እነዚህ ሁለት የወንጀል ታሪኮች የተፈፀሙበት ጊዜ ጥቂት ዓመታት ወደኋላ ይርቃል፡፡ ሁለቱም ወንጀሎች የተለያዩና የሚያገናኛቸው ነገር የሌለ ቢሆንም ማጠቃለያቸው ግን ሞት መሆኑ ያመሳስላቸዋል፡፡ በተለይ በተለይ የህይወት ህልፈቱ ሳይታሰብ እንደዘበት መፈጠሩ ‹የተቆረጠለት ቀን› የሚባለውን አይነት አሟሟት ያስታውሳል፡፡ ሁለት ነፍሶች በተለያየ ዓመት በተለያየ ሁኔታ በተለያዩ ቀናትና በተለያየ ምክንያት እንደዘበት አልፈዋል፡፡ ሳይታቀድና ሳይታሰብ ህይወታቸውን የተቀሙት ሰዎች መቃብር ውሎባቸው- ገዳዮቹም አስር ቤት አሽጓቸው ተረሳስተዋል፡፡
አንድ
ቀልድ የጠራው ሞት
ጥር ወር 1996 ዓ.ም
አዲስ አበባ
የየካ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 15 ነዋሪ ‹አንዳች እንከን የማይወጣለት ፍቅር ያላቸው ናቸው› ይላል፡፡ ለዓመታት በመቀራረብና በመተሳሰብ የዘለቁት ጓደኛሞች ፍቅራቸው ለብዙሃን ምሳሌ ሆኖም ኖሯል፡፡ በመካከላቸው ያለው የእምነት ልዩነት፤ የህይወት ፍልስፍና አለመገናኘት፤ የቤተሰብ ሁኔታ አንድ አለመሆንና ሌሎችም የጋራ ያልሆኑ መለያዎቻቸው ቢበዙም ከዚህ ሁሉ በላይ ገዝፎ የወጣ የጓደኝነት ፍቅራቸው ሁሉን አስረስቷቸው አንድ አድርጓቸዋል፡፡ እንደብዙዎቹ እምነት የጓደኝነት ሙሉ ትርጉም ስፍራ ይዞ የሚታየውና ጎልቶ የሚንፀባረቀው በእነዚህ ሰዎች ነው፡፡
ሁለቱ ወዳጆች አብረው የሚበሉ አብረው የሚጠጡ መሆናቸው ብቻ አይደለም ‹ጓደኛ› የሚለውን ስያሜ ያሰጣቸው፡፡ ሁለቱም ከመብላትና ከመጠጣት በላይ የህይወታቸውን ክፍተት የሚሞሉበትን ፍቅር መሰጣጣት የቻሉ ነበሩ፡፡ አንዱ ሲቸግረው ሌላው እየረዳው፤ አንዱ ሲጨንቀው ሌላው እያዋየው፤ አንዱ ደስ ሲለው ከሌላው እየተካፈለው ስሜታቸውን እየተጋሩት ኖረዋል፡፡ መወለድ ቋንቋ ነው እስከሚባል ድረስ ሁለቱ ወዳጆች አምሳልነታቸውን አንድ አድርገው ዘልቀዋል፡፡ ዓመታትን የተሻገሩትና የወዳጅነታቸውን ዘመን ትሩፋት የተቋደሱት በመካከላቸው ባለው ፍቅርና መቻቻል ነው፡፡ ለዚህም ይሆናል አንዱ ሌላውን ሲያስተዋውቅ ‹ጓደኛዬ ነው› የሚለው ቃል ብቻውን የሚወክልለት የማይመስለውም፡፡ ‹እንደወንድሜ የማየው ጓደኛዬ ነው› በሚል ቃል የወዳጅነታቸውን ልክ ሞቅ አድርጎ መግለፅን ነው የሚያዘወትሩት፡፡
ብዙዎች የእነዚህን ወዳጅነትና ፍቅር ይቀኑበት ነበርና የአብሮነታቸው ‹ሳይንስ› ለማወቅ ይጥሩ ነበር፡፡ ከሁለቱም ጋር የቅርብ እውቂያ የነበረው ወጣት እንደገለፀው ጓደኛሞቹን አንድ ያደረጋቸው ነገር ሁለቱም ቀልድና ጨዋታ መውደዳቸው ነው፡፡ ‹‹መጫወትና መቀለድ ይወዳሉ፡፡ እንደ ህፃን ልጅ ይላፋሉ፡፡ ይደባደባሉ፡፡ ሰዎች እስከሚገርማቸው ድረስ አይለያዩም፡፡ እንደውም አንዱ ሌላውን ካጣው ‹ሳላይህ ስውል ትናፍቀኛለህ› የሚባባሉ ወጣቶች ናቸው፡፡ ይህ ቅርርባቸው አንዱ ሌላውን እንደራሱ አድርጎ እስኪያውቀው ድረስ ልብ ለልብ ያጣመራቸውን ሁኔታ ፈጥሮም ነበር፡፡
አልፎ አልፎ ቢጋጩም ፀባያቸው ብዙም አይከርርም ነው የሚሉት የሚያውቋቸው፡፡ አንድ ሰው ‹‹ሁለቱም ለሳቅና ለጨዋታ ቅርብ የመሆናቸውን ያህል ለኩርፊያም ያንኑ ያህል ናቸው፡፡ ነገር ግን ኩርፊያቸው ራሱ የቀልድ ስለሆነ የሚያመር የለም፡፡ ለምን አኮረፍከኝ ብሎ መጠያየቅም የለም፡፡ ራሳቸው ማንም ሳይመጣ ይቀራረቡና መኮራረፋቸውን እንኳን ይረሱታል፡፡ ኩርፊያ ሲባል ታዲያ ከሰዓታት ያልዘለለው ዓይነት እንጂ ቀናት የሚፈጀው አይደለም›› ብለዋል፡፡
ጥር 23 ቀን 1996 ዓ.ም
ቀን ላይ ሁለቱም ከየዋሉበት መጥተው ተገናኙ፡፡ የዋሉበትም እዚያው ቀበሌ 15 ክልል ‹‹ኬር ኢትዮጵያ እርዳታ ድርጅት›› አካባቢ ነው፡፡ በተለመደው ፍቅርና ሰው ባወቀው የወዳጅነት ውሏቸው ነው ዛሬም የቀጠሉት፡፡ የሚያወቋቸው ሰዎች በሁለቱም ላይ ያነበቡት የተለየ ገፅታ የለም፡፡ የተለመደው ሳቅ- የተለመደው ጨዋታ- የተለመደው ልፊያ- የተለመደው መጎነታተል ዛሬም አለ፡፡ ያያቸው ማንነታቸውን እንኳ ከማወቁ በፊት የአብሮነታቸውን ፍቅር ከፊታቸው የሚቀዳባቸው ሁለቱ ጓደኛሞች ዛሬን እስከ ከቀኑ 10፡00 ሰዓት ያሳለፉት ከዚህ ባልተለየ ሁኔታ ነው፡፡ በመጨረሻ ላይ ግን አንድ ቃል ከሁለቱ ፍቅር መሀል ጥለቅ አለች፡፡ ‹‹ሸፋፋ›› የምትል ቃል፡፡
ተናጋሪው የዘወትሩ ንግግሩን ውጤት የጠበቀ ከፈገግታና ከሳቅ ጋር የሚመላለስ ምላሽ ውስጥ ነው፡፡ አንደኛው እግሩ በመጠኑ ዘወር ያለ መሆኑን አይቶ ነው ሌላውን ሸፋፋ ብሎ የሰደበው፡፡ በእርግጥ ከዚህ ቀደም ይህንን ቃል ተጠቅሞበት አያውቅም ነበር፡፡ ተሰዳቢው ‹ሸፋፋ› የሚለውን የቀልድ ስድብ ሲያደምጥ ውስጡ አንዳች ቁጣ የተተራመሰ መሰለው፡፡ ዘወትር እንደሚያደርጉት ያለ መተራረብ ነውና ተናጋሪው ከአፉ ለወጣው ቃል ቀልብ የሰጠው አልመሰለም፡፡ ከዚህ ቃል በኋላ የዕለቱ የፍቅር ውሏቸው ተቋጨና ተለያዩ፡፡ ተናጋሪው በውስጡ ነገን እየናፈቀና አብረው የሚውሉበትን ሰዓት እያሰበ ወደ ቤቱ ሲገባ ‹ሸፋፋ› የተባለው ደግሞ ከራሱ ጋር እያወራና ብስጭቱ ያመጣበትን ግልፍተኝነት ለማረጋጋት እየሞከረ ሄደ፡፡ ጥቂት ሰዓታት አለፉ፡፡
ተናጋሪው ሰውዬ ከቤቱ ወጣ፡፡ ሚስቱና ልጁን ሰላም ብሎ ወደ ጎረቤት ነበር አወጣጡ፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ቴሌቪዥን ለማየት ነው፡፡ ቤቱ ቴሌቪዥን የሌለ በመሆኑ ጎረቤት ወዳለው ጓደኛው ነበር የሄደው፡፡ እዚያ እየተጫወተና በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ሙዚቃ እየኮመኮመ ቆየ፡፡ ቀኑ ማመሻሸት ጀምሮ ነበርና ልቡ ወደ ቤቱ በመሄድና እዚያው በመቆየት መካከል ሲወላውል ስሙ ሲጠራ የሰማ መሰለው፡፡ የልጁ ድምፅ ነው፡፡ ‹አባዬ ና ትፈለጋለህ› ሲል ሰማው፡፡
ይህን የ10 ዓመት ህፃን የላከው የአባቱ ጓደኛ የሆነው ያ ‹ሸፋፋ› ተብሎ የተተረበ ሰው ነው፡፡ በልቡ ያሰበውን እኩይ ተግባር አንግቦ ወደዚህ ወዳጁ ቤት ሲመጣ በዚያ እሳት የለበሰ ስሜቱ ውስጥ እንዳለ ሆኖ የፈለገውን ማግኘት አልቻለም፡፡ የሰውየው ሚስት ‹ባልሽ የት ሄደ?› ተብላ ስትጠየቅ ነገሩ ስላላማራት ቤት አለመኖሩን ትናገራለች፡፡ ምንም የማያውቀው የ10 ዓመት ህፃን ደግሞ ብቅ ብሎ ‹አለ- ጎረቤት ቴሌቪዥን ሊያይ ሄዶ ነው› በማለቱ ነው ጥራው ተብሎ የጠራው፡፡
የሚፈልገው ሰው ማን እንደሆነ ለማወቅ ብቅ ያለው ወጣት ጓደኛው መሆኑን ሲያውቅ ፈገግ ብሎ ተናገረው፡፡ ‹‹ምነው በሰላም ነው? አብረን ውለን ትፈልገኛለህ?› ብሎ ነበር የጠየቀውና ወደ ቆመበት የተጠጋው፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ሚስትና ህፃን ልጅ ቆመው ይመለከታሉ፡፡ ወደ ጠሪው ሲቃረብ ያ ‹ጥሩልኝ› ያለ ወጣት በጥፊ ተቀበለው፡፡ ራሱን ለመከላከል ሙከራ በሚያደርግበት ወቅት ደግሞ ያላሰበውን ጩቤውን ከጎኑ አውጥቶ አንገቱ ላይ ሽጦበት ሮጦ ሄደ፡፡ ልጁና ሚስት በሁኔው ተደናግጠው ሲጮሁ የተወጋው ሰው ጥቂት ለመንገታገት ሞክሮ ባለመቻሉ በቁሙ ተዘረረ፡፡ ጎረቤቶች ጩኸት ሰምተው ሲወጡ ከተጎጂው አንገት ስር የሚወርደው ደም አካባቢውን አበላሽቶት ነበር፡፡ ወደ ሕክምና ሊወስዱት ሲያነሱት ግን ህይወቱ አልፋለች፡፡
ማንም ባላሰበውና ባልገመተው ሁኔታ ገዳይ ‹ሸፋፋ አለኝ› በሚል ምክንያት ቤቱ ገብቶ ጩቤ ታጥቆ ለግድያ መውጣቱ ብዙዎችን አስገርሟል፡፡ ቀናቸውን በመተራረብና በመሳሳቅ የሚያሳልፉ ሁለት ጓደኛሞች በግድያ የቆየ የወዳጅነት ፋይላቸውን ሲዘጉ መስተዋሉም ለብዙዎች እንቆቅልሽ ነበር፡፡
ተጠርጣሪው ከሸሸበት በህዝቡ ትብብር ተይዞ ሲጠየቅ ‹በፈለገው ነገር ቢቀልድ ምንም አይመስለኝም፡፡ ነገር ግን በተፈጥሮዬ እንዴት ይቀልዳል?› ነበር ያለው፡፡ ሁሌም የለመዱት መተራረብና መሰዳደብ ላልታሰበ ግምት ሊያደርሳቸው እንደሚችል የጠረጠረ የለም፡፡ ሟችም ሀገር አማን ብሎ የተቀመጠ- እንኳን በጓደኛ በሌላ ሰው እጠቃለሁ ብሎ የማያስብ እንዲሁም እስከመጨረሻዋ ደቂቃ ለገዳዩ የነበረው ፍቅር ያልቀነሰ ምስኪን ነው፡፡ በአንዲት ቃል ህይወት ጠፋ፡፡ የጓደኛው ሞት ያሳዘነው የሚመስለው ገዳይ ‹‹ሳላስበው ሰይጣን አሳስቶኝ ያደረኩት ነገር ነው›› አለ፡፡ የሁለቱ ፍቅር በመቃብርና በእስር መደምደሙ ግን ግድ ሆነ፡፡ እናትና ልጅም እያዩት አባወራቸውን ቀበሩ፡፡
ሁለት
የ‹ዱብ ዕዳ› ምሽት
ነሐሴ ወር
1998 ዓ.ም
መሽቷል፡፡ አፋር ኬክ ቤት አካባቢ ከፒያሳ ወደ ሰይጣን ቤት በሚስደው ቁልቁለት መንገድ ላይ የክረምቱ ዝናብ መውጫ መግቢያ አሳጥቶት የዋለው አዲስ አበቤ በየካፌዎቹና በየሬስቶራንቱ ተጠልሎ ጋብ ሲልለት ነው ወደ አስፓልቶቹ ወጣ ያለው፡፡ በአንፃሩ ሌሎች በየቤታቸው ተቀምጠው የነበሩ ወደ ካፍቴሪያዎች ‹ሞቅ ላለ ሻይ› ጎራ ብለዋል፡፡ ጭር ያለው የክረምት ቀን ምሽቱ አካባቢ ደመቅ ያለ ይመስላል፡፡
ስዩም የ27 ዓመት ወጣት ነው፡፡ የዚያን ዕለት ከእናቱ ጋር ነው የዋለው፡፡ ወደ አመሻሹ ላይ ሲወጣ እቁብ ክፈል ተብሎ የተሰጠውን አንድ ሺ ብር ይዞ ነበር፡፡ ብቻውን ወደ አፋር ኬክ ቤት ጎራ ያለው ሻይ ለመጠጣት ብሎ ነበር፡፡
የስዩም ሰፈር እዚያው አካባቢ ነው፡፡ ቴዎድሮስ አደባባይ አስከሬን አበባ የሚሸጥበት በተለምዶ አበባ ሰፈር ተብሎ የሚጠራው አካባቢ በአካባቢው ልጆች ጋር የሚቀራረብ ቢሆንም ብዙዎች ግን የግሩፕ ፀብ የሚወዱ በመሆናቸው ብዙም ሊጠጋቸው አይፈልግም፡፡ የዚህ ወጣት ስራ መማር መስራት ህይወቱን በአግባቡ መምራት ብቻ ነው፡፡
ሻዩን ጠጥቶ ሲወጣ ከ3 የሚበልጡ ወጣቶች ቆመዋል፡፡ አያውቃቸውም፡፡ እነርሱ ግን የሚያውቁት መሰለው፡፡ አስተያየታቸው አላማረውም፡፡ ከምሽቱ 2 ሰዓት ሆኗል፡፡ አንደኛው ‹ና ወደዚህ› አለው፡፡ ስዩም አካባቢውን ቃኘት አደረገ፡፡ ብዙ ሰው የለም፡፡ ፈራ፡፡ የጠሩት በሰላም እንዳልሆነ ገብቶታል፡፡ ነገር ግን አማራጭ አልነበረውምና ተጠጋቸው፡፡ አጠገባቸው ከደረሰበት ደቂቃ ጀምሮ መጨረሻ እስከሆነው ነገር ድረስ ያዩ ሰዎች ነገሩን ለፖሊስ ተርከውታል፡፡
‹‹ተጠጋቸው፡፡ በዚህ መሀል ወዲያው በላይ የተባለው አንደኛው ጠጋ አለና በያዘው ጫፉ ላይ ብረት ያለው ዱላ አናቱን መታው፡፡ ስዩም ወደቀ፡፡ በወደቀበት ቦታ ጥለውት ይሄዳሉ ሲባል ከየት እንደመጡ ያልታወቁ 11 ወጣቶች ድንገት ደረሱና በወደቀበት ቀጠቀጡት፡፡ ጌቱ የተባለ አንድ ወጣት የስዩም መቀጥቀጥ አልበቃ ብሎት ድንጋይ አምጥቶ ጭንቅላቱን መታው፡፡ ስዩም ጣር ላይ ነበር፡፡ ድንገት ብድግ ብሎ ከዚያ ውርጅብኝ ለማምለጥ ሮጠ፡፡ ብዙ ርቀት ግን አልተጓዘም፡፡ ተደናቀፈና ቦይ ውስጥ ወደቀ፡፡ በዚው ቀረ፡፡ ይህን ያዩና ሲሮጥ የተከታተሉት ደብዳቢዎቹ አልተዉትም፡፡ እዚያው የየድርሻቸውን ደብድበውት ጥለውት ሄዱ፡፡ በዚያን ጊዜ የአካባቢው ሰዎች ለማገላገል ያደረጉት ሙከራ የለም፡፡ የቡድን ፀብ በጣም ይፈራ ስለነበር ነገሩን በዝምታ ከመከታተል ውጪ ምርጫ ያለው አልነበረም፡፡ በቅፅበት ውስጥ የተከናወነው ድብደባ ደግሞ ፖሊስ ለመጥራት አመቺ አልነበረም፡፡ ያም ሆነ ይህ ትቦ ውስጥ የወደቀውን ተደብዳቢ ለማንሳት ወደ ስፍራው የሄዱት የአካባቢው ሰዎች ወጣቱ በዘግናኝ ሁኔታ መሞቱን አወቁ፡፡ በጨለማ ድብደባው ወቅት ሌዘር ጃኬቱን፣ ያጠለቀውን የወርቅ ሀብልና ኪሱ ውስጥ የተገኘውን 1 ሺ ብር የወሰዱት ደብዳቢዎች ተሰውረዋል፡፡
ጥቂት ቀናት ከፈጀ ምርመራና ክትትል በኋላ የተያዙት 11 ተጠርጣሪዎች ግድያውን አንዱ በአንዱ ላይ ሲያላክኩ ቆዩ፡፡ በተለይም የገደልኩት እኔ አይደለሁም ለማለት ከፍተኛውን የድብደባ ደረጃ ወደ ሌላ ለማዞር ጥረት ተደርጎም ነበር፡፡
የግድያው መነሻ የተባለው ነገር ነው ለሁሉም አስገራሚ የነበረው፡፡ ሁሉም ተጠርጣሪዎች ስዩምን አያውቁትም፡፡ ከሁሉም ውስጥ አንዱ ‹ና› ብሎ የጠራው ብቻ ስዩም ‹የአበባ ሰፈር› ልጅ እንደሆነ ያውቃል፡፡ ስዩም ተማሪ ይሁን አስተማሪ ሰራተኛ ይሁን ስራ አጥ የሚያውቅ የለም፡፡ ነገር ግን አንድ እውነት አለ፡፡ ስዩም የአበባ ሰፈር ልጅ ነው፡፡ በአበባ ሰፈር ነዋሪዎችና በእነዚህ ወጣቶች መካከል የተፈጠረው አለመግባባት ወደ ፀብ አምርቶ አሁን ሁለቱም ሰፈሮች ለጥቃት ተዘጋጅተው የተቀመጡ ናቸው፡፡ ይህን ደግሞ አንድም ወጣት ቢሆን ‹ሰፈሩን ላለማስደፈር› እንዲነሳ አድርጎታል፡፡ ይህም የቡድን ፀብን አስፋፍቷል፡፡
ስዩም አንዳች በማያውቀውና በማይጠረጥረው መንገድ ህይወቱ ሲጠፋ ለሰሚ ግራ የሚያጋባ ነበር፡፡ የቡድን ፀብ ተሳታፊ ሳይሆን አበባ ሰፈር የሚኖር ሰው በመሆኑ ብቻ የፀበኞች ጥማት ማስታገሻ መሆኑ ብዙዎችን አሳዝኗል፡፡
ለዚህ እንደዘበት ያለፈ ህይወት ብዙዎች ‹ቀኑ ከዚህ አትለፍ ቢለው ነው› በማለት ሃሳባቸውን ሊሰጡ ቢሞክሩም ይህን መሰል ክስተቶች ማመዛዘንና ማሰብ በተሳናቸው ሰዎች ወደሚፈፀሙ የወንጀል ድርጊቶች እንደሚመራ ፖሊስ ተናግሯል፡፡
የቡድን ፀብ የአዲስ አበባ ከተማ ዋነኛ ችግር በነበረበት በዚያን ዓመት በተለያዩ የከተማዋ ክፍሎች የሚፈፀሙ ወንጀሎች ተበራክተው- ብዙዎችም ከህይወት ህልፈት እስከ ንብረት ውድመት ደርሶባቸው መኖራቸው ፖሊስ ችግሩን ለመከላከል ጠንካራ አሰሳ እንዲያደርግ አድርጎታል፡፡ የዚያም ውጤት ነው እነዚን ከ11 ያላነሱ የቡድን ፀብ ተዋንያን ለዚህ አንድ ነፍስ መጥፋት ዋና እና ተባባሪ ወንጀለኛ አድርጎ እንዲከስሳቸውና ወደ ዘብጥያ እንዲያወርዳቸው ምክንያት የሆነው፡፡