Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

ለኢትዮጵያ መምህራን የቀረበ ጥሪ ከ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር

$
0
0

አንዲት አገር ካለባት ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር ወጥታ በስልጣኔ ጎዳና እንድትጓዝ፣ ከሌሎች አገራት ጋር ተወዳድራ እንድታሸንፍ ትምህርት ቁልፍ ሚና ይጫወታል፡፡ ያለ መምህር ትምህርት ለውድድርና ለእድገት የሚያስችል አይሆንም፡፡ የዘመናዊ ትምህርት ከመጀመሩ አስቀድሞ ሀይማኖት ለሚያስተምሩት መምህራን ከፍተኛ ክብር ይሰጥ እንደነበር ታሪክ ያስረዳል፡፡ የዘመናዊ ትምህርት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶም ለመምህራን ከፍተኛ ክብር ይሰጥ እንደነበር በቂ ማስረጃዎች አሉ፡፡ በዚህም ምክንያት አገራችን በርካታ ምሁራንን ማፍራት ችላለች፡፡ በመሆኑም ኢትዮጵያ ውስጥ በተደረጉት የለውጥ እንቅስቃሴዎች መምህራንና የቀረጹዋቸው ተማሪዎች ቀዳሚውን ሚና ሲወጡ ታይተዋል፡፡
semayawi

በአንጻሩ በዚህ ትምህርት ቁልፍ መሳሪያ በመሆነበት የሉላዊነት ዘመን አገራችን በትምህርት ዘርፍ ከፍተኛ ውድቀት ደርሶባታል፡፡ ይህም የሆነው ለመምህራን የሚገባቸውን ትኩረትና ክብር ባለማግኘታቸው ነው፡፡ ባለፉት 24 አመታት ከመምህራን ይልቅ ካድሬዎች የህጻናትን አዕምሮ በፕሮፖጋንዳ እንዲበርዙ ሆን ተብሎ ተሰርቶበታል፡፡ መምህራን በነጻነት እንዳያስተምሩ በካድሬዎች ጣልቃ ገብነት ተማርረዋል፡፡ የመምህራን ማህበራት በገዥው ፓርቲ እጅ በመውደቃቸው መብቶቻቸውና ጥቅሞቻቸው ሊከበር አልቻለም፡፡ በየ መድረኩ በሚያነሱዋቸው ጥያቄዎች ከስራቸው ይፈናቀላሉ፡፡ ኑሯቸው የምትሸንፈውን አነስተኛ ደሞዛቸውን ይቀጣሉ፡፡ ይታሰራሉ፡፡ የገዥው ፓርቲ አባል ባለመሆናቸው ሁሌም በጥርጣሬ አይን ከመታየታቸው ባለፈ የተለያዩ እርምጃዎች ይወሰድባቸዋል፡፡

የኢትዮጵያ መምህራን ቀጣዩን ትውልድ ለመቅረጽ ከመጣርና በኢትዮጵያውያን ላይ የሚደርሰው በደል ላይ ቀዳሚነቱን ወስዶ የትግሉ አካል እንዳይሆን ስርዓቱ ከፍተኛ ጫና እያሳደረባቸው ይገኛል፡፡ ይህም ሆኖ የራሱንና የሌሎቹን ድምጽ በማሰማት የቻለውን ያህል እያደረገ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ በየ ዕለቱ ከሚታሰሩት፣ ከስራቸው ከሚባረሩትና ሌሎች የስርዓቱ አፈናዎች ከሚደርስባቸው ባሻገር አድማጭ ሲያጣ ራሱን መስዋዕት ያደረገው መምህር የኔሰው ገብሬን መጥቀስ በቂ ነው፡፡ ስርዓቱ በመምህራን ላይ ከሚያደርገው ከፍተኛ አፈና አንጻር ያልተነገረላቸው በርካታ መስዋዕቶች እንዳሉም መገመት ይቻላል፡፡

በአሁኑ ወቅት በመምህራን ላይ የተጫነው ጭቆና የአጠቃላይ አገሪቱ ውስጥ ያለው ጭቆና አንድ አካል ነው፡፡ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ነጻ ካልወጡ መምህራን ብቻቸውን ነጻ መሆን አይቻላቸውም፡፡ ነገር ግን ትግሉን በቀዳሚነት የመምራት የሙያና የሞራል ግዴታ እንዲሁም አጋጣሚ እንዳላቸው ግልጽ ነው፡፡ በመምህራን ላይ የተጫነውን ጭቆና ከድሮው የተለየ የሚያደርገው መምህራን ህዝብ ላይ እየደረሰ ለሚገኘው መከራ ይቅርና ለራሳቸውም እንዳይጮሁ፣ በራሳቸው የእለት ተእለት ችግሮችና ፍርሃት ተጠምደው እጥፍ ድርብ ጫና የሚፈጸምባቸው መሆኑ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት መምህራን የሚገባቸውን ሚና እንዳይወጡ ተደርገዋል፡፡

መምህራን ያልቀረጹት ትውልድ ለራሱም ሆነ ለአገሩ ነጻነትና ክብር ሊቆም አይችልም፡፡ ባለፉት 24 አመታት በመምህራንና ትምህርት ላይ የተፈጸመው በደልም አሁን ላለንበት ጭቆና የራሱን ሚና ተጫውቷል፡፡ በመሆኑም ለራሱም ሆነ በቀሪው ማህበረሰብ በግንባር ቀደምነት የሚታገል ትውልድ ለመፍጠር የመምህራን ሚና ከመቼውም ጊዜ በላይ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል፡፡

በአሁኑ ወቅት የ9ኙ ፓርቲዎች የአንድ ወር መርሃ ግብር ቀርጸው እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ፡፡ ምንም እንኳ አፈናው እየበረታ ቢሆንም መምህራን ቀዳሚ ሚና ሊወጡ እንደሚችሉ እናምናለን፡፡ በመሆኑም ራሳቸውን ነጻ አውጥተው ለህዝብ መብትና ለአገር ክብር ለመቆም ትግሉን እንድትቀላቀሉ ጥሪ እናቀርባለን፡፡ መምህራን የአንድ አገር ህዝብ ላይ የሚፈጸመውን በደል ለማጋለጥና ህዝቡንም ለማንቃት ካላቸው ተደራሽነት እንዲሁም የሙያ ግዴታ ግንባር ቀደም ሚና በመጫወት ታሪካዊ ግዴታችሁን እንድትወጡ ጥሪ እናደርጋለን፡፡ በተለይ ህዳር 27/28 በተጠራው የአዳር ሰልፍ በመሳተፍና በሙያም ሆነ በሌሎች አጋጣሚዎች የምታገኙዋቸውን ኢትዮጵያውያን በመቀስቀስ ጥሪውን እንዲቀላቀለሉ በማድረግ ግንባር ቀደሙን ሚና እንድትወጡ ጥሪ እናቀርባለን፡፡ ይህ ቀን ኢትጵያውያን ከፍርሃት ወጥተን ድምጻችን በጋራ የምናሰማበት እንዲሆን ቀዳሚ ሚና እንድምትወጡም እምነታችን ነው፡፡


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>