Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

ስምንት ጠቃሚ ነጥቦች ከእስራኤላውያን -ክፍል 2 (ዮፍታሔ)

$
0
0
  1. ድርጅት፣ ድርጅት፣ ድርጅት፤ ተቋማት፣ ተቋማት፣ ተቋማት።

 

Jewish+Ethiopians+Reunited+Families+Israel+o1h5oGhsf2Vlበክፍል አንድ አይሁድ አገራቸውን ከተነጠቁ በኋላ በመላው ዓለም እንደተበተኑ፣ በየሄዱበት አገር ተመሳስለው ለመኖር ቢሞክሩም ከጥቃት እንዳልዳኑ፣ ለዚህ መፍትሔ እንዲሆን ‘አይሁድ ወደ ጽዮን (አገራቸው) ተመልሰው አገራቸውን እንደገና ማቋቋም ያስፈልጋቸዋል’ በማለት ቴዎዶር ሄርዝል (Theodor Herzel) የተባለ የአይሁድ ዝርያ ያለው ጋዜጠኛ ሁሉንም ነፃነት ወዳድ አይሁዳዊ በአንድ ጣራ ሥር የሚያሰባስብ አንድ ጠንካራ ድርጅት በዳያስፖራ ማቋቋሙ ተገልጿል።

በእውነት ድርጅት አገራቸውን በግፍ አገዛዝ ለተነጠቁ ያስመልሳልን? መልሱ ከዚህ ታሪክ በግልጽ እንደምንማረው አዎ! ጠንካራ ድርጅት አገራቸውን በግፈኞች ለተነጠቁ አገራቸውን ያስመልሳል፤ ከአገርም ነፃና የበለጸገች አገር ያጎናጽፋል የሚል ነው። ምን ዓይነት ድርጅት? እንዴት? እኛስ ምን እናድርግ? ይህ ወደመጀመሪያው ትምህርታዊ ነጥብ ይወስደናል።

በእስራኤላውያን (አይሁድ) ላይ የተጋረጠው ችግር ቀላል አልነበረም። ፍልስጤምን (እስራኤልን) የሚያውቀው ትውልድ አልፎ እስራኤልን የማያውቅ ትውልድ ተተክቷል። የእብራይስጥ ቋንቋ እንደመግባቢያ (ንግግር) ቋንቋ ፈጽሞ ጠፍቷል። እንደዛሬው ግዕዝ ሁሉ የእብራይስጥን ቋንቋ ከአምልኮ ስፍራ ውጪ (ከመጽሐፍ በማንበብ ብቻ) ማንም አይገለገልበትም። አሁን ያለው አይሁዳዊ ዝርያ ያለው (አለኝ ብሎ የሚያምነው) ትውልድ በተለያየ አገር የሚኖር፣ ዘሩም፣ ባሕሉም፣ አኗኗሩም እንደየአገሩ የተለያየና ያለበትን አገር ‘አገሬ’ የሚል ነው። በየሚገኝበት አገር ሁሉ ቁጥሩ አናሳና በተናጠል ምንም ዓይነት ተጽእኖ መፍጠር የሚችል አልነበረም። ይህን ሕዝብ በመጀመሪያ ማሰባሰብ ያስፈልጋል።

 

ከዚያም ሞቶ በነበረው አይሁዳዊነት ስሜት ላይ ነፍስ መዝራትና የአንድነትና የመተባበር መንፈስ በዚህ ሕዝብ ውስጥ እንደገና መፍጠር ያስፈልጋል። ያ ከተሳካ በኋላ ደግሞ አይሁድ ተሰባስበው የሚሰፍሩበት ቦታ ያስፈልጋል (የመጀመሪያዎቹ ሰፈራዎች ከፍልስጤማውያን ላይ ቦታ በመግዛት ጭምር የተከናወኑ መሆናቸው ይታወቃል)። ያ ሲሟላ ደግሞ በሚሊዮን የሚቆጠረውን የአይሁድ ዝርያ ያለውን ማኅበረሰብ ከተለያዩ አገራት ወደ እስራኤል ማጓጓዝ ያስፈልጋል። ይህን ለማድረግ አይሁድ ይኖሩባቸው ከነበሩት አገሮች ሁሉ ፈቃድ ያስፈልጋል። ጉዞው በአንድ ጊዜ የተከናወነም ባይሆን ለመጓጓዣ የሚያስፈልገው ገንዘብ ቀላል አልነበረም። በአንድ ጊዜ ብቻ (Fifth Aliyah) ከ 225ሺህ እስከ 300ሺህ ሰዎች የተጓጓዙበት ጊዜ የነበረ ሲሆን በጠቅላላው በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ የአይሁድ ዝርያ ያላቸው ሰዎች ወደ እስራኤል ተጓጉዘዋል።

 

ከዚያም እውቅና ያለው ደኅንነቱ የተረጋጋጠ አገር መመሥረት ያስፈልጋል። ስለፈለጉ አገር መመሥረት ደግሞ በጊዜው ለዚያውም ለአይሁድ ቀላል አልነበረም። በጊዜው ወሳኝ የሆኑትን መንግሥታት (ፍልስጤም ከሮማውያንና ኦቶማን ቱርኮች በኋላ በጊዜው በእንግሊዝ ትተዳደር ነበር) እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶችንና ማኅበረሰቡን ማሳመን ያስፍልግ ነበር።

 

ስለዚህ ችግሩ ቀላል አልነበረም። ቀላል ያልሆነ ችግር ደግሞ ጠንካራ መፍትሔ ያሻዋል። የወርልድ ዛዮኒስት ኦርጋናይዜሽን (World Zionist Organization) ገና ከጅምሩ ሲቋቋም ለዚሁ ታስቦ የተዘጋጀ ጠንካራ ድርጅት ነበር። በየዓለሙ መዳረሻ የአይሁድን ጥቃት ለመከላከል/ለመቋቋም መቻል በራሱ ትልቅ ዓላማ ነበር። ብዙዎች ያሰቡትም ይህ ድርጅት ይህንኑ ሊያደርግ ይችላል የሚል ነበር። ድርጅቱ ግን ይህንንና ሌሎችንም ጠቃሚ ሥራዎች እያደረገ ዋና ግቡን አልፎ ሄዶ እያንዳንዱ አይሁዳዊ በነፃነትና በክብር የሚኖርበት የእኔ የሚለው አገር በመመሥረት ላይ አደረገ። በመጀመሪያ ነገር በየዓለሙ የተበተኑትን አይሁዳውያን በአንድ ማዕከል የሚያሰባስብ የአይሁዳውያን ሁሉ ወኪል የሆነ ዓለም አቀፍ ድርጅት ነበር ማለት ይቻላል። በየአገሩ ተበትነው የነበሩ የአይሁድ ዝርያ ያላቸውን ግለሰቦች አባል እንዲሆኑ ያበረታታል፣ በየአንዳንዱ ከተማ የአይሁድን ቁጥር መዝግቦ ይይዛል፣ ገንዘብና ቁሳቁስ ከአባላቱና ከለጋሽ ግለሰቦች፣ ድርጅቶችና መንግሥታት ያሰባስባል፣ በሥሩ በተለያየ መስክ ሥራ የሚሠሩ ተጨማሪ ተቋማትንና ድርጅቶችን ያቋቁማል፣ በፍልስጤም እና በዳያስፖራ ለሚኖሩ አፋጣኝ ርዳታ ለሚያስፈልጋቸው የገንዘብ፣ የቁሳቁስ፣ የጤናና የትምህርት ርዳታ  ያደርጋል፣ በፍልስጤምና በዳያስፓራ በሚገኙ አይሁድ ላይ የሚቃጣውን ጥቃት ይከላከላል፣ በአይሁዳውያን ዘንድ የግንዛቤ፣ በሌሎች ዘንድ የአይሁዳውያንን ችግር የማስገንዘብ፣ የመቀስቀስና  የፕሮፖጋንዳ ሥራ ይሠራል፣ ከመንግሥታት ጋራ ይገናኛል፣ ተጽእኖ ፈጣሪ ከሆኑ ግለሰቦችና ድርጅቶች ጋራ አብሮ ይሠራል። በአጭሩ ለእስራኤላውያን በውጭ የሚገኝ ጊዜያዊ መንግሥት ነበር ማለት ይቻላል።

 

ለወገኖቹ ለእስራኤላውያን በሠራው ሥራ “የእስራኤል አባት” እየተባለ ሲወደስ የሚኖረው ቴዎዶር ሄርዝል (Theodor Herzel) የዓለም የጽዮናዊነትን ድርጅት ሲያቋቁም ጓደኞቹ ሳይቀሩ እንደ እብድ ቢቆጥሩትም የእርሱ ዓላማ ቆርጦ ለተነሳበት ወገኖቹን የመሰብሰብና አገር የመመሥረት እቅዱ በየደረጃው አስፈላጊ የሆኑትን ዝግጅቶች የሚያሟሉ በሁሉም መስክ ብቃት ያላቸው ጠንካራ ድርጅትና በስሩ በርካታ ተቋማትን መፍጠር ነበር። በዚህም መሠረት በገንዘብ፣ በሰው ኃይልና በእውቀት የዳበሩ ተቋማትን ማቋቋሙን ገፋበት።

 

በሥሩ ካቋቋማቸውና በትብብር ይሠሩ ከነበሩ ጥቂት ድርጅቶችና ተቋማት መካከል “Jewish National Fund/ብሔራዊ የአይሁድ የገንዘብ ድጋፍ ማሰባሰቢያ” (በፍልስጤም ለአይሁድ መስፈሪያ የሚሆን ቦታ መግዣ ገንዘብ የሚያሰባስብ የነበረ አሁንም ያልከሰመ)፣ የ “Jews Agency/የአይሁድ ወኪል” (ለ3 ሚሊዮን አይሁድ መመለስ ሁኔታዎችን በማመቻቸትና መኖሪያ በማዘጋጀት፣ በአስተዳደር፣ በመረጃ፣ በደኅንነትና በውትድርና በፍልስጤም ድርጅቱን በመወከል ይሠራ የነበረ እስካሁንም ያልከሰመ)፣  “Jewish Federations of North America/የሰሜን አሜሪካ የአይሁድ ፌዴሬሽኖች” (ለ Jews Agency ዋናው የገንዘብ ምንጭ የነበረ፤ በአሜሪካና ካናዳ የሚገኙ በርካታ የአይሁድ ፌዴሬሽኖች በሥሩ ያሰባሰበ ድርጅት)፤ “Zionist Organization of America/የአሜሪካ የጽዮናዊነት ድርጅት” (በአሜሪካ ድርጅቱን በመወከል ዲፕሎማሲን ጨምሮ በተለያዩ መስኮች እስካሁንም የሚሠራ)፣ “Women’s Zionist Organization of America/የሴቶች ጽዮናዊ ድርጅት በአሜሪካ” (የመጀመሪያዎቹን ነርሶችና ዶክተሮች በውጭ አሰልጥኖ ወደ እስራኤል ከመላክ ጀምሮ በየከተማው ክሊኒኮችን፣ ሆስፒታሎችንና የጤና ምርምር ተቋማትን ያቋቋመ፤ በተጨማሪም የዲፕሎማሲ፣ የማኅበረሰብና የትምህርት ሥራዎችን የሚሠራ ድርጅት)፣ “Women’s International Zionist Organization”/ ዓለማቀፍ የሴቶች ጽዮናዊነት ድርጅት” (በማኅበራዊ ደኅንነት፣ በትምህርትና በሴቶች እኩልነት ላይ ይሠራ የነበረ)፣ “Zionist Youth Movement”/ የወጣቶች ጽዮናዊ ድርጅት (ወጣቶችንና ልጆችን በትምህርት፣ በማኅበራዊና በአይሁድ ባህልና ታሪክ ያሰለጥን የነበረ፤ የትምህርት ፕሮግራሙ በኋላ በእስራኤል የትምህርት ፕሮግራም ተካቷል) እና ሌሎችም ይገኙበታል።

 

እነዚህ ድርጅቶች በሁሉም የተሟሉና ልምድ አስቀድመው ያካበቱ ስለነበረ በ1948 (እ. ኤ. አ) እስራኤል ስትመሠረት የዋናው ድርጅት መሪ ዴቪድ ቤንጉሪዮን (David Ben-Gurion) የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ የ “Jews Agency” መሪ የነበረው ቻይም ዋይዝማን (Chaim Wiesmann) የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ለመሆን ሲበቁ በውጭ አስቀድመው የተመሠረቱት በተግባር የተፈተኑት ድርጅቶችና ተቋማት ደግሞ በየመስኩ የአዲሲቱ አገር እስራኤል ተቋማት በመሆን ሊቀጥሉ ችለዋል። በፍልስጤም ለነበሩት ሞዴል በመሆን ያገለገሉትም እነዚሁ በውጭ የተቋቋሙት ድርጅቶችና ተቋማት ነበሩ።

 

ሁላችንንም የሚያሰባስብ እንዲህ ዓይነት ጠንካራ ዓለም አቀፋዊ ድርጅትና በሥሩ የተለያየ ኃላፊነት የሚያከናውኑ ጠንካራ ተቋማት ለእኛ ለኢትዮጵያውያንስ በውጭ አያስፈልጉንም? መልሱ እጅግ በጣም ያስፈልጉናል የሚል ነው። ይህ ቢኖረን ምን ማድረግ እንደምንችል ለመገመት አስቸጋሪ አይደለም።

 

ይህን ለማድረግ የሚያስችሉ አበረታች ጅምሮች አሉን። እነርሱን በማጠናከር ይህን የመሰለ ሥራ የሚሠራ በተለያዩ አገራት የተሰራጨው ሁሉም ነፃነት ወዳድ ኢትዮጵያዊ በአንድ ማዕከል የሚሰባሰብበትና ውጤት የሚያመጣበት በሰው ኃይል፣ በፋይናንስና በእውቀት እጅግ የጠነከረ አሁን ያለንበትን ችግር ማስወገድና ዜጎቿ በነፃነት፣ በእኩልነትና በፍትህ የሚኖሩባት አገር ከማድረግም በላይ በአጭር ጊዜ ከአደጉት አገሮች ተርታ የምትሰለፍ አገር የሚያደርግ ከሁለም የተውጣጣ ድርጅት መመሥረት ይኖርብናል። ይህ የተጋረጠብንን አገር አጥፊ አምባገነንና ዘረኛ አገዛዝ ከማስወገድም በኋላ የሚመሠረተውን ሥርዓት አስተማማኝ ለማድረግ ትልቅ ዋስትና ይኖረዋል።

 

ችግራችን የተወሳሰበ ከመሰለን መፍትሔውም እስካሁን ከሄድንበትና ከተለመደው በተጨማሪ ትንሽ የተለዩና ከዚህ ቀደም በሌሎች ተሞክረው አስተማማኝ ውጤት ያስገኙ መንገዶችንም እንድንከተል ግድ ይለናል።

 

የአገዛዙ ጥቃት ፓለቲካዊ ኢኮኖሚያዊ ብቻ ሳይሆን ዘርፈ-ብዙ ስለሆነ ትግሉም አንድ አቅጣጫ ብቻ ሳይሆን ዘርፈ ብዙ መሆን ይጠበቅበታል። ስለዚህ በዋናው ድርጅት ጃንጥላ ሥር ራሳቸውን የቻሉ የመረጃ (ጥናትና ምርምር)፣ የቴክኖሎጂ፣ የሕግ፣ የዲፕሎማሲ፣ የትምህርት፣ የጤና፣ የባሕል፣ የቋንቋ ተቋማት መቋቋም ይኖርባቸዋል።

 

ይህን ዋና ድርጅትና ተቋማቱን መመሥረትና ማደራጀት አሁን እየተካሄደ ያለውን የፖለቲካ እንቅስቃሴ በብዙ መቶ እጥፍ ወደፊት እንዲራመድ በማድረግ ድሉን የሚያፋጥንና ከድል በኋላም የሽግግሩንና የአገር ግንባታውን አስተማማኝ የሚያደርግ ቀጣይነት ያለው እንጂ አሁን እየተካሄዱ ባሉት እንቅስቃሴዎች ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እንደሚያስከትል ተደርጎ መታሰብ አይኖርበትም።

 

ተቃዋሚዎችና ዳያስፖራው ለአገራቸው ምን ሊያደርጉ እንዳሰቡና ምን ሊያደርጉ እንደሚችሉ ከወዲሁ በሥራ የሚያሳዩበትና የሚያስመሰክሩበት እድል ያገኛሉ። የሚሠሩት ሥራና ለሁሉም የሚታየው ድርጅታዊ አቅምና ጉልበታቸው የጠላትን ቅስም የሚሰብር በኢትዮጵያ ሕዝብ፣ በኃያላኑ መንግሥታት፣ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብና በጎረቤት አገራት ዘንድ ከፍተኛ ክብርን፣ መተማመንንና ዋስትናን የሚፈጥር ይሆናል። በአጭሩ አሁን ያለውን ሁኔታ ከመሠረቱ በመገልበጥ (በእንግሊዝኛው Game Changer የሚሉትን ክስተት በመፍጠር) ለአገርና ለመላው ነፃነትና ፍትሕ ወዳድ ሕዝብ አመቺ ሁኔታን የሚፈጥር፣ የሕወኀትን ቀን የሚያሳጥር፣ ሽግግሩን እንከን የለሽ የሚያደርግና መጪውን ጊዜ ሁሉም የሚመኛትን የበለጸገች አገር በአስተማማኝ መገንባት የሚያስችል ያደርገዋል።

 

የዚህን ድርጅት መሥራች ጉባኤ አሁን ካሉት ድርጅቶች የተውጣጣ፣ በሕዝብ አመኔታን ያገኙ የሀይማኖት መሪዎች፣ የአገር ሽማግሌዎችና ታዋቂ ግለሰቦች የሚገኙበት አካል ለዝግጅት ትንሽ ጊዜ ወስዶ ነገር ግን ሳይውል ሳያድር ለብዙሐኑ አመቺ በሆነ ከተማ ጉባኤውን በተገኘው መንገድ ሁሉ በማሰራጨትና እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ዘንድ እንዲደርስ ሰፊ ቅስቀሳ በማድረግ በየመስኩ ያሉትን ባለሙያዎችና መላውን ዳያስፖራ በመጋበዝ፤ በአካል ሊገኝ የማይችለው መላው ኢትዮጵያዊ ከየሚኖርበት ቦታ በቪዲዮ ኮንፈረንስ፣ በስካይፕ (Skype) እና በቀጥታ የሳተላይት ቴሌቪዥን ስርጭት በቀጥታ የሚሳተፍበትንና የሚከታተልበትን የግንኙነት ቴክኖሎጂ አስቀድሞ በማዘጋጀት ይህን መስራች ጉባኤ እውን ሊያደርጉት ይገባል።

 

በዚህ የመጀመሪያውን ነጥብ አጠቃለን ወደሁለተኛው እናልፋለን።

 

  1. የተጋረጠውን ፈተናና መፍትሔውን ዓለምአቀፋዊ ማድረግ።

 

(ይቀጥላል)

 

ኢትዮጵያ በቆራጥ ልጆቿ ሥራ ታፍራና ተከብራ ለዘለዓለም ትኖራለች!

 

 

 


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>