ይድነቃቸው ከበደ
“ልዩነት የግድ ጥላቻን ወይም ድብድብን ማስከተል አለበት ብለው የሚያምን እና የሚያስብ በድርጊቱም የሚገፉ ካለ ከባድ ስዕተት ነው፡፡ ፣ልዩነትን በአንድ ጊዜና ሙሉ በሙሉ ማጥፋት ባይቻልም በሰለጠነና በሰከነ አካሄድ በውይይትና በሀሳብ ልውውጥ ማጥበብ ይቻላል፡፡” ለዚህም ይመስላል አንድነት ፓርቲ ውስጣዊ ችግሩን ሙሉ ለሙሉ ባይባልም መሠረታዊ ችግሩን በሰለጠነ መንገድ ለመፍታት የቻለው፡፡ የዚህም ጥሩ ማመላከቻ የሚሆነው ኢ/ር ግዛቸው ሽፈራው በገዛ ፍቃዳቸው ሃላፊነታቸውን መልቀቃቸው እና በምትካቸው የአብዛኛውን የፓርቲ አባል መልካም ፍቃድ ያገኙት፣ አቶ በላይ በፍቃዱ መመረጣቸው ነው፡፡ይህ ደግሞ ለአመራር ለውጥ የተሄደበትን መንገድ በአብዛኛው ጤናማ ለመሆኑ በቂ መረጃ ነው፡፡
እርግጥ ነው በሂደቱ እንደ መልካም ተሞክሮ ለመውሰድ የሚቸግሩ፣ ጠቃሚ ያልሆኑ የሃሳብ ልውውጦች ለማየት እና ለመታዘብ ተችሎአል፡፡በተለይ በኢ/ር ግዛቸው የስራ አፈፃፀም ደስተኞች ባልነበሩ በተወሰኑ የፓርቲው አባላት የታዩ ችግሮች መኖራቸው የማይካድ ሃቅ ነው፡፡ይሁን እንጂ በፓርቲው አባላቶች እና አመራሮች እንዲሁም በድጋፍ ሰጪዎች ከባድ ጥረት የተገኘው ውጤት፤ያለፈው ስዕተት በማስታወስ ዋጋውን የሚያስቀንሰው አይደለም ! በመሆኑም አሁን ላይ ለደረሳችሁበት አስደሣች ውጤት እንኳን ደስ አላችሁ ላለማለት ለውጥ ፈላጊ ለሆነው ሁሉ ለዴሞክራሲ ሃይሎች ምክንያት ይኖራል ብዬ አልገምትም፡፡
ይበልጥ ደግሞ ሂደቱን ለየት የሚያደርገው ኢ/ር ግዛቸው በገዛ ፍቃዳቸው ከስልጣናቸው መልቀቃቸው ሳይሆን የለቀቁበት መንገድ ነው፡፡ ለሁላችንም ግልፅ እንደሆነው ሁሉ አብዛኛው የአንድነት ፓርቲ አባላት በኢ/ር ግዛቸው የስራ አፈፃፀም እና ውሣኔ አሰጣጥ ደስተኞች አልነበሩም ፡፡ሆኖም ግን ምንም ጊዜ ቢወስድም “በእኔ የሰራ አፈፃፀም ደስተኛ ባለመሆናችሁ፣ ከምንም በላይ ደግሞ ፓርቲው ስለሚበልጥ ሃላፊነቴን በገዛ ፍቃዴ ለቂቃለው” ማለታቸው እና ውሳኔቸውን ተግባራዊ ማድረጋቸው ለኢ/ር ግዛቸው አድናቆትን የሚያሰጥ ነው፡፡
ከምንም በላይ ግን በኢትዮጵያ የ23 ዓመት የተቃዋሚ ፓርቲዎች ጉዞ በአባላት ቅሬታ እና ነቀፊታ ከስልጣን ዘመኑ በፊት ሃላፊነቱን የለቀቀ የፓርቲ መሪ ቁጥር አንድ ሊያስብል የሚያስችል ታሪክ ኢ/ር ግዛቸው ለማስመዝግ ችለዋል፡፡ ይህ ማለት ግን የኢ/ሩ የቀድሞ ስዕተቶች ይረሳሉ ማለት አይደለም፡፡ለቁጥር የበዛ በማወቅም ባለማወቅም በኢትዮጵያ የተቃውሞ የፖለቲካ እንቅስቃሴ የሰሯቸው ስዕተቶች አሉ፡፡ በተለይ ዛሬ ላይ ሆነው የሰሩት መልካም ስራ ማለትም የአባለት ቅሬታ እና ነቀፌታ የማዳማጥ ልምድ “ያኔ ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም ያካተተው የ “መርህ ይከበር” ጥያቄ ወቅት አድርገውት ቢሆን ኖሮ አንድነት ፓርቲ ብቻ ሣይሆን የኢትዮጵያ የተቃዋሚ እንቅስቃሴ ከፍ ከማለትም ባለፈ ፤አሁን ካለበት ደረጃ በእርግጠኝነት የወያኔን የአገዛዝ ሥርዓት ጭርሶ ባያጠፋውም የሚያሽመደምደው ነበር፡፡
በመሆኑም ሰው በገባው ልክ የሚኖር ፉጡር እንደመሆኑ መጠን በገባቸው ቀን የሚገባቸውን በማድረጋቸው እኔም ብሆን አድናቆቴን ለመግለፅ እገደዳለው፡፡ አሁን ላይ በመሆን የባለፈውን በማንሳት ለተጀመረው ሁለንታናዊ የሰላማዊ ትግል ወደፌት ፈቀቅ የማያደርግ፣ ማናቸውን ነገሮች ማንሣት አስፈላጊ እንዳልሆን፤ መገመት ቀላል ነው፡፡ ሆንም ግን ችግሮችን ማስታወስ ክፋት አይኖረውም፡፡ስለዚህም ዛሬ አንድነት የደረሰበት አስደሳች ውጤት ያለፉትን ስዕተቶች ድርጅታዊ ለውጥ ለማምጣት እንደግባት ከመጠቀም ሊያግደው የሚችል ነገር አይደለም ለማለት ያስደፍራል፡፡
አንድነት ዛሬ ከችግሮች መካከል አንዱን ቀረፍ እንጂ ሙሉ በሙሉ ውስጣዊ የፓርቲ ችግሮችን ፈታ ማለት አይደለም፡፡ከዚህ ቀደም የነበረ፣አሁን ደግሞ የተገኘውን ውጤት መሠረት ያደረገ በራሱ የሚፈጠር ብዙ ችግሮች ይኖራሉ፣ውጫዊ የገዥው ሥርዓት ተፅኖ እንደተጠበቅ ሆኖ ፡፡ ስለዚህም አዲሱ የፓርቲው ሊ/ቀ ወጣቱ በላይ ፍቃዱ ከፍተኛ የሆነ ስራ ይጠብቀዋል፣ በተለይ ደግሞ የእሱ የሃሳብ ተቀናቃኝ የሆኑት የአንድነት ፓርቲ አባለት ከበሆደ ሰፊነት ባለፈ ሃሳባቸውን ሊሰማቸው እና በተግባር ሊያሳትፋቸው ይገባል፡፡በይበልጥ ደግሞ ከሌላ አቻ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር መዋቅራዊ ወይም የስራ ግንንነቶች በይበልጥ እንዲፈጠሩ የማድረግም ሃላፊነት ጭምር አለበት፡፡በአሰራሩም ግልፅነት እና ተጠያቂነት ያለው የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ሲያቆቁም ሥራን እንጂ ሌላ የጎንዩሽ ጥቅምን መሠረት ያላደረገ መሆኑ ማረጋገጥ አለበት፡፡ኢ/ር ግዛቸውም በፓርቲያቸው ውስጥ አቅማቸው እና ጊዚያቸው በፈቀደው መልኩ የማገልገልም ሃላፊነታቸውም እንደተጠበቀ ነው፡፡
በመጨረሻም ለአንድነት ፓርቲ አባለት፣አመራሮች ፣ድጋፍ ሰጪዎች እና ለአዲስ ወጣቱ ሊ/ቀ በላይ ፍቃዱ ለደረሳችሁበት ውጤት እንኳን ደስ አላችሁ ለማለት እወዳለው! ይህ የግሌ የሆነው ሃሳብ ከማጠቃለሌ በፊት የጋሽ መስፍን “ሥልጣን ባህልና አገዛዝ ፖለቲካና ምርጫ” ከሚለው መፃፈቸው ገፅ 32 የሚገኘውን ፅሑፍ ሁላችንም ት/ት እንድንወስድበት በመጋበዝ ነው፡፡ “እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ወደ ፖለቲካ ሲገባ ከልጅነት እስከ እውቀት በውስጡ የተመረገውን ጌትነትና የሎሌነት ባህል ፍቆ ፈቅፍቆ ማረገፍ አለበት፡፡ በግድ የአስተሳሰብ የጽዳት ዘመቻ ያስፈልገናል፡፡ ዓላማን የማጥራት ዘመቻ ያስፈልገናል፡፡ በግድ የነጻነትና የእኩልነት አራማጆች በቁርጠኝነት መነሳትና ማሳየት ያስፈልገናል፡፡ ብዙዎች የተቀናቃኝ መሪዎች ላይ የሚታየው የድሮው መኳንንትና መሳፍንት ለመምሰል የመሞከር ጠባይና ከዚህም ጋር ተያይዞ ሎሌዎችን በገንዘብ ሆነ በወደፊት ተስፋ እየገዙ የአገዛዝን ባህል ለማራመድ የሚደረገው ሙከራ የፖለቲካውን ሥርዓት አያራምድም፡፡ ጥረቱ ሁሉ በሥልጣን ላይ ያሉትን ሰዎች ለመለወጥ እንጂ ሥርዓትን ለመለወጥ አይመስልም፡፡”
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር !!!