በተለያዩ ጊዜያት በሃገራችን የነበሩ የሰንደቅ አላማዎች እንደሚከተለው እንመልከት
ኢትዮጵያ ዘመን ተሻጋሪ የሰንደቅ አላማ ታሪክ ካላቸው ሃገራት መካከል አንዷ ናት ፤ የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ እስከ 1890ዎቹ ሁለተኛ አጋማሽ ድረስ በቀለማትም አንድ ወጥ አልነበረም ፤ አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ቀለማት ያሉት ሰንደቅ አላማ ቀለማት ወጥነት ባለው በተያያዙ አራትማእዘናት በጥቅም ላይ የዋሉት በ1890ዎቹ መጨረሻ ነው ፤ በሃገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ ለሰንደቅ አላማ ልዩትርጓሜና ስርፀት የተሰጠው በ1898 እንደሆነ ይነገራል ፤ ቢጫ የብርሃን፣ ቀይ የመስዋዕትነትና አረንጓዴ የተስፋምልክት ተደርጐ ይወሰዳል፡፡
ከዚህ በኋላ ሰንደቅ አላማችን አንድ ጊዜ መንፈሳዊ ሌላ ጊዜ ፖለቲካዊ ትርጓሜ እየታከለበት ዘመን ተሻግሯል ፤ እኛ ኢትዮጵያውያን በሰንደቅ አላማችን ስም በጐም ሆነ መጥፎ ተግባራት በተፈፀሙባቸው ዘመነ መንግስታት ጭምር ለሰንደቅ አላማችን ያለን ፍቅርና ክብር እጅግ ጥልቅ ነው ፤ ጥንታውያንጀግኖች ወላጆቻችን ሰንደቅ አላማችንን ይዘው አስደናቂ ትግልና ውጊያ በማካሄድ ከባዕዳውያን ቀጥተኛ ተፅዕኖ ነፃ የሆነች ሃገር አስረክበውናል ፤ በአንዲት ባንዲራቸው ጥላ ስር በመሆን ወራሪውን ሃይል በእግዚአብሔር ረዳትነትና እና በታማኝ አርበኞች ጀግንነት ከቀኝ ግዛት ነጻ የሆነች ሀገር አቆይተውልናል ፡፡
ኢትዮጵያውያን ለአያሌ ዘመናት ብሔራዊ ክብራችንን ባዋረደና እንደ ህዝብ አንገታችንን ባስደፋን አስከፊ የድህነትማቅ ውስጥ ኖረናል ፡፡ አሁን ሰንደቅ አላማችን የጭቆናም የጭፍጨፋ አርማ አይደለም። የሰንደቅ አላማችን አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ቀለማት እንደ ዱሮው ሁሉ የልምላሜ የተስፋና ለነፃነት የሚከፈል መስዋዕትነት ምልክቶቻችን ናቸው ።
“አፍ ሲያመልጥ ራስ ሲመለጥ አይታወቅም” እንደሚባለው የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አውቀው ይሁን ሳያውቁ “ባንዲራ ጨርቅ ነው” በማለት በአደባባይ ሲናገሩ ጆሯን ሰምቷል ፤ በዚህ ንግግራቸው በርካታ ኢትዮጵያውያን የባዲራው ነገር የገባቸው እጅጉን ውስጣቸው ተጎድቷል ፤ እድሜ ልካቸውን ለሀገር ብለው ከጠላት ጋር ጦር ሜዳ ለተዋደቁ አባቶቻችን ይህ አባባል አጥንት ዘልቆ የሚሰማ ስሜት ፈጥሮባቸው አልፏል ፤ አቶ መለስ ይህን በተናገሩ በሳምንታት ውስጥ አፋቸውን ሞልተው “ይቅርታ መናገር አልነበረብኝም ተሳስቻለሁ” የማይሉ ሰው ስለሆኑ ምን ማለት እንደፈለጉ በሌላ አባባል ንግግራቸውን መስመሩን ማስቀየር ችለው ነበር ፡፡
የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ቀን በዓል መከበር የጀመረው በአዲሱ ሚሊኒየም መጀመሪያ ላይ ነው ፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያፀደቀው የሰንደቅ አላማ አዋጅ በዓሉ በየአመቱ በመስከረም ሁለተኛ ሳምንት ሰኞ እንዲከበር ይደነግጋል ፤ አዋጁ መስከረምን የመረጠው ወሩ ለሃገራችን የዘመን መለወጫና አዲስ የተስፋ የስራና የለውጥ መንፈስ የሚፈጠርበት መሆኑን ታሳቢ በማድረግ ይመስላል ፤
የሰንደቅ አላማችን አረንጓዴ ቢጫና ቀይ ህብረ-ቀለማት ያለፈውም ሆነ የመጪው ጊዜ በልማት የመለወጥ ፣ በነፃነትና በተስፋ የመኖር ራዕያችን አሻራዎች ናቸው፡፡ የአግድም ቀለሞች አረንጓዴ- ስራ፣ ልምላሜና እድገት ፤ቢጫ -የተስፋ፣የፍትህና የእኩልነት ቀይ- ለነጻነትና ለእኩልነት መስፈን የሚደረግ የመስዋዕትነትና የጀግንነት ምልክት ነው፡፡ ይህን የቀለም ህብረት ኢትዮጵያ መጠቀም የጀመረችው ከአድዋ ጦርነት በፊት መሆኑን ታሪክ ይናገራል ፤ በርካታ የአፍሪካ ሀገራት ይህን የቀለም ህብረት መጠቀም የጀመሩት ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እንደሆነ ይታወቃል ፤ ኢትዮጵያ የአፍሪካ የነጻነትና የቅኝ አለመገዛት ተምሳሌት የሆነች ሀገር በመሆኗ በርካቶች ይህን ለመጠቀማቸው ቀዳሚ ምክንያን መሆኑን የታሪክ ምሁራን ይናገራሉ፡፡
ምንጭ፡ አንድ አድርገን