Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

በኢትዮጵያችን በጥርስና በጥፍር የሚደረግ ትግል እንዴት ይቁም? (ግርማ ሠይፉ ማሩ)

$
0
0

ግርማ ሠይፉ ማሩ

girmaseifu32@yahoo.com

girmaseifu.blogspots.com

(ግርማ ሰይፉ)

(ግርማ ሰይፉ)

አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ/አንድነት አሳዛኙን የ2002 ምርጫ ውጤት ተከትሎ ፍራሽ አንጥፎ ኢህአዴግን ምርጫ ዘረፈ ከሚል መደበኛ ለቅሶ መውጣት አለብኝ ብሎ ቁርጠኛ ውሳኔ በመወሰን ውስጣችንን መፈተሸ ተገቢ አቅጣጫ ነው ብሎ በማመን በእኛ በኩልስ የነበረው ችግር ምንድነው? የሚለውን ጥያቄ አንስቶ ለመመለስ ከፍተኛ ጥረት አድርጎዋል፡፡ ይህ ነገሮች ወደ ውጭ ከማላከክ በዘለለ ሙሉ ቁጥጥር ባለን በራሳቸን ላይ የውስጥ ፍተሻ ማድረግ ጠቃሚና ተገቢ ነው ከሚል እምነት የመነጨ ነበር፡፡ ይህ ማለት ግን የውጭ ጫናዎች በተለይም የኢህአዴግ አፈና የነበራቸውን ተፅዕኖ አሳንሶ ማየት እና የኢህዴግን አፋኝነትን ዝቅ አድርጎ መመልከት አድርገው የሚውስዱ ሰዎች አይጠፉም፡፡ ዋናው ጉዳይ እና ቅድሚያ መሰጠት ያለበት የውሰጥ ጥንካሬና ድክመትን ማወቁ ነው የሚለው ነበር፡፡ በዚህም መነሻ አንድነት በተቃዋሚ ፓርቲዎች ታሪክ የመጀመሪያ የሆነውን የአምስት ዓመት ሰትራቴጂና ዕቅድ አዘጋጅቶ ለህዝብ ይፋ አድርጓል፡፡ ይህም ሆኖ ግን ሪፖርተርን የመሰሉ ጋዜጦች ተቃዋሚዎችን በጅምላ የሚመሩበት አቅጣጫ የሌላቸው አድርገው መፈረጃቸወን አላቆሙም፡፡ ሌሎችም ቢሆኑ ይህን ተከትለው ከማሰተጋባትና ተቃዋሚዎችን በጅምላ ከመክሰስ ወደኋላ አላሉም፡፡ ለማነኛውም ፍረጃው እንደተጠበቀ ሆኖ አንድነት ያለፉትን አራት ዓመታት ጎዞዉን ባስቀመጠው ሰትራቴጅና አምስት ዓመት ዕቅድ መሰረት አድርጎ ቀጥሏል፡፡ የእቅዱ ማጠቃለያ ዘመንም ከምርጫ ሁለት ሺ ሰባት ምርጫ ጋር የሚገጣጠም ነው፡፡

ይህ የአምስት ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ ወደፊት እንደሚካሄድ ታሳቢ ተደርጎ የመጨረሻው ዓመት ሊኖረን የሚገባው ዋነኛ ሰራ ምርጫን መሰረት ያደረገ እንደሚሆን ይታወቃል፡፡ ከዚህ አንፃር ገዢው ፓርቲ በጥርሱም በጥፍሩም ምርጫን ለማሸነፍ እየተንቀሳቀሰ ሲሆን እግረ መንገዱን ደግሞ የተቃዋሚዎችን በተለይም ደግም የአንድነትን ጥርስ ማውለቅና ጥፍር ማዶልደሙን ተያይዞታል፡፡ የጫወታው ህግ በጥርስም በጥፍርም መጫወት የሚፈቅድ ከሆነ ተወዳደሪዎች በተመጣጣኝ ጥርስም ጥፍርም ሊኖራቸው ይገባል፡፡ በቦክስ ጫወታ ደረጃ የሚወጣው በኪሎ ነው፡፡  አጫዋቹም/ዳኛውም ጫወታው ከመጀመሩ በፊት ቅድሚያ ሰጥቶ ማረጋገጥ ያለበት ይህን ጉዳይ ሁሉም ተወዳዳሪዎች ማሟላታቸውን ነው፡፡

 

አንድነት በዚህ ዓይነት የጥርስና የጥፍር ጫወታ ውስጥ ገዢው ፓርቲ ለማድረግ እንደሚፈልገው የተወዳደሪን ጥርስ ማርገፍና ጥፍር ማዶልዶም ተመጣጣኝ ምላሹ የገዢውን ፓርቲ ኢህአዴግ ጥርስ ማርገፍና ጥፍር ማዶልዶም መፍትሔ ይሆናል ብሎ አያምንም፡፡ ለውድድሩ ጥርስም ጥፍርም አስፈላጊ ከሆነ የአንድነት ፓርቲ ጥርስና ጥፍር እንዳይጎዳ መጠበቅ ቅድሚያ ይሰጠው ነው፡፡ ይህ ነው በቁጥጥራችን ስር የሚገኘው እና ዋና ትኩረታችን ሊወስድ የሚገባ እንዲሁም ተገቢ ጊዜ መስጠት አለብን የምንለው፡፡ የገዢውን ፓርቲ ጥርስ ለማርገፍና ጥፍርሩን ለማዶልዶም የምናባክነው ጊዜ የራሳችን በመጠበቅ ብሎም በቁርጠኝነት ባለማስደፈር ቢሆን የበለጠ አዋጭ ነው ብለን እናምናለን፡፡

በገዢው ፓርቲ መንገድ የምንሄድ ከሆነ ግን ወደፊት ለሚደረግ ውድድር በሁለቱም ወገን የሚኖሩ ተወዳደሪዎች በድድ እና በዱልዱም ጥፍር የሚወዳደሩ ይሆናሉ ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ የጫወታውን ህግ መለወጥ የሚጠይቅ ይሆናል፡፡ በዛሬው የጥርስና ጥፍር ተምሳሌት ዋነኛ ወካይ ባህሪዎች በሁለቱም ጎራ የተሰለፉ ኢትዮጵያዊያን መሆናቸውን ነው፡፡ ኢህአዴግ የተቃዋሚዎችን በተለይ የአንድነትን ጥርስና ጥፍር ላይ አደጋ አደረሰ ማለት በየደረጃው ያሉ የአንድነት አባላትና ደጋፊዎች ላይ የሚወስዳቸው ቅጥ ያጡ ህገወጥ እርምጃዎች ማለታቸን ነው፡፡ በአፀፋው አንድነት ይህን ያድርግ ሲባል ደግሞ በኢህአዴግ አባላትና ደጋፊዎች ላይ ቅጥ ያጡ ሕገ ወጥ እርምጃዎች እንውሰድ ማለት ነው፡፡ የእነዚህ ድምር ውጤት ኢትዮጵያዊያንን በፖለቲካ አቋማቸው ከመጉዳት የሚተናነስ አይደለም፡፡ በዚህ ሁኔታ በተጎዳ ህዝብ ውስጥ ወደፊትም ቢሆን የተሸለ እና የሰለጠነ አማራጭ ይዞ በፖለቲካ መወዳደር ይቻላል የሚል እምነት አይኖርም፡፡ ለዚህም ነው ጉልበታችንን የኢህአዴግ አባላትን ለመጉዳት ወይም ለመበቀል ሳይሆን የአንድነት አባላትና ደጋፊዎችን አቅም በማሳደግ የአይደፈሬነት ሰነልቦና ማዳበር መሆን ይኖርበታል የምንለው፡፡

በአንድነት በኩል የአባላቶቻችንን አቅም እናሳድጋለን ብለን ስንነሳ በዋነኝነት በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የሚደረግ ውድድር የሚመነጨው አንዱ ሀገር ወዳድ ሌላው ጠላት ነው ከሚል መንፈስ፣ ወይም በግል በደረሰብን በደል በቁጭትና ለበቀል መሆን እንደሌለበት በማሰተማር ነው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚለያዩት በሚመርጡት የርዕዮተ ዓለም፣ ይህን ለመተግበር በሚያወጡት ፖሊሲና የማስፈፀሚያ ስትራቴጂዎች መሆኑን በማስረዳት በማስከተለም እነዚህ ልዩነቶች ሀገርን ሊጎዱ እንደሚችሉ ለህዝብ በማሰየት ህዝብ ለሚሰጠው ብይን ተገዢ ለመሆን ዝግጁ ሲኮን ነው፡፡ ይህን ልዩነታችንን ከጠባብ ቡድናዊ/የፓርቲ ወይም ሌላ ስብስብ ፍላጎት ከመነሳት “ሀገር ወዳድ እና የሀገር ጠላት” በሚል እንድንፈራረጅ ምክንያት ከሆነ የጋራ ሀገር እንዲኖረን እየሰራን ነው ማለት አይቻልም፡፡ ኢትዮጵያ ሀገራችን ለሁሉም ፓርቲዎች የጋራ መኖሪያ ከመሆን በዘለለ የሁሉም ፓርቲዎች አባላት የሚኖሩባት ብቻ ሳትሆን ለልጅ ልጆች በተሻለ ደረጃ ልናስተላልፋት ትልቅ ራዕይ ሰንቀን የምንቀሳቀስ መሆኑ በሁሉም ዘንድ መታወቅ አለበት፡፡ ኢትዮጵያችን እንድትኖር እኛም በእርሷ እንድንኮራ በሁሉም ጎራ የተሰለፍን ኢትዮጵያዊያን ሁሉ ከፍተኛ ሀገራዊ ኃላፊነት እንዳለብን አውቀን መንቀሳቀስ ይኖርብናል፡፡

በኢህአዴግ በኩል የሚገኙ አባላት ብሎም ከፍተኛ አመራሮች ጭምር የተቃዋሚ ፓርቲዎችን “ኪራይ ሰብሳቢ” ከሚል ቅጥ አንባሩ ከጠፋው ፍረጃ በላይ ግልፅ ሆኖ በወጣ መልኩ በተቃዋሚ ጎራ የተሰለፍን ዜጎች በፍፁም ለሀገር ደንታ የሌለን አድርገው መሳል የተለመደና አስልቺ ፕሮፓጋንዳ ከሆነ ቆይቶዋል፡፡ ይህ በእውነቱ የኢህአዴግ በጥርስም በጥፍርም ለመጫወታ እንዲመቸው የሌላውን ጥርስ ማርገፍና ጥፍር ማዶልዶሚያ ስትራቴጂው ነው፡፡ ይህ መንገድ ግን ብዙ ርቀት የማያስኬድ ብቻ ሳይሆን ለሀገራችን ዘላቂ ሰላም የሚበጅ ነው የሚል እምነት የለንም፡፡

በተቃዋሚ መስመር የተሰለፍን ሰዎች መካከልም ኢህአዴግን መሳደብ እንደ ዋና የትግል ሰልት የተያዘ እስኪመስ ድረስ ጥግ እንደምንሄድ አምኖ መቀበል ስህተታችንን ለማረም ጉልዕ ድርሻ አለው፡፡ አንዳንዴም የሃሳብ ልዩነትን በሰለጠነ መንገድ ከመግለፅ ይልቅ ሰነምግባር በጎደለው ሁኔታ በተለይ የግለሰቦችን ስብዕና የሚነኩ አላስፈላጊ የቃላት ጫወታዎች እንዳሉ እንረዳለን፡፡ “ቅኔው ሲጣፋበት ቀረርቶ ሞላበት” የሚለው አባባል በሁለቱም ጎራ የመከራከሪያ ሃሰብ ድርቀት ምልክት ሊሆን ይቻላል፡፡ ይህንን ከመሰረቱ ለመቅረፍ ከላይ እንደተገለፀው አባላትን በስነምግባር መኮትኮት እና ዋነኛው የፓርቲዎች ልዩነት መሰረት መሆን የሚገባው የፖሊሲና የስትራቴጂ ጉዳዮች ላይ እንዲያተኩሩ ማድረግ ነው፡፡ ይህ ሲሆን በከፍተኛ ሀገራዊ መግባባት ሰሜት መንቀሳቀስ ይቻላል የሚል ፅኑ እምነት ይዳብራል፡፡

 


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>