Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

“የትኛውም የሥራ ፈጠራ የሚመነጨው ከችግር ነው” –ከፎርጂዱ ዶ/ር ኢ/ር ሳሙኤል ዘሚካኤል ጋር የተደረገ ቃለምልልስ

$
0
0

የሰሞኑ አነጋጋሪ ሰው ፎርጂዱ ዶ/ር ኢ/ር ሳሙኤል ዘሚካኤል በአንድ ወቅት አድርጎት የነበረው ቃለምልልስ ስለግለሰቡ ግንዛቤ ይሰጣችኋል።

የዛሬ 35 ዓመት አንድ ሕፃን ከድሃ ቤተሰብ በጋንዲ ሆስፒታል ተወለደ፡፡ ያ ሕፃን ከተቀሩት ኢትዮጵያውያን ሕፃናት የተለየ ችሎታ አልነበረውም፡፡ ቤተሰቦቹ ድሃ ስለነበሩ በእንክብካቤና በቅምጥል አላደገም፡፡ አባቱን አያውቃቸውም፡፡ የአምስት ወር ህፃን ሳለ ነው በሞት የተለዩት፡፡
ገና በወጣትነት ዕድሜ የትዳር አጋርን በሞት መነጠቅ ከባድ ፈተና መሆኑን መገመት አያዳግትም፡፡ ልጆቻቸውን የማሳደግና ቤተሰቡን የማስተዳደር ሸክም እናቱ ትከሻ ላይ ወደቀ፡፡ ኑሮና ብቸኝነቱን መቋቋም የከበዳቸው እናቱ፤ ሕፃኑ ሁለት ዓመት ሲሞላው “ከአንድ፣ ሁለት መሆን ሳይሻል አይቀርም” በማለት ባል አገቡ፡፡ አዲሱ ባላቸውም አላሳፈሯቸውም፡፡ ልጆቻቸውን፣ እንደ “እንጀራ አባት” ሳይሆን ከስጋ ልጆቻቸው እኩል ተንከባክበው አሳደጓቸው፡፡
ያ ከድሃ ቤተሰብ የተወለደው ሕፃን፤ በእልህ አስጨራሽ ትግልና ጥረት፣ በከፍተኛ የእውቀት ፍቅርና ትጋት ድህነትን ድል ነስቶ፣ ከራሱ አልፎ ለሌሎች ለመትረፍ በቃ፡፡ የድሃ ወንድም እህቶቹ መመኪያና መኩሪያ ሆነ፡፡ በአሁኑ ሰዓት 13 ወላጅ አልባ ህፃናትን እያሳደገ ያስተምራል፡፡ በተለያዩ ችግሮች የተነሳ የከፍተኛ ተቋም ትምህርታቸውን ሊያቋርጡ የደረሱ በርካታ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን በገንዘብ በመደገፍ፣ ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ አድርጓል፡፡
ዶ/ር ኢ/ር ሳሙኤል ዘሚካኤል በሙያው መሃንዲስ ነው፡፡ በ1995 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከቴክኖሎጂ ፋኩልቲ የትምህርት ክፍል የመጀመሪያ ዲግሪውን በሲቪል ኢንጂነሪንግ አገኘ፡፡ ሁለተኛ ዲግሪውን በኮንስትራክሽን ቴክኖሎጂ ማኔጅመንት በ2000 ዓ.ም ከአውስትራሊያ ካምቢራ ዩኒቨርሲቲ፣ ሦስተኛ (ዶክትሬት) ዲግሪውን ደግሞ በአርባን ፕላኒንግ በቅርቡ ከአሜሪካ ሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲ መቀበሉንና ከባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ደግሞ የተባባሪ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ እንደተሰጠው ተናግሯል፡፡ በተጨማሪም “ላይፍ ኮች ኤንድ ሞቲቬሽን ስፒከር” (የሕይወት ጥበብ አሠልጣኝና የሚያነቃቁ ንግግሮች አቅራቢነት) ሥልጠናዎችን በመውሰድ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የመጀመሪያ ዲግሪ (ቢኤ) እንዳለውና በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች በመዘዋወር ስለምህንድስና ትምህርት እንደሚሰጥ ገልጿል፡፡
የአዲስ አድማሱ መንግሥቱ አበበ ከዶ/ር ኢ/ር ሳሙኤል ዘሚካኤል ጋር ያደረገውን ቃለ ምልልስ እንድታነቡ ተጋብዛችኋል፡፡
eng samuel z
ከዩኒቨርሲቲ እንደተመረቅህ የት ነበር ሥራ የጀመርከው?

በጥሩ ውጤት ስለተመረቅሁ የመጀመሪያው ሥራዬ በዩኒቨርሲቲው ቀርቼ ማስተማር ነበር፡፡ ሁለተኛ ሥራዬ በአዲስ አበባ መስተዳድር የመሬትና ግንባታ ጉዳዮችን ማማከር ነበር፡፡ ዎርልድ ቪዥን በተባለው ግብረ ሰናይ ድርጅት፣ በኢንቨስትመንት ቢሮና በተለያዩ ተቋማትም ሠርቻለሁ፡፡

ከመንግሥት ሥራ የለቀከው ለምንድነው?

የመንግሥት ሥራ የለቀኩት በ1998 ዓ.ም ነበር፡፡ ምክንያቴ ደግሞ ሰነፍ ሆኜ ወይም በሌላ ምክንያት ሳይሆን የራሴን ሥራ ለመጀመር ነው፡፡

ያኔ ደሞዝህ ስንት ነበር? የጀመርከውስ ሥራ ምን ነበር?

ከቅጥር ስወጣ ደሞዜ 22ሺ ብር ነበር፡፡ ሥራ የለቀኩት፣ ደሞዝ አነሰኝ ብዬ ሳይሆን፣ በቀሰምኩት እውቀት የራሴን ሥራ ለመጀመር አስቤ ነው፡፡
አፍሪካን ቪዥነሪስ ዴቨሎፕመት ኩባንያን ከጓደኛዬ ጋር በአንድ ሚሊዮን ብር ካፒታል አቋቋምን፡፡ ለሁለት እናቋቁም እንጂ ገንዘቡ የእኔ ነበር፡፡ ይህንን ኩባንያ የመሠረትኩት፣ ራሴን እንደ አፍሪካዊ ባለራዕይ ስለምቆጥር፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ እኔ ካለፍኩ በኋላ የማይቆም (የማይቋረጥ) ኩባንያ እንዲሆን ስለፈለግሁ ነው፡፡ ብዙ ድርጅቶች ባለቤቱ ሲሞት ሕልውናቸው ያቆማል፡፡ የእኔ እንደዚያ እንዲሆን አልፈለግሁም፡፡

ኩባንያው ዘመን ተሻጋሪ እንዲሆን ነው የፈለግኸው?

አዎ! እዚህ በመዲናችን ሂልተን ሆቴል አለ፡፡ በመላው ዓለም በተመሳሳይ ስም የሚጠሩ በርካታ ሂልተን ሆቴሎች አሉ፡፡ ማክዶናልድ፣ በአንድ ሱቅ ነው የጀመረው፡፡ አሁን በመላው ዓለም 36ሺ ቅርንጫፎች አሉት፡፡ ስለዚህ አፍሪካዊ መለያ (ብራንድ) ያለው፣ በተለያዩ የአፍሪካ አገሮች እየተስፋፋ የሚሄድ፣ አፍሪካውያን የግዙፍ ኩባንያ ባለቤት የመሆን አቅም እንዳላቸው የሚያመለክት ድርጅት እንዲሆን በማሰብ የተቋቋመ ድርጅት ነው፡፡

ተሳካልህ ታዲያ? ኩባንያህ አሁን ምን ላይ ደርሷል?

አዎ ተሳክቶልኛል፡፡ ከጠበኩት ፍጥነት በላይ እየተጓዘ ነው፡፡ የቱንም ያህል አድካሚ ቢሆንም ውጤታማ እየሆነ ይገኛል፡፡ እኔ ከተለያዩ ባንኮች ጋር ነው የምሰራው፡፡ መንግስት የቀረፃቸውን አሰሪ ፖሊሲዎች በመጠቀም በስፋት እየተንቀሳቀስኩ ነው፡፡ በነገራችን ላይ በርካታ ብልህ ሰዎች አንድን ስራ ለመስራት ከባንክ ጋር በጥምረት ይሰራሉ፡፡ እኔም ይንንን የስኬታማ ሰዎች መርህን ነው የምከተለው፡፡ ለምሳሌ በአገራችን ኢኮኖሚ ትልቁን ሚና እየተጫወተ የሚገኘው ደርባን ሲሚንቶ ከ360 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጥቶበታል፡፡ ከዚህ ውስጥ ባለሀብቱ ያወጡት 60 ሚሊዮን ዶላሩን ሲሆን ቀሪውን 300 ሚሊዮን ዶላር ግን ከአፍሪካ ልማት ባንክ እና ከሌላ የፋይናንስ ተቋም ነው ያገኙት፡፡ እንደሚታወቀው ባለቤቱ የአለማችን ቢሊየነር ናቸው፡፡ ግን ይህንን የብልሆች መርህ ይከተላሉ እንጂ ያላቸውን ገንዘብ ሁሉ አንድ ፕሮጀክት ላይ አላዋሉም፡፡ እኔም እንደ አቅሚቲ የተከተልኩት ይህንን አለም አቀፍ የኢንተርፕረነሮች መርህን ነው፡፡
የዚሁ ኩባንያ አካል የሆነ የአፍሪካ ቪአይፒ (VIP) ክበብ ከጐረቤታችን ኤርትራና ከሰሜን አፍሪካዊቷ ሞሮኮ በስተቀር በተቀሩት የአፍሪካ አገራትና በአገራችን ዩኒቨርሲቲዎች ተመስርቶ በራሳቸው የሚተማመኑ፣ ቀና አስተሳሰብ ያላቸው ባለራዕይ የዩኒቨርሲቲ ተማሪችንና መምህራንን እያፈራ ይገኛል፡፡

አፍሪካ ቪዝነሪስ ዴቨሎፕመንት ካምፓኒ ምንድነው የሚሠራው?

ይህ ድርጅት በዋናነት ተግባሩ፣ የኮንስትራክሽን ሥራ ይሰራል፡፡ ኮፊ ላንድ ኮፊ የተሠኘ የወጪና ገቢ ንግድ ድርጅታችን፣ የኢትዮጵያን ቡና ወደ ውጭ ይልካል፡፡ ቀደም ሲል ከሌሎች አጋሮች ጋር በኢቴቪ “ባለ ራዕይ” የሚል ቶክሾው ነበረን፡፡ የሚዲያና የሞቲቬሽን ሥራዎች እንሠራለን፣ የአስጐብኚ ድርጅት አለን፡፡ ከሕንድ ኩባንያ ጋር በጆይንት ቬንቸር ጣና ሐይቅ ላይ የሪዞርት ሥራ ጀምረናል፤ በሀዋሳ ሐይቅ ላይም ሪዞርት ለመሥራት ከሚመለከታቸው ኃላፊዎች ጋር በመነጋገር የቦታ ጥናት እያደረግን ነው፡፡
ዴቨሎፕመንት ኢንስቲቲዩቱም ለተለያዩ ግለሰቦችና ድርጅቶች ሥልጠና ይሰጣል፡፡ ሥልጠናው በአብዛኛው በት/ቤት ከሚሰጠው የአካዳሚክ ሥልጠና የተለየ ነው፡፡ አንድ ሰው በዙሪያው ያለውንና በውስጡ የሚገኘውን እምቅ ችሎታና ኃይል እንዲያውቅ፤ እንዲፈትሽ፣ እንዲያይ፣ በውስጡ ያለውን መክሊት አውጥቶ በሚገባ እንዲጠቀም የሚያደርግ፣ ሥልጠና ነው፡፡ በአጠቃላይ አንድ ሰው ከራሱ አልፎ ለሌላው መትረፍ እንደሚችል የሚያግዙትን ሥልጠናዎች እንሰጣለን፡፡
ፍርሃታችንን እንዴት እንገራለን? የሚለው ከማኔጅመንት ሥልጠናዎች አንዱ ነው፡፡ አንዳንድ ሰው የራሱን ሥራ ለመሥራት ወስኖ ሲያበቃ፣ ያለውን ገንዘብ አውጥቶ ቢዝነስ ለመጀመር ይሰጋል፡፡ ሌላው ትዳር ለመያዝ ይፈራል፣ የተለያዩ የፍርሃት መንገዶች አሉ፡፡ ፍርሃት በተወሰነ ደረጃ ሲሆን መጥፎ አይደለም፤ ለጥንቃቄ ይረዳል፡፡ ከልክ ሲያልፍ ግን፣ እጅና እግር አሳስሮና ሽባ አድርጐ ያስቀምጣል፤ በድህነትና በችግር ታስረን እንድንኖር ያደርጋል፡፡ ይህንን ዓይነቱን ፍርሃት የሚያስወግድ ሥልጠና እንሰጣለን፡፡
ሁለተኛው ሥልጠና ሥራ ፈጠራ ወይም ኢንተርፕሪነርሺፕ ነው፡፡ ይህ ሐሳብ ብዙ ጊዜ ለበርካታ ሰዎች ግልጽ አይደለም፡፡ ሥራ መፍጠር ማለት በዙሪያችን ያሉትን ችግሮች መቅረፍ ማለት ነው፡፡ አንዳንድ ሰዎች ገንዘብ አላቸው፡፡ ነገር ግን ገንዘባቸውን እንዴት በአግባቡ መጠቀም እንዳለባቸው አያውቁም፡፡ እኛ ችግራቸውን ተገንዝበን መፍትሔውን ከፈጠርንላቸውና ካሳየናቸው በገንዘባቸው ይገዙናል፤ እኛም በገንዘቡ እንጠቀማለን፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ችግር አለ ወይ? አዎ በሽበሽ ነው፤ ሞልቷል፡፡ ሥራ ለመፍጠር ዕድሎች አሉ ወይ? አዎ በጣም ሞልተዋል፡፡ ሥራ መፍጠር ማለት ይህ ነው፡፡
በነገራችን ላይ ትልልቅ ሕልም ያላቸው ሰዎች፣ ችግሮችን ከማማረር ይልቅ አንዳች ፈታኝ ሁኔታ ሲያጋጥማቸው መፍትሔውን ወደመፈለግ ይሄዳሉ፡፡ ይህም አዲስና ሌላ ተጨማሪ የስራ እድል ይፈጥርላቸዋል፡፡ የትኛውም የሥራ ፈጠራና መፍትሔ የሚመነጨው ከችግር ነው፡፡ እያንዳንዱ ሰው፣ ወደዚህች ዓለም ሲመጣ፣ ችግር መፍቻ መክሊት ወይም መፍትሔ ይዞ ነው የሚመጣው፡፡

ቢል ጌት እንኳን ተወለደ – እሱ በመወለዱ የማይክሮሶፍት ሶፍትዌርን ማግኘት ቻልን!
ስቲቭ ጆብስ እንኳን ተወለደ – እሱ በመወለዱ የአይፎንን ምርቶች ማግኘት ችለናል!
ኼነሪ ፎርድ እንኳን ተወለደ – የሰውን ድካም የሚቀንስ መኪና ፈጥሯልና!
የራይት ብራዘርስ ወንድማማቾች እንኳን ተወለዱ – የእነሱ መምጣት፣ ከአንዱ የዓለም ጥግ ወደ ሌላው የምናደርገውን ጉዞ አሳጥሮልናልና!

የሕክምና የፈጠራ ሰዎች እንኳን ተወለዱ – በእነሱ መወለድ፣ ብዙ ሰዎች ከሕመምና ስቃይ ፈውስ አግኝተዋልና!

አንተ እንኳን ተወለድክ – ሰዎችን የሚያነቃቁ መረጃዎችን በጋዜጣችሁ በማውጣት፣ እኔን ጨምሮ ብዙ ሰዎች ቅዳሜ ቅዳሜ አዲስ አድማስን በናፍቆት እንድንጠብቅ አድርገሃልና!…

እኔ የቱንም ያህል ብማር፣ ከማውቀው ይልቅ የማላውቀው፣ ከደረስኩበት ይልቅ ያልደረስኩበት፣ ከገባኝና ከተረዳሁት ይልቅ ያልገባኝ ይበልጣል፡፡ ምናልባት ኢንጂነር የሚለው ማዕረግ አብሮኝ ስላለ፣ አንዳንዶች ያወቅሁ፣ የተረዳሁ የጨረስኩ ሊመስላቸው ይችላል፡፡ የኢንጂነሪንግ ትምህርት 104 ዘርፎች አሉት፡፡ ቴክስታይል፣ ሌዘር፣ ኬሚካል፣ ዎተር፣ ረዚደንስ፣ ኃይዌይ ወዘተ…ኢንጂነሪንግ የተባሉ ብዙ ዘርፎች አሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ እኔ የማውቀው አንዱን ቁንፅል ዘርፍ ነው – ሲቪል ኢንጂሪንግን፡፡

የበለጠ ለማወቅ ብዙ መረጃዎች መሰብሰብና ማንበብ አለብኝ፡፡ ስለዚህ የእናንተንም ጋዜጣ አነብባለሁ፣ ምክንያቱም አንተ የምታቀርበው የስኬታማ ሰዎች ታሪክ በጣም ያነቃቃኛል፡፡ በዩኒቨርሲቲ ቆይታችን በመጀመሪያ፣ በሁለተኛና በሦስተኛ ዲግሪ ትምህርታችን የምንቀስመው እውቀት 20 በመቶ ነው፡፡ ቀሪውን እውቀት የምንማረው ከሌላ የሕይወት መስክ ነው፡፡ ት/ቤት ገብቶ መማር ጥሩ ነው፡፡ ግን በቂ አይደለም፡፡ ሁል ጊዜ ባለን ላይ መጨመርና ዘወትር ራስን ከዘመኑ እውቀት ጋር ማስማማት (አፕዴት ማድረግ) ያስፈልጋል፡፡ ሙሉ ሰው መሆን የምትችለው ያኔ ነው፡፡ አንተም እንኳን ተወለድክ ያልኩት፣ ሙሉ ሰው ለመሆን ስለረዳኸኝ ነው፡፡

ሥራ እንድንፈጥር የሚያደርገን ቀና አስተሳሰብ (ፖዘቲቭ ቲንኪንግ) ነው፡፡ አንዳንድ ሰዎች “ኢትዮጵያ ውስጥ ከምወለድ፣ አሜሪካ ውስጥ እንስሳ፣ ዛፍ፣…ሆኜ ብወለድ ይሻል ነበር፡፡ እዚያ እንስሳው ይከበራል፣ ዛፉም እንክብካቤ ያገኛል፡፡ እዚህ ግን…” በማለት ያማርራሉ፡፡ እዚህ ያለውን እውነት መቀበል ይቸግራቸዋል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ አብዛኛው ሰው ከመንግስት ይጠብቃል፡፡ ለእኔ ከመንግስት በፊት የሚቀርበኝ አንድ ሰው አለ፡፡ ያም ሰው እኔ ነኝ፡፡ ቀና አስተሳሰብ የምንለው እንዲህ ዓይነት አመለካከት እንዲኖረን የሚያደርግ ነው፡፡

ብዙ ሰው ራዕይ (ቪዥን) የለውም፡፡ ከአምስት ዓመት በኋላ የት እንደሚደርስ አያውቅም፡፡ የዛሬ ዓመት ምን ያህል ገቢ እንደሚኖረው አይረዳም፡፡ ዝም ብሎ በዘልማድ እየኖረ ይመሻል ይነጋል፡፡ የብዙዎቹ ኑሮ ተመሳሳይ ነው፡፡ ለአቅመ አዳም ወይም ለአቅመ ሔዋን መድረስ፣ ከዚያም ማግባት፣ የተገኘውን መስራት፣ ልጅ መውለድ፣ ሲሞቱ በዕድርተኞች ተሸኝቶ መቀበር ነው፡፡ ብዙ መስራትና ታሪክ መፍጠር እየቻለ የዚህ ዓይነት ተራ ህይወት ኖሮ እስከወዲያኛው የሚያሸልበው ሰው በርካታ ነው፡፡ እኔ ሳልፍ ግን ዕድር አያስፈልገኝም፡፡ ምክንያቱም በመሰረትኳቸው ድርጅቶች ውስጥ የተቀጠሩ ብዙ ሺ ሰራተኞች ወጥተው ይሸኙኛል፡፡ የማከናውናቸው ስራዎችም ብዙ አድናቂዎችና ወዳጆች ስለሚፈጥሩልኝ ወደ ማይቀረው ቤቴ የማደርገው ጉዞ አያሳስበኝም፡፡

አንዳንድ ሰዎች ሺ ዓመት ላልኖር ምን ያስጨንቀኛል? ይላሉ፡፡ ግን ከፈለጉ መኖር ይችላሉ፡፡ የምርጫ ጉዳይ ነው፡፡ ላሊበላ ለብዙ መቶ ዓመታት እየኖረ ነው፡፡ ንጉሥ ላሊበላ በሌለበት ዘመን እኛ ስለላሊበላ እያወራን ነው፡፡ አክሱማውያን ስላቆሙት ሐውልት አሁንም እያወራን ነው፡፡ ስለውቅር አብያተ ክርስቲያናት፣ ስለአብርሃ ወአፅብሃ፣ ስለሶፍ ዑመር፣ ዛሬም ይወራል፡፡ እነዚህን ድንቅ የስልጣኔ ናሙናዎች የሰሩ ጠበብቶች ስማቸው ከመቃብር በላይ እየተነሳ ነው፡፡ ለእኔ ሺ ዓመት መኖር ማለት ይሔ ነው፡፡ እንግዲህ ሺ ዓመት መኖርን የሚያስቡ ዜጎችን ለመፍጠር ነው 52 ሥልጠናዎችን የምንሰጠው፡፡

በሚዲያና በምንሰጣቸው ስልጠናዎች የሰው አእምሮ በመለወጥ፤ ስራ ወዳድና ባለራዕይ፣ ባለፈጠራና ቅን አሳቢ … ለመሆን የሚረዱ መጻህፍት ከውጭ እያስመጣን ለዩኒቨርሲቲዎችና ለተለያዩ ድርጅቶች እናከፋፍላለን፡፡
ከዚህ ውጭ በአስጎብኚ (ቱር ኤንድ ኦፕሬተር) ዘርፍ፣ ቱሪስቶችን እጅግ ዘመናዊ በሆኑ ስምንት ቪ 8 መኪኖችና በስድስት ቫን መኪኖች፣ ወደተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎች በመውሰድ እናስጎበኛለን፡፡ በግንባታ ዘርፍም ለምንሰጠው አገልግሎት የሚውሉ የተለያዩ መሳሪያዎችና መኪኖች አሉን፡፡

በምትሰጠው የማነቃቂያ (ሞቲቬሽን) ሥልጠናና በምታደርገው ንግግር የሰው አቀባበል
እንዴት ነው?

እኔ የምሰጣቸው ስልጠናዎች፤ ሰዎች በሚገጥማቸው ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ ተስፋ እንዳይቆርጡ፣ ሌላ የተሻለ ቀን ከፊታቸው እንዳለ እንዲያስቡ፣ የሚያውቋቸው ትልልቅ ስኬታማ ሰዎች ሁሉ እነሱ በነበሩበት ሁኔታ ውስጥ እንዳለፉ፣ እነዚያ ስኬታማ ሰዎች ከእነሱ የሚለዩት፣ ተስፋ የሚያስቆርጡ ነገሮችን ተስፋ በማስቆረጥ፣ ጨክነው በመሻገራቸው ውጤታማ እንደሆኑ … እንዲያውቁ ነው የማደርገው፡፡

ለምሳሌ፤ ዛሬ እኔ የደረስኩበትን በማየት አንዳንድ ተማሪዎቼ እንደ እድለኛ ሊቆጥሩኝ ይችሉ ይሆናል፡፡ በእርግጥም ዕድለኛ ነኝ፡፡ ሆኖም ግን የእኔ ዕድለኛነት ከእነሱ የተለየ አይደለም፡፡ አቃቂ ከተማ ውስጥ በፈረስ ጋሪ የጠዋት ተማሪ ስሆን ከሰዓት፣ የከሠዓት ተማሪ ስሆን ጠዋት እየሰራሁ ነው የተማርኩት፡፡ ሰው ቤት በእረኝነት ተቀጥሬ ከብቶች እየጠበቅሁና እያጠብኩ፣ አዛባቸውን እየጠረግሁ አበሳ አይቼ ነው የተማርኩት፡፡ በማገኘው ገንዘብ መጻሕፍት እገዛለሁ፣ ማንበብ ያለብኝን አነብባለሁ፡፡ እንዲህ አይነት አስቸጋሪ ፈተናዎች፣ በፅናት ተቋቁሜ በማለፍ ነው ዛሬ ለደረስኩበት ደረጃ የበቃሁት፡፡ ሰው ቤት በእረኛነት ተቀጥረህ እየሰራህ የ12ኛ ክፍልን መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተና መውሰድ ይከብዳል፡፡ ነገር ግን የተሻለ ጊዜ ማየት ከፈለግህና ጎዳና ላይ ከመውደቅ እነዚያን አስቸጋሪ የሆኑትን ስራዎች በማከናወን ነገ የበለጠ አስቸጋሪ የሚሆነውን ጊዜ ልትሻገር የምትችልበትን ዕድል ትፈጥራለህ፡፡

አንድ የፈረንጆች አባባል አለ፡፡ Opportunity Plus Preparation = Luck፡፡ ዝግጁነትና አጋጣሚ ሲደመሩ ነው ዕድል የሚባለው፡፡ በዚህ ቀመር መሰረት፣ ሁሉም ሰው ዕድለኛ ነው፡፡ ሥራን ሳይንቅ ለመስራት ዝግጁ ከሆነ የማያሸንፍበት ምንም ምክንያት የለም፡፡

የቀድሞውን የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት የክቡር ግርማ ወ/ጊዮርጊስን የሕይወት ታሪክ በአማርኛና በእንግሊዝኛ አዘጋጅቼ እየተጠናቀቀ ነው፡፡ የእሳቸውን ታሪክ አንዳንድ ሰዎች ያውቃሉ ብዬ እገምታለሁ፡፡ በጣም የሚገርም ታሪክ አላቸው፡፡ 12 ዓመት የቆዩበት ኢዮቤልዩ ቤተመንግስት ሲሰራ፣ በቀን ሰራተኛነት ተቀጥረው 1.50 ማሪያ ትሬዛ እየተከፈላቸው ድንጋይ አንጥፈዋል፤ አሸዋ አቡክተዋል፡፡ ከራሳቸው አንደበት ነው የሰማሁት፡፡ ሸቀጣ ሸቀጥ ነግደዋል፣ ከገጠር ዕንቁላል እየገዙ ከተማ አምጥተው ሸጠዋል፣ አንድ ወር ጨለማ ቤት ታስረው ያውቃሉ፡፡ በአንድ ወቅት ጦር ፍርድ ቤት ቀርበው ለሞት አንድ እርምጃ ሲቀራቸው ነው የተረፉት፡፡ እኚህ የፅናት ምሳሌ የሆኑ ሰው፤ የጥቁሮች የነፃነት ዓርማ እንደሆነች የሚነገርላትና የሰው ልጅ መገኛ የሆነች አገር ርዕሰ ብሄር መሆን የቻሉት፣ የሚያጋጥሟቸውን ችግሮችና ውጣ ውረዶች አልፈው ነው፡፡

እንደሳቸው ያሉ ሰዎችን የሕይወት ታሪክ ከሰማህና ካነበብክ አንተም ተመሳሳይ ችግር ሲመጣብህ፣ የእነሱ ገጠመኝ ትዝ ይልሃል፡፡ ምን ዓይነት አቅም ይሰጥሃል መሰለህ! ተስፋ ቆርጠህ ለየትኛው ጊዜዬ ነው? ብለህ እርግፍ አድርገህ እንዳትተው ያደርግሃል፡፡ ከጨከንክና መከፈል ያለበትን ዋጋ ከከፈልክ ነገ ወደተሻለ ነገር ታልፋለህ፡፡ ይህንን ነው ታሪካቸው የሚናገረው፡፡ ብዙ ትንንሽ ሰዎች’ኮ ናቸው ትልልቅ የሆኑት፡፡ ከእናቱ ማኅፀን ሀብትን፣ እውቀትን ዝናን… ይዞ የመጣ ሰው የለም፡፡

ብዙ የሚያነቃቁ መጻሕፍት ተተርጉመው ገበያ ላይ ውለዋል፡፡ እነዚያን መጻሕፍት የሚያነቡ ሰዎች እምብዛም ሲለወጡ አይታዩም፡፡ ለምን ይሆን? ከአተረጓጎም ስህተት ነው ወይስ ሌላ ምክንያት አለ?

ለዚህ ጥያቄ ብዙ መልሶች አሉ፡፡ መጻህፍቱን አንብበው ለመለወጥ የሚያቅዱ ሰዎች ለእቅዳቸው ታማኝ አይደሉም፡፡ ጠዋት በ12 ሰዓት ብትመጣ እኔን ቢሮ ታገኘኛለህ፣ ማታ በ5 ሰዓት በዚህ ስታልፍ ብታየኝ አለሁ፡፡ የጻፍኩትን መጽሐፍ እኖራለሁ፣ የምኖረውን ነገር እጽፋለሁ፡፡ የስኬት መፃህፍትን የማነበው “ጎበዝ እንባቢ ነው…” ለመባል ሳይሆን፣ ያነበብኩትን በቀጥታ ለመተግበር ነው፡፡ ሁሌም ያነበብኩትን በተግባር እኖረዋለሁ፡፡ ስለዚህ መጻሕፍት ይጠቅሙኛል ማለት ነው፡፡

አንድ ሰው ማለት፣ የተማረው ትምህርት፣ ያነበባቸው መፃህፍት፣ ከሰው ታሪኮች የቀሰማቸው እውቀቶች… ድምር ውጤት ነው፡፡ አንዳንድ ግነት የሚበዛባቸው መጽሐፍት እንዳሉ ይገባኛል፡፡ ጥቂት መጻሕፍት ሲተረጎሙ፣ የእንግሊዝኛውን ትርጉም በትክክል ላያስተላልፉ ይችሉ ይሆናል፡፡ ነገር ግን አብዛኞቹ የተጻፈላቸውን ዓላማና ግብ እንዲመቱ ተደርገው ነው የሚቀርቡት፡፡ ችግሩ ዘርፈ ብዙ ቢሆንም ዋናው ግን የተፃፉትን መጻሕፍት ካነበቡ በኋላ፣ ወደ ህይወት ለመተርጎም አለመድፈር፣ አለመቁረጥ፣ አለመጨከን ነው፡፡ ብዙ ሰው ሀብታም መሆን ይፈልጋል፡፡ ነገር ግን ሀብታሞች የሚከተሉትን የአኗኗር መርህ ለመከተል ፈቃደኛ አይደለም፡፡

የሀብታሞች መርህ ምንድነው?

ብዙ ናቸው፤ ዋነኛው ግን ቁጠባ ነው፡፡ ትንሽ ገንዘብ ሲያገኝ ለዚህም ለዚያም እየጋበዘ ካባከነ፣ ትንሽ ሳንቲም ሲይዝ ሁሉ እያማረው ካጠፋ፣ እንዴት ነው ሀብታም የሚሆነው? መቆጠብና ማጠራቀም ያስፈልጋል፡፡ አቅሙ በሚኖርበት ጊዜ በዓለማችን አለ በሚባለው ሪዞርት ውስጥ ለአንድ ሌሊት ሺ ዶላሮች ከፍለህ ማደር ትችላለህ፡፡ ለሁሉም ጊዜ አለው፡፡ ገበሬውን ብታየው ይሞታታል እንጂ ለዘር ያስቀመጠውን እህል አይበላም፡፡ መነሻ ካፒታል ማለት ዘር ነው፡፡ ብዙ ሰዎች መነሻ የሚሆናቸውን ካፒታል ያገኙና ያጠፉታል፡፡ አንዳንዱ ፍቅረኛውን ለማስደሰት ሲል በይሉኝታ ያባክናል፣ አንዳንዱ ከልማዳዊ የኑሮ ዑደት ጋር በተያያዘ ለ40፣ ለ80፣ ለሙት ዓመት፣ ለሰርግ፣… ሊያውለው ይችላል፡፡ ልማዳዊ ባህል እንደሆነ ይገባኛል፡፡ ሟችን ሲሸኙ ድሆችን መርዳት ያለ ቢሆንም፣ ያለውን ሁሉ አውጥቶ ማባከን የሃይማኖቱ ትምህርት እራሱ የማይደግፍ መሆኑን አባቶች ሲናገሩ እየሰማን ነው፡፡ እነዚህ ልማዳዊ ድርጊቶች ያለንን ጥሪት አሟጠን እንድናጠፋ፣ ጊዜያችንን እንድናባክን ያደርጉናል፡፡

ሌላው ችግር ብዙ ሰው በትንሽ ነገር ይረካል፡፡ በትንሽ ነገር መርካት አያስፈልግም፡፡ እኔ በትንሽ ነገር አልረካም፡፡ ብልጽግና፣ ትልቅነት፣ አሸናፊነት ይገባኛል፡፡ በዓላማ ነው ወደዚች ዓለም የመጣሁት፡፡ ከራሴ አልፌ ለሌሎች መትረፍ ይገባኛል… ብዬ ውስጤን አሳምኜዋለሁ፡፡ የእኔ ወላጆች እንዲህ አምነው ቢሰሩ ኖሮ፣ ያሳለፍኩት ውጣ ውረድ አይገጥመኝም ነበር፡፡ በእኔ የትውልድ ሃረግ፣ ከአሁን በኋላ ድህነት እንደማይኖር እርግጠኛ ነኝ፡፡ አንደኛ ልጆች ስወልድ አባካኝ እንዳይሆኑና የስራ ሰው እንዲሆኑ ኮትኩቼ ነው የማሳድገው፡፡ ሁለተኛ፤ አባት ያቆየላቸውንና ሕይወታቸውን የሚለውጡበት ዘር ወይም እርሾ ያገኛሉ፡፡ የብዙዎቹ ሰዎች ችግር ይህንን አለማግኘት ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡

አዋዋልም ወሳኝ ነው፡፡ የአገሬ ሰዎች “አዋዋልህን ንገረኝና ማንነትህን እነግርሃለሁ” የሚል አባባል አላቸው፡፡ እኔ ሕይወትን በትግል ካሸነፉ ሰዎች ጋር እንጂ አሉታዊ አስተሳሰብ ካላቸው ሰዎች ጋር አልውልም፡፡ ምክንያቱም እምነቴን፣ ራዕዬንና ዕቅዴን እንዲያበላሹብኝ አልፈልግም፡፡ ሰው ውሎውን ነው የሚመስለው፡፡ እኔ የምውላቸው ሰዎች በአንድ የልብስ ስፌት መኪና ተነስተው ከ3ሺ ሰራተኛ በላይ መቅጠር ከቻሉ የጋርመንት፣ ሪልእስቴትና የሆቴል ባለቤቶች ጋር ነው፡፡ ከጣራ ጠጋኝነትና ከቀለም ቀቢነት ተነስተው ለ6,200 ዜጎች የስራ እድል መፍጠር ከቻሉ ሰው ጋር ነው የምውለው፡፡ ድሮ አንድ ጫማ እንደቡታጋዝ ክሮቹን እየቀየሩ ሶስት ዓመት ያደርጉ የነበሩ ሰው፣ በሚሊዮን ብሮች አምረው በተሰሩ ቤቶች ውስጥ ከሚኖሩ፣ ሶስትና አራት ሚሊዮን ብር ታክስ የሚከፈልባቸው መኪኖች ከሚያሽከረክሩ ሰዎች ጋር ነው የምውለው፡፡ አብሬአቸው ስውል የየዕለቱን የስራ ዲሲፒሊን፣ የገንዘብ አጠቃቀማቸውን፣ የሰራተኛ አያያዛቸውን፤… ዩኒቨርሲቲ ከምማረው በላይ ከእነሱ በቀጥታ የምቀስመው ነገር አለ ማለት ነው፡፡

እነዚህ ሰዎች ዛሬም ድረስ ተግተው የሚሰሩት ራዕያቸውን ለማስፈጸም እንጂ ለምግባቸውና ለልብሳቸው አይደለም፤ ለዚያማ ያላቸው በቂ ነው፡፡ ነገር ግን እንቅልፍ የማያስወስድ ራዕይ አላቸው፡፡ ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች የመትረፍ ሕልም አላቸው፡፡ ይህ ራዕይ፣ የእኔም ራዕይ ነው፡፡ ለእንጀራና ለምግብ ቢሆን፣ ስራ ለቅቄ ስወጣ የወር ደሞዜ 22ሺ ብር ነበር፡፡ እኔን በምቾት ለማኖር በቂ ነበር፡፡ ከስራ ስወጣ የከፈልኩት ዋጋ አለ፡፡ የተሰጠኝ መኪና ነበረኝ፤ ያንን ትቼ ታክሲ መጋፋት ጀመርኩ፣ ዝናብ ደብድቦኝ እቤት ስገባ ራዕዬ ያልታያቸው፣ ህልሜ ያልገባቸው እናት፣ እህትና ጉረቤቶቼ “እሰይ ይበልህ! ድሎት አስጠልቶህ የመረጥከው ሕይወት ነው፤…” ይሉኝ ነበር፡፡ ያኔ “ተሳሳትኩ እንዴ? ተመልሼ ልግባ?” የሚል ሃሳብ አልመጣልኝም ግን በውስጥህ የሚንቦገቦገው ህልም፣ ከፊት ለፊትህ የታየህን ራዕይ ለመጨበጥ እንድትቆርጥ፣ እንድትጨክን ያደርግሃል፡፡

ራዕይ እንዴት ይገለፃል?

ራዕይ ለሌሎች የማይታይ ነገር ማየት ማለት ነው፡፡ አዎ ለሌሎች የማይታየው ላንተ ቁልጭ ብሎ ይታይሃል፡፡

ኼነሪ ፎርድ፤ ዘመዶቹ፣ አክስት፣ አጎትና ጎረቤቶቹ፣…. በቅሎ፣ ፈረስ፣ አህያ… ሲጠቀሙ እሱ ዘመዶቹ ያልታያቸው መኪና ነበር የታየው፡፡ ይህ ነው ራዕይ፤ ሌሎች አይቻልም ያሉትን ይቻላል ብሎ ማድረግ፣ ሌሎች አይቻልም ብለው ፈርተው ያፈገፈጉበትን ይቻላል ማለት፣ ደፍሮ መግባት… ማለት ነው ራዕይ፡፡

ራዕይን በተመለከተ እኔ የምጠቀምበት አንድ መርህ አለኝ “ራዕይ ማለት የሚታትሩለት ብቻ ሳይሆን አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ የሚሞቱለት ጭምር ነው” የሚል፡፡ ልትሞትለት የተዘጋጀህለትን ራዕይ ለማሳካት እንቅልፍ ብታጣ ትልቅ ነገር አይደለም፡፡ ምክንያቱም ልትሞትለት’ኮ ተዘጋጅተሃል፡፡ ለመሞት የተዘጋጀህለትን ለማሳካት በምታደርገው እንቅስቃሴ ውስጥ የሚገጥምህ ውጣ ውረድ ከሞት ስለማይበልጥ፣ ችግሮቹን መቋቋምና መጋፈጥ አይከብድም፡፡

ራዕይን ለማሳካት መንገዱ ሁሉ አልጋ በአልጋ አይደለም፡፡ ሕይወት ራሱ’ኮ ያስተምረናል፡፡ ስንወለድ በእናታችን እቅፍ ውስጥ ነበርን፡፡ ከዚያ ዳዴ ማለት ብንጀምርም ወዲያው መራመድ አልቻልንም፡፡ ጠረጴዛ ይዘን እየወደቅንና እየተነሳን ደግሞ እየቆምን፣ የእናትን እጅ ይዘን እየተራመድንና እየወደቅን፣ በኋላ ደግሞ እየጠነከርን፣ …. ነው ያደግነው፡፡ እኔ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የማውቃቸው ስኬታማ ትልልቅ ሰዎች በሙሉ ያልወደቁ አይደሉም፤ ወድቀው የተነሱ ናቸው፡፡ ያልተፈተኑ አይደሉም፤ እንደወርቅ በእሳት ውስጥ አልፈው ተፈትነው ነጥረው የወጡ ናቸው፡፡ እጅህ ላይ ያለውን ወርቅ፤ “ምን ሆነህ ነው እንዲህ ያማረብህ? ዋጋህስ ከሌሎች ማእድናት ውድ የሆነው ለምንድነው?” ብለህ ብትጠይቀው “በእሳት ውስጥ ተፈትኜ ስላለፍኩ ነው” ይልሃል፡፡ በፈተና ውስጥ ማለፍ ዋጋ ይጨምራል ማለት ነው፡፡

ራዕይህን እንዳታሳካ አንዳንድ ነገሮች ሊያዘገዩህ ይችላሉ፡፡ የተወሰነ ወቅት ላይ ለስራ የማያመቹ ፖሊሲዎች፣ የብድር ማጣት፣ ሰው ሰራሽ አደጋዎች፣ የፋይናንስ እጥረት… ሊያዘገዩህ ይችላሉ፡፡ ወዲው መፍትሄ ስለምትፈልግለት ከግብህ ግን ሊያስቀሩህ አይችሉም፡፡ ይህንን ነገር ነው እንግዲህ ለተማሪዎቻችን የምንነግረው፡፡ ባለፉት ሶስት ዓመታት ውስጥ ከ32 ዩኒቨርሲቲዎች በ27ቱ ከአንድ እስከ ሶስት ሳምንታት፣ ለዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቶች፣ ለመምህራን፣ ለአስተዳደር ሰራተኞችና ለተማሪዎች ያለምንም ክፍያ ሥልጠና ሰጥቻለሁ፡፡ እውቀቴን በጂዲፒ ፕሮግራሙ በማካፈል፣ የዜግነት ድርሻዬን በመወጣት ጥሩ ምሳሌ መሆን እፈልጋለሁ፡፡ ለምሳሌ በአሁኑ ሰዓት ኬንያ በሚገኘው ናይሮቢ ናሽናል ኤይር ወይስ አምስት መቶ አርባ ሺህ ብር ከፍዬ የፓይለቲንግ ትምህርት እየተማርኩ ነው፡፡ ሳጠናቀቅ የግል ጀት የማብረሪያ ላይሰንስ (ፈቃድ) ይኖረኛል፡፡ በቀጣይም የግል ጀት እንደሚኖረኝ አምናለሁ፡፡ አየህ በዚህ ሁሉ ለተማሪዎቼ ምሳሌ ለመሆን እየጣርኩ ነው፡፡

በዚህ ስልጠና አንዳንድ ፈታኝ ሁኔታዎች ገጥሟቸው ትምህርታቸው ሊያቋርጡ የደረሱ ተማሪች፣ ለካንስ እንዲህ ነው ወይ? ብለው ጨክነው እንዲማሩ ያደርጋቸዋል፡፡ በዚህ አይነት በየዩኒቨርሲቲዎቹ የአፍሪካ ቪአይፒ ክለብ አቋቁሜአለሁ፡፡ ይኼ የአፍሪካ ባለራዕዮች ክለብ ነው፡፡ በሚቀጥሉት 10 ዓመታት አንድ ሚሊዮን የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ለማፍራት እየሰራሁ ነው፡፡

ተማሪዎቼ ራሳቸውን በጣም አስፈላጊ ሰው አድርገው ነው የሚቆጥሩት፡፡ ከተመረቁ በኋላ እንደ ሰንሻይን ኮንስትራክሽን ባለቤት እንደ አቶ ሳሙኤል 6,200 ሰራተኞች፣ እንደግሪን ኮፊ ባለቤት እንደ አቶ ታደለ አብርሃ 13ሺ ሰራተኞች፣ እንደ ኖክ ኩባንያ ስራ አስፈፃሚ እንደ አቶ ታደሰ ካሳና በአጋሮቻቸው እንደተቋቋመው የንግድ ድርጅት 15ሺ ሠራተኛ… መቅጠር ባይችሉም፣ እያንዳንዳቸው 100 ሰው መቅጠር ቢችሉ፣ ከ19 ዓመት በኋላ የእኔ ተማሪዎች ለ70 ሚሊዮን ዜጎች የሥራ ዕድል ይፈጥራሉ፡፡ ስለዚህ፣ አሁን ወገኖቼ ወደ ሱዳን የሚሰደዱባቸው መንገዶች፣ ሌሎች በመኪኖች ተሳፍረው ለስራ ፍለጋ ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡባቸው ጎዳናዎች ይሆናሉ፡፡ ይህ ነው ራዕይና ግቤ፡፡ ይህ ምኞች ሳይሆን ራዕይ ነው፡፡ በምኞትና በራዕይ መካከል ትልቅ ልዩነት አለ፡፡ ራዕይ የሚታይና የሚጨበጥ እውነት ነው፡፡
አፍሪካ ቪዥነሪስ ዴቨሎፕመንት ካምፓኒ በአሁኑ ወቅት ለ144 ቋሚ ሰራተኞች ለ 122 ጊዜያዊ ሰራተኞች በአጠቃላይ ለ 246 ዜጎች የሥራ ዕድል ፈጥሯል፡፡ ካፒታሉም ወደ መቶ ሚሊየን ብር እየተጠጋ ይገኛል፡፡ በቀጣይም በሌሎች ዘርፎች ለመሰማራት እየተንቀሳቀስን እንገኛለን፡፡
ዶ/ር ኢ/ር ሳሙኤል ለዛሬው ማንነቱ ያበቁት ሰዎች ባለውለታዬ ናቸው ይላል፡፡ የመጀመሪያዋ ድሃም ቢሆኑ ከልጅነት አንስቶ ጥሩ ሰብእና እንዲኖረው በስነ ምግባር ቀርፀው ያሳደጉትን እናቱን ወ/ሮ እኔቱ ወርቅነህ ናቸው፡፡ የእንጀራ ልጅ ነው ሳይሉ እንደወለዱት ልጅ ያሳደጉትን 12ኛ ክፍል ወድቆ ዝዋይ ሄዶ ሲማር ከፍተኛ ድጋፍ ያደረጉለትን ለአባቱ ለአቶ ዘሚካኤል ኃ/ኢየሱስ ከፍተኛ አክብሮት እንዳለው ገልጿል፡፡ በሮል ሞዴልነት ለቀረፀው ለኢ/ር ኤርሚያስ አሰፋና ነገሮችን ሁሉ ላሳካለት ለእግዚአብሔር ከፍ ያለ ምስጋናውን አቅርቧል፡፡
መቅድም

ከሁሉ በማስቀደም ይህንን መፅሐፍ ማዘጋጀት የምችልበትን እድል በማግኘቴ የተሠማኝን ወደር የለሽ ደስታ ለመግለፅ እወዳለሁ፡፡ በእርግጥም ከትንሽ ነገር ተነስቶ ትልቅ ደረጃ መድረስ እንደሚቻል በተግባር ያተረጋገጠ ጀግናን የህይወት ተሞክሮ የሚተርክ መፅሐፍን አዘጋጅቶ ማሳተም በራሱ ልብን በሐሴት ይሞላል፡፡ በተለይ እንባቢ እጅ ገብቶ እንዲህ ሚሊዮኖችን ለመልካም ሥራ ሲያነሳሳ ከመመልከት በላይ የሚያረካ ነገር የለም፡፡ የዚህ ታሪክ ባለቤት የሆኑት ክቡር ግርማ ወ/ጊርጊስ በጎ ተፅዕኖ ካሳረፉብኝ በጣት ከሚቆጠሩ ጥቂት ስኬታማ ሰዎች መካካል አንዱ ናቸው፡፡ ከታሪክ መዛግብት እንደተረዳሁት፣ ከአብሮ አደግ ጓደኞቻቸው እና በቅርብ ከሚያውቋቸው ወዳጆቻቸው እንዲሁም ረጅም ጊዜን አብረዋቸው ካሳለፉት ከስራ ባልደረቦቻቸው ምስክርነት እንደተገነዘብኩት ከሁሉ በላይ ደግሞ በአካል ቀርቤ እንዳረጋገጥኩት በእርግጥም የክቡርነታቸው የህይወት ተሞክሮ በአስገራሚ እና የትኛውንም ሰው የማነቃቃት ኃይል ባላቸው ገጠመኞች የተሞላ ነው፡ እኔ በበኩሌ ከፅናታቸው ፅናትን ተምሬያለሁ፡፡ ባስመዘገቧቸው ድሎች እና እጅግ በሚያስደምመው ስኬታቸው ብዙ ጊዜ ተነቃቅቻለሁ፡፡ አሁን ደግሞ ተራው ያንተ ነው፡፡ ከርሳቸው ገድለ ታሪክ ብዙ ነገር እንደምትማርበት አምናለሁ፡፡ ይህንን መፅሐፍ ለማዘጋጀት የተነሳውበትም ዋነኛ ዓላማ የርሳቸውን ፈለግ የሚከተሉ ዜጎችን ለማፍራት ነው፡፡ ትዝ ይለኛል ከቀደሞው የኢፌድሪ ፕሬዝዳንት ክቡር ግራማ ወልደ ጊዮርጊስ ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ በአካል የተዋወኳቸው ከዛሬ አስር ዓመት በፊት ነው፡፡ በወቅቱ የአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ቴክኖሎጂ ፋካሊቲ ተማሪ እና የተቋሙ ተማሪዎች ህብረት ፕሬዝዳንት ነበርኩ፡፡

መንግስትም ያን ጊዜ ከወጣቱ ይልቁንም ከዩንቨርስቲ ተማሪ ጋር ተቀራርቦ የመስራት ፍላጎት ስለነበረው በተደረገልን ጥሪ እና በተያዘልን ቀጠሮ መሰረት የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር አቶ መለስ ዜናዊን ጨምሮ ሌሎች የሚመለከታቸው ባለ ድርሻ አካላት በታደሙበት ልዩ ፕሮግራም ላይ በብሔራዊ ቤተመንግስት ተገናኝን፡፡ እንግዲህ ከእዚያ የሚጀምረው የእኔና የእርሳቸው ትውውቅ ስር ሰዶ ዛሬ ላይ ደርሷል፡፡ በተለይ ባለፉት ሰባት አመታት የጠበቀ ጥሩ ቅርርቦሽ ነበረን፡፡ እንደ ጌታ እና ሎሌ ሳይሆን እንደ አባት እና ልጅ እየተመካከርን በርካታ ወገኖችን የሚጠቅሙ ስራዎችን ሰርተናል፡፡ ምንጊዜም ቢሆን ካላቸው የካበተ የሥራ ልምድ በመነሳት የሚያካፍሉኝ ገንቢ ሓሳብ ከብረት ይልቅ ብርቱ እና ጠንካራ እንድሆን አድርጎኛል፡፡ በዛ ላይ እንደ ወርቅ ተፈትኖ ነጥሮ የወጣው አስገራሚ የህይወት ተሞክሯቸው እና ጥልቅ የሆነው እውቀታቸው በራሱ መሳጭ እና ለላቀ ስራ የሚያነሳሳ በመሆኑ ሁልጊዜም ቢሆን እርሳቸውን ማግኘትም ሆነ ከእርሳቸው ጋር መስራት ያስደስተኛል፡፡ ጥናታዊ መረጃዎች እንደሚያረጋግጡት ብዙ ትልልቅ ሰዎች በአንድ ወቅት ትንንሽ እና ታናናሽ ነበሩ፡፡ ይሁንና ግን በዚያ የብላቴናነት እድሜያቸው በዚያች ሚጢጢዬ ልባቸው ውስጥ ትልልቅ ህልም ነበራቸው፡፡ ያንን የልጅነት ህልማቸውንም እውን ለማድረግ መክፈል ያለባቸውን ዋጋ ሁሉ ለመክፈል የጨከኑ እና የቆረጡ ስለሆኑ ያስቡትን ከማሳካት ያገዳቸው የተመኙትንም ከመሆን ያስቀራቸው ነገር የለም፡፡ ከእነዚህ ከትንሽ ነገር ተነስቶ ትልቅ ደረጃ መድረስ እንደሚቻል በተግባር ካረጋገጡ ህያው ምስክሮች መካከል አንዱ ክቡር ግርማ ወልደ ጊዩርጊስ ናቸው፡፡

በአፍሪካ በህዝብ ብዛቷ ሁለተኛ የሆነችን ታላቅ አገር በርዕስ ብሔርነት ለ 12 ዓመታት የመሩት እኚህ ሰው በእርግጥም ዘንድሮ ሳይሆን ድሮ ትንሽ ሰው ነበሩ፡፡ ትንሽ!!! እኚህ ሰው መራብንም መጠማትንም ያውቃሉ፡፡ ምንም እንኳ የአገሪቱ ርእሰ ብሔር እስከመሆን ቢደርሱም አንድ ወቅት ግን እጅግ ዝቅ ብለው ሥራ ሳይንቁ በቀን ሰራተኝነት ተቀጥረው የሰሩ ሰው ነበሩ፡፡ እናም ከትናንት እስከ ዛሬ ህይወታቸው በይቻላል ባይነት መንፈስ የተሞላ እና በራስ የመተማመን መንፈስ የተቃኘ በመሆኑ ከታች ተነስተው እላይ ቢደርሱ አይገርምም፡፡

የያኔው ትንሹ ግርማ ትንሽ ሆኖ አልቀረም፡፡ ይልቁንስ ከራሱ አልፎ ለሌሎች ይተርፍ ዘንደ ሌሊትና ቀን ሲተጋ ኖረ፡፡ ተሳካለትም፡፡ ቀን አልፎ ቀን ሲተካ የእርሱም ህይወት እያደር እየተለወጠ እለት እለትም እኗኗር እየተቀየረ መጣ፡፡ ቀስ በቀስም ያ ትንሹ ልጅ ኑሮን ታግሎ በማሸነፍ የተደነቀ እና የተከበረ ሰው ሆነ፡፡ አሁን እኔ እንግዲህ ያዘጋጀሁት የዚህን ጀግና ገድለ ታሪክ ነው፡፡ ናፍቆቴ ከመሳጭ ታሪኩ ቁም ነገርን ቀስመህ አንተም ሌላ ታሪክ ሰሪ እንድትሆን ነው! ጋሽ ግርማ ይህንን መፅሐፍ በማዘጋጅበት ሂደት የህይወት ተሞክራቸውን ሲያካፍሉኝ እያንዳንዱ ገጠመኛቸው የሚያስደንቀኝ ከመሆኑ ባሻገር የማስታወስ ችሎታቸው ያስገርመኝ ነበር፡፡ እያንዳንዷን ክስተት እና ያሳለፉትን ነገር ሁሉ ከእነ ቀኑ ብቻ ሳይሆን እለቱን እና ሰዓቱን ጭምር በቀላሉ በማስታወስ ያለምንም የሐሳብ መደነቃቀፍ ነበር የሚተርኩልኝ፡፡ ቦታና የሰው ስምም ቢሆን በፍፁም አይጠፋቸውም፡፡ እያንዳንዱን ነገር ዛሬ እና አሁን እንደተደረገ ድርጊት በቀላሉ ሲገልፁ ግርምትን ያጭራሉ፡፡ በዛ ላይ ቁም ነገሩን በቀልድ እያዋዙ ስለሚናገሩ የአድማጭን ቀልብ በቀላሉ ሰቅዘው ይይዛሉ፡፡ እውነት ነው ጋሽ ግርማ ጨዋታ አዋቂ ናቸው፡፡ አይሰለቼ የሆነው ታሪካቸውን ሲያስከመኩሙ አፍ ያስከፍታሉ፡፡ ተስፋ አደርጋለሁ አንባቢም ተመሳሳይ ስሜት እንደሚሰማው፡፡ እኔ በበኩሌ በመኖሪያ ቤታቸው /Semi-palace/ በሚገኘው ቢሮአቸው ይህን መሳጭ ታሪካቸውን እየኮመኮምኩ አያሌ ቀናትን ሳሳልፍ በውስጤ ይፈጠር የነበረው አይነት መነቃቃት በአንባቢዬ ላይ እንደሚፈጠር አምናለሁ፡፡ በዛ ላይ በጨዋታችን መካከል ያልተነሳ ጉዳይ የለም፡፡ እርግጥ ነው ከአገር ደህንነት አኳያ መገለፅ ከሌለባቸው ጉዳዮች በቀር በወጋችን ያልተዳሰሱ ነጥቦች የሉም፡፡ ክቡርነታቸው በርዕዮት ዓለም እና በሚያራምዱት ፓለቲካዊ ፍልስፍና ወይም አይዶሎጂ የተነሳ ፍፁም ተቃራኒ በሆኑ ሶስት መንግስታት ውስጥ በከፍተኛ ኃላፊነት ሰርተዋል፡፡ ሆኖም ከጨቋኝ ገዢዎች እና ከአምባገነን መሪዎች ጋር ወግነው ህዝብን ያስመረሩበት አጋጣሚ የለም፡፡

ከሶስት መንግስታት ጋር መስራታቸው በራሱ የህዘብ ልጅ ለመሆናቸው በቂ ማሳያ ነው፡፡ እውነታው ይሄ ባይሆንማ ኖሮ እኮ በሶስቱም ዘመነ መንግስታት ህዝቡ በከፍተኛ ድጋፍ እና በሙሉ ይሁንታ መርጦ እንደራሴው አያደርጋቸውም ነበር፡፡ የሆነው ግን ይሄ ነው፡፡ እናም እምነት ጥሎ ድምፁን ለሰጣቸው ህዝብ ሲታገሉ ኖረዋል፡፡ እንደማንኛውም የአገሬ እና የወገኔ ጉዳይ ያገባኛል ብሎ ቆርጦ እንደተነሳ ባለ ራዕይ ወጣት ለህዝብ ጥቅም እና ለአገር ልማት መከፈል ያለበትን ዋጋ ሁሉ ከፍለዋል፡፡ ብዙዎችን ከአላማቸው አጨናግፎ ከመስመር ያስወጣቸው ራስ ወዳድነት እርሳቸውን የማንበርከክ ጉልበት አልነበረውም፡፡ በተለያየ አጋጣሚ ፅኑ አቋማቸውን የሚፈታተን መደለያ ቢቀርብላቸውም አንድም ቀን የግል ጥቅማቸውን አስቀድመው አገራቸውን እና ህዝባቸውን ለድርድር አቅርበው አያውቁም፡፡

በሰሩባቸው መንግስታዊ በሆኑና ባልሆኑ መስሪያ ቤቶች የሚገኙ የግል ማህደሮቻቸውም የሚመስክሩት ይህንኑ ሀቅ ነው፡፡ እንዲያውም በስራ ባሳለፉባቸው ረጅም አመታት ያበረከቱትን ጉልህ አስተዋፅዎ የተመለከቱ በርካታ ተቋማት በተለያየ ጊዜ ልዩ ልዩ ሽልማቶችን አበርክተውላቸዋል፡፡ በቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ ዘመነ መንግስት ከንጉሰ ነገስቱ እጅ ከፍተኛ የክብር ኒሻን ከተሸለሙ ጥቂት ኢትዮጵያውያን መካከልም አንዱ ናቸው፡፡ በብዙ ውጣ ውረድ ውስጥ አልፈው ያስመዘገቡትን ዘርፈ ብዙ ስኬት የተገነዘቡ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ለሰራቸው ስራዎች እውቅና በመስጠት አድናቆታቸውን ከአክብሮት ጋር ገልፀውላቸዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር ክቡርነታቸው ሶስት የክብር ዶክትሬት ዲግሪዎችን ተቀብለዋል፡፡ እርሳቸው አንድም ብዙም ናቸው፡፡ ጋሽ ግርማ ያለ አንዳች ግነት ያልተሳተፉበት የስራ ዘረፍ የለም ማለት ይቻላል፡፡ ያሁኑ ሳይሆን የያኔው ትንሹ ግርማ የሸክም ስራ ሰርቶ ያውቃል፡፡ ባይገርማቸሁ ንግድን አሀዱ ብሎ የጀመረው ደግሞ እንቁላል በመሸጥ ነው፡፡ ደሞ ሌላ ጊዜ አንድ ጣልያናዊ ጋር በቀን ሠራተኝነት ተቀጥሮ ነበር፡፡ እኔ ከሁሉም በላይ የሚደንቀኝ ደግሞ በድንጋይ ጠራቢንት ፤ በአሸዋ አንጣፊነት እና በወለል ገንቢነት በዚያ ለጋ እድሜው ተቀጥሮ የሰራው ቤተመንግስት መሆኑ ነው፡፡ ታድያ ይህ ብላቴና ከአመታት በኋላ ርዕሰ ብሔር ሆኖ ዳግመኛ በዚያው ቤተ መንግስት ይኖራል ብሎ ማን ያስባል? በብዙዎች ዘንድ እዚህ ግባ በማይባል ዝቅተኛ የስራ መስክ ላይ የተሰማራ አንድ ቀን ሰራተኛ እዚህ ይደርሳል ብሎስ ማን ይገምታል? ያ ልጅ እንደ ተራ ሰው በሚቆጠርበት ስፍራ ታሪክ ተለውጦ ነገር ተገልብጦ የተለየ የክብርን ሥፍራ ያገኛል ብሎስ ማን ይጠረጥራል? በዛ ላይ ስልጣኑ የተገኘው እኮ በኃይል አይደለም፡፡ የአገሬ የዘመናት እውነታ እንደነበረው በደም መፋሰስ ወይም በተንኮል የተገኘም አልነበረም፡፡ እኔ እስከገባኝ ድረስ ሹመቱ የተገኘው በብቃት ነው፡፡ በብቃት፡፡
ለመሆኑ የዚያ የትንሹ ልጅ እና የእዚህ የትልቁ ሰው የስኬት ምስጢር ምንድን ነው? ከትቢያ ላይ ተነስቶ የሰው ልጅ መገኛ እና የጥቁር ህዝቦች የነፃነት አርማ የሆነች አገርን እስከ መምራት የደረሰው እንዴት ነው? እኔ በበኩሌ ገና ከ 10 ዓመቱ ጀምሮ አገሩን በታማኝነት አገልግሎ ከበቂ በላይ የዜግነት ድርሻውን እንደተወጣ ይሰማኛል፡፡ እውነት ነው በርዕስ ብሔርነት ባሳለፉባቸው ዓመታትም በደል የደረሰባቸው እና ፍትህ የተነፈጉ ዜጎችን ተቀብለው በማስተናድ ከህዝብ የተጣለባቸውን ኃላፊነት በብቃት ተወተዋል፡፡ በቅርበት እስከማውቀው ድረስ ቢሮአቸው ለማኛውም ባለጉዳይ ክፍት ነበር፡፡
ማንም እንደሚመሰክረው ዘመናቸውን ሁሉ ያሳለፉት የአገርን እና የህዝብን ጥቅም በሚያስጠብቁ ጉዳዮች ላይ ነው፡፡ እነዚያ ያሳለፏቸውን አመታት ዛሬ ላይ ሆነው ሲያስታውሷቸው በእጅጉ እደሚደነቁ አጫውተውኛል፡፡ ባስመዘገቧቸው ተደራራቢ ስኬቶችና በተጎናፀፏቸው ድሎች መንፈሳዊ ኩራት እንደሚሰማቸው ጭምር ነግረውኛል፡፡ በአንፃሩም አንዳንድ አሳዛኝ እና የሚቆጩባቸውን ገጠመኞቻቸውንም ሳይነግሩኝ አላለፉም፡፡ በቅርቡ ዘጠና አመት ሞልቷቸው የልደት በዓላቸውን ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት፣ የወዳጅ አገር አምባሳደሮች፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ አድናቂዎቻቸው እና ጓደኞቻቸው በተገኙበት ከቤተሰቦቻቸው ጋር በድምቀት ያከበሩት ክቡርነታቸው እዚህ እድሜ ላይ ደርሰው እንኳ ትንሽ ልረፍ ሳይሉ አሁንም ድረስ በርካታ ስራዎችን እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ያለው የሻከረ ግንኙነት እንዲፈታ የጀመሩትን የሰላም ጥረት እያቀላጠፏት ነው፡፡ ከድንበር ይገባኛል ጥያቄ ባሻገር ያለውን እንቆቅልሽ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመፍታት ከሚከለከታቸው አካላት ጋር በትብብር በመስራት ላይ ናቸው፡፡ ለመሆኑ ይህ የሰላም ጥረት ምን ደረጃ ላይ ደርሷል? ኤርትራውያንንስ እንዴት ይገጧቸዋል? ሲጀመር የችግሩ ዋነኛ ምንጭስ ምንድን ነው?

እንደሚታወቀው ኤርትራ እና ኢትዮጵያ በንጉሱ ዘመን በፌዴሬሽን ተጣምረው ይኖሩ ነበር፡፡ ይሁንና ግን ብዙም ሳይቆይ ይህ የጋራ መርህ ተጥሶ ያስተሳስራቸው ሰንሰለት ተበጣጠሰ፡፡ በዚህ ድንገተኛ ውሳኔ ያልተደሰቱ ወገኖች ነፍጥ አንስተው ሸፈቱ፡፡ ሌሎችም የመገንጠልን ዜማ እያቀነቀኑ ተቀላቀሏቸው፡፡ ትግሉም በዚህ መልኩ ተቀጣጥሎ የአንድ አገር ህዝቦች እርስ በእርሳቸው ለዘመናት ተላለቁ፡፡ ክቡርነታቸው ከዚህ ክስተት ጋር በተያያዘ የሚሉት ነገር አላቸው፡፡ ስለምን ንጉሱ ፊዴሬሽኑ እንደበተኑ ያጫውቱናል፡፡ የቀዳማዊ አፄ ኃይለስላሴ ውሳኔንም “ታላቅ ስህተት” ብለው ይገልፁታል፡፡ ለምን? ስለዚህ ነገር ብዙ ብዙ ያወጉናል፡፡

በአንፃሩም እንደ ሰም እቅልጦ እንደ ገል ቀጥቅጦ 17 አመት ረግጦ ስለገዛን ስለ ደርግ እና ስለ ዋናው ሰውዬ ስለ ጓድ መንግስቱ ኃይለማርያ የሚያጫውቱን ነገር አላቸው፡፡ በተለይ በኤርትራ ስላሳለፏቸው ሁለት አስርት አመታት ይተርኩልናል፡፡ በነገራች ላይ ስለ ኤርትራዊያን ተናግረው አይጠግቡም፡፡ ስለዚያ ህዝብ ቅንነት እና ደግነት መስክረው አይረኩም፡፡ እነዚህ ከአንድ አብራክ እንደተወለዱ መንትያ ልጆች ከአንዲት ጥንታዊት አገር የፈለቁት ሁለቱ ህዝቦች አሁን ተለያይተው እና የቅርብ ሩቅ ሆነው ቢኖሩም እንኳ አንድ ቀን በመካከላቸው ያለውን ጠብ አብርደው እና እርቅ አውርደው ሠላማዊ ጉርብትና ይመሰርታሉ የሚል ፅኑ እምነት ስላላቸው የሁለቱን አገሮች እንቆቅልሽ ለመፍታት ዛሬም ድረስ እያደረጉ ያሉትን ጥረት ክቡርነታቸው ያጫውቱናል፡፡ በአንፃሩም ይበጃል ብለው የሚያምሩበትን የመፍትሄ ሃሳብንም ያካፍሉናል፡፡ ሌላው የሚያጫውቱን እንዴት ለኢ.ፌ.ድ.ሪ ፕሬዝዳንትነት እንደታጩ ነው፡፡

በተለይ በቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ ሥርዓተ መንግስት ተበሳጭተው “ምን አለ አንድ ቀን መንግስት ብሆን” ብለው የተመኙት ምኞት ሰምሮ በፓርላማ የአገሪቱ ርዕሰ ብሔር ሆነው በተመረጡበት እለት ለመሆኑ ምን አይነት ስሜት ነው የተሰማቸው? በብሔራዊ ቤተመንግስት ያሳለፏቸው አስራ ሁለት አመታትስ ምን ይመስላሉ? እንደ ፕሬዝዳንትነታቸው በእነዚያ አመታት ሠራኋቸው ብለው የሚኮሩባቸው አበይት ተግባራት የትኞቹ ናቸው? ህገ መንግስቱ የሠጣቸውን ስልጣን እና ግለሰባዊ የመሪነት ነፃነታቸውን ተጠቅመው ካስተላለፏቸው ታላላቅ ውሳኔዎች መካከል ከፍተኛ የህዝብ አድናቆት ያተረፉባቸው የትኞቹ ናቸው? ምናለ ባላደርገው ኖሮ ብለው የሚፀፀቱበት ጉዳይስ አጋጥሟቸው ይሆን? ዛሬ ላይ ሆነው ሲያስቡት የሚቆጫቸውስ ነገር አለ? እርሳቸው “አዎ አለ” ብለው አጫውተውኛል፡፡ እጅግ ደስ ብሏቸው እንደ እንቦሳ ጥጃ ስለ ቦረቁባቸው አያሌ ቀናት እና በተቃራኒው ክፉኛ ስላዘነባቸው ሶስት አጋጣሚዎችም ነግረውኛል፡፡ ለመሆኑ እነዚያ የፈነደቁባቸው እና የተከፉባቸው ጉዳዮች ምን ምን ናቸው?

በነገራችን ላይ ክቡርነታቸው በአንድ ወቅት በአገር ክህደት ወንጀል ተከሰው ያውቃሉ፡፡ በወቅቱ የተመሰረተባቸው ክስ እኪጠናቀቅ በእስር ላይ ከመንገላታታቸው ባሻገር የተጠቀሰባቸው የወንጀል ክስ የሞት ፍርድ የሚያስፈርድ ነበር፡፡ ያን አስቀያሚ እና አስደንጋጭ የሆነውን ክስተትንም ዛሬ ላይ ሆነው ሲያስቡት በህይወት መኖራቸው ያስገርማቸዋል፡፡ ፊታቸው ላይም አንዳች የመደነቅ ስሜት እየተነበበባቸው “ልክ እንደ እስራኤል ንጉስ እንደ ቅዱስ ዳዊት ለሞት አንድ እርምጃ ቀርቶኝ ሳለ ለጥቂት እኮ ነው በተዓምር የተፈፍኩት” ነበር ያሉኝ የሁኔታውን ከባድነት በሚያስታውቅ ቅላፄ፡፡ እኔም ይህንን እውነተኛ ግን ደግሞ አስፈሪ ገጠመኛቸውን ሲያጫውቱኝ የሰማዋቸው ሲበዛ እድለኛ መሆናቸውን በውስጤ እያንሰላሰልኩ ነበር፡፡ ለመሆኑ ለእስር የዳረጋቸው እና የጦር ፍርድ ቤት ያቆማቸው ጉዳይ ወይንም ሰሩት የተባለው ወንጀል ምን ነበር? እንዴትስ ከዚያ ጨለማ እስር ቤት ወጡ? እንዴትስ ፊት ለፊታቸው ተደቅኖ ከነበረው ሞት አመለጡ? ምላሹን በዝርዝር ይተርኩልናል፡፡

ሌላኛው እኔን ያስደነቀኝ የህይወታቸው ክፍል ደግሞ ከግል ስብዕናቸው እና ከቤተሰብ አመሰራረታቸው ጋር ይያያዛል፡፡ ክቡርነታቸው አሁንም ድረስ ከእርሳቸው ጋር አብረው ከሚኖሩት ከወ/ሮ ሳሌም ጳውሎስ ጋር 66 ዓመታትን በጋብቻ ተጣምረው አሳልፈዋል፡፡ ይሄ ትዳር ብዙ ዋጋ ተከፍሎበታል፡፡ በተለይ ጅማሬው ላይ ጥንዶቹን የገጠማቸው ፈተና እንዲህ በቀላሉ በቃላት የሚገለፅ አይደለም፡፡ በሁለቱ ጥምረት ያልተደሰቱ ብዙዎች በርካታ ወጥመድ እየዘረጉ እና ነገር እየሸረቡ ቁም ስቅላቸውን አሳይተዋቸዋል፡፡ ይሁንና ግን “እንዴት ተራ ወታደር ታገቢያለሽ” በሚል ሽፋን የተነሳውን የተቃውሞ ማዕበል በፅናት የተቋቋመችውና በያኔው ግርማ ፍቅር የነሆለችው ትንሸ ሳሌም አልተበገረችም፡፡ እናም በፍቅር ከረታት ከተናቀው ከዚያ ምስኪን ጋር አብራ ተሰደደች፡፡ እርሱም ቢሆን አላሳፈራትም፡፡ ታላቁ መፅሐፉ “እምነት ፣ ተስፋ ፣ ፍቅር እነዚህ ሶስቱ ፀንተው ይኖራሉ፡፡ ከእዚህም የሚበልጠው ፍቅር ነው” እንዲል በፍቅሩ ተማርካ የተከተለችው እና ጥሎ አይጥለኝም ብላ ልቧን ያሳረፈችበት ግርማ አንድ ቀን ትልቅ እና የተከበረ ሰው ይሆናል የሚለው ተስፋዋም አልተለወጠም፡፡ ይልቁንስ ካሰበችው እና ከገመተችው በላይ ያ ትንሽ ልጅ የተከበረ ታላቅ ሰው ሆነ፡፡ ገና ከመነሾው በፍቅሯ የተረታው ትንሹ ግርማ ስለ እርሷ ሲል ያላለፈው የመከራ ሸለቆ የለም፡፡ እርሱ ስለ ፍቅር ተሰዷል፡፡ ቀን በወጣላቸው በጊዜው ሰዎች መዳፍ ወድቆ እስር ቤት ተወርውሯል፡፡ ግና ያኔም ቢሆን ለውዱ የገባውን ቃል አላጠፈም፡፡ መሐላውንም አላፈረሰም፡፡ እኔ ይህንን ክስተት ከባለታሪኮቹ አንደበት ለመጀመሪያ ጊዜ የሰማሁ እለት ተደምሜያለሁ፡፡ እናንተ ማንበባችሁን ቀጥሉ እንጂ እኔስ ይህንን የሁለቱን ጥንዶች የፍቅር ታሪክ አስኮመኩማችኋለሁ፡፡ ጋሽ ግርማ በትዝታ ማዕበል ውስጥ እየዋኙ ከ66 ዓመታት በፊት ያሳለፏትን የፍቅር ህይወት ሲያጫውቱኝ በህሊናዬ ውልብ ያለብኝ “ፍቅር አያረጅም” የሚለው ህያው ቃል ነው፡፡ እውነት ነው ፍቅር ሁለት ጥንዶችን አጣምሮ አብሮ ያስረጃል እንጂ እሱስ አያረጅም፡፡ ክቡርነታቸውን “ለእኔ ሳሌም ያኔም ዛሬም ያው ናት፡፡ በፍቅር የምወዳትና የማከብራት” ያሰኛቸውም ይሄው ሃቅ ሳይሆን ይቀራል? ነው እንጂ … አልያማ ሌላ ምን ሊሆን ይችላል?

ይህ ትዳር 5 ልጆችን 15 የልጅ ልጆችን እና 28 የልጅ ልጆችን አፍርቷል፡፡ ከአብራካቸው ክፍያቸው አንዷ ባህር ማዶ የምትኖር ስትሆን ስሟ ከተቃዋሚዎች የፖለቲካ እንቅስቃሴ ጋር አብሮ ይነሳል፡፡ እርግጥ ነው አባቷ ግርማ የገዢው ፓርቲ አባል ባይሆኑም ተቃዋሚ ግን አይደሉም፡፡ እርሷም ብትሆን የእርሳቸው አቋም የግድ መጋራት ላይጠበቅባት ይችላል፡፡ ይሁንና ግን ጥያቄው እንዴት በተቃራኒ ጎራ ልትቆም ቻለች? የሚለው ነው፡፡ ሌላው እውነታ ደግሞ እርሳቸው ሥልጣን ላይ እያሉ ወደ አገር ውስጥ ለስራ ጉዳይ በመጣችበት አጋጣሚ ልጃቸው ታስራ ነበር፡፡ ሆኖም ስልጣናቸውን ተጠቅመው ጣልቃ ከመግባት ይልቅ ስራዋ ያውጣት ብለው ነበር ዝምታን የመረጡት፡፡ ለመሆኑ ልጅቱ ማን ትባላለች? አሁን የምትኖረውስ የት ነው? እዚህ ያሉ ልጆቻቸው ስለ አባታቸው ምን ይላሉ? አባትና እናታቸውስ እንዴት ይገልጧቸዋል? ስለ እነዚህ ጉዳዮች ይህ መፅሐፍ በዝርዝር ያስረዳናል፡፡ ክቡርነታቸው ምን ያዝናናቸዋል? ከምግብና ከመጠጥ የትኛውን ያዘወትራሉ? ጉደኛ ዳንሰኛ እንደሆኑ ስለሚነገረው ጉዳይስ ምን ይላሉ? ሌላው በብዙዎች ህሊና ከሚመላለሱ ጥያቄዎች መካከል አንዱ ከእርሳቸው በፊትም ሆነ አሁን ካሉት መሪዎች መካካል የማን አድናቂ ናቸው የሚል እንደሚሆን ይገመታል፡፡ እንዳጫወቱኝ ከሆነ ከአሜሪካ እና ከኢትዮጵያ የሚያደንቋቸው ሶስት መሪዎች አሉ፡፡ ለመሆኑ እነዚያ ሰዎች እነማን ናቸው? ስለምንስ ያደንቋቸዋል? ሮል ሞዴላቸውስ ማን ነው? በቅርቡ በሞት ስለተለዩን ስለ ቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስተር ስለ አቶ መለስ ዜናዊስ ምን ይላሉ? ለመጀመሪያ ጊዜ ሁለቱ የተዋወቁት መቼ፤ እንዴት እና የት ነበር? ምን ያህልስ ይቀራረቡ ነበር? የስራ ግንኙነታቸውስ ምን ይመስላል? ጠቅላይ ሚንስትሩን እንዴት እና በምን ይሆን የሚገልፅዋቸው? ይህ መፅሐፍ ለእነዚህ እና ለመሰል ጥያቄዎች ቁልጭ እና ቅልብጭ ያለ ምላሹን ይሠጣል!

መግቢያ

ይህንን መፅሐፍ ለማዘጋጀት ካሰብኩ አመታት ተቆጥረዋል፡፡ ፍላጎቱም ያደረብኝ ለመጀመርያ ጊዜ ከተዋወኳቸው ቀን አንስቶ ነበር፡፡ በእለቱ ለእኔም ይሁን አብረውኝ ለነበሩ ታዳሚዎች የህይወት ተሞክሯቸውን ከረጅሙ በአጭሩ ከብዙ በጥቂቱ ሲያካፍሉ ያዳመጥኳቸው በመደነቅ እንደነበር ዛሬም ደረስ ትዝ ይለኛል፡፡ ከዚያ በኋላ ስለ እርሳቸው የሚያተርኩ ልዩ ልዩ አይነት መጣጥፎች እያነፈነፍኩ እከታተል ነበር፡፡ በተለይ አገሬን ወክዬ በምሳተፍባቸው አህጉር እና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ከእርሳቸው ጋር የምሰራበት እድል ያገኘሁባቸው አመታት እርሳቸውን በቅርበት እንዳውቃቸው ረድተውኛል፡፡ ይሄኔም ታሪካቸው፣ የህይወት ፍልስፍናቸው፣ ለአገር እና ለወገን ያላቸው ተቆርቋሪነት ይበልጥ እየሳበኝ መጣ፡፡ እያደርም ባዬግራፊያቸውን የያዘ መፅሐፍ የማዘጋጀቱ ፍላጎት እየጎለበተ ሄደ፡፡ አንድ ቀንም እዚያው ቤተመንግስት ቢሮአቸው ሳሉ ይህንን መሻቴን ገለፅኩላቸው፡፡ የእርሳቸውን የህይወት ተሞክሮ የሚያካፍል መፅሐፍ የማሳተም፣ ዘጋቢ ፈልም የማዘጋጀት እና በእውነተኛ ታሪካቸው ላይ የተመሰረተ ፊልም ለመስራት ፍላጎቱ እንዳለኝ ገለፅኩላቸው፡፡

እርሳቸውም በትህትና “ምን ሥራ ሠራሁና ነው ለጀግና የሚሰጠውን ክብር ልትሠጠኝ የወደድከው? ከሌላውስ ምን የተለየ ታሪክ አለኝና ነው? እንዲህ አይነት ለኔ የማይገባ ታላቅ ነገር ያሰብክልኝ” የሚል ጥያቄ አዘል ምላሽ ሰጡኝ፡፡ ይህ ትህትና የተሞላበት ምላሻቸው በፊት በነበረኝ መገረም ላይ ሌላ መደነቅ ጨመረብኝ፡፡ ወዲያውም አያቴ “ፍሬው የበዛ ማሽላ አንገቱን ጎንበስ ያደርጋል” ብላ በልጅነቴ የነገረችኝ ግሩም አባባል ከፊቴ መቶ ገጭ አለ፡፡ ወዲያውም “እውነቷን ነው እማማ” አልኩ በልቤ፡፡ እኝህን ሰው ለዚህ ክብር ያበቃቸው ይሄው ትህትናቸው ነው ብዬ ይበልጥ ተደመምኩ፡፡ ቀጥዬም ለጥያቄያቸው ምላሽ ይሆናል ብዬ ያመንኩበትን ምላሽ ሰጠኋቸው፡፡ ዋነኛ ዓላማዬንም በዝርዝር አስረዳኋቸው፡፡ ይሄኔም ጥያቄዬን በፀጋ ተቀብለው ሙሉ ፍቃደኝነታቸውን ገለጹልኝ፡፡ ከዚያም መጠነኛ ፕሮፖዛል ቀረጬ አቀረብኩላቸው፡፡ ወደዱትም፡፡ በመጨረሻም የጋራ ስምምነት ላይ ደርሰን ስራዬን አሀዱ ብዬ ጀመርኩኝ፡፡ እርግጥ ነው የሙያዬም ሆነ የስራዬ ፀባይ ወደ ተለያዩ የአለም ክፍሎች እንድንቀሳቀስ ግድ ይለኛል፡፡ ይሁንና ግን በተቻለ አቅም አገር ውስጥ እስካለሁ ድረስ በሳምንት ሁለት ቀን ቃለ መጠይቅ /Interview/ አደርጋቸው ነበር፡፡ በተለይ ማክሰኞ እና ሐሙስ ጠዋት ጠዋት እየተገናኘን ከሦስት ሰአታት በላይ እናሳልፍ ነበር፡፡ ከዚያም ለሥራ ጉዳይ ወደ ባህር ማዶ ወጣ ስል በማርፍባቸው ሆቴሎች እስከ ውድቅት ለሊት ድረስ እየቆየሁ ቃለ መጠይቁን በጽሑፍ አሰፍረው ነበር፡፡ በቀሪዎቹም እለታት መረጃዎችን ከተለያየ ሥፍራ የማሰባሰቡን ስራ ተያያዝኩት፡፡

ከብሔራዊ ቤተመንግስት፣ ከፕሬዝዳንት ፅ/ቤት፣ ከቤተመንግስት አስተዳደር፤ ከውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት፣ ከሲቪል አቪየሽን ባለስልጣን፣ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ከትራንስፖርት ሚንስትር፣ ከአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ጥናትና ምርምር ኢንስቲትውት፤ ከኢትዮጵያ ሬድዮ እና ቴሌቪዥን ድርጅት፤ ከኢትዮጵያ ደራስያን ማህበር፤ ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፤ ከልዩ ልዩ የግል ሚድያ፤ ከኢትዮጵያ አየር ኃይል፤ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፤ ከፌደሬሽን ምክር ቤት፤ ከኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር፤ ከአገር መከላከያ ሚንስቴር፤ ከላየንስ ክለብ፤ ከለም ኢትዮጵያ፤ ከስካውት ማህበር፤ ከአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር፤ ከአዲስ አበባ እድሮች ህብረት፤ ከጥንታዊ ኢትዮጵያ አርበኞች ማህበር፤ ከኢትዮጵያ አየር ኃይል ጡረተኞች ማህበር፤ ከሆሎታ ወታደራዊ መኮንኖች ማሰልጠኛ፤ ከአዋሽ ኢንሹራንስ ኩባንያ እስከ ከአዋሽ ኢንተርናሽናል ባንክ ፤ ከወጋገን ባንክ፤ ከግቤ እርሻ ልማት፤ ከቆርኪ ፋብሪካ፤ ከሜሪ ጆይ የልማት ተራድዖ ድርጅት እና ከብሔራዊ ቤተመዛግብት ልዩ ልዩ ሰነዶች እያገላበጥኩ ጠቃሚ ናቸው ብዬ ያመንኩባቸውን የድምፅ፣ የምስል እና የሰነድ መረጃዎችን ኮፒ በማድረግ አከማቸሁኝ፡፡ በተጓዳኝም ከአብሮ አደግ ጓደኞቻቸው፣ ከረጅም ጊዜ የሥራ ባልደረቦቻቸው፣ ከልብ ወዳዶቻቸው እና ከቅርብ ቤተሰቦቻቸው ጋር በቀጠሮ በመገናኘት ተጨማሪ ግብአቶችን አሰባሰብኩ፡፡ ቀጥሎም እያንዳንዱን መረጃ በመተንተን እና በማቀናጀት በግብዓትነት ተጠቅሜ መፅሐፉን በዚህ መልኩ ወደማዘጋገቱ ተሻገርኩ፡፡ ዋነኛ ዓላማዬም ሚሊዮኖች ከእርሳቸው የህይወት ተሞክሮ በርካታ ቁም ነገሮችን በመቅሰም የእርሳቸውን አሰራ ፍኖት እንዲከተሉ ለማድረግ ነው፡፡ እኔ በበኩሌ እንዲህ ነው ብዬ የምገልፀው እውቀትን ከእርሳቸው ቀስሜያለሁ፡፡ አፌን ሞልቼ የምናገረውም ክቡርነታቸው የአላማ ፅናት፣ የውሳኔ ሰጪነት ብቃት፣ ኃላፊነትን የመሸከም ክህሎት፣ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን በብልጠት የማለፍ ጥበብ፤ በራስ መተማመን፣ ቆራጥነት፣ ተዓማኒነት፣ ጥንቁቅነት፣ ግልፅነት እና የማሳመን ክህሎት ያላቸው ብቁ እና ግልፅ ሰው መሆናቸውን ነው፡፡ አዎ እርሳቸው የልጅነት ህልማቸውን እውን ያደረጉ ውጤታማ እና ስኬታማ ሰው ናቸው፡፡ ከትንሽ ነገር ተነስቶ ትልቅ ደረጃ መድረስ እንደሚቻል በተግባር ያረጋገጡ እና በእሳት ተፈትነው እንደ ከበረ ማዕድን ነጥረው የወጡ የኢትዮጵያ ወርቅ ልጅ ናቸው፡፡ እርሳቸው ዘመናቸውን ያሳለፉት በድል ላይ ድል በመቀዳጀት ነው፡፡

በዛ ላይ ወድቆ መነሳትን፣ ታግሎ ማሸነፍን እና ተከራክሮ መርታትን ያውቁበታል፡፡ ይሁን አንጂ እንዳለመታደል ሆኖ እንደነዚህ ያሉ ምድራችን ያፈራቻቸውን እንቁዎች ስናጌጥባቸው አይስተዋልም፡፡ ለጥቂት ጀግኖቻችን እንኳ መታሰቢያ ያቆምንላቸው ካለፉ በኋላ ነው፡፡ በዚህ ረገድ እኔ ተሳክቶልኛል፡፡ እኚህ የአገር አድባር እና ተንቀሳቃሽ ቅርስ የሆኑ ሰው በህይወት ሳሉ ሊሞገሱ፣ ሊወደሱ፣ ሊዘከሩ፣ ሊሸለሙ እና ሊከበሩ ስለሚገባ አምቦ ዩኒቨርስቲ የሚገኘው ግዙፉ ላይብራሪ በእርሳቸው ስም እንዲሰየም ያቀረብኩት ኃሳብ በሴኔቱ ሙሉ ተቀባይነት አግኝቶ ተቋሙ ለክብርነታቸው የክብር ዶክትሬት ዲግሪ በሰጣቸው እለት ቤተ መፃህፍቱም በእርሳቸው ስም ተሰይሟል፡፡ ከዚህ የልቀት ማዕከልም በቀጣዮቹ አመታት በርካታ የነቁ እና የበቁ፤ ያወቁ እና የመጠቁ እንዲሁም የተማሩ እና የተመራመሩ ብዙ ምሁራን እንደሚፈልቁበት እልፍ ግርማዎችም እንደሚበቅሉበት አምናለሁ፡፡

የዚህ መፅሐፍ ዓላማ ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡ ዋነኛ ግቤ በእርሳቸው ስኬት ተነቃቅተው ለመልካም ስራ የሚነሳሱ ውጤታማ ዜጎችን ማፍራት ነው፡፡ ይህ ህልሜም ይህንን መፅሐፍ በሚያነቡ በርካታ ወጣቶች ላይ እውን እንደሚሆን እርግጠኛ ነኝ፡፡ ሚሊዩኖች በይቻላል ባይነት መንፈስ ሲሞሉ እና በራስ የመተማመን አቅማቸውን ሲጎለብት ይታየኛል፡፡ የእኚህ በእውቀት የሸመገሉ እና ሽበታቸው ሺህ ውበት የሆነላቸውን ስኬታማ ሰው ፈለግ ከሚከተሉ ባለ ራዕዮች መካከልም አንዱ አንተ አንደምትሆንም ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ በመጨረሻም መልካም ንባብን እየተመኘሁ ወደ መፅሐፉ ፍሬ ሃሳብ እንድትገቡ በፍቅር እና በአክብሮት እጋብዛለሁ፡፡
ደራሲው


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles