Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

የወታደራዊ አገዛዝ 40ኛ ዓመት ከግንቦት 1966 –ግንቦት 2006 ዓ.ም

$
0
0

የሺዋስ አሠፋ
(ለነገረ ኢትዮጵያ ጋዜጣ እንደጻፉት)

የአንድ ሀገር ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች በሙሉ መንግስት ጨቋኝ ቁጥጥር ስር ሲሆኑ፣ የህዝቡ እንቅስቃሴዎችና ክንውኖች ከመንግስት በሚወርድ መመሪያ ብቻ ሲመክኑ፣ በህጋዊ ውሳኔና በፖለቲካዊ ውሳኔዎች መካከል ምንም ልዩነት ሲጠፋ ያች ሀገርና በውስጧ ያሉ ዜጎች በወታደራዊ አገዛዝ ስር የወደቁ ናቸው፡፡ በሀገሪቱ ያለው አገዛዝ በግልፅና በስውር በሚያሰማራቸው ወታደሮች፣ ፖሊሶች፣ ሚሊሻዎች፣ ደህንነቶች የነዋሪዎችን/የዜጎችን፣ የመንቀሳቀስ ሀሳብን የመግለፅና የመደራጀት መብት በቅርብ ክትትልና ቁጥጥር ስር ያለና የተገደበ ወይም ከፍተኛ ጫና ያለበት ይሆናል፡፡

mengistu hailemariam
የወታደራዊ አገዛዞች ሁሉም ለማለት በሚቻል መልኩ ወደ ስልጣን የሚወጡት በመደበኛ ጦርነት፣ በሽምቅ ውጊያ፣ በመፈንቅለ መንግስት ወይም በተለያዩ ሁኔታዎች በሚፈጠር የስልጣን ክፍተት ነው፡፡ በወታደራዊ አገዛዝ ካለፉ ሀገሮች መካከል ሶቪየት ህብረት፣ ምስራቅ ጀርመን፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ቺሊ፣ ኩባ፣ ሰሜን ኮሪያ፣ ፓኪስታን፣ ኢትዮጵያ… ጥቂቶቹ ናቸው፡፡በሀገራችን እንዳየነውና ከሌሎችም ሀገሮች ተሞክሮ እንዳነበብነው የእነዚህ አገዛዞች ዋና ዋና ባህሪያት ከሚባሉት ውስጥ ከነሱ በፊት የነበሩ ስራዎችን መልካም ጅምሮችንም ጨምሮ መደምሰስና ማጥፋት፣ አዲስ መሰረትነው ለሚሉት ሀገርና ልማት ህዝቡን በእዝ ሰንሰለት በመጠርነፍ አስገድዶ ለማሰራት መሞከር፣ የሚከናወኑ ተግባራት በሙሉ በአስቸኳይ ጊዜና በዘመቻ ስራ እንዲሰሩ ማስገደድ፣ ስለተሰሩ ስራዎች ውጤት ሳይገመገም ሌላ ዘመቻ በማስከተል ህዝቡን ረፍት ማሳጣ፣ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገር አንድ ኃይል በጠላትነት መሳልና የህዝቡን አይን ከአገዛዙ ድክመት ወደሚመጣው ጠላት ማዞር፣ በሚቆጣጠረው ብዙሃን መገናኛ የህዝቡን ሕይወት በፕሮፓጋዳ መያዝ፣ የተለየ ሀሳብ ያላቸውን ከጠላት ጋር በመፈረጅ፣ ሀገር ጠባቂና ለህዝብ ተቆርቋሪ መስሎ መታየት፣ የሀገሪቱን ሀብት በመበዝበዝ የገዥዎችን የአስተሳሰብ ድክመት በገፍ በሚወጣ የሀገር ሀብት ለማካካስ መሞከርና መሰል ድርጊቶች መለያዎቹ ናቸው፡፡

የዘውዳዊ ስርዓት እያረጀና ማስተዳደር እየተሳነው ሲሄድ ከወታደሩ የተሰባሰቡና ራሳቸውን ጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ ብለው የሰየሙ፣ ከኢትዮጵያ መለዮ ለባሾች የተውጣጡ ለንጉሱ የማታለል ታማኝነትን እየገለፀ የቀዳማዊ ኃይለ ስላሴን መንግስት የገለበጠው ወታደራዊ ቡድን ስልጣኑን ያዘ፡፡
ሻ/ል ተስፋዬ ርስቴ ‹‹ምስክርነት›› በሚለው መፅሐፋቸው እንደገለፁት ደርግ የራሱ የሆነ ርዕዮት ዓለም አልነበረውም፤ ድንገት በተሰባሰቡ መኮንኖች የተሞላ ነበር፡፡ ከየካቲት 1966 ጀምሮ ከ6 ወራት ባነሰ ስልጣኑን በእጁ ካስገባ በኋላ ጊዜያዊ አስተዳደር መንግስት በመመስረት መለዮ ለባሾችን በሚኒስትርነትና በኮሚሽነርነት ማዕረግ በማስቀመጥ ከጠመንጃ አፈሙዝ ያገኘውን ስልጣን ለ17 ዓመታት ገፋበት፡፡

ከተለያዩ የጦር ካምፖች የተውጣጡ መኮንኖች አራተኛ ክፍለ ጦር ጠቅላይ መምሪያ ከተሰባሰቡ በኋላ በቅድሚያ መነጋገር የጀመሩት ምን እናደርግ? በሚል አጀንዳ ነበር፡፡ ይህ ግንቦት 1966 ምንም መርህ ያልነበረው ወታደራዊ ቡድን ከመስከረም 1967 ጀምሮ ስልጣኑን ጠቅልሎ በመያዝ ሀገሪቱን የጦርነትና የዘመቻ ቀጠና በማድረግ ሲያተራምሳት ኖረ፡፡ በዚህ ወቅት ከተደረጉትና ተመልካቹን ካስደነቁት ነገሮች አንዱ የአብዮቱ መሪና የደርጉ ሊ/መንበር የነበሩት ኮ/ል መንግስቱ ኃ/ማርያም ለጋዜጠኛ ሚሊዮን ተረፈ ሲመልሱ የሚሊቴሪ ልብሳቸውን በሱፍ ቀይረው እኔ ዋና ፀሐፊ ነኝ ‹‹ወታደራዊ መንግስት የታለ? አሁን ያለው መንግስት ሲቪል መንግስት ነው›› ሲሉ መደመጣቸው ነበር፡፡

ደርግ ሀገሪቱን ደቁሶ ከወደቀ በኋላ በእሱ እግር የተተካው ኢህአዴግ በሽግግር መንግስቱ ውስጥ ያካታተቻው ሚኒስትሮች ጋንታ መሪዎች፤ ተዋጊና አዋጊ ወታደሮች የነበሩ ሲሆኑ ከአቶ መለስ ዜናዊ ጀምሮ ሁሉም ባለስልጣናት የወታደር ልብሳቸውን ለውጠው ሙሉ ሱፍ የለበሱ ወታደሮች ናቸው፡፡ ስብሃት ነጋ፣ ስየ አብርሃ፣ ፀጋዬ በርሄ፣ አባይ ወልዱ፣ አዲሱ ለገሰ፣ በረከት ስምኦን፣ አባዱላ ገመዳ ወዘተ ሁሉም ወታደሮች የነበሩ ሲሆን አንዳንዶቹ ከጄነራልነት በቀጥታ አቶ ወደሚል ማዕረግ ወርደው አገዛዙን ሲቪል ለማስመሰል የተሞከረበት መንገድ ቢታይም እንደ 1997 ዓይነት ፈታኝ ጊዜ ሲመጣ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀምሮ ሁሉም አዋጊ ጄነራሎች ሆነው ታይተዋል፡፡

በብዙኃን ሲቪል ህብረተሰብ እንደሚታወቀው ወታደር በከፍተኛ ታዛዥነትና ዲሲፕሊን የሚያምን፣ ቀድሞ በገባ የሲኒየሪቲ ባህል የሚገዛ (ይሄ ዛፍ ከአንተ ቀድሞ እዚህ ግቢ የበቀለ በመሆኑ የሲኒየር ሰላምታ ስጥ ሲባል እስከመቀበል የሚደርስ)፣ ለ6 ወራት ባገኘው ስልጠና ከ60 ዓመታት በላይ
የሚኖርበት፣ በበዓልም ሆነ በአዘቦት፣ በሰርግም ይሁን በለቅሶ በጠዋት ተነስቶ እንቅስቃሴ የሚሰራ፣ ፂሙንና ፀጉሩን የማስተካከል የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ካልሰራ፤ ጫማው ካልተቀባ፣ የሸሚዙ ኮሌታ ካልነፃ፣ ሱሪው ቀጥ ብሎ ካልተተኮሰ፣ ቁርሱን የማይቀምስ ህይወቱን በሙሉ በተጠንቀቅ የሚኖር፣ ለሀገሩ ጋሻና መከታ የሚሆን፣ ሀገሪቱ በአገዛዝ ስር ስትሆን ደግሞ የአለቃው ዱላ የሚሆን ነው ወታደር ማለት፡፡ ይህን የወታደር ህይወት በመንግስት ስርዓት ውስጥ ስናየው ዛሬ ሀገራችን ያለችበት አጠቃላይ ሁኔታ ያሳየናል፡፡ ለሚከናወኑ ማህበራዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ተግባራት ህዝብን አማክሮና የህዝቡን ይሁንታ አግኝቶ ከመንቀሳቀስ ይልቅ በተለመደው ወታደራዊ አሰራር የአንድን ግለሰብ ሀሳብ ባለው የጥርነፋ መዋቅር መሰረት ከላይ ወደታች ለማውረድና ለማስረፅ ሌት ከቀን በሚዲያ መለፈፉና በየቀበሌው ከአመት አመት ስብሰባ የካድሬዎቹና የህዝቡ ህይወት ሆኖ እያየን ነው፡፡

ለ23 ዓመታት በዚህ ሁኔታ የሚገዙን ግለሰቦች ከስማቸው በፊት ያለውን ቅፅል ቢቀይሩም፣ ወታደራዊ መለዮአቸውን ቀይረው የሲቪል ልብስ ቢለብሱም ሲያዋጉና ሲያዋጉ የኖሩ ናቸው፡፡ ሀገራችን ኢትዮጵያም ለ17 ዓመታት በደርግ፣ ለ23 ዓመታት በኢህአዴግ በጠቅላላው ለ40 ዓመታት በወታደራዊ አገዛዝ ስር የምትማቅቅ ሀገር ናት፡፡የደርግ ባለስልጣናት የነበሩት መንግስቱ ኃ/ማርያም፣ አጥናፉ አባተ፣ ተፈሪ በንቲ፣ አማን አንዶም፣ መላኩ ተፈራ፣ ለገሰ አስፋው፣ ፍ/ስላሴ ወግደረስ እና ሌሎችም ይህንና ያንን ያደርግነው መጀመሪያ ኢህአፓ ስላደረገው ነው ወይም በመኢሶን ምክር ነው በማለት የአገዛዙን መጥፎ ድርጊቶች በሌላ ወገን ለማላከክ ቢሞክሩም የመንግስታቸውን ወታደራዊ አገዛዝነት አይከዱም፡፡
eprdf-tplf
የኢህአዴግ ባለስልጣናት ግን ፈፅሞ በወታደርነት ያልተሰለፉ ለማስመሰል ከሲቪል መካከል በምርጫ የመጡ ተደርገው እንዲታዩ ጥረት ሲያደርጉ ይስተዋላል፡፡ እውነታው ግን በወጣትነት ጊዜያቸው በተቀረፀባቸው የአድርግ አታድርግ በወታደራዊ ትዕዛዝ የተቀየዱ መሆናቸው ነው፡፡ ይህ የወታደር መስመራዊ
ትዕዛዝ በዘርና በወንዝ ልጅነት ሲጠፈር ፍፁም የሆነ የጋሪ ፈረስ አይነት መከተልን ያመጣል፡፡ የችግሩም ምንጭ ጥልቀት ይሄን የተቀየደ አሰራር ወደ ሲቪል ተቋማት ለማውረድና በዚሁ መሰረት የጉልበትም ሆነ የአእምሮ ስራዎችን አስገድዶ ለማሰራትና ሀገርን ለማስተዳደር ሲሞክር ነው፡፡ በ2002 ዓ.ም መጨረሻ አካባቢ የኢትዮጵያ ቴሌኮሚኒኬሽን ኮርፖሬሽን መስሪያ ቤትን አስተዳደር ለፈረንሳይ ኩባንያ እንሰጣለን የሚል ትዕዛዝ መጣ፡፡ በወቅቱ ይህን ለማስፈፀም ላይ ታች ሲሯሯጡ የነበሩት አቶ ደብረ ጽዮን የተባሉ የህወሓት ወታደር የነበሩ በኋላ ልብሳቸውን ቀይረው ሚኒስተር የተደረጉ ሰው ነበሩ፡፡
በወቅቱ እዚያው እሰራ ስለነበር ከተሰብሳቢዎች መካከል ነበርኩ፤ በስብሰባው መክፈቻ ላይ እኒህ ግለሰብ ያስተላለፉት ትዕዛዝና ያንን ትዕዛዝ ለማስተላለፍ የተጠቀሟቸው ቃላት ቀጥታ ከኢታማጀር ሹሙ የተቀበሉትን ወታደራዊ ትዕዛዝ ለሰራዊቱ የሚያስተላልፉ ጄኔራል ይመስሉ ነበር፡፡ ስለ ጭቆና፣ ስለ
ኪራይ ሰብሳቢነት፣ ስለሽብር፣ ስለመበታተን አደጋ ምንም የማይመለከተው ቦታ ላይ ተናገሩ፡፡ ስለቴሌ መፍረስና ስሙም አትዮ ቴሌኮም ወደሚል መቀየሩን፣ ሰራተኛ እንደማይቀነስ ወዘተ… ብዙ ተናገሩ፡፡ የእኛን ሀሳብ ግን አንዱንም ለማድመጥ ፈቃደኛ አልነበሩም፡፡ የመጡት ወታደራዊ ትዕዛዝ ማስተላለፍ ስለነበር፡፡ላለፉት 40 ዓመታት በባንክ፣ በቴሌ፣ በመብራት ኃይል፣ በአየር መንገድ፣ በህንፃ ኮንስትራክሽን፣ በመንገድ ትራንስፖርት ላይ በመሳሰሉት ተቋማት ወታደራዊ ትዕዛዝና የዘመቻ ስራ ትንፋሽ እስኪያጥራቸው ሲያዋልባቸው ኖሯል፡፡ የሚደንቀው ግን አስበውና አቅደው ሳይሰሩ ያለፈውን ተግባር ድክመ
ትም ሆነ በጥንካሬ መነሻ ሳያደርጉ ለማደግ መታሰቡ አልፎም አድገናል መባሉ ነው፡፡ በሰላም በምንገዛላቸው ጊዜ ይህን ቢያደርጉም ስልጣኑን የሚነቀንቅ ሁኔታ ሲከሰት ልብስና ማዕረግ ቀያይረው በቴሌቪዥን መስኮት ብቅ ማለት የነዚህ ወታደራዊ አገዛዝ መሪዎች ባህሪ ነው፡፡ በሀገራችን ኢትዮጵያም ሆነ
በሌሎች እንደ ኩባ፣ በርማ እና ደቡብ ሱዳን መሪዎች የቅርብ ጊዜ ትዝታዎቻችን ናቸው፡፡

የወታደራዊ አገዛዝን ከነፍሱ የሚጠሉት ጄን ሻርፕ አገዛዞች በጣም ብልጥና ውስብስብ ሆነዋል ይላሉ፡፡ ህዝቡን እርስ በርስ ከማጋጨት በተጨማሪ ከዲሞክራት መንግስታት ጋር ለመወዳጀት ይሞክራሉ፣ ህዝባቸውን በውሸት ምርጫ በማታለል ከሲቪሉ የተመረጡ ለመምሰል ይጥራሉ፡፡ ለዓለም አቀፍ ድርጅቶች የተሳሳተ መረጃ በመስጠት በመሬት ላይ ከሚታየው ውጭ የሆነ እድገት ያስመዘገቡ ይመስላሉ ወዘተ፡፡ ስለዚህም ህዝቡ በመጀመሪያ የወታደራዊ አገዛዙን አመጣጥ፣ አሁን የቆመባቸውን ምሰሶዎችና፣ ወደፊትም በስልጣን ለመቆየት የሚፈነቅላቸውን ድንጋዮች ማወቅና መደራጀት ተገቢ ነው፡፡
በወታደራዊ አገዛዝ ለ40 ዓመታት እንደተያዝን እየታወቀ አሁንም በዚያው መንገድ ካለንበት ለመውጣት ሲታሰብ እጅግ ያስደንቃል፡፡ ወታደር ስሪቱ አንድ ነው፡፡ መጀመሪያ መደምሰስ፣ ቀጥሎ ማረጋጋት፣ ቀጥሎ ጊዜያዊ መንግስት መመስረት ቀጥሎ… አለቀ፡፡ ወታደራዊ አገዛዝን ለመጨረሻ ጊዜ ማስወገድ የሚቻለው ህዝብ በቃኝ ሲል፣ በአንድ ድምፅ አልገዛምሲል ነው፡፡ ይህን ለማድረግ ህዝቡ ማወቅ አለበት፡፡ ህዝቡ እንዲውቅ ደግሞ የህዝቡን ቀልብ የሳበና ህዝቡ የሚሰማውና የሚከተለው የፖለቲካ ድርጅት አስፈላጊ ነው፡፡በሀገሪቱ ያለው የመጨረሻው ትልቅ ኃይል ህዝቡ ነው፡፡ የፖለቲካ ድርጅት ህዝቡ እንደሚሰማው እርግጠኛ ከሆነ በሰላማዊ መንገድ አገዛዙን ሊያንበረክከው ይችላል፡፡ የአገዛዙ የመጨረሻ ጉልበት ወታደሩ ነው፡፡ ወታደሩን ዱላ በማድረግ ህዝቡን ማስፈራራት፣ ማሰር፣ መግደል የመጨረሻ አማራጭ ይሆናል፡፡ የፖለቲካ ድርጅቱ እያንዳንዱ ተራ ወታደር ከህዝቡ የወጣ እንዲሆነ በመገንዘብ ለእያንዳንዱ በተለያዩ ቦታ ለተሰማራው ወታደር ቅርብ እንደሆነ በመገንዘብ እያንዳንዱ በተለያዩ ቦታ ለተሰማራው ወታደር የቅርብ ዘመዴ ወይም ቤተሰቤ ከሚለውና መልዕክት/ደብዳቤ እንዲደርሰው ያደርጋል፡፡

በዚህ አይነት አንድ ወታደር ቢያንስ ከአምስት ሰዎች ከእኛ ጋር ቁም፤ ከወገንህ ጎን ቁም፤ የአምባገነን ዱላ አትሁን፣ ለሀገርህ እንጂ ለአገዛዙ አሽከር አትሁን የሚል ደብዳቤ ያደርሰዋል፤ የእነዚህን አይነት የሰላማዊ ትግል ስልቶች የህዝቡን የሞራል ልዕልና ከማሳደጋቸውም በተጨማሪ ለወታደራዊ አገዛዙ ፍፁም በማያዳግም ሁኔታ ሽባ የሚያደርጉና በአጭር ጊዜ ነፃነትን የሚያጎናፅፉ ናቸው፡፡ በሀገራችን የሰላማዊ ትግል ብዙ ያልተለመደና በህዝቡ ልብ ያልነበረ በመሆኑ ለ40 ዓመታት የተጫነብንን የብረት አገዛዝ ለመገርሰስ ሌላ ብረት በማንሳት መሞከር ወደሌላ አዙሪት እንደሚከተንም አብሮ መታሰብ ያለበት ሀቅ ነው፡፡ ሰላማዊና ህዝባዊ እንቢተኝነቱ የተሳካና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲያመጣ የፖለቲካ ድርጅትና የብዙኃን መገናኛዎች ወሳኝ ሚና አላቸው፡፡ ጋሽ መስፍን (ፕ/ር መስፍን) እንደገለፁት የፖለቲካ ድርጅት ያስባል፣ ያቅዳል፣ ይወስናል፣ የብዙኃን መገናኛዎች ውሳኔውን ያስተላልፋሉ/ያሰራጫሉ፤ የትግሉ ዋና ኃይል የሆነው ህዝቡ ይፈፅማል/ይተገብራል፡፡ በዚህ አይነት የምንተገብራቸው፣ የ40 ዓመታት የጭቆና ቀንበር አሽንቀጥረን ለመጣል የሚያስችሉን 200 የሚደርሱ ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያላቸው የሰላማዊ ትግል ስልቶች መኖራቸውንም ልብ ይሏል፡፡

ቸር ይግጠመን!


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>