Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

የጎንደር መንፈስ ይጠራል (ክፍል –አራት) ከሥርጉተ ሥላሴ

$
0
0

ጎንር ክፍል – አራት
የጎንደር መንፈስ ይጠራል።
ከሥርጉተ ሥላሴ 05.06.2014 (ሲዊዘርላንድ – ዙሪክ)

Gondor„የበለጠና የከበደ ኃላፊነት እንደሚጠብቀኝ ባውቅም ለእኔ የከበደኝ ግን ከጎንደር ህዝብ መለዬቴ ነው“ጓድ አበበ በዳዳየጎንደር ክ/ ኢሠፓ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ጉዳይ ኃላፊ ለጂንካ የክ/ ኢሠፓ አንደኛ ጸሐፊ ሆነው ሲሄዱ መሸኛቸው ላይ የተናገሩት ነበር። የጎንደር አቀራረብና የአያያዝ ሙያው ከውስጥና በመሆን ሰንደቅ የከበረ ነው። ጎንደር ኖሮ መለዬት ትዝታዎቹ በቀላሉ ሊፋቁ የማይችሉ፤ እንዲያውም ትውስታዎች እያመረባቸውና ወዘናቸው እዬፈካ በናፍቆት አሳምረው የሚያሹ፤ በራሳቸው ጊዜ በመንፈስ ቤተኛ መሆን የሚችሉ፤ ተመክሮን ያስመቹና ያሰበሉ የመልካምነት ማሳ ናቸው።

የማከብራችሁና የምናፍቅቻሁ የሀገሬ ልጆች ጹሑፉ ተከታታይ ይሆን ዘንድ ክፍል ሦስት ማጠቃለያው እንዲህ ይል ነበር።  — ሌላው ቀርቶ የታሪካችን አካል የሆነው የግራኝ መሐመድ እረፍት እኮ ጎንደር ነበር። ደንቢያ ላይ የግራኝ በር ይባላል። በነገራችን ላይ በዛ ዘመን የትግራዩ እንደርታና የጎንደሩ ደንቢያ በከንቲባ የሚተዳደሩ ዕውቅና የነበራቸው ከተሞች ነበሩ። ዛሬ ግን የእንደርታን ባላውቅም፤ አይደለም ደንቢያ ጎንደር አንዲት መንደር ናት በጨለማው ዘመነ በወያኔ – የታሪክ ረግረግ። ታሪክ ማለት እንደ ሥርጉተ ዕይታ – የህዝብ ወላዊ አዎንታዊና አሉታዊ አምክኖዊ፣ ክስተታዊ ክንውኖች ዕደሜ ጠገብ ሲሆኑ ታሪክ ይባላል። ይህን መክፈል ወይንም እንደ ዶሮ መበለት አይቻልም። ታሪክ ከአንገት በላይና በታች፤ ወይንም ሲሶና እርቦ ተብሎ ሊከፈል ከቶውንም አይችልም። አሉታዊም ሆነ አዎንታዊው ክንውኖች ለታሪክ ወጥ ገፀ – ባህሪው ወይንም ሙሉ ቁመናና መልኩ ነው፤ ታሪክ የትርጉም ሥራ አይደለምና።

ጎንደር ክፍል አራት ማጠቃለያ።

እንደ መግቢያ በር —- ድርጊት በድርጊት ላይ እዬተባ ውጤት ላይ ሲውል በዚያ ስሜት ውስጥ እራስን ማዬትና መመዘን የተገባ ነው። ሃሳብን አዞ ሃቅን በምልሰት በማሰማራት ለህሊና ችሎት ማብቃት የተገባ ትውልዳዊ ድርሻ ይመስለኛል። አንድ የጥበብ ሰው ገጠመኞቹን ገልቦ ወይንም ጨልፎ አላዬሁም አልሰማሁም ማለት አይችልም። ይህን ካደረገ እሱ በመኖር ውስጥ እዬኖረ ሳይሆን መኖር እሱን እዬኖረበት ነው ማለት ነው። ይህ ማለት ደግሞ ክስተታዊ ሁነቶች የታላቁን ሰብዕና ጸጋ እንዲጋፉ ፈቅዷል ማለት ይሆናል። ህም! እራስን ይግባኝ አልባ መደፍጠጥ። በተለይም የጥበብ ቤተኛ የማህበረሰቡን ህይወት እንደዋዛ ሳይሆን በጥንቃቄ ያሰተውለው ዘንድ የከያኒነት ገመናው ግድ እንደሚለው አውቆ፤ የህይወቱን ልምድ ለማበልጸግ፤ ያለውንም ለማካፈል መትጋት ከጥበብ ፍቅሩ ተግባር የመጀመሪያው ሊያደርገው ይገባል። አንድ ጸሐፊ ዛሬን ተሻግሮ ትናትንም መኖር አለበት፤ ትናንት የኖረበት ማህበራዊ እውነት ውበት ነውና። ውበት ያለ እውነት፤ እውነት ያለ ውበት አይኖርም። ውበትን ካለ እውነት እውነትን ካለ ውበት ማሰብ የቃር አቸቶ ነው እልለሁ – እኔው።

የጎንደር መንፈስ አሳምሮ ይጠራል።

„ ቡልጋ በሚባለው አገር ይቀመጡ የነበሩ ህዝቦች በ484 ዓ.ም ጥር 11 ቀን በአለ ጥምቀትን ለማክበር ተሰብስበው የነበሩ ሰዎች ካህናቱ በማኃሌት፤ ጨዋው በዘፈን ሲወዛወዙ ሰዐተ ቅዳሴው አለፈባቸው። በዚህ ጊዜ አንድ ባህታዊ ድንገት ደርሶ ቅዳሴውን ከእግዚአብሄር የታዘዙ ግሁሳን ቀድሰውታል በናንተ ግን ማት ታዞባችኋልና መዳኃኒተ ነፍሳችሁን ፈልጉ ብሎ ስለነገራቸው፤ ምን ብናደርግ ይምረን ይሆን  ብለው ጠዬቁት። እሱም እዬሩሳሌም ሄዳችሁ የጌታችን መቃብር ብትሰሙ ይቅር ይላችኋል አላቸው። እነሱም ወደ ቤታቸው ሳይመለሱ ታቦታቸውን እንደያዙ ለቅን አሳብ ወደ እዬሩሳሌም ለመሄድ ጉዞዋቸውን ቀጥለው ሲሄዱ የእነሱን መሄድ የሰሙ ባጠገባቸው ያሉት ህዝቦች ሁሉ ተከተሏቸው ። “  ዬእግዚአብሄር መንፈስ መንገዱን እንዴት ቀዬሰላቸው? „ መንገዳቸው በቀጥታ ወደ ስሜን የነበረውን ትቶ ወደ ስሜን እዬመራ ጎንደር አድርጎ ስቋር አደረሳቸው። በዓፄ አላሜዳ ቀዳሜ መንግሥት በ485 ዓ.ም መጋቢት 27 ቀን አብርንታት ደረሱ። ከአማራ ሳይንት ጀምሮ ያለፉባቸውን ቦታዎች ሁሉ ሥም እዬሠጡ ነበር የተጓዙት።“  (ገጽ 38 – 39)*  „ እነዚህ አቨው ሥርዓተ ገዳሙን ጠብቀው 278 ዘመን ከቆዩ በኋላ በ852 ዓ.ም ጉዲት በሰይፍ አስፈጃጃቸውና የጉዲት ዘመነ መንግሥት አልፎ አንበሳ ውደም እስኪነግሥ ድረስ በስውር ካሉት ግሑሳን በቀር በቦታው በግልጽ የሚታዩ መነኮሳት አልነበሩም። እግዚአብሄር በቸርነቱ ብዛት የጉዲትን ዘመነ መንግሥት አሳልፎ አንበሳ ውደምን በአባቱ ዙፋን ባስቀመጠው ጊዜ በ891 ዓ.ም ከሽዋ400መናኞች መጥተው ተሰውረው ከቆዩት ከፊተኞች አቨው ምንኩስናን ተቀብለው ተቀመጡ። እነዚህ 400 መናኞች ገዳሙን አጽንተው የመጣውን እያመነኮሱ እነሱ ሲያልፉ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻቸውን እዬተተኩ 389 ዓመት ያለሁከት በሰላም ከኖሩ በኋላ በ1277 ዓ.ም በዐፄ አግባ ጽዮን ዘመነ መንግሥት ገዳሙ ጠፋ። 40 ዘመን ጠፍ ሆኖ ከቆዬ በኋላ በ1319 ዓ.ም በአንደኛው አምደ ጽዮን ዘመነ መንግሥት ሳሙኤል ዘዋልድባ ወይም ዘገዳመ ዋሊ የተባሉት አቡነ ሳሙኤል መጥተው ገብተው ጠፍቶ የነበረውን ገዳም አቋቁመው 70 ዓምት በገዳሙ ቆይተው በ1389 ዓ.ም በዚሁ ገዳም አረፉ።“ (ገጽ 43)* የማክበርችሁ መግቢያው ላይ በርካታ ዝርዝር ታሪኮችን ዘልያለሁ። እንዳይበዛባችሁ በማሰብ፤ የተወሰነውን ከፊል ክፍል በቀደመው የጸጋዬ ራዲዮ በ2013 አርኬቡ ላይ ትረካው ስላለ ወደ ኋላ ሄዳችሁ የ2013ን በቅደም ተከተል ታገኙታላችሁ። ዋናውመሰረታዊ ሃሳብ ግን ጎንደር ወገኖቹን እቅፍ ድግፍ አድርጎ፤ ጸጋቸውን አክብሮ፤ አባትነታቸውን ከልብ ተቀብሎ፤ ቤተክርስትያን በስማቸው አስቀርፆ ገዳምትን በስማቸው ሰይሞ መኖር ተፈጥሮው ብቻም ሳይሆን የኖረበት መክሊቱ ስለመሆኑ ለማጠዬቅ ነው።

ከገዳመ ዋልድባ ሳልወጣ ማህበረ ምእመናን መጋቢት 27 ማዬ ዮርዳኖስ በዓል ለማክበር ከዬትም የሀገራችን ክፍል ሲመጡ፤ በተጨማሪም ቀብራቸው ከዛ ቅዱስ ቦታ እንዲሆን የወሰኑ ወገኖች እሬሳ ይዘው ሲያልፉ የሚደረገውን ተልምዶዊ ባህል ሊቁ ጸሐፊ አቶ በሪሁን ከበደ እንዲህ ገልጸውታል። „ አባቴ ግራዝማች አስናቀው አበራ ይኖሩ የነበረው ወደ ገዳሙ በሚወስደው መንገድ ዳር ምዝክር አቦ ከተባለው ቦታ ላይ ስለሆነ 3ጋን ጠላ 3 እንቅብ ቆሎ ተዘጋጅቶ ማንም ሰው አስከሬን ይዞ ለቀብር ወደ ገዳሙ ሲያልፍ ይቀርብለታል። እንዲህ የሚደረገው በሳምንት አንድ ቀን ወይንም በወር ሁለት ቀን ሳይሆን ለምሳሌ በ30 ቀን 30 ሬሳ ወደ ገዳሙ ቢያልፍ ለ30ው ቀን ሁሉ የተደገስው ድግስ ያለማቆራጥ ይቀርባል። በዚህ መልክ 25 አምት አገልግለዋል። ምስክሩም ገዳሙና የጠለምት ህዝብ ነው። አባቴ ሲያልፉም ወንድሜ በቦታው ተከትክቶ ተግቶ ይከውናል“ (ገጽ 98 – 99)* ከገዳሙ በእጅ የተጻፈላቸው የምስጋና ደብዳቤም መጸሐፉ ውስጥ ተያይዟል። ለክብረ በዐል የሚመጣውም በሚደርስበት ቦታ ሁሉ ማህበረሰቡ እዬተነጠፈ እዬተጎዘጎዘ ፍቅር በሩን ከፍቶ ይጠብቀዋል።

ክብረቶቼ – ጎንደር እኮ ጥሩ ሰው፣ መልካም ሥነ – ምግባር ያለው እኮ ታጭቶ ነው የሚገባው። ሊቃናት ልቅናቸውን በሚያገኙበት የቅኔ የንባብ የእድምታ የሚስጥራት አብነት ት/ ቤቶች የቆሎ ተማሪዎች ውስጥ አራት ዓይናማዎችን ጎንደር ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ዝም ብሎ አይሸኛቸውም። ሞኝ አይደለም። መምህሩ ሴት የደረሰች ካላቸው የራሳቸውን፣ በስተቀር የቅርብ ዘመድ ተፈልጎ ይህም ሳይሳካ ቢቀር ከሀገሬው ቆንጆ ልጅ ተምርጣ፤ ያ ሙሑር በጋብቻ ታስሮ እንዲቀር ይደረጋል። ይህ ለጎንደር ክህሎቱ ነው – ልዩ ሥጦታው። ታናሼ ተክሌሻ በ2010 በሁለት ክፍል የጻፈው ነበር። ጹሑፉን ሳነብ እስቅበት ነበር …. ምክንያቱም ልጥፍ ግምት ስለነበረ። ሊቃውንት አያቶቼ ቁጭ አድርገው የቆሎ ተማሪነት ጊዜያቸውን እንደ ትልቅ ይነግሩኝ ነበር። ሰፊ ቤተሰብ ውስጥ ለእኔ የተለዬ አያያዝ ነበረኝ። አባቴ እራሱ ሲያሳድገኝ አሳ ዘይት እያጠጣ ነበር። አሁን እኔ ሙሉ ዕድሜ ላይ ነኝ – ምን ያህል የቀደመ ህዝብ ነው – እሰቡት።

ጎንደርና አብነቱ – በጥቂቱ፡

በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት በኢትዮጵያ ሠራዊት ላይ የደረሰው ግፍና መከራ ከቦታው የነበሩ ወገኖች አሉበት። እኔ መግለጽ የምፈልገው ባለቤት ያልነበረው፤ ከእሳት ወጥቶ ቋያ ውስጥ ዬተርመጠመጠው ዬኢትዮጵያ ሠራዊት ሲበተን በለስ በቀናው አኳኋን ተጉዟል። ወደ ጎንደር አቅጣጫ የተጓዙት ወገኖች በምን ሁኔታ ማህበረሰቡ ተቀበላቸው የሚለውን ተከድኖ የተቀመጠ የድርጊት ልዩ ጸጋ መተንፈሻ እስኪ ይሠራለት በማለት ነው።

የሠራዊታችን አባላት ከጎንደር ደንበር ከገቡበት ጊዜ ጀምሮ ህዝቡ በተለዬ ሲቃ በክብር ነበር የተቀበላቸው። አብሶ ወደ ጎንደር ከተማ እዬቀረቡ ሲመጡ የጎንደር ከተማ ህዝብ ከ20 እስከ 30 ኪ.ሜ  እስከ ኮሶዬ ድረስ ተጉዞ ነበር ድንኳን እዬጣለ የእንኳን ደህና መጣችሁ አቀባበል ያደረገላቸው። ሁላችሁም እንደምታውቁት በርሃ – ለበርሃ ለረጅም ጊዜ ካለቅያሬ ልብስ ሲከላተም የቆዬ ወገን በምን ሁኔታ ላይ እንደሚሆን እሰቡት። በመንፈሱ የመሸነፍ – ድቀቱ፤ እልሁ፤  የመስዋዕትነቱ ዋጋ አልባነት፤ የትዳሩ – የቤቱ – የጎጆው – የወጣትነቱ መስዋዕትነትና አዝመራው – ከንቱነት፤ መግቢያ ቤቱም የሚጠብቀው የተቆለፈ የቋሳ ክምችት ሁለመናው ውልቅልቅ ያደረገው የተጎሳቆለ አካል ነበር።

በዚያ የመከራ፤ በዚያ የፈተና ጊዜ ግን የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች ወገኖቻቸው በመደገፍ፤ በሙሉ አለንላችሁ በማለት፤ መንፈስን በማጽናናት ነበር የተቀበሏቸው። እያንዳንዱ ነዋሪ በነፍስ ወከፍ እስከ 10 የሠራዊቱ አባላት ነበር እየተቀበለ ያሰነበተ። ኑሮው እራሱ ምስቅልቅል ባላበት፤ የራስን ቤተሰብ ለማስተዳደር በተበተነ ሃሳብ በሚባዘንብት፤ ሰላሙ ባልተረጋጋበት ሁኔታ በርሃ የከረመን ጎስቋላ እንግዳን ችሎ ማስተናገድ ከፈተና በላይ ውሃ ያዘለ ተራራ የመሸከም ያህል ነበር። ነገር ግን ጎንደር ተወጣው። ከእኔ ከወላጅ እናቴ ቤት አባትዬው በአባት ጦር፤ ልጅዬው በመደበኛ የሄዱ አባትና ልጁ በተለያዬ አቅጣጫ ተጉዘው እዛው ከእናቴ ቤት ተገናኙ። የልጁ እናት፣ የአባወራው ባለቤት ከአዋሳ ድረስ መጥተው ቤተሰቡን ተዋውቀው መልካም ቀጣይ ግንኙነትም መስርተው በፍቅር ተሰነባብተዋል። ይህ ዘመኑና ታሪክ የፈጠረውን ወላዊነት ኢትዮጵያዊነትን አብዝቶ ያዘመረ የተባ የተግባር ዓዕምድ ዓውድም ነው – እንዳሻው እዬተደፈጠጠ የሚደመጠው።

እንግዳ መጥቶ ወደ ቤቱ ለመሄድ ሲነሳ ጎንደር ላይ አስተናጋጆች በሙሉ ሊሸኙት አብረው ይወጣሉ። ከሊቅ አስከ ደቂቅ፤ ሲወጡ ቤታቸውን ከፍተው ነው። አንዳንድ ጊዜ እንግዳውን ከቤቱ አድርሶ መመለስ አለ። ለዚህም ነው „ሲሻኛኙ አደሩ“ የሚል ብሂል የኖረው። ከተማ ላይ አስፓልቱ ሞልቶ ለአንድ እንግዳ መላ ቤተሰቡ ወጥቶ ይሸኛል። ገጠር ላይ ወንዝ አሻግሮ ነው የሚመለሰው እንግዳ አሰንባቹ። ከእንግዳ ጋር ለመለዬት በጊዜያዊነት እንኳን ፍቅሩ ማህተም ነው። ከዚህ ጋር አንድ በኽረ ጉዳይ ላንሳ። ሻብያና ወያኔ ኢትዮጵያን የማፍረስ የጫጉላ ጊዜያቸውን ዕርገት የተከወነው ኤርትራውያኑን ንብረት አልባ በመመለስ ነበር። ሁሉንም መከራ የኢትዮጵያ ህዝብ በትዝብት አይቶ ቀን ሲሾልክ ግን፤ ንብረታቸውን ተረክቦ በተገኘው መገናኛ ሁሉ እዬሸጠ እዬላከላቸው ነው። ጎንደር ያኖሩበት የሚገኝበት፤ በማተቡብም የጠና ነው የሚባለውም እንዲህ መሰል ፈተና ሲገጥም ግራ ቀኙን አስቀምጦ ፈርኃ እግዚአብሄር ያለው ተግባር ስለሚከውን ነው። ወገኖቼ ተረት ተረት አይደለም የምናግራችሁ የሆነውና የተደረገውን ነው። ቂም ዕዳ ነው – እዳነቱ ደግሞ የነፍስ ነው ብሎ ማህበረሰቡ በጽኑ ያምናል። አሁን ወያኔ ይህን ያህል ቀጥቅጦ እዬገዛ ነው። ቢሰናበትም ጎንደር እንደ ተፍጥሮው ይቀጥላል። አብሮ መብላትና መጠጣት፤ አብሮ መኖርና ሃዘን ተፍሥኃውን መጋራት ሃይማኖት ነው ብሎ ያምናል – ጎንደር።

የጎንደር ያልመከነ መከራው – በጥቂቱ።

እኔ የማውቃቸውን ጥቂት ነገር ልብል። ትግራይን ብቻ አይደለም የደርግ መንግሥት ዬለቀቀው። ሰቲት ሁመራንና አብደራፊንም ጭምር ነበር። ሲለቀቅ የፓርቲው አካላትም አብረው ከህዝቡ ጋር እንዲለቁ ነበር የተወሰነው። ለእነሱ ለብቻ መጓጓዣ አልተላከም ነበር። የሰቲት ወረዳ ኢሠፓ የሥ/አ/ኮሜቴ አባል የሆነ ወጣት አንድ ጹሑፍ ስለ ጉዞው ጽፎ ነበር። ንዑስ እርእሱ „የጎተተኝ“ ይል ነበር። „አንዲት አራስ አብራን ትጎዝ ነበር። አቅም አንሷት ስለነበር ወደ ኋላ ነበረች። ውሃ ጥማቱ መካራ ስለነበር አራስ ልጇን ከግራር ሥር አድርጋ ውሃ ልትጠጣ ሄደች። ስትመልስ አራስ ልጇ አልነበረም። በጣም ስትጮኽ ወደ ኋላ ተመልሰን አገኘናት። የሆነውን ነገረችን። ያለን ምርጫ ወደ ፊት መሄድ ስለነበርን አብራን እንድትመጣ ነገርናት። በርሃ ነው የሚያቃጥል – ቋያ። እሷ ግን አሻም አለች። ልጄን ትቼ አልሄድም አለችን። አራሱ ህፃን የለም አንቺ ከእኛ ጋር ነይ ብለን በዛለ አቅማችን ለመናት። ግን አልቻለችም። አስገድደን ተሸክመን ለመጓዝ እሷን፣ እኛም አቅማችን እዬሟሸሸ ነበር – አልቻልነም። ትናነት መጣን፤ እኔ ብመጣም ግን ወደ ኋላ የሚጎተኝኝን ትቼ ነው። ዓይኗ መከራውን አያይም ነበር። ልጇን ፍለጋ ይማስን ነበር እንጂ። ምንግዜም ጸጸቴ ነው“ ይል ነበር ጸሐፊው። ይህ መከራ በወሎም እንደተፈጸመ አስባለሁ። አሁን የሚያስፈልጉን መሪዎች ይህን የመከራ ጊዜ መርምረው የሚችሉትን ለማድረግ ሰብአዊነት የሚመራቸውን ነው። መንግሥት ህዝብን ከቦታ ሲያስለቅቅ የሚደርሰው ሰቀቀን መከራ በቃላት መንዝሮ ለመግለጽ አይቻለም። ተርፈው የመጡትስ? ይህም ሌላ ጥያቄ ነው።

በተፋፋመ ውጊያ ላይ እያለን ጎንደር የነበሩ የሠራዊቱ ማዕከሎች ተነቅለው ወደ ሌላ ቦታ እንዲዛወሩ ተደረገ። የጨለማ – ደባ ነበር። የነበረው ምርጫ በሀገሬው ሃይልን አጠናክሮ መቀጠል ነበር። እርግጥ ሠራዊት ከማዕከል ለማምጣት አንድ እድል ነበር፤ ዳኮታ የሚያሰርፍ ቦታ ማዘጋጀት። ለዛ ደግሞ አዬር ማረፊያውው አይችልም ነበር። ስለዚህ ነዋሪው ጊዜያዊ መጠለያ ተሰርቶለት በፍጥነት የዳኮታ ማረፊያ ማሰራት ነበር። ነዋሪው በድንገት አፈር ለብሶ በዘመቻ በሚሠራለት ጊዜያዊ መጠለያ መጠለል ግድ ሆነ። ፈቃድም – ንግግር የለም። ከዛው እዬታደረ ያለ የሌለው ሃይል ሁሉ ተሰማራ ለድርብ ግዳጅ። ዳኮታ የሚያሳርፍ ጊዜያዊ አውሮፕላን ማረፊያ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተሰናዳ። እኔ የአንድ ኮሜቴ ሰብሳቢ ነበርኩኝ። አንድ እድል ብቻ ነበር። ምን እንደተላከ ታውቃላችሁ። ዳኮታው እንደተነሳ የራዲዮ መልእክቱ ስንቅ እንደተላከ ነበር መርዶው። ስንቁን እኮ የጎንደር ህዝብ ያቀርብ ነበር። የተፈለገው ሠራዊት ነበር። ብቻችን ነበርን። ደንቀዝ ላይ የሚለቀቀው የጠላት ከባድ መሳሪያ በቀጥታ አውሮፕላን ማረፊያውን ዒላማ ያደረገ ነበር። ከዚያ በኋላ ዳኮታውን ማሳረፍ አልተቻለም።

ያ ንጹህ የአዬር ማረፊያ ኗሪ የጦርነት ጊዜ ስለነበረ ካለ ካሳ ህፃነት – ሽማግሌ – የታመመ – በቃሬዛ፤  ነፍሰጡር ሁሉም ቤታቸው ፈርሶ ሜዳ ላይ እያሉ ወያኔ ገባ። ….. ባለቤት የሌለው ህዝብ በቀን ወደ 20 ቆርቆሮ ማልበስና የመጀመሪያ ምርጊቱን ማጠናቀቅ ነበር ዘመቻው፤ ባዶ ግድግዳ እንደቆመ፤ ወይንም ቆርቆሮ ሳይለብስ በቃ እንደተበተነ ሁሉም ተበተነ። ያ መከረኛ ህዝብ በግራ በቀኝ ተማገደ። በደልጊ በደንቢያ ዞን ክፍት ነፃ መሬት ነበር። የተንጣለለ ቦታም ነበር – አዬር ወለድ ለማምጣት እሱንም ቁብ የሰጠው የበላይ አካል አልነበረም። ለዛውም በደንቢያ በኩል የማልናገረው የተሻለ ሁኔታ ነበር …. አልሆነም። በኢዲዩም፤ በኢህአፓም፤ በደርግም፤ በወያኔም ዛሬም በአርበኛ ያው ቦታው በጦርነት ቀጠናነት ይማገዳል። ከዚህ ሌላ ወያኔ መሽጓል የሚል የተሳሳተ መረጃ እዬተሰጠ ያለቀ መንደር እናቱ ትቁጠረው ….. መናገር የቻለ ሁሉ ደግሞ እስካሰኘው ድረስ ይወቃዋል።

በጦርነቱ ጊዜ በሰማይ የመንግሥት በምድር የወያኔ መሳሪያ ከጫፍ አስከ ጫፍ ገበሬ – መንደር – እርሻ – የተፈጥሮ ሃብት – ነደደ – ተቃጠለ – ተርመጠመጠ። የሰውን ልጅን እራስ ውሻ …. እም ነው! ይህንን የገዘፈ መከራ ይፍታኃ ዬሚል  ቅዱስ መንፈስ መፍጠር የትግሉ መሰረታዊ መንገድ ይመስለኛል።

እንቡጢጣ -ማከያ ። ሻ/ ገብረህይወት የሚባሉ የደርግ አባል ነበሩ። የስሜን አውራጃ አስተዳደሪ ነበሩ። ከመንግሥት መዋቅር ህግና ደንብ ውጪ አስተዳደሪ ያላቸው አውራጃዎች የበላይ ሆነው እንዲያሰተዳድሩ በተሾሙበት ጊዜ፤ ጌታ አልነበራቸውም። ለአሰሳ ሲወጡ ጥቃት የሚሰነዘርበት ኢህአፓ ብቻ ነበር። ለወያኔ ግን አልጋ ባልጋ ነበር። ሹመታቸው ለስሜን – ለጭልጋና – ለወገራ አውራጃዎች ነበር። የሦስቱም አውራጃ ገበሬዎች ሰፊ ቅጣት ነበራቸው። እኔ የማውቀውን ልናገር። ባለፈው ጊዜ ጋዜጠኛ አብርኃም ደስታ ጮንጮቅ ላይ ወያኔ ያደረስውን መከራ ዘግቦ ነበር። እጅግ አመሰግነዋለሁ። ጮንጮቅ በጭልጋ አውራጃ የሚገኝ የምክትል ወረዳ ዋና የገጠር ትንሽዬ ከተማ ናት። 5 ቆርቆሮ ቤቶችና ሌሎች ግን በርካታ ጎጆ ቤቶች ነበሯት። በእግር ከጭልጋ ከተማ 4 ሰዓት ለኮበሌ ነው።  ከዛ የመጡ ገበሬዎች ልጆቻቸውን ይዘው አንድ ቀን እንዲህ አሉኝ „ እሙሃይ ነበር የሚሉኝ፤ እሙኃይ ሁሉን ለገብርህይወት ሰጠን አሁን ሁሉንም ጨረስን፤ የቀሩን ልጆቻችን ነውና ተምኖ ይውሰዳቸው“ አዎን በዬገብያው የሴት ቀሚስ እዬለበሰ የሚንጠለጠለው እጅግ በርካታ ገበሬ ነበር። ሦስት ጓደኞሞች ዘመቻ ጀመርን። አልቻልነም ይህን ተሸክሞ መኖር። ዘመቻችን ጭልጋ አውራጃ ሰላማዊ አስተዳደሪ ስላለው በእራሱ አስተዳደር ይመራ ነበር ፍሬ ነገሩ። ሻ/ ገብረሕይወት ይነሳ ነበር ጉልበታሙ አድማ።

በዛው ሰሞን ሻ/ ገብረህይወት የጭልጋን ህዝባዊ ድርጅቶች ቢሮ ገንዘብ ልመና ወጣቶችን ሰብስቦ ወደ ጎነድር ይዘውን ሄዱ። ቋራ ከሚባል የመንግሥት ሆቴል „ምግቡ በቅደም ተከተል ይቀርብ ነበር“ ለእኔ የቀረበውን አልበላሁም። የወጣልኝ ደፋር ነበርኩ። ብይ ስባል ደም አልበላም አልኩኝ። በህይወት ያሉት ይመሰክራሉ። በጥርስ የገባሁበት ቀንም ነበር። በቃ እኔ ብቻ ነበርኩኝ ያልበላሁት። ደግሞም ልክ ነበርኩ ጽዕዱ መሆን የልብ ያደርሳል – እንደ ልብም እንዲህ ያናግራል። አንዱ የሰከነው ጓዴ በህይወት የለም ኬኒያ ላይ አልፏል። ጓድ ዬኋንስ የኋላ ይባል ነበር። እንዳንታፈን ሻ/ ገብረህይወት ከመምጣታቸው በፊት መረጃ ለሦስታችንም ይሰጠን ነበር። ወጥተን እንድናድር፤ በኋላ ብልሁ ጓድ ገ/መድህን በርጋ የድርጅት ጉዳይ ኃላፊና ጓድ ወንደወስን ኃይሉ የርዕዮተ ዓለም ጉዳይ ኃላፊ የወቅቱ የፓርቲው አደራጆች ሁለታችን የካቲት 66 ፓለቲካ ኢንስትቲዩት አንዱን ጀርመን ሀገር ላኩት። ከትምህርት በኋላ ወደ ጎንደር እንዳልመለስም የተደረገው ምክንያትም በዚህ ነበር። ጥሩ እድል ነበር አርሲን ዬመሰለ ሀገር፤ ያን ፍቅር የሆነ የጢቾ አውራጃ ህዝብ ጋር እንድሰራ አጋጣሚ አገኘሁ። በተጨማሪም ጓድ ስለሺ መንገሻን የመሰለ ለስላሳ – ሥልጡን – ፈጣን የአርሲ ክ/ ኢሠፓ ኮሜቴ ተጠሪ ለማዬት በቃሁ። በእውነት የተለዩ ነበር። እሳቸውን የሚያጅብ አንድም ስፔሻል የሚባል አልነበረም። እንዲያውም ተንጠልጥለው „አንተ“ ነበር የሚባሉት።  ጠባቂያቸው ህዝቡ ነበር። እሳቸውም ወጣት ነበሩ። ከወጣቶች ጋር ኳስ የሚጫወቱ፣ ሙዚቃ መኪና ውስጥ የሚያዜሙ ነበሩ። ልጅ ስለነበርኩ ናፍቆቱን ስላልቻልኩ ብቻ በለቅሶ በሃዘን በዬቦታው ልዩ ዝግጅት ተደርጎልኝ ተሸልሜ ወደ ጎንደር ተመልስኩኝ። ዕድለኛ ወጣት ነበርኩኝ። ሁሉም የሚሳሳልኝ።

እንዲህ ሆነላችሁ — ሻ/ ገብረህይወትም  ከሰቲት ሁመራ ወደ ጎንደር በጦር ኤሊኮፍተር ሲበሩ ሰማይ ላይ አመድ ሆኑ – በሁለት ቢላዋ እንደበሉ ነደዱ። ሬሳቸው እራሱ አልተገኘም። የጭልጋ፤ የወገራ፤ የስሜን አውርጃ ህዝብ አረፈ – ተገላገለ ከሃሞራቢ የቋሳ ሽምቅ ቅጣት – ተመስገን! ምንም እንኳን ዛሬም መከራው ተግ ባይልም።

እርገት ይሁን። ግለሰብ ጥፋት ወንጀል ሊፈጽም ይችላል። አጥፊውን ነጥሎ መውቀስ መንቀስ ይቻላል። የአካባቢው ህዝብና የአለም ውርስና ቅርሶች ያሉበትን የታሪክ ማህደርን ግን ግፍ ነው። ትውፊቱ ህዝቡ ቅርሱ የመንፈስ ጥበቃ ሊደረግላቸው ይገባል። ጎንደር በዚህ ዘመን እልፈቴ ነበር ብሎ የሚናገረው የሰላም ጊዜ ታሪክ የለውም። ይህም ሆኖ ባህሉን፤ ልማዱን፤ ወጉን፣ ትውፊቱን፤ ታሪኩን፤ እምነቱን ጠብቆ የኖረ ህዝብ ነው። „በሚስትና በሀገር ቀልድ የለም“ እዬተባለ ያደገ ስለሆነ ትንፋሹ ድፍረት፤ ትጥቁ ጽናት የሆነ። በማተቡ አዳሪ። ለቃሉ ተገዢ። አደራ አውጪ። ፍቅሩ ጽኑ የሆነ ህዝብ የመብቱ ዳር ድንበር ሊከበርለት እንደሚገባ በአጽህኖት እያሳሰብኩ ጹሑፌን እደምድማለሁ።

የእኔ ክብሮች ትእግስታችሁን ሳተሰስቱ ሸልማችሁ አብረን በአንድ መሰረታዊ ጉዳይ ዙሪያ ሰነበትን። እግዚአብሄር ያኑርልኝ። አምላኬ ይጠብቅልኝ። የ05.06.2014 የጸጋዬ ራዲዮ ፕሮግራሜ ዘና ያለ ናፍቆትን ብቻ ያጫወተ፤ የመግቢያ ትውውቁ – የዝግጅቱ ሆድ ዕቃ፤ ስንበቱን አክሎ በሥነ ግጥም ነበር። ትንሽ ግር እንዳይላችሁ እንደዚህም ዓይነት መንገዶችም መለመድ አለበት ነው ቁም ነገሩ። ኩምትርትር ያለ መንፈስ አስቲ በአመት አንዲት ሰዓት እንኳን የእርፍት ቀን ሊኖረው ይገባል ብሎ  የአብርኃሙ የጸጋዬ መሠሪያ የሥነ ግጥም ቀን ነበረው Tsegaye Radio Lora Aktuell Sendungen ብላችሁ ለጉግል ነፍሱ ስትነግሩት፤ ወይንም በቀጣዩ ሊንክ አምጣልን ብላችሁ ስታዙት ይዞ ከች ቀልጣፋው።  www.tsegaye.ethio.info ነገ ፓስት ያድርጉታል፤ ጊዜው ሲኖራችሁ ጎራ በሉ …. ደግሞ በቀጣዩ ለምለም ዝግኗን እንደትጠብቅ ….. ቸር ያገናኘን።

የቀደሙት ሊንኮች ….

ክፍል አንድ http://en.wikipedia.org/wiki/User:Aatebeje

ክፍል ሁለት http://www.zehabesha.com/amharic/archives/30526#respond

ጎንደር ክፍል ሦስት http://www.zehabesha.com/amharic/archives/30763

  • ኮከብ ያለባቸው አቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባ መጸሐፍ በሊቁ ጸሐፊ ከአቶ በሪሁን ከበደ የተወሰደ ሲሆን፤ መጸሐፉም ተሽጦም ገቢ የሆነው  ለአብረንታት ዋልድባ ገዳም ነው።
  • ዓ.ምህረቱ በግእዝ ስለሆነ ብዙ ነገር ስለረሳሁ ግድፈት ካለ ይቅርታ ዝቅ ብዬ ሎሌያችሁ እጠይቃለሁ።
  • ግሑሳን – በአይን ማይታዩ የተሰወሩ ግን ለአግልግሎት በቋሚነት የተሰማሩ ንዑዳን፤

 

ፈተናን አሸንፎ የተፈጠረ ሚስጥር ኢትዮጵያዊነት።

እግዚአብሄር ይስጥልኝ።

 


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>