Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

[የሃረሩ ቃጠሎ ጉዳይ] መቃጠል መቃጠል መቃጠል –ከፋሲል የኔዓለም (ጋዜጠኛ)

$
0
0

ጋዜጠኛ ፋሲል የኔዓለም

ጋዜጠኛ ፋሲል የኔዓለም

ከአስራ ምናምን ዓመታት በፊት ፔሩቪያዊው ኢኮኖሚስት ሄርናንዶ ደ ሶቶ ስለ “ኢንፎርማል” ኢኮኖሚ በጻፈው መጽሃፍ ውስጥ ፣ በአለም ላይ በህጋዊ መንገድ ያልተዘመገበ ከ10 ትሪሊየን ዶላር በላይ ሃብት መኖሩን፣ ይህን ሃብት መዝግቦ የባለቤትነት ህጋዊ መብት በመስጠት ብዙ ዜጎችን ከድህነት ማውጣት እንደሚቻል ገልጾ ነበር። ደ ሶቶ እንደሚለው በደሃ አገራት ሁለት አይነት ኢኮኖሚ አለ። አንደኛው ጥቂቶች የሚያንቀሳቅሱትና በመንግስት እውቅና የተሰጠው ኢኮኖሚ ሲሆን ሌላው ደግሞ መንግስት የማያውቀው በአብዛኛው ህዝብ የሚንቀሳቀሰው ኢኮኖሚ ነው ፤ ይህ ኢኮኖሚ በመንግስት እውቅና ያልተሰጠው በመሆኑ በዚህ ስር የታቀፉ ዜጎች ከባንክ ተበድረው ቢዝነሳቸውን ለማስፋፋት አይችሉም፤ መንግስትም ከእነዚህ ሰዎች ተገቢውን ታክስ አያገኝም። በደሃ አገራት ውስጥ መንግስታት እውቅና ሳይሰጡት የሚንቀሳቀሰው ሃብት እውቅና ከተሰጠው ሃብት ይበልጣል። ደ ሶቶ እንደሚመክረው ህጋዊው የኢኮኖሚ ስርአት የማያውቃቸውን ሀብቶች በመመዝገብና ህጋዊነት በማላበስ ዜጎች ሃብትና ንብረት እንዲያፈሩና ድህነትን እንዲሻገሩ ማድረግ ይቻላል።

የ ደ ሶቶን ሃሳብ ለማየት በአዲስ አበባ የተገነቡ የጨረቃ ቤቶችን እንመልከት። ነዋሪዎቹ ቤቶችን ለመስራት ብዙ ገንዘብ፣ ጉልበትና ጊዜ አፍስሰዋል፣ ይሁን እንጅ የመንግስትን የባለቤትነት ማረጋገጫ ቁራጭ ወረቀት ለማግኘት ባለመቻላቸው የሰሩት ቤት ሃብት ሊሆን አልቻለም። ቤታቸውን መሸጥ፣ መለወጥ እንዲሁም በባንክ አስይዘው ገንዘብ መበደር አይችሉም። እነዚህ ሰዎች የባለቤትነት ካርታ እስካላገኙ ድረስ ቤታቸው ሃብታቸው ነው ማለት አይቻልም። ነገር ግን የይዞታ ማረጋገጫ ብጣሽ ወረቀት ባገኙ በሰከንድ ውስጥ ቤታቸው ሃብታቸው ይሆናል፣ መሸጥ መለወጥ፣ ቤታቸውን አስይዘው ከባንክ መበደር ይችላሉ። በአንድ ወረቀት የቤቶቹ ባለቤቶች ከድህነት ወደ ሃብት ባለቤትነት ተሸጋገሩ፣ በሌላ አነጋገር የድህነትን መጋረጃ ቀደዱ ማለት ነው። መንግስት ህጋዊ እውቅና ለሌላቸው ሌሎች ቢዝነሶችም ህጋዊ እውቅና ቢሰጥ ፣ ሰዎችን ባለሀብት ማድረግ ብቻ ሳይሆን መንግስትም ከእነዚህ ቢዝነሶች ብዙ ግብር መሰብሰብ ይችል ነበር። በኢትዮጵያ ያለው የገዢዎች ስብስብ ግን ንብረት በማውደም የሚደሰት ይመስላል። ቤት ማፍረስና ንብረት ማቃጠል ልዩ መልክቱ ሆኗል። ባለፉት 22 ዓመታት ስንትና ስንት ቤቶች ፈረሱ፣ ስንቶቹ ተቃጠሉ፣ ስንትና ስንት የአገር ሃብት አብሮ ወደመ፣ ስንቶቹ ደኸዩ፤ ወረቀት በማደል ህጋዊ ማድረግ ሲቻል ሳይቻል ቀረ።

ከረጅም አመታት በሁዋላ የደ ሶቶን መጽሃፍ እንዳስታውስ ያደረገኝ በሀረር በተደጋጋሚ የሚታየው የእሳት ቃጠሎ ነው። የንግድ ቤቶችን የሚያቃጥላቸው መንግስት ከሆነ የመንግስት የድንቁርና ብዛት ልክ ማጣቱን የሚያመለክት ነው። መንግስት ቤቶችን ሲያቃጥል፣ ቤታቸው የተቃጠለባቸው ሰዎች ወደ ድህነት ጎራ መግባታቸውን አያውቅም ለማለት አልደፍርም። እነዚህ ሰዎች ህጋዊ እውቅና የላቸውም ቢባል እንኳን፣ የህጋዊነት ማረጋገጫ ብጣሽ ወረቀት በመስጠት፣ ህጋዊ በማድረግ ድህነትን እንዲሻገሩ ማድረግ ይቻል ነበር። ንብረትን በእሳት በማጋየት የሚገኝ የኢኮኖሚ እድገት ምን እንደሆነ በፍጹም አይገባኝም፤ የማውደም ኢኮኖሚክስ የሚባል ነገር መኖሩንም አላውቅም።
Harar City
መንግስት አነስተኛና ጥቃቅን እንዱስትሪ የሚለው ነገር አለ። ሃሳቡ ፖለቲካዊ ይዘት ባይኖረው ጥሩ ነው። አውሮፓኖች ያደጉት በተለያዩ ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንዱስትሪዎች በጊዜው አጠራር ( ጊልዶች) ነው። የዛሬዎቹ ግዙፍ የአውሮፓ ኢንዱስትሪዎች በተለያዩ አነስተኛ ጊልዶች የተመሰረቱ ናቸው። በእኛ አገር ግን መንግስት ጥቃቅንና አነስተኛ የተባሉትን ድርጅቶች ከቢዝነስ አውጥቶ የፖለቲካ ስራ ስለሚያሰራቸው ተደካሙ፣ እነዚህ ድርጅቶች የቢስነዝ ድርጅቶች ከሚባሉ፣ ጥቃቅንና አነስተኛ የፖለቲካ ድርጅቶች ቢባሉ ይቀላል። መንግስት እነዚህን ድርጅቶች በመደገፍ ወደ መለስተኛ እንዱስትሪነት እንዲለወጡ ከማበረታታት በራሱ ትላልቅ ግንባታዎችን ያካሂዳል። አምባገነን መንግስታት ሁሌም ትላልቅና ብልጭልጭ ግንባታዎችን መስራት ያስደስታቸዋል። ግንባታዎቹ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ይኑራቸው አይኑራቸው፣ በህዝቡ እስከታዩና “ ዋው” እስካስባሉ ድረስ ግድ የላቸውም። ለምሳሌ የተከዜን የሃይል ማመንጫ እንመልከት። የወጣበት ገንዘብ የትየለሌ ነው፣ ጠቀሜታው ግን እዚህ ግባ የሚባል አይደለም ፣ ግልገል ጊቤም እንደዛው ነው። በአባይ ግድብ ኢኮኖሚያዊ አዋጭነት ላይም ጥርጣሬ አለኝ- በተለይ ከደለል ጋር በተያያዘ የሚፈጠረው ችግር በቀላሉ አይፈታም። በአዲስ አበባ የሚገነባው ባቡር ብዙ ጦሶችን ይዞ እንደሚመጣ እድሜ ከሰጠን እናየዋለን። መንግስት ለታይታም ቢሆን በሚያስገነባቸው ግዙፍ ግንባታዎች አነስተኛ ኢንዱስትሪዎች ተረስተዋል፣ በዚህም የተነሳ እድገቱ መሰረት የሌለው የእቧይ ካብ ሆኗል።

በሃረርና በተለያዩ ከተሞች የሚገኙ ነጋዴዎችን ንብረት ከማውደም በአነስተኛ ማህበራት እያደራጁ የኢኮኖሚው መሰረት እንዲሆኑ ማድረግ ይቻል ነበር፤ ነገር ግን ለዜጎቹ የሚቆረቆር መንግስት የለምና ሁሉም ነገር በምኞትና በነበር ይቀራል።
harar city fire


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>