Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

የተዋረደው ሰንደቅ አላማ ‹‹የክብር›› ቀን (ጌታቸው ሺፈራው)

$
0
0

ጌታቸው ሺፈራው

በዓለማችን ተፅዕኖ ፈጣሪ ከሆኑት ሰንደቅ አላማዎች መካከል የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ በቀዳሚነት ይገኝበታል፡፡ በጸረ-ቅኝ ግዛት ትግሉ ወቅት በመላው ዓለም የሚገኙ ጥቁሮች ከነጻነት ምልክትነቱም በተጨማሪ አንዳች ኃይል ያለው አድርገው ወስደውታል፡፡ በተለይ ከቅኝ ግዛት ትግሉ በኋላ በርካታ የአፍሪካና የካሪቢያን አገራት የኢትዮጵያን ሰንደቅ ምልክታቸው አድርገው ተጠቅመውበታል፡፡ ከዚህም የተነሳ በሰንደቅ አላማ ላይ ጥናት የሚያደርጉ ምሁራን የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ የአፍሪካ ሰንደቅ አላማዎች ዘር ይሉታል፡፡

10482065_596327470492915_3458501353410632231_nየኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ተጽዕኖ ፈጣሪ ከሆኑት ከዓለም ሰንደቅ አላማዎች ቀዳሚው እንደመሆኑ ለሌሎች ህዝቦች ተጽዕኖ ፈጣሪ ሆኖ በራሱ መሪዎች የተዋረደው ብቸኛው ሰንደቅ አላማም ሳይሆን አይቀርም፡፡ በርካታ የአፍሪካና የካሪቢያን አገራት የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ በምልክትነት ሲወስዱ የወቅቱ የኢትዮጵያ ገዥዎች ግን የኢትዮጵያውን ሰንደቅ አላማ ቀለም ትተው ከአውሮፓና ከአረብ አገር የተዋሱትን ሰንደቅ አላማ ክብር ከነበረው የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ጎን ያንጠለጥሏቸዋል፡፡

ሻዕቢያና ጀብሃ ሰንደቅ አላማውን ለማዋረድ (ጨርቅ ለማስመሰል) ከዓረብ አገራት በእርዳታ ያገኙት የነበረውን ዱቄትና በሰሜን ኢትዮጵያ የሚበቅለውን በለስ ቋጥረውበታል፡፡ ከሻዕቢያ ስር ሆኖ የጎለመሰው ህወሓት የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ ስለማዋረድ ከሻዕቢያ ልምድ ቀስሟል፡፡ በመሆኑም እሱም እንደ ሻዕቢያ የዱቄት መቋጠሪያ አድርጎት እንደነበር ይነገራል፡፡ አቶ መለስ ዜናዊ ሰንደቅ አላማውን ‹‹ጨርቅ›› ያሉትም ከምንም ተነስተው ሳይሆን በአንድ ወቅት ሻዕቢያ ባስተማራቸው መሰረት እንደ ጨርቅ ሲጠቀሙበት ስለነበር ነው፡፡ ህወሓት/ኢህአዴግ ሰንደቅ አላማውን የማዋረድ ታሪክ ገና ከጫካ የጀመረ በመሆኑ ለሰንደቅ አላማው ያላው ንቀትና ጥላቻ በዚሁ መልኩ ደሙ ድረስ ዘልቆ ገብቷል ማለት ይቻላል፡፡ ለዚህም ነው አከበርኩ እያለ እንኳን ማክበር ያልቻለው፡፡

ህወሓት/ኢህአዴግ መጀመሪያ ላይ ንጹሁን ከዛም በኋላ ውሃማ ሰማያዊ ክብ ያለበት፣ በቅርቡ በ654/2001 ዓ.ም በወጣው የሰንደቅ አላማ አዋጅ ደግሞ ደማቅ ሰማያዊ መደብ ላይ ያረፈ ክብ ያለበት ሰንደቅ አላማን የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ አድርጎ እየተጠቀመበት ነው፡፡ በዚህም መሰረት በቅርብ አመታት የሰንደቅ አላማ ቀን በዓል እያከበረ ነው፡፡ ከውስጥ ያልመነጨን ነገር መተግበር አይቻልምና አከብራለሁ እያለም እያወረደው ዛሬ ድረስ ደርሷል፡፡ በሌላ በኩል ገዥዎቹ ለሰንደቅ አላማ ክብር የሌላቸው መሆናቸውና የአሁኑ ሰንደቅ አላማ (በተለይ መሃል ላይ ያለው ምልክት) ያለ ህዝብ ፈቃድ መለጠፉ አሁን ‹‹የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ›› የሚባለው ህዝቡም ከላይ የተጫነበት እንጂ የራሱ እንዳልሆነ በማመኑ በሁሉም ወገን ክብር ተነፍጎታል፡፡

የዚህ ጽሁፍ አላማም ኢህአዴግ ለሰንደቅ አላማው አዋጅ አውጥቶ፣ የክብር ቀን ቆርጦ አከብረዋለሁ ቢልም ለይስሙላህ እንጂ ክብር እንደማይሰጠው ለማሳየት ነው፡፡ በሰንደቅ አላማው አዋጅ በአንቀጽ 6/1 መሰረት ‹‹ሰንደቅ አላማው ከላይ አረንጓዴ፣ ከመሃል ቢጫ፣ ከታች ቀይ›› ይኖረዋል ይላል፡፡ መሃል ላይ ያለው ኮከብ አቀማመጥንም ያስቀምጣል፡፡ ነገር ግን በየ ካፌው ሌላ ሰንደቅ አላማ (መሃል ላይ ክብ ያለውን) ከሌለው ንጹህ ሰንደቅ አላማ በማዳቀል (በክር ተሰፍቶ) የተሰቀሉት ይበልጣሉ፡፡ ምንም እንኳ በየካፌው ሰንደቁን መስቀል የማይፈቀድ ቢሆንም፣ ህጉ ተጥሶ በዘፈቀደ ተንጠልጥሎ ይገኛል፡፡

በአዋጁ ከተቀመጠው ቀለምና አቀማመጥ ውጭ የተሰቀለ ሰንደቅ አላማ በእስርና በገንዘብ እንደሚስቀጣ ተደንግጓል፡፡ ሆኖም ግን አዋጁን የደነገጉት አካላት አይጠቀሙበትም፡፡ ለአብነት ያህል አቶ መለስ ዜናዊ ከመሞታቸው ከወራት በፊት ኬንያ ላይ ሰንደቅ አላማውን ከላይ ወደታች ገልብጠውት ታይተዋል፡፡ በአዋጁ መሰረት አቶ መለስ ዜናዊ ቢያንስ በገንዘብ 3000 ብር አሊያም አንድ አመት እስር ይጠብቃቸው ነበር፡፡ ሆኖም ግን አቶ መለስ ዜናዊ ምንም ሲባሉ አላየንም፡፡

በዚሁ በማይከበረው አዋጅ 6/2 መሰረት ‹‹ቀለማቱ ብሩህና ደማቅ መሆን አለባቸው›› ይላል፡፡ ነገር ግን የተለያዩ ቁልፍ የ‹‹መንግስት›› ተቋማት ሳይቀሩ ይህን ህግ በሻረ መንገድ ሰንደቅ አላማውን ሲያውለበልቡ ይታያሉ፡፡ ለአብነት ያህል በሽብርተኝነት ተጠርጥረዋል ተብለው የሚታሰሩ ኢትዮጵያውያን የሚቀርቡበት የአራዳ ችሎት ለረዥም ጊዜ የተጠቀመበት የተበጣጠሰ ሰንደቅ አላማ (ሰሞኑን ቀይረውታል) በምሳሌነት ማንሳት ይቻላል፡፡ ከዚህም ባሻገር እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ፓርላማ ያረጀና የተቀዳደደ ሰንደቅ አላማ ያውለበልብ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ሁለቱን መስሪያ ቤቶች ጨምሮ በበርካታ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ሰንደቅ አላማው ማታ ሲወርድ አይታይም፡፡ በአራዳ ችሎትና ፓርላማውን የመሳሰሉት ምን አልባትም ከአመት በላይ ሰንደቅ አላማው ሳይቀየር ስለተሰቀለ ነው እንደዛ የተበጣጠሰው፡፡ ለይስሙላ የወጣው አዋጅ ግን ጠዋት 12 ሰዓት ተሰቅሎ ማታ 12 ሰዓት መውረድ አለበት ብሎ ደንግጓል፡፡

በአዋጁ 6/3 የሰንደቅ አላማው ወርድ የቁመቱን እጥፍ ይሆናል ይላል፡፡ በሌላ የአዋጁ ክፍልም ለህንጻዎች መሸፈኛ መሆን የለበትም ይላል፡፡ ነገር ግን በተለያዩ ካፌዎች፣ ባንኮችና የመንግስት መስሪያ ቤቶች ሰንደቅ አላማው አብዛኛውን የህንጻዎች ክፍል ሸፍኖ ይታያል፡፡ (የፈተናዎች ድርጅት ህንጻ፣ የአዲስ አበባ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ፣ አዋሽ ባንክ ላይ ማየት ይቻላል) ይታያል፡፡ በእነዚህና በሌሎች መስሪያ ቤቶችና ህንጻዎች ሰንደቅ አላማው የህንጻዎቹን አብዛኛ ክፍል ሸፍኖ (ማስጌጫ ሆኖ) ይታያል፡፡

የሰንደቅ አላማው አዋጅ አንቀጽ 10 ሰንደቅ አላማው 6 የተለያዩ መጠኖች እንደሚኖሩት ይገልጻል፡፡ 1ኛ. 210 በ420፣ 2ኛ 150 በ300፣ 3ኛ 135 በ 270፣ 4ኛ 105 በ 210፣ 5ኛ 90 በ180፣ 6ኛ 21 በ 42 ናቸው፡፡ አንደኛው በከፍተኛ አደባባይ ላይ የሚሰቀል ነው፡፡ ሁለተኛው በመካከለኛ አደባባይ ይሰቀላል፡፡ ሶስተኛው በመስሪያ ቤቶች፣ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፣ በትልልቅ የመንግስት ህንጻዎችና የድርጅቶች አደባባዮች የሚሰቀል ነው፡፡ አራተኛው በትልልቅ ህንጻዎች ይሰቀላል፡፡ በከፍተኛ መርከቦችና በሰልፍ ጊዜ በክብር ዘብ ይያዛል ይላል፡፡ አምስተኛው የውጭ አገር እንግዶችን ለመቀበልና በበዓላት በየ መንገዱ የሚውለበለብ ነው ይላል፡፡ በስድስተኛ ደረጃ የተቀመጠው ሰንደቅ አላማ መጠን በፕሬዝዳንቱ፣ በጠቅላይ ሚኒስትሩና በአምባሳደር ጽ/ቤት ጠረጴዛ ላይ እንደሚቀመጥ ይደነግጋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በፕሬዝዳንቱና በአምባሳደር መኪና ላይ 20 በ 30 ሴንቲ ሜትር የሆነ ሰንደቅ አላማ ይሰቀላል ይላል፡፡ ከተደነገገው ህግ ውጭ በሌሎች የመንግስት መስሪያ ቤቶችም (በተለየ ህግ ካልተከለከለ በስተቀር) ይሰቀላል ይላል፡፡ በካፌ፣ ጸጉር ቤት፣ ስጋ ቤት፣….ይሰቀላል ብሎ የሚደነግግ ነገር የለም፡፡ ለዛሬው በዓል ግን እነዚህ ቤቶች በተለያየ ቁመትና ወርድ ሰንደቅ አላማ ከቀበሌ ታድሏቸው በየ ቦታው አንጠልጥለውታል፡፡

ትልቁ ሰንደቅ አላማ (210 በ420) በአደባባይ የሚሰቀለው ነው፡፡ ይህ ማለት ደግሞ ትልቁ ከ2 እስከ አራት ሜትር ተኩል ብቻ እንደሚሆን የሚያሳይ ነው፡፡ ሆኖም የመንግስት መስሪያ ቤቶችና ባንኮች አብዛኛውን ህንጻቸውን ያስዋቡት እንዳለ ሆኖ ለዛሬው በዓል የቀበሌ መዝናኛዎች፣ ካፌዎችና ሌሎች ንግድ ቤቶች ከአንደኛው በረንዳ ጫፍ እስከ ሌላኛው በረንዳ ጫፍ የሰቀሏቸው ሰንደቅ አላማዎች በአንደኛ ደረጃ ከተቀመጠው በብዙ እጥፍ የሚበልጡ (የሚረዝሙ) ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ በተለያዩ ንግድ ቤቶች አንዳንዶች ከግራ ቀደ ቀኝ አረንጓዴ፣ ቢጫ ቀይ አሊያም በተገላቢጦሹ ሰቅለውታል፡፡ ካድሬዎቹን ለማስደሰት እንጅ የሚያምኑበት ብዙዎቹ ባለመሆናቸው አንዳንዶቹ ታዛው ላይ፣ ሌሎቹ መስኮት አሊያም ያገኙት ቦታ ላይ መሬት እስኪነካ አንዘላዝለውታል፡፡

በአዋጁ አንቀጽ 16 የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ከላይ በተደነገገው መሰረት አንድ አይነት ነው ይላል፡፡ ነገር ግን ለዛሬው በዓል ከተሰቀሉት መካከል በአሁኑ አዋጅ የተቀየረው መሃሉ ላይ ውሃማ ሰማያዊ ያለበትም በስፋት ተሰቅለው ይገኛሉ፡፡ አንቀጽ 17 ሲያረጅ፣ ሲበላሽ ወይንም በሌላ መንገድ በክብር ይቃጠላል፤ ይቀበራል ቢልም ይህ ግን ሲሆን አይታይም፡፡ አንቀጽ 18 ሰንደቅ አላማው ከክልል ሰንደቅ አላማዎች ጋር የሚሰቀልበትን መንገድ የተዘረዘረበት ነው፡፡ ከፍ ብሎ መሰቀል አለበት፡፡ ከሁለት ጋር ቢሆን መሃል ላይ ይሆናል፡፡ ከሁለት በላይ ከሆኑ በስተቀኝ በኩል መጨረሻ ሆኖ ይውለበለባል፡፡ ይህም ቢሆን ሰንደቅ አላማው ውስጣቸው በሌለው ገዥዎች ዘንድ የሚታወስ አይደለም፡፡ ለአብነት ያህል ስድስት ኪሎ አካባቢ የሚገኘው የኦሮሚያ የፍትህ ቢሮ ላይ ሁለት የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማዎች ያውም ያሰቃቀሉን ህግ በማያሟላ መልኩ ከክልሉ ሰንደቅ አላማ ዝቅ ብሎ ተሰቅሏል፡፡

አንቀጽ 22 በማኝኛውም ጊዜ ሰንደቅ አላማው ዝቅ ብሎ አይውለበለብም ይላል፡፡ እነሱ ግን በየ ጉራንጎሩ ሲፈልጉ ገልብጠው ያውለበልቡታል፡፡ ምንም እንኳ በፕሬዝዳንቱ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩና አምባሳደሩ መኪና ብቻ እንደሚውለበለብ ቢደነገግም ለዚህ በዓል ሲባል ታክሲና ባባጆች ሳይቀር እንዲያውለበልቡ ታድሏቸዋል፡፡

አንቀጽ 22 ሰንደቅ አላማ በቀብር ወቅት መሆን ስላለበበት ሁኔታ የሚገለጽበት ነው፡፡ በአንቀጹ ‹‹ቀብሩ ከመፈጸሙ በፊት በአስከሬን ሳጥኑ ላይ ያረፈው ሰንደቅ አላማ በተገቢው ስነ ስርዓት ተጣጥሮ መነሳት ያለበት ሲሆን በማንኛውም መልኩ መሬት መንካት የለበትም›› ይላል፡፡ ነገር ግን በአንድ ወቅት ጨርቅ እንዲመስል ዱቄት የቋጠሩበት፣ ከዛም ጨርቅ ብለው የዘለፉት፣ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ ገልብጠውት የታዩት አቶ መለስ ዜናዊ አስከሬን ላይ ሲቀበር ሁላችንም በቴሊቪዥን ያየነው ኃቅ ነው፡፡

ህወሓት/ኢህአዴግ በሰንደቅ አላማው ላይ ይህን ያህል ኃጢያት ሲሰራ አንድም ቀን ይቅርታ ጠይቆ አያውቅም፡፡ ይህን ሁሉ ሲሰራ ማንም ጠይቆት አሊያም ተቀጥቶ አላየንም፡፡ በተቃራኒው ግን ለሰንደቁ እንደቆመ ለማሳየት ይሞክራል፡፡ የዛሬው በዓልም ለማያምንበትና በውስጡ ለሌለው ሰንደቅ አላማ ክብር እሰጥበታለሁ የሚለው እንዲህ ከራሱ ህግ ጋር እየተቃረነ እና እያዋረደው ነው


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>