ይህንን አጭር ልቦለድ ከማንበባችሁ በፊት በቪዲዮ የተቀናበረውን የተመስገን ደሳለኝን ወንድም የታሪኩ ደሳለኝን ጽሑፍ እንታዳምጡ ልጋብዛችሁ። በቪዲዮው ላይ የቀረበው የታሪኩ ጽሑፍ እውነተኛ ታሪክ ሲሆን የእኔይቱ መጣጥፍ ግን ልቦለድ መሆኗን እንድትረዱ በማስጠንቀቅ ወደ ንባቡ ልምራችሁ።
(ቪዲዮው ከዚህ ይገኛል፦ https://www.youtube.com/watch?v=MChq7mR_wCk)
+++
ከዕለታት አንድ ቀን …
እትዬ ሸዋዬ ቤት ውስጥ። ስኒው ተዘርግቶ ቡናው በአንድ ጎን ይቆላል። የተንተረከከው ፍህም ቅላቱ የአፋርን እሳተ ገሞራ የቀለጠ ዐለት ያስታውሳል። በአንድ ጥግ ዳንቴል ለብሳ የተንጠለጠለች ብርቄ ሬዲዮ የምሳ ሰዓት ዜና ታሰማለች። ሕጻናት ውጪ ደጃፉ ላይ ሲጫወቱ የሚያስነሱት አቧራ ገርበብ ብሎ በተከፈተው በር ዘልቆ ይገባል። እንደ ሌላው ጊዜ “እንደው እነዚህ ውጫጮች፤” ብሎ የሚያባርራቸው የለም። ሴቶቹ በሙሉ ጆሯቸውን ከራዲዮኑ ደቅነው በዓይኖቻቸው የልጆቻቸውን ሩጫ ይመለከታሉ። ባሎች ወደ ኦጋዴን ግንባር ከዘመቱ ቆይተዋል። በሰፈሩ ውስጥ ዕድሜያቸው ከገፋ አረጋውያን እና በተለያየ የመንግሥት መሥሪያ ቤት ከሚሠሩ ሰዎች በስተቀር ደልደል ያለ ወንድ በሰፈሩ ብዙም አይታይም። ወንዱ ሁሉ የናት አገር ጥሪ ብሎ ሚሊሻ ሆኗል።
በርግጥ ሬዲዮኑ ይሸልላል፤ ይፎክራል። ቤት ያሞቃል። ሴቶቹ ግን በዚያ ሁሉ የጀግና ፉከራና ቀረርቶ፣ “ውረድ በለው ግፋ በለው፤ ግደል ተጋደል በአባትህ ወኔ …” መካከል የባሎቻቸው ሕይወት፣ በእነርሱ ላይ እንዳይደርስ የሚፈሩት ነገር ሥጋት …. ያለ አባት ልጅ የማሳደግ ጭንቀት … እየተገለባበጠ ይመጣባቸዋል። ልጆቹ አቧራቸውን ያቦናሉ።
+++
ከወር … ከሁለት ወር በኋላ ….
የእትዬ ሸዋዬ ልጆች አሁንም ከደጃፉ እየተሯሯጡ ይጫወታሉ። ግቢው ውስጥ የተተከለው ድንኳን ድብብቆሽ ለመጫወቻ ተመችቷቸዋል። ሰርግ ይሁን መልስ ይሁን ለቅሶ ይሁን ሰንበቴ ለእነርሱ ምኑም ልዩነት አልሰጣቸውም። ሚሊሻ አባታቸው እንደማይመለሱ ገና በቅጡ አልተገለጠላቸውም። ያለ አባት …. በእናት እጅ ማደግ … ያለ ርዳታ … ገና አልገባቸውም።
ቆይቶ … ነፍስ ሲዘሩ፣ ችግር በዚያ በቀዝቃዛ አለንጋው ቤተሰቡን ሲገርፍ … ያኔ ነው የሚገባቸው። ለአሁኑ ልጆች ናቸውና ለለቅሶ የተተከለው ድንኳን እነርሱን ለማጫወት የመጣ ሳይመስላቸው አልቀረም። በልጅነታቸው። ከሌላው ሰው ተለይቶ የእነርሱ ብቻ ቤት ድንኳን ስለተጣለበት ድንኳን የሌላቸውን ጓደኞቻቸውን ለማስቀናት ሞክረዋል።
“እኛ ቤት ድንኳን አ…..ለ፤ ደሞ፤ በ….ቃ” እያሉ ጉራቸውን ነዝተውባቸዋል። ድንኳን የሌላቸውን የመምህር አንበርበር፣ … ደግሞ የመምሬ ከበደ … ወዲያ ማዶ ያሉት ባለሱቁ … የጋሽ አብደላ … ልጆች በሙሉ መጥተው ድንኳኑ ውስጥ ሲጫወቱ ውለዋል። በድንኳኑ ስፋት … እየተደነቁ።
ከዓመት ሁለት ዓመት በኋላ …
ልጆቹ በሙሉ ተሰብስበው ሲጫወቱ ይውሉና … ከዚያ ያ ሁሉ ፍቅራቸው ፈርሶ በዚያው በፍቅሩ መጠን አምርረው ተጣልተው ሰፈር ይረብሻሉ። ከሁሉም ግን የእትዬ ሸዋዬ ልጆች ላይ ነገር ይጠናባቸዋል። ሴት ያሳደገው ልጅ ድሮስ?” ይባላሉ። ሰው ፊት ሰምተው እንዳልሰሙ የሚሆኑት ወ/ሮ ሸዋዬ ዘወር ብለው ድምጽ የሌለው ዕንባ፣ የብቻ ዕንባ ያፈሳሉ። ልጆቻቸው ዕንባቸውን እንዲያዩ አይፈቅዱም።
“ሴት ያሳደጋቸው ልጆች” ሲባሉ ብዙ ጊዜ ሰምተዋል። አማርኛው ግን ገና አልተረዳቸውም። ስድብ መሆኑ እስኪገባቸው ሌሎች ዓመታት መጠበቅ አለባቸው። ገና ልጆች ናቸው። ሚሊሻ አባታቸው ቢኖሩ ይህ ስድብ እንደማይኖርባቸው ለመረዳት ጥቂት ዓመታት ይቀሯቸዋል። በልጅነት ትዝታ የሕልም ያህል ውል ውል የሚሉባቸው የአባታቸው ትዝታ ነፍስ እስኪዘራባቸው ጥቂት ዓመታት መጠበቅ አለባቸው። ጊዜው ሲደርስ “ሴት ያሳደገው ልጅ” ሲባሉ በነብር ቁጣ፣ በአንበሳ ግርማ ከሰው ጋር ለመተናነቅ ለመነሣት ጊዜው አልደረሰም ነበር። ልጆች ናቸዋ።
ከተጨማሪ ዓመታት በኋላ …
ልጆቹ አድገዋል። እርስበርሳቸው መጽናኛቸው የጎረቤት መሳደቢያዋ ቃል ናት፦ “ባክህ እናታችንን እንዳናሰድባት። ሴት ያሳደጋቸው እንዳናስብላት” ይሉ ጀመር። በነበር ቁጣ በአንበሳ ግርማ፤ ነገር ግን ጭምቶች ሆነዋል። እናት የቤቱ አባ ወራም እማ ወራም ናቸው። ልጆች ሰው እንዲሆኑ የታጠቀ ወገባቸውን አልፈቱም። የባላቸውን መርዶ የሰሙ ቀን ቅስማቸው ተሰብሮ ልጆቻቸውን ሳያሳድጉ አልቀሩም። ያኔ የታጠቁትን መቀነት ለማላላት ልጆቻቸው “ቦታ ቦታ እንዲይዙ” ለራሳቸው ምለው ነበር።
ዛሬ ከዓመታት በኋላ ሴት ያሳደጋቸው እነዚያ ልጆች ቦታ ቦታ ሲይዙ የብልግና መነሻ አገሩ አድርጎ ይቆጥራቸው የነበረ ጎረቤት አሁን በአለክብሮት ያያቸዋል። “አይ ወ/ሮ ሸዋ፤ ሴት ሳትሆን እኮ ወንድ ናት። አታዩም ልጆቿን? አንዱም ዩኒቨርሲቲ ያስተምራል፤ አንዱም ጎበዝ ጋዜጠኛ ሆኗል” ይሏቸዋል።
ከሌሎች ዓመታት በኋላ ….
ፍርድ ቤቱ የጋዜጠኛውን ክስ መመልከት ከጀመረ ቆይቷል። በተከሳሽ ሳጥን ውስጥ ቆሞ ባሻገር ወንድሙን እና እናቱን በአንድ ወገን፣ ባለቤቱንና ትንሽ ልጁን በሌላ ወገን ይመለከታል። ሕጻን ልጁ እናቱ ጭን ላይ ተቀምጦ ከኋላው ወንበር ካለ ሰው ጋር ድብብቆሽ ቢጤ ይጫወታል። “አየሁህ …. አየሁህ …..” ይላል።
ወዲያው ድንኳን እቤታቸው ተተክሎ የሰፈር ሕጻናትን ሰብስበው ሲጫወቱ የተደሰቱት ደስታ ትዝ አለው። “ጋዜጠኛ ነኝ፣ ሚሊሻ አይደለሁም። እንደ አባቴ ጦር ሜዳ አልሄድኩም። በርግጥ ፍርድ ቤቱ አሁን ድንኳኔን እየጣለው ነው?” ይላል።
የልጃቸውን ዓይን የተከተሉት ወ/ሮ ሸዋዬ እናቱ እቅፍ ውስጥ የሚጫወተውን ልጅ ሲያዩ የልጃቸው ሐሳብ ምን እንደሆነ እንደተከሰተላቸው ሁሉ ትኩስ ዕንባ ግድቡን ጥሶ ሊፈስ ይታገላቸው ያዘ። ግን ልጆቻቸው ፊት አለማልቀስን ለረዥም ዘመናት ተለማምደውታል። የከባድ ኑሮን ቀንበር አሸንፈው ልጆቻቸውን ዳር አድርሰዋል። ራሳቸውን ጎድተው ልጆቻቸውን ሰው አርገዋል። አሁን ግን የልጃቸውን ልጅ ሲያዩ ጉልበት ከዳቸው። ጋዜጠኛው ልጃቸው የአባት ልቡ ለሕጻን ልጁ ሲንሰፈሰፍ የርሳቸውን ጥንካሬ ናደባቸው። ከፈቃዳቸው ውጪ በየትም ቦታ በየትም ጊዜ እንዳይፈስ ያሰለጠኑት ዕንባቸው ግድቡን ደረመሰ። ወደ ወሕኒ የሚሔደውን ልጃቸውን በዕንባቸው መካከል ያዩታል። በተሰባበረ መስተዋት ውስጥ እንደሚታይ መልክ በተሰባበሩ ዕንባዎችና የዕንባ ዘለላዎች መካከል … በነጠላ ጫማ … “ጺሙ እንዴት አድጓል?” ከወገቡ ጎበጥ ያለ መሰላቸው። መምህሩ ልጃቸው ትከሻቸውን አቅፎ እየመራቸው በተሰባበሩ ዕንባዎች እግራቸውን በዘፈቀደ እየተረገጡ ከፍርድ ቤቱ ወጡ። ሌላ አባት የማያሳድገው ልጅ … የእናቱ ብቻ ዕዳ የሆነ … በኅሊናቸው መጣባቸው። ልጆቻቸውን ሲያሳድጉ ጭንቀታቸውን ወደሚያራግፉበት የእስጢፋኖስ ቤተ ክርስቲያን ደጃፍ ሲደርሱ እንደድሮው ብቻቸውን ብር ብለው አልነበረም። መምህሩ ልጃቸው አሁን እንደደገፋቸው ነው። የተለመደች ታዛቸው ሥር ሆነው “ሰማዕቱ፣ የልጆቼን ነገር አደራ አላልኩህም ነበር? ውለታችንን ረሳኸው?” ሲሉ ልጃቸው እንደሚሰማቸው ትዝም አላላቸው። በዕንባ እና በጸሎት ያደገ ልጅ። እርሱም መሐረሙን አፍንጫው ላይ ከድኖ ድብቅ የወንድ ዕንባውን ማፍሰሱን እሳቸው አላዩም። አንዳንዴ ወንድ ብቻውን አያለቅስም።
(መታሰቢያ፦ ለተመስገን ደሳለኝ፣ የእናታቸውን ታሪክ በግሩም ብዕር ለነገረን ለተመስገን ወንድም ለታሪኩ ደሳለኝ እና ለአረጋዊ እናታቸው።)