(ክፍል አንድ)
ከያሬድ ኃይለማርያም
ብራስልስ፣ ቤልጂየም፤
መግቢያ
ይህ ጽሑፍ በኢትዮጵያ ላለፉት አስርት አመታት ጎሣና ኃይማኖትን መሰረት አድርገው በተደጋጋሚ ጊዜያት በተከሰቱት ግጭቶች ዙሪያ እና ግጭቶቹ ባስከተሉት ሰብአዊና ቁሳዊ ጉዳት ላይ የሚያተኩር ነው። በተለይም ከ1983 ዓ.ም. ወዲህ ጎሣን መሰረት ያደረገውን የኢሕአዴግ ፌዴራላዊ የመንግስት አወቃቀር ተከትሎ በአገሪቱ የተለያዩ ክልሎች ውስጥ የተከሰቱ ዋና ዋና ግጭቶችን ይዳስሣል። ለግጭቶቹ መንስዔ ተደርገው የሚጠቀሱትን ጉዳዮች፣ በግጭቶቹ ሳቢያ በሰው ሕይወትና በሕዝብ ንብረት ላይ የደረሰውን የጉዳት መጠን፣ ግጭቶቹ እንዳይከሰቱ ለመከላከልም ሆነ ከተከሰቱ በኋላም ለማብረድ እና ዘላቂ በሆነ መልኩ ለመፍታት በመንግስት የተወሰዱ እርምጃዎች፣ የመንግስት የግጭቶች አፈታት ስልት፣ እና ሌሎች ተዛማጅ ጉዳዮችን ይህ ጽሑፍ በመጠኑ ይዳስሳል።
የጽሑፉም ዋነኛ ዓላማ ጎሣን እና ኃይማኖትን መሠረት አድርገው የሚቀሰቀሱ ግጭቶች፤ ሰብአዊ መብቶች በገፍ በሚጣሱበት፣ ዴሞክራሲያዊ መብቶችና ነፃነቶች በማይከበሩበት እና የሕግ ልዕልና ባልተረጋገጠበት፤ እንዲሁም ነፃና ገለልተኛ የፍትሕ ተቋማት በሌሉበት እንደ ኢትዮጵያ ባለ አገር ውስጥ የሚኖራቸውን መጥፎ ገጽታ ማሳየት ነው። በተለይም የኢሕአዴግን የጎሣ ፖለቲካ አወቃቀር ተከትሎ በአገራችን ተደጋግመው በመከሰት ላይ ያሉት የጎሣ ግጭቶች በአገሪቱ የልማት እንቅስቃሴዎችና በሕዝቡ ሰላምና ደኅንነት ላይ የሚያስከትሉትን ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ማኅበራዊ ቀውሶች ማመላከት ነው።
ወደዚህ ጽሑፍ ዋና ክፍል ከመግባቴ በፊት ለአንባቢዎቼ ከላይ ከገለጽኳቸው የጽሑፉ አላማዎች በተጭማሪ የተወሰኑ ነገሮችን ከግምት ውስጥ እንድታስገቡልኝ ለማሳሰብ እወዳለሁ። በመጀመሪያ ይህን ጽሑፍ ለማዘጋጀት ምክንትያት የሆነኝን ነገር ልግለጽ። ለስምንት አመታት በሰብአዊ መብት ጥሰቶች አጣሪነት በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) ውስጥ ተቀጥሬ ባገለገልኩበት ዘመን ድርጅቱ ተከታትሎና አጣርቶ መግለጫ ባወጣባቸው በርካታ የጎሣና የኃይማኖት ግጭቶች ውስጥ በምርመራ ሥራ ተሳትፌአለሁ:: የተወሰኑትን ግጭቶች ከሌሎች የሥራ ባልደረቦቼ ጋር በመሆን ሥፍራዎቹ ድረስ በመገኘት፤ የተቀሩትን ደግሞ ሌሎቹ የድርጅቱ የምርመራ ሠራተኞች፤ በአካል ተገኝተው ካሰባሰቡዋቸው መረጃዎች በመነሳት ያካፈሉኝን እውቀትና መረጃ በመንተራስ ነው። ለዚህም ጽሑፍ በዋነኛነት ኢሰመጉ በግጭቶቹ ዙሪያ የወጣቸውን መግለጫዎች በማጣቀሻነት እጠቀማለሁ። እንዲሁም ሌሎች አለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ድርጅቶች ያወጡዋቸውን መግለጫዎችና ሰነዶች በአባሪነት እጠቅሳለሁ።
ይህ ጽሑፍ ሦስት ክፍሎች ሲኖሩት፤ በመጀመሪያው ክፍል በጎሰኝነት ስሜት ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ አደረጃጀት እና አስተሳሰብ፣ የጎሣ ግጭቶች እና ከሰብአዊ መብቶች አጠባበቅ ጋር ያላቸውን ግኝኙነት በተመለከተ አለም አቀፍ ድንጋጌዎችን እና ሌሎች ሰነደችን በማጣቀስ የሚዳሰስበት ክፍል ነው። የዚህ ክፍል አላማም በኢትዮጵያ ውስጥ እየታየ ያለውን የጎሠኝነት ስሜትና እያስከተለ ያለውን ግጭት ባህሪይ እና አካሄድ በቅጡ ለመረዳት ይረዳ ዘንድ መሰረታዊ በሆኑ ጠቅላላ አስተሳሰቦችና በሌላው የአለም ክፍልም ይህ አይነቱ ችግር ያለውን ገጽታ በመጠኑ የሚዳስስ ነው። ሁለተኛው ክፍል በኢትዮጵያ ውስጥ በተደጋጋሚ ስለተከሰቱትና እየተከሰቱ ባሉት ግጭቶች ላይ የሚያተኩር ነው። በዚህ ክፍልም ውስጥ ኢትዮጵያ ውስጥ የተከሰቱትን ግጭቶች ባህሪ፣ መንሰዔያቸውን፣ የደረሱትን ጉዳቶች፣ የመንግስትን ሚና እና ሌሎች ተዛማጅ ጉዳዮች ላይ ያነጣጠረ ነው። የመጨረሻውና ሦስተኛው ክፍል የኢሕአዴግ መንግስት የሚከተለው ፖሊሲ፣ ያወጣቸው ሕጎች፣ ግጭቶችን ቀድሞ እንዳይከሰቱ የመከላከልና ሲከሰቱም በቀላሉ ተቆጠጥሮ ዘለቄታዊ መፍትሔ የመስጠቱ ሂደት ምን እንደሚመስል በመጠኑ የሚፈትሽ ነው።
I. ጎሠኝነት፣ የጎሣ ግጭቶች እና ሰብአዊ መብቶች
1.1. ጎሠኝነት
የሰው ልጆች ሁሉ በሰብአዊ ፍጡርነታቸው ክቡር መሆናቸውን፤ እንዲሁም እኩልና ሊነጣጠሉ የማይችሉ መብቶች እና ነፃነቶች ያሏቸው መሆኑን በአለም አቀፍ ድንጋጌዎች ላይ ሰፍሯል። የእነኚህ መብቶች እና ነፃነቶች በአግባቡ መረጋገጥና መከበር ለአለም ሰላም እና ለሕዝቦች ደኅንነት ዋነኛ ምሰሶም እንደሆነ ተገልጿል። የሰው ልጆች በሰብአዊ ፍጡርነታቸው ተገቢውን ክብር በማያገኙበት፣ ሰው በመሆናቸው ብቻ የተጎናጸፉዋቸው መብቶች እና ነፃነቶቻቸው ባልተረጋገጠበት እና በገፍ በሚጣሱበት ሥፍራዎች ሁሉ አይነታቸውና ደረጃቸው ይለያይ እንጂ ግጭቶች፤ ከፍ ሲልም ጦርነቶች ይከሰታሉ። በመላው አለም መብቶቻቸው የተረገጡባቸውና ሰብአዊ ክብርን የተነፈጉ ሰዎች ለነፃነቶቻቸው መረጋገጥ እና ከጨቋኞቻቸው ነፃ ለመውጣት የሚያደርጉትን ትግል ተከትሎ በርካታ ጦርነቶች እና ግጭቶች በአለም ተከስተዋል፤ አሁንም በተለያዩ ሥፍራዎች ይታያሉ። አለማችን እጅግ ዘግናኝ የሆኑ እና በሚሊዮኞች ለሚቆጠሩ የሰው ልጆች መጥፋት ምክንያት የሆኑ በዘር ጥላቻና በጎሠኝነት ስሜት የተቀጣጠሉ በርካታ ግጭቶችን እና ጦርነቶችን አስተናግዳለች።
የተባበሩት መንግስታት ባወጣቸው የተለያዩ ሰነዶች ላይ እንደተጠቆመው ድርጅቱ ከተቋቋመበት፣ እ.ኤ.አ. ከ1945 ወዲህ እንኳን ከተከሰቱት በርካታ ጦርነቶች ውስጥ ዐብይ በሚባሉት ከመቶ በላይ በሆኑ ትላልቅ ጦርነቶች ብቻ ከ20 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ሞተዋል። በአሥር ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ደግሞ በጦርነቶቹ ሳቢያ ለስደት፣ ለርሃብ፣ ለድህነት እና ለበሽታ ተዳርገዋል። አብዛኛዎቹ ግጭቶች የዘር ልዩነትን መነሻ ባደረጉ ውጥረቶች፣ ያመረረ እና ጽንፍ የያዘ ብሔራዊ ስሜትና አክራሪ ጎሠኝነትን ተከትለው የተቀሰቀሱ ናቸው። አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያመላክቱት ከሆነ ከሁለተኛው የአለም ጦርነት ወዲህ በመላው አለም በፖለቲካ ብጥብጥ ሳቢያ ከሚሞቱ ሰዎች መካከል 80 በመቶ የሚጠጉት በጎሣ ግጭቶች ምክንያት ነው። በአለም ታሪክ ውስጥ ጎላ ብለው ከሚጠቀሱት ግጭቶች መካከል በአይሁዳዊያን ላይ የደረሰው ስቃይና የጅምላ ጭፍጨፋ፣ በጂፕሲዎችና በሶዶማዊያን ላይ የተካሄደው እልቂት፣ በሩሲያ እስታሊን በሰው ዘር ላይ የፈጸመው አሰቃቂ ወንጀል፣ በደቡብ አፍሪካ የአፓርታይድ ሥርዓት፤ እንዲሁም በዚምባብዌና በናሚቢያ ንኡሳን ነጮች (አውሮፓዊያን) የፈጸሙዋቸው እልቂት፣ በላይቤሪያ፣ በሩዋንዳ፣ በሱዳን፣ በሱማሌ እና በሌሎች የአፍሪካ አገሮች በተከሰቱ የእርስ በርስ ግጭቶች ሳቢያ ሚሊዮኖች ያለቁባቸውን ሁኔታዎች መዳሰስ እንችላለን።
በመጀመሪያ ደረጃ በጎሣ (ethnicity) እና በዘር (racial) ማንነት መካከል ያለውን ልዩነትና ዝምድና በመጠኑ ለመዳሰስ እወዳለሁ። የጎሠኝነት ስሜትና ማንነት የሚመነጨውና የሚጎለብተው እያንዳንዱ ሰው እራሱን ከአንድ በቋንቋ፣ በባሕል፣ በአካባቢያዊ ሁኔታ፣ ልማዶች እና ሌሎች ማኅበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከተሳሰረ የዘር ግንድ ጋር መነሻ በማድረግ የተደራጀ ወይም የተሰባሰበ የኅብረተሰብ ክፍል አባል አድርጎ ሲቆጥር እና በእነዚሁም መስፈርቶች እራሱን ከሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች የተለየሁ ነኝ ብሎ ማሰብ ሲጀምር ነው። በዘር ላይ የተመሰረተው ማነነት በርካታ ጎሣዎችን በውስጡ ያቀፈ ሲሆን ተመሳሳይ የሆነ ተፈጥሮአዊ የሆነ አካላዊ መገለጫዎችን መሰረት በማድረግ የቡድንኑ አባላት እራሳቸውን ከሌሎች ለይተው የሚገልጹበት ወይም በሌሎች ዘንድ የተለዩ የተርገው የሚገለጹበት ሁኔታ ነው፡፡ ይህ አይነቱ የቡድን ዘር መገለጫ በሥነ-ተፈጥሮ ሳይንስ የተደገፈ ሳይሆን ለቡድኑ
Ethnicity, conversely, is defined as a sense of common ancestry based on cultural attachments, past linguistic heritage, religious affiliations, claimed kinship, or some physical traits (1998, 19)፡ http://stanford.library.usyd.edu.au/entries/race/#RacVerEth
Racial identities are typically thought of as encompassing multiple ethnic identities (Cornell and Hartmann
መገለጫ በሚሰጠው ሰው አስተሳሰብና ምርጫ ላይ የተመሰረተ ነው። በሁለቱ መካከል ያለው ትልቁ ልዩነት የጎሣ ማንነት በእያንዳንዱ የጎሣው አባል መርጫና ፍላጎት ላይ የተመሰረተ ነው። አንድ ሰው የአንድን ጎሣ ባህል፣ ቋንቋ፣ ልማዶች እና ሌሎች መገለጫዎችን ወዶና ፈቅዶ ሲያደርጋቸውና እራሱ የዛ ጎሣ አባል አድርጎ ሲቆጥር ነው የማንነቱ መገለጫ የሚሆነው። የዘር ማንነት መገለጫ ግን በእያንዳንዱ ሰው ፍላጎትና ምርጫ ሳይሆን በሌሎች አካላት ውሳኔ የሚጫን ነው። ለጥቁሮች መገለጫ የተደረገውን negro የሚለውን አገላለጽ የወሰንድ እንደሆነ በነጭ አክራሪዎች በመላው አለም ጥቁር የቆዳ ቀለም ላላቸው የሰው ልጆች ሁሉ የሰጡት መጠሪያ ነው።
የጎሣ ማንነት ቋንቋን፣ ባህልን፣ ኃይማኖታዊ ሥርዓቶችን ለማስተዋወቅ፣ ለማበልጸግ እና ይዞ በማቆየትም ከትውልድ ትውልድ እንዲተላለፉ ለማድረግ በመነጨ ፍላጎት ላይ ብቻ ሲወሰን እና ከዚህ አልፎ ለፖለቲካ ፍጆታ ሲውል የሚኖረው ውጤት እና ገጽታ ፍጹም የተለያየ ነው። በመጀመሪያው የአስተሳሰብ መስመር ላይ የተመሰረተው የጎሣ ማንነት ልዩነቶችን አጉልቶ በማውጣት ለመናቆሪያ ሳይሆን እንደ ጥለት ክር የተጠላለፉት የእያንዳንዱ የኅብረተሰብ ክፍል ባህሎች፣ ቋንቋዎች፣ ኃይማኖታዊ እና ታሪካዊ ትውፊቶች ለጠቅላላው ማኅበረሰብ የጥንካሬ እና ኅብረ ውበት ምንጮች ተደርገው ነው የሚቆጠሩት። በዚህ አይነቱ ማኅበረሰብ ውስጥ የአንዱ ክፍል ቋንቋ፣ ባህልና ሌሎች ማኅብራዊ እሴቶች ሁሉ የሌሎቹ የኅብረተሰብ ክፍሎች ሃብትና ጌጦች ናቸው። አንዱ ያለሌሎቹ፤ ሌሎቹም ያለአንዱ ውበትና ጥንካሬ የላቸውም። ይህ አይነቱ ማኅበረሰብ በውስጡ ግጭቶችና ቅራኔዎች ባያጡትም አንዱ የሌላውን ዘር ከምድረ ገጽ ለማጥፋት በመነሳት ወደሚፈጸሙ ዘግናኝ እልቂቶች አያመሩም። ልክ በአንድ ቤተሰብ አባላት መካከል ግጭቶች ተነስተው በእርቅ እንደሚፈቱት ሁሉ በዚህ አይነቱ ማኅበረሰብ ውስጥም የሚነሱ ቅራኔዎችና አለመግባባቶች በየአገሩ ወግና ባህል ወይም በሕግ አግባብ አፋጣኝ መፍትሄ ሲለሚያገኙ ወደ እልቂት አያመሩም።
ሁለተኛውና ለፖለቲካ ግብ ማሳለጫ መንገድ ተደርጎ የሚወሰደው ጎሣን መሰረት ያደረገው የማንነት መገለጫ እና የኅብረተሰብ ክፍሎች መቧደን ከላይ ከተጠቀሰው የጎሣ ምልከታ ጋር ከሚጋራው አንድ ነገር ውጪ እጅግ የተለየ መልክ እና ይዘት ያለው ነው። ሁለቱም የጎሣ ምልከታዎች መነሻቸው አንድ ነው። ይህውም በአንድ ማኅበረሰብ ውስጥ በቋንቋ ወይም በባህል ወይም በኃይማኖት ወይም በሌሎች የማንነት መገለጫ ተደረገው በልማድ በሚወሰዱ ልዩነቶች ዙሪያ የተሰባሰቡ የኅበረተሰብ ክፍሎች መኖራቸው ነው። አንድ ወጥ የሆነ ቋንቋ፣ ባህል፣ ኃይማኖትና ታሪክ ባለው ማኀበረሰብ መካከል የተለያየ የኅብረተሰብ ደረጃዎችና ክፍሎች ቢኖሩም የጎሣና የጎሠኝነት ጎዳዮች ጭርሱኑ የሚታሰብ ነገሮች አይደሉም። የጎሣ ልዩነቶች ከኅብር ውበት መገለጫነትና ባህልን፣ ቋንቋን፣ ታሪክን እና ኃይማኖታዊ እሴቶችን ለማስተዋወቅና ለማዳበር ከሚኖረው ፋይዳ ባለፈ የፖለቲካ አስተሳሰቦች ማቀንቀኛ እና የፖለቲከኞች የመታገያ መሳሪያ መሆን ሲጀምር ውበቱ ይደበዝዛል ወይም ጭርሱኑ ይጠፋል። ጎሠኝነት ፖለቲካዊ ገጽታው እጅግ ተጋኖና ጎሎቶ በወጣ ቁጥር ያንን ማኅብረተሰብ አቆራኝተው እና አፋቅረው ያቆዩትን ሠንሰለቶች የመበጣጠስ ኃይል አለው። በጎሣ በተሰበጣጠረው የኅብረተሰብ ክፍል ውስጥ የሚኖረው አወንታዊ ሚና ይቀርና የልዩነት ግንብ ይሆናል። የእያንዳንዱ ጎሣ ቋንቋ፣ ባህል፣ ታሪክና ኃይማኖታዊ እሴቶች የራሱ ብቻ ይሆናሉ። አንዱ የሌላው ውበትና የጥንካሬ ምንጭ መሆኑ ይቀርና በፉክክርና በመበላለጥ ስሜት ላይ የተመሰረተ ልዩነት ይፈጥራል። ከዚያም አልፎ በጠላትነት የመተያየት ስሜት ይመነጫል። እያንዳንዱ ጎሣም በልዩነት ግንብ ውስጥ የራሱን ደሴት ይመሰርታል። በእንዲህ አይነቱ ማኅበረሰብ ውስጥ የሚፈጠረው ጎሣን መሰረት ያደረገ ቅራኔ ሁለት መልክ ይይዛል።
የመጀመሪያው በእያንዳንዱ የጎሣ ክፍል ውስጥ ፖለቲካዊ ይዘት ያለው ፉክክርና ግብግብ ጥላቻን ይወልድና ወደ አካላዊ ግጭትም ያመራል። ጎሠኝነት ከዘረኝነት ጋር የተዛመደ እንደመሆኑም የጎሠኝነት ስሜት የሚመነጨውና የሚጎለብተው እያንዳንዱ ሰው የኔ የሚለው የዘር ሀረግ ወይም ጎሣው ከሌሎች ሰዎች ዘር ወይም ጎሣ የተሻለ ወይም የበለጠ ነው ብሎ ማሰብ ሲጀምር ነው። ይህ አይነቱ አስተሳሰብም ሰዎች ሁሉ በፈጣሪያቸው ፊት እኩል እንደሆኑ የሚገልጸውን ኃይማኖታዊ አስተሳሰብ የሚቃረንና ይህንኑ መሰረት በማድረግም “ሰዎች ሁሉ እኩል ክብርና መብቶች ይዘው ነፃ ሆነው ተፈጥረዋል። የማሰብና የማመዛዘን ችሎታ በተፈጥሮ ስለታደሉ እርስ በርሳቸው በወንድማማችነት መንፈስ ሊተያዩ ይገባል።” በማለት የሚደነግገውን የሰብአዊ መብቶች ዓለም አቀፍ ቃል ኪዳን አንቀጽ 1 የሚጥስ ነው።
ሁለተኛው ግጭት ደግሞ በእያንዳንዱ የጎሣ ቡድን ወስጥ የሚፈጠረው የግለኝነትና ጤናማ ያልሆነ የመበላለጥ ስሜት ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍሎች አንድ አድርገው ይዘው ያቆዩትን ታሪካዊ እና ሌሎች አገራዊ መገለጫዎች ይንዳል፤ እንዲሁም የጋራ ጥቅምን ማስከበሪያ የሆነውን ሕገ-መንግስታዊ ሥርዓትን ያናጋል። አልፎ ተርፎም አገርን እስከማፍረስ የሚዘልቅ ችግርን ያስከትላል። በዚህ አይነቱ ችግር ምክንያት በርካታ ትላልቅ አገሮችች ፈርሰው በጎሠኞች ደሴቶች ተቀይረዋል። የጎሠኝነት ስሜት በጠነከረና አብጦ በወጣ ቁጥር አገራዊ ስሜት ይከስማል፣ የአብሮነት ታሪክ ይዘነጋል፣ ጠባብነትና ጎጠኝነት ይነግሳሉ። እዚህ ደረጃ ላይ የደረሰ ማኅበረሰብ በበቀልና በጥላቻ ስሜት ተወጥሮ ስለሚቆይ የእልቂት አፋፍ ላይ ነው የሚቆየው። ተያይዞ ለመጥፋትና ቁልቁል መቀመቅ ለመውረድ ትንሽ ነገር ይበቃዋል። በሩዋንዳና በሌሎች የአለማችን ክፍሎች አስከፊ በሆነ መልኩ የተፈጸሙት የዘር ማጥፋት ወንጀሎች ምንጫቸው ይሄው ነው።
በአለም አቀፍ ደረጃ የተደረጉ አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ጎሠኝነትን ወይም የጎሣ-ብሔረተኝነትን መነሻ ያደረጉ ግጭቶች ባህሪያቸው እና መገለጫቸው የተለያየ ነው። ጥቂቶቹን ለመዳሰስ ያህል፤ የፖለቲካ ሥልጣንን በማዕከላዊነት በያዘ የኅብረተሰብ ክፍል እና ከፖለቲካ ምህዳሩ ተገልሎ የዳር ተመልካች እንዲሆን በተደረገ የኅብረተሰብ ክፍል ማካከል ያለውን ቅራኔ መሰረት ያደረገው የጎሣ ግጭት አንዱና በዋነኝነት የሚጠቀሰው ነው። ሁለተኛው ደግሞ በብሄር ምንጫቸው ምክንያት ወይም በቆዳ ቀለማቸው ወይም በሚከተሉት እምነት ወይም በኃይማኖታቸው ወይም በሌሎች ምክንያቶች የተነሳ በእኩልነት የመኖር መብታቸውን እና መሰረታው መብቶቻቸውን በተነፈጉ እና ጥላቻን መሰረት ላደረገ መድልዎ እና ጥቃት የተጋለጡ የኅብረተሰብ ክፍሎች የሚያነሱትን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ የእኩልነት ጥያቄዎችን ተከትሎ የሚቀሰቀሰው የጎሣ ግጭት ነው። ሦስተኛው ደግሞ፤ በሚኖሩበት ማኅበረሰብ ውስጥ ተገቢውን የፖለቲካ እና ኢኮኖሚያዊ ድርሻ ተነፍገናል ወይም የሚገባንንን ያህል አላገኘንም የሚል ጥያቄን መነሻ በማድረግ ከሌላው ማኅበረሰብ ተገንጥዮ የራሴን አገር እና ግዛት እመሰርታለው የሚሉ ኃይሎች የሚያነሱትን ጥያቄ መነሻ አድርጎ ከሌላው የኅብረተሰብ ክፍል ጋር የሚደረገ ግጭት ነው። አራተኛው የጎሣ ግጭት ደግሞ በአንድ ግዛት ውስጥ ሁለት ወይም ከዚያ በላይ በሆኑ የጎሣ ቡድኖች መካከል የኢኮኖሚና የፖለቲካውን የበላይነት ለመቆናጣጠርና የማዕከላዊውን መንግሥት ሥልጣን በበላይነት ለመቆጣጠር የሚደረጉ ፉክክሮችን ተከትሎ በሚፈጠር አለመግባባት የሚቀሰቀስ ግጭት ነው።
ከላይ የተጠቀሱት የጎሣ ግጭቶችና መንሰዔዎቻቸው በግልጽ እንዲሚያሳዩት ጎሠኝነትን መሠረት ያደረጉ የማንነት መገለጫዎች የፖለቲካ ግብ ማሳኪያ ሲሆኑ መድረሻቸው ጥላቻና ሌሎችን ‘የእኛ ጎሣ አካል አይደሉም’ የሚሉዋቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎች ማግለልና ሲከፋም ዘራቸውን ከምድረ-ገጽ ለማጥፋት እስከ መሞከር ይዘልቃል። ይህ ችግር የተከሰተው እንደ ኢትዮጵያ ባለ እጅግ በተሰበጣጠረ ማኅበረሰብ ውስጥ ሲሆን የዘረኝነት መርዙ በብዙ መንገዶች ሊንጸባረቃ ይችላል። በልማት እንቅሳቅሴ፣ በትምህርት ዘርፍ፣ በኢኮኖሚና የንግድ ዘርፍ፣ በመሬት አጠቃቀም ፖሊሲ፣ በግብር አከፋፈል ሥርዓት፤ እንዲሁም በተለያዩ አስተዳደራዊ ዘርፎች ሁሉ የጎሠኝነቱ ስሜትና ውጤቱ በግልጽ ይስተዋላል። ለምሳሌ በፊሊጲንስ ቅጥ አጥቶ የነበረው ጎሠኝነት በአገሪቱ የኃይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል አጠቃቀም ላይ ጭምር በግልጽ ይስተዋል ነበር። በማሌዢያ እና በታንዛኒያ ደግሞ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት አቅርቦት ላይ የጎሣ መድልዎ አፍጥጦ ይታይ ነበር። በሌሎች አገሮችም የተለያዩ መገለጫዎች ያላቸው ጎሠኝነትን መሰረት ያደረጉ ክፍፍሎችና መድልዎች ተስተውለዋል፤ አስከፊ ግጭቶችንም አስከትለዋል።
በጎሣ የሚደራጁ የፖለቲካ ፓርቲዎች መነሻቸው ከሁለት ክስተቶች የሚመነጭ ነው። የመጀመሪያው ውስጣዊ ምክንያት ነው። ይኽውም በእያንዳንዱ የጎሣ ክፍል ውስጥ ካለው ማኅበረሰብ ከራሱ የሚመነጭ ነው። የአንድ ጎሣ አባላት ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፓለቲካዊ ጥቅማቸውን በተሻለ ሁኔታ ለማስጠበቅ ሲሉ በፖለቲካ የሚደራጁበት ሁኔታ ነው። ሁለተኛው ደግሞ ውጫዊ ምክንያት ነው። ይኽውም የአንድ ጎሣ አባላት በተደጋጋሚ ከአንድ ወይም ከሌሎች ጎሣዎች ጥቃት ሲደርስባቸው፣ ከሌሎች ጎሣዎች በተለየ መልኩ መድሎና መገለል ሲደርስባቸው፣ ከኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጥቅሞችና ተሳትፎዎች እንዲገለሉ ሲደረግ እና በሌሎች ተመሳሳይ ምክንያቶች አደጋ ሲጋረጥባቸው ይህን መሰሉን ጥቃት ለመከላከል በሚል አካባቢው በፈጠረባቸው አስገዳጅ ሁኔታ በመነሳት የጎሣቸውን አባላት ጥቅም እና ደኅንነት ለማስጠበቅ በማሰብ በፖለቲካ የሚደራጁበት ሁኔታ ነው። በመሆኑም ጎሣን መሰረት አድርገው የሚመሰረቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ድጋፍ የሚያገኙት እንወክለዋልን ከሚሉት የኅብረተሰብ ክፍል ብቻ ስለሆነ የሚታገሉትም ሆነ ሥልጣን ሲቆናጠጡ ቅድሚያ ተጠቃሚ የሚያደርጉት የደገፋቸውን እና የሚወክሉትን የጎሣ ክፍል ብቻ ነው። ጎሣን መሰረት ያደረጉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከጠቅላላው ማኅበረሰብ ጥቅም አንፃር እጅግ ጠባብ የሆነ የቡድን ፍላጎትና አጀንዳን ነው የፖለቲካ ግብ አድርገው የሚነሱት። እነዚህ ኃይሎች የፖለቲካውን ሥልጣን በተቆናጠጡበት ሥፍራ ሁሉ ታዲያ የእኛ ከሚሉት ጎሣ ክፍል በተነጻጻሪ ባለው ቀሪው የኅብረተሰብ ክፍል መካከል ግልጽ የሆነ የጥቅምና የመብት መበላለጥን ይፈጥራሉ። ይህ ሁኔታም እያደር ቅራኔንና ጥላቻን ያራባል።
የጎሠኝነት ስሜት አብጦ በወጣበትና ድርጅታዊ ቅርጽ ይዞ በጎለበተበት አገር ሁሉ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎችና አስተሳሰቦች የሚመዘኑትና የሚመነዘሩት በእያንዳንዱ ጎሣ መስፈርት ነው። የፖለቲካ ፓርቲዎችም የሚደራጁትና የሚታገሉት ጎሣዎችን መሰረት በማድረግ ነው። የጎሠኝነት ስሜት ገኖ በሚታይበት ሥፍራ ሁሉ ሰብአዊ መብቶችን ችላ ማለት፣ አሰቃቂ የሆኑ የመብት ጥሰቶችን በሌሎች ላይ መፈጸምና ሰዎችን በፍርሃትና በከፋ ችግር ውስጥ መጣል የተለመዱ ተግባራት ናቸው። ይህ አይነቱ ሁኔታ እጅግ በተከፋፈለ ማኅበረሰብ ውስጥ ሲከሰትና ፓርቲዎችም የጎሣን መስመር ተከትለው መደራጀት ሲጀምሩ ጠንካራ የፖለቲካ ተፎካካሪ ኃይሎች መሆናቸው ጥያቄ ውስጥ ይወድቃል። ምክንያቱም ድጋፍ የሚያገኙት ከሚወክሉት ጎሣ አባላት ብቻ ስለሆነ። ከዚህም ባሻገር ለጠቅላላው ሕዝብ ጥቅም የሚቆሙ ብሔራዊ የፖለቲካ ኃይሎች እንዲዳከከሙ እና እንዲጠፉም ምክንያት ይሆናል። ለዚህም ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ የአፍሪካ፣ ኢስያ እና ካረቢያን አገራት ዛሬ የሚገኙበትን ሁኔታ ማጤን በቂ ነው። በዚህ መጠነኛ የዳሰሳ ጽሁፍ ውስጥ የጎሠኝነተን አስተሳሰብ፣ መሰረታዊ እና ታሪካው ምንጭ እንዲሁም በጎሣ ግጭቶች ዙሪያ የሚነሱ የተለያዩ ሃሳቦችን ሁሉ ለማካተትም ሆነ በመጠኑም እንኳን ለመቃኘት አይቻልም። እራሱን የቻለ ሰፊ ጥናትና ምርምር የሚጠይቅ ስለሆነ ይህ ዳሰሳ ለዚህ ጽሁፍ ቀጣይ ክፍሎች እንደ መንደርደሪያ ተደርጎ እንዲወሰድ ለማሳሰብ እወዳለሁ።
በቀጣዩ ክፍል እስከምንገናኝ በቸር እንሰንብት።
ያሬድ ኃይለማርያም
http://humanrightsinethiopia.wordpress.com/