ባድማ በጃርት ተሰቅዛ
በአረማሞ አራሙቻ ናውዛ
እህህን ሰንቃ ደንዝዛ
ሰቀቀን ታጥቃ አርግዛ።
በ’ሬት ጨጎጎት ተደልዛ
መቀነት በእሾኽ ተገንዛ፣
ቁም ስቅሏን አዬች
ይህው በልዛ።
`ጃርተ ምርት እሾህ
ፍጥረተ ነገሯ ውጋት
በበቀል – ተዋቅራ
በደም – ተቋድሳ
በደጋን ታምሳ – ተደቁሳ፤
እሾህ አዘራች መልሳ፤
የጃርት ገላ መላልሳ።
ህልመ ራዕዩ ምልግልግ
የላንቁሶ ውሃ ዝልግል
ጃርተ – ልብ፤ የእሾህ ልግ
የአሜክላ የቋሳ ድግዳግ።
ጃርትስ አሰኛት የበቀል ብቅል
ቋቱ ’ማያውቅ ግልግል
የጃርት ህሊና የውጋት ግልገል፣
ሰባራ ገል።
እሾህስ አልቦ የለም ጃርት
ከዘረ እሾህ የለም ምርት
የጠቀራ ናስ ሃሞት
ዙሪያ ገባው ማት፤
… ህልፍት የሐገር ቅብረት።
አንተ አለህና በቤትህ
ትሰማለህም ታያለህም
የጃርትን ትዕቢት፤ … የቀን ጥሰት
የበቀል አምላክ አትለፋት፤
የህዝብን ዕንባ ህማማት፤
እ!-እ!-እ!-እ!እ!-እ!-
እም – እም – አም እ——-ም!
ውስጥ
ይህን ግጥም ለመጀመሪያ ጊዜ መድረክ ላይ ያቀርብኩት የመጀመሪያዋ ሐገራዊ ፓርቲ ሊ/መንበር ክብርት ዳኛ ብርቱካን ሜዴቅሳ የፓርቲያዋን የአንድነትን ዓላማና ተግባር ለማስተዋወቅ፤ እንዲሁም ደጋፊ አካላትን ለማዋቀር እ.አ.አ በ2008 በታህሳስ ወር አውሮፓ በተዘዋወረችበት ወቅት ሲዊዝ ጄኔባ መጥታ በነበረችበት ጊዜ ነበር። ከመክፈቻ ንግግሬ በኋላ ግጥሙን አቅርቤ ስጨርስ እንዲህ አለች „አንቺ ምን አለብሽ?! እንዲህ የልብሽን በነፃነት ታቀርቢያለሽ። እኛ የግጥም ምሽት አዘጋጅተን ከቢሮችን ውስጥ በታጣቂዎች ተከበብን“ በማለት ተክዛ ቆዬችና አይኗን ወደ እኔ ላከችው።
አዬሩ ፈቅዶ ሁለታችንም አገናኘን። በመንፈስ ተቀራረብን – ተዋኽድን። አስተውላም አዬችኝ በውስጧ – እኔም ምላሹን ደረብኳት። ህልሜ ተሳክቶ ሴት አቅሟን ብቃቷን እንዳዛ በወሳኝ የኃላፊነት ቦታ በእርግጠኝነት ስታቀርብ ከማዬት በላይ ሐሴት አልነበረም። ተስፋውንም ቀጠልኩበት። ቃሌን ሳላጥፍ ከተግባር አርበኞቿ፤ ከሲዊዝ የአንድነት ድጋፍ ሰጪ አካሎቿ ጋር ጥሩ የሰመረ የሰላም ጊዜ አሳለፍን። እንዲሁም በአለም ዙሪያ ካሉ ተቆርቋሪዎቿ ጋርም የሚያስመካ የፍቅር አንድነት ገነባንበት። አቅለ ቢሱ ወያኔም ስትመለስ እግር ብረት ለእሷና ለልጇ ለሀልዬ አዘጋጅቶ ቢጠባቅታም ደጋፊዎቿ ግን በያሉበት ታጥቀውና ተግተው ታገሉ። ከአውሮፓ ወደ ቃሊት። እጅግ አስደንጋጭና መራራም ነበር። ዛሬ ደግሞ ለሴት ተቆርቋሪ ሆኖ ሙጃው ወያኔ አለሁኝ ሲል አዳመጥን።
እኔ በግሌ ከጃርት የእሾህ ፈል እንጂ ሌላ እምጠብቀው የለም። ጠንከር ያሉ ትችቶችን ላጥ አድርጎ ማስመሰሉን አቀለጠበት – አይፍር መንፈሱን በአሻቦ ያወራረደ – ግልብ። እንደዚህ ላጥ እያደረገ ቀሰማውን እንደሚያስነካው ስለምን የተባበሩት መንግስታት ድንጋጌዎች አክብሮ በሰቧዕዊ መብት ላይ የሚደልቀውን ጭፈራ አይገታም? ወኔ ካለው በሺህ የሚቆጠሩ ሴት እስረኞች ካለምንም ቅድመ ሁኔታ ይፍታ። ከዚህ ከለበጣ ኮሜዲ ተግባሩ በፊት። ሲያንጎላች ይከርምና እንዲህ ይባንናል – የጉም ሽንት። ለቅብ እንዳረገደ እንዳረገረገ 23 ዓመት —– ነጎደ።
የኔዎቹ በሉ ተመራርቅን አንለያይ። የተመቼ ጊዜ እንሆ ተመኘሁላችሁ። ፍቅርና ናፍቆት በገፍም ተላከ ለእናንተ ——– — ለክብረቶቼ።
ማሳሰቢያ — 1. ግጥሙ – ግንቦት 20 ቀን 2000 ዓ.ም ክላይነአንደልፊንገን – ሲዊዘርላንድ ተጻፈ። ከመጀመሪያው መጸሐፌ „ተስፋ“ ላይ ከገጽ 49 እስከ 50 ይገኛል።
2. ይህቺ ምልክት ’ ለንባብ እንዲያመች አንድ ፊደል መዋጡን ታመልካታለች – ከትህትና ጋር።
ለቅሶ የሚያበቃበት ቀን ናፈቀኝ!
እግዚአብሄር ህዝባችንና ልዕልት ኢትዮጵያን ይጠበቅ። አሜን!
እግዚአብሄር ይስጥልኝ።