Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

አገሩን ያልተቀማው ተመስገን!

$
0
0

ከጌታቸው ሽፈራው

ህዝብን ተስፋ ካስቆረጠው 97 ምርጫ በኋላ አዲስ ነገረ ጋዜጣ የመረጃ ምንጭ፣ የመወያያ መድረክና ነቃሽ መሆን ችላ ነበር፡፡ ብዕርን አብዝቶ የሚፈራውና ህዝብ አማራጭ መረጃ ሲያገኝ እንቅልፍ የሚያጣው ገዥ ፓርቲ የአዲስ ነገር ጋዜጠኞችን ማዋከቡን ተያያዘው፡፡ ጫናው እየተጠናከረ በሄደበት አንድ ቅዳሜ ጋዜጠኛ መስፍን ነጋሽ ‹‹ይህ አገር የማን ነው?›› በሚል ስርዓቱ የሚያደርገውን አፈና፣ አዲስ ነገር ላይ እየደረሰ ያለውን በደል ዘርዝሮ አስረዳ፡፡ አገሩ የኢትዮጵያውያን ቢሆንም ገዥዎቹ እንደነጠቁን፣ መስራት እንዳልተቻለ በድንቅ የጽሁፍ ችሎታው ቀምሮ አስነበበ፡፡ ተወዳጇ አዲስ ነገር ከዛ ቀን በኋላ ለአንባቢዎች አልደረሰችም፡፡ አገራቸውን የተነጠቁት የአዲስ ነገር ጋዜጠኞችም የተቀሙትን አገር ትተው ተሰድደዋል፡፡
temesgen desalegn

አዲስ ነገር ከተዘጋች በኋላ አውራምባ ታይምስ በአማራጭነት አንባቢዎች እጅ መድረስ ጀመረች፡፡ አሁን ደግም ገዥዎቹ ሙሉ አቅማቸውን ወደ አውራምባ አዙረዋል፡፡ በአንድ ማስክሰኞ ጠዋት ላይ የያኔው ጋዜጠኛ ዳዊት ከበደ የጋዜጠኛ መስፍን ነጋሽን ርዕስ ተውሶ ‹‹ይህ አገር የማን ነው?›› የሚል መጣጥፍ አሰነበበ፡፡ ርዕሱን ፊት ላይ ላየው አንባቢ መልዕክቱ ግልጽ ነበር፡፡ አስደንጋጭ መልዕክልት፡፡ ‹‹አውራምባዎች ሊሰደዱ ነው፡፡›› የተፈራው አልቀረም ዳዊት ከበደ ተሰደደ፡፡ አውራምባ ተዘጋች፡፡

ከዚህ በኋላ ፍትህ ሌላ አማራጭ ሆና ወጥታለች፡፡ አርብ አርብ ‹‹ፍትህ ምን አለች?›› ብለው ተቀዳድመው የሚገዟት ተበራክተዋል፡፡ በተለይ በፊት ገጽ ላይ ይዛው የምትወጣው የፎቶ ቅንብር መልዕክቱን በግልጽ የሚያስተላልፍ በመሆኑ የማያነበውን አልፎ ሂያጅ ህዝብም ጭምር የሚስብ ነበር፡፡

ግን አሁንም ገዥው ኢህአዴግ ነው፡፡ አፈናው በዛ እንጅ ሊቀንስ አልቻለም፡፡ እናም ፍትህ ላይም አፈናው ተጠንክሮ ቀጥሏል፡፡ ፍትህ በምትጠበቅበት አንድ አርብ ጠዋት ላይ ያ አስደንጋጭ ርዕስ ለሶስተኛ ጊዜ ተደገመ፡፡ አንባቢዎች ደነገጡ፡፡ ‹‹ይህ አገር የማን ነው?›፡፡ መልዕክቱ ግልጽ ነበር፡፡ ፍትሆች መሰደዳቸው ነው፡፡ ጽሁፉን የጻፈው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ነው፡፡ አብዛኛው የጽሁፉ ክፍል ጋዜጠኛ መስፍን ነጋሽም ሆነ ጋዜጠኛ ዳዊት ከበደ ከጻፉት ጋር የሚስማማበት፣ የአፈናውን አስከፊነት የሚገልጽበት በመሆኑ ተመሳሳይ ነው፡፡ ይህ ጽሁፍ የሚለየው በድምዳሜው ብቻ ነው፡፡

ተሜ! አገሩ በገዥዎች ቁጥጥር ስር ብትሆንም ለማንም ጥሎ እንደማይሄድ ቃል ገባ፡፡ ‹‹አልሰደድም!›› አለ፡፡ የመጣው ቢመጣ ያለመሰደድ ምልክት ሆነ፡፡ ተሜ! አገሩ በሌሎች እጅ ቢሆንም አገሩን አምኖ ያልተቀማው ጋዜጠኛ ነው፡፡ ፍትህ ስትዘጋ አዲስ ታይምስ፣ እሷም ስትዘፋ፣ በፋክት በመምጣትም ተስፍ ያለ መቁረጥም ምልክት ሆነ፡፡

ተመስገን ደሳለኝ በየጊዜው ከሚከፈቱበት ክሶች ባለፈ በ‹‹ሙስሊም›› ስም ኢሜል እንደተላከለት፣ ከአልሻባብ ጋር ግንኙነት እንዳለው በማስመሰል ‹‹ሊጠልፉት›› ሞክረዋል፡፡ እሱ ግን ቀድም ‹‹አልሸባብና ፍትህ ምን አገናኛቸው?›› ሲል የሚሰራበትን ሴራ አጋልጧል፡፡ ከአገር እንዲወጣ በተለያየ መንገድ እንደገፋፉት ተሰምቷል፡፡

በአንድ ወቅት ስፖርት፣ አሊያም ፋሽን ጋዜጣና መጽሄት ላይ ሲሰሩ የነበሩ ሚዲያዎች የ‹‹ፖለቲካው ገበያ›› ሲደራ ስምና ቅርጽ እየቀየሩ ሲመጡ ይታያል፡፡ በዚህም ምክንያት ሚናውን ለይቶ የሚገባ ሚዲያና ጋዜጠኛ ቁጥሩ አነስተኛ ነው፡፡ ተሜ ለአገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ ያስፈልጋል ያለውን የሚዲያ ሚና (የአርነት ሚዲያ) ለይቶ የገባ ጋዜጠኛ ነው፡፡ ቢከስር፣ ቢታፈንበት፣ ማስታወቂያ ባይኖረው፣ ማከፋፈያውና ሌላው ቦታ ላይ ችግር ቢኖር ‹‹ያበላል›› ወዳለው አላወላወለም፡፡ ፍትህ፣ አዲስ ታይምስ፣ ፋክት ሚናቸው ተመሳሳይ ነበር፡፡ ከኢንተርኔት እየቃረሙ ከሚያሳትሙት፣ በገዥው ፓርቲ ጎትጓችነት ሳይቀር ማስተዋቂያ የሚቸራቸው፣ በነጻ በሚባል ዋጋ ጋዜጠኛውን ከሚበዘብዙ ሚዲያዎች ጋር እየተወዳደረ ከቆመበት ሚና ወደኋላ አላለም፡፡ ‹‹አገሬ በገዥዎቹ ስር ብትሆንም፣ ለእኔም አገሬ ናት፡፡ አልሰደድም!›› ያለው ተመስገን አገሩን አሰልፎ፣ አምኖ አልተቀማምና እስከመጨረሻው በዓላማው ጸንቷል፡፡

በስርዓቱ አፋኝነት ምክንያት ብዙዎቹ ምሁራን በገዛ ፈቃዳቸው አፋቸውን አፍነዋል፡፡ ጋዜጠኞች ብዕራቸውን ድርቋል፡፡ ብዙው ደግሞ ከዝምታም በላይ አድር ባይ ሆኗል፡፡ አገሩን ከመቀማቱ በፊት አሳልፎ ሰጥቷል፡፡ ተሜ! ሀሳብን በነጻ መግለጽ ባልተከበረበት ሀሳቡን በነጻነት ለመግለጽ ይጥራል፡፡ ህግ በሌለበት ህጉን አክብሮ ስለ ህግና ፍትህ ያወራል፡፡ ገዥዎቹ አገር ቀማን ሲሉ እሱ ግን ‹‹አገሩማ የእኔ ነው!›› ብሎ ደፍሮ ይጽፋል፡፡ አገሩን አልተቀማምና ተመስገን የድፍረትም ተምሳሌት ነው፡፡

አንድ ጋዜጠኛ ስለ ተመስገን ድፍረት እንዲህ አወራኝ፡፡ ይህ ጋዜጠኛ ተመስገንን ‹‹አቤን ድፍረቱ!›› ይለዋል፡፡ በአንድ ወቅት ነው፡፡ በርከት ያሉ ጋዜጠኞች ተከሰው (ማዕከላዊ ነው መሰለኝ) ይቀርባሉ፡፡ ፖሊስና ደህንነት ጋዜጠኞቹ ላይ ከጸያፍ ስድብ ጀምሮ ‹‹ለምን አርፋችሁ አትቀመጡም፣ ይቅርባችሁ!›› አይነት ምክር ያቀርቡላቸዋል፡፡ ደግሞም ያስፈራሩዋቸዋል፡፡ ጋዜጠኛው ‹‹ሁላችንም ጸጥ አልን፣ አንዳንዶቹ ደግሞ ስህተት እንደሰራን በመግለጽ ጭምር ከመጣብን መከራ ለመዳን ጣሩ፡፡›› ይላል፡፡ የተመስገን ድፍረት ግን ይገርመዋል፡፡ ተመስገን ስድብ ሲወርድባቸው፣ ያልረባ ምክር ሊሰጡ ሲሞክሩ፣ ሲያስፈራሩዋቸው እንደሌሎቹ ዝም አላለም፡፡ ተከራከራቸው፡፡

አገሩን የራሳቸው አድርገው የሚወስዱት ደህንነቶችና ፖሊሶች ህግ ጠቀሰ አልጠቀሰ አገር እንዳለው ሰው ደፍሮ የሚናገር ሰው ያበሳጫቸዋል፣ በምክንያት ቢያምኑ የተሸነፉ ይመስላቸዋል፡፡ በምክንያት መከራከር አይችሉምና ስድብ፣ ዛቻ፣ ከዛም አለፍ ሲል ኃይል ነው ምርጫቸው፡፡ በተሜ ላይም ይህ ሁሉ ተፈጽሞበታል፡፡ ይህ ሁሉ ሲደረግ ሌሎቹ ጋዜጠኞች ‹‹በቃ! ገደሉት!›› እያሉ ለተሜም ይፈሩለታል፡፡ እሱ ግን ክርክር ከማይችሉት ጋር ይከራከራል፣ ምክንያት የማያውቁትን ህግ ለማስረዳት ይጥራል፡፡ በስተመጨረሻ እንደማያምኑለት ሲያውቅ፣ እሱንም በኃይል ለማሳመን ሲጥሩ የተለመደው አቋሙን ገለጸላቸው፡፡ ‹‹ይህኮ አገሬ ነው!›› አገርን ሌሎች ቢይዙትም አምኖ ያልተቀማ ‹‹አገሬ ነው!›› ያለ ደፍሮ ይናገራል፣ ደፍሮ ይጽፋል፣ ደፍሮ ይታሰራል፡፡ እንደ ተመስገን ደሳለኝ፡፡

ተሜ! በርታልን!


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>