ሕወሓትና በትግርኛ ተናጋሪዎች ሙሉ ቁጥጥር ስር የወደቀዉ መከላከያ ሠራዊት
ከአራት አመታት በኋላ በድጋሚ ሲፈተሽ
መስከረም 26 2007 ዓ.ም.
ሕዝባዊ ሓርነት ወያኔ ትግራይ (ሕወሓት) ምን ያክል የኢትዮጵያን የፖለቲካ መዋቅሮች እንደሚቆጣጠር ለማወቅ በአገሪቱ የመከላከያ፣ የደህንነትና የፖሊስ ተቋሞች ዉስጥ ዋና ዋና የትዕዛዝ ሰጪና ቁጥጥር ቦታዎች ላይ በሀላፊነት የተቀመጡትን የትግራይ ተወላጆች ብዛት መመልከቱ በቂ ይመስለናል። የሕወሓት መሪዎች ስልጣን በያዙባቸዉ በመጀመሪያዎቹ ጥቂት አመታት ዉስጥ እየገነቡት ላይ ያለዉን ስርዐት መልካምና ሁሉን አቀፍ ስርዓት ለማስመሰል አንዳንድ ከነርሱ ቁጥጥር ዉጭ መተንፈስ እንኳን የማይችሉ የሌላ ብሄረሰብ ተወላጆችን አልፎ አልፎ ስልጣን ላይ አስቀምጠዋቸዉ ነበር። ዛሬ ሕወሓቶችን እራሳቸዉን እጅግ በጣም በሚያሳፍር መልኩ እነዚህ በጥንቃቄ ለቅመዉ ያመጧቸዉንም የሌላ ብሄረሰብ ተወላጆች ወደመጡበት መልሰዋቸዉ በሁሉም መስክ ቁልፍ የሆኑ የአገሪቱን የስልጣን ቦታዎችን የሚቆጣጠረዉ የትግራይ ተወላጅ ሕወሓቶች ብቻ ሆነዋል። አያሌ ኢትዮጵያዉያን የህወሓትን አገዛዝ “ዘረኛ” አገዛዝ ነዉ ብለዉ የሚጠሩት ይህንን ሙልጭ ያለ በዘር ላይ የተመሰረተ ጭፍን አገዛዝ ተመልክተዉ ይመስለናል።
ዛሬ ኢትዮጵያ ዉስጥ ወያኔ ለፈጠረዉ ዘረኛ ስርዓት ብቸኛ ምሳሌ ሆኖ መቅረብ የሚችለዉ ደቡብ አፍሪካ ዉስጥ ነጮች የፈጠሩት ዘረኛ (Apartheid) ስርዓት ብቻ ነዉ። በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ዉስጥ በተለይ በቁጥሩ ከፍተኛ ብልጫ ያለዉና ትግርኛ ተናጋሪ ያልሆነዉ ሠራዊት እጅግ ያኮረፈ፤ የተቆጣና ያመረረ ሠራዊት ከመሆኑ የተነሳ እራሱን የሚመለከተዉ እንደ አገር መከላከያ ሠራዊት አባል ሳይሆን አንደ ህወሓት የቤት ዉስጥ አገልጋይ ባሪያ ነዉ። ይህ የሕወሓት ዘረኞች በሠራዊቱ ላይ የፈጠሩት የመገዛትና የበታችነት ስሜት በየቀኑ ከፍተኛ ቁጣና የዉስጥ ለዉስጥ ተቃዉሞ የሚገጥመዉ ቢሆንም ህወሓት በዘረጋዉ ከፍተኛ የአፈና መረብ የተነሳ የህዝብ መነጋገሪያ አርዕስት መሆን አልቻለም። የህወሓት መሪዎችም ቢሆኑ ይህንን ቁጣና ተቃዉሞ በሚገባ ስለሚያዉቁ “ግምገማ” እያሉ በሚያዘጋጇቸዉ መድረኮች ላይ እንደዚህ አይነቶቹን በእነሱ የበላይነት ላይ የሚነሱ ጥያቄዎችን ማስተናገድ ቀርቶ ጥያቄዎቹ እንዲነሱም አይፈቅዱም። አንዳንዴ ደፍረዉ እነዚህን ጥያቄዎች የሚያነሱ ግለሰቦች ሽብርተኛ፣ የደርግ ስርዐት ናፋቂዎች፣ ጠባብ ብሄረተኞች ወይም የጥላቻ ፖለቲካ አራማጆች የሚል ተቀጽላ ስም ይሰጣቸዋል። ዛሬ የዕድሜ ልክ እስራት ተፈርዶባቸዉ በተለያዩ የወያኔ እስር ቤቶች ዉስጥ የሚሰቃዩት ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች ለዚህ አሳዛኝ ሁኔታ የበቁት በመከላከያ ተቋሞች ዉስጥ ሠራዊቱን በየትኛዉም እርከን የሚመሩ መኮንኖች አመዳደብ ወታደራዊ አመራር ችሎታን፤ ልምድንና የብሄር ስብጥርን ያካተተ መሆን አለበት ብለዉ ደፍረዉ በመናገራቸዉ ነዉ።
ዛሬ የወያኔን መከላከያ ሠራዊት እየለቀቁ ከአገር የሚወጡ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች ቁጥር በየቀኑ እየጨመረ በመሄድ ላይ ይገኛል። እነዚህ ወታደራዊ መሪዎች፤ የበታች መኮንኖች፤ ባለሌላ ማዕረጎችችና ተራ ወታደሮች ከጠላት እንከላከላን ብለዉ የማሉላትን እናት አገራቸዉን እየለቀቁ የሚወጡት በወያኔ ጦር ዉስጥ ስር የሰደደዉ ዘረኝነትና በዚህ ዘረኝነት ላይ የተመሰረተዉ አመራር የሚያደርስባቸዉ በደል አንገፍግፏቸዉ ነዉ። በየጎረቤቱ አገር ተሰድደዉ በችግር ላይ የሚገኙ ምርጥ የኢትዮጵያ የወታደራዊ ሳይንስ አዋቂዎች ሁሉም በአንድ ድምፅ የሚናገሩት ሠራዊቱ ዉስጥ ይደርስባቸዉ የነበረዉ ንቀትና ዉርደት የሰዉ ልጅ መሸከም ከሚችለዉ በላይ መሆኑን ነዉ።
ሕወሓትን ለረጂም ግዜ የመራዉ መለስ ዜናዊና ጓደኞቹ ሥልጣን በያዙባቸዉ በመጀመሪያዎቹ ሁለትና ሦስት አመታት ጊዜያት ቁልፍ የሆኑ ቦታዎች ሰዎች መያዛቸዉን አስመልክተዉ ሲናገሩ ህወሓት ለ17 አመታት የደርግን አምባገነናዊ ስርዓት ሲዋጋ የፈጠረዉ ወታደራዊና ድርጅታዊ ግዝፈት አብዛኛዉ የወታደራዊና የደህንነት አመራር ቦታ በህወሓት ታጋዮች አንዲያዝ ምክንያት ሆኗል ብለዉ ከተናገሩ በኋላ ይህ አሰራር በሂደት ሙሉ በሙሉ እንደሚቀይርና የኢትዮጵያ የፖለቲካና ወታደራዊ የሥልጣን ክፍፍል የአገሪቱን ብሄር ብሄረሰቦች ጥንቅር ያገናዘበ ይሆናል ብለዉ ተናግረዉ ነበር። ሆኖም ዛሬ ይህ ከተነገረ ከሃያ አመታት በኋላና ይህንን የተናገረዉ መለስ ዜናዊ ከዚህ አለም በሞት ከተለየ ከሁለት አመታት በኋላ የሕወሓት የሥልጣን ቁጥጥር ጭራሽ አጋሽቦ ዛሬ ኢትዮጵያ ዉስጥ ከትግርኛ ቋንቋ ዉጭ የሌላ ቋንቋ ተናጋሪዎች ወደ ሥልጣን አይመጡም የሚባልባት አገር ሆናለች። በኢትዮጵያ ዉስጥ ወያኔ በገነባዉ መከላከያ ሠራዊት ዉስጥ የዕዝ፤ የክፍለጦርና የመምሪያዎች አዛዥ ለመሆን ዋነኛዉ መለኪያ የትግራይ ብሄረሰብ ተወላጅና የሕወሓት ታማኝ አገልጋይ መሆን ነዉ እንጂ ችሎታ፤ ልምድ፤ ብቃትና የወታደራዊ ሳይንስ ክህሎት አይደለም። ችሎታ፤ ልምድና ብቃት መመዘኛ ሆነዉ የሚቀርቡት በመጀመሪያ ለሹመት የታጨዉ መኮንን የትግራይ ተወላጅ እና የሕወሓት ታማኝ አገልጋይ መሆኑ ከተረጋገጠ በኋላ ብቻ ነዉ።
የሕወሓት የስልጣን ሞኖፖሊ በወታደራዊ ደህንነት ተቋሞች ላይ ብቻ ተወስኖ አያበቃም። አብዛኛዉን የአገሪቱ የኤኮኖሚና ማህበራዊ ተቋሞችም ወይ ከላይ አለዚያም ከታች ሆነዉ የሚቆጣጠሩት የሕወሓት ታማኝ አገልጋይ ትግርኛ ተናጋሪዎች ናቸዉ። ዛሬ ኢትዮጵያ ዉስጥ ለይስሙላ የተቀመጠና ከተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦች የመጡ ሰዎች የሚገኝበት አገዛዝ አለ፤ በዚህ አገዛዝ ዉስጥ ደግሞ አገሪቱን ወዳሰኘዉ አቅጣጫ በዘፈቀደ የሚዘዉረዉና ከትግርኛ ተናጋሪዎች ዉጭ ሌሎች የማይገኙበት በአገዛዙ ዉስጥ ሌላ ቡድናዊ አገዛዝ አለ። ዛሬ እነ ኃ/ማርያም ደሳለኝ፤ አባዱላ ገመዳና ደመቀ መኮንንን የመሳሰሉ ምስለኔዎች ስልጣን ላይ የተቀመጡ ነገር ግን የሕወሓት ጌቶቻቸዉ ከሚነግሯቸዉ ዉጭ በራሳቸዉ ምንም አይነት ትዕዛዝ መስጠት የማይችሉ አሻንጉሊቶች መሆናቸዉን እነሱ አራሳቸዉም የተገነዘቡት ይመስላል።
ግንቦት ሰባት- የፍትህ፤ የነጻነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ የዛሬ አራት አመት (እ.ኤአ.በ2009) በዘር የተደራጀዉን የወያኔ መከላከያ ተቋም አደረጃጀት ምን እንደሚመስል በመረጃ አስደግፎ ለአለም ህዝብ ማቅረቡ የሚታወስ ነዉ። ግንቦት ሰባት ይህ ይሻሻላል ወይም አደረጃጀቱ በሂደት ይለወጣል ተብሎ የተነገረለት የወያኔ መከላከያ ተቋም ጭራሽ ከድጡ ወደማጡ እያዘገመ መሆኑን በጥናታዊ መረጃዎች አስደግፎ እንደሚከተለዉ ያቀርባል። በዚህ ጥናት ዉስጥ የወያኔን መከላከያ ሠራዊት ይዘትና ቅርጽ በሚገባ የሚያዉቁ፤ ሠራዊቱን ለቅቀዉ የወጡና አሁንም በሠራዊቱ ዉስጥ በማገልገል ላይ የሚገኙ ከፍተኛ መኮንኖች ተሳትፈዋል። ከዚህ ቀጥሎ የሚቀርበዉ ሠንጠረዥ የተለያዩ የመከላከያ ተቋም የስልጣን ቦታዎችን፣ በስልጣን ቦታዎችን እነ ማን እንደተቀመጡና የተወለዱበትን ብሄረሰብም ጭምር ያሳያል።