ክፍል አንድ
1 . መግቢያ
ህወሃት ኢህአዴግ ባለፉት ኢትዮጵያን በመራባቸዉ አመታት አገሪቷን እና ህዝቦቿን በግፍ ሲመራ ለመቆየቱ ምስክሮቹም ተጠቂዎቹም እኛዉ ነን። ለዚህ ጥቃታችን መፍትሔ ለመፈለግ የተደረጉ ትግሎችን ከግብ ለማድረስ የተደረገዉ እንቅስቃሴ ውጤታማ አልነበረም።ነገር ግን ምንም አስተዋጽኦ አላደረገም ብዮ አልደመድምም ። ምክንያቱም የህወሃት ኢህአዴግ ባህሪን ለማጋለጥ ያደረገዉ አስተዋጽኦ ቀላል አይደለምና ።
ለትግሉ ከግብ አለመድረስ ምክንያቶች ደግሞ የትግሎቹ መበታተን ፣ግቦቹ ግልጽነት የጎደላቸዉ መሆን፣በጋራ ሊያታግሉ የሚችሉና ግልጽ አላማ ያላቸዉ አለመሆናቸዉ ፣ አካባቢያዊና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎችን ከግንዛቤ ያላስገቡ መሆናቸዉ፣የህወሃት ኢህአዴግን የጭካኔ አቅም የሚመጥን ትግል አለመኖሩ፣በህወሃት የተሰጠንን የመለያየት የቤትስራ ሰርተን ባለመጨረሳችን፣ህወሃትን እንደ አገር ነጻ አውጭ ሃይል መቀበላችን ፣አንደኛዉ ሲጠቃ ነግ በኔ አለማለታችን፣የዉጭ ሃይሎች እንዲረዱን በአብዛኛዉ ጊዜ መጠበቅና ሌሎችም ።
በተለይም ህወሃት እንድንከፋፈል የሚያቀርብልንን ግብዣ በቸልተኝነት፣በአርቆ አስተዋይነት ማነስ ፣በራስ ወዳድነት፣ከሃገር ይልቅ ለግልና ለቡድን እንዲሁም ለፓርቲ እውቅና መሯሯጥ ፣ሰፊ ልዩነቶችን የሚፈጥሩ የፖለቲካና የማህበራዊ አስተሳሰቦችን ይዞ መቅረብና ሌሎችም ይገኙበታል። በእነዚህ ምክንያቶች ለአመታት ተከፋፍለን በመኖራችን ምክንያት ዛሬ ኢትዮጵያዉያን ለለየለት ጭቆና ተዳርገናል።
በተጨማሪም የውጭ ሃይሎች በህወሃት ኢህአዴግ ላይ ያላቸዉ ግንዛቤ የታሳሳተ መሆኑና አዉቀዉም እነሱ የሚያቀርቡትን ጊዜያዊና ዘለቀታዊ ጥቅሞቻቸዉን በሙሉ ፍላጎትና ተነሳሽነት የማስፈጸሙን ስራ ህወሃት በተገቢዉ መልኩ ማከናወኑ ሌላዉ ጉዳይ ነዉ። በተቃዋሚዉ በኩል የተቀነባበረ የዲፕሎማሲ ስራ አለመሰራቱና በቂና የተደራጀ ሃይል አለመገኘቱም ሌላዉ ችግር እንደሚሆን ግልጽ ነዉ።
የኢትዮጵያና የህዝቦቿ ችግር መፍትሔ ያለዉ በራሳችን በኢትዮጵያዉያን እጅ እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለኝም ። ስለሆነም ግዜዉ አሁንም አረፈደም።አሁንም ግዜ ሳይረዝም ፤በፈጠነ ሁኔታ ፤ ግልጽ የሆኑ አቋሞችን ወስዶ ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ መግባት ከሁሉም አገር ወዳድ ኢትዮጵያዉያን በሙሉ የሚጠበቅ ነዉ ።ለዚህም ይረዳ ዘንድ በየትኛዉም የትግል መስመር ያሉ ኢትዮጵያዉያን ልዩነቶችን ማጥበብ መቻልና በዉይይት ወደ መፍትሄ መምጣት ይጠበቅብናል፤ ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ መግባትም አብይ ጉዳይ ነዉ ብየ አምናለሁ።
2. ዋና ዋና የትግል ግብአቶች
ለመግቢያ ያህል ከላይ የተጠቀሱትን ካልኩኝ ይበቃል። አሁን ወደ ዋናዉ የርዕሴ ጉዳይ ልግባና ጥቂት የመነጋገሪያና የመፍትሄ ሃሳቦችን አቀርባለሁ።እንደኔ ከሆነ ወይም እንደኔ አስተሳሰብ ሁለት ትልልቅ ጉዳዮች የትግሉን አቅጣጫና ዉጤታማነት የያዙ ጉዳዮች ናቸዉ ብዮ አምናለሁ ።እነሱም የተቀዋሚዉ ሃይል መሰባሰብና ሁሉንም የህወሃት ኢህአዲግን መዋቅሮች በጠላትነት መፈረጅ ስህተት መሆኑ።
ሀ/ የተቀዋሚዉ ሃይል መሰባሰብ መቻል
የተቀዋሚዉ ሃይል መበታተን ከምንም በላይ የጎዳዉ እራሱን ተቃዋሚዉን ሲሆን በተቃራነዉ ህወሃትን በከፍተኛ ሁኔታ ጠቅሞታል ። በሚለያዩን ጉዳዮች ላይ ዉስጥ ውስጡ ከመተማማት ይልቅ፤ቡድናዊና ጎሳዊ ከሆኑ ጉዳዮች በዘለለ አገራዊ ይዘት ያላቸዉን ጉዳዮች በማንሳት ለትዉልድ ጭምር በማሰብ መነጋገር፣ መፍትሔ ማስቀመጥና መተግበር ይጠበቅብናል።ይህም የመለያየቱ የቤት ስራ አልቆና ጊዜዉ ያለፈበት መንገድ መሆኑንም ለጋራ ጠላታችን በማሳየት ወደ ስራ መግባት ፤የወደፊቱንም ችግሮች እየፈታናቸዉ እንድንሄድ ያስችሉናል።
ለ/ የህወሃት ኢህአዴግን መዋቅሮች በሙሉ በጠላትነት መፈረጅ ስህተት መሆኑ
አሁን ኢትዮጵያ ካለችበት ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር ትግሉ ከብዙ ሃይሎች ጋር የሚደረግ ትግል ነዉ ብዬ አላምንም። ምክንያቱም አሁን ኢትዮጵያ የምትተዳደረዉ በጥቂት የህወሃት ሃይሎች እና በየክልሉ ካስቀመጣቸዉ ተወካዮቻቸዉ ጋር እና የጥቅም ተጋሪዎቻቸዉ ጋር ነዉ። ስለሆነም ትግሉን ዉጤታማ ለማድረግ ያስችል ዘንድ ነጻ ሊወጡ የሚገባቸዉን ሕዝቦች ፣ፓርቲዎች፣ የስልጣን ተዋርዶችን፣አደረጃጀቶችንና የገዥዉ የህወሃት የጭቆና ቀንበር የያዛቸዉን ተቋማት በሙሉ ለይቶ ከህወሃት ጭቆና ነጻ ማዉጣት ይጠበቅብናል።
በዚህም መሰረት ለዛሬ በዚህ በሁለተኛ ደረጃ የያዝኩትን ሃሳብ/ለ/ ወይም ጉዳይ ትኩረት እሰጠዋለሁ ። የጽሁፉም ዓላማ ህወሃትን እንዴት መነጠል ይቻላል በሚለዉ ላይ ያተኩራል።
2. 1. ነጻ ሊወጡ የሚገባቸዉ የህወሃት መዋቅሮች እና ሃይሎች
ሀ/ ነጻ የሚወጡ ህዝቦችን መለየትና የትግሉ አካል ማድረግ
ህወሃት በታሪክ አጋጣሚ እዚህ ለመድረሱ መነሻ ያደረገዉ ምክንያት የትግራይ ህዝብ ተጨቁኗል መባሉና ለትግላቸዉም ጭቆናዉን መነሻ አድርገዉት መታገላቸዉ ነበር።ነገር ግን በእዉነቱ ከሆነ የትግራይ ህዝብ በደርግ ዘመን ተፈጸመበት ከሚባለዉ ጭቆና በበለጠ ለአለፉት ሰላሳ ዘጠኝ አመታት ህዝቡ በህወሃት መገደሉን፣መታሰሩን፣መሰደዱን፣ በስቃይ ላይ መኖሩን እራሱ የትግራይ ህዝብ ምስክር ነዉ።ስለዚህ ይኸንን የሚያዉቅ ሁሉ ይህንን ህዝብ በየትኛዉም መንገድ ከህወሃት ጭቆና ማላቀቅ ችላ የሚባል ጉዳይ አይደለም ። የትግራይ ህዝብ የህወሃትን የጭካኔ በትር ከሌላዉ ኢትዮጵያዊ በላይ ለ39 ዓመታት ጠንቅቆ ያዉቀዋል።ስለዚህ ይኸንን ህዝብ በተለየ መልኩ ነጻ ማዉጣት ህወሃት መሸሸጊያ እንዳያገኝ ስለሚያደርገዉና ለህዝቡም እረፍት ስለሆነ ትኩረት ሊሰጠዉ ይገባል እላለሁ።ይህ ማለት የሌሎች ህዝቦች ጭቆና መጠን ለማሳነስ ሳይሆን ህወሃት ከለላ አድርጎና በስሙ የሚጠቀምበት ህዝብ ስለሆነም ጭምር ነዉ ። የሌሎች የአገራችን ህዝቦች ነጻ መዉጣት በህወሃት ዉክልና ተሰጥቶአቸዉ ህዝባቸዉን የሚጨቁኑ ጥቂት ሃይሎች ወይም የኢህአዴግ አካል ፓርቲዎችና ሌሎች ደጋፊ ተብለዉ ህወሃት የፈጠራቸቸዉ ፓርቲዎችን ከህወሃት ጭቆና ነጻ ለማዉጣት በሚደረገዉ ትግል ህዝቡን ነጻ ማዉጣት ያስችላል ብዮ አምናለሁ ።
ለ/ የኢህአዴግ አካል ፓርቲዎችንና ደጋፊ ፓርቲዎችን ነጻ ለማዉጣት መጣርና የትግሉ አካል ማድረግ
ሌሎች ከህወሃት ዉጭ ያሉ የኢህአዴግ አካል ፓርቲዎችንና ደጋፊ ፓርቲዎችን ከህወሃት ጭቆናና የበላይነት ነጻ ለማዉጣት ትልቅ እንቅስቃሴን የሚጠይቅ ቢሆንም የህወሃትን የበላይነት ለመሸርሸር ትልቅ ግብአት ሆኖ ስለሚያገለግል እዚህ ላይ ትልቅ ትኩረት ሊሰጠዉ ይገባል እላለሁ ። በእነዚህ ድርጅቶች ዉስጥ ያሉ አባላቶች ህወሃት በህዝቦቻቸዉ ላይ የሚፈጽመዉን ልክ ያጣ ግፍ እንዲያንገሸግሻቸዉ በማድረግ፤ ከዉስጥ ትግላቸዉን እንዲያቀጣጥሉ በማነሳሳት፤ ወደ ነጻነት የትግሉ ጎራ እንዲቀላቀሉ እድል በመስጠትና ድጋፍ በማድረግ፤ የትግሉን መፋጠን እንዲያግዙ በማድረግ ህወሃትን እርቃኑን እንዲቀር ማድረግ ይቻላል። ስለዚህ በጅምላ እነዚህን በጠላትነት ከመፈረጅ ይልቅ የነጻ መዉጣቱን ትግል እንዲቀላቀሉ ማድረግ ይጠበቅብናል።በዚህም ምክንያት በስራቸዉ ያሉ ህዝቦችን ነጻ ለማዉጣት ትልቅ መሰረት ይጥላል።
ሐ/ የመከላከያና የፖሊስ ሰራዊትን ነጻ ለማዉጣት መጣርና የትግሉ አካል ማድረግ
የኢትዮጵያ የመከላከያና የፖሊስ ሰራዊት የህወሃት የገዥ መደብ የብዝበዛና የጭቆና መሳሪያ ሆኖ እያገለገለ ስለመሆኑ ብዙዎቹ እያወቁ መሆኑና የተወሰኑ የሰራዊቱ አባላት ከግንዛቤ እጥረት የተነሳ ይህንን የጭቆና መሳሪያነታቸዉን የማያዉቁም እንዳሉ አንዳንድ ግንዛቤዎች አሉ ። ይሁንና በህወሃት የዘር ጭቆና እየተማረሩ በስቃይና በንዴት የነጻነቱን ትግል ጎራ ለመቀላቀል የሚፈልጉ ቁጥራቸዉ ቀላል እንደማይሆን ምንም ጥርጥር የለም። ይህንን ሰራዊት ነጻ ለማዉጣት ጥረት ማድረግ፣ ከለላ እንዲያገኝ መፍትሄ መፈለጉና በጠላትነት አለመፈረጁ ትልቅ የትግሉ ዉጤታማነት ግብአት ነዉና በዚህ ዙሪያ ትልቅ ስራ ሊሰራ ይገባል።
ይህ ጽሁፍ ተከታታይ በመሆኑ በሚቀጥሉት ጽሁፎች ላይ ሌሎች አስፈላጊ የትግል ግበአቶችንና የትግበራ ግብአቶችን እጠቁማለሁ።
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ!
↧
ጠቃሚ የትግል ግብአቶች
↧