. – ሁሉንም ታግሰሽ ተሸከምሽ።

ውዴ! ታመሽ ባጠገብሽ ማንም ሳይኖር፣ አረመኔው ወያኔ እያለሽ ሞት የፈረደብሽ የዛሬም፤ የነገም የነፃነት ወጋገን…. አይዞሽ! … እናትዬ አምላካችን ፈተና ከሰጣቸው ጋር ነውና ብርታቱ ተስፋሽ፤ ቅዱስ መንፈሱ ደግሞ ጠባቂሽ ይሆናል። ቀን ደግሞ ለቀን ይሰጥና ቋሰኞችን እዬደነ ይቀጣል። ይህን ያደርጋል የፈጠረሽ አምላክ። ለቅኖች ቅርብ ነውና የመሃፀን ምር ሀዘንም ፈሶ አይቀርም … እንዲህ እንደ ዋዛ ወጣትነትሽን ለነፃነት አርበኝነት ወደሽ ማስበለታሽ ከንቱ አይሆንም። አንድ ቀን አዎን አንድ ቀን … ምላሹ ጣፋጭ ይሆናል። የመከራሽ ዋጋ ታሪክን ይፈጥራል – ይሰራልም። ታሪክ ያደምጣል – ትውፊት በአስር እጣቱ ፈርሞ ይቀበላል። የሴቶች የወጣቶች ዝክረ ገድል የህዝብ አንጡራ ሃብት ይሆናል።

ውስጥሽ ፍሬ – ዘር
ትንፋሽሽ – የነፃነት ሃር፤
ርዕዮት የነገ መንበር!
አንቺ የእኛ ….
አንቺ ብርቱ የአርነት ጽኑ ዘበኛ፤
የፍቅር ማዕድ ሁነኛ!

ይህቺ ፍቅር! ትንሽ ብልህ ብላቴና! በዚህ ዕድሜ፤ ከእሳት ከውሃ በሚባልበት ወቅት ላይ ወጣትነቷ የሚያዛትን ሥነ – ሕግጋት ተላልፋ በቃኝን በድርጊት ቀድማ፤ በአርያነት እንሆ ትመራናለች የመሆን እሸት። ወጣትነቷን ይፈሩታል፤ ሴትነቷንም እንዲሁ። ለዚህም ነው የእግር ብረት ቤተኛ እንድትሆን የተፈረደባት። በፈንጅ ወረዳ ተከባ ስለ እውነት መሰከረች፤ ስለሃቅ ሰበከች፤ ስለ ነፃነት አወጀች፤ ረመጡን ፈቅዳ በመቀበል ስለ ነገ ብሩህ ቀን ተግባርን ቀለበች፤ ስለ አዲስ የፍትህ ሥርዓት ነገረች – „ጠንክራቸሁ ታገሉ“ ብላም ጥብቅ መልዕክት ላካች – ጋዜጠኛና …. መምህርት ርዕዮት ዓለሙ።
እኛስ ወገኖቼ … ካለንበት ወይንስ ብጣቂ ፈቀቅ አልን ይሆን? እንፈታተሽ – ከህሊናችን ጋር …. ለፊርማ አንኳን ተለምነን ነው። የእኛ ተግባር የሎቢ ሆኖ፤ አትራፊነቱም የወርቅ ክምችት ሆኖ ግን አንተጋም። ነጮቹ አይደለም የብዙኃን ሰብሰብ ያለ ድምጽ ቀርቶ ለአንድ ሰው ብጣቂ አረፍተ ነገር እንኳን ክብር አላቸው። እባካችሁ እንበርታ፤ ቋሚ ተግባራትንም ተከታታይነት ባለው ሁኔታ እንፈጽም። አንድ ሰሞን ሞቅ ሌላ ጊዜ ቀዝቀዝ አናድርገው፤ የወያኔ የካቴና ኑሮ እዬባሰ፤ እዬከፋ ከመሄድ እኮ ለዘብ አላለም ….

መንፈስሽ ሲያማትር
ነፃነት ሊመትር …..
ሆንሽለተኝ ማገር።

የእኔ ውስጥ!…. የእኔ እናት አንቺ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን አሥራት ….
ለህግ የበላይነት፤ ለሰብዕዊ መብት መከበር፤ ለተስተካከለ ሚዛናዊ አስተዳደር፤ እኩልነትን ለሁላችን ልትመግብ የምትችል እናት ኢትዮጵያን ለማግኘት፤ ከቶም በማይቻልበት ሁኔታ፤ ፊት ለፊት ተጋፍጠሽ የምትከፍይው መስዋዕትነት ለትውልዱ ታላቅ ክበረ ወሰን ነው። ዓለምንም አስተምሯል። እስር ቤት እንኳን፤ በዛች በተጣበቀች የድቅድቅ ዛኒጋባ እንኳን፤ ይህም ተቀንቶበት አዬሩ እንዲታውክ በውስጥም በውጭም ሙጃው ወያኔ የሚያደርስብሽ ተጽዕኖ የበቀል አምላክ ቸል ሳይለው በእጥፍ ድርብ ዋጋቸውን እንደሚሰጣቸው በፈጣሪዬ እተመመናሉሁ! ዕንባ ፈሶ አይቀርም፤ ዋጋ ያስከፍላል በእጥፍ ድርብ።

