Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

ቅድመ-ውህደቱና ልዩ ገጠመኞቹ

$
0
0

በ  ዘሪሁን ሙሉጌታ
ሰንደቅ

 

የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) እና አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) የቅድመ ውህደት ስምምነት ሰኔ 1 ቀን 2006 ዓ.ም በመኢአድ ጽ/ቤት በተካሄደው የግማሽ ቀን ስነ-ስርዓት ተከናውኗል። በስነስርዓቱ ላይ በርካታ ታዋቂ ሰዎች፣ ፖለቲከኞች፣ የሚዲያ ባለሙያዎችና ዲፕሎማቶች ተገኝተው ነበር

የቅድመ-ውህደቱ አጠቃላይ ይዘት

Politiczedየውህደቱ የፊርማ ስነ-ስርዓት በተካሄደበት ወቅት የሁለቱ ፓርቲ አመራሮች ሰፋ ያለ ንግግር አድርገዋል። የሁለቱም መሪዎች ንግግር ውህደቱ ከመዘግየቱ በስተቀር አስፈላጊ መሆኑን አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል። ከቅድመ ውህደት ስነ-ስርዓት ፊርማው በኋላ ለጋዜጠኞች አጠር ያለ ጋዜጣዊ መግለጫ ፕሮግራም ተዘጋጅቶ ስለነበር በፕሮግራሙ ላይ የተለያዩ ጋዜጠኞች ለሁለቱ ፓርቲ መሪዎች ጥያቄ አቅርበውላቸው ነበር።

ከቀረቡት ጥያቄዎች መካከል በቀጣይ በአንድ ወር ውስጥ ጠቅላላ ጉባኤ ተጠርቶ የሚመሰረተው ፓርቲ ስያሜ ምን ይሆናል የሚል ነበር። ለዚህ ጥያቄ ምላሽ የሰጡት ኢንጅነር ግዛቸው ሽፈራው ስያሜው የሁለቱን ፓርቲዎች ስያሜ ባቆራኘ መልኩ አዲስ ስም ይወጣል ብለዋል። ስያሜው የሚፀድቀው በአዲሱ ውህድ ፓርቲ ጠቅላላ ጉባኤ መሆኑንም አስረድተዋል።

በተመሳሳይ ሌሎች ፓርቲዎችን ታሳትፋላችሁ? ለሚለው የጋዜጠኞች ጥያቄ መኢአድና አንድነት በመዋቅር ጥንካሬና በአባላት ብዛት በአንፃራዊ ደረጃ ከሌሎች ፓርቲዎች የተሻሉ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ይህ ብቻ በቂ ባለመሆኑ ሌሎች ፓርቲዎች እንዲገቡበት በማድረግ ኢህአዴግን የሚፎከር አብይ ብሔራዊ ፓርቲ ለማቋቋም መታሰቡን ገልፀዋል። የአሁኑም የአንድነትና የመኢአድ ቅድመ-ውህደት እንደ ውህደት ማዕከል ሆኖ እንደሚያገለግል ያላቸውን ተስፋ ገልፀዋል።

በተጨማሪም በአንድ ወር ውጥ ጠቅላላ ጉባኤ ተጠርቶ አዲሱን ውህድ ፓርቲ ለመፍጠር የአቅም ጉዳይ በጋዜጠኞች ተነስቶ የነበረ ሲሆን፤ “ችግራችን የአመራር እና ድርጅታዊ አቅምን የማንቀሳቀስ እንጂ የአቅም አይደለም። አባላቶች በከፊልም ቢሆን የራሳቸውን ወጪ በመሸፈን ወደ አዲስ አበባ በመምጣት የሁላችንንም ፍላጎት እናሳካለን” ሲሉ ኢንጂነር ግዛቸው መልሰዋል። በቅርቡም የሁለቱም ፓርቲዎች ብሔራዊ ም/ቤት የጠቅላላ ጉባኤ አዘጋጅ በመሰየም ሁኔታውን ያፋጥናል ብለዋል። አዲሱ ውህድ ፓርቲም ከሁለቱ ፓርቲዎች የተውጣጣ 400 የጠቅላላ ጉባኤ አባላት ይኖሩታል ብለዋል።

ቀደም ሲል በመኢአድ በኩል “አንድነት ከመድረክ ካልወጣ ውህደቱ አይሳካም” የሚለውን ጥያቄ በተመለከተ ከጋዜጠኞች ለተነሳው ጥያቄ ጉዳዩ በሕግ ባለሙያዎች ታይቶ በመድረክም ሆነ አዲስ በሚፈጠረው ውህድ ፓርቲ ላይ የሚፈጥረው ተፅዕኖ እንደሌለ መረጋገጡ፣ አንድነት ከመኢአድ ጋር ውህደት በሚፈፅምበት ወቅት ሕጋዊ ሰውነቱን ወዲያውኑ ስለሚያጣ ከመድረክ ጋር የሚኖረው ግንኙነት ወዲያውኑ የሚቋረጥ በመሆኑ ችግር እንደማይፈጠር ተረጋግጧል ሲሉ ኢንጂነር ግዛቸው ተናግረዋል።

ሌላው ከጋዜጠኞች የቀረበው ጥያቄ፤ ቅድመ ውህደቱ የተሳካው በፓርቲዎቹ አመራሮች ሳይሆን፤ በሽማግሌዎች ግፊት ስለሆነ ምን ያህል ዘላቂነት ይኖረዋል የሚል ነበር። ለዚህ ጥያቄ ምላሽ የሰጡት ኢንጂነር ግዛቸው፤ በሁለቱ ፓርቲዎች መካከል የውህደት ፍላጎት መንፀባረቅ የጀመረው ከአራት ዓመት በፊት መሆኑን አስታውሰው፤ ለመዋሐድ ፍላጎቱ የመጣው ከአባሉና ከአመራሩ መሆኑን ጠቅሰዋል፤ ነገር ግን ሽማግሌዎቹ የመጡት በመጨረሻ ውህደቱ እንዲፋጠን ድጋፍ ለማድረግ ነው ብለዋል።

አቶ አበባው መሐሪ (የመኢአድ ሊቀመንበር) በበኩላቸው አንድነት ከመድረክ ጋር ስላለው ግንኙነት ሲመልሱ፤ እስካሁን ድረስ ውህደቱን ሲያጓትት የቆየው የአንድነትና የመድረክ ግንኙነት የጠራ ባለመሆኑ ነው ብለዋል። መኢአድ ከአንድነት ጋር ሲዋሐድ ይሄው ችግር ወደ ውህዱ ፓርቲ እንዳይሄድ በመፍራት ጥያቄው በመኢአድ በኩል መነሳቱን ገልፀዋል። ሆኖም ችግሩን የሚያጠና ሁለት ገለልተኛ የሕግ ባለሙያዎች ተመድበው የመድረክና የአንድነት እንዲሁም የመኢአድ ከምርጫ ቦርድ ሕግና ደንብ ጋር ታይቶ በመጨረሻ ወደ ውህዱ ፓርቲ ሊተላለፍ የሚችለው የገንዘብና የንብረት እንጂ የፖለቲካ ባለመሆኑ በዚሁ በመተማመን የቅድመ-ውህደት ሰነዱ ሊፈረም መብቃቱን ተናግረዋል።

ሽማግሌዎቹ በአደራዳሪነት ይሳተፉ እንደነበር የጠቀሱት አቶ አበባው፤ የሽማግሌዎቹ በጎ አስተዋፅኦ ቢኖርም፤ አሁን ግን ሁለቱ ፓርቲዎች ድርድሩን በራሳቸው የጨረሱት መሆኑን ገልፀዋል።

በተጨማሪነት ከጋዜጠኞቹ የቀረበው ጥያቄ ፓርቲዎቹ የውስጥ ችግራቸውን ሳይፈቱ ወደ ቅድመ-ውህደት ፊርማ ለምን መጡ? የቅድመ-ውህደት ፊርማው ከማካሄዱ በፊት በር ላይ ቅሬታ ሲያሰሙ የነበሩ ወገኖች ነበሩ ለሚለው ጥያቄ፤ አቶ አበባው ሲመልሱ በዚህ ወቅት ፓርቲዎቹ በውስጥ ችግር ላይ አለመሆናቸውን ይልቁኑ ቅድመ ውህደቱን እንዳይፈረም ሁከት የፈጠሩት የመኢአድ አባላት ሳይሆኑ የአዲስ አበባ የኢህአዴግ አባላት ናቸው ብለዋል። “የኢህአዴግ አባል የመኢአድን የውስጥ ችግር ይፈታ የማለት መብት የለውም” ሲሉ በመግለፅ ጉዳዩ ፓርቲዎቹን ውህደት እንዳይፈፅሙ በመንግስት በኩል የተቀናጀ ጥረት መኖሩን የሚያመለክት ከመሆኑም በላይ ኢህአዴግ ጠንካራ ፓርቲ እንዳይፈጠርና በሕዝባችን ላይ የጭቆና ቀንበር ጭኖ ለመቀጠል መፈለጉን የሚያመላክት ነው ብለዋል።

ፓርቲዎቹ ከሚያደርጉት ውህደት ጎን ለጎን በ2007ቱ ምርጫ የሚኖራቸው ተሳትፎና ለዚያም የሚሆን ስትራቴጂ ምን እንደሆነ ከጋዜጠኞች ተጠይቀው የነበረ ሲሆን፤ ምርጫውን በተመለከተ የውህዱ ፓርቲ የሚወስነው እንደሆነ ኢንጂነር ግዛቸው ጠቅሰው፤ በአጠቃላይ ሁለቱም ፓርቲዎች የምርጫ ፓርቲዎች እንደመሆናቸውና በሰላማዊ ትግል የሚያምኑ በመሆኑ ምንጊዜም ለምርጫ ዝግጁ መሆናቸውን አስረድተዋል። በአንድነት ፓርቲ በኩል አማራጭ ፖሊሲ የምርጫ ስትራቴጂ፣ ማኒፌስቶ፣ ማዘጋጀት ዕጩዎችንና ታዛቢዎችን እየፈተሸ መሆኑንና በመኢአድም በኩል ይሄው ጉዳይ ስለሚኖር የሁለቱንም አጣምረን እንቀጥላለን ብለዋል። በምርጫ መሳተፍ፣ አለመሳተፉ ግን ወደፊት እንደሚወሰንና የዴሞክራሲ ተቋማቱ ነፃ መሆንና መጠናከር ወሳኝ መሆኑን አብራርተዋል።

በጋዜጠኞች ከተነሱ ሌሎች ጥያቄዎች መካከል ከፓርቲዎች ውህደት በኋላ አንጃዎች የመፈጠር ሁኔታዎች ስለሚስተዋል ለዚህ ችግር የተቀመጠ ስትራቴጂ አላችሁ ወይ የሚል ነበር። ለዚህ ጥያቄ ምላሽ የሰጡት ኢንጂነር ግዛቸው፤ ውህደቱን ተከትሎ አንጃ መውጣቱ ፓርቲዎቹን እንደማያሳስባቸው ነገር ግን የሚወጣው አንጃ ስርዓት አልበኛ ሲሆን ነው ችግሩ ብለዋል። አንጃ የሚወጣ ከሆነም ሁለቱ ፓርቲዎች በተቀመጠው መዋቅር በዴሞክራሲያዊና በሰለጠነ መንገድ መወጣት ይቻላል። ነገር ግን በስርዓት አልበኝነት ቢሮ በመውረር ከኢህአዴግ ጋር በመገናኘት መሰናክል የመፍጠሩ አካሄድ አንጃ መፍጠር አይደለም ብለዋል።

“ውህደቱ አልተስማማኝም የሚል ቡድን ካለ መብቱ ነው። ሌላ ፓርቲ ማቋቋም ይችላል። የሰለጠነ ፖለቲካ ለማካሄድ የጉልበት፣ የመደባደብና ከባህል ውጪ የሆነ ነገር ሲሆን ግን ያሳፍራል” ሲሉ ኢንጂነሩ የገለፁ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት ከዚህ አንፃር በአንድነት በኩል የሚያሰጋ ነገር የለም ብለዋል።

ውህደቱ በመዘግየቱ እንደተቋም ሁለቱን ፓርቲዎች በፍጥነት ባለመስራታቸው ኃላፊነቱን እንደሚወስዱ ሁለቱም አመራሮች ገልፀዋል። በተለይ አቶ አበባው መሐሪ ውህደቱ ለምን ዘገየ ለሚለው የጋዜጠኞቹ ጥያቄ ሲመልሱ፤ የፓርቲዎችን መዋቅርና የፖለቲካ ፕሮግራም በማጣጣም ሂደት እንጂ ከግል ፍላጎት አለመመቸት ጋር የተያያዘ አይደለም ብለዋል። በአጠቃላይ ከአንድ ወር በኋላ በሚጠራው ጠቅላላ ጉባኤ ከመኢአድ 200 ከአንድነት 200 የጠቅላላ ጉባኤ አባላት አዲስ ውህድ ፓርቲ ይፈጠራሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የቅድመ-ውህደቱ ልዩ ገጠመኞች

የቅድመ-ውህደት ስነ-ስርዓቱን ልዩ ካደረጉት አጋጣሚዎች መካከል የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲ ፓርቲ (ኢዴፓ) አመራር አባል የሆኑት አቶ ሞሼ ሰሙ በፕሮግራሙ ላይ መገኘት አንዱ ነበር። የእሳቸው በቦታው መገኘት ከምርጫ 97 በኋላ ከፖለቲካ ልዩነት ባሻገር በግለሰብ ደረጃ የተፈጠረውን መቃቃር ሊያለዝብ የሚችል ጥሩ ጅምር እንደሆነም እየተገለፀ ነው። የአንድነትም ሆኑ የመኢአድ የፓርቲ አመራር አባላት ለአቶ ሞሼ ሰሙ ያሳዩት አዎንታዊ አቀባበል በዕለቱ የነበሩ ጋዜጠኞችን ትኩረት ስቦ ነበር። አብዛኛዎቹ የአንድነትና የመኢአድ አመራሮች አቶ ሞሼን ያገኙዋቸው ከምርጫ 97 በኋላ መሆኑን በአድናቆት ሲናገሩ ታይተዋል።

አቶ ሞሼ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሰፊ የፖለቲካ ተሳትፎ እያሳዩ የመጡ ፖለቲከኛ ናቸው። በገዢው ፓርቲ ፖሊሲዎች ላይ ከሚያነሱዋቸው የሰሉ ትችቶች ባሻገር ለሀገሪቱ ፕሬስ መጠናከር የሚሰጡዋቸው ገዢ ኀሳቦች በመስኩ ባለሙያዎችና አጋሮቻቸው ጭምር እውቅና እየተሰጠው ነው። አቶ ሞሼ በሰኔ አንዱ የመኢአድና የአንድነት የቅድመ ውህደት ስምምነት ስነ-ስርዓት ላይ በድፍረት በመገኘታቸውም በኢዴፓ እና በሌሎች ተቃዋሚዎች መካከል ለረጅም ጊዜ የቆየውን ያለመተማመን ስሜት በመጠኑም ቢሆን እንዲለዝብ ምክንያት ሊሆን ይችላል ብሎ መገመት ይቻላል።

ሌላው በዕለቱ ስነ-ስርዓት ላይ ከታዩ አወዛጋቢ ጉዳዮች መካከል ሊጠቀስ የሚገባው የቅድመ ውህደት ስምምነቱን ለመረበሽ የተደረገው ጥረት ነው። የውህደቱን ስነ-ስርዓት ለማወክ የተደረገው ጥረት እንደ ሀገር የሚያሳፍር፣ እንደ ዜጋም የሚያሳዝን ነው።

ከአስተባባሪዎቹ ገለፃ መረዳት እንደሚቻለው የውህደት ስምምነቱ እንዳይካሄድ በር በመደብደብና ፀያፍ ቃል በመናገር ሲበጠብጡ የነበሩት ሦስት ግለሰቦች ነበሩ። በእርግጥ ስነ-ስርዓቱ ወደሚከናወንበት ስፍራ እንዲገቡ የተፈለገው አስቀድመው የተጠሩ እና ለዚያም ልዩ ባጅ ያደረጉ ብቻ ነበሩ። ሆኖም የተወሰኑ ሰዎች “ልግባ፣ አትገባም” የሚል ውዝግብ በሩ ላይ ይስተዋል ነበር። በመጨረሻም ውዝግቡ ተባብሶ በር እስከመገንጠልና ድንጋይ እስከመወራወር ተደረሰ። በመሀሉም በተወረወረ ድንጋይ በመኢአድና በአንድነት ከፍተኛ አመራሮች ላይ የጥርስ መውለቅ አደጋ በመድረሱ ሁኔታውን አሳዛኝ ትዕይንት አድርጎታል። በዕለቱም ስብሰባውን ከረበሹ ሦስት ሰዎች መካከል አንዱ የኢህአዴግ አባል መሆኑ ተገልጿል፡፡

በቅርቡ ሃያ ሦስተኛው የግንቦት ሃያ በዓል ሲከበር ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ከተናገሩዋቸው በርካታ ርዕሰ ጉዳዮች መካከል ለሀገሪቱ መድበለ ፓርቲ መዳበርና ለተቃና የምርጫ ስርዓት ከተቀመጡ ሕጎችና አሰራሮች ባሻገር ኢህአዴግ አባላቱን በስነ-ምግባር በማነፅ ተከታታይ ስልጠና እየሰጠ መሆኑን፣ በሂደቱም የሚያጠፉ አባላቱን ለመቆጣጠር ከድርጅቱ የማንንም ምክር ሳይፈልግ በራሱ የእርምት እርምጃ እንደሚወሰድ መግለፃቸው አይዘነጋም።


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>