ከደብረጊዮርጊስ
ሰሞኑንን ስለማኅበረ ቅዱሳን በቤተ ክህነት ተደረጎ በነበረና “ፓትርያርክ” አቡነ ማቲያስ በመሩት ስብሰባ ላይ የደብር አለቆችና ተወካዮች የተናገሩትን በተለያዩ የመገናኛ መድረኮች ላይ በስፋት ሰምተናል። እንደኔ እይታ የተባሉትና የተደረገው ነገር ሊገጣጠምልኝ አልቻለም። ለመሆኑ ማኅበር ቅዱሳን መቼ ነው መንግሥትን ተቃውሞ የሚያውቀው? ማኅበረ ቅዱሳን ብዙ የመንግሥት ደጋፊ፣ ብዙ የመንግሥት ቀኝ እጅ የሆኑና የመንግሥት ባለሥልጣናት በአባልነት ያሉበትና የሚቆጣጠሩት፤ በመንግሥት ላይም ምንም ዓይነት ተቃውሞ እንዳያነሳ ወይንም እንዳያስተባብር በቅርብ የሚጠብቁት ማኅበር ነው። ሌላው ቀርቶ ስለ ሃገር ጉዳይ አይደለም በቀጥታ ቤተክርስቲያኗን የሚጎዳ ነገር እንኳን መንግሥት ቢፈጽም ማኅበረ ቅዱሳን አንዲት የተቃውሞ ብጣሽ ወረቀት መግለጫ አውጥቶ አያውቅም። እንዲያውም የመንግሥቱ ተባባሪ፣ በሃገርና በቤተክርስቲያን ላይ በደረሰውና እየደረሰ ባለው ውድመት ውስጥ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተካፋይ ማኅበር ነው። እስኪ በተጨባጭ መረጃዎች እንየው፦
1. መንግሥት የቤተክርስቲያኗን ሉዓላዊነተና ቀኖና በመጣስ በሥልጣን ላይ የነበሩትን 4ኛውን ፓትርያርክ ብጹእ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስን አባሮ የራሱን ፖለቲካ የሚደግፉና መንግሥትም በሚፈጽመው ጥፋቶች ምንም ዓይነት ተቃውሞ ያላሰሙ እና ለመንግሥት ጥብቅና የቆሙ ሰው ፓትርያርክ አድርጎ ሲያስቀምጥ ማኅበረ ቅዱሳን አሜን ብሎ መቀበል ብቻ ሳይሆን የተሾሙትን ፓትርያር የነካ አይኔን ነካ አይነት ያን ሕገ ወጥ ሥራ የተቃወሙትን ሲቃወም፣ ሲኮንን እና የሐሰት ስም ሲለጥፍ የኖረ ማኅበር ነው።
2. ከዚሁ ጋር በተያያዘ በመንግሥት ጣልቃ ገብነት የተፈጠረውን የአባቶች መከፋፈልና በአንድ ወቅት የሁለት ፓትርያርኮች መኖር አስወግዶ በአባቶች መካከል ሰላምና እርቅ ለማምጣት ለበርካታ አመታት ይደረግ የነበረውን ጥረት መንግሥት በመጨረሻ በቀጥታ ጣልቃ በመግባት ሲያፈራርሰው እና ዳግም ጥፋት ሲፈጸም ለዚሁ ጉዳይ የ6ኛ ፓትርያክ ምርጫ ሲደረግ በመንግሥት ተወክሎ የአስመራጭ ኮሚቴ አባል አልነበረምን ማኅበረ ቅዱሳን? የለም እርቅና ሰላም ይቅደም መጀመሪያ የአባቶች አንድነት ይፈጠር ማለት ሲገባው መራጭና አመራራጭ ሆኖ ነው የተገኘው ማኅበረ ቅዱሳ።
3. ታላቁ የዋልድባ ገዳም ተደፍሮ መነኮሳቱ የድረሱልን ጥሪ ሲያቀርቡ አንዲት ብጣሽ የተቃውሞ መግለጫ አላውጣም። እንዲያውም በወቅቱ ገዳሙ አልተነካም እያሉ ማስተባበያ ይሰጡ የነበሩትን የመንግሥት ባለሥልጣናት መግለጫ የመሰለ ማስተባበያ በየሃገሩ ሲያደርግ ነበር። እንደ እድል ሆኖ ገዳሙ ከፍታ ቦታ ላይ ነው ውሃው ወደታች ነው የሚፈሰው እያሉ የተላኩበትን ማስተባበያ ሲሰጡ በአይኔ አይቻለሁ በጆሮዬ ሰምቻለሁ። ይህ የቤተክርስቲያንን ታሪክ የማትፋት ሂደት ሲፈጸም ማኅበሩ ሳያውቀው ቀርቶ ነው? ከ10 እና 20 አመት በኋላ ዋልድባ የሚባል ብዙ ሺህ ነዋሪዎች ያሉት ታላቅ ከተማ በዋልድባ ውስጥ መፈጠሩ እንደማይቀር ማኅበሩ ሳይታየው ቀርቶ ይሆን ወይስ …?
4. ማኅበሩ የሚሰራቸው በጎ የሆኑና የሚመስሉ ነገሮች አሉ። ነገር ግን እንኳን የቅዱሳንን ታሪክ ማዘከር ይቅርና ፈጽሞ በስማቸው ሊጠራ የማይገባው መሆኑንን እስኪ እንመልከት። በቤተክርስቲያናችን ትምህርት እንደምናውቀው ቅዱሳን ካላቸው ላይ ከፍለው ብቻ ሳይሆን ያላቸውን ሸጠው ለውጠው ለድሆች አካፍለው በክርስቶስ ኃይል ለክርስቶስ ብቻ የኖሩ እና የኒኖሩ ናቸው። የእኛ ማኅበረ ቅዱሳን ግን ባለዘመናዊ የቢሮ ሕንጻ ገንብቶ እዛ ውስጥ በተሽከርካሪ ወንበር ተቀምጠው በብዙ ሺህ የሚቆጠር ገንዘብ ለደመወዝ፣ ለተለያዩ የአገልግሎት ክፍያዎሽ እያወጡ ከሕንጻው ሥር ደግሞ የታረዙና መውደቂያ ያጡ ጧሪ ቀባሪ የሌላቸው እናት አባት የሌላቸው ፈሰው በእነርሱ ላይ እየተረማመዱ ሊጸድቁ የሚፈልጉ ሰዎች ማኅበር ነው።
5. ለረዥም አመታት ማኅበሩ የቆሎ ትምህርት ቤቶችን በዘመናዊ መልኩ ልናሰራ ነው በዚህ አካባቢ በዚህ ቦታ እንዲህ ያለ የቆሎ ትምኅርት ቤት ተዘጋ ተማሪዎቹ ተበተኑ እያለ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ አሰባስቧል። እስኪ እዚህ ቦታ ይህ የቆሎ ትምህርት ቤት በዚህን ያህል ወጪ በዘመናዊ መልኩ አሰራን የሚሉትን ያሳዩን ? ባካፋ ዝቀው በማንኪያ እዚህና እዛ ጠብ እያደረጉ ያቺን ደግሞ አጋኖና ተአምር የተሰራ አስመስሎ በማቅረብ ተአማኒነት ለማግኝት ከሚደረግ ማታለያ በስተቀር ማኅበሩ በርግጥም ለቤተክርስቲያን የቆመ ሳይሆን ተልዕእኮው በደምብ ሊጤን የሚገባው ነው። እንደ ሰሞኑ ማኅበሩን ሲከሱ እንደተሰሙት ግን ማኅበሩ የመንግሥት ተቃዋሚ ሳይሆን ነገሩ የተገላቢጦሽ ነው ባይ ነኝ። ወጣቱ ትውልድ በተለይም ለሃገሩ ተቆርቋሪና ለውጥ ሊያመጣ የሚችለውን የሕብረተሰብ ክፍል ሞራልና የሃገር ፍቅርስሜት እየሰለበ እንደ አውሮፓ ቅኝ ገዥዎች በጸሎት ነው እያለ ኅዝቡን እያደነዘዘ ያለ ማኅበር ማኅበረ ቅዱሳን ነው። ጉልበት ያለው በጉልበቱ አባቶች በጸሎት ሃብታሙም በገንዘቡ ለሃገሩ ሏአላዊነትና አንድነት መቆም ሲገባው ዛሬ ማኅበረ ቅዱሳን ይህን ለውጥ አምጪ ወጣት በመሰለቡ የሃገርና የቤተክርስቲያን ጠላቶች መውደቂያ ጊዜ ለመዘግየቱ አንዱና ዋነኛው ምክንያት ነው ባይ ነኝ።
6. ከአንድ አመት አካባቢ የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ተማሪዎች በመንግሥት የተመደቡትን ”መምህራን” መሳይ ግለሰቦች በመቃወም ታላቅ መስዋዕትነት ሲከፍሉ እና በረሃብ ሲቀጡ፣ ማደሪያ ሲያጡ እንደ አንድ ለቤተክርስቲያኗ ቆሜያለሁ እንደሚል ማኅበር በተማሪዎቹ ላይ የደረሰውን ጥቃት በአንዲት ቆራጣ ወረቀት መግለጫ አልተቃወመም። እና ይህ ማኅበር ዛሬ የመንግሥት ተቃዋሚ ነው ቢሉኝ እኔ አላምንም።
7. በማኅበሩ ውስጥ እጅግ በጣም ብዙው አባላት በእውነትና በቅንነት ለእምነታቸውና ለቤተክርስቲያን የቆሙ ቢሆንም በማኅበሩ መመሪያ መሠረት አባላቱ አውቀውም ሆነ ሳያውቁ የመንግሥት ደጋፊ መሆን ምንም ችግር የሌለው መንግሥት በአገሪቷ ላይ የሚፈጽመውን በደል ይቅርና በቤተክርስቲያኗ ላይ በቀጥታ የሚያደርሰውን ጥቃት እንኳን መቃወም “ፖለቲካ” ውስጥ መግባት እንደሆነ አምነው እንዲቀበሉ ብሬን ወሽ የተደረጉ ናቸው። እናም ዛሬ በማኅበሩ ውስጥ እጅግ በጣም ብዙ የመንግሥት ደጋፊዎች እና ባለስልጣናት አሉ ተቃዋሚ ሆኖ ግን ከማኅበረ ቅዱሳን ጋር መቀጠል አይቻልም።
8. መቼም አገር ውስጥ መንግሥት ተብዬ አካል ስለሚገድል፣ስለሚያስርና ስለሚያዋክብ ነው እንበል በውጪ አገራት የመንግሥት ደጋፊዎችና የለየላቸው ካድሬዎች ጋር በመሆን በተለይም የቤተክርስቲያንን ሰላምና አንድነት እየበጠበጡና እያስበጠበጡ ያሉት እኮ የማኅበረ ቅዱሳን አባላት ናቸው። ትክክለኛውና ዘላቂው ሰላምና አንድነት የሚመጣበትን የሰላምና የእርቅ ሂደት በማፍረስ ሂደት ውስጥ ቀጥተኛ ተሳትፎ ያለው ማኅበር በውጪም አገር አንድነት የሚመጣው የመንግሥትን የቤተክህነት ሹማምንት ስንቀበል ነው በማለት ስንቱን ሰላማዊ ቤተከርስቲያን በጥብጠዋል አስበጥብጠዋ ? ለእነርሱ ሲሆን የፈለጉትን ጳጳስ አንቀበለውም ስሙንም አንጠራም ማለት ይቻላል ሌላው ህዝብ ግን ስለቤተክርስቲያን አንድነት፣ ስለሰላምና እርቅ ሲል አባቶቻችን ይታረቁ ሲል የቤተክርስቲያን ሥርአት ጠፋ ኃይማኖት ተቀየረ በማለት ሰላም የሚነሱት እኮ የማኅበረ ቅዱሳን ሰዎች ናቸው። እስኪ የማኅበረ ቅዱሳን አባላት በውጪው ዓለም የት የት ቤተክርስቲያን ነው ያላችሁት?
9. በኢትዮጵያ ታሪክ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ጉልህ ድርሻ ያላት ነች። ነገር ግን ይህ ታላቅ ባለውለታነቷ እየተንቋሸሸ መብቷና ስሟ ሲጠፋ፤ መለኪያው ኦርቶዶክስ የነበረውን ሰብረነዋል አከርካሪውን መተነዋል ሲባል ማኅበረ ቅዱሳን ምን ይጠብቅ ነበር ???
10. እናም የሰሞኑ ሁካታ ማኅበረ ቅዱሳን የመንግሥት ተቃዋሚ ነው ለማለት የተነገረ አይመስለኝም። አንድም ማኅበሩን ተቃዋሚ አስመስሎ ተቃዋሚ ጎራ ውስጥ ለመክተት የሚደረግ የእነ አቶ ክህደቱ አይነት አካሔድ ነው አልያም አንዳንድ የቤተክርስቲያን መጠቃትን ለም የሚሉ የማኅበሩ አባላት እየተፈጠሩ ስለሆነ እንርሱን ለማስደንገጥና ለማጽዳት የሚደረግ ስልት ነው። ከዚህ በዘለለ ግን እውነት እንኳን ደግሞ ቢሆን ጨዋታው አብዮት ልጇን ትበላለች ነው።