Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

ነሀሴ 26ን በደቦ ሸኝተን 2006 ዓ.ምን በተስፋ!

$
0
0

araya
የዘንደሮ ክረምት ከቀደምቶቹ በጥቂቱ ጠንከር ያለና ብዙዎችን በተለይም አዲስ አበቤዎችን እያማረረ ነው፡፡ ሌላው “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” የሚያስብለው ደግሞ የከተማዋ መንገዶች በአብዛኛው ጥገና ላይ መሆናቸውና በዚህም ሳቢያ የበርካቶች መኖርያና የንግድ ሱቆቻቸው መፍረሳቸው ነው፡፡ ይህንን ሁኔታ በምናብ ለማየት ለምትፈልጉ ቅዳሜ ነሀሴ 4 ቀን 2005ዓ.ም በወጣቺው ፋክት መጽሄት ላይ ፕ/ር መስፍን እንዲህ ሲሉ ገልጸዋታል “አዲስ አበባ በመሬት መናወጥ ፈራርሳ በመጠገን ላይ ያለች ከተማ ትመስል የለም እንዴ”:: ብቻ ክረምቱም ወደማለፉ እየተቃረበ አዲሱንም ዘመን ለመቀበል ሽርጉዱ ሳይጀመር አይቀርም፡፡
ምን ክረምቱ ብቻ ፖለቲካውም ክረምቱን ተከትሎ ከ8 ዓመታት በኋላ እሱም ጠንከር ያለ ይመስላል፡፡ ላለፉት ጥቂት ዓመታት በሀገር ውስጥ ሲደረጉ የነበሩት የፖለቲካ ፓርቲ እንቅስቃሴዎች በአመት ውስጥ እንኳ አንድ የሚረባ ለዜና የሚሆን ስራ ሳይሰሩ በውስጥ ጉዳያቸው ተጠምደው፤ የሀገሪቷን የፖለቲካ እንቅስቃሴ ከህብረተሰቡ እኩል ተመልካች መስለው ነበር፡፡ ምንም እንኳ የአሁኑ የፖለቲካ ጡዘት መነቃቃት የፈጠረው ግንቦት 25 በአዲስ አበባ የተደረገው ሰላማዊ ሰልፍ ነው ብንልም፤ ላለፉት 2 ዓመታት ፍጹም ሰላማዊ በሆነ መልኩ ሰላማዊ ትግሉን በጽናት ሲያካሄዱ የቆዩት የሙስሊሞቹን እንቅስቃሴ ለአፍታም ሳንዘነጋ መሆን ይኖርበታል፡፡
ወደዋናው የጽሁፌ አላማ ስመለስ የፊታችን ነሀሴ 26 ቀን 2005ዓ.ም በሰማያዊ ፓርቲ አዘጋጅነት የሚካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ ከመድረሱ በፊት ከኛ ምን ይጠበቃል የሚለውን መነሻ ሀሳብ ለማቅረብ ነው፡፡ ከዚህ ቀን ቀደም ብሎ አንድነት ፓርቲ ከአዲስ አበባ ውጪ የሚያደርጋቸውን በርካት ሰላማዊ ሰልፎችን እና ስብሰባዎችን ሳልዘነጋ ነው፡፡ ይህ የነሀሴ 26 ግን በይዘቱም በጥያቄዎቹም እንዲሁም በቦታውም ለየት ያለ በመሆኑ የተለየ ትኩረት ይሻል፡፡ በመጀመሪያ በፓርቲው የተነሱት ጥያቄዎች በቀጥታ ከድርጅቱ የተገኛኙ ሳይሆኑ አጠቃላይ ድርጅቱ እታገልለታለሁ ያለውን ህብረተሰብ የሚወክሉ በመሆናቸውም ጭምር ነው፡፡
የተነሱት አራት መሰረታዊ ጥያቄዎች ለማስታወስ ያህል፡-
• የመጀመሪያው “ለፍትህና ዲሞክራሲያዊ ስርዓት መስፈን የሚታገሉ ጋዜጠኞችን፣ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችንና አባላትን በአሸባሪነት ስም ማሰርና ማሰቃየትን አጥብቀን የምንቃወም መሆኑንና እስረኞችንም እንዲፈታ”
• በሁለተኛ ደረጃ የተነሳው ደግሞ “የዜጎችን ሰብዓዊና ሕገ መንግስታዊ መብቶችን በመጣስ ለዘመናት ከኖሩበት ቦታ ኢሰብዓዊ በሆነ ድርጊት በታጠቁ ኃይሎች እንዲፈናቀሉ ማድረግ የዘር ማጥፋት ወንጀል በመሆኑ የድርጊቱ ፈፃሚዎች ለፍርድ እንዲቀርቡና የተፈናቀሉት ዜጎችም በአስቸኳይ ወደየመኖሪያቸው ተመልሰው እንዲቋቋሙ በመንግስትም ሆነ በግብረ ሰናይ ድርጅቶች አስፈላጊው ድጋፍ እንዲደረግላቸው”
• ሶስተኛው ጥያቄ “መንግስት በኃይማኖታችን ጣልቃ አይግባ፣ የእምነት ስርዓታችንና የሃይማኖት መሪዎቻችንን እምነታችን በሚፈቅደው ብቻ እናከናውን ያሉ የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮችን በአሸባሪነት ወንጀል በመክሰስ በእስር እንዲማቅቁና ሰብዓዊ መብታቸው እንዲጣስ መደረጉ እንዲቆምና ያነሷቸውም የእምነት ነፃነት ጥያቄዎቻቸው እንዲከበር”
• በአራተኛነት የተነሳው “የኑሮ ዉድነትን፣ የሥራ አጥነትንና በሙስና የተዘፈቁ የመንግስት ሌቦችን የሚቆጣጠርባቸውን መንገዶችና ፖሊሲዎች በማዉጣት ሐገራችንን ከቀውስና ዜጎችንም ከሰቆቃ እንዲያወጣ”
የሚል ነው ይህ ጥያቄ በአብዛኛው የስርአቱ ተቃዋሚዎችን የሚወክል በመሆኑ እንዲሁም ይህንን ጥያቄ ለመደገፍ እና ለዚህ ታላቅ ሰላማዊ ሰልፍ ድጋፍ ለማድረግ የማንንም የፖለቲካ ፍልስፍና ወይም አቋም የማይጻረር እና ሰማያዊ ፓርቲም የራሱን የፖለቲካ ፍልስፍናም ሆነ አቋም ለመጫን ያልሞከረበት በአጠቃላይ የእያንዳንዱ ሀገር ወዳድ ዜጋ መሰረታዊ ጥያቄዎች ናቸው ብዬ ስለማምን ነው፡፡
ምንም እንኳ ፓርቲው ለነዚህ ጥያቄዎች ከመንግስት መልስ እንዲሰጠው ለ3 ወር ጊዜ የሰጠው ቢሆንም፤ ስርዓቱ ግን ይባስ ብሎ አፈናውን በማጠናከር ከማሰርና ከማፈናቀል በዘለለ ንጹሀን ዜጎችን አንድ ተራ ሽፍታ እንኳ የማይፈጽማቸውን በህጻናት እና በእናቶች ላይ ተኩስ መክፈትና መግደል ጀምሯል፡፡
ይህ ምናልባት ለኢህአዴግ መራሹ መንግስት አዲስ ታሪኩ ባይሆንም ከ20 ዓመታት በላይ ድርጅቱን በፍጹም አምባገነናዊነት የመሩት አቶ መለስ ሞትን ተከትሎ ተስፋ ላደረጉ ጥቂቶች የስርዓቱን መበስበስና የማይቀየር መሆኑን አሳይቷቸዋል፡፡ ይህንን ስርዓት ከህብረተሰቡ ጫንቃ ላይ ለማንሳት የሚደረገው የሰላማዊ ትግልም ከዚህ የስርዓቱ ባህሪ አንጻር ፍጹም መራርና ከባድ መስዋዕቶችን ሊያስከፍን እንደሚችል መገመት አያዳግትም፡፡
ከነዚህ የሰላማዊ ትግሎች ውስጥ ግንቦት 25 ቀን 2005 ዓ.ም የተጀመረው የሰማያዊ ፓርቲ እንቅስቃሴ አንዱ ነው፡፡ ፓርቲው ከሰልፉ በኋላ ሲያደርጋቸው የነበሩት እንቅስቃሴዎችም የሚቀጥለው እንቅስቃሴው ከሰልፍ በዘለለ የሰላማዊ ትግል መርሆችን እየተከተለ መሆኑን ያሳያል፡፡ ከዚሁ ጋርም ተያይዞ ነሀሴ 26 የሚደረገው ሰልፍ አዲስ አበባ ላይ መሆኑ የሰልፉ ስኬታማነት አንድነት ፓርቲ በክልሎች ከጀመረው የማንቃት ስራ ጋር ተዳምሮ ለመላዊ የሀገሪቱ ህዝብ ትልቅ መነቃቃትንና ቁርጠኝነት ሊፈጥር ይችላል “አዲስ አበባ ላይ ያካፋው ክልል ላይ ይዘንባል” እንዲሉ ፡፡
እንግዲህ ለዚህ ሰልፍ ወደ 15 ያህል ቀናት ይቀሩታል፡፡ በነዚህ በተቀሩት ቀናቶች የዚች ሀገር የቁልቁለት ጉዞ የሚያሳስባችሁ በተለይ ለኤሌክትሮኒክስ ሚዲያዎች፤ ለድረ ገጽ ባለቤቶች እና ለማህበረ ድረ ገጽ አክቲቪስቶች ይህንን የነሀሴ 26 ሰልፍ ከቀደመው ግንቦት 25 ሰልፍ ላቅ ባለና የሁሉንም ኢትዮጵያዊ ጥያቄ ያካተተ ይሆን ዘንድ ከእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ዜጋ በተለየ መልኩ ያለባችሁን ሀላፊነት ከቡድናዊ ስሜት ወጥታችሁ በሀገራችን በአሁኑ ሰዓት ያለውን የሚዲያ ክፍተት በመሙላት የተጀመረውን ትግል አንድ እርምጃ ወደፊት እንድትገፉ በኢትዮጵያዊ ዜግነቴ እጠይቃለሁ፡፡ እንደምታውቁት በአዲስ አበባ ከሌሎቹ ከተሞች በተለየ የተሻለ የኢንተርኔት ስርጭት ያለበት በመሆኑ በዚህ ከተማ የሚገኘውን ማህበረሰብ ለመቀስቀስና ለማስተማር ማህበራዊ ድረ ገጾች የፈረጠመ አቅም አላቸው፡፡
የዚህን ክረምት ድብታ ከፖለቲካ ድብታችን ጋር ነሀሴ 26 ሸኝተን የሚቀጥለውን 2006 ዓ.ም በተስፋ እና በመነቃቃት እንጀምረው ዘንድ የሁላችንንም ያላሰለሰ ጥረት ይጠይቃል፡፡ በድጋሚ የሚቀጥሉትን 15 ቀናት ሁላችንም በትጋት እንስራ፡፡
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!
አርአያ ጌታቸው
(majiesty02@gmail.com)
ነሀሴ 2005 ዓ.ም


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>