Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

“አድርገህልኛልና ለዘላለም አመሰግንሃለሁ (ሥርጉተ ሥላሴ )

$
0
0

(መዝሙረ ዳዊት ምዕራፍ 51 ቁጥር 9)

ከሥርጉተ ሥላሴ 24.10.2014 (ሲዊዘርላንድ ዙሪክ)

“እርግብ በር” 7ኛው አዲሱ መጸሐፌ ነው። የትውልዱ ነገር ከልጅነቴ ጀምሮ ይጨንቀኛል። በተለይ ወላጆቻቸው ተለያይተው ስለሚያድጉ ልጆች፤ ከጋብቻ ውጪ ስለሚወለዱ ልጆች በእጅጉ አስባለሁ።

trtአንድ ሰው ልጅ መውለድ ያለበት በተለይ ትዳር ላይ ከሆነ አብሮ ለማሰደግ ሲወስንና ሲቆርጥ ብቻ መሆን አለበት። ይህን ሳያጓድሉ መከራውንና ፈተናውን ታግሰው ልጆቻቸውን በጋራ የሚያሳድጉ የቤተሰብ አባ ወራና እማ ወራዎች የትውልዱ ልዩ ጌጦች ናቸው። ከዚህ በላይም ትውልዳዊ ድርሻ የለምና ለዚህ የታደሉትን ከልብ  በአክብሮት ላመስግን አውዳለሁ። የ አዲሱ ትውልድ ግርማ ሞገሶች ናቸውና።

ምክንያቱም ወላጆቻቸው የተለያዩባቸው ልጆች እስከ ህይወታቸው ፍጻሜ ድረስ መንፈሳቸው በተከደነ ቁስለት ይፈናቀላል። አባት የእናትን፤ እናትም የአባትን ድርሻ፣ ጉርሻ፣ ተፈጥሮዊ ክህሎት፣ ሊያተካኩ አይችሉም። ለልጆች ወላጆቻቸው አብረው ሲሆኑ የመኖር ንጹህ አዬራቸው ነው። ተስፋቸውም ለምለም ይሆናል። ሙሉ  እንደሆኑ ይሰማቸዋል።

ከዚህ ማዕቀፍ ወላጆች ልጆችን ሲያወጧቸው ግን የቀንበጦች ጠቅላላ ሰብዕናቸው ጥላሽት ይለብሳል። በፈለገው ዓይነት ቀመር ቢሆን ደስታቸውን ሙሉዑ ሊያደርገው አንዳችም ነገር አይኖርም። መኖርን እንደ ፈሩት፤ መኖርን እንደ ሸሹት መኖርን ሳይተረጎሙት ሳይኖሩበትም ባልተመለስ ጥያቄ መንፈሳቸው እንደናወዘ መዋዕለ ዕድሜያቸው በጠቆረ ግን በተመሰጠረ ዬመከራ ዘመን ይከወናል። በህይወታቸው እንደ ጦር የሚፈሩት ነገርም ጋብቻን ይሆናል። በጋብቻ ጉዳይ ደፋሮች አይሆኑም – በፍጹም። በልጅነት ጊዜያቸውም የፈለገ ብቃት፤ ችሎታ፤ ክህሎት፤ ጸጋና ሥጦታ ቢኖር ወይ ተቀብሮ ወይ አንክሶ ወይ ተጋድሞ ይቀራል። ይህን እኔ በስማበለው ሳይሆን በራሴ የደረሰ ስለሆነ ወገኖቼ ዕውነቱን ነው የምነግራችሁ። ስለሆነም “እርግብ በር” መጸሐፌን የፃፍኩበት አብይ ጉዳይ በዚህ ምክንያት ነው። የልጆች የነገ ንድፍ ተጨናግፎ – አሮ – ተቀጭቶ እንዳይቀር።

“እርግብ በር” ረቂቁ በ2006 ተሰርቶ ጹሑፉ ደግሞ በ2013ና 2014 እስኪበቃኝ ለሁለት ዓመት አሽቶኝ ተጠናቀቀ። ወላጆች ለልጆቻቸው የሚያወርሷቸው ትልቁ ነገር የቤተሰብ ምስረታ – ማገሩ ፍቅር መሆን ስለአለበት አትኩሮቱ ይኼው ነው። ይህን ደግሞ ወላጆች መሆን ሲችሉበት ነው። ልጆች ከሚሰሙት ይልቅ በሚያዩት ነገር ይማራሉ። ልጆች የዕውነተኛው ዓለም ጭብጦች ናቸውና።

“ፍቅር” ጥሩ አስተዳዳሪን ከገኘ ፈተናን የማሸነፍ አቅሙ ልክ የለውም። የሰውን ልጆችን የፈጠረው ፍቅር እንደ ተፈጥሮው ሊያዝና  በአግባበቡ ጸጋው ሳይጓደል ድርጊትን ማዬት አብዝቶ ይሻል። ፍቅር ሊተርኩት ሳይሆን ሊኖሩበት የተፈጠረ፤ በራሱ በፈጣሪው በመዳህኒትዓለም ደም የጸደቀ የመኖር ብቸኛው ሃይማኖት ነው። ስለሆነም የሰው ልጅ ሥጦታውን ያጌጥበት ዘንድ ሳይታክት ተግቶ በዕለት ተግባሩ ውስጥ ሊሆንበት ይገባል። “የእርግብ በር” መጸሐፍ መሰረታዊ ዓላማ ይሄው ነው።

ትልቁን የሰማይ የደስታ ጸጋ፤ የሰናይ ሃብት፤ ጥቃቅን ተውሳኮች እንዳያሳምሙት ወይንም እንዳያምሱት ጥንቃቄ እንዴት ሊደረግ ይገባል ነው የመጸሐፉ ተልዕኮ። ትዳር ሲጸና ልጆች ካለስጋት ነገን ያልማሉ። ስለሆነም ነገ ለትውልዱ ቀጥ ያለ ፍቅርን እንዲጠብቅ ወሳኙ ድርሻ ያለው ከተጋቢዎች ዘንድ ነው። ውርርሱም በአግባቡ ይሆናል።

የመጸሐፌ እርእስ ከላይም እንደጠቀስኩት “እርግብ በር” ነው። ደጉ ንጉሥ ዓፄ ፋሲል ካሰሩት ቤተ መንግስት ከ12ቱ በሮች የአንዱ በር መጠሪያ ነው። ስለሆነም መግቢያው ላይ ታሪክ ቀመስ ነገሮችን መጸሐፉ አነሳስቷል። ይህን በማድረጌ አዘውትራ እናቴ ክብዬ ታሪክ ቀመስ መጸሐፍቶች ላይ እንዳተኩር ስታሳስበኝ ስለነበር እንሆ ፍላጎቷን ስለፈጸምኩኝ ዝቀሽ ምርቃን አገኛለሁ ብዬም አስባለሁ። በሌላ በኩል በወላጆቼ መለያዬት ምክንያት ያጣኋቸው ለጋ ዕድሎቼ፤ ተጨናግፎ የቀረው የመማር በኽረ ህልሜ በነገ ትውልዱ ላይ ላይ እንዳይደገም ትንሽ ነገር በማድረጌም ደስተኛ ነኝ። ስለዚህ ሐሤቴ እጥፍ ድርብ ነው።

በተረፈ በህይወት ወስጥ እኩል በሆነ ግንዛቤ ህይወትን መተርጎም ስለማይቻል፤ እኔም ያለኝን እርሰዎም ያለወትን አክለን ነገን ለማንጋት በወልዮሽ የምንችላትን ከከወን፤ ትውልዱ ከሚነቀስበት ጉዳይም እንድናለን – ለጋራችን። መቼም ይህ ትውልድ መከረኛ ነው። ሁልጊዜም እንደ ተረገመ ነው …..

በተረፈ መጸሐፉ የዘመን ግጭት እንዳይፈጠር እንደ ተፈጥሯችን አሳምረን በፍቅር ተጠቃሚ እንሆን ዘንድ በስድና በግጥም መልክ የተቀነባበረ ጫሪ ጉዳዮችን ነካክቷል። አንዳንድ ሰዎች ዕድሎኞች ናቸው  ከሰጡት በላይ ያገኛሉ። የእኔ ቢጤዎች ደግሞ የሚመጥን ቀርቶ የነበረውን ያጣሉ። በፍቅር ህይወት ውስጥ መሆን የሚገባውን በትንሽ ምሳሌ ብገልጸው መልካም ይሆናል።

ምርቃተ – ምሳሌ።

ሁለት ተመሳሳይ ብርጭቆ በተመሳሳይ መጠን ውሃ ጨምሩ። ውሃውን ወደ አንዱ ብርጭቆ ጭልጥ አድርጋችሁ ሙሉት – ጠብ ሳይል። ፍቅር ፈዋሽ ጠበል ነው። የሥጋም የነፍስም። አንዱ ባዶ ሌላው ሙሉ ይሆናል። አንደኛው ስለሞላም፤ ሁለተኛው ባዶ ስለሆነ ሁለቱም ሥራ የለቸውም። ማለት ሥራ ፈት ሆነዋል ማለት ነው። ስለዚህ ከአንድ ቦታ ላይ ግንኙነቱ ተበጥሷል ማለት ነው። ባዶው – ባዶውን ነው በቃ የነጠፈ ጉድ። …. አልተመለሰለትም። የሞላለት ግን ጨልጧል። ነገር ግን ስስታምና ቆጥቋጣ ስለሆነ ተመጣጣኙን አልመለሰም። … ስለዚህ ይህ ንጡሕ ፍቅር አይደለም።

ለእኔ ሲገባኝ ፍቅር ማለት በተመሳሳይ ብርጭቆ እኩል መጠን ያለው ውሃ ሳይቋረጥ አንዱ ሌላው ሲቀዳለት ሌላው ተቀብሎ መልሶ ሲቀዳለት ሳይቋረጥ ሌትና ቀን በመስጠትና በመቀበል ሁለቱም ባተሌ ሲሆኑ ነው። አልፎ አልፎ የጥራት ሳይሆን የመጠን ከፍ ወይንም ዝቅ ሊል ይችላል። በውስጣዊና ውጪያዊ ተጽዕኖች ወይንም በመሬትና በአዬር ለውጥ፤ ወይንም በጨረቃ ሙሉነትና ግማሽነት ወይንም በዝንቁ ጎድጓዳ ዓለም ትርምስ። የሆነ ሆኖ ዝቅ ያለው መልሶ በዛው መጠን ይመጣለታል – ይቀበላል – ይሰጣል … ሳይተጓጎል አይቋረጥም። ፍቅር አይደክመውምና። ልክ በዚህ መልክ የሚኖር ፍቅር ነው የሰው ልጅ የሚያሰፈልገው ….  ይሄነን ሁለት ብርጭቆ አዘጋጅታችሁ ሁለቱንም እኩል መጠን ያለው ውሃ ጨምራችሁ ሞክሩት … አቃዱት እራሱ ሂደቱ ጥበብ አለበት ውህደቱ አይታይም ስሜት ብቻ ነው ጠረኑን ማወቅም መተርጎም የሚችለው።  …. የተሰጠው ነውና ….

“እርግብ በር” መጸሐፌ በ333 ገጽ እጅግ በርካታ ርእሰ ጉዳዮችን አነሳስቷል። መፋቻም በመጠኑ አለው። ከድካሙ ጋር ጥረቱና ፍሬው ሳዬው ግን እሱ ራሱ ፍቅር ነውና ፍቅርን ለግሶኛል። አታሚው ድርጅት እራሱ በጣም በጥንቃቄና በአክብሮት ነበር የሠራልኝ። እያንዳንዱን ጥቃቅን ነገር እያማከረኝ። ምክንያቱም ፋሲል ግንብ ቅርስነቱ – ውርስነቱ ሆነ ትውፊትነቱ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለዓለምም በመሆኑ። ለሽፋኑ ሆነ ለህትምቱ ወረቀት ምርጫ ሰፊ ጊዜ ነበር የወሰድነው። ክብረቶቼ – ዋና መማር ትፈልጋላችሁን.? ከፈለጋችሁ ፍቅርን ይዛችሁ ወንዝ ውረዱ። ፍቅር ጥሩ የዋና መምህር ነውና ….

የኔዎቹ ጌጦቼ – “እርግብ በር” ከመጨረሻ ሽፋኑ  …. እርገቱ በእሱ ይሁን ….

“ፈጽሞ

ማንነት ያለው ተስፋ ስላለኝ የመንፈስን እስር የመፍታት አቅሙ ፈተና ላይ አይወድቅም። ይልቁንም ማንነት ያለው መፍትሄ የመፍጠር ዕሴቱ ሆነ አቅሙ ጉልበታማ ነው። ጉልበታሙ ማንነቴ ወደ ፊት የሚፈጥረው ግፊትና የሚጨበጥ ራዕዩ ደግሞ ትጥቅና ስንቄም ነው። በተሟላ ስንቅና ትጥቅ  የተሰናዳ ማንነት ደግሞ ጉልህና – አሸናፊ ነው። ከዚህ በኋላ ወይንም ከእንግዲህ ወዲህ በቃኝ ብሎ ለስንፍናና ለፍርኃት እጁን አይሰጥምና እና …. ፈጽሞ” …. ከረዳቴ ከፈጣሪ አምላኬ ጋርምበጣም በእርግጠኝነት የመንፈስ ሃብታት ፍሰት በተመሳሳይ ሙቀት ተጠናክሮ ይቀጥላል።

በመጨረሻ ትናንት 23.10.2014 ምን አስቦ ምን እንደከወነ በጸጋዬ ራዲዮ ፕሮግራም ማወቅን ትሻላችሁን? እንግዲያውስ www.lora.ch. Aktuelle Sendung Radio Tsegaye ያዳምጡ ዘንድ በአክብሮት አሳስባለሁ። መሸቢያ ሰንበት።

 

“አድርገህልኛልና ለዘላለም አመስግንሃለሁ።”

 

እግዚአብሄር ይስጥልኝ።

 


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles