Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

ስምንት ጠቃሚ ነጥቦች ከእስራኤላውያን -ክፍል 3 (ዮፍታሔ)

$
0
0

ዮፍታሔ

  1. የተጋረጠውን ፈተናና መፍትሔውን ዓለምአቀፋዊ ማድረግ።

Jewish+Ethiopians+Reunited+Families+Israel+o1h5oGhsf2Vlበጊዜው ይሆናል ተብሎ ሊታሰብ የማይችለው የእስራኤላውያን ወደ እስራኤል ተመልሶ መሰብሰብና ሕጋዊ የአገር ምስረታ ሊሳካ ከቻለባቸው ዋና ዋና ምክንያቶች አንዱ የነበረባቸውን ችግር፣ ወደ ፍልስጤም የመሰባሰባቸውንና አገር የመመሥረታቸውን እቅድ የነርሱ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የሌሎችም ሕዝቦች፣ መንግሥታትና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጉዳይና ኃላፊነትም እንዲሆን በማድረጋቸው ነው።

ይህ በተለያየ መንገድ ተከናውኗል። በመጀመሪያ ብዙኀኑ የአውሮፓ አገሮች ቀድሞውንም አይሁዳውያንን ከየከተሞቻቸው በማስወገድ በካምፕ ውስጥ ማስፈር የለመዱትና የሚፈልጉትም ስለነበረ ለአይሁዳውያን መሪዎች ይህንኑ የአውሮፓውያን ፍላጎት በመጠቀም ከየአገሮቻቸው ወጥተው በሌላ አገር ለብቻ ለመኖር እንዲፈቅዱላቸው ማሳመን ነበር። በዚህ አማካኝነት ከአይሁዳውያን ጋራ በተያያዘ በየአገሩ ይከሰት የነበረውን ግጭት፣ ይባክን የነበረውን ወጪ እና የንግድና የሀብት ፉክክር እንደሚያስወግዱ፤ የአይሁድ ነፃነት ለአውሮፓውያንም ነፃነት እንደሆነና አይሁድ በነፃነት ቢኖሩ ለዓለምና ለሰው ዘር በጠቅላላ ሊያበረክቱ የሚችሉትን አስተዋጽዖ በማጉላት እስራኤላውያንን ከየአገሩ አስወግዶ በራሳቸው አንድ አገር መሰብሰብ የሁሉም (በተለይም የሠለጠነው ዓለም) ኃላፊነት እንደሆነ ማሳመንና ሁሉም እንዲተባበር ማድረጋቸው ነው።

ቴዎዶር ሄርዝል ባሰራጨው መጽሐፉ የሚከተለው ይገኛል፦

“I consider the Jews question neither a social nor a religious one, even though it sometimes takes these and other forms. It is a national question, and to solve it we must first of all establish it as an international political problem to be discussed and settled by the civilized nations of the world in council”

ትርጉሙ፦ “ምንም እንኳን የአይሁድ ጥያቄ አንዳንዴ ማኅበራዊ፣ ሀይማኖታዊና ሌሎችንም ቅርጾች ቢወስድም እኔ የማየው እንደዚያ አይደለም። የአይሁድ ጥያቄ ብሔራዊ ጥያቄ ነው። እናም ችግሩን ለመፍታት በዓለም ጉባዔ በሠለጠኑት አገራት ውይይት ተደርጎበት እልባት ማግኘት ያለበት ዓለማቀፋዊ የፖለቲካ ችግር መሆኑን ከሁሉም አስቀድሞ ማረጋገጥ ያስፈልጋል”

የኢትዮጵያውያንም ጥያቄ ዛሬ አገር የማዳን ጥያቄ፤ ይህም ማለት ብሔራዊ ጥያቄ ከሆነ መቆየቱን ልብ ማለት ያስፈልጋል።

በሌላ በኩል ቴዎዶር ሄርዝል በዚህ ጥቅስ “civilized nations/ የሠለጠኑት አገራት” በማለት ለይቶ ኃያላኑን መንግሥታት መጥቀሱን እንመለከታለን። ይህ የሌላው ጠቃሚ ነጥብ አስኳል ስለሆነ በአእምሮአችን ሰሌዳ ይዘነው እንቆያለን።

በመጀመሪያው ጉባኤ ደግሞ ይህን ብሎ ነበር፦

The world will be liberated by our freedom, enriched by our wealth, magnified by our greatness. And whatever we attempt there for our own benefit will rebound mightily and beneficially to the good of all mankind”

