ማስታወሻ፡ ይህች ጽሁፍ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ከተከሰሰባቸው ሁለት መጣጥፎች አንደኛዋ ናት። በመጭው ወር በአሶሳ የሚደረገውን የብሄር ቀን ድራማ እሳቤ በማድረግ – በርካታ አንባብያን በጠየቁት መሰረት እነሆ በድጋሚ ለንባብ አቅርበናል።
— ክንፉ አሰፋ –
“እኛ ጭቁን ብሄረሰቦች ከዚህ ቀደም በየሰው ቤት ተቀጥረን የምንሰራ፣ አሽከሮች እየተባልን ነበር የኖርነው። አሁን ግን ይኸውና ህገ-መንግስታችን መብታችንን ሰጥቶናል… ኑሯችንም ተሻሽሎ ዛሬ ዘመናዊ ኑሮ እየኖርን ነው።”
እያለ የሚናገርን አንድ ጎልማሳ የቴሌቪዥኑ መስኮት ያሳያል። የደቡብ ቅላጼና ዘዬ ባለው አማርኛ ከደቡብ የመጣ ጎልማሳ ነው በቴሌቪዥን ቀርቦ መግለጫ እየሰጠ ያለው። ከአነጋገሩ በቀን ሶስቴ የሚበላ፣ የባቡር ሃዲድ እና የኤሌክትሪክ መስመር ገብቶለት፣ የስልክና የኢንተርኔት አገልግሎት ተጠቃሚም… ይመስላል።
የዚህ ምስኪን ሰው ገጽታ እና አለባበሱ የሚነግረን ግን ሌላ ነው። በኢህአዴግ ዘመን መብቱ እንደተከበረና ኑሮው እንደተሻሻለ የሚነግረን ይህ ሰው፣ መሰረታዊ የሆነውን የሰው ልጆችን የኑሮ ፍላጎት እንኳን አላሟላም። ለእግሩ ጫማ የለውም። በባዶ እግሩ ነው የቆመው። ሃፍረተ ስጋውን ከሸፈነለት ብጣቂ ጨርቅ በስተቀር ሰውነቱም እርቃኑን ነበር።
ለመገናኛ ብዙሃን ፍጆታ አነጋገሩ እንዲያሳምር ተነግሮት ሊሆን ይችላል – ንግግሩ ልክ መካከለኛ ገቢ ካላቸው የምዕራብ አውሮፓ ሃገሮች ተርታ የተሰለፈ ይመስላል። ይህ ደግሞ ገና የ’ትራንስፎርሜሽኑ’ ተስፋ እንጂ፤ ለውጡ በብሄር ብሄረሰቦቹ ላይ እንደማይታይ የቪድዮ ምስሎቹ ፍንትው አድርገው ነው የሚያሳዩት። ኢትዮጵያ በአምስት አመት ጊዜ ውስጥ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሃገሮች ተርታ ላይ እንደምትደርስ ኢህአዴግ ቃል ገብቷል። በአሁኑ ግዜ ሰባት በመቶ ብቻ የሆነው የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ብሄር ብሄረሰብ እና ሕዝብ በአምስት አመቱ እቅድ 80 በመቶ ይደርሳል ብለውናል። በእስር ያለው ጠንቋይ ታምራት ገለቴ ነግሯቸው ካልሆነ በስተቀር መቼም ይህንን ተረት ተረት በማህበራዊውም ሆነ በተፈጥሮ ሳይንስ ሊያረጋግጡልን እንደማይችሉ እርግጥ ነው። ከፈረሱ ጋሪው… እንዲሉ ከተግባሩ ወሬው፣ ከ’ህዳሴው ግድብ’ ስራም ሽልማቱ ቀድሞ መያዣ – መጨበጫው የጠፋ ነው የሚመስለው።
ከገጠር እየታፈሱ ለሚመጡት ለነዚህ ምስኪን ወገኖች የ ‘ብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች’ መብት ማለት በአመት አንዴ በጎዳና ላይ እየወጡ መጨፈር እና ያለፈውን ስርዓት ማውገዝ ብቻ ነው የሚመስለው። ጭፈራውና ውግዘቱ እንደ ጥምቀት በዓል ስለተለመደ የግድ መደረግ እንዳለበት ያመኑበትም ይመስላል።
የደርግ ስርዓት ሰዎች በባህላቸውና በቋንቋቸው እንዳይዘፍኑ ከልክሎ እንደነበር የሚጠቁም መረጃ የለም። ደርግ አስራ ሰባት አመት ገዛ፣ 20 አመት ሙሉ በብሄር ጭቆናው ሲወገዝ ኖረ። በባንዲራ ቀን ውግዘት፣ በከተሞች ቀን ውግዘት፣ በብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን ውግዘት፣ በግንቦት ሃያ ቀን ውግዘት…. በየሽልማቱ ስነ ስርዓት እና በየበዓላቱ ቀን ውግዘት….። የደርግ ሃጢያት መብዛት የነሱን ግፍ ይሸፍን ይመስል የኢህአዴግ በዓላት እና ውግዘቱ ከለት-ተለት ሲጨምር ብቻ ነው የምናየው – እንደ 11 በመቶው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚያ እድገት።
የዚህ ሳምንት ወሬ ደግሞ በመቀሌ ስለተካሄደው ስድስተኛው የ ‘ብሄር – ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ቀን’ ነው። የመከር ወቅት ስራቸውን እንዲያቆሙት ተደርገው፣ ከየክልሉ እየተጫኑ ለጭፈራ መቀሌ የገቡ አርሶአደሮች ቁጥር ቀላል አይደለም። በዲያጎን እየተፈለጉ የተለቀሙ ልማታዊ አርቲስቶች እና የመድረክ አስተዋዋቂዎችም በስፍራው ተገኝተዋል።
የእውቁ ኪነጥበብ ሰው – የኪሮስ አለማየሁ ልጅ ዛፉ ኪሮስ ‘አንበሳ ገዳይ’ በሚለው የትግርኛ ዘፈንዋ መድረኩን ይዛዋለች። በርከት ያለ ሰው መድረኩን ከቦት ይጨፍራል። አዳራሹም በ ‘ብሄር – ብሄረሰቦች እና ህዝቦች’ ተሞልቷል። መቀሌ፣ ኅዳር 27 ቀን 2004 ዓ.ም.።
የእለቱ የመድረክ አስተዋዋቂ ‘አንበሳ ገዳይ’ የሚለው የዛፉ ኪሮስ ዘፈን የተስማማው አይመስልም፤ አልተዋጠለትም። አልያም ዘፈኑን እዚያው መድረክ ላይ እንዲያስተባብል ተነግሮታል። ተራውን ጠብቆ ማይክራፎኑን ያዘ።
“ህገ መንግስታችን ለብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ብቻ ሳይሆን ለዱር እንስሶችም…”
ብሎ እየተናገረ እያለ እንደተለመደው መብራት ተቋረጠ።
በዚህ ‘ታላቅ’ ቀን መብራት መቆራረጡ ቢያበሳጭም፣ በእንግድነት ወደ መቀሌ የተጓዙት ‘ብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች’ ኤሌክትሪክ ምን እንደሆነ ስለማያውቁ አልደነቃቸውም – የሚያውቁት ደግሞ የለመዱት ስለሆነ – ለእነሱ እንግዳ ነገር አይደለም። ከቆይታ በኋላ ግን መብራት መጣ። ልማታዊው አርቲስትም ንግግሩን ቀጠለ።
“…ህገ መንግስታችን ለብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ብቻ ሳይሆን የዱር አራዊቶችንም መብት ስላስከበረ አንበሶች አሁን አይገደሉም።…”
በማለት የዘፈኑን መልእክት ለማስተባበል እና ጭብጡን ለብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ለማስረዳት ሞከረ። እዚህ ላይ የመድረክ አስተዋዋቂው እና ዘፋኝዋ እንዳልተግባቡ መገመት ይቻላል። ዛፉ ኪሮስ ዘፈንዋን በዚህ መድረክ ታቅርበው እንጂ መልእክቱ ላሁኑ ትውልድ ሳይሆን ምናልባት ‘ተራራ ላንቀጠቀጠው’ ለዚያኛው ሊሆን ይችላል ብሎ ማሰብ የተሳነው ይመስላል። ያ ቡድን የትኛውን ተራራ እንዳንቀጠቀጠ ባይገለጽልንም አሁን ያጠለለበት የለውጥ ደመና ግን በተራው እያንቀጠቀጠው ለመሆኑ ከሚያደርጋቸው ግራ ገብ ድርጊቶቹ መረዳት ይቻላል።
የሆነው ሆኖ በአሉ ለመቀሌ ህዝብ ልዩ ስሜት እንደሰጠው ይታያል። ይህ ህዝብ ከሌላው ኢትዮጵያዊ ወገኑ ተለይቶ፣ በእነ መለስ እና በረከት ካድሬዎች ታጥሮና ታፍኖ የሚገኝ ህዝብ ስለመሆኑ በርካታ መረጃዎች ይመሰክራሉ። ከስፍራው የሚደርሱን መረጃዎች እንደሚተቁሙት ከመንግስት ራዲዮ እና ቴሌቪዥን ውጭ ያሉ የመገናኛ ብዙሃንን በዚያ ክልል መጠቀም ራሱ እስከ ስድስት ወር የሚያሳስር ወንጀል ነው። ለ20 አመታት የታፈነ ህዝብ ከሌላው ወገኑ ጋር ተቀላቅሎ ፣ አብሮ ሲጨፍር የሚፈጥርበትን ስሜት መገመት አያደግትም። የደርግ ስርዓት የአሜሪካ እና የጀርመን ድምጽ ራዲዮን የትግራይ ህዝብ እንዳይሰማ አልከለከለም ነበር። ወያኔ ግን የትግራይ ህዝብን የመናገር ብቻ ሳይሆን የመስማት መብቱንም ጭምር ነው የነፈገው።
የሳተላይት ዲሽ ቴሌቪዥን ክልክል በሆነበት በዚያ ክልል የኢቲቪ አኬልዳማ ድራማ ይደገምልን ብሎ የትግራይ ህዝብ ቢጠይቅ ሊደንቀን አይገባም። ጆሮ ካሰለቸው የ’ህዳሴው ግድብ’ ወሬ እና እጅ እጅ ካሉት ከነ ሰራዊት ፍቅሬ አኬልዳማ ትንሽም ቢሆን ዘና ሳያደርጋቸው አልቀረም። የቴሌቪዥኑ መግቢያ ላይ ታዲያ ‘እንደምን አመሻችሁ ዲሽ የሌላችሁ” ብሎ ነው የሚጀምረው እየተባለም ይቀለዳል። ይህ ህዝብ በስሙ ሲነገድበት እና ከሌላው ወገኑ ጋር እንዲቃቃር ሲደረግ የትግራይ ኢሊቶች ዝም ማለታቸው እጅግ የሚያሳዝን ጉዳይ ነው።
ስለ ዱር አራዊት መብት እና ስለ አንበሳ መግደል ሲነሳ ትዝ ያለኝ የ1983ቱ የአምባሳደር ተስፋዬ ሃቢሶ ንግግር ነበር። ቻርተሩ ሲጸድቅ በነበረበት ጊዜ የከምባታና ሃድያን ጎሳ እወክላለሁ ብለው ወንበር ይዘው የነበሩት አቶ ተስፋዬ ሃቢሶ በወቅቱ ሲናገሩ።
“እኛ አናሳ ብሄር ብሄረሰቦች ዲሞክራሲ ብቻ ሳይሆን የሚያስፈልገን፣ እንደብርቅዬ እንስሣ እንክብካቤም ይገባናል።” ብለው ነበር።
ኢህዴግም በወቅቱ ለእነኚህ ‘አናሳ ጎሳዎች’ ልዩ እንክብካቤ እንደሚያደርግ ነበር ቃል የገባው።
አቶ ተስፋዬ ይህንን በተናገሩ ከአመታት በኋላ ታዲያ በሃዲያ እና ወላይታ ወገኖቻችን ላይ ጥይት እና ቦምብ እንደዝናብ ወረደባቸው። የ1993ቱ ብሄራዊ ምርጫ ተጭበርብሯል፣ ‘ድምጻችን ይከበር’ ብሎ የጮኸው የደቡብ ወገናችን በመለስ ወታደሮች ያለ ርህራሄ ነበር የተጨፈጨፈው። ልዩ እንክብካቤው እና ዴሞክራሲው ቀርቶ ይልቁንም የቆሙለት፣ በስሙም ስልጣን ያገኙበት፣ የራሳቸው ጎሳ በጥይት ሲቆላ አቶ ተስፋዬ ሃቢሶ ሹመታቸውን ላለማጣት ሲሉ ትንፍሽ አላሉም። እንዲያውም ዛሬም ስለ ‘ብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች’ መብት መከበር ከሚነግሩን እና የሌሎችን ጽሁፎች እየሰረቁ ከሚጽፉት ሰዎች አንዱ ናቸው።
ማሌሊቶቹ የሃገሪቱ የዘመናት ችግር የብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች መብት መነፈግ ነው ሲሉ ሰበኩ። የዚህ ችግር መፍቻ ቁልፍም በእጃቸው እንዳለ ነገሩን። በለስ ቀንቷቸው ምኒሊክ ቤተ መንግስት ሲገቡም ጫካ ውስጥ የጻፉትን ያንን የስታሊን ፍልስፍና ወደ ህገ-መንግስትነት ቀየሩት። መፍትሄ ያሉት የጎሳ ፖለቲካም በጥላቻና በበቀል ተተካ።
የማሌሊት ፍልስፍና ሲተገበር ታዲያ የመጀመርያ ሰለባ የሆነው አማራው ወገናችን ነበር። ለፖለቲካ ትርፍ ሲሉ እነ አቶ መለስ ዜናዊ ይዘውት የመጡት የጥላቻና የብቀላ ፖለቲካ እንደስካር ቶሎ በረደ እንጂ አካሄዱ እጅግ ዘግናኝ ነበር። በምስራቅ እና በምእራብ ኢትዮጵያ የአማራ ዘር ጨርሶ እንዲጠፋ ተዘምቶበት ነበር። የአማራን ዘር ጭካኔ በተሞላበት መንገድ ከተበቀሉት በኋላም ጽዋው ወደ አኙዋክ – ጋምቤላ ሄደ ፣ ከአኙዋክ ጭፍጨፋ በኋላ ደግሞ ዘመቻው በኦሮሞ ወገናችን ላይ ቀጠለ። በወላይታ ተከተለ፣ በኦጋዴን… ተዛመተ። የብሄር መብት እስከመገንጠልን ያስከበረው ህገ-መንግስት ጸድቆ በወረቀት ላይ ተቀምጧል። ይህንን መብት እየጠየቁ ያሉ ኢትዮጵያዊ ወገኖቻችንን ግን በዘራቸው ብቻ እየተመረጡ ማጥፋቱ ዛሬም በሚያሳዝን ሁኔታ እንደቀጠለ ነው።
እነ መለስ እነ በረከት ለዘመናት ተዋልዶና አብሮ ሲኖር የነበረን ህዝብ እንደ እንግሊዝ ከፋፍለህ ግዛው ቅኝ ስርዓት ለአገዛዝ እንዲያመቻቸው ህዝቡን እርስበርስ እያጋጩት ላለፉት 20 አመታት ለመቆየት ችለዋል። የዘር ፖለቲካው ምስጢር ይኸው ነው። ይህንን ባያደርጉ ኖሮ እስካሁን እንደ ጉም ተበትነው በጠፉ ነበር።
ወደመቀሌው በዓል እንመለስ።
ብሄር ብሄረሰቦቹ በመቀሌ ከተማ በቡድን በቡድን እየዘፈኑና እየጨፈሩ ይጓዛሉ። በተለይ ከደቡብ የመጡት ብሄር ብሄረሰቦች መብታቸው ተከብሮላቸው ወደ እድገት ጎዳና ከተጓዙ ከሃያ አመት በኋላም – ጥንታዊው የጋርዮሽ ስርዓት ከሚመስለው አለባበሳቸው እንኳን አልተቀየሩም።
መር ከሃያ አመት በፊት ቅጠል ለብሶ ይጨፍራል፣ ዛሬም ቅጠሉን አልቀየረም። ዳውሮ ድሮ ለእግሩ ጫማ አያደርግም ነበር አሁንም ጫማ የለውም። ከፊቾ ከ20 አመታት በፊት ከቀንድ የተሰራ የሙዚቃ መሳርያ ነበር የሚጠቀመው፣ አሁንም እሱኑ ይዞ ነው መቀሌ የመጣው…። ሁሉም አንዳች ለውጥ አይታይባቸውም። ታድያ የዚህ ሕዝብ ነጻነቱ፣ ለውጡ እና እድገቱ የቱ ላይ እንደሆነ ማን ይሆን የሚያስረዳን?
ህገ መንግስታዊ መብቴ ይከበርልኝ ባለ ብቻ ምላሹ የጥይት እና ቦንብ የሆነ ሕዝብ ቅጠል ለብሶ መጨፈሩ ምን ትርጉም ይሰጠናል? ይህ ነጻነቱን ያሳየናል እንዴ? ወይንስ ዛሬም የእግር ጫማ እንኳን አለማድረጉ እንደ ባህል ተቆጠረለት?
ጎንደሬው ሁመራ ላይ ለማረስ ፈቃድ ከመቀሌ መጠየቁ ነው የመብቱ መከበር? ወይንስ መቀሌ ላይ ሄዶ እስክስታ መምታት? አፋርና ኢሳ – ጉርጉራ ላይ ካላረሰ – አማራው ኦሮሞ ምድር ላይ እንዳይሰራ ከታገደ መብቱ ምኑ ላይ ነው?
ተረስቶ ይሆን ይሆናል እንጂ “የአክሱም ሃውልት ለወላይታው ምኑ ነው?…” ብለው ነበር አቶ መለስ። ታዲያ ዛሬ ምን አዲስ ነገር ተገኘ? በመቀሌ እየተደረገ ያለው የወላይታ ጭፈራስ ለአድዋው ምኑ ሊሆን ነው?
‘የኢትዮጵያ ጥንታዊ ስልጣኔ አንተን አይመለከትህም’ ተብሎ የነበረ የወላይታ ህዝብ ዛሬ የመለስን ፎቶ እና ‘ለልማት የተጋ ብቸኛው መሪ’ የሚል መፈክር ይዞ በመቀሌ እንዲሰለፍ ተደርጓል።
ደቡቡ የየራሱን የአፍ መፍቻ ቋንቋ እርግፍ አድርጎ ትቶ ኢህአዴግ በፈጠረለት ‘ወጋ ጎዳ’ እንዲናገር አቶ መለስ፡ ሲያስገድዱት እነሱ ግን ልጆቻቸውን በአለም አቀፍ ቋንቋ ብቻ እንዲማሩ ነው ያደረጉዋቸው። ዛሬ አቶ መለስ የነዚህን ጎሳዎች መብት መከበር ነው በመቀሌ እያበሰሩ ያሉት።
ይህ ህዝብ እንዲሁ ‘ብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች እየተባለ ሲቀለድበት እንደዋዛ ሃያ አመታት አለፉ።
በኢህአዴግ ዘመን ተወልዳ፣ ተምራ ዩኒቨርሲቲ የተመረቀች ወጣት አንድ አፍሪካ ሃገር አግኝቼ አወራኋት። ሜሮን ትባላለች። ስለ ብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች መብት እና ነጻነት ልትነግረኝ ሞከረች። ዩኒቨርሲቲ የሚያስገባ ውጤት ሳይኖራት ይልቁንም ኢህአዴግ በሰጣት እድል ዩኒቨርሲቲ ገብታ እንደተማረች ስለተነገራት የመለስ ዜናዊ አድናቂ ናት።
በወሬያችን መሃል በድንገት ‘ብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ማለት ምን ማለት ነው?’ ብዬ ጠየቅኳት። ጥያቄዬ ዱብዳ ነገር ሆነባት። ለሚለኒየም ግብ ሲባል ከተከፈቱት ዩኒቨርሲቲዎች ለስታስቲክስ ማሟያ የተመረቀች ስለመሆንዋ አመለካከትዋ፣ አስተሳሰብዋ እና ንግግርዋ ይገልጸዋል።
ጥያቄዬን ለመመለስ እንደከበዳት ተረዳሁ። ብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች የሚለውን ቃል የሜሮን ትውልድ ለሃያ አመታት ያለማቋረጥ ሲሰማው የነበረው ጉዳይ ነው። ለዚህ ትውልድ የብሄር መብት ማለት ግን በየአመቱ በጎዳና ላይ ከሚደረግ ጭፈራ ውጭ የሚሰጠው ሌላ ትርጉም ያለ አይመስለኝም።
ማን ነው ብሄር? ብሄረሰሰቦችስ የትኞቹ ናቸው? ህዝቦች የሚባሉትስ? ለዚህ ጥያቄ እንኳንና ሜሮን – ወያኔም መልሱ እንደሚቸግረው ይገባኛል።
ሜሮን ግን ኮስተር ብላ “ህገ መንግስቱ ነዋ!” አለችኝ።
ከዩኒቨርሲቲ ከተመረቀች ወጣት ቀርቶ ከአንደኛ ደረጃ ተማሪ እንኳን የማልጠብቀውን መልስ በማግኘቴ ባዝንም – በመልስዋ ግን ትንሽ ፈገግ ማለቴ አልቀረም።
ከአፍታ ቆይታ በኋላ – ብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ማለት ራሱ መለስ ዜናዊ ይመስለኛል ስትል ቀለደች ሜሮን።
እዚህ ላይ ልብ በሉ! ‘የህዳሴው ግድብ’ ሽልማት ስነ ስርዓት እየተደረገ በነበረበት ግዜ የግድቡ “ወደር የሌለው ተሸላሚ”ን ሰራዊት ፍቅሬ በቴሌቭዥን ሲያስተዋውቅ የሆነው ነገር ታወስውኝ። ነገሩ ጤነኛ አእምሮ ላለው ሰው እንግዳ ነበር።
ሰራዊት እና ሙሉአለም እየተቀባበሉ – እየደጋገሙም ‘የህዳሴው ግድብ ወደር የሌለው ተሸላሚ’ ይላሉ። ከብዙ ደቀቃ በኋላም የህዳሴው ግድብ ወደር የሌለው ተሸላሚ ይፋ ሆነ።
“ብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች!” ሲል ሰራዊት ፍቅሬ በሚለኒየም አዳራሽ ለተሰበሰበው ህዝብ አበሰረ።
ሸልማቱን የሚሰጠው አቶ መለስ ዜናዊ ፣ ሽልማቱን የሚቀበለው የኢህዴግ ተወካይ ሲሆን ፣ ይህም በተዘዋዋሪ አቶ መለስ ዜናዊ መሆኑ ነው።
ሜሮን ይህንን ማለትዋ ከሆነ – ጥያቄዬን በትክክል እንደመለሰችልኝ ተረዳሁ።
ሽልማቱ መጣም አልመጣ ለብሄር ብሄረሰቦቹ የሚፈይደው ነገር አይኖርም። በየአመቱ የሚደረገው የጎዳና ላይ ጭፈራ ግን የብሄረሰቦች መብት ብቻ ሳይሆን ግዴታቸውም ሆኗል ብለን እንደምድም።
የብሄር ነጻነት እስከ መጨፈር! ከዛ ካለፈ ግን የህይወት ዋጋም ያስከፍላል። ኦጋዴንን ያስተውሏል?
***