Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

ያረጋገጥነው የምግብ ኢዋስትናን (ዋስትና አላልኩም) ነው

$
0
0

(ሠሎሞን ታምሩ ዓየለ)

ክፍል 2
በገባሁት ቃል መሠረት ተመልሼ መጣሁ። በጨዋታ ልጀምር። የከፍተኛ ትምህርቴን በቀድሞዋ ሕዝባዊት ሪፐብሊክ ቡልጋሪያ በሚገኝው የአንድ እርሻ ተቋም ውስጥ ስከታተል ( 1983 _ 1989 እ አ አ) አብሮን የሚማር ብዙአየሁ ቦሶ የሚባል የአርባ ምንጭ ከተማ ልጅ ነበር። ብዙአየሁ ጨዋታ ሲጀምር ሁልጊዜ “ላስለብልባችሁ” ይላል። እኔም ይችን ቃላት ከወንድሜ ብዙ ልዋስና እናንተን ” ላስለብልባችሁ” ብል ቅር የሚላችሁ አይመስለኝም። ታዲያ እኮ በጨዋታው ሕግ መሰረት እናንተም አንባቢዎቼ እሺ “ አስለብልበን” ማለት አለባችሁ። ያው የያዘኝ የመጻፍ ዛር ምሱን አግኝቶ ከላዬ ላይ እስከሚወርድ ድረስ እንግዲህ ልበለው። ያው ጎጃሜዎቹ ” እንዲያ በል” ይሉ የለ ነፍሳቸው ደስ የሚላትን ነገር ሲወዱ። አንድ ማሳሰቢያ አለችኝ። እንግዲህ አንድ ዕውነት አለ። ይኽውም ተወደ ሐረር ተወልደን ያደግን ጨዋታና ቀልድ እንወዳለንና አንዳንዴም “መፈተል “ እንላታለን ይህችን ተግባር። በተለይ በቅንፍ ውስጥ ያሉ ቃላቶች እንዳያስከፉአቺሁ ከወዲሁ ይቅርታዬ ይድረሳችሁ። ልቀጥል ነው ወደ ቁምነገሩ።
ባለፈው መልዕክቴ ሰለ ምግብ ዋስትና ስናወራ በቅድሚያ ልናወራ የሚገባን በስድሳና በሰባ ሚሊዮኖች ውስጥ የሚገመቱትን ትንሽዬ መሬት ይዘው በቂ ምርት የማያገኙትን አነስተኛ አርሶ አደሮችና፤ አነስተኛ ገቢ ያላቸውን የቀን ሥራ ሠርተው የሚተዳደሩትን፤ በቂ የወር ሆነ የዓመት ገቢ የሌላቸውን ሠራተኛውን ክፍል፤ እየራባቸው የሚበሉት አጥተው ወደ መኝታቸው በባዶ ሆድ የሚሄዱትን፤ ጠኔ ይዞአቸው አቅም አጥተው በየስፍራውና በየጥሻው የትም ወድቀው የሚቀሩትን፤ ልጇዋን በደረቷ አቅፋ ምንም ወተት ከጡቷ የማይፈሰውን እናት፤ በየሆቴሉ ደጃፍ ተኮልኩለው የተረፈ ምግብ ለመግዛት ሰልፍ ይዘው የሚጠባበቁትን፤ በየጎዳናው ጥግና የትራፊክ መብራት ማቆሚያ አካባቢዎች በልመና ላይ የሚገኙትን፤ በየቤተ ክርስቲያኑና በየመስጊዱ ደጃፍ ቆመው እርጥባን የሚጠይቁትንና ዛሬ ዛሬ ደግሞ በየቆሻሻው መጣያ አካባቢ ምግብ ፍለጋ የሚንከራተቱን የኅ/ሰብ ክፍሎችና ለሎችንም ለዓብነት ያልተጠቀሱትንም ይጨምራል።
ጎበዝ! እነዚህ በኑሮአቸው ልቀው የሄዱቱ ደግሞ የአገሪቱን ለኑሮ ምቹነት፤ ጣዕም ያለው መሆኑን፤ ቄንጠኝነትና ጥራቱን ለመግለጽ በምንመገባችው የምግብ ዓይነቶችና ይዘት ለመግለጽ ይጥራሉ። እንደውም አንድ አባባል አላቸው። ልጥቀሰው ባማረውና መግለጽ አቅም ባለው አማርኛዬ። “ አንተነትህ በምትበላው የምግብ ዓይነትና ይዘት ይገለጻል “ ይሉናል። አጃኢብ አሉ የሐረር ሰዎችና ልጆች። “ ጽድቁ በቀረብኝና በቅጡ በኮነኑኝ” ነው ያለው የአገሬ ሰው። በርግጠኝነት ግን መናገር የሚቻለው ያው “ያለው ማማሩ” እንደሚባለው የምግብ ዋስትናቸው የተረጋገጠለቸውማ ወዛቸው ይገልጸል። እንደ አገሬ ድሃ ሕ/ ሰብ የነጣጡ፤ በፕሮቲን እጦትና እጥረት ሆዳቹው የተቆዘረና የቀጨጩ ህጸናት፤ እግርና እጃቸው ላይ ያለው የጡንቻ ሥጋ መጠን ልዩነቱ የማይታወቅና ሰውነታቸው የከሳ አይደለም። ሁልጊዜ ፊታቸው አምበሬ ጭቃ የተባለ ቅባት እንደተቀባ ያብለጨልጫል።
ከአራት ዓሥርት ዓመታት በፊት መሰለኝ ተወዳጁና የሁለዜ ( የኔታ ፈለቀ ዓለሙ የተባሉ ከዋንዛ ዛፍ ጥላ ሥር አስተማሪዬ የተማርኩት ቃል ነው) ተደናቂው ጥላሁን ገሠሠ (የሙዚቃው ንጉሥ) ” ምግብማ ሞልቶአል” ና ከመሀሙድ አህመድ ( ዛሬ ዛሬ የትዝታው ንጉሥ ዱሮ ዱሮ ፍራሽ አዳሽ ) ጋርም በመቀባበል ” አትክልትና ፍሬ” የሚለው ጣዕመ ዜማ የተለቀቀባት አገር እንዲሁም አበበ ተሰማ፤ ድረስ አንተነህ፤ ወሰኑ ዲዶ ( በአፋን ኦሮሞ)፤ ዓለማየሁ ቦረቦር፤ መሃሙድ አህመድም በ 1968ዎቹ ፤ አንዲት የቀድሞው ጅማ ፖሊስ ድምጻዊት ስሟ አልማዝ መሰለኝ ለሎችም ያልጠቀስኴችሁ ሁሉ የአገሬን ገበሬ ታታሪነትና በቂ ምግብ አምራችነትና አቅራቢነት ችሎታ በድምጻችሁ ያሞካሻችሁ እኛም ተቀብለን ዳንኪራ የረገጥንና ትዝታው በላያችን ላይ የቀረብን ሕዝብ ሆይ! ታዲያ አቦ ዛሬ ምን ነካን ፖለቲካን በሩቁ እንዳላልን ዛሬ ደግሞ ምግብንም በሩቁ ሆኖብን ተቸገርን ። ሌላም ልድገም። ዱሮ ብርቄም ሆነ ፊልፕስ ራዲዮ የነበራችሁ ሁሉ ጠዋት ጠዋት የኢትዮጵያን ሬዲዮ ስንከፍት የእርሻ ፕሮግራም አዘጋጅ የሆኑቱ ገበየሁ ውቤ የገበሬውን የዕለት ተዕለት ጉዋደኞችን የሆኑትን የዶሮዎችን ማስካካት፤ የበጎች፤ የፍየሎች፤ የበሬ፤ የላሞችና የጥጃዎችን ድምጽ እንዲሁም የነዚህ ሁሉ አባት የሆነውን በሬውን ጠምዶ በማረስ ላይ የሚገኘውን ገበሬ በተዋበው አማርኛው በሬውን እያባበለው መሬቱን የሚንደውንና የዘፈነውን ለጊዜው ስሙን የማላስታውሰው ” አራሹ ገበሬ አራሹ ገበሬ አቦና በለው ተመለስ በሬው” ትዝ አይላችሁም። በተጨማሪም የሜካናይዝድ እርሻ መጀመሪያ የሆነውን ትራክተሩን የጀመርንበትና ” የአራርሶ” ማረሻ ማስታውቂያ በአስተዋዋቂው ሲነገር መስማት ምንኛ ደስ የሚል ነበር። ነገሮች ሁሉ በነበር ቀሩ እንጂ።
የምግብ ዋስትናን ጥያቄ ለመመለስ እነዚህን መሰረታዊ ነገሮች መመለስ መቻል አለብን። ምርት፤ የተጠቃሚው ሕዝብ ገቢውንና የምርቱ የገበያ ዋጋን ወይም የሽማቹን ኅ / ሰብ የመግዛት አቅም ናቸው። እነዚህን ሁኔታዎች ሳናገናዝብ የምንሰጠው መልስ ተገቢና ትክክለኛ አይደለም። ገበሬው ስኴር ገዝቶ መጠቀም ስለ ጀመረና በቅርቡ ደግሞ እንደተገለጸው ጤፍ መብላት በመጀመሩ አይደለም። የሕዝቡ የመግዛት አቅሙ በመዳከሙ ነው። ለዚህም እንደ ዋነኛነት መጠቀስ ያለበት አገራችን ኢትዮጵያ የምትከተለው የኢኮኖሚ ሥርዓት አይነት ኢፍትሃዊና ሥነ ሥርዐት የሌለው በመሆኑ ምክንያት ብቻ ነው።
ባጭሩ የምግብ ዋስትና ማለት ለነቃና ጤናማ ሕይወትን ለመምራት የሚያስችል በቂ ምግብ ለሁሉም የሰው ልጆች በተፈለገው ጊዜና ቦታ ማለት ነው።
ለመሆኑ የምግብ ዋስትናችንን ለማረጋገጥ ምንድነው የተሳነን? አንኳር አንኳር ነጥቦችን ለመጥቀስ እንዲመቸኝ እንደዚህ ልክፈለው። 1ኛ፡ ተፈጥሮአዊ ፦ በአብዛኛው የግብርናችን እንቅስቃሴ የዝናብ ጥገኛ ነው። ተፈጥሮ ፊቷን ስታዞርብን እዬዬ ነው። ዝናብ በዛ፤ ዝናብ ጠፋ፤የዝናብ ሥርጭቱ አልተስተካከለም፤ ድርቅ ነው። ሁለዜ ለቅሶ ነው። ታዲያ ሁሌ ለቅሶ ጥሩ ነው እንዴ? ለቅሶ ስናበዛማ ለመስሪያ ጊዜ እኮ የለንም። ይሄን ጊዜ ነው እኛን ቆራጡ መሪያችንን “ አድሃሪያንን ብቻ ሳይሆን ተፈጥሮንም በቁጥጥራችን ሥር እናደርጋታለን” እያሉ በየአደባባዩ የቀለመ ጠርሙስ ሲሰብሩ ያጨበጨብንላቸው መሪ ዓይነት የሚያስፈልገን መሰለኝ። ስማቸውን በፍጹም አልጠራም። ለምን ብትሉኝ? አንዴ እንዲህ ሆነላችሁ። በ1992 ዓም የጥቅምት ወር መግቢያ ላይ መ/ ቤቴን ወክዬ ወደ ጎንደር ጠ/ ግዛት ( ዋ! ክፍለ ሃገር የማትል አትሉኝ በጎንደሪኛ) መተማ ተጓዝን። ለምን? የሩዝ ሰብል ዝርያ ዓይነት ሙከራ ውጤት የመስክ ላይ ግምገማ ለማድረግና ጥሩ ሆነው የተገኙንትን ዓይነቴዎች የኢትዮጵያ የዘር ኢንዱስትሪ ድርጅት እንዲመዘግባቸውና ወደ አገልግሎት እንዲዘልቁና የሐገሬ ገበሬ እጅ ገብተው ምርት በምርት እንዲሆን። ይህን ማን ይጠላል? ዛዲያማ ሥራችንን ሠርተን ስንመለስ ጊዜና (በጎንደርኛ) ወደ አይከል አካባቢ ስንደርስ ሰለ መንግሥቱ ዘመን እያወራን ክፉ ክፉውን ድንገት መንገዱን እፍን ያለ ጉም ሸፈነውና ፍርሀት ውስጥ ከተተን። ክፉ መንፈሳቸው በመንገዳችን ላይ መጣና መጔዛችንን አቁመን ጉም እስተሚገልጥልን ጫካ ውስጥ መጠበቅ ተገደድን። ቴያ ወዲያ ስማቸውን ላልጠራ ተናዝዤ ነበር።( እኔ ያልኩት ለፉገራ እንጂ እሳቸው ተመልሰው ይምጡ አልወጣኝም) ወደ ሌላኛው የተፈጥሮ ችግር ስንሄድ ደግሞ የሰብል ተባዮች ብለን የምንጠራቸው ማለትም ፦ ነፍሳት ተባዮች ( ሦስት አጽቂዎች)፤ የሰብል በሺታ አምጪ ህዋሳቶች፤ አረሞችና ጥገኛ አረሞች፤ የወፍ መንጋና ዓይጥና ዓይጥ መጎጦች በዋናነት ተጠቃሽ ናቸው። አንባቢያን ሆይ! የሰብል ተባዮች በተለይ በድንገትና በፍጥነት መራባት የሚችሉቱ ቶሎ ካልተደረሰባቸው ጥፋታቸው እንዲህ በቀላሉ አይገመትም። አንድ መረጃ ልስጥ ለጠቅላላ ዕውቀት እንዲረዳን። ይህ ስታትስቲክስ ለመጀመሪያ ጊዜና የማውቀው በ 1971 ዓም ( እ ኢ አ) የአምቦ እርች ተቋም የመጀመሪያ ዓመት ተማሪ ሳለን የዛን ጊዜ የሰብል ጥበቃ ኮርስ አስተማሪዬ አቶ ዳዲ መሃሪ እንደነገሩን ዛሬም ሳይለወጥ አለ። ይኽውም እንደሚከተለው ነው። በመስክና በጎተራ የሚደርሰው ብክነትና ጥፋት በመቶኛ ሲሰላ ሠላሣ ነው። ልብ በሉ እዚች ጋ ! ይህንኑ የ ጥፋት መጠን ለመቀነስ ትንሽ እንኩዋን ደህና አድርገን ብንሰራ የምናመርተው ሊበቃን እንደሚችል አዋቂዎች ይመክራሉ። ማን ነበር ተመክሬ፤ ተመክሬ አልሰማሁም ያለው? የብ አ ዴ ን መሪ የነበረው መልከ መልካሙ ታምራት ላይኔ አይደሉም እንዴ በፓርላማው ፊት በ 1989 ዓም። የሳቸው አዚም ( የሐረር ልጆች ቋንቌ ነች) ይዞት ነው መሰለኝ ይኽኛውም መንግሥት አይሰማም። ታሜ አይቀየሙኝም! አሁንማ እንደኛው ስደተኛው (ዳያስጶራ )አባል አይደሉ ኣንዴ? አንዴ በነካካ እጄ ደግሞ ሰለ ታሜ አንድ ጨዋታ ልድገማችሁ። በ1989 ዓም የጥቅምት ወር አገራችን ኢትዮጵያ ተመረጠችና አንድ ዓለም ዓቀፍ ደረጃ ያለው የአንበጣ መከላከል ወርክሾፕ በዝዋይ ከተማ በትብብር መልክ ከምስራቅ አፍሪካ የበረሃ አንበጣ መከላከል ድርጅትና በዓለም ምግብና እርሻ ድርጅት ድጋፍ ተዘጋጀ ። ቦታውም ቱሪስት ሆቴል ውስጥ ካለው አዳራሽ ነበርና በዕርፊት ሰዓት ሻይ ለመጠጣት ወደ ቡና ቤቱ አዳራሽ ከሥራ ጉዋደኛዬ ከሆነው ወንድሜ አሁን ግን በአካል ከሌለው ተቀምጠን ሳለ ያዘዝነው ሻይ መጥቶ ጠረጴዛውን ሲነካ ለካስ ሻዩ ስኴር አንሶት ኖሮ አስተናጋጁን ጠራና እባክህን ታምራት ላይኔ ጨምርለኝ አለው። ምን ማለትህ ነው ብዬ ስጠይቀው? የታሜ ቅሌት ” ስኴር “ ስለተባለ ስኴር ስሟን ቀየረች እኮ አለኝ። ትንሽ ፈገግ ቢያደርጋችሁ ብዬ እኮ ነው።
ሌላኛው ምክንያት ደግሞ የለም መሬት በውሃና በንፋስ ሃይል እየተረዳ በተለይ ምንም ዓይነት የእጽዋት ሺፋን በሌለበት የሰሜኑ የአገራችን ክፍል በመታጠብ ጎረቤት አገሮችን ሲያለማ እኛን በድህነት አረንቋ ውስጥ የከተተን የመረት መከላት ነው። ለሙ አፈር ታጥቦ ሲሄድ የመሬቱ ዋጋና አገልግሎቱም በዚያው ልክ ይቀንሳል። ኢትዮጵያ በየዓመቱ በቢሊዮን ቶን የሚቆጠር አፈር ታጣለች። ይኽውም የተከላው አፈር መጠን በመሬት ስፋት ሲለካ በብዙ ሺ ሄክታር መሬት ሲገመት ከተገመተው መሬት ላይ የሚገኝው የሰብል ምርትም በሚሊዮኖች ኩንታል ይደርሳል።
እሳት፤ የመሬት መራድና የጎርፍ መጥለቅለቅም ( የ1971 ዓም ውቧን አዲስ አበባን የግንፍሌ ወንዝ ገንፍሎ ያደረሰውን ጥፋትና ጉድለት ስንቶቻችን እናስታውሰው ይሆን? ) ያሁኑ መንግሥት እንኳን ያኔ የለም ከደርጊ ወታደሮች ጋር ይፋለም ነበር። አዋሽማ ክረምት በመጣ ቁጥር እንዳስለቀሰን አለ። ማን ትኩረት ቸሮት ተው ይበለው። እነዚህ ችግሮች ሁልጊዜ ባይመጡም የሚያደርስት ጥፋትም አነስተኛ አይባልም።
2ኛውና እጅግ አደገኛው ሰው ሰራሹ ነው። የመንግሥት የተገላወደ፤ የተንሻፈፈና ያልተስተካከለ በሕዝብ ፍላጎት ላይ ያልተመሰረተ የግብርናና የሌሎች ኢኮኖሚ ዘርፎች ፖሊሲዎችና ተጠያቂነት የጎደለበት አሰራሮች ናቸው። በተለይ ደግሞ መንግሥት በሙስና በተጨማለቀና መንግሥታዊ የቀጥታ ሌብነት አሰራር እጁን በሰፊው በዘረጋበት አሥተዳደር ችግሩ ሥር የሰደደ ነው። አምባ ገነኖች የምግብ ዋስትናን ጥያቄ ድሆችን ለማምበርከክ ይረዳቸው ዘንድ እንደ ፖለቲካ መሣሪያ ይገለገሉበታል። ለሚደግፏቸው ለጋስ ግን ለሚቃወማቸው የሕዝብ ክፍል ደግሞ እንደ መቅጫ ይገለገሉበታል። የኛዎቹ ገዢዎች ገበሬውን በተለይ አስተዳደራቸውን የሚቃወመውን እንዴት ከመሬቱ ለማፈናቀልና ለማባረር እንደሚገለገሉበት እማኝ መጥራት የሚያስፈልገኝ አይመስለኝም። ሌላም ልጥቀስ ። የብድር አገልግሎት ለማግኘት፤ የመሬት ማዳበሪያ፤ የምርጥ ዘርና የጸረ_ ተባይ መከላከያ ለመግዛት ገበሬው ከፈለገ የግድ መንግሥትን መደገፍ አለበት። በከተማም ቢሆን የመንግስትን ሰዎች ማንኛቸውንም እንቅስቃሴ እሺ ብለው እስካልተቀበሉ ድረስ ማናቸውንም የመንግስት ድጋፍ፤እርዳታና አገልግሎት በሚያስፈልግዎ ቦታና ጊዜ እንደ ዜጋ ተቆጥረው አያገኙዋትም።
አምባገነኖች ግብዞች፤ ጉረኞች፤ ክፉዎች፤ ጩካኞች፤ አረመኔዎች፤ለግል ስብዕናቸው እንጂ ሰለ ሃገር ደንታ ቢሶች፤የሰው በጎ ሃሳብ ሰርቀው የራሳቸው ብቻ ሃሳብ አድርገው ለማቅረብና እርካሽ ዝናን ለማትረፍ ይቅበዘበዛሉ። አዋቂ መስለው ለመታየት የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም። አንዳንዴም በዙሪያቸው በሚኮለኩሏቸው ምሁራን አማካኝነት አዋቂነታቸው እንዲሰበክላቸው ይጥራሉ። ይሰብካሉ። በየመገናኛው ብዙሃን ከምሁራን ጭንቅላት የቃረሙት ዕውቀት ሲመረቅኑና ሲተፉት ልሂቅ ይመስላሉ። አንዳንዴም የሚገርመውና የሚደንቀው ምሁራን ተብዬውቹ አጃቢ ሆነው የራሳቸውን ሙያ፤ ክህሎትና ዕውቀት ወደ ጎን ትተው አምባገነኖችን አድራጊና ፈጣሪ አድርገው ሲያሞካሹአቸው መመልከቱና መስማቱ እጅግ ይሰቀጥጣል። አንዳንድ የአምባገነን መሪዎችን ቅኝት ለመጫወት መሪውን ለመጨበጥ የሚቅበዘበዙ የሥልጣን ጥመኞች ደግሞ የአምባገነኖች ቃል ሳይበረዝ ሳይደለዝ (አዜብ ጎላን ያስታውሱ) እያሉ በየሰብሰባው የአምባገነኖች ቃል እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ቃል ለዘልዓለም ሕያው ሆኖ እንዲኖር ያላዝኑብናል። የሃገር እድገትና ልማት በሃገርኛው ሕዝብ ተሳትፎ ሳይሆን በነሱ ዕውቀትና ችሎታ ብቻ እንደሚመጣ አድርገው አጥብቀው ይሰብካሉ። እነሱ ከሌሉ አገር ይፈርሳል ብለው ያስተምራሉ። በአንድ ቋንቋ ሙዋርተኞች ናቸው። አምባ ገነኖች ሞተውም ክፉ መንፈሳቸው በህያውያን ላይ ሳይቀር እየተገለጠ ስለነሱ ህያውያኑ እንዲለፈልፉ ያወራጫቸዋል። እንደኔ እንዴኔ ግን አምባገነኖች ሁሉ ባዶ ጣሳና የወረቀት ፓኮ ናቸው።
አምባገነኖች ለሥልጣናቸው ጉጉና ቀናኢ በመሆናቸው የሚወስዱትን እርምጃዎች በሙሉ የሚለኩት ለነሱ በሚሰጡት ፋይዳ እንጂ የሕዝብ ፍላጎትና ፍቃድ የሚባል ቃል ምናቸውም አይደለም። ሕዝብ ወደደው አልወደደው ለእነርሱ ጉዳያቸው አይደለም። ሕዝብ የኔ ያላለው ልማትም ሆነ ግንባታ ጊዜው ዘምበል ያለ እለት የመጀመሪያው የጥፋት መጀመሪያ መሆኗን መንግሥታችን አያውቅም፤ አይረዳም ለማለት ግን አይዳዳኝም። የደርግ መውደቂያን የወያኔ ኢህአደግ መግቢያ ጊዜን ማስታወስ ይበቃል። ምግብ አምራቹን ገበሬ ከሚውዳት መሬቱ ያፈናቅሉታል፤ ያባርሩታል፤ ያስሩታል፤ በረሃብ ይቀጡታል፤ ያሰድዱታል፤ እንዲያም ሲል ይገድሉታል። እስቲ በምን ፍዳ ይህ ሁሉ በደል በገበሬ ላይ ይታሰባል። ልመስክር፤ በደርጉ ጊዜ በየጣቢያው እዚህም እዚያም ለእርዳታ እህልና ለምርት ግብአት ማከማቸነት የተሰሩ ትልልቅ ቤቶች አሉ። አንዱም እኔ የማውቀው በሐረር ከተማ ዙሪያ ድሬ ጠያራ እየተባለ በሚጠራው ስፍራ ይህ ማከማቻ ይገኛል። የምርት መሰብሰብያ ወቅት በመጣ ሰሞን ይህ ማከማቻ አንዱ አገልግሎቱ የምርት ግብዓት ብድር ወስደው ባንድ ሆነ በሌላ ምክንያት መክፈል ያልቻሉ ገበሬዎች ምክንያታቸው በባለ ሙያ ሳይጠና ፖሊስ ስራ እንዳይፈታ ይመስላል ገበሬዎች በአካባቢው የመንግሥት ባለሥልጣኖች ይዋከባሉ፤ ይታሰራሉ። ገበሬ በተፈለገበት ጊዜ ይፈታል። ግብርና መ/ ቤት ገበሬ ያሳስራል፤ ያስፈታል። በአገሪቱ ስንት ዓይነት ድሬ ጠያራዎች አሉ? የታወቀ ነገር የለም። በደህናው የትምህርት ጊዜ በዚያው የአምቦ እርሻ ተቋም ተማሪ በነበርኩበት ጊዜና የኢኮኖሚክ ጄኦግራፊ መምህሬ የነበሩት ግርማ ያዴሳ ያስተማሩን አንድ እውነት ነበር። አገራችን ኢትዮጵያ በዚያኞው ጊዜ በነበረው አስተዳደር በ 102 የአውራጃና ከ565 በላይ የወረዳ አስተዳደር እንደተዋቀረች አስረድተውኛል። አንባቢያን ምንአልባት ይሄንን ቁጥር መሰረት አድርገው የገበሬ ማሰሪያውን ሊያሰሉት ይችላሉ። ጊዜው 2000 ዓም ( እ አ አ )መጨረሻ በዛን ጊዜ አለቆቼ ፍቃድ ልበለው በጀርመን አገር ለአንድ ወር ሥልጠና ተላኩኝ። በቆይታዬም ወቅት እድል ቀንቶኝ ወደ 5ት የሚጠጉ ገበሬዎችን በመስክ ጎበኘናቸው። ይገርማል። እዚያ በጀርመን ውስጥ ከ 2ት በላይ እስከ 5ት ልጅ ያለው፤ ሰፋ ያለ መኖሪያ ቤት ያለው፤ ተግባሩን ደህና አድርጎ ካከናወነ ከመንግስትም ጥሩ ድጋፍ የሚያገኘው አንዳንዴም እባክህን ከዚህ በላይ አታምርት እየተባለ ምክር የሚሰጠው አምራቹ ገበሬ ነው። በጀርመን ገበሬ ሃብታም ነው። እስቲ ንብረቱን አስብት፦ ትራክተር፤ ማረሻ፤ መኮትኮቻ፤ መዝሪያ፤ የጸረ_ተባይ መርጫ መሳሪያ፤ የከብቶቹ ጋጣ፤ ማጨጃ፤ መሰብሰብያና መውቂያ፤ የምርት ማቀናበሪያና ማደራጃና ማሽጊያ፤ የቤት መኪናዎችና ለሎችንም አስቡና በዓይነ ኅሊናችሁ ደግሞ የአገሬን ገበሬ ከነበደሉ አስቡት። መጥኔ አለ የአገሬ ሰው። አዎን የአገሬ ሰው። ” ከክፉ ተወልጄ ስፈጭ አደርኩኝ” ማለት ይኼውም አይደል።
ለዛሬው ላብቃና በሚቀጥለው ክፍል 3 እንገናኝ። በአብሮነታችን እንቆይ ነው የሚባለው።


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>