Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

“ሰው በላ” በሆኑት የኢህአዴግ ሙሰኞች ላይ ኮሚሽኑ ለምን ይሽኮረመማል?

$
0
0

ሳሙኤል ተወልደ በርሔ/ሃርስታድ ኖርዌይ/
የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ በነበሩበት የጠቅላይነት ዘመን የተጀመረው እና ቀጣይነት እንደሚኖረው የተነገረለት የከፍተኛ ባለስልጣናት ‹‹የሀብት ምዝገባ››ን የበላው ጅብ ምነው አልጮህ አለ?…ጥያቄው ይህ ነው፡፡ የሚመለከተውም ጸረ ሙስና ኮሚሽንን ነው፡፡ ጸረ ሙስና ኮሚሽን የገቢዎች ባለስልጣናቱን እነ አቶ መላኩ ፈንቴን በሙስና ወንጀል ጠርጥሮ ካሳሰራቸው በኋላ ፀረ ሙስና ስሙ የመታደስ አዝማሚያ ታይቶበት ነበር፡፡ ትናንሽ ባለስልጣናት ላይ እንደሚበረታ የሚነገርለት ፀረ ሙስና ኮሚሽን የነ አቶ መላኩ ፈንቴን በቁጥጥር ስር መዋል ተከትሎ ከአይን ያውጣህ ተብሎ ነበር፡፡

ይህ ራሱን የቻለ ጉዳይ ቢሆንም፣ ለዚህ መጣጥፍ መነሻ የሆነኝ ግን ተጀምሮ የተቋረጠው ወይም ወደፊት ይፋ ይሆናል ተብሎ በእንጥልጥል የቀረው የከፍተኛ ባለስልጣናት የሐብት ምዝገባ ይፋ የማድረግ ሒደት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ሙስና እና ሙሰኞች እንዳሉ ባለጉዳዩ ኢህዴግም ያምናል፤ ያውቃል፡፡ የሀገር እና የህዝብን ሀብት የተለያየ ቅርንጫፍ ካለው የሙስና ግንድ መታደግ የሚቻለው ባለስልጣናትን በማሰር ብቻ አይመስለኝም፡፡
የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ባለቤት ወይዘሮ አዜብ መስፍን በአንድ ወቅት፡- “መለስ የ6 ሺ ህብር ደመወዝተኛ ነበር፡፡ ቤተሰቡን ከወር እስከወር ያስተዳድር የነበረውም መንግስት በሚከፍለው ደመወዝ ብቻ ነበር…” በማለት እንደተናገሩ (እንደተሳለቁ) አይዘነጋም፡፡ ለተቀረው ኢትዮጵያዊ ቀርቶ ለራሱ ለኢህአዴግ አባላት እንኳን ፌዝ የሆነው የወ/ሮ አዜብ መስፍን ንግግር በፀረ-ሙስና ኮሚሽን ዘንድ እንዴት እንደሚታይ (እንደሚተረጎም) አላውቅም፡፡ ኮሚሽኑ “በ6 ሺህ ብር ደመወዝ ነበር የምንተዳደረው” ከሚለው የወይዘሮዋ ንግግር ተቃራኒ የሆነ የሀብት ክምችትን ያጋልጥ ይሆን?…ወይስ ወይዘሮ አዜብ እንዳሉት “የመለስ ቤተሰብ በ6 ሺህ ብር ይተዳደር ነበር፡፡ አሁንም ቢሆን ከሚቆረጥላቸው የባለቤታቸው የጡረታ ገንዘብ ውጪ ቤሳቤስቲን የላቸውም” በማለት ፖለቲካዊ ጥብቅና ይቆምላቸው ይሆን?…አብረን የምናየው ይሆናል፡፡
“ዓላማዬ ሙስናን እና ሙሰኞችን ማጋለጥ ነው፡፡ ህብረተሰቡም ይተባበረኝ…” እያለ በተደጋጋሚ የሚደሰኩረው ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ለረዥም ጊዜ አፍኖ ያቆየውን (“ሲመዘግብ የነበረውን”) የባለስልጣናት ሀብት ያለ አንዳች “ሴንሰር” ወይም ኦርጂናሉን ንብረታቸውን ይፋ እንደሚያደርግ ሰሞኑን በድረ-ገፆች ከተሰራጩ መረጃዎች መገንዘብ ይቻላል፡፡ እዚህች ጋር ጥያቄ አለኝ፤ ኮሚሽኑ “ይፋ” የሚያደርገው የባለስልጣናት ሃብት በምን ዓይነት የምርመራ ስትራቴጂ የደረሰበት ነው?…ወይስ ባለስልጣናቱ “እኔ የመንግስት ሰራተኛ ነኝ፤ ከዬት አምጥቼ ሀብት አከማቻለሁ?…ያለችኝ ይቺ ናት” ብለው የተናዘዙትን ጥቃቅንና አነስተና ንብረት ነው “ይፋ” የሚያደርገው?
“ያለቺኝ ይቺ ናት፤ ይህችኑ መዝግብ” ተብሎ የተሰጠውን ሀብት ይፋ የሚያደርግ ከሆነ በህዝብ ንብረት ላይ መሳለቅ ነው የሚሆነው፡፡ የተለያዩ ዓለም ዓቀፍ ተቋማት በቢሊዮን የሚቆጠር በሕገ-ወጥ መንገድ ገንዘብ ከኢትዮጵያ ወደ ውጪ እንደሚኮበልል በየጊዜው ያጋልጣሉ፡፡ እንዲህ ያለ ዘግናኝ ገንዘብ መቼም በተራ ኢትዮጵያዊ ወደ ውጪ ይኮበልላል ማለት የዋህነት ነው፡፡ በኮበለለው እና ወደፊትም በሚኮበልለው የህዝብ (የሀገር) ገንዘብ ውስጥ የቱባ ባስልጣናት እጅ እንዳለበት አያጠራጥርም፡፡ ታዲያ ኮሚሽኑ በምን መንገድ ነው በከባድ ሙስና ኮብልሎ በውጪ ሀገር ባንኮች የተከማቸውን ገንዘብ የሚያጋልጠው?…የሚለው ጥያቄ የግድ አጥጋቢ ምላሽ ማግኘት አለበት፡፡
ፀረ-ሙስና ኮሚሽን የነ አባዱላ ገመዳን፣ የነበረከት ስምኦንን፣ የነዶ/ር ደብረፅዮንን…ትክክለኛ ሀብትና ንብረት ካላሳወቀን ኮሚሽንነቱ ቀርቶ እንደ መርካቶ “ቁጭ በሉ” እያታለለን ቢኖር “መልካም” ነው፡፡ ምክንያቱም፡- የመርካቶ “ቁጭ በሉ” ለተነሳለት “ዓላማ” ባዳ በመሆኑ የትኛውም ዓይነት ኃላፊነት ደንታ አይሰጠውም፡፡ ስለሆነም በኮሚሽነር አሊ ሱሌይማን የሚመራው ፀረ-ሙሽና ኮሚሽን የበረከት፣ የደብረፂዮን ወይም የአዜብ “ዓይን ገረፈኝ” ብሎ የተዛባ መረጃ የሚያቀርብልን ከሆነ “ውጉዝ ከመ አርዮስ” ከመባል አይድንም፡፡
ምክንያቱም ከዚህ ምስኪን ሕዝብ የተሰበሰበ ገንዘብ እንደ “ቦዘኔ” ልጅ የትም ወጥቶ ሲቀር ከማየት በላይ የሚያስቆጭም የሚያናድድም ድርጊት የለም፡፡
ጸረ-ሙስና ኮሚሽን ከደብረፂዮን ጋር ሲሆን ሕወሓትን፣ ከበረከት ጋር ሲሆን ብአዴንን፣ ከአባዱላ ጋር ሲሆን ኦህዴድን…መምሰሉን ትቶ ለኢትዮጵያ ህዝብ ዘብ እንዲቆም ከዛሬ ጀምሮ በአስቸኳይ ዝግጁ መሆን አለበት፡፡ ካለበለዚያ ካገኘው ወይም የሩሲያ ቮድካ ከጋበዘው ባለስልጣን ጋር ሁሉ እንደ እስስት እየተመሳሰለ የኢትዮጵያን ህዝብ ላብ እንደ ደም መምጠጥ እንደሌለበት ካሁኑ መገንዘብ አለበት፡፡ እንዲሁም እንደ ልጃገረድ መሽኮርመሙን አቁሞ የባለስልጣናቱን ሀብት “ይፋ” ማድረግ አለበት፡፡ ምክንያቱም ሙስና የገንዘብ ዝርፊያ ቢሆንም፤ እንደ “ሰው በላ” አውሬ ሀገሪቱን ቀርጥፎ ይጨርሳታል ባይ ነኝ፡፡
ከፍተኛ ባለስልጣናቱ ያላቸውን ሀብት በይፋ ካስመዘገቡ እና የተመዘገበው ሀብታቸው ለህዝብ ይፋ ከሆነ፣ ከደሞዛቸው በላይ የሆነ መኪና ለመንዳት ብዙም ድፍረት እንደማያገኙ ይታመናል፤ ምናልባት ዓይን በጨው በማጠብ የመጣው ይምጣ ብለው ካልፎከሩ በስተቀር፡፡ እናም ፀረ ሙስና ኮሚሽን ሆይ ያኔ ማለትም የዛሬ ሁለት እና ሶስት ዓመት ገደማ የከፍተኛ ባለስልጣናት ሀብትን መዝግበህ አንደነበር አይዘነጋም፡፡
ወይስ የከፍተኛ ባለስልጣናቱ ፊት እንደ እሳት ገረፈህና የነሱን የሀብት መጠን ለማሳወቅ ጉልበትህ ከዳህ? በርግጥ ልክ ነህ፤ የቱባ ባለስልጣናቱን ሀብት መዝግበህ ይፋ ከምታደርገው የሀብት መጠን በላይ ህንፃ ሲገነባና መኪና ሲሸጥ ያገኘኸውን አይነኬ ባለስልጣን መንካት ምን ያህል ከባድ እንደሆነ አናጣውም፡፡
ይህ ማለት ግን በአንድም ሆነ በሌላ ምክንያት የህዝብ ሀብት ሲመዘበር መሽኮርመም አለብህ ማለት አይደለም፡፡ ኃላፊነትህ ሀገር እና ወገንን ከምዝበራ ማዳን እስከሆነ ድረስ በአብዛኛው በልመና እና በእርዳታ የምትተዳደር ሀገርን አሳልፈህ መስጠት የለብህም፡፡ በኢትዮጵያ ህዝብ ስም የሚመጣው የእርዳታ እና የልመና ገንዘብ የተለመነለትን አላማ ሳያሳካ የሚቀርበት ጊዜ እንዳለ ከማንም የተሰወረ አይደለም፡፡
ይሄ ጉዳይ ደግሞ ከማንም በላይ ሊያሳምመው የሚገባው በኮሚሽነር አሊ ሱሌይማን የሚመራውን የፌደራል የስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽንን ነው፡፡ እንደ እንጉዳይ እየበቀሉ የሚያድሩ ከሚመስሉት የአዲስ አበባ ዘመናዊ ህንፃዎች መካከል ምን ያህሎቹ ለሐሜት የተጋለጡ እንደሆኑ እናውቀዋለን፡፡
ይሄ ህንፃ እከሌ የተባለ ባለስልጣን ንብረት ነው፤ ያኛው ድርጅት የእገሌ ነው ለሚል የአደባባይ ሐሜት የተጋለጡ ንብረቶች መኖራቸው ፀረ ሙስና ኮሚሽንን እንቅልፍ ሊነሳው በተገባ ነበር፡፡ እንዲህ አይነቱ የአደባባይ ሐሜት ተመርምሮ እና ተጣርቶ ተጠርጣሪዎቹ ማግኘት የሚገባቸውን ቅጣት እንዲያገኙ ያስችላል በሚል ምክንያት የሐብት ማሳወቂያ እና ማስመዝገቢያ አዋጅ ቁጥር 668/2002 ወጥቶ ስራ ላይ ከዋለ ሰነባብቷል፡፡ በነገራችን ላይ አዋጁ ወጥቶ ስራ ላይ ከዋለ በኋላ በመጀመሪያው አመት ማለትም በ2003 ዓ.ም 18ሺህ 94 ሰዎች ሐብታቸውን አስመዝግበዋል፡፡
ከነዚህም መካከል የኤፌድሪ ፕሬዚዳንት፣ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት እና ፌዴሬሽን ም/ቤቶች አፈ ጉባኤዎች፣ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት፣ የኢፌድሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ሀብታቸውን እንዳስመዘገቡ የፀረ ሙስና ኮሚሽን መረጃ ያመላክታል፡፡ ግን የትኛው ባለስልጣን ምን ያህል ሀብት እንዳለው ኮሚሽኑ ይፋ አላደረገም፡፡ ይህን ማድረግ እያለበት ያላደረገበት ምክንያት ነው ሊያነጋግር የሚገባው፡፡
የከፍተኛ ባለስልጣናቱ ሀብት መመዝገብ አንድ ርምጃ ነው፤ ዋናው ስራ ግን ሀብታቸውን ይፋ የማድረጉ ሒደት ይመስለኛል፡፡ አቶ በረከት ስምኦን፣ ወይዘሮ አዜብ መስፍን፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል፣ አባዱላ ገመዳ…ወዘተ ሀብታቸው እንደተመዘገበ ቢነገርም የሀብታቸው መጠን ይፋ አለመሆን ህብረተሰቡ ከሙስና የፀዳች ኢትዮጵያን ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት ውስጥ ሊጫወት የሚገባውን ሚና አዳክሞታል የሚሉ አስተያየቶች ይደመጣሉ፡፡
አቶ መለስ ዜናዊ በአንድ ወቅት ‹‹ዜጎች ከታችኛው አስከላይኛው መዋቅር የመንግስት አካል ድረስ ሙስና እንዳይኖር የሚያስችል ከባቢ መፍጠር አለባቸው›› ማለታቸውን አስታውሳለሁ፡፡ እኔ ደግሞ እንዲህ እላለሁ፡- ዜጎች እንዲህ አይነቱን ከባቢ መፍጠር የሚችሉት ፀረ ሙስና የመዘገበውን የባለስልጣናት ሀብት ለህዝብ ይፋ ሲያደርግ ነው እላለሁ፡፡
አንድ ባለስልጣን ካስመዘገበው ሀብት በላይ ሲቀማጠል ያየው ሰው ለሚመለከተው አካል ጥቆማ ሊሰጥ የሚችለው የባለስልጣናቱ ሀብት አስቀድሞ ይፋ ሲሆን ብቻ ነው፡፡ በተረፈ ጠንቋይ በመቀለብ ሙስናን መዋጋት አይቻልም፡፡ እንደ ፀረ ሙስና ኮሚሽን መረጃ ከሆነ ከላይ የጠቀስኳቸውን ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎች ጨምሮ 393 ከፍተኛ ተሿሚዎች፣ 498 የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ 10334 የሌሎች የመንግስት መስሪያ ቤቶች ተሿሚዎች እና የመንግስት ሰራተኞች፣ 3225 የአዲስ አበባ አስተዳደር ምክር ቤት አባላት ተሿሚዎች እና የመንግስት ሰራተኞች፣ 3644 የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ሰራተኞች በአጠቃላይ 18ሺህ 94 ሰዎች ሐብታቸውን ቢያስመዘግቡም፣ አሁንም ድረስ የመንግስት ኃላፊዎች ሀብት ምን ያህል እንደሆነ ጸረ ሙስና እና እግዜር ብቻ ናቸው የሚያውቁት፡፡ እንደው ፀረ ሙስና እግዜር ረድቶት የቱባ ባለስልጣናትን የሀብት መጠን ቢያሳውቀን ጥሩ ነበር፤ ደግሞም ያጓጓልም፡፡
የኃይለማርያም ደሳለኝ ሀብት ምን ያህል እንደሆነ ለማወቅ የማይፈልግ ሰው አለን? የበረከት ስምኦን እና የአዜብ መስፍን ሀብት ስንት እንደሆነ ማወቅ አያጓጓምን? የሌሎቹንም ባለስልጣናት ሀብት ማወቅ ከልብ አንጠልጣይ ፊልም በላይ ያጓጓል፤ ያቁነጠንጣል፡፡ እናም ፀረ ሙስና ኮሚሽን ሆይ ለመጓጓታችን ብቻ ሳይሆን ለፀረ ሙስና ትግሉ ስትል ጭምር የባለስልጣኖቻችንን ሀብት በፈጠረህ አሳውቀን፡፡ አለበለዚያ የፀረ ሙስናውን ትግል ራስህ እንደ ጀመርከው ራስህ እዛው ትጨረስዋለህ፡፡
ህብረተሰቡን የትግሉ ተሳታፊ ማድረግ የሚቻለው፣ ትግሉ በድል እንዲጠናቅ የሚያስችሉ መረጃዎችን ይፋ በማድረግ ነው፡፡ ነገር ግን ኮሚሽኑ መረጃዎቹ ላይ አንጥፎ ተኝቶ ህብረተሰቡ የነቃ የፀረ ሙስና ትግል እንደሚያካሂድ መመኘት እንደማሞ ቂሎ ፍሬ አልባ መሆን ነው፡፡ የፀረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ አሊ ሱሌይማን የባለስልጣናቱን የሀብት ምዝገባ መረጃ በአጭር ጊዜ ውስጥ ይፋ በማድረግ አባክዎን ትግሉን ያጧጡፉ!!!


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>