ትርጉሙ፡ “በእኛ ነፃነት ዓለም ነፃነቱን ያገኛል፣ በሀብታችን ይበለጽጋል፣ በታላቅነታችን ይጎላል። እናም በዚያ (በእስራኤል) ለራሳችን ጥቅም ብለን የምንጣጣርበት ማንኛውም ነገር በሙሉ ኃይሉና ጠቃሚነቱ ተመልሶ ለመላው የሰው ዘር የሚበጅ ይሆናል።”

 

በሌላ በኩል በአይሁዳውያን ላይ ይደርስ የነበረውን ጭቆናና ጥቃት እየተከታተሉ ማጋለጥና የሁሉም አገሮች ሕዝቦች፣ መንግሥታትና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ከሰብዓዊ መብት አኳያ ኃላፊነት እንዳለባቸው ማስገንዘብና ይህ እንዲቆም መላው ዓለም የነርሱን እቅድ እንዲደግፈው ማድረግ ነው።

 

ሦስተኛው ደግሞ ባፈረጠሙት የገንዘብ፣ የድርጅትና የግንኙነት አቅማቸው ተጽእኖ የሚፈጥሩ መንግሥታትን፣ ድርጅቶችንና ግለሰቦችን በማግባባት የነርሱ ችግር ዓለማቀፋዊ ችግር እንደሆነ እንዲያንጸባርቁና የእስራኤልን መመሥረት እንዲደግፉ በማግባባት የተሠራው ሥራ ነው።

 

በዚህ ዓይነት በየደረጃው በመጀመሪያ እንግሊዝ እንድትቀበለው በማድረግ ቅኝ ገዢዋ (ሞግዚቷ) የተቀበለችውን ደግሞ ሌሎች አገሮችና የተባባሩት መንግሥታት ሊቀበሉት ችለዋል።

 

የደቡብ አፍሪካውያን ነፃነት እውን እንዲሆን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ካደረጉት ክንውኖች መካከል እነ ኦሊቨር ታምቦን (Oliver Tambo) የመሰሉ ቆራጥ ጀግኖች በውጭ እየተንቀሳቀሱ ትግሉን ከደቡብ አፍሪካ አውጥተው ዓለም አቀፋዊ ማድረግ መቻላቸው እንደሆነ በግልጽ ታይቷል። እነ ኦሊቨር ታምቦ በውጭ ያደረጉት ትግል ዳያስፖራው ምን ያህል አቅም እንዳለው በግልጽ ያሳየም ነበር። የደቡብ አፍሪካ የትግል ታሪክ ራሱን የቻለ አያሌ ትምህርቶች የሚገኝበት ነው። ወደፊት በሌላ ርእስ መመልከት ያስፈልጋል።

 

እኛስ በአገራችንና በወገናችን የተጋረጠውን ፈተና ዓለም-አቀፋዊ ማድረግ የማንችልበት ምክንያት ምንድን ነው? እኛስ በረሀብ፣ በድህነትና በኋላቀርነት ምክንያት ሌላውን ዓለም አላስመረርንም? እኛስ ለባጀታችን በቢሊየኖች የሚቆጠር ገንዘብ ከአደጉት አገሮች እየተደጎምን በመኖር ለጋሽ አገራትን አላስመረርንም? እኛስ አውሮፓን፣ ሰሜን አሜሪካን፣ አውስትራሊያንና እስያን በስደት አላጨናነቅንም? ዛሬ የኢትዮጵያውያን የሰብዓዊ መብት አያያዝ በኢትዮጵያና በአረብ አገራት የማያሳስበው የሰብዓዊ መብት ድርጅትና የዓለም መንግሥት ይገኛልን? በስደት በውኃ የሚወሰዱና በኮንቴይነር ሞተው የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ጉዳይ ራስ ምታት ያልሆነው የቅርብ ጎረቤትና የሩቅ መንግሥት ይኖራልን? የኢትዮጵያ ጉዳይ በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር፣ ደረጃውን ባልጠበቀ የሕፃናት የማደጎ ዝውውር (ሽያጭ) እና በውስጥ አካል ችርቻሮ ከእኛ አልፎ ከሕግና ከሞራል የተነሣ ችግሩ ያላንኳኳው መንግሥት ይኖራልን?

 

እኛስ ዘርን ማዕከል ባደረገ አፓርታይድን በሚያስንቅ አገዛዝ ሥር መሆናችን ለዓለም ይመቸዋልን? ዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ፣ ኃያላን መንግሥታትና ጎረቤት አገራት ከአሁኑ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጎን በመቆም ለጋራ መፍትሔ ካልተባበሩ ሕወኀት በኃይል ተገፍቶ በሚወድቅ ጊዜ ሊፈጥረው የሚችለው ያለመረጋጋት ለሽብርተኝነት ተጨማሪ እድል በመፍጠር ኃያላኑን መንግሥታትና መላውን ሰላም ወዳድ ዓለማቀፍ ማኅበረሰብ አያሳስባቸውምን?

 

ይህ ሁሉ የሚያሳስባቸው እንደሆነ ግልጽ ነው። በየጊዜው ከሚወጡት ሪፖርቶችና ዜናዎች የምንረዳውም ይህንኑ ነውና። ይህ ከሆነ ለኢትዮጵያውያን ትግሉንና መፍትሔውን ዓለማቀፋዊ ለማድረግ የሚያስችሉ ከላይ የተጠቀሱትና ሌሎችም በርካታ መንገዶች እንዳሉ ለመረዳት አያስቸግርም ማለት ነው። መፍትሔ ከተገኘ ዓለማቀፉ ማሕበረሰብ ለመተባበርም ወደኋላ እንደማይል ግልጽ ነው። ነገር ግን ይህ እንዲሆን ችግሩን ሊያስወግድና አስተማማኝ ሥርዓት ለመመሥረት የሚያስችል ተጨባጭ እቅድ ይዞ መቅረብ ይጠበቅብናል፤ ሳንሰለች ደጋግመን በር ማንኳኳት ይጠበቅብናል፤ የዓለማቁፉን ማኅበረሰብ የሚያረጋጋና ለቀጣዩ ጊዜ ዋስትና የሚሰጥ ጠንካራ ድርጅታዊ ብቃት ማሳየት ይጠበቅብናል፤ ገንዘብ እንዲኖረን ሁሉንም ዓይነት ጥረት ማድረግና ሲኖረን ገንዘባችንን በአግባቡ ልንጠቀምበት ይገባል። ይህን ማድረግ ስንችል ያለጥርጥር የኢትዮጵያ ጉዳይ ዓለማቀፋዊ ይሆናል። ያን ጊዜ ግፈኛውን አገዛዝ ማስወገድ ብቻ ሳይሆን አስተማማኝና ዘላቂ ሥርዓት በኢትዮጵያ መመሥረት አስቸጋሪ አይሆንም።

 

  1. የዳያስፖራው ወሳኝ ሚና

 

ከእስራኤል ታሪክ የምንማራቸው ብዙ አብይ ቁምነገሮች አሉ። ከነዚህ መካከል በአገር ላይ ለሚደረግ ማንኛውም በጎ ለውጥ ዳያስፖራው ወሳኝ ሚና ያለው መሆኑን በሚገባ መገንዘብ  ዋነኛው ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም።

 

እ. ኤ. አ 70 ዓ.ም በኋላ አብዛኛዎቹ አይሁድ (የዛሬዎቹ እስራኤላውያን) በሌሎች አገሮች ቢበተኑም ከዚያ በፊትም ሆነ በኋላ በየትኛውም ዘመን በፍልስጤም የሚኖሩ በሺዎች የሚቆጠሩ አይሁድ እንደነበሩ የሚታወቅ ነው። በውጭ ይኖሩ ከነበሩት አይሁድ ባልተናነሰ ብዙ ግፍ ይፈጸምባቸውም ነበረ። ይህ ሁሉ ሆኖ በፍልስጤም ይኖሩ የነበሩት አይሁድ በቅኝ ገዢዎቹ ላይ በማመጽና በመሳሰሉት አንዳንድ ሙከራዎች ከማድረግ ባለፈ መሠረታዊ ለውጥ የሚያመጣ ተጨባጭ ነገር ማድረግ አልቻሉም።  በግፍ አገዛዝ አፈናና ተጽእኖ ውስጥ የነበሩ ከመሆኑም በላይ ራሳቸውን ነፃ ለማውጣትና አስተማማኝ ሥርዓት ለመፍጠር የገንዘብ፣ የእውቀት፣ የአስፈላጊ ቁሳቁስና የድርጅት ብቃት ሊኖራቸው አይችልም። በአገራችን ባለፉት 23 ዓመታት የታዘብነው ከዚህ የተለየ አይደለም። ምክንያቱ ግልጽ ነው። ዳያስፖራው አይሁዳዊ ግን የድርጅት፣ የገንዘብ፣ የአስፈላጊው ቁሳቁስ፣ የእውቀትና እንደልቡ ተንቀሳቅሶ ከተለያዩ መንግሥታት፣ ዓለም-አቀፍ ድርጅቶችና ተጽእኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ጋር የመገናኘት እድሉና አቅም ነበረው። እነዚህን በመጠቀሙ ፈጽሞ ይሆናል ተብሎ ያልታሰበው በሚሊዮን የሚቆጠረው እስራኤላዊ መሰባሰብና የእስራኤል አገር ምሥረታ እውን ሊሆን መብቃት ብቻ ሳይሆን በኢኮኖሚ፣ በሳይንስ፣ በቴክኖሎጂ፣ በሚሊተሪ፣ በመረጃ፣ በሕክምና፣ በእርሻ ወዘተ በዓለም ጠንካራ ከሚባሉት ጥቂት አገሮች መካከል የምትመደብ አገር እንዲኖራቸው ለማድረግ በቅተዋል።

 

ወደራሳችን ስንመለስ የአገራችንን ችግር ያኔ ፍልስጤም በተለያዩ ቅኝ ገዥዎች ትገዛበት ከነበረው ዘመን ጋር የሚያመሳስለው ብዙ ነገር አለ። መልካቸው እኛኑ በሚመስሉ ሰዎች ምናልባትም ከቅኝ ገዢዎች በባሰ ሁኔታ ውስጥ የምንገኝ መሆኑ የአደባባይ ሚስጥር ነው። ይህ የመጀመሪያው የሚያመሳስለን ነው። አፈናው፣ እመቃው፣ አደንቁሮ መግዛቱ፣ ሕዝቡን ከማንኛውም ፓለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ተሳትፎ ማግለሉ ቅኝ ገዢዎችን ያስንቃልና። በሌላ በኩል ግን ከያኔዎቹ የእስራኤላውያን ጠላቶች (በፍልስጤም ሮማውያን፣ ቱርኮችና እንግሊዝ፤ በውጭ አብዛኛው አውሮፓና ይልቁንም ጀርመን) ጋራ ወያኔን ስናነጻጽረው በየትኛውም ማወዳደሪያ እዚህ ግባ የማይባል ደካማ አገዛዝ መሆኑን ልብ ማለት ያስፈልጋል። ይህ ለነፃነት ናፋቂው ሕዝብና ለተቃዋሚዎች ትልቅ ጥቅም ነው።

 

ሁለተኛው ተመሳሳይነት ልክ እንደያኔው አይሁዳውያን ሁሉ በኢትዮጵያ ያለውን አፈና በመሸሽና የተሻለ ኑሮ ፍለጋ በተለያዩ የዓለማችን አገሮች ተሰዶ የሚኖር በሚሊዮን የሚቆጠር ኢትዮጵያዊ ዳያስፖራ በውጭ የሚገኝ መሆኑ ነው። ልዩነት ከተባለ በእስራኤል ጉዳይ የዳያስፖራው ቁጥር ፍልስጤም ውስጥ ይኖር ከነበረው አይሁዳዊ በቁጥር የሚበልጥ ሲሆን በኢትዮጵያ ጉዳይ በአገር ውስጥ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ በዳያስፖራ ከሚኖረው በቁጥር የሚበልጥ መሆኑ ብቻ ነው። ይሁን እንጂ በጊዜው የነበረው አጠቃላይ አይሁዳዊ ዳያስፖራ ከኢትዮጵያዊው ዳያስፖራ በቁጥር ያለው ብልጫ ለውጥ ለማምጣት የሚያስፈልገውን ተጽእኖ በመፍጠር ደረጃ እዚህ ግባ የሚባል የጎላ የቁጥር ልዩነት አልነበረውም። ይልቁንም ኢትዮጵያዊው ዳያስፖራ (ልጆቹንም የትግሉ ተሳታፊ፤ የታሪኩ፣ የባሕሉና የቋንቋው ወራሽ በማድረግ በኩል የጎላ እንቅስቃሴ ማድረግ ያለበት መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ) በዘመኑ እንደነበረው ዳያስፖራ እስራኤላዊ አገሩን፣ ማንነቱን፣ ባሕሉን፣ ታሪኩን፣ ቋንቋውን ረስቶና በየሄደበት ተዋልዶና ተቀላቅሎ በአካል ብቻ ሳይሆን በመንፈስም ተበታትኖ የሚገኝ ያለመሆኑ የኢትዮጵያዊውን ዳያስፖራ አቅም ከእስራኤላውያኑ ዳያስፖራ ይልቅ የጠነከረና ውጤት ላይ ለመድረስም ትግሉን ከእስራኤላውያን የቀለለ ያደርገዋል። ሦስተኛው የሚያመሳስለን በውጭ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ የሁለተኛ ደረጃን ትምህርት ከማጠናቀቅ ጀምሮ እስከከፍተኛው የትምህርት እርከን ድረስ የተማረ፣ ለመረጃ፣ ለግንኙነትና ለቴክኖሎጂ ያኔ እስራኤላውያን ከነበሩበት ጊዜ በብዙ እጥፍ የተሻለ ደረጃ ላይ የሚገኝ መሆኑ ነው። ከፍተኛ የገንዘብም አቅም ያለው ስለመሆኑ ለቤተሰቦቹ ወደአገር ቤት በየዓመቱ የሚልከውን የገንዘብ መጠን (Remittance) ብቻ በማየት መገመት ይበቃል። አራተኛው እንደያኔው እስራኤላዊ ሁሉ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ዳያስፖራ በባእድ አገር መኖር፣ ባይተዋርነት፣ የዘር መድልኦ፣ ልጆቹን በማይቀበለው ባሕልና መጥፎ ልማድ ውስጥ ማሳደግ፣ በአገሩ ድህነትና ኋላቀርነት ምክንያት ዝቅ ተደርጎ መታየት ያንገሸገሸው፣ እልፍ ሲልም እንደያኔው እስራኤላዊ የባርነትን በሚመስል ሁኔታ በየአረብ አገራት በግርድናና ሰብአዊነትን በሚነኩ ሥራዎች የተሰማራና አልፎ ተርፎም በየሄደበት የሚታሰርና የሚገደል ነው። ከዚህ የበለጠ ማን ነፃነት እንዲናፍቀው ይጠበቃል!

 

ለዳያስፖራ አይሁዳውያን በነበረባቸው አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆነው ከምንም ተነሥተው (እንግሊዝን ከመሰለ ቅኝ ገዢ መዳፍ በመፈልቀቅ) አገርን የሚያህል ነገር ለመመሥረትና ብሎም ይህችን ትንሽ አገር በርካታ ጠላቶቿን የምትቋቋም ብቻ ሳትሆን ነፃ፣ ዲሞክራሲያዊትና የበለጸገች ለማድረግ ከቻሉ አገራችን ኢትዮጵያን ካለችበት ሁኔታ አውጥቶ ነፃ፣ ፍትሐዊትና የበለጸገች አገር ማድረግ ለዳያስፖራው ኢትዮጵያዊ በፍጹም አስቸጋሪ ሊሆን አይችልም። ለዚህም ነው በተለምዶ “ዳያስፖራው ነፃ አያወጣህም” የሚባለው አስተያየት ከሕወኀት ፕሮፖጋንዳ ወይም ከየዋሀን ተረት ተረትነት የማያልፈው።

 

ይሁን እንጂ ይህ እንዲሳካ አይሁድ በብቃት ያደረጉትና እኛ ሳንውል ሳናድር ማድረግ የሚጠበቅብን ነፃነት ፈላጊው ኢትዮጵያዊና ድርጅቶች በአንድ ጥላ ሥር የሚሰባሰቡበት ከሁሉም የተውጣጣ አንድ ጠንካራ ዓለም አቀፍ ድርጅት ማቋቋም ነው። በዚህ ድርጅት ጥላ ሥር ደግሞ ለአገር ግንባታ የሚሆኑ በተለያየ ዘርፍ ሥራ የሚሠሩ ከላይ የተጠቀሱትን የተለያዩ ተቋማት ማቋቋም ጊዜ ሳይሰጠው ሊከናወን የሚገባው ተግባር ነው። የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጅ መሆኑን ደጋግሞ ያስመሰከረው አክቲቪስት ታማኝ በየነ በቅርቡ ያቋቋመው የመረጃ ማዕከል አስፈላጊ ከሆኑት ተቋማት መካከል አንዱ ነው። ዳያስፖራው ይህን ማድረግ ይችላል። ይህን ማድረግ ሲችል ሕወኀትን ማስወገድ ብቻ ሳይሆን ተራራውን ወደጎን ሂድ ቢለው ይሄዳል። ሕወኀትን አስወግዶ በሁሉም የተሟላ አስተማማኝ ሥርዓት መመሥረትና አገራችንን በአጭር ጊዜ ከበለጸጉት አገሮች ተርታ ማሰለፍም ሕልም ብቻ አይሆንም። እውን ይሆናል።

 

በዚህ ወደ 4ኛው ነጥብ እናልፋለን።

 

(ይቀጥላል)

 

ኢትዮጵያ በቆራጥ ልጆቿ ሥራ ታፍራና ተከብራ ለዘለዓለም ትኖራለች!

 

 


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>