ጌጤ! … አንቺ የነገን ቀና መንገድ አላሚ — የዕውነት ፍሬ እግዚአብሄር አምላክ መከራውን ሁሉ የምትታገሺበት ጉልበትና አቅም ይሰጥሽ ዘንድ አዘውትሬ ለአምላኬ፤ ለፈጣሪያ ሳልቦዝን አቀርባለሁ። ድንግልም አትተውሽም እናት ትደባብስሽአለች። አቅሜ ይህ ብቻ ነውና። አሁንም አይዞሽ! በርችልን የእኛ የነፃነት ራህብተኛ፤ የርትህ ናፋቂ፤ የእኩልነት አስተማሪ – የሰማይ ሲሳይ!
ክውና
አንቺ የእኔ ለጋ፤ እጅግ የምሳሳልሽ ታናሼ ጋዜጠኛ ርዕዮት አለሙ … እንዲህ የተግባር ጋት ሙሉዑ ሆኖ መስካሪ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ክብር ነው። በዚህ ዘመን ኢትዮጵያን ከገደለ፤ ዳር ደንበሯን ካስደፈረ፤ ትውልዱን ከተበቀለ፤ ታሪክን ከደለዘ፤ ነገን ሳይመጣ አስቀድሞ ለማሰረር ታጥቆ ከተነሳ፤ እልፎችን በማንአለብኝነት ከቀጠቀጠ አረም ድርጅት ከወያኔ – ፓሊሲ ጋር – ግብረ አበር ሳትሆኝ፤ ነገር ግን የነፃነት መዝሙር፤ የአርነት ዜማ መሆንሽ ኩራት ነሽና ጽናቱን ፈጣሪ አምላካችን ጨምሮ በገፍ ይሥጥልኝ። አሜን! የተመረጥሽው ለዚህ ነው። ይህ ጸጋሽ ነው። አምላክሽ የመረቀልሽ – ሻማነት! እኛም ታድለናል ለሞት የቆረጣች ታናሽ እህት ስለ አገኘን። ከሁሉም ነገር መማርን ከፈቀድንለት መማር እንችላላን። ባለውለታችን ነሽ። የሀገራችን ሆኖ የመገኘት ሰንደቅዓለማም።
በተጨማሪም ድንቁ ነገር የቤተሰቦችሽ ብርቱነት ናሙናነት ነው። የነፃነት ትርጉም የገባቸው ወላጅ አባትሽም በጣም ብዙ ርቀው አሰተማሩን። አጋጣሚው በብዕር ካገናኘን ዘንዳ ዝቅ ብዬ ምስጋናዬን አቀርብላቸዋለሁ። አምላካችን እኛን የፈጠረበት ምክንያት እንድናመሰግነው ነውና አንቺን ለሰጡን እንዲሁም በቅርብ ሆነው ሁሉንም ፈተና ለሚጋሩት ለተከበሩት መላ ቤተሰቦችሽም እግዚአብሄር ይስጥልን እላለሁ። ለወላጅ በዚህ ቀንበጥ ዕድሜ ከሙሽርነት – እስር ቤት ፍሬን ማዬት ከባድ ነው – እጅግ። እነሱም አብረው እዬደቀቁ ነውና ብርታቱን ይስጥልኝ አምላኬ። አሜን!

የማከብራችሁ ታዳሚዎቼ ቀለማሙ የብዕር ቆይታ ከአድማስ ባሻገር አብሮ በፍቅር አቆዬን። ፈቅዳችሁ ለሰጣችሁኝ ቅኑ ጊዜ ዘንካታውን ኢትዮጵያዊ ምስጋና በአክብሮት እንሆ – የኔዎቹ! እናንተን ያኑርልኝ።

ሴቶች የድርጊት ጀግኖች ናቸው!
ሴቶች የመሆን መቻል ጉልህ ምልክት ናቸው!

ማሳሰቢያ …
* እናንተ ድንቅ የሀገሬ ልጆች በዘመን አመጣሹ ፌስ ቡክና ሌሎችም አካውንት ያላችሁ የእንኳን አደረሸሽ ሻማ ትለዋወጡ ዘንድ በትህትና እጠይቃለሁ። ከዋዜማው ጀምራችሁ …. በእጃችን ባለ፤ ማድረግ በምንችለው አጋርነታችን አዳንቆታችን ምስጋናችን እንገልጽላት ዘንድ አሳስባለሁ። አብሶ ሴቶች ቅን ወንድሞቻችንም በዬቤታችን ሻማ እናበራለት ዘንድም እጠዬቃለሁ በጥር 21. 20014 … እንዳትረሱ አደራ! ፍቅራችሁን በፊርማችሁም ግለጹ …. አመሰግናችኋለሁ።
Facebook – just click here to share the petition on Facebook.
Here’s the link:

http://www.change.org/petitions/free-reeyot-alemu-imprisoned-award-winning-ethiopian-journalist-with-breast-tumour?share_id=tzbOCsHCEK&utm_campaign=signature_receipt&utm_medium=email&utm_source=share_petition

እግዚአብሄር ይስጥልኝ።


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles