Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

“ኢሕአዴግ ፖለቲካውን የሚመራው በዕዝ ነው እንጂ በሃሳብ የበላይነት አይደለም”–አቶ ሃብታሙ አያሌው

$
0
0

አቶ ሃብታሙ አያሌው የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ብሄራዊ ምክር ቤት አባልና ምክትል የህዝብ ግኑኝነት ሃላፊ ነው፡፡ወደ ፖለቲካው ዓለም የገባው በኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ሰንበት ትምህርት ቤት በማስተማር አገልግሎት ተጠምዶ ሳለ አንድ ችግር ይነሳና ቤተክርስቲያኑ በሚገኝበት ቀበሌ በአስተዳደሩ ይጠራል፡፡በቀበሌው የተገኘው ሃብታሙ የተፈጠረውን ችግር ያብራራበት መንገድ በአሁኑ ሰዓት ከፍተኛ የኢህአዴግ ባለስልጣን የሆኑ ግለሰብን ይማርካል፡፡ግለሰቡ ከስብሰባው በኋላ ሃብታሙን በመቅረብ በቅርቡ የሚመሰረት አንድ ነጻ የወጣት ማህበር ስላለ በዚያ የምስረታ በዓል ላይ እንዲገኝ ያግባባዋል፡፡መንፈሳዊው ሃብታሙም በህይወቱ ለመጀመሪያ ጊዜ አጀንዳውን መንፈሳዊ ህይወት ባላደረገ ማህበር ምስረታ ላይ ይታደማል፣በዚያው ዕለትም ስሙ ተጠቁሞ ይመረጣል፡፡ ዳዊት ሰለሞን ከገዢው ፓርቲ ጋር በቅርበት በመስራት በአሁኑ ሰዓት ገዢውን ፓርቲ እየታገለ የሚገኘውን ሃብታሙን በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዩች አነጋግሮታል፡፡
habtamu
ላይፍ — አምላክን ከማገልገል ህይወት ወደ ፖለቲካ የመምጣት ውሳኔን ማሳለፍ ምን ያህል አስቸጋሪ ነበር ?
ሃብታሙ—ፖለቲካ እውቀት ብቻ ሳይሆን ስብዕናን ይፈልጋል፡፡ፖለቲካን ከሃይማኖት የሚለየው ምድራዊ መሆኑ ነው፡፡ሃይማኖት ለመንፈሳዊ በረከት የምትሰራበት ከሞት በኋላ ስላለ ህይወት በአብዛኛው የምትኖረው ነው፡፡ሃይማኖት የሚፈልገው ስብዕና ይህ ስብዕና ውሸትን መጠየፍ፣እውነትን መከተልና ለተበደለው መጮህን የሚይዝ ነው፡፡ፖለቲካውም ይህንን ይፈልጋል፡፡እርግጥ ነው ፖለቲካው ከስብዕና በተጨማሪ እውቀትን ይፈልጋል፡፡ነገር ግን ይህንን ክፍተት መሙላት ይቻላል፡፡በሃይማኖት ቤቶች ፖለቲካውን የአለማዊ ሰው መገለጫ በማድረግ የመመልከት አዝማሚያ አለ ይህ ግን መለወጥ መቻል አለበት፡፡ፈሪሃ እግዚአብሄር ያላቸው ሰዎች ወደ ፖለቲካው መምጣት እንደሚገባቸው አምናለሁ፡፡
ላይፍ — ወደ ማህበሩ ከመጣህና በአመራርነት ከተመረጥክ በኋላ ምን ተፈጠረ ?
ሃብታሙ — የአዲስ አበባ ፎረም ሲመሰረት የሄድኩት ከአንድ ጓደኞዬ ጋር ነበር፡፡አንድ የማላውቀው ሰው ስሜን ጠርቶ በአመራርነት እንድመረጥ ጠቆመኝ፡፡እኔ ግን ምንም ልምድ እንደሌለኝ በመግለጽ ጥቆማውን ለመቃውም ሞከርኩ፡፡መጀመሪያ የጠቆመኝን ሰው ከአመታት በኋላ አግኝቼው ካድሬዎች እኔን እንዲጠቁም ስላዘዙት እንደጠቆመኝ ነግሮኛል፡፡ጥቆማውን እንድቀበል በዚያ የነበሩ ሰዎች ግፊት ስላሳደሩብኝም ተመረጥኩ፡፡ከዚያም የማህበሩ የክፍለ ከተማው ምክትል ሰብሳቢ ሆኚ ተመረጥኩ ብዙም ሳይቆይ የአዲስ አበባ የፎረም ሰብሳቢ ተደረግኩ፡፡በመለጠቅም ዘጠኝ አደረጃጀቶች ማለትም የአዲስ አበባ ወጣት ፎረም፣የኢህአዴግ ሊግና ሌሎች ማህበራት የመሰረቱት ፌደሬሽን ፕሬዘዳንት ሆኜ ተመረጥኩ፡፡ከመንግስት በደረሰኝ ደብዳቤም የሕዝብ ግኑኝነት ሆኜ እንድሰራ ተደረግኩ፡፡ነገር ግን በዚህ መንገድ ከሁለት አመት በላይ መቀጠል አልቻልኩም፡፡
ላይፍ — ምንድን ነው በዚህ መንገድ እንዳትቀጥል ያደረገህ?
ሃብታሙ — ፌደሬሽኑም ሆነ የወጣቶች ፎረም ሲመሰረት ኢህአዴግ በነጻነታቸው ዙሪያ ምንም ጥያቄ አላነሳም፡፡ነገር ግን ቀስ በቀስ ማህበራቱን በካድሬ ትዕዛዝ ለመምራት መንቀሳቀስ ተጀመረ፡፡በዚህ ላይ ማህበራቱ መቶ በመቶ በጀታቸውን የሚያኙት በመንግሰት መሆኑም በነጻነታቸው ዙሪያ ጥያቄ ያስነሳል፡፡የሲቪክ ማህበራት በነጻነት እንዲንቀሳቀሱ የሚያደርጋቸው የህግ ድንጋጌ ቢኖርም መሬት ላይ ያለው እውነታ ግን ከዚህ ወጣ ያለ ነው፡፡እኔም ሆንኩ ሌሎች ወጣቶች አንዲህ መሆኑን በግልጽ ስንቃወም ቆይተናል፡፡በመጨረሻ ግን የነበረውን ነገር በውስጥ ትግል መለወጥ እንደማይቻል ስገነዘብ ለቅቄ ወጥቻለሁ፡፡
ላይፍ — በፎረምና በፌደሬሽኑ ውስጥ የነበረህን ከፍተኛ ሃላፊነት ከለቀቅክ በኋላ ባለ ራዕይ ወጣቶች ማህበርን መስርተሃል፡፡ማህበሩን ለመመስረት መነሻ የሆነ ምክንያት ምንድን ነው?
ሃብታሙ — አንድ ነገር ማስታወስ እፈልጋለሁ በሃላፊነት በነበርኩባቸው ወቅቶች ዘወትር ይነሱ የነበሩ ክርክሮች ‹‹አንተ ከኢህአዴግ ጋር እየሰራህ እንዴት ማህበራት ነጻ መሆን አለባቸው ትላለህ? ይህንን የምትለው በኢህአዴግ ስለማታምን ነው ይሉኝ ነበር፡፡ሃሳቤን ለማስለወጥም ብዙዎች ሽምግልና እስከመቀመጥ ደርሰው ነበር፡፡ባለ ራዕይ ማህበርን ለመመስረት ያበቃን በኢትዩጵያ ውስጥ ለማንም ወገንተኛ ያልሆነ ሲቪክ ማህበር መኖር አለበት የሚል አቋም ያለን ወጣቶች በተለያዩ አጋጣሚዎች መገናኘት በመቻላችን ነው፡፡
ላይፍ — ከገዢው ፓርቲ በመለየትና ታገኘው የነበረን ጥቅማ ጥቅም በመተው ‹‹በቃኝ ››የሚል ውሳኔን መሳለፍ ከባድ ምርጫ አልነበረም ?
ሃብታሙ — ኢህአዴግ ቤት እያለሁ ወፍራም ደሞዝ ነበረኝ ፣መኪና ተመድቦልኝ የተለያዩ አበሎች ይከፈሉኝ ነበር፡፡ስልጣን በራሱ የሚፈጥረው ወዳጅም አለ፡፡በሆድ ለሚያስብ ሰው እኔ ከነበርኩበት ሁኔታ መውጣት አስቸጋሪ ነው፡፡እኔ ግን ህሊናዬ ላልፈቀደው ነገር በሆዴ እየተደለልኩ መኖር የምችል ሰው ባለመሆኔ የምመራውን ህይወት በህሊና ለመለወጥ አልተቸገርኩም፡፡ በርካታ ዜጎች በችግር እየተቆራመዱ ለስደት ሲጋለጡ እያየሁ እኔን ተመችቶኛልና ስለ ሌላው ምንም አያገባኝም ለማለት አልደፈርኩም፡፡ኢህአዴግ ለተቃዋሚዎች ምን እንደሚያስብም አውቃለሁ ነገር ግን ያንን ኢህአዴግ ለተቃዋሚዎቹ ያዘጋጀውን ጽዋ መጠጣት ለእኔ ክብር እንደሆነ በማሰቤም በቃኝ ለማለት እንዳልቸገር አድርጎኛል፡፡
ላይፍ — ወደ ተቃዋሚው ጎራ ስትመጣ በዚያ ያሉ ሰዎች ከኢህአዴግ ጋር የነበረኝን ቆይታ ስለሚያውቁ ሊያምኑኝ አይችሉም የሚል ስጋት አላደረብህም ?
ሃብታሙ — በእርግጥ የአገራችን የፖለቲካ አስተሳሰብ የሚገኝበት ደረጃ በጣም ዝቅተኛ በመሆኑ ነገሮች አስቸጋሪ ይሆናሉ፡፡ከገዢው ፓርቲም ሆነ ከተቃዋሚነት ወደ ኢህአዴግነት ለሚሄዱ ሰዎች ሁኔታዎች ቀላል አይሆኑም፡፡በሁሉም ወገን በጥርጣሬ የመታየት ዕድል ሰፊ ነው፡፡በእኛ አገር የአንድ ፓርቲ አባል ከሆንክ እስከ ዕለተ ሞትህ የዛ ፓርቲ ወይም አስተሳሰብ አካል እንደሆንክ እንደምትቀጥል ይጠበቃል፡፡ለምሳሌ ኢህአዴግ ቤት ሃሳብ በመሸጥ መቀጠል አይቻልም፡፡በኢህአዴግ ውስጥ ኢህአዴግን በሃሳብ መታገል አይቻልም፡፡ፖለቲካውን የሚመራው በዕዝ ነው እንጂ በሃሳብ የበላይነት አይደለም፡፡በእንዲህ አይነት በዕዝ ሰንሰለት በሚመራ ድርጅት ውስጥ መቆየት ደግሞ የማይታሰብ በመሆኑ የተቃውሞውን ጎራ ለመቀላቀል አብቅቶኛል፡፡
ላይፍ — ኢህአዴግ ቤት በነበርክባቸው ወቅቶች ያፈራሃቸው ጓደኞች አሁን የቀድሞውን መስመር ስትቃወም ሲመለከቱ ምን ይሉሃል?
ሃብታሙ — እኔ ወደ ህዝብ የምሄደው እኔን ብቻ አድምጠኝ ለማለት አይደለም፡፡በግሌ በፊትም ይሁን በቀጣይ የሚኖሩኝ ወይም የነበሩኝ ጓደኞች አቋም እንዳለው ሰው እንዲያስቡኝ እፈልጋለሁ፡፡እስካሁንም ያለው ነገር ይህ ነው፡፡ኢህአዴግን የተውኩትና አንድነትን የተቀላቀልኩትም የአቋም ልዩነት ነው፡፡በአንድነት ውስጥ ዲሞክራሲያዊ ሃይሎችን በማግኘቴ ለውጥ እናመጣለን የሚል እምነት በመሰነቄ እየታገል እገኛለሁ፡፡
ላይፍ — ተቃዋሚዎችን በመቀላቀልህና ኢህአዴግን በመታገልህ የደረሰብህ ችግር የለም?
ሃብታሙ — እውነቱን ለመናገር ችግር የለም ማለት አይቻልም፡፡ችግር ብቻ ሳይሆን የተከተልኩት መስመር የህይወት መስዋዕትነትን ጭምር የሚጠይቅ መሆኑን አውቃለሁ፡፡ገዢው ፓርቲ የምበላውን አጥቼ እንድንበረከክ በመፈለግ ያሸነፍኳቸውን ጨረታዎች እንኳን እንዳላገኝና በዜግነቴ ሰርቼ እንዳልኖር እያደረገ ይገኛል፡፡ይህንን የሚያደርገው ግን ኢትዩጵያዊያንን ካለማወቅ በመሆኑ አልገረምም፡፡ኢትዩጵያዊ ክብሩን የሚጠብቅና ለፍርፋሬ ሲል ማተቡን የማይበጥስ ነው፡፡
ላይፍ — ወደ ፓርቲው ህዝባዊ ንቅናቄ እንምጣ ፣አንድነት እያደረገው የሚገኘው ሰላማዊ ሰልፍና ህዝባዊ ስብሰባ ሌላ ፓርቲ በቅርቡ ማድረጉን ተከትሎ በኩረጃ መልክ እየተደረገ የሚገኝ ነው ወይስ በጥናት ነው?
ሃብታሙ — ማንንም አልኮረጅንም ፣እያደረግነው የምንገኘው እንቅስቃሴ በስትራቴጂክ መጽሀፋችን ቀደም ብሎ የሰፈረ ነው፡፡ስለዚህ እየሰራን የምንገኘው በእቅዳችን መሰረት ነው፡፡ዞሮ ዞሮ ማንም አደረገው ማን የተደረገው ነገር የአገሪቱን ፖለቲካ አንድ እርምጃ ከገፋው ጥቅሙ የሁላችን በመሆኑ ጀማሪው እከሌ ነው አይደለም የሚለው ነገር አስጨናቂ አይሆንም፡፡አንድነት በዚህች አገር ለውጥ እንዲመጣ ያቅማቸውን ላበረከቱና እያበረከቱ ለሚገኙ ሁሉ እውቅና ይሰጣል፡፡በደፈናው ባለፉት አርባ አመታት ምንም አስተዋእጾ አልተበረከተም የሚል ድምዳሜ ላይ ፓርቲያችን አይደርስም፡፡እነ ፕሮፌሰር አስራትን ጨምሮ በዙ ሺህዎች ለዚህች አገር የህይወት መስዋዕትነትን ከፍለዋል፡፡ለዚህ እውቅና መቸር ይገባናል፡፡እውንት ለመናገር ሰላማዊ ሰልፍ በማድረግ የህዝብን አይን የገፈፉት በታዲዩስ ታንቱ የሚመራው የአገር ወዳድ ኢትዩጵያዊያን ማህበር ነው፡፡ለግራዚያኒ ሃውልት እንዲቆምለት መወሰኑን በመቃወም ሰልፍ እንዲጠራ ያነሳሱት እን ታዲዩስ ናቸው፡፡ለዚህ ተገቢውን አክብሮት ሊቸራቸው የሚገባ ቢሆንም ሌሎች መድረኩን በመቆጣጠር የማይገባቸውን ውዳሴ ለመሸመት ተንቀሳቅሰውበታል፡፡በሃይል በተቀለበሰው ሰላማዊ ሰልፍ ከአርባ በላይ አባላቶቹ የታሰሩበት ባለ ራዕይ ማህበርም ከሰላማዊ ሰልፉ አዘጋጆች አንዱ ነበር፡፡
ላይፍ — መስከረም አምስት አንድነት በአዲስ አበባ ለማድረግ ያቀደውን ሰልፍ የአንድ ፓርቲ ሊቀመንበር‹‹አንድነት ይህንን ሰልፍ የጠራው እነ አንዷለም የታሰሩበትን ቀን ለማክበር ነው፣እኛ ግን ሰልፍ የምንወጣው እነ አንዷለም እንዲፈቱ ነው ››ብለዋል፡፡እስኪ የሰልፉን አላማ ንገረኝ?
ሃብታሙ — (ረዥም ሳቅ)ፖለቲካ እንግዲህ እንደተርጓሚው ነው፡፡ይህ አስተሳሰብ ተገቢ ባይሆንም አስተሳሰቡ ግን የመደመጥ ዕድል ማግኘት እንደሚገባው ይሰማኛል፡፡ግለሰቡ እንዲህ የሚያስቡ ከሆነ ማድረግ የሚጠበቅብን አስተሳሰባቸውን እንዲያሳድጉ መርዳት ነው፡፡ለኢትዩጵያ ፖለቲካ የሚጠቅም አስተሳሰብ ባለመሆኑም የራስን ገጽታ ለመገንባት የሌሎችን መልክ ማቆሸሽ ቅንነት የጎደለው ድርጊት ነው፡፡በግሌ ይህንን የተናገሩት አቶይልቃል አንድ ሰልፍ በመጥራት ስማቸው በየቦታው መነሳት በመጀመሩ ስካር ውስጥ የገቡ ይመስለኛል፡፡ኢትዩጵያ ውስጥ ፓርቲ አለ ብዬ አላምንም ማለትና በመድረክና በአንድነት ውስጥ ለጊዜው ተፈጠረ የተባለውን ልዮነት በማራገብ እየተባሉ ነው ማለት እንዴት አይነት ፖለቲካ እንደሆነ አይገባኝም፡፡እዚህ አገር ፓርቲ የለም ብሎ የሚያምን ፓርቲ በምን ስሌት ከሰላሳ ሶስት ፓርቲዎች ጋር በትብብር ለመስራት መፈራረሙ አስገራሚ ነው፡፡የሉም ካሉ እንዴት አብረው ሊሰሩ ፈረሙ፡፡ኢህአዴግም እኮ የሚለው ይህንኑ ነው አኔ ከሌለው ይህች አገር ትጠፋለች የሚለው ፓርቲዎች አሉ በማለት ስለማያምን ነው፡፡ይህንን ጥያቄ ስላነሳህው ልመልሰው እንጂ ዝሆን የሚያባርር ለወፍ ድንጋይ አይወረውርም፡፡እኛን እንቅልፍ የሚነሳን የአገራችን ጉዳይ ነው፡፡እንዴት ይህንን አምባገነን ስርዓት እንለውጣለን የሚለው ያስጨንቀናል እንጂ የቃላት እሰጥ ገባ ውስጥ በመግባት ጊዜ ማባከን አንፈልግም፡፡የኢትዮጵያ ህዝብ ግን ፍርዱን እንደሚሰጥ በግሌ አምናለሁ፡፡
ላይፍ –ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ በቅርቡ አንዳንድ የፖለቲካ ድርጅቶች በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ በመግባት ርካሽ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት እየተሯሯጡ ነው፡፡እነዚህ የፖለቲካ ሃይሎች ከዚህ ድርጊታቸው ካልተቆጠቡ እርምጃ እንወስዳለን በማለት ዝተዋል፡፡ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስም ባይጠሩም ይህ ማስጠንቀቂያ በዋናነት አንድነትን የሚመለከት አይመስልህም?
ሃብታሙ –ኢህአዴግ ሲጨነቅ የሚናገራቸው ነገሮች ፍጹም የማይገናኙ ናቸው፡፡አቶ ሃይለማርያም በምንና እንዴት መታገል እንደሚገባን ሊያዙን ወይም የምንታገልባቸውን ነገሮች እየቆነጠሩ ሊሰጡን አይችሉም፡፡እኛንና እሳቸውን የሚዳኘን የአገሪቱ ህግ ነው፡፡ስልጣን ስለያዙ ለህገ መንግስቱ ቅርብ ናቸው አያስብልም፡፡እኛም የህገ መንግስት ጥሰት እየተፈጸመ ነው በማለት እየከሰስን ነው፡፡ነጻ የፍትህ ስርዓት ቢኖር ማን ህጉን እንደጣሰም በግልጽ ይታይ ነበር፡፡ለማንኛውም ግን ሙስሊም ወገኖቻችን ያነሱት ጥያቄ የሃይል ሳይሆን ስልጡን ምላሽ እንዲሰጠው ከመጠየቅ ወደ ኋላ አንልም፡፡በማስፈራሪያው በመሸማቀቅ ለወገኖቻችን አጋርነታችንን ከማሳየት እንደማንቦዝንም መታወቅ አለበት፡፡


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>