Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

ወጣትነትና አስትዋጾው

$
0
0

የአንድ አገር ቀጣይነት ያለው እድገት የሚለካው በአላት ሃብትና ንብረት ብቻ ሳይሆን ያንን ተረክቦ በአደራ ለትውልድ ማስተላለፍ የሚችል ትውልዳዊ ትስስር ሲኖር ነው። ይህንንም እንደ ድልድይ ሆኖ  ከአንዱ ትውልድ ወደቀጣዩ ትውልድ የሚያስተላልፈው ወጣቱ የህብረተሰብ ክፍል ነው። በማንኛውም አገር፣ ጊዜና ዘመን እያንዳንዱ ተተኪ ትውልድ የአገሩ ወራሽ፣ ተተኪና ተረካቢ፣ ጠባቂና ለሚቀጥለውም ትውልድ የማውረስ፣ የማስተላልፍና የማስረከብ ኃላፊነትና ግደታ  አለበት። አገርን ከእነ ሙሉ ክብራ ለሚቀጥለው ትውልድ ማስተላለፍ ከወጣቱ የዜግነት ግደታ ነው። አገር በአንድና በሁለት ትውልድ ብቻ የሚቆምና የሚያልፍ ሳይሆን የማያቋርጥ ቀጣይነት ያለው ትውልድ ሁሉ የሚቀባበለው፣የሚጠብቀው ያለፈውንና የሚመጣውን ትውልድ ሁሉ የያዘና ያቀፈ የአገርና የሕዝብ የታሪክ ሂደት ነው።ወጣት ለአንድ አገር በሦስቱም ዘርፍ ማለትም በማህበራዊ፣ በሥነ ምጣኔ ሃብታዊና በፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያደርጋል። ለዚህም ነው ወጣት ለአንድ አገር የጀርባ አጥንት ነው የሚባለው።

ethio-prisons023ወጣትነት፦ ወጣትነት ማለት በሰው ልጅ ሥነ ሕይወታዊ ምዕራፍ አንድን የእድሜ ክልል የሚወክልና የተለያዩ ምጣኔ ሃብታዊ፣ ሥነ ልቦናዊ፣ ማህበራዊ፣ አካላዊ አቋምና ደረጃ ያለው ነው።  አገራት ከራሳቸው ማህበራዊ፣ ባህላዊና ሌሎች እሴቶችን መሰረት በማድረግ ለወጣትነት የሚሰጡት የእድሜ ክልል ይለያያል። ለምሳሌ፦ አውሮፓ ከ15—30፣ አፍሪካ ከ15_35 ያለውን የሕብረተሰብ ክፍል ይወክላል።በዚህ የዕድሜ ክልል የሚገኙ ሰዎች የወጣትነት መገለጫወች/ምልክቶች ይታዩባቸዋል፤ ለውጦችም በከፍተኛ ደረጃ የሚከሰቱበት ነው። ማለትም አካላዊ/physical፣ ስሜታዊ/emotional፣ አዕምሮአዊ/cognitive፣ እውቀታዊ/ knowledge፣ ጥበባዊ/ skill እና መስተጋብራዊ/relationships። ወጣትነት ከእነዚህ ከፍተኛ ለውጦች ጋር በተያያዘ እራስን ለማወቅ የሚደረገው ጥረት በጣም ከፍ የሚልበት፣ ለችግር ተጋላጭነት የሚጨምርበት፤ አንድን ነገር በማድረግ በሰዎች ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት ለማትረፍ የሚሮጥበት እንጂ በሚደረገው ነገር የሚፈጠረው መጥፎ  ነገር በውል የማይጤንበት ጊዜ ነው። በዚህ ወቅት ከፍተኛ ጾታዊ ፍላጎት የሚቀሰቀስበት እና የወጣቶች አዕምሮ የሚባክንበት፤ ለልዩ ልዩ ሱሶች የሚጋለጡበት፤ እኔ ያልኩት ካልሆነ የሚሉበት ወዘተ ጊዜ ነው። በወጣትነት የእድሜ ዘመን ጠቃሚም ጎጅም ምልክቶች ይታዩብናል። ከእነዚህም መካከል የዳበረ አካላዊ ብቃት፣ተለዋዋጭ ስሜት፣ በራስ መተማመን/መመካት፣ ገደብ ማጣት/ገደብን አለመቀበል፣ በልጦ መታየትና ፈጣንነት ናቸው። በተለይ ሁሉንም ነገር ለማየት፣ ለመፈተሽ፣ የመቅመስ ስሜት የሚታይበት ነው። ክፉውንም መልካሙንም፣ የሚጠቅመውንም የማይጠቅመውንም ለመለየት ማየት፣ ማድረግና መሞከር የሚፈለግበት ዘመን ነው። እንዲሁም የወጣትነት ዘመን ከሁሉ በእውቀትም፣ በኃይልም፣ በውበትም፣ በሙያም፣ በችሎታም የምበልጠውና የምሻለው እኔ ነኝ የሚባልበት ጊዜ ነው። የተሻለ ሁኖ ለመገኘት የመፈለግ ስሜት የሚታይበት ነው። ለምሳሌ,፦ ከሌሎች መካከልተውቦ ለመገኘት፣ ተናግሮ ለመደበጥ/ለማሳመን፣  ጽፎ ለማስነበብ፣ አሸንፎ ለመሞገስ በአጠቃላይ አይነ ግቡ ሁኖ ለመገኘት የሚደከምበት ዘመን ስለሆነ ወጣትነት በአግባቡ ከአልተያዘ ጉዳቱ ከፍተኛ ነው።

በአጠቃላይ የዘመኑን ወጣት ለአገሩ በአለው አመለካከት በሦስት መክፈል ይችላል።

  1. ወጣትነትን ተጠቅሞ ለአገሩ የሚያስብ የሚጨነቅ፣ አገራዊ ስሜት ፍቅር ያለው፣ የለውጥ ኃይል የሆነ፣ ለነጻነትም የሚታገል፣ለአገር እድገትና ዲሞክራሲ ግንባታ የሚፋጠኑ
  2. አገሩን የማያውቅ፣ ማንነቱን የረሳ፣ ማዎቅም የማይፈልግ፣ ለጠቅም ብቻ የሚጓዝና ተስፋ የለሽ ወጣት
  3. በስሜት የሚጋዝ፣ አንዴ አገር ወዳድ ይሆናል፣ ወደነፈሰበት የሚጋዝ፣ ዓላማና ግብ የሌለው

አገር እና ዲሞክራሲ ሲባል

አገር በዘርፉ ያሉ ባለሙያዎች እንደሚናገሩት አንድ አገር ፣ ሉዓላዊ አገር  ለመባል  ሦስት መሰረታዊ ነገሮች ያስፈልጓታል። ከእነዚህ መሰረታዊ ነገሮች መካከል አንዱ ከተነካ ሉዐላዊት አገር የሚለው ይቀርና ሌላ ስም ይሰጣታል። እነዚህ ሦስቱም ተደጋግፈውና አንዱ የአንዱን ሉዐላዊነት መጠበቅ፣ ማስጠበቅ ይኖርበታል። አንዱ አንዱን ካጣ ምዕሉ ሊሆን አይችልም። የአንድ አገር ሦስቱ መሰረታዊ ነገሮች የሚባሉት ግዛት፣ ህዝብና መንግስት ናቸው። እንዲሁም ሁሉም ብሄር ብሄረሰቦችን አንድ የሚያደርጋቸውና ከፍ አድርገው የሚያውለበልቡት የአንድ ሀገር መለያ ባንዲራ/ሰንደቃላማ ሲኖራት ነው።

ግዛት፦ የአንድ አገር ግዛት ማለት ወሰኗ፣ ድንበሯ፣ የቆዷ ስፋቷ፣ በውስጧ የየያዘዛቸው ወንዝ፣ ተራራ፣ሸለቆ፣ ባጠቃላይ ሙሉ ካርታዋ ማለት ነው። የኢትዮጵያ ግዛት ስንል በምስራቅ፣ በሰሜን፣ በደቡብና በምዕራብ ከሚያዋስኗት ግዛቶች የምትለይበት ቦታ፣ ድንበር ወይም ክልል ጀምሮ በውስጧ የየያዘዛቸው ወንዝ፣ ተራራ፣ሸለቆ ወዘተ ሙሉ የቆዳ ስፋቷን ያዋስናል። ከዚህ የቆዷ ስፋቷ ትንሽ ከተነካ ግን የነበራት ሙሉ ግዛት አይኖራትም። መንግሥት ለግዛቷ ሲጨነቅ አናይም። እንደ ጥሬ እቃ ግዛቷን ሲሸጥም፣ ሲደራደርባትም እናያለን። ይህን ግዛቷን ለማስጠበቅ ወጣቱ  በመተባበርና በመጠበቅ ሁሉም የድርሻውን መወጣት አለበት።

ለሕዝብ፦ ከሁሉም በላይ ክብርና ሥልጣን ሊሰጠው የሚገባ ነው። ሕዝብ ከሌለ የምንላቸው ነገሮች የሉም። ህዝብ ከሌለ ለግዛት ስም ጠርቶ፣ ወሰን ወስኖ ሊያስቀምጥ የሚችል አካል የለም። ስለዚህ ሕዝም ውድ ዋጋ ያለው ነው። በሌላም በኩል ፈጣሪ አክብሮና ባለ አዕይምሮ አድርጎ የፈጠረው መተኪያ የለለው ፍጡር ነው። ስለዚህ ግዛት በሕዝም ይከበራል፤ መንግሥት ደግሞ በሕዝብ ይከብራል/ይነግሣል። ላከበረው፣ ላነገሠው ሕዝብ መንግሥት ዋጋ ሊከፍልለት ይገባል። ከዚያ ውጭ ግን(የዜግነት ክብር በኢትዮጵያችን ፀንቶ፣ ታየ ህዝባዊነት ዳር እስከዳር በርቶ)እያልን የአገር መለያ፣ የማንነታችን መገለጫ የሆነውን ባንዲራ እያውለበለብን የምንዘምረው የህዝብ መዝሙር ከንቱና ዋጋ አልባ ሆኗል ማለት ነው። ባንዲራ ደግሞ ጨርቅ አይደለም ልዩ መለያ ማንነታችን ነው። ይህን የማንነት ጉዳይ ሊያስከብረው የሚችል ደግሞ ህዝብ ነው። ሕዝብ ማለት ደግሞ እያንዳንዳችን ስብስብ/ድምር ውጤት ነው። ስለዝህ ለህዝብ የሚያስፈልገውን ነጻነት፣ እድገት፣ብልጽግና እንዲያገኝ እኛ ወጣቶች የበኩላችንን ድርሻ መወጣት አለብን፤ ግዴታችንም ነው።

መንግሥት፦ መንግሥት ማለት በጥሬ ትርጉሙ በአንድ አገር  ውስጥ ሕጎችን ለማውጣትና ለማስፈጸም፣ ሕዝብን ለማስተባበርና ደኅንነቱን ለማስጠበቅ፣ አገርን ለማስከበር  ስልጣንና ኃላፊነት ያለው አካል ማለት ነው። እንዲሁም በምርጫም ይሁን በሌላ መንገድ በሕዝብ ድጋፍ ስልጣን ላይ የወጣ አካል ነው። ስለዚህ ይህ በሕዝብ ድጋፍ ሥልጣንን የያዘ አካል ከስሙና ከትክክለኛ ትርጉሙ አንፃር ለህዝብና ለአገሪቱ ግዛት ከማንም በላይ የሚጨነቅ፣ የሚያስብና የሚቆረቆር አካል መሆን ይኖርበታል። ምክንያቱም ሕዝብ ከሌለ መንግሥት የለም፤ ግዛትም ከሌለ እንዲሁ። ከምንም በላይ ለመንግሥት መኖር ሁለቱም ወሳኝ ጉዳዮች ናቸው። የየትኛም አገር መንግሥት ይህን ተገንዝቦ ለሁለቱም የሚገባውን እንክብካቤና ክብር መስጠት ካልቻለ የመኖር ዋስትናው ጥያቄ ውስጥ ይገባል። አወዳደቁም በእጅጉ የከፋ ይሆናል።

ዲሞክራሲ፦ ማለት የዲሞክራሲ ጥንታዊ ትርጉም “ የህዝብ ሃይል” ወይም “ የህዝብ አስተዳደር” ሲሆን መሰረቱም ሁለት የግሪክ ቃላቶች ዴሞስ(demos)“ህዝብ” እና ክራቶስ (kratos)“ሃይል” ውህደት ነው:: የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት በነበሩት አብረሃም ሊንከን አተረጓጐምም መሰረት ደግሞ ዲሞክራሲ ማለት በህዝብ የተመረጠና ለህዝብ የቆመ የህዝብ መንግስት ማለት ነው:: በዚህ ዓይነት ስርዓት ውስጥ የተመረጡ መሪዎች ቀጥተኛ ተጠሪነታቸው (accountability) ለህዝቡ ሲሆን የሚሰጡት አገልግሎትም በህዝቡ ፍላጎት ላይ የተመሰረተ ብቻ እንደሆነ ይገለጻል:: ዘመናዊው የዲሞክራሲ ምንነት በቀደምቶቹ ትርጉሞች ላይ የዳበረ ሲሆን የሰው ልጅ መሰረታዊና ፖለቲካዊ መብቶች የማክበር፣ በህዝቦች መካከል የሰፈነ እኩልነት፣ ነጻና ፍትሃዊ የመምረጥና የመመረጥ መብት ያለው፣ ሃሳብን በነጻነት መግለጽ የሚፈቅድ፣ እንዲሁም ከማንኛውም ተጽዕኖ ነጻ የሆነ የፍትህ ሥርዓትንና ነጻ ፕሬስን ያካተ ተቋም መሆን እንዳለበት ይታወቃል።

ኢትዮጵያ አገራችን ብዙ  መንግሥታትን ያስተናገደች አገር ናት። ሆኖም ግን ለዘመናት ታሪኳን፣ ባህሏን፣ እምነቷን፣ አንድነቷን፣ ድል አድራጊነትን እና ዳር ድንበሯን ጠብቃ አስጠብቃ  የኖረች እና መተሳሰብን፣ መከባበርን፣ እንግዳ ተቀባይነትን፣ ዘርንና ጎሳን መሰረት ሳታደርግ ለዘመናት የቆየች የጀግኖች አገር ናት።

ዛሬ መንግሥት ነይ ባዩ የወያኔ/ሕወሓት ቡድን ግን፦

  • ኢትዮጵያ የምትባል አገር እንዳትኖር የሚፈልግ፣  አገራዊ ስሜት ፈጽሞ የማይታይበት፣ ህዝቧና አገሪቱን የድህነት ሰለባ አድርጎ ከመኖር ወደ አለመኖር ዳርጎናል።
  • ትውልድ ገዳይ/ ወጣት አልባ /አገራዊ ስሜት እንዳይኖረን/ከሥርዓተ ት/ቱ ጀምሮ
  • የሰባዊ መብት ጥሰትና ረገጣ በግንባር ቀደም የሚጠቀስ፣ ከራሱ ቡድን ውጭ ሰው እንደሰው የማይቆጠርበት አገር አድርጓታል።
  • ተፈጥሮአዊና መሰረታዊ መብት የማምለክ፣ የመንቀሳቀስ፣ የመሥራት፣ የመኖር ነጻነታችንን ነፍጎናል፤
  • ዲሞክራሲያዊ መብታችን የመደራጀት፣ የመቃወም፣ የመወያየት፣ የመምረጥ  ወዘተ በዲሞክራሲ ስም ፀረ ሰላም፣ ፀረ ልማት፣ ፀረ ዲሞክራሲ፣ ፀረ ህግ ተብሎ በፀረ ሽብር ህግ አማካኝነት አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን የሚገደሉበት፣ የሚታሰሩበት፣ የሚንገላቱበት፣ የሚደበደቡበት፣ የሚሰደዱባት (አንዳርጋቸው ጽጌ፣ እስክንድር ነጋ፣ ውብሸት ታየ፣ አንዷለም አራጌ፣ ርዮት ዓለሙ፣ ጦማርያን፣ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ሳይቀሩ)
  • ልማት ለወያኔ በተግባር ሳይሆን በቃል ብቻ 11% ማደግ፣ አገርን መሸጥ እና ሰባዊ መብትን ከመገንባት ይልቅ ህንጻና መንገድ መገንባት ማለት ነው።

ይህን ጨቋኝና አፋኝ ሥርዓት አሶግዶ አገራዊ ስሜት ለመላበስ እንዲሁም ለአገር እድገትና ዲሞክራሲ ግንባታ የወጣቱ አስትዋጾ ከፍተኛ መሆኑን ተረድቶ ለነጻነት መታገል የእያንዳንዱ ወጣት አገራዊ ግዴታም ኃላፊነትም ነው።

አገራዊ ስሜት መላበስ ሲባል አገርን በሚገባ ማወቅና በማነኛውም መልኩ ለችግሯ ደራሽና ተቆርቋሪ መሆን ማለት ነው። ለባንዲራዋ ክብር መስጠት ነው። ኢትዮጵያዊነት ማለት ምን ማለት እንደሆነ ማወቅ መገንዘብ ነው። ወያኔ ወጣቱን ስለአካባቢው እንጂ እንደ አገር ማውራት እንዲያቆም አድርጎናል። ስለ ኢትዮጵያ ሲወራ እንደ ሁለተኛ ሦስተኛ ዜጋ ሁነን ቁመን የምንሰማ በርካቶች ሁነናል። ትርጉሙም ስሜቱም ጠፍቶብናል። ወጣቱም ብሔርን፣ ቋንቋን ይሰብካል። የፖለቲካ ድርጅቶችም ይህንኑ ያስተጋባሉ። ለአገር ሳይሆን ለብሔር ብቻ የቆሙ ናቸው። ይህን ከባድ ችግር አሶግደን አገራዊ ስሜት ሰንቀን ኢትዮጵያዊነት ምን ማለት እንደሆነ ከተረዳን የወያኔ ቡድን አሁን በኢትዮጵያውያን ላይ የሚደርሰውን ችግር ማስቆም እንችላለን። አገራዊ ስሜት በውስጣችን ከነገሰ ለአገር፣ ለወገንና ለክብራችን ዘብ እንቆማለን።

አገራዊ ስሜት ያለው ወጣት ከሌሎች የሚለዩበት፦

  • ፍቅር …ሰባዊና አገራዊ ፍቅር፣ ለሰው ልጅ ሰው በመሆኑ ብቻ ክብርና ፍቅር መስጠት።
  • ተስፋ …ለተተኪ ትውልድ አርቆ ያስባል፣ መልካም ነገሮችን በተስፋ መነጸር መመልከት ይችላል፣ ተስፋ ኃይልና ብርታት ይሆናል፣ በተስፋ የነጻነት፣ የፍትህና የዲሞክራሲ ብርሃን ማየት ይቻላልና።
  • ግልጽነትና ተጠያቂነትን ገንዘብ ያደርጋል, የሚሰራውን ተግባር በግልጽና በተጠያቂነት ያከናውናል፣ ለሥራው ሁሉ ለራሱ፣ ለአገሩና ለወገኑ ተጠያቂ ይሆናል።
  • ሙስናን ፈጽሞ ይጠላል፣ ያጋልጣል/ይቃዎማል።
  • መልካም ሥነ ምግባር የተላበሰ/ ከማይጠቅም ነገር እራስን ያርቃል።
  • የአገርን ግዛቷን፣ ታሪኳን፣ ባህሏን መጠበቅ መመስከር፤ ለአገሩ ደራሽና ተቆርቋሪ ነው።
  • እራስን ሁኖ መኖር ይችላል፣ ማንነቱን ጥንቅቆ ያውቃል፣ በማንነቱም ይኮራል።
  • ለነጻነት፣ ለፍትህና ለዲሞክራሲ እየታገሉ ምሳሌና አርያ የሆኑ ኢትዮጵያውያንን ይከተላል።

አገራዊ እድገትና ዲሞክራሲ ለማስፈን ወጣቱ ሊከተላቸው የሚገቡ ነገሮች

  1. ዓላማ፦ በመጀመሪያ ከስሜት ወጠን ዓላማና ግብ ሊኖረን ይገባል።  ምን እንደምንሰራ እና የት ለመድረስ የሚሉትን ነገሮች ከመጀመራችን በፊት በሚገባ ማዎቅና መገንዘብ፣
  2. ቆራጥነት፦ ዓላማችንን ከግብ ለማድረስ ቆርጦ መነሳት ያስፈልጋል። ፈራ ተባ ማለት ለውጠት አያበቃም። ወጣትነት ኃይል፣ጉልበት አለንና።
  3. እውቀት መገብየት፡ በቆራጥነት ለተነሳንበት ዓላማ በቂ እውቀት ያስፈልገናል። ስለ ታሪካችን፣ ባህላችን፣ማንነታችን እውቀት ያስፈልጋል። በቅኝ ግዛት በተገዛን ኑሮ  የሚል ወጣት ይሰማል ከእውቀት ማነስ የተነሳ፣ የቅኝ ግዛት ምንነትና አስከፊነት ባለመረዳትና አባቶቻችን ለምን ሰማዕትነትን እንደተቀበሉ ካለመረዳት።.ስለዚህ ለሁሉም ነገር እውቀት አስፈላጊ ነው። እውቀትን ከህይወት ተሞክሮ፣ ከት/ት፣ ከመልካም ጋደኛ፣ ከቤተሰብ፣ ከታላላቅ ሰዎች እንቀስማለን።
  4. ስልታዊ ዕቅድ መንደፍ፦ በአገኘነው እውቀት ተጠቅመን ሊያዋጣና ሊያስኬድ የሚችል ስልት፣ ሁለገብ የትግል ስልት መንደፍና መከተል። ከዓላማችን ሊያደርሰን የሚችል ወቅታዊና ዘላቂ እድገትን፣ መብትን፣ ሰላምን፣ ሊያጎናጽፍ የሚችል ስልት መከተልና ውጤታማ ለመሆን መታገል እንደሚያስፈልግ ልንገነዘብ ይገባል።
  5. ነጻነትን ማዎጅ፦ ነጻነት የሚለውን ቃል ሰዎች የተለያየ አተረጓጎም ሊሰጡት ይችላሉ፡፡ ሆኖም ግን ነጻነት ማለት ከግዞት መውጣት፤ ከሌሎች ተጽኖዎች መውጣት፤ በራስ መወሰን ማለት ነው፡፡ ይህ ማለት ማንም ሌላ ሰው ሳያስገድደን እና የማንንም መብት ሳንነፍግ በነገሮች ላይ በራስ ወይም በጋራ መወሰን መቻል ነው፡፡ ደሞክራሲ ሊባልም ይችላል፡፡ ነጻነት አለ ካልን ሃሳባችን ወይም ተሳትፏችን ተሰሚነትና ተቀባይነት አለው ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ነጻነትን አውጀን  ለሰላም፣ ለፍትህና ለዲሞክራስ ቆርጦ  መነሳት ያስፈልጋል።
  6. አንድነታችን መጠበቅ፦  ወጣቱ ሊያከናውን ከሚገባው ነገር አንዱና ትልቆ ጉዳይ አንድነትን ብሄራዊነትን፣ አገራዊነትን ማምጣት ነው።ችግር ለመፍታትም ሆነ መፍትሔ ለመፈለግ እኛ አንድ መሆን ይኖርብናል። መግባባት፣ መነጋገር፣ መወያየት በምንችልባቸው ነገሮች ላይ አንድ መሆን አለብን። በአንድ አገር ውስጥ የተለያየ ቋንቋ፣ ባህል፣እምነት ያለው ህዝብ በአገሪቱ ግዛት አንድ መሆን መቻል አለብን። ይህንን ሊያስተባብርና ሊመራ እንዲሁም አንድ ሊያደርገን የሚችል መንግሥት ሊኖረን ይገባል። ከዚያ ውጭ በቋንቋ፣ በባህል፣ በእምነት እንደተለያየን ሁሉ አንድ ሊያደርገን የሚችል የጋራ የሆነ ነገር ከለሌን ችግሩን በህብረት መቅረፍም ሆነ መቀነስ አንችልም። ወያኔ/ህወሓት ብሔር፣ ጎሳ፣ ቋንቋ፣ እምነት እያለ ሊከፋፍለን፣ ሊለያየን አይገባም። ይህን ድርጊት የፖለቲካ ድርጅቶች፣ የሀይማኖት ተቋማት፣ የግል/ሰባዊ መብት ድርጅቶችና ሕዝብ ሁላችንም  ማውገዝና ማስቆም ይኖርብናል። በተለይ ወጣቱ ትውልድ ትልቅ ኃላፊነት አለበት።

በአጠቃላይ የወጣቱ አስትዋጾ ዘርፈ ብዙ ነው፤ በዚህ ወይም በዚያ ብሎ መወሰን ከባድና አስቸጋሪ ነው። የለውጥ ኃይል እስከሆነ ድረስ በሁሉም ዘርፍ መገኘት እና አገርን ወደተሻለ ደረጃ ማድረስ የዜግነት ግዴታ አድርጎ  መውሰድ ይኖርብናል።

በማነኛውም መልኩ አገራችንን ለማገልገል እራሳችንን ብቁና ዝግጁ ማድረግ ይገባል።ለአገር እድገት፣ ለነጻነት፣ ለፍትህ፣ ለዲሞክራሲ ግንባታ የወጣቱ አስትዋጾ ከፍተኛ መሆኑን ተረድተን በምንችለው ሁሉ የበኩላችንን ኃላፊነትና ግዴታ መወጣት አለብን። መንግሥት ነኝ ባዩን የህወሓትን ቡድን በቃህ መብትና ህግ ይከበር ብለን በአንድነት መነሳት አለብን።

 


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>