ተክሌ የሻው
አለማወቅ እንደልብ ያናግራል። አላዋቂ ሰዎች ሲገሩ ካፋቸው የሚወጣው ቃል በማኅበረሰቡ ባህል፣ ወግ፣ አኗኗር፣ ሰላምና አጠቃላይ ማኅበራዊ ግንኙነት ውስጥ ሊያስከትል የሚችለውን ጥቅምና ጉዳት አያመዛዝኑም። ከአንደበታቸው የሚወጣው ቃል በትውልድ ላይ ጥሎት ሊያልፍ የሚችለውን መጥፎም ሆነ መልካም አሻራ አይመዝኑም። በመሆኑም ንግግራቸው አንደበታቸው ያቀበላቸውን እንደወረደ ወደ አድማጫቸው ስለሚለቁት የሰዎችን አዕምሮ ያቆስላል፤ የማኅበረሰቡን ባሕልና ወግ ይንዳል። ከሁሉም በላይ አላዋቂነት በፖለቲካ ሥልጣን ሲታጀብ ማን አህሎኝነት ስለሚጨመርበት የሚናገሩት ንግግር ልጓም አልባ ስለሚሆን ንግግራቸው ከጥቅሙ ጉዳቱ በእጅጉ ይበላጣል። ይህም ለአገርና ለትውልድ የነገር፣ የቂምና የጥላቻን ቁርሾ ጥሎ ስለሚያልፍ የሰላምና የአንድነት ፀር ይሆናል። ባጭር አገላለጽ « አላዋቂ ሳሚ ንፍጥ ይለቀልቃል» ዓይነት ነው።
ለዚህ አባባል ሰሞኑን የኢትዮጵያው የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ነኝ የሚለው ዶ/ር ሽፈራው ተክለማርያም የተባለው ማተብን አስመልክቶ የተናገረው ጥሩ ያላዋቂነት ምሳሌ ነው። ሰውየው «ማተብ የክርስትና ሃይማኖት መለያና ምልክት ከሆነ እንቆርጣለን» ሲል፣አፉን ሞልቶ በማን አለብኝነት የተናገረው ፣«ጨዋታ ሲደራ እናቴ ባርያ ናት» ያሰኛል እንደሚባለው፣አባባሉ ሊያስከትል የሚችለውን ሁኔታ፣ በማኅበረሰቡ አጠቃላይ ግንኙነት ሊፈጥር የሚችለውን እንደምታ አለማወቅ ወይም ማመዛዘን አለመቻል የወለደው እብሪት እና ድንቁርና ነው።
በአንፃሩ ዐዋቂዎች የሚናገሩትን በማስረጃ ስለሚያስደግፉ የሰሚዎቻቸውን አዕምሮ እና ኅሊና ይስባሉ። አድማጫቸውን ያስደስታሉ፣ ያሳውቃሉ፣ ያዝናናሉ። የዘሩት መብቀል ብቻ ሳይሆን ያፈራል ። ሰዎችን አያስከፉም፤ የሌሎችን መብት አይፃረሩም፤ የማኅበረሰቡን ባሕልና ወግ ያከብራሉ፤ ይጠብቃሉ፤ የነርሱን መልካም ነገር በመጨመር ያለፈውን በመልካም ጎኑ እንዲዳብር ያደርጋሉ። የንንግግራቸው መቋጫ አንድነትና ሰላም ነው።
እንዳው ወደማተብ ቆረጣው ይሳካል፣ አይሳካም፣ ወደሚለው ከመግባታችን በፊት የማተብን ምንነት፣ በኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ውስጥ ያለውን ባሕላዊ፣ ሃይማኖታዊ ፋይዳና የያዘውን ዕሴት እንመልከት።
በኢትዮጵያውያን የቆየ መልካም ባሕል ውስጥ ማተብ ልዩ ቦታና ትርጉም ያለው የሐቅና የዕውነት ማስረገጫ፣ የተገቢና የትክክለኛ ነገር መግለጫ ነው። አዋ እገሌ፣ እሜቴ እገሊት ማተበ ጥኑ ናቸው፤ አቶ እገሌ፣ ወ/ሮ እገሊት ባለማተብ ናቸው፤ የሚባሉት አባባሎች አደራ ተቀባዮችን፣አደራ አስቀማጮችንና የታማኝ ሰዎችን ሥብዕና የሚንገልጽበት ኃይለ ቃል ነው። « የተናገሩት ከሚጠፋ የወለዱት ይጥፍ» ብለው ለቃላቸው የሚቆሙትን፣ ሃይማኖት አክባሪ፣ እግዚአብሔን ፈሪ የሆኑ ሰዎችን ከሌሎቹ ለይተን የምንጠራበት ውብ የሐቅ መገለጫ ቃል ነው። ቃሉ የራሳቸውን ለመለገስ እንጂ፣የሌሎችን ቤሳ ቤስቲ የማይፈልጉትን፣ አጠቃላይ ሕይዎታቸውና ኑሮአቸው ሐቅን፤ ዕውነትን መሠረት አድርገው የሚንቀሳቀሱ ሰዎች ማንነት መገላጫ የሆነ ቃል ነው። ይህ ቃል ከቃልነት አልፎ የሐቅ መገለጫ ለመሆን የበቃ ስለሆነ ባህል ነው። የዕውነት መገለጫ ነው።
በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ ማተብ የሥላሴዎች አንድነትና ሦስትነት የሚገለጽበት ረቂቅ ሚስጥር የያዘ ነው። በማቲዎስ ወንጌል ምዕራፍ 28 ከቁጥር 18 እስከ 20 እንዲህ ይላል። « ኢየሱስም ቀረበና እንዲህ ብሎ ተናገራቸው፣ ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጠኝ። እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፣ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ እነሆ እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተጋር ነኝ።» ሲል አምላካችንና ፈጣሪያችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ በሰጠው ትዕዛዝ መሠረት የሚፈጸም ተጠማቂው ከመንፈስ ቅዱስ የመወለዱ ምልክት ነው። አጥማቂው ካህን «በአብ ስም አጠምቅሃለሁ፤ በወልድ ስም አጠምቅሃለሁ፣ በመንፈስ ቅዱስ ስም አጠምቅሃለሁ፤» ካለ በኋላ ለመጠመቁ ምልክት ይሆን ዘንድ ፣ሦስት ጥቁር፣ቀይና ብጫ ቀለም ያላቸውን ክሮችን ባንድነት ገምደው (ሸርበው) በአንገቱ ላይ ያስራሉ። የክሮቹ ሦስትነት የአብ ወልድ እና መንፈስ ቅዱስ ምሳሌ ሲሆን፣ ተገምደው አንድ መሆናቸው የሥላሶችን ሦስትነትና አንድነት ምሳሌ ነው።
የቀለሞቹ ትርጉምም ቀዩ የሰማዕትነት፣ ጥቁሩ መሰቀሉንና መከራ የመቀበሉ፣ብጫው የመንግሥተ ሰማየት ተስፋ ምልክቶች ናቸው። ጥምቀት ወንድ በተወለደ በ40 ቀኑ፣ ሴት በ80 ቀኗ የሚከናወን ፣ተጠማቂዎቹ ከመንፈስ ቅዱስ የመወለዳቸው መረጋገጫ ነው። ሁለት ልደት የምንለውም ሰው በአካል ከወላጆቹ የመወለዱ አንዱ ሲሆን፣ሁለተኛው በመጠመቁ ከመንፈስ ቅዱስ የመወለዱ ሚስጢር ነው።
ማንም የኢትዮጵያን ኦርቶዶክ ተዋሕዶ ሃይማኖት ቀኖና፣ዶግማ፣ ሥርዓትና ታሪክ ጠንቅቆ ለሚያውቅ ሰው የመጀመሪያዋ ብቸኛ የመንግሥትና የሕዝብ ሃይማኖት ሆና በአብርሃና በአጽብሃ ዘመን የታወጀች ሃይማኖት መሆኗን አይዘነጋም። ቤተክርስቲያኒቱ በዚህ ዕድሜ ጠገብ በሆነ ረጅም ታሪኳ ለኢትዮጵያና ለዓለም ሕዝብ እጅግ ብርቅና ድንቅ የሆኑ ዘመን የማይሽራቸው የቋንቋ፣ የሥዕል፣ የሥነ ሕንፃ፣ የመድኃኒት ቅመማ፣ የሥነፍጥረት፣ የቀን አቆጣጠር ቀመርን ያበረከተች ናት። ዛሬ የአገሪቱ የውጭ ምንዛሬ ማፍሪያ ከሆኑት አንዱ የሆነው የቱሪስት መስኅቦች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ውጤቶች ናቸው። የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያኖች፣ ጣና ሐይቅ ውስጥ የሚገኙ አድባራትና ገዳማት፣ መሰቅል (ደመራ)፣ ጥምቀት፣ የያሬድ ዝማሬና መሰሎቹ የቤተክርስቲያኑቱ አንጡራ ሀብቶች ናቸው።
ለግዕዝና ለአማርኛ ቋንቋ ድምፅ የሚወክሉ ፊደሎችን ከነሥርዓታቸው ቀርጻው ቋንቋውን የቃል ብቻ ሳይሆን፣ በጽሑፍም እንዲገለጽ ያደረገች ናት። ሌጦን ፍቀውና አለስልሰው ብራና ሠርተው መጽሐፍን ደጉሰው ታሪክ ለትውልድ እንዲተላለፍ ያደረገች ናት። ከመቃ ብዕር ሠርታ ጽሕፈትን ያስተማረች ናት። ሊቃውንቶቿ፣ሥራሥሩን ምሰው፣ ቅጠላቅጠሉን በጥሰው ቀጥቅጠውና ጨምቀው የሠሩት ቀለም እስካሁን በውበቱም ሆነ በጥራቱ ተወዳዳሪ ያልተገኘለትን ቀለም ያበረከተች ናት። ይህም በመሆኑ የሃይማኖቷ ሥርዓት ከሃይማኖትነት አልፎ የሕዝቡ ባሕልና የኢትዮጵያዊነት መልካም መታወቂ ለመሆን የበቃ ነው።
ቤተክርስቲያኗ እንደዛሬው ሕዝቡ ወንጀለኞችን የሚዳኝበት የወንጀለኛ መቅጫ እና የፍትሐብሔር ሕግ ሳይኖር፣ ፍትሐ-ነገሥትን ከዓለማዊና ከመንፈሣዊ ሕይዎት ጋር አጣጥማ ሕዝቡ ፍትሕን እንዲያገኝ የሕግን ሥርዓት በተጨባጭ ያሳየችና ያስተማረች ናት።
በሌላ በኩል የኦርቶዶክስ ሃይማኖት «አትግደል፣ አታመንዝር፤ አትስረቅ፣ አትዋሽ፣ በውሸት አትመስክር ፣ወዘተ» የሚለውን አምላካዊ ቃል አጥብቃ ስለምትከተል አማኟ ሰብአዊነትን፣ ሕጋዊነትን፣ ሰው አክባሪነትን፣ ሐቀኝነትን፣ ባህሉ እንዲሆን( ይህ ዘመናዊነት የተባለው አመለካከት ገብቶ ክሕደትና ቅጥፈት በአገሪቱ ሕዝብ ሥነልቦና ውስጥ ሁነኛ ቦታ እስኪይዝ ) ከፍተኛ ሚና የተጫዎተች ናት። ሕዝቡ መልካሙንና መጥፎውን፣ ደጉንና ክፉውን፣ ዓለማዊውንና መንፈሣዊውን ለይቶ እንዲያውቅ ያስተማረች ወንጌልን የሰበከችና ያስፋፋች በመሆኗ የአገርና የሕዝብ ባለውለታ ናት። ይህም ብቻ አይደለም፤ አገርን የሚወር፣ ሃይማኖትን የሚያስክድ፣ ነፃነትን የሚገፍ፣ ወራሪ ኃይል ሲነሣ፣ ሕዝቡን አስተባብራ በወራሪዎች ላይ ክንዱን በማንሳት ነፃነቱን እንዲጠብቅ፣ ሃይማኖቱን እንዲያጠና፣ የአገሩን አንድነት እንዲያስከብር የግንባር ቀደምትነት ሚና ስትጫዎት የኖረች ናት፤ ፍትሕ ሲጓደል፣ድሐ ሲበደል ነገሥታቱን የምትገስጽ፣ እንዲያም ሲል እንደዛሬው ሳይሆን፣ሕዝቡን አስተባብራ በክፉዎችና ባረመኔዎች ላይ የምታስነሳ የፍትሕ ተቋም ናት።
ይህን ሁሉ አጣምረን ስናይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክ ተዋህዶ ሃይማኖት ከእምነት አልፎ ባሕልና የመልካም ሥርዓት መሠረት ለመሆን የበቃ ነው። የሃይማኖቱ ሥርዓት እንግዳ መቀበልና ማክበርን፣ ባይተዋርን መርዳትና መንከባከብን፣ ለተራቡ መመገብን፣ ለታረዙ ማልበስን ለተጠሙ ማጠጣትን፣ ለታሰሩ ማስፈታትን የጽድቅና የመልካም ሥራ አርኣያ አድርጎ ስለሚወስድ የተለያዩ ሃይማኖቶች ወደ አገሪቱ ሲገቡ የተቃውሞ ድምፅ አልተሰማም። ለዚህም ነው የነበዩ መሐመድ ቤተሰቦች በቁራይሾች ሲሳደዱ፣ ነቢዩ «ወደ ኢትዮጵያ ሂዱ፣ከዚያ መልካም የክርስቲያን መንግሥት አለ» ብለው የላኩዋቸውና ከጥፋት ለመዳን የበቁት። ለዚህም ነቢዩ መሐመድ ባለማተብ (ሀቀኛ) ስለነበሩ፣ውለታን አዋቂ በመሆናቸው ማነኛውም የእስልምና ተከታይ ኢትዮጵያን እንዳይነካ ነቢያዊ ቃል የሰጡት። እስልምናም ሆነ ሌሎች ሃይማኖቶች በአገሪቱ ውስጥ በእንግድነት ሲገቡ ፣የአገሪቱና የሕዝቡ ሃይማኖት የሆነው የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት በማናቸውም ሃይማኖት ላይ ጥላቻ ሳያሳድር ጎን ለጎን መኖር የተቻለው፤ሃይማኖቱ እንግዳ ተቀባይ፣ የተቸገረ ረጅ፣ ላጣ መጽዋች ከመሆኑ የመነጨ ነው። ዕውነተኛው ታሪክ ይህ መሆኑ በግልጽ እየታየና እየታወቀ፣ በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት ተጽዕኖ ደርሶብናል፣ በአክራሪ ኦርቶዶክሶች ተበድለናል የሚሉ ወገኖች ፣ዛሬ ከሃይማኖት አልፎ የሕዝቡና የኢትዮጵያዊነት መታወቂያ፣ የሐቅ መግለጫ የሆነውን ማተብ እንቆርጣለን ሲሉ መደመጣቸው በማተቡና በሕዝቡ ባሕል፣ በማተቡና በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት መካከል ያለውን ቁርኝትና አንድነት በቅጡ ካለማወቅ ወይም «ሊበሏት ያሰቧትን አሞራ ጅግራናት ይሏታል» እንዲሉ፣ በዚህ አመካኝተው ይህኑ ከኦርቶዶክስ ሃይማኖት ጋር ቁርኝት አለው የሚባለውን የዐማራ ነገድ ነጥሎ ለመምታት የተሸረበ ታላቅ ሤራ መኖሩን የሚጠቁም እንደሆነ መገንዘብ አይገድም።
ሕዝቡ፣ በተለይም የኦርቶዶክስ ሃማኖት አማኙ፣ ማወቅ ያለበት፣ ባንዲራ ያንዲት አገር መለያ፣ መታወቂ እንደሆነ ሁሉ፣ ማተብም የኦርቶቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታይ መለያ፣ ከመንፈስ ቅዱስ ስለመወለድ ማረጋገጫ የሆነ ነው። ማተብ ካንገት መበጠስ የሚቻለው ኦርቶዶክሳውያንን በፍፁም ማጥፋት ሲቻል ብቻ ነው። ይህ እንዳይሆን ኦርቶዶክሳውያን ሃይማኖታዊ ሥርዓታቸው በሚያዘው መሠረት ሃይማኖተ ጥኑ፣ ለዕውነት ሟችና ተሟጋች ሆነው መቆም ይጠበቅባቸዋል።
ሌላው መታወቅ ያለበት የክርስትና ሃይማኖት ተከታይ ሰው አከረረ ወይም አክራሪ ነው የሚባለው፣ ይህን ዓለም ትቶ፣ለማያልፈውና ለወዲያኛው ዓለም ቤቱን ለመሥራት በፀሎትና በስግደት ተወስኖ ለመኖር ገዳም ሲገባነው። ሃይማኖቱ አትግደል ስለሚል፣መግደል ታላቅ ሐጢያት በመሆኑ፣ ክርስቲያን በመግደል አክራሪ ሊሆን አይችልም። ክርስቲያን የሆነ በአክራሪ ሃማኖተኛ ስም ሌሎችን መግደል ከጀመረ ያሰው ክርስቲያን ሳይሆን ሰይጣንና ዳቢሎስ የሰፈሩበት ወንጀለኛ እንጂ፤ ክርስቲያን ተብሎ ሊጠራ የማይችል ነው። ምክንያቱም መግደል በሃይማኖቱ የተከለከለ የዳቢሎስ ሥራ በመሆኑ ነው።
አክራሪነትን የምናየው ገድሎ ሃይማኖቱን በግድ ለሚያስፋፋውና ይህን በማድረጉ «በጀነት 73 ልጃገረዶች ይጠብቁሃል» እየተባለ፣ ከጠላቶቻቸው ባላይ ራሳቸውን እየጠሉ የአጥፍቶ መጥፋት ወንጀል የሚፈጽሙት ናቸው። ይህ ዛሬ በምንኖርበት የምሥራቁ ዓለም የተለመደ ክስተት ከመሆን አልፎ ፣ባህልም እየሆነ መጥቷል። ይህ ዓይነቱ ተግባር በኦርቶዶክስ ሃይማኖት ብቻ ሳይሆን፣ በሌሎችም የክርስትና ሃይማኖቶች የተወገዘና የተከለከለ ከመሆን ዘሎ፣ ወደ መንግሥተ ሰማያት በር የማያስገባ የዳቢሎስ ሥራ እንደሆነ በየጊዜው የሚሰበክ ነው።
ዛሬ በኢትዮጵያ ሕዝብ ጫንቃ ላይ ተንፈራጠው የተቀመጡ ዘመነኞች፣ ይህችን የታሪክ፣ የባህል፣የቋንቋ፣ የሥ-ነምግባር ፣ የፍትሕ፣ የአስተዳደር የሥነ-ሥዕል፣ የሥነ-ሕንፃ ጥበብ ባለቤትና አውራሽ የሆነችን ጥንታዊ ሃይማኖት ለማጥፋት የሚያደርጉት ዙሪያ ገብ አፍራሽ ጥረት ሃይማኖቱን ብቻ ሳይሆን፣ መልካም ባሕላችንም ጭምር ለማጥፋት ታጥቀው የተነሱ መሆኑን ስለሚያረጋግጥ፣ ከሁሉ በፊት የኦርቶዶክስ ሃይማኖት አማኙ ሃይማኖቴ ወይም ሞቴ ብሎ እምነቱን ለማስከበር አንድነቱን ማጠንከር ይጠበቅበታል። በሁለተኛ ደረጃ ሃይማኖቱ ከእምነት አልፎ ባህል ስለሆነ፣ የእኛነት መገለጫ ስለሆነ፣ ኢትዮጵያዊው ለማንነቱ መከበርና መጠበቅ በአንድነት እንዲሰለፍ ግድ ይለዋል። በዚህ ሂደት የቤተርስቲያኗ አባቶች የአቡነ ጴጥሮስንና የአቡነ ሚካኤልን አርኣያነት በመከተል ሕዝቡን ከነጣቂ ተኩላዎች መጠበቅ፣ ሃይማኖቷን ሊያጎድፍ የተዘጋጀውን ኃይል ሕዝቡ ተባብሮ እምነቱን እንዲጠብቅ ሳያሰልሱ ማስተማር ይጠበቅባቸዋል።
በሌላ በኩል ማተብ ይበጠስ የሚሉ ሰዎች ሐቅ ይጥፋ፣ ውሸት ይንገሥ፣ መታመን የፋራ ነው፣ አለመታመን ብልጥነት ነው(አራዳነት ነው)፣ ለዕውነት መቆም ኋላቀርነት ነው፣ ከሐሰት ጋር ማበር አዋቂነት ነው እያሉን መሆኑን ልብ ልንል ይገባል። አዎ !በሥልጣን ላይ ያሉት ሰዎች እከሌ ከእከሌ ሳይባል፣መሠረተ ባንዳ የባንዳ ልጆች ስለሆኑ ለነርሱ ሐቅ፣ዕውነት ምናቸውም አይደለም። የአገሪቱን የረጅም ጊዜ ታሪክ በመቶ ዓመት የገደቡት፣ የኢትዮጵያን ሕዝብ አንድነት የካዱት፣ ባንዲራችን ጨርቅ፣ ያሉት ዕውነትን የማያምኑ፣ ሐቅን የማይቀበሉ ከሐዲዎችና ሐሰተኞች ከመሆናቸው የመነጨ ነው። ማተብ ሲበጠስ ሃይማኖት የሚበጠስ ሳይሆን፤ቀድሞ ሊበጥስ የተነሳውን ብቻ ሳይሆን፣ያሰበውን የሚበጥስ ኃይል ከሕዝቡ ጋር ያለ መሆኑን ከጌታቸው ከዳቢሎሱ መለስ ዜናዊ እና ከአባ ጳውሎስ ሕልፈተ ሞት ትምህርት ሊወስዱ በተገባቸው ነበር። ዳሩ «ያደቆነ ሰይጣን ሳያቀስስ አይለቅም» ሆኖ ባቸው፣ የሃይማኖታችንና የእኛነታችን መገለጫ የሆነውን ማተባችን ሊቆርጡ አሰቡ። ሽፈራው በመቶ ሽዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ደም ከተጨማለቁት ሰዎች አንዱ ነው። ይህንም ማተብ የማስቆረጥ ምኞት መቃጣት እንጂ መማታት አይደለም ብለን ልንተረጉመው ፈጽሞ አይገባም። መቃጣት በራሱ ወንጀል ነው። ይህም ከወያኔ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን እስከ ወዲያኛው ለማጥፋት ለተያያዘው የጥፋት ዘመቻ አንዱ አካል መሆን አውቀን ጥፋቱ ዕውን ከመሆኑ በፊት ስለኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት የሚጮኸው ወገን ከወዲሁ መላ ማለት ይጠበቅበታል። የእጅን ለቆ መሟገት ሰማይን መቧጠጥ ነውና ማተባችን ከወዲሁ ጠበቅ ለማድረግ እንዘጋጅ!