Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

የሁለት ፈረሶች ጥያቄ (ዳንኤል ክብረት)

$
0
0
ዳንኤል ክብረት
ሁለት ፈረሶች እንደነበሩ ተነገረ፡፡ አንደኛው እጅግ ለምለም በሆነ ሰፊ ሜዳ ላይ ተሠማርቶ፣ ሲያሻው ደግሞ በግራ በቀኝ ገብስ ፈስሶለት፣ ሲጠማው የሚጠጣው ውኃ በሜዳው መካከል ኩልል ብሎ እየወረደለት፣ አውሬ እንዳይተናኮለው ዙሪያውን በውሻ እየተጠበቀ ይኖር ነበር፡፡ ሁለተኛው ደግሞ የሣር ዘር ለአመል ያህል ብቻ እዚህም እዚያም በበቀለበት፣ ጭው ባለ ደረቅ ሜዳ ላይ ተሠማርቶ ያገኛትን እየነጨ፣ ከዕለታት በአንድ ቀን ከደጋ የዘነበ ዝናብ በአካባቢው ሲያልፍ የሚያገኘውን ጥፍጣፊ ውኃ እየተጎነጨ፣ ሌትና ቀን ምን ዓይነት አውሬ መጥቶ ይዘነጥለኝ ይሆን? እያለ በሥጋት ይኖር ነበር፡፡
daniel-kibret-300x207

ዳንኤል ክብረት

ምንም እንኳን ሁለቱም ፈረሶች በኑሮ በማይቀራረብ ሜዳ ላይ በመከራና በቅንጦት ተለያይተው ቢኖሩም የኑሮ ጥያቄ ግን አገናኝቷቸው ኖሯል፡፡ ያ እንዲያ በለመለመ መስክ ተሠማርቶ እምብርቱ እስኪነፋ ሆዱ እስኪቆዘር እየበላ ሲተኛ ሲነሣ የሚውለው ፈረስ ‹‹ይኼ ሣር ያለቀ ዕለት፣ ይኼም ውኃ የነጠፈ ጊዜ፣ እነዚህም ውሾች እኔን መጠበቅ ትተው የሄዱ ጊዜ፣ ይኼስ ገብስ የጠፋ ቀን ምን ይውጠኝ ይሆን? ያስ ቀን መቼ ይሆን? ይል ነበር፡፡ ይኼ ጥያቄ ምንጊዜም ይረብሸው ነበር፡፡

 

 ያ በደረቅ ሜዳ ላይ እዚህም እዚያም የበቀለች ሣር እየነጨ ከርሱን ሲደልል የሚውለው ፈረስ ደግሞ ‹‹መቼ ይሆን አልፎልኝ ለምለም መስክ ላይ ውዬ፣ ከፈሰሰ ውኃ እንደ ልቤ ተጎንጭቼ፣ ያለ ሥጋት አድሬ የሚነጋልኝ? ያ ቀን መቼ ይሆን?ይል ነበር፡፡

እዚህ ሀገር ያለን ሰዎች በሁለቱ ፈረሶች ጥያቄ ውስጥ ወድቀናል፡፡ አንደኛው መስኩ ለምልሞለት፣ ውኃው መንጭቶለት፣ ሥጋቱ ጠፍቶለት፣ ሕይወቱ ቀንቶለት የሚኖረው ሰው ጥያቄ ነው፡፡ እንዴት ሜዳው ላይ እንደደረሰ አያውቀውም፤ ብቻ አንድ ቀን ተቀለጣጥፎም፣ ተጣጥፎም፣ ተለጣጥፎም፣ ራሱን ሜዳ ላይ አግኝቶታል፡፡ ለስንትና ስንት ፈረስ የሚበቃውን መስክ ብቻውን ተሠማርቶበታል፡፡ አገር የሚያጠጣውን ወንዝ ብቻውን ይንቦራችበታል፡፡ ጥጋብን ከልኩ በላይ፣ ምቾትንም ከመጠን አልፎ ቀምሶታል፡፡ ድህነትን ረስቶ የት መጣውን ዘንግቶታል፡፡ ግን ሥጋት አልለቀቀው ይኼ መሥመር የተበጠሰ ዕለት፣ ይኼ ሥርዓት ያለፈ ቀን፣ ከእገሌ ጋር የተጣላሁ ጊዜ፣ ቀን የዞረችበኝ ሰዓት፣ የተነቃ ለታ፣ ዕቁቡ የተበላ ጊዜ፣ ካርታው ያለቀ ቀን፣ መንገዱ የታወቀ እንደሆን፣ ሕግ የተቀየረ ቀን፣ ምን ይውጠኝ ይሆን? ያችስ ቀን መቼ ትሆን? እያለ ይጠይቃል፡፡ እየበላ ይሠጋል፣ እየጠጣም ይጨነቃል፤ አይቷል፣ ሰምቷል፡፡ ድንገት ለምለሙ ሜዳ ላይ ተገኝተው ድንገት ከሜዳው የጠፉ አሉና፡፡
አሁን ሆዱ ተቀይሯል፤ አንገቱ ተቀይሯል፤ እጁ ተቀይሯል፤ መቀመጫው ተቀይሯል፤ ማረፊያና መዋያው ተቀይሯል፡፡ ይህንን ያጣ ዕለት ምን ይውጠዋል?
ያኛውም ፈረስ አለ፡፡ እንደ ዐርባ ቀን ዕድል ሆኖ የደረቀ መስክ ላይ ውሎ እንዲያደር የተፈረደበት፤ ቢሄድ ቢመጣ፣ ቢወርድ ቢወጣ ከዚያ መስክ መላቀቅ ያቃተው፡፡ መቼ ይሆን የእኔስ ሜዳ በሣር ተሞልቶ እንደነዚያ ሣር የምጠግበው እያለ ምኞት የገደለው፡፡ የእኔስ ወንዝ መቼ ይሆን ውኃ ሞልቶት ሳልጨነቅ የምጠጣው? እያለ ሃሳብ ያናወዘው፡፡ የእርሱ ቤት እየፈረሰች ከጎረቤቱ ዘጠኝ ፎቅ ሲበቅል አይቷል፡፡ ስትተከል፣ ውኃ ስትጠጣ፣ አላያትም፡፡ እንዲሁ ብቻ ፎቋ በቀለች፡፡ ስትገዛ ያላያት፣ ፍንጥር ያልጠጣባት መኪና እንዲሁ ሽው እልም ስትል አያት፤ እናም ምን ዓይነት ፈረሶች ይሆኑ ለዚህ የሚበቁት እያለ ይጠይቃል፡፡ ዝርያቸው ምን ቢሆን ነው? መልካቸውስ ምን ቢሆን ነው? የፈረስ ጉልበታቸውስ ምን ያህል ቢሆነ ነው? ፍጥነታቸውና ቅልጥፍናቸውስ እንዴት ያለ ቢሆን ነው? ጌቶቻቸውንስ እንዴት አድርገው ቢያገለግሏቸው ነው? እንዲህ ለምለም መስክ ላይ የለቀቋቸው? እኛም ስናገለግል ኖረናል፤ ጋሪ ስንጎትት፣ እህል ስንሸከም፣ ዕቃ ስናጓጉዝ ኖረናል፤ ጌቶቻችን ሲጋልቡን ኖረናል፤ ግን እነርሱ ምን ያህል ቢያስደስቷቸው ነው ይህንን ዕድል የሰጧቸው? እያለ ይጠይቃል፡፡
ለመሆኑ እነርሱ ናቸው ወደ እኛ የሚመጡት ወይስ እኛ ነን ወደ እነርሱ የምንሄደው? ለመሆኑ የኛን ድህነት ነው ወይስ የእነርሱን ሀብት ነው የምንካፈለው? በርግጥ ከኛም የሄዱ አሉ፤ ከእነርሱም የሚመጡ አሉ? ይላል፡፡ አንዱ ሜዳ ላይ ተሠማርተን እንደ አቅማችንና እንደ ችሎታችን መጋጥ ሲገባን ለምን ሁለት ዓይነት ሜዳ ሆነ፡፡ አሁን እኛና እነርሱ እኩል ‹‹ፈረስ›› ተብለን እንጠራለን? እኛ ‹‹ሌጣ ፈረስ›› ነን፣ እነርሱ ደግሞ ‹‹ባለ ወግ ፈረስ›› ናቸው፡፡
ግን ይሁን፤ እሺ መቼ ይሆን እኛስ እንደነርሱ የምንሆነው? መቼ ይሆን ያለ ሥጋት ውለን የምናድረው? ለምለሙን መስክ ማን ይነካዋል፤ ላለው ነው ድሮም የሚጨመርለት፤ የኛ የድኾቹን መስክ ነው ለሀብታሞቹ የሚሰጡት፤ የድኾቹን ደረቅ መስክ ሀብታሞቹ የሚቀኑበትን ያህል እኛ በእነርሱ ለምለም መስክ አንቀናም፡፡ ደግሞ አንድ ቀን ይመጣሉ፡፡ ‹‹ይህንን መስክ ለምለም ማድረግ እንፈልጋለን›› ይላሉ፡፡ እኛም ደስ ይለናል፡፡ የዘመናት ምኞታችን አይደል? መንገዱ ጠፍቶን እንጂ እኛም ለምለም ማድረግ እንፈልግ ነበርኮ? መንገዱን ያወቀው ሰው ሲመጣ ለምን እንቃወመዋለን፡፡
ግን ይቀጥሉና ሌላ ነገር ይሉናል፡፡ ‹‹መስኩን ግን ለምለም የምናደርገው ለእኛ እንጂ ለእናንተ አይደለም›› ይሉናል፡፡ ለምን? ለምን? እኛ ለምለም ሣር አይወድልንም? እኛ ለምለም የምናደርግበትን መንገድ ለምን አያሳዩንም? ባያሳዩንስ ለምን አይፈቅዱልንም? ባይፈቅዱልንስ ለምን አይተውንም? እንላለን፡፡ ይህ ግን ጥያቄ ነው እንጂ መልስ የለውም፡፡ እኛም ጥያቄውን የምናውቀውን ያህል መልሱን አናውቀውም፡፡ ስንጠይቅም ‹‹ምላሽ›› እንጂ ‹‹መልስ›› የሚሰጥ አናገኝም፡፡
እኛም ከዚያ መስክ እንወጣለን፣ ወደሌላ መስክም እንዛወራለን፤ አሁንም ቅንጥብጣቢ ሣር እንፈልጋለን፤ ጥፍጣፊ ውኃ እናስሳለን፡፡ ያ እኛ የነበርንበት መስክ ግን በአንድ ጊዜ ይለመልማል፡፡ ውኅው ጅረት ሆኖ ይፈስበታል፡፡ ይገርመናል፡፡ እኛ እዚያ ሳለን፡፡ ውኃ አልነበረም፡፡ እንደ ወር በዓል ቀን ቆጥረን ነበር የምናገኘው፡፡ አሁን ግን ይንፎለፎላል? ለመሆኑ እኛ ምን ብለን መጠየቅ ነበረብን? ይኼ ራሱ ሌላ ጥያቄ ይሆንብናል፡፡ መቼ ይሆን እኛስ እንዲህ ባለው መስክ ላይ የምንሠማረው? እንላለን፡፡ የማይሳካ ምኞት እንመኛለን፤ የማይመለስ ጥያቄ እንጠይቃለን፡፡
እዚያም ቤት ሌላ ጥያቄ አለ፡፡ ፀሐይዋ እንደወጣች ትቀጥል ይሆን? ወንዙ እንደፈሰሰ ይቀጥል ይሆን? ነፋሱ እንደነፈሰ ይቀጥል ይሆን? ሣሩ እንደለመለመ ይዘልቅ ይሆን? እኔስ እንደተወደድኩና ሞገስ እንዳገኘሁ እኖር ይሆን?
ሰውየው ስለ አውሮፕላን አነዳድ የሚገልጥ ማኑዋል አገኘና አውሮፕላኑን አስነሥቶ አበረረ፡፡ ገጹን ይገልጣል፤ የተጻፈውን ይፈጽማል፤ አውሮፕላኑም ይበራል፡፡ በቀጣዩ ገጽ ላይ ምን እንዳለ የሚያውቀው ነገር አልነበረም፡፡ ገጹ ተገንጥሎ ቢገኝ ምን ማድረግ እንዳለበትም የሚያውቀው ነገር አልነበረም፡፡ ብቻ ይገልጣል፣ ያነባል፣ ይነካካል፣ ይበራል፡፡ አውሮፕላኑ ተነሥቶ በሃያ አምስት ሺ ጫማ ከፍታ ላይ ሲደርስ የመጨረሻው ገጽ ላይ ደረሰ፡፡ ‹‹ክፍል ሁለትን በክፍል ሁለት መጽሐፍ ይመልከቱ›› ይላል፡፡ ክፍል ሁለት መጽሐፍ ግን የለውም፤ የት እንዳለም አያውቅም፡፡ ምን ማድረግ እንዳለበትም አልተዘጋጀም፡፡ ስለዚህም እንደወጣ መውረድ ጀመረ፡፡ ያውም በዝግታ ሳይሆን እየተምዘገዘገ፡፡
እናም እኛ በለምለም መስክ ላይ ያለን ፈረሶች፣ አንድ ክፉ ቀን መጥቶ ‹‹ክፍል ሁለትን በሌላ መጽሐፍ›› ቢለንስ? ምን ይውጠናል? ለመሆኑ ክፍል ሁለት የት ነው ያለው? እስካሁን ያሳየን የለም፡፡ እኛ የምናውቀው የየዕለቱን ምዕራፍ ብቻ ነው፡፡ ያንን እናነባለን፣ በእርሱ እንኖራለን፣ ቀጣዩን ምዕራፍ አናውቀውም? ስለዚህም እኛም እንጠይቃለን? እንዲሁ እንዘልቅ ይሆን? ብለን፡፡

© ይህ ጽሑፍ በአዲስ ጉዳይ መጽሔት ላይ የወጣ ነው

Source: Danielkibret


